ንጉሥ አርማሕ (ነጃሺ) ሰልሟልን..? የአርኬኦሎጂ ጥናት ምን ይላል..?


ሙስሊሞች እንደ አንድ ታሪካዊ ሐቅና የአስተምሕሮቱ አካል አድርገው የሚቆጥሩትን ይህን አጀንዳ አስመልክቶ በክርስቲያኖች ዘንድ በበቂ መጠን አልተባለም፡፡ ይህም ዝምታ ለረዥም ዘመን የቀጠለ ነበረ፡፡ ይህ ዝምታ ግን መነሻው በሌለ ነገርና ባልተፈፀመ ታሪክ ላይ አንዳች ማለት ስለማይገባ እንደሆነ በቀላሉ መረዳት አያዳግትም፡፡ ሆኖም “በአክሱም ነገሥታት መካከል ከክርስትና ወደ እስልምና የተቀየረ ንጉሥ አለ” የሚለው ጩኸት እየተደጋገመ ሲመጣ  የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መንበረ ፓትርያክ ጠቅላይ ጽ/ቤት በ2000 እና በ2001 ዓ.ም ምላሽ ሰጥቷል፡፡ 

ጽ/ቤቱ በተከታታይ ባወጣቸው ሁለት መጽሔቶች “አሕመድ አል-ነጋሺ የሚባል ንጉሥ በኢትዮጵያ አልነበረም” በሚል ርዕስ መረጃዎችን  በማጣቀስ የሰለመ ክርስቲያናዊ ንጉሥ በአክሱም ነገሥታት ውስጥ  እንዳልነበረ አመልክቷል፡፡ ይህ መልስ የቤተክርስቲያኒቱን የተገለጠ  አቋም የሚያንፀባርቅ ከመሆኑም በላይ ታሪካዊ ሐቆችም የተዳሰሱበት ነበረ፡፡ ከዚያም በኋላ ከሌሎች ርዕሶች ጋር ተቀናጅቶ በዚህ ጉዳይ  የተፃፉ ጥቂት ጽሑፎች አሉ፡፡ ቢሆንም ይኸው ርዕስ በሙስሊሞቹ ወገን ተደጋግሞ መነሳቱ በመቀጠሉ ታሪካዊ እውነቶችን በመዳሰስና  ተጨማሪ የሙግት ሥልቶችን በመጠቀም የሰለመ ክርስቲያናዊ ንጉሥ እንዳልነበረ ማመልከት አስፈልጓል፡፡ ይህንንም ከኢትዮጵያ የታሪክ ምንጮች፣ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር ዘመናዊ የታሪክ ምሑራን ከተዘጋጁ የታሪክ መጻሕፍት፣ በተመራማሪዎች ከቀረቡ የአርኪኦሎጂ ውጤቶችና ከራሳቸው ከሙስሊሞች መጻሕፍት በተገኙ መረጃዎች  መከራከሪያችንን እናቀርባለን፡፡ 

1) የአርኬኦሎጂ የምርምር ውጤቶች

በታሪክ ጥናት ውስጥ ለመረጃ ምንጮች የደረጃ ምደባ መስጠት የተለመደ አካሄድ ነው፡፡ በዚህም ምደባ ለእውነተኝነት ይበልጥ  የቀረቡት ቀዳማይ የመረጃ ምንጮች (Primary Sources) ሲባሉ  ከእነዚህ አንጻር በተአማኒነትም ሆነ በእውነተኝነት (authentic) በቀጣይነት የሚመደቡት ካልአይ የመረጃ ምንጮች (Secondary Sources) ይሰኛሉ፡፡ የታሪክ ምሑሩ ፕሮፌሰር ሥርግው ሀብለ ሥላሴ ይህን አስመልክቶ የሚከተለውን ብለዋል በዚህም መደብ በኢትየጵያ ታሪክ ውስጥ በመጀመሪያ ምንጭነት የሚያገለግሉት፦

🔹የተቀረፁ ጽሑፎች (Inscription) 
🔹የገንዘብ ሳንቲሞች (Coins)
🔹ደብዳቤዎችና አዋጆች (Letters and Decrees)
🔹ሐውልቶች (Monuments) 

ሲሆኑ.. እንደ ሁለተኛ ምንጭነት የሚቆጠሩት ደግሞ፦

🔹የግሪክ ጸሐፊያን (Greek Writers)
🔹የላቲን ጸሐፊያን (Latin Writers)
🔹የአረብ ጸሐፊያን (Arab Writers)
🔹የኢትዮጵያ የእጅ ጽሑፎች (Ethiopian Manuscripts) ናቸው፡፡ ¹

በጥንታዊነትና በተቀባይነት ቀዳሚ የተባሉ የመረጃ ምንጮች ካሉ እነርሱን አስቀድሞ መመልከቱ ተገቢ ነው፡፡ በጥንታዊት ኢትዮጵያ የነበሩ ሐገራዊ ጸሐፍት አቻዎቻቸው እንደነበሩት የግብፅ፣ የሮማ፣ የቁስጥንጥንያና የግሪክ ታሪክ ጸሐፊዎች በዘመናቸው የነበረውን ታሪክ ሁሉ ፅፎ ማስቀመጡን ልብ ያላሉት ነገር እንደሆነ የታሪክ ተማራማሪዎች ሁሉ በቁጭት የሚያነሱት ጉዳይ ነው፡፡ አብዛኛው ጥንታዊ ጽሑፍ መንፈሳዊ ብቻ በመሆኑ የተሟላ ሀገራዊ ታሪክ የሚያስተላልፍ አይደለም ብለው ቅር የሚሰኙም አሉ፡፡ ይሁን እንጂ በኋላ ዘመን የተነሱ አውሮፓውያን የታሪክ ተመራማሪዎች ከእነዚሁ የቅዱሳን ገድላትና መንፈሳዊ ድርሳናት፣ ቆሞ ከሚገኘውና ፈርሶ ከወደቀው ሐውልት፣ በቁፋሮና በየቤተመዝገቡ ከሚገኙ ቁሶችና 
መገበያያ ገንዘቦች በመቅዳትና በመመርመር የታሪክ መጻሕፍትን እያዘጋጁ በተለያዩ ቅጾች አሳትመዋል፡፡ 

በዚህም መሠረት የተለያዩ ታሪካዊ እውነታዎች አሁን ላለው ትውልድ ግልፅ ለመሆን ችሏል፡፡ ለምሳሌ በአራተኛው ክፍለ ዘመን ያለውና ከዚያም ቀድሞ የነበሩት የአክሱም ነገሥታት የግዛት ወሰናቸው ቀይ ባሕርን ተሻግሮ የደቡብ አረብ ምድርን ሁሉ ያጠቃልል እንደነበር የታወቀው ንጉሥ ኢዛና ባስቀረፀው የሐውልት ላይ ጽሑፍ ነው። ከዚያም ቀጥሎ በ6ኛው ክፍለዘመን በደቡብ አረብ የነገሰው አይሁዳዊው (ዙ ነዋስ ወይም ፊንሐስ) በናግራን በሚኖሩ ክርስቲያኖች ላይ በፈፀመው መጠኑና ጭካኔው የበዛ ጭፍጨፋ ምክንያት አፄ ካሌብ ባሕር ተሻግሮ እንደደመሰሰው የታወቀው በተመሳሳይ መንገድ ነው፡፡ 

የአክሱም ነገሥታት እንደ ግሪክና ቁስጥንጥንያ ነገሥታት ምስላቸውን፣ አንዳንድ መግለጫና መጠነኛ ጽሑፍ የያዙ መገበያያ ሳንቲሞች ያዘጋጁ ነበር፡፡ በሥፍራው በተደረገ ቁፋሮና ምርመራ በተለያየ ዘመን የነገሱ የልዩ ልዩ ነገሥታት መገበያያ ሣንቲሞች ተገኝተዋል፡፡ ሣንቲሞቹ ላይ ያሉት መግለጫዎች የየዘመኑን ዕውቀት የሚገልጡ ልዩ ልዩ ናቸው፡፡ 

ሙስሊም ጸሐፊዎች “ሰልሟል” በማለት “ነጃሺ” እያሉ የሚጠሩት ንጉሥ ሀገራዊ ስሙ አርማሕ እንደሆነ የተለያዩ ጽሑፎቻቸው ይናገራሉ፡፡ ለምሳሌ “ኢትዮጵያና ኢስላም” የሚባለው የሙሐመድ ጦይብ መጽሐፍ የንጉሥ አርማሕን አነጋገስ በተመለከተ ተረት መሳይ ነገር ከተረከ በኋላ ‘አር-ረውዶል ኡንፍ’ የተሰኘ መጽሐፍ በመጥቀስ ስለ ንጉሥ አርማሕ የሚከተለውን ይላል 

“ ‘አር-ረውዶል ኡንፍ’ በተሰኘ መጽሐፍ (ጥራዝ 2 ገጽ 249) የታሪክ ሊቃውንት በነቢዩ ዘመን የነበረው የኢትዮጵያ ንጉሥ አርማሐ (ዳግማዊ አርመሐ) በመባል እንደሚታወቅና በስሙም ቅንስናሽ ሳንቲም እንደታተመ አመልክተዋል። ሳንቲሞቹ ላይ ‘ንጉሥ አርማሐ አዛኙና ሰላማዊው’ የሚል ጽሑፍ ተከትቧል፡፡ ንጉሡ ፍትሐዊና ሰላማዊ ነበር” ²

ምንም እንኳ ሌሎች እስላማዊ ጽሑፎች የንጉሡን ስም በተለያየ አጠራር “አስሐማ፣ እለ ጸሐም፣ አጽሐማ፣ ጸሐማ...” እንደሆነ ቢጠቅሱም አርማሕ የሚለው ስያሜ ይበልጥ ገላጭ ይመስላል። ወይም አስሐማና እለ ጸሐም ተብሎ የተጠቀሰው ራሱ አርማሕ ነው። በዘመናዊ የመፈለጊያ ድሮችም “ነጃሺ” ተብሎ ቢፈለግ በቅድሚያ የሚያወጣው ይህንን አርማሕ የሚል ስም ነው፡፡ 

ይህ አርማሕ የተሰኘ ንጉሥ እንደተጠቀሰው በስማቸው የተሠሩ መገበያያ ገንዘቦች ካዘጋጁት ነገሥታት የሚቆጠር ነው፡፡ ሆኖም ከላይ ያለውን መጽሐፍ የጠቀሰው መጽሐፍ ሳይገልፀው ያለፈው መሠረታዊ ነገር አለ፡፡ እርሱም በሣንቲሙ ላይ በግልፅ የሚታይ መስቀል መኖሩን ነው። የአክሱም ነገሥታት በአራተኛው ክፍለ ዘመን ኢዛና (አብርሃ ወ አጽብሐ) የክርስትና ሃይማኖትን በአዋጅ የመንግሥት ሃይማኖት ካደረጉት በኋላ መገበያያ ገንዘባቸው ላይ መስቀል ማስቀረፃቸው የተለመደ ባሕል እንዳደረጉት ማየት ይቻላል፡፡ 

ንጉሥ አርማሕም ይህንኑ ባሕል በማስቀጠል በስሙ በታተመ መገበያያ ገንዘብ ላይ መስቀል አድርጓል፡፡ ይህም ጽኑ ክርስቲያንነቱን የሚያሳይ በመሆኑ “ሰልሟል” የሚለውን ንግግር ተረት ያደርገዋል፡፡ በዘመኑ የነበሩ የነገሥታት ሣንቲሞች በታሪካዊ የመረጃ ምንጭነት አንደኛ ደረጃ የሚሰጣቸው መሆኑን የታሪክ ምሑሩን ፕሮፌሰር ሥርግው ሀብለ ሥላሴን እማኝ አድርገን ጠቅሰናል፡፡ ይህን የሚታይና የሚጨበጥ ታሪካዊ ሐቅ ይዘን ስናበቃ በምን መንገድ ክርስቲያናዊውን ንጉሥ ሰልሟል እንበለው..? 

ብዙዎቹ እስላማዊ ጽሑፎች የዚህን ንጉሥ የንግሥና ዘመን ከ615 - 630 ነው የሚያደርጉት፡፡ ይህ ማለት ንጉሡ ሙሉውን የንግሥና ዘመኑን ከስደተኞቹ ሙስሊሞች ጋር አሳልፏል እንደማለት ነው፡፡ ምክንያቱም ብዙዎቹ ስደተኞች ለ16 ዓመታት በሀገራችን መቆየታቸው ተገልጿልና፡፡ በሌላ አነጋገር ስደተኞቹ ወደ እክሱም ሲመጡ ያገኙት ንጉሥ ገና መንበረ ሥልጣኑን የተረከበ አዲስ ንጉሥ ነበር ማለት ነው፡፡ ይህ ንጉሥ የሙስሊሞቹን ቃል ሰምቶ ከሰለመ እንዴት መገበያያ ገንዘቡ ላይ ክርስቲያንነቱን የሚገልፅ መስቀል ያስቀርፃል የሚል ጥያቄ ያስነሳል፡፡ ይህን ያደረገው ገና እንደነገሰ ነው ቢባል እንኳ በቀሪው ረዥም የሥልጣን ዘመኑ ይህንን ድርጊቱን የሚያርምና መስለሙን የሚያስረዳ ምልክት ያለበት መገበያያ ገንዘብ ያስቀርፅ ነበር፡፡ ይህ ለመሆኑ ግን አንዳችም የአርኬኦሎጂ መረጃ የለም፡፡ 

በአርኬኦሎጂ የምርምር ውጤቶች የንጉሥ አርማሕ መገበያያ ሣንቲም ክርስትናውን መመስከሩ ብቻ አይደለም፡፡ በተቃራኒው ማዕዘን ስናየው ደግሞ የሰለመ አክሱማዊ ንጉሥ ለመኖሩ አንድም የሐውልት ላይ ጽሑፍ ወይም የመገበያያ ገንዘብ መግለጫ አልተገኘም፡፡ የዚህ ነገር ምክንያቱ ምንድነው ቢሉ መልሱ “ቀድሞውኑ ያልሆነ ነገር ሊፃፍ፣ ያልነበረም ነገር ሊገኝ አይችልምና” የሚል ነው፡፡ ከንጉሥ አርማህ ዘመነ ንግሥና ወደ ኋላ ባለው ዘመን የነገሱ ነገሥታትም መገበያያ ገንዘባቸው ላይ የመስቀል ምሥል ያደርጉ እንደነበር ተረጋግጧል፡፡ ከእነዚህም ነገሥታት ንጉሥ ሐታዝ እና ንጉሥ ኢዩኤልን በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል፡፡³ ይሄ ሁሉ ነገር በኢትዮጵያ ረዥም ዘመን የሀገረ መንግሥት ታሪክ የክርስቲያኖች ንጉሥነት ሳይቆራረጥ ለመቀጠሉ ማሳያ ይሆናል።

ማጣቀሻዎች 

¹ Sergew Hable Sellassie, Ancient and Medieval Ethiopian History to 1270 pp 11

² ኢትዮጵያና ኢስላም ገጽ 8

³ ተክለ ጻድቅ መኩሪያ፡ የኢትዮጵያ ታሪክ - ኑብያ፣ አክሱም፣ ዛጉዬ 1951 ዓ.ም ገጽ 217-218

(የሳንኮፋ ሰንኮፍ እና ሌሎች ከገጽ 66-72)
Share on Google Plus

ስለ የተለጠፈበት ቀን

    Blogger Comment
    Facebook Comment