ድቀተ ካህናት (የካህናት ውድቀት)

መ/ር ዘመድኩን በቀለ

"…እንበለ ደዌ ወሕማም፤ እንበለ ፃማ ወድካም፤ ዓመ ከመ ዮም፤ ያብጽሐነ ያብጽሕክሙ ለብርሃነ ትንሣኤሁ እግዚአብሔር በፍሥሐ ወበሰላም። ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በሰሙነ ሕማማት ሳምንት ውስጥ በዛሬው ዕለት በዕለተ ረቡዕ ተፈጸሙ ከምትላቸው ሦስት ዐበይት ሁነቶች መካከል "ምክረ አይሁድ" እንደሆነ ታስተምራለች። "…በዚያን ጊዜ የካህናት አለቆች የሕዝብም ሽማግሎች ቀያፋ በሚባለው በሊቀ ካህናቱ ግቢ ተሰበሰቡ፥ ኢየሱስንም በተንኰል ሊያስይዙት ሊገድሉትም ተማከሩ፤ ማቴ 26፥ 3-4… እናም ይህን የምከረ አይሁድን ዕለት በዚህ መልኩ እያሰብን በሀዲስ ኪዳን በተለይም በዛሬይቱ ኢትዮጵያችን የሚገኙትን የሀዲስ ኪዳን ካህናት የሚሞገቱበትን ባለፈው ሳምንት በነበረ የሊቃውንተ ኢትዮጵያ የውይይት ጉባኤ ላይ "ድቀተ ካህናት (የካህናት ውድቀት) በሚል ርእስ በዕለቱ ተረኛ አቅራቢ የቀረበን ዲስኩር እኔ ዘመዳችሁ በሚከተለው መልኩ በርእሰ አንቀጽ መልኩ አዘጋጅቼ አቅርቤላችኋለሁ። አንብቡት። 

"…ሀገራችን ኢትዮጵያ አሁን ላለችበት ውድቀት ዋና ተጠያቂ ይላል ዕለቱ አቅራቢ ሀገራችን ኢትዮጵያ አሁን ላለችበት ውድቀት ዋና ተጠያቂ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክህነት ነው በማለት ነው ንግግሩን የጀመረው። ይቀጥልናም ወደ ዝርዝር ጉዳዩ እንዲህ እያለ ይቀጥላል። ቤተ ክህነቱ የሀገሪቱ ዋና የጀርባ አጥንት፣ ኢትዮጵያን ጠፍጥፎ የሠራ፣ ኢትዮጵያ በሥልጣኔ፥ በኢኮኖሚ፥ በባህል፥ በሥርዓት፥ በሥነ ጽሑፍ በልጽጋ የዓለም ብርሃን እንድትሆን ያደረገ ነበር። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክህነት ሥራው ከሌሎች የክህነት ሥራዎች ይለያል። እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የክህነት አካካን ሦስት ደረጃን አልፎ የመጨረሻው ሦስቱን በአንድ አጣምሮ የያዘ ነው። ልዩ የክህነት ቅብብሎሽን ያስቀጠለ፣ ከዓለም የተለየ ድንቅ ምስጢርን የያዘ ነው። የመጀመሪያው የክህነት ሥልጣን ከአዳም ከአባታችን የተገኘ ነው። 

"…አባታችን አዳም ክህነትን፣ ንግሥናንና ነቢይነትን ከፈጣሪው የተሾመ ካህን፣ ንጉሥና ነቢይ ነው። ይህ ሲወርድ ሲዋረድ ከአዳም ወደ ሴት፣ ከሴት ወደ ኖህ፣ ከኖህ ወደ ካም፣ ከካም ወደ ከነአን፣ ከከነአን ወደ ዮቶር፣ ከዮቶር ወደ ዘመነ ኦሪት የተሸጋገረ ነው። አባታችን አዳም የሕገ ልቡና ካህን ተብሎ ይጠራል። በዚህ ክህነት አበው ሕዝባቸውን ባርከውበታል፤ መሥዋዕት አሳርገውበታል፤ አዳም ለኃጢአቱ፣ አቤል ለሚስቱ፣ ኖህ የሰብአ ትካትን ርኩሰት ለማስወገድ፣ ምድሪቱን ለማንጻትና ቃልኪዳን ከፈጣሪው ለመቀበል መሥዋዕት አቅርበውበታል። ይህንን ክህነት የእኛ ኢትዮጵያውያን ካህናት ከአዳም እስከ ቀዳማዊ ምኒልክ ድረስ ጠብቀው አስቀምጠውታል። አባታችን አዳም እግዚአብሔር በደሉን ይቅር እንዲለው፣ ወደ ገነት እንዲመልሰው፣ በደብር ቅዱስ መሥዋዕት አቅርቦ ፈጣሪውን በጸሎት ሲጠይቅ ፈጣሪው "በሥጋህ ጥረህ ግረህ ብላ፤ በነፍስህ ከሰማየ ሰማያት ወርጄ ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ" አለው። ይህን አስመልክቶ ኢትዮጵያዊው ቄርሎስ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ እንዲህ ይላል: "አመ ይወጽእ አዳም እምሀገረ ጽጌ ገነት ዘአዕረገ ብኪ ዕጣነ ጸሎተ ማርያም ስኂነ ሰንበልት።" ይላል። አባታችን አዳም ለልጆቹ እንደሚወርድ እንደሚወለድ በተስፋ ሲነግራቸው እኩሌቶቹ በፀሐይ እኩሌቶቹ በከዋክብት እኩሌቶቹ በጨረቃ ሲቆጥሩ ኖሩ። 

"…የኢትዮጵያ ካህናተ አበው በሦስቱም በፀሐይም በጨረቃም በከዋክብትም ሳያዛቡ በመቁጠር ፀሐይን ከዋክብትንና ጨረቃን ለዘመን መቁጠሪያ ለምልክትና ለመገለጫ ተጠቅመው እንደ ሌሎቹ ሳያመልኩ እስከ ዘመነ ኦሪት አደረሱ። አራቱ እንስሳዎች የሚፈራረቁበትን ዘመን እየቀመሩ እንደ ግብጽ፣ እንደ ፋርስ፣ እንደ ሮም፣ እንደ ግሪክ ሳያመልኳቸው ክብራቸውን ዝቅ ሳያደርጉ ጠብቀዋል። 

"…የጣዖት አምልኮ የተጀመረው እግዚአብሔር ለአዳም የሰጠው ተስፋ የሚፈጸምበትን ዘመን ለማወቅ በፀሐይ፣ በጨረቃና በከዋክብት ሲቆጥሩ በዘመነ ገጸ ሰብእ እንደሚወለድ አዳም ስላስረዳቸው የእሱ ልጆች ከጊዜ በኋላ ፀሐይን፣ ጨረቃን ከዋክብትን ወደ አምላክነት ቀይረው እነሱን ማምለክ ጀመሩ። ግብጽ የፀሐይ ከተማ መሥርታ ከአርባዕቱ እንስሳ አንዱን ገጸ ላሕም አምላክ አድርጋ ቀርጻ፣ ፀሐይን አምላክ ገጸ ላሕምን ጣዖት አድርጋ፣ የራሷን አምላክ ፈጥራ ለእጇ ሥራ ስትሰግድ፣ ቶትን ከፀሐይ የወረደ የፀሐይ ልጅ ብላ ስትቀበልና ለቶት ማደሪያ የጸሐይ ከተማ ገንብታ ስትስት ነበር። ግሪክ ጨረቃን አምላክ አድርጋ፣ ከአርባዕቱ እንስሳ ገጸ ንስርን ጣዖት አድርጋ አርጤምስንና ዜውስን የጨረቃ ልጆች ከጨረቃ የወረዱ ውሉደ አማልክት ብላ ስታመልክ ነበር። ፋርስ ከዋክብትን አምላክ ብላ ከከዋክብት የሚበልጠውን በእኛ ናርኤል በእነሱ ሬፋን የሚባለውን ታላቁን ኮከብ አምላክ አድርጋ ከገጸ ሰብእ ገጸ አንበሳን አሽራ ብላ ጣዖት አድርጋ የሰው መስዋዕት ለአሽራ እየሰዋች የወንዶችን ዘር በግብረ ሰዶም ከጣዖቱ መድረክ እያፈሰሰች ስትሰዋ ነበር። ሌሎች ህንድ፣ አረብ፣ ሮማና የመሳሰሉት ደግሞ ምድራዊ  አምላክ መሎክን፣ አድራማሌክንና የመሳሰሉትን እየፈጠሩ ሲያመልኩ ከአርባዕቱ እንስሳ በገጸ ሰብእ የሰው ጣዖት ሲያበጁ ሲሰግዱ ሲስቱ ኖረዋል። ኢትዮጵያ ግን ከዋክብትን የአዝማናት መቀመሪያ፣ ፀሐይን የቀን፣ ጨረቃን የሌሊት መቁጠሪያና መለኪያ አድርጋ ፈጣሪዋን ሳትዘነጋ ለጣዖት ሳትንበረከክ እስከ ዘመነ ኦሪት የደረሰችው በካህናቶቿ ጥንቃቄ ነው። ለዚህ ነው ኢትዮጵያ የተለየች ነች የምንለው። የጣዖት የአምልኮ ባዕድ ጥንተ አመጣጡ ፈጣሪን በመፈለግ ሂደት የመጣ ውድቀት ነው። "ፈጣሪ ይወልዳል ይወለዳል" የሚለውን አስተምህሮ ሰይጣን ተጠቅሞ "ከፀሐይ የወረዱ፣ ከጨረቃ የወረዱ፣ ከከዋክብት የመጡ" እያለ በሰው ልቡና እያደረ እንዲመለኩ አደረገ። እውነተኛው አምላክ የሰጠውን ተስፋ አጣሞ ለራሱ ተጠቀመበት። "በአንድ አምላክ የምናምን ነን" ብለው የሚኩራሩት እስራኤላውያን እንኳ በዚህ ተፈትነው ወድቀዋል። አባታችን አብርሃም ከአሽራ የአምልኮ ጣኦት አምልጦ ከጣዖተ ካህናት ሸሽቶ ተመራምሮ ነው አምላኩን ያገኘው። 

"…እኛ ኢትዮጵያውያን ከአባታችን አዳም በቅብብሎሽ ሳናዛባ ወደ ግራ ወደ ቀኝ ሳንል የሰማያትን ጌታ ከማምለክ አልቦዘንም። ይህ የካህናቶቻችን ብርታት ዕውቀት ነው። ለምሳሌ ያህል ሙሴ "በቀዳሚ ገብረ እግዚአብሔር ሰማየ ወምድረ" የሚለውን የኦሪት ዘልደት አስተምህሮ ያገኘው ከአባታችን ከኢትዮጵያዊው ካህን ከዮቶር ነው። ፀሐይ ጨረቃ ከዋክብት፣ ሰማይና ምድር፣ መላእክትና ሰው፣ እንስሳትና አራዊት፣ አዝርዕትና አትክልት የተፈጠሩ ግዑዛን ፋጥረታት እንጂ ፈጣሪ እንዳልሆኑ፣ የተንሰራፋውን የባዕድ አምልኮ አስተሳሰብ የሚንድ የኦሪት ዘልደት አስተምህሮን፣ የጠልሰም ምልክትን፣ ባሕር መክፈልን፣ መና ማውረድንና ጠላት በተአምራት መቅሠፍት መቅበርን ሙሴ የተማረውና በደንብ የጠነቀቀው ከኢትዮጵያዊው ካህን ከዮቶር ነው። ሙሴ ከዮቶር ጋር ከመገናኘቱ በፊት ማን ነበር? ፋል የሚባለውን የግብጽ የቶትን አስማት የተማረ፣ ፈሪ፣ ድንጉጥ፣ ሞትን ፈርቶ ከፈርዖን የሸሸ ተራ ሰው ነበር። ከዮቶር ከተገናኘ በኋላ የሙሴ ማንነት እንዴት እንደተቀየረ የሚታወቅ ነው። ለዝርዝሩ ሕይወተ ሙሴ ወይም ተአምረ ሙሴ የሚለውን የሙሴን ታሪክ ኢትዮጵያውያን አበው ከትበው በብራና ያስቀመጡትን ማንበብ ይበጃል። በአጭሩ የኢትዮጵያውያን ካህናት ጥንካሬና ዕውቀት ከሌላው ዓለም ካህናት ይለያል።…👇①✍✍✍
👆②✍✍✍ "…በዚህ መልክ እስከ ንግሥተ ሳባ ድረስ ቀጥሎ ቀዳማዊ ምኒልክ ሕገ ኦሪትን ወደ ኢትዮጵያ ይዞ ሲመጣ በሙሴ ሕግ መሠረት ከዘመነ አበው አሿሿም ወደ ሌዋውያን አሿሿም ተሸጋገረ። ከሌዋውያን አሿሿም የሌዋውያንን አምሳል መርገፍ አድርገው ወደሚጠብቁት እውነተኛው ክህነት ወደ ሐዲሱ የክህነት አሿሿም ተሸጋገረ። ሦስትነትን በአንድ ያዋሐደ የክህነት ሥርዓት ያሰኘው ይህ ነው። ማለትም ክህነተ አዳም፣ ክህነተ አሮን፣ ክህነተ ሐዋርያት ሦስቱንም በአንድ አጣምሮ የያዘ ከኢትዮጵያ ውጭ ሌላ ዓለም አናገኝም። በዚህ ሥርዓት የመጡት ካህናት ሰማያዊ ፊደል ቀርጸው፣ ሰማያዊ ዜማ አውርደው፣ በምስጢር ተራቀው ኢትዮጵያን ከነሙሉ ክብሯ አቆይተውልናል። ኢትዮጵያን ኢትዮጵያ እንድትሆን ያደረጋት የኢትዮጵያውያን ካህናት ሚና ነው። 

"…የኢትዮጵያ ካህናት ሰማያዊ ኪሩብ ምድራዊ አዳም ሆነው ሀገራቸውን፣ ሕዝባቸውንና ፈጣሪያቸውን አገልግለዋል። ኢትዮጵያን ምድራዊ ገነት አድርገው ተክለዋታል። ነገሥታቱን አብርሃ ወአጽብሃን፣ ዓፄ ካሌብን፣ ዓፄ ገብረ መስቀልን፣ ቅዱስ ላሊበላን፣ ዓፄ ፋሲልን፣ ዓፄ ቴዎድሮስን፣ ዓፄ ምኒልክን አስተምረው ለንግሥና አብቅተው ለኢትዮጵያ አበርክተዋል። ቀብተው ካነገሧቸውና አስተምረው ካበቋቸው ነገሥታት ጋር አብረው ዘምተው፣ አብረው ተዋግተውና አብረው ደምተው የሀገር ድንበር አስከብረዋል። ትውልድ እንዳይደነቁር ይልቁንም በትምህርት እንዲራቀቅ የትምህርት ፖሊሲ ቀርጸው አስተምረዋል። ዜማን በዜማ ልክ ሚዛን መዝነው፣ በዜማ ላዳን ሰፍረው፣ የድጓ የአቋቋም የዜማ የቅኔ የመሳሰሉትን ለነፍስም ለሥጋም ለሀገርም ለፈጣሪም የሚሆን ሥርዓተ ትምህርት የቀረጹት፣ ከዓለም ብቸኛዎቹን ካህናት እነ ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖትን፣ እነ ቅዱስ ያሬድን፣ እነ አቡነ ኢየሱስ ሞዐን፣ እነ አባ ጊዮርጊስን የወለዱ ወላዴ አዕላፍ ናቸው። ኢትዮጵያውያን ካህናት የዓለምን እውቀት መጠበቅ ሳያሻቸው፣ የእንግሊዝ የአሜሪካ የጣልያን የእስራኤል የፈረንሳይ ዩኒቨርሲቲዎችን ምርምር ሰነድ ማጣቀስ ሳያስፈልጋቸው፣ ዘመናዊ የጽሕፈት መሣሪያ ሳይፈጠር በጻፏቸው ብራናዎች የተሞሉ ምጡቃነ አዕምሮ ናቸው። እኛ በእነሱ ልንኮራባቸው ይገባ ነበር። ሆኖም እኛ አባቶቻችንን በልካቸው ያላወቅናቸው፣ ከመንገዳቸው ወጥተን የማሰንን፣ እነሱ በእኛ ሥራ ከመኩራት ይልቅ የወላድ መካን እንዲሆኑ ማድረጋችን ያስቆጫል። ካህናተ ኢትዮጵያ የደረሷቸውን ድርሳናትና የጻፏቸውን መጻሕፍት ያነበበ ሰው እውነተኛው የነቢያትና የሐዋርያት መንፈስ በእነሱ ላይ እንደነበረ ያውቃል። መጽሐፍ ቅዱስ እውነተኛ እንደሆነ የሚገለጠው በኢትዮጵያውያን ካህናት ሥርዓት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ያለ ኢትዮጵያ ካህናት ስውር ነው፤ ዐይን የሚዘሩበት ካህናተ ኢትዮጵያ ናቸው። ለዚህ ነው ብራናዎቻቸው በመብራት የሚፈለጉት።  

"…በዚህ ልክ ከሆነ ታዲያ፣ የኢትዮጵያ ካህናት ውድቀት እንዴት ጀመረ? ስንል በርካታ ምክንያቶች አሉ። የበቁ የነቁ ካህናት በዮዲት ጉዲት መታረዳቸው፣ የበቁት ዕውቀታቸውን ሳያስተላልፉ መሰወራቸው፣ በዘጉበት ዋሻ በመነኑበት ተራራ ማረፋቸው፣ እና በዋናነት የግራኝ አህመድ ወረራ ባስከተለው ውድመት መጥፋታቸው ይታወቃል። ኢትዮጵያ ከግራኝ አህመድ በፊት የሀገሪቱ ሥርዓተ ትምህርት ለወንድ ለሴት ሳይባል ይሰጥ ነበር። ሴቶቹ እንደ ወንደቹ በገና ደርዳሪ፣ ቅኔ ዘራፊ፣ አቋቋምና ድጓ አዋቂ ነበሩ። ለአብነት ያህል የጥንቶቹ እነ መስቀል ክብራ፣ እነ ክርስቶስ ሰምራ፣ እነ ወለተ ጴጥሮስ ይጠቀሳሉ። የቅርቦቹን እነ እማሆይ ገላነሽን መጥቀስ ይቻላል። ከግራኝ አህመድ በኋላ በጦርነቱና በጭፍጨፋው መምህራን ስላለቁ የነበረው አማራጭ ከቀዬው ወጥቶ፣ መምህር ካለበት ሩቅ ሀገር ሄዶ፣ መምህር ፈልጎ መማር ግዴታ ሆነ። ሀገሪቱ ለመምህራን ደመወዝ ለተማሪዎች በጀት ማቅረብ የማትችል ሆነች። ስለዚህ ተማሪው መንደር ተሰጥቶት በእንተ ስማ ለማርያም ብሎ በየመንደሩ እየለመነ እንዲበላ መንደሩ እንዲዘከር እስከ ዛሬ ሥርዓት ሆነ። ሴቶች ከቀዬአቸው ወጥተው ከውሻ ተከላክለው መምህር ፈልገው መማር አቅማቸው ስለማይፈቅድ አደጋ ስለሚያጋጥማቸው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓተ ትምህርት ለወንዶች ብቻ የተመሠረተ እስኪመስል የወንዶች ብቻ ሆኖ እስከ አሁን ድረስ ቀጥሏል። አሁን አሁን በየሰንበት ትምህርት ቤቱ ለሴቶች ለማስተማር ቢሞከርም እንደ እማሆይ ገላነሽ ያሉትን የሚያፈራ ውጤታማ መሆን ግን አልቻለም። 

"…ለካህናት መውደቅ የግራኝ አህመድ ክስተት ያሳደረው ጠባሳ የጎላ ነው፤ እስካሁንም ማገገም አልተቻለም። ግራኝ አህመድ እንዳያገኛቸውና እንዳያቃጥላቸው ሲባል ከምናውቃቸው የሐዲስ ኪዳን፣ የብሉይ ኪዳን፣ የስንክሳር፣ የሊቃውንትና የድርሳናት መጻሕፍት ውጭ ከአዳም፣ ከሄኖክ፣ ከኖህ ሲተላለፉ የመጡ ባሕር የሚከፍሉ፣ መና የሚያወርዱ፣ በደመና የሚጭኑ፣ የሰማይን መስኮት የሚዘጉ፣ የሚከፍቱ፣ በመጽሐፍ ያልተጻፉ፣ በልበ ሊቃውንት ብቻ በምስጢር የተያዙ የምስጢር መጻሕፍት አሉ። ከግራኝ ለማሸሽ በከርሰ ምድር በየዋሻው ተቀብረው ስለኖሩ መጎዳታቸው፣ ያልተቀበሩት በተረፉ ሊቃውንት እጅ የነበሩት አገር ሲረጋጋ ግራኝ ሲሞት መልሰው ወደ ተቋም አለመመለሳቸው፣ ሊቃውንቱ ከመመለስ ይልቅ ለልጆቻቸው ማስተላለፋቸው፣ ተረካቢ ሲያጡም አቃጥለውና ቀብረው በመሞታቸው፣ ልጆቻቸው ለራሳቸው ብቻ በማድረግ የሀገርን ጥበብ የግል ማድረገቸው፣ ከመልካሙ ይልቅ ክፉውን መጠቀማቸው፣ ትውልዱ እውቀትን በክፉ ዐይን እንዲመለከት ማድረጋቸው የሚያስቆጭ ነው። ዓለት የሚቀልጥበትን ቀመር የያዙትና ጥበብ እንደ ውኃ እንዲፈስ የመጽሐፍ ቅዱስን ምስጢር በተግባር የሚያሳዩት ምስጢራዊ መጻሕፍት ተቀባይ አልባ ሆነው መጥፋታቸው፣ ተሪፎቹ በሚሽነሪዎች መመዝበራቸውና እስካሁን ከምዝበራ የሚያድናቸው አለመገኘቱን እንገነዘባለን። ስለዚህ አሁን በዘመናችን ያለን ካህናት ተግባራዊ ካህናት ከመሆን ይልቅ ተራኪ ብቻ እንድንሆን አስገድዶናል። እንደ ሙሴ፣ እንደ ነቢያት፣ እንደ ሐዋርያት፣ እንደ አባቶቻችን እንደ አቡነ ተክለ ሃይማኖት፣ እንደ ቅዱስ ላሊበላ፣ እንደ አቡነ ኢየሱስ ሞዓ ተግባራዊ ተአምር ሠሪ ካህናት መሆን አልቻልንም። 

"…ኢትዮጵያ የወደቀችው የካህናትን ውድቀት ተከትሎ ነው። አጋንት አስወጣን፣ ተአምር ሠራን የሚሉ እንደነ 'አባ' ዮሐንስ፣ እንደ ኮማንዶ ግርማ ያሉት ምስሐበ ዛሮች ሠርቶ መብላት ሲያቅታቸው በሰው ቁስል ኑሯቸውን የመሠረቱ፣ ነቢያተ ሐሰት፣ የኤልዛቤል ቅልብተኞች፣ ኤልያስ እስኪገለጥ የሚያታልሉ፣ የአክአብን ፍርፋሪ የሚለቅሙ፣ ለምስሐበ ዛር ለበአል ሰውነታቸውን በካራ እየተለተሉ ደማቸውን የሚያፈሱ፤ አጥማቂ ሳይሆኑ መዝባሪ ናቸው ቢባሉ እነሱም ተከታይ ምእመናንም የማይሰሙ፤ ተከታይ ያበዙ፣ በራሳቸው ራሳቸውን ያበቁ፣ ጉደኞች በአንዲት እናት ቤተ ክርስቲያን ጥላ ሥር እንዲፈሩ ያደረገው ይህ የጥበብ መሠወር ወይም የካህናት ውድቀት ነው። የኢትዮጵያ ካህናት መውደቅ ኢትዮጵያን አብሮ ይዟት ወደቀ። መለኮታዊ ምስጢር ያላወቀ፣ እንደተጫነች አህያ የተጫነውን ድጓ፣ ቅኔ፣ ጵጵስናና ምንኩስና ሳያውቀው የተሸከመው ለራሱም ለሕዝቡም መሆን አልቻለም።👇②✍✍✍

👆③✍✍✍ "…ምስጢረ መለኮትን ለማወቅና ተአምራት ለማድረግ፣ ውዳሴ ከንቱን ፍቅረ ንዋይን ሐሲሰ ሲመትን ለመናቅ፣ ሕዝብን ለማገልገል መጀመሪያ እንደ ሙሴ ነበልባሉ ከሐመልማሉ፣ ሐመልማሉ ከነበልባሉ ሲዋሐድ ማየት ያስፈልጋል። ከሕዝቡ ተለይቶ ወደ ደብረ ሲና መውጣት፣ አርባ ቀን መጾም፣ በደመና መሸፈን፣ ከደመናው የመለኮትን ድምጽ መስማት፣ ያዩትን ምስጢር የሰሙትን ድምጽ በምስጢር መጠበቅ ያሻል። በዚህ መልክ የተሾመ ካህን ወይም ጳጳስ ከተሰጠው መለኮታዊ ዓላማው ፈቀቅ አይልም። በሰይፍ ቢመተር፣ ከእሳት ቢጣል፣ ከጉድጓድ ቢገባ፣ በመጋዝ ቢሰነጠቅ፣ በመንኮራኩር ቢፈጭ፣ ቆዳው ቢገፈፍ፣ እጅ እግሩ ቢቆረጥ እንኳ ወደ ኋላ አይልም፤ ወንጌልን ለመስበክ ከሕዝብ ጎን ለመቆም በቅርጫት ተጭኖ ይኳትናል። ለምን? ቢባል ነቢዩ ቅዱስ ዳዊት "ጠዐሙ ወታእምሩ ከመ ኄር እግዚአብሔር፤ እግዚአብሔር ቸር እንደሆነ ቅመሱ ዕወቁም" እንዳለው ምስጢረ መለኮትን ስለቀመሰ ነው። 

"…አሁን በአገልግሎት ላይ ያለን ካህናት ግን ድጓንና ቅኔን ተጭነን፣ ጣዕሙን የማናውቀው ምስጢር ተሸሸጎብን፣ የእውቀት መጻሕፍት ተሰውረውብን፣ ከሞኝ ጓሮ ሞፈር ይቆረጣል እንደሚባለው ከእኛ ከቤተ ክርስቲያን ጓሮ ዘልቀው ነጮች ቅዱስ ላሊበላን ሲቆፍሩ፣ ጎንደርን ሲንዱ፣ የእውቀትና የምስጢር መጻሕፍት ሲመዘበሩ ካልቆጨን፣ ይልቁንም ከሚመዘብሩት ጋር አብረን ፈርመንና ሰነድ አርቅቀን አመቻችተን ከሰጠናቸው ይህን ድቀተ ካህናት የካህናት ውድቀት ከማለት ውጭ ምን እንለዋለን? ጳጳሳቱን እስኪ እንያቸው? ከየት ነው የመጡት? ጵጵስና ለማግኘት ጉቦ የሰጡ፣ ለሆዳቸው ብለው ገዳማቸውን የተዉ፣ በዘር በፖለቲካ የተሾሙ፣ ምስጢረ መለኮትን ሊቀምሱ ቀርቶ ሰምተው የማያውቁ፣ የኤልዛቤል ቅልብተኞች፣ የአቢይን ፍርፋሪ የሚለቅሙ፣ በተግባረ እድ የሚተዳደሩ፣ በእነሱ ድክመት ቤተክርስቲያንን የሚያስለኩ ናቸው። አንድ ጳጳስ ከግብጽ መጥቶ መላ ኢትዮጵያን አስተምሮ ሕዝቡን በማገልገል ተደራሽነቱን ሳያቋርጥ  ሀገሪቱን በበረከት ሲያትረፈርፍ ነበር። ምክንያቱም ምስጢረ መለኮትን የቀመሰ ስለነበር ነው። 

"…አሁን ጳጳስ እንደ ፍየል እንደ በግ እየተንጋጋ ምን ሠራ? የመናፍቁን ብዛት፣ የሀገሪቱን ውድቀት፣ የሕዝቡን መንገላታት እስኪ ተመልከቱ። "የፈሪ ዱላ አስራ ሁለት ነው" እንደሚባለው የኢትዮጵያ ካህናት ውድቀት ለግብጻውያኑ ጳጳሳት ተሰጥቶ ኢትዮጵያዊ ጳጳስ ቢሾምም በባሰ መልኩ ቀጥሎ ከግብጽ ከመገንጠል አሁን ወደ ትግራይ መገንጠል፣ ግብጽን ጳጳስ ሹሙልን ብሎ ከመማጸን አሁን በራሱ የጨረቃ ጳጳስ መሿሿም ላይ ተደረሰ። ወሮበላ ሲነግሥ ወንበዴ ሲጰጵስ ከዚህ በላይ የካህናት መውደቅ ምን አለ? የኢትዮጵያ ካህናት ለሀገሪቱ ውድቀት ተጠያቂ ናቸው። መለስ ዜናዊ በአርባ ቀኑ የተጠመቀ ኦርቶዶክስ ነበር። ከተጠመቀበት ቀን ጀምሮ ትምህርተ ቤተክርስቲያን ቢማር እንደ ቅዱስ ላሊበላ እንደ ዓፄ ካሌብ ይሆን ነበር። ካህናቱ አጥምቀው ብቻ በመልቀቃቸው አሁን ላለንበት ምስቅልቅል በቃን። አሁን ያለው ካህን የተወለደን ከማጥመቅ፣ የሞተን ከመቅበር ውጭ ምን ሥራ አለው? ታቦት አቁሞ ጥላ ዘቅዝቆ መጎናጸፊያ አንጥፎ የሚለምን ለገንዘብ የደቆነ፣ ለገንዘብ የቀሰሰ፣ ለብር የጰጰሰ፣ ዜማው ጉቦ፣ ቅዳሴው ቦነስ፣ ወንጌሉ ጥቅሱ ንዋይ የሆነ፣ አወዳደቁ ለማንሳት የማይቻል ሰባራ አህያ የሆነ ቤተክህነት ነው አሁን ያለው።

"…የጥንቶቹ ወይም አሁን የገጠሮቹ ካህናት ቤተክርስቲያንን ለመጽደቅ እንጂ የደመወዝ ማስገኛ ቢሮ ያላደረጉ፣ ቀን ሲያርሱ ሌሊት ማኅሌቱን ሰዓታቱን እንደ መላእክት የሚዘምሩ፣ በተግባረ እድ የሚተዳደሩ፣ አራሽ ቀዳሽ ተኳሽ የሆኑ አራት ዐይና ናቸው። የእሳት ልጅ አመድ ነውና እኛን ወለዱ። አሁን ያለን ካህናት እንደ አፍኒንና እንደ ፊንሐስ የአቢይ ጦር የሚጨርሰን ነን። ሲኖዶሱ ከወንበሩ ተቀምጦ የሙዳየ ምጽዋትን መድረቅ ሲያይ፣ በምእመናን መፈናቀል አዲስ አበባ ባዶዋን ስትቀር፣ ቅድስት ሥላሴ፣ ቅዱስ እስጢፋኖስ፣ አራዳ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ እና ሌሎችም ከምዕመናን ባዶ መሆናቸውን ሲሰማ ከወንበሩ ወድቆ ታጥፎ ይሞታል። እግዚአብሔርም የመካኒቱን የሐናን ልጅ ሳሙኤልን ከቤተመቅደሱ ያስነሳል። ሳሙኤልም በአርማቴም በመሴፋ በትግራይ በዐማራ በኦሮሚያ በመላው ኢትዮጵያ ላይ ይፈርዳል፤ ዳዊት ፋኖን ይቀባል። የሲኖዶሱ ኃጢአት ግን በጸሎትም በመስዋዕትም እንደ ኤሊ ኃጢአት የማይሰረይ ይሆናል በማለት የዕለቱን ይሄን አእምሮ የሚሰውር፣ አጥንትን የሚያለመልም፣ አማርኛው፣ የፊደል አጣጣሉ፣ ለዛው የሚያምር እንደ ምግብ የሚበላ፣ እንደ ውኃ የሚጠጣ ግሩም ዲስኩር አቅርበው የተሰጣቸውን ሰዓት በአግባቡ ተጠቅመው ፈጽመዋል። 

"…ከጉባኤው መሃል "ይቅርታ ድቀተ ካህናት (የካህናት ውድቀት) በሚል ርእስ ያቀረቡትን ሊቅ የካህናቱ ትንሳኤ የላቸውም ወይ? በዚህ ላይ አንድነገር ቢሉን በማለት ላቀረቡት ጥያቄ እኚሁ የዛሬውን ድቀተ ካህናት (የካህናት ውድቀት) አቅራቢ በሚል ርእስ ዝግጅታቸውን ያቀረቡት ሊቅ "ከውድቀትም ከሞትም በኋላማ ትንሣኤ ግድ ነው። እናም ይህ ታላቅ ጉባኤ ከፈቀደለኝ በቀጣይ "ትንሣኤ ካህናት" በሚል ርእስ ተዘጋጅቼ እንድመጣ ይፈቀድልኝ በማለታቸው ጉባኤውም ጥያቄውን በደስታ ተቀብሎ የመጋቢት 20 ቀን 2018 ዓም የእኩለ ሌሊት ጉባኤያችን በሰላም ተጠናቅቋል። ጉባኤው አውሮጳ እና አፍሪካ ላለን ሌሊት ሲሆን አሜሪካና ካናዳ ላለት ቀን ላይ ነው የሚሆነው። ፀጥታው ግን ደስስ ሲል። የሊቃውንት ጉባኤው ተጠናክሮ ቀጥሏል። እናንተም ጠንክራችሁ አንብቡ፣ ሓሳብም ስጡ። ማን ያውቃል ከእናንተም መሃል በሊቃውንተ ኢትዮጵያ ታጭቶ ጉባኤውን የሚቀላቀል ይኖራል። በጥቂቶች እንዲህ ከተሠራ የብዙዎች ስንሆንማ አስባችሁታልን? ረጅም ዕድሜ ለሊቃውንተ ኢትዮጵያ አባት ወንድሞቻችን ይስጥልን። 

  
Share on Google Plus

ስለ የተለጠፈበት ቀን

    Blogger Comment
    Facebook Comment