✍ ቆሞስ አባ ጳውሊ | ከግንባር
እንደሚታወቀው በአሁኑ ሰዓት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ትልቅ ፈተና ውስጥ ናት:: አገዛዙ ያለ የሌለ ኃይሉን በመጠቀም እያፈራረሳት ይገኛል:: እንዴት ሃይማኖታችንን መጠበቅ እንዳለብን ከማመልከቴ በፊት ሃይማኖት የሚለውን ቃል በትንሹ እንቃኘው:: ሃይማኖት ሃይመነ፣ አሳመነ ከሚለው የግዕዝ ግስ የተገኘ ሲሆን ትርጉሙም ማመን፣መታመን፣አመኔታ ማለት ነው። ይኸውም ቅድመ ዓለም ከሁሉ በፊት የነበረ ፍጥረታትን የፈጠረ፤ ዓለምን ፈጥሮ የሚገዛ፤ ዓለምንም አሳልፎ የሚኖር፤ ለእርሱ ግን አስገኝ አሳላፊ የሌለው፤ በአንድነት በሦስትነት ያለ ሁሉን ቻይ አምላክ እንዳለ ማመን ነው። ሮሜ ፲፥፱
የእግዚአብሔር የአካል ሦስትነት፣ የባሕርይ፣ የሕልውና፣ የመፍጠር፣ የመስጠትና የመንሣት፣ መለኮታዊ አንድነት፣ የክርስቶስን በፍጹም፥ተዋሕዶ ሰው ሆኖ መገለጥ፣ መከራ መቀበል፣ መሞት፣ መነሣት፣ ማረግና ዳግም መምጣትን ማመን፤ ያለ ጥምቀት፣ ያለ እርሱ ቅዱስ ሥጋና ክቡር ደም ሕይወት እንደሌለ መቀበልና በፍጻሜም ሰው ከሞተ ከፈረሰ ከበሰበሰ በኋላ ይነሣል ብሎ ጽኑዕ ተስፋን መያዝ ማለት ነው፡፡
ዘፍ. ፩፥፳፮፤ ፫፥፳፪
መዝ. ፵፱፥፪
ኢሳ. ፯፥፲፬፤ ፱፥፮
ኢሳ. ፵፥፲
ኢሳ. ፳፮፥፲፭-፲፮
ዳን. ፲፪ ፥ ፭፪
ሚክ. ፭፤፩
ዮሐ. ፫፥፭
ማር. ፲፮፥፲፮
ዮሐ. ፮፥፶–፶፱
ማቴ. ፳፮፥፳፮
ራእ. ፳፪፥፲፪
ይህች ከላይ ያየናት ሃይማኖት በስሙ አምነው ለተጠሩት ሁሉ የተሰጠች ናት። በዚች ሃይማኖት ለመኖር እንተጋለን። ስርዓቷ እና ዶግማዋ በሚያዘን መልኩ ነፍሳችንን ለማዳን በጥላዋ እንከላለን። ከዚህ በዘለለ እንደተጠራንበት መክሊት ሃይማኖታችንን እናስተምራለን እንዲሁም እንጠብቃለን። ሃይማኖታችንን የማስተማር ማለትም የመመስከርና የመጠበቅ ኃላፊነት ይኖርብናል። ልክ እንደ ሐዋርያትና ከእነርሳቸውም እንደተተኩ አበው አባቶቻችን ወንጌልን ለዓለም ሁሉ ማዳረስና የብርሃን መንገድን መግለጽ ሲኖርብን እንደ ቀድሞ ነገስታት ደግሞ ሃይማኖታችንን መታደግ ይኖርብናል። ይህ ማለት አሁን ያለውን የቤተክርስትያን ጠላት ወንጌል በማስተማር የምንመልሰው አይደለም። ምዕመናንን በመጨፍጨፍና አብያተ ክርስቲያናትን በማቃጠል፣ ትውልዱን በማምከንና ሃይማኖትን በማጥፋት በልዩ ልዩ ዘዴዎች እየተዋጋን ይገኛል። አሁን በቤተክርስቲያን ላይ የተነሳው የጥፋት በትር በቁጥር አነስተኛ በሆኑ ሰዎች አይደለም። የተደራጀና መንግስታዊ ስለሆነ ይህን አምባገነን ስርዓት አስወ*ግዶ ሌላ ቤተክርስቲያንን የማይገዳደር ወይንም የቤተክርስቲያንን ኅልውናዋን የማይፈታተን ስርዓት ማምጣት ይኖርብናል። ይህ ዓይነት ተጋ*ድሎ ሰማእትነትና ክብርን የሚያጎናጽፍ እንጂ እንደምታስቡት ኩነኔ አይደለም። የቀድሞ አባቶቻችን ቤተክርስትያንን ያቆዩልን እንደዚህ አድርገው ነው። ቤተ ክርስቲያን እዚህ የደረሰችው ደምና አጥንታቸውን በገበሩ ሰማዕታት ነው። በዚህ ዘመን ያለ ክርስቲያን ቤተክርስቲያን እዚህ እንዴት እንደደረሰች በውል አይረዳም። ሰማዕታት ሲባል ሃይማኖትን መስክረው ያለፉ ብቻ ይመስለዋል። ነገር ግን እንደዚህ አይደለም ብዙ ሰማዕታት ቤተክርስቲያንን በክንዳቸው ጠብቀዋታል። የቀድሞ እናት አባቶቻችን ኢትዮጵያን ሲከላከሉ ዋና ዓላማቸው ቤተክርስትያን መጠበቅም ነበር። ለምሳሌ ያክል በምኒልክ ዘመነ መንግስት የነበረውን እናንሳና ሃገራችን በቅኝ ገዢዎች ተገዝታ ቢሆን ኖሮ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት አትኖርም በምትኩም የካቶሊክ ሃይማኖት በኢትዮጵያ ምድር ላይ ትሰለጥን ነበር። ቀደምትና ታሪካዊቷ ብሉይንና ሐዲስን አስማምታ የያዘችው እውነተኛዋና ቀጥተኛዋ ሃይማኖታችን ትልቅ ፈተና ውስጥ ትወድቅ ነበር። ሆኖም ግን ሃማኖታችን ሰማያዊት ስለሆነች የሚመጡባትን ፈተና በመንፈስ ቅዱስ ጠብቆት እና በልጆችዋ ብርታት ተጠብቃና ተከብራ ኖራለች። ከላይ ያነሳሁላችሁ በምኒልክ ዘመነ መንግስት የተደረገውን መከላከል እንደ አብነት ጠቀስኩላችሁ እንጂ አባቶቻችን እና እናቶቻችን ለበርካታ ዘመናት በዚህ መሰል ፈተና ውስጥ እያለፉ ቤተክርስቲያንን በቅብብሎሽ እዚህ አድርሰውናል።
የዚህ ትውልድ በነጠላ ብቻ ያሸበረቀ ክርስቲያን ነኝ ባይ እጅግ በጣም ያሳዝናል። ከመተችት እና ታሪክን እያነሳ ከመዘከርና በሆሆታና በግርግርታ ከመኖር ውጭ ቤተክርስትያንን እንዴት ላድን ብሎ የማያስብ ሆኗል። ቤተክርስትያንን በነጠላ በመብለጭለጭና ጻድቅ በመምሰል ልንከላከላት አንችልም። ጠላታችን ቤተክርስቲያንን ለማጥፋት ለረጅም ጊዜ አቅዶበት ራዕይና ተልእኮ ይዞ የመጣ ስለሆነ ይህንን ለመመከት እየተባበረ ክንድ ያስፈልገናል፤ ይህን ስላችሁ የሚፀልዩ ይፀልዩ የሚከላከሉ ይከላከሉ! ቤተክርስቲያንን ለመጠበቅ የምናደርገው ማንኛውም እርምጃ ሁሉ ጽድቅ ሰማዕትነትንም የሚያሰጥ የሚያሸልም ነው። እንደዚህ ካልሆነማ ዛሬ የምንዘክራቸውና የምናከብራቸው አባት እናቶቻችን ኃጢአት ሰርተዋል ወደ ማለት ስህተት ይወስደናል። ስለዚህ ክርስቲያኖች ሆይ አትታለሉ ቤተክርስቲያናችሁን ጠብቁ ሃይማኖታችሁን አስከብሩ።
ሃይማኖታችን ስጦታችን ናት። ስጦታችንን መጠበቅ መንከባከብ ይኖርብናል። ሃይማኖትህን ልክ እንደ ጓሮህ አትክልት ተመልከታት! በዙሪያዋ የበቀሉ አረሟን መንቀል ሊያጠፋት የሚመጡ አራዊቶችን ማሳደድና መከላከል ይኖርብሃል! በሌላ አነጋገር መልካም ገበሬዎች እንሁን ማለት ነው። ወዳጄ ሆይ ሃይማኖትህ ሕይወትህ ናት ጠብቃት ተንከባከባት።
ብዙ ጊዜ እርሶ መነኩሴ ነዎት ወደ ገዳምዎት ይግቡ እያሉ የሚያሸፉ ሰነፎችን እያየሁ ነው። እነዚህ ከሆዳቸው ውጭ ምንም የማይታያቸው ሰነፎች ናቸው። ገዳማት በምን ችግር ውስጥ እንዳሉ እንኳን መረዳት ባይችሉ መስማት ሳይችሉ ቀርቶ አይደለም። እኔ ለዓላማ ወጥቻለሁ! በገዳማት ውስጥ ዳዋ ጥሰው ድንጋይ ተንታረሰው ሌት ተቀን የሚፀልዩ በርካታ አባት እናቶቻችን አሉ። ለዚህ ዓላማ የወጣን ሁላችን የሃይማኖት አባቶች በሙሉ ከበርሃ እስከ ደጋ ከደጋ እስከ በረሃ ለዓላማችን ጽኑ ነን። የዚህ ዘመን ክርስቲያን ግን እንዴት አስመሳይ እና ተመጻዳቂ ብቻ ሆነ! ይልቁንስ ንቁ! ቤተክርስትያናችን ችግር ላይ ናት። እኛ አንድ ከሆን ቤተክርስቲያንን በተመሳሳይም ደግሞ ሃገርን ማዳን እንችላለን። ለምን ስንኩላን እንደሆን በጣም እየገረመኝ ነው! ሁሉ አስመሳይ ሁሉ ፈሪ! ወዳጆች ሆይ ታሪክን ዘካሪ ብቻ አንሁን ታሪክም እንስራ እንጂ።
እናንት የቤተክርስቲያን ዕንቁ ልጆች ሆይ ዝም ብላችሁ እጃችሁን አጣጥፋችሁ ከተቀመጣችሁ ልክ የሶሪያና የሌሎች አውሮፓና የሩቅ ምስራቅ ጣፈንታ ይገጥመናል። እነዚያ የክርስቲያን ምድር የነበሩ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት በጣት ሚቆጠሩ ብቻ ናቸው የቀሩት። ከ1950 ዓ.ም ጀምሮ ኢትዮጵያውያን ሰነፎችና ግደለሽ በመሆናችን በጣም ዋጋ እያስከፈለን ይገኛል። በተለይ አሁን በብልጽግና መንግስት ስርዓት ቤተክርስቲያን ከባድ አደጋ ተጋርጦባታልና ልንነቃ ግድ የሚለን ሰዓት ላይ እንገኛለን። ፍትህ ፍትህ ፍትህ....በማለት የሚቀየር አንድም ነገር የለም! ፍትህ ክንድህ ላይ ነው! ዛሬ ካልገባህ መቼም አይገባህም! ስንፍናህ ወይንም ከብልጽግና የሚወረወርልህ አጥንት ዓይኖችህን ጋርዶሃል። ከዘላለምዊ ርስትህ ከሃይማኖትህ ጊዜያዊ ጥቅምህ ከበለጠብህ አንተ ሰው አይደለም! አንተ ያንቀላፋህ ክርስትያን ሆይ ንቃ። ከብልጽግና ስርዓት ጋር የቆመ ክርስትያን በሙሉ የቤተክርስቲያን ጠላት ነው። ለሚጨፈጨፉ ምዕመናንና ለሚቃጠሉ አብያተ ክርስቲያናት አብሮ ተጠያቂ ነው። እግዚአብሔር ከዚህ የጥፋት አገዛዝ ጋር ዋጋውን ይከፍለዋል፤ የጊዜ ጉዳይ ነውና ሁሉንም እናየዋለን። ስለዚህ ሁላችሁም ከጥፋት መንገድ ተመለሱ ወደ ቤተክርስቲያናችሁ ቅረቡ። ከሌሎች ቤተክርስትያንን ከሚያከብሩ የሃይማኖት ተቋማት ተከታዮች ጋር አንድ ሆነን የሀገራችንን ሰላም ማምጣት ይኖርብናል። ብሔር ብሔረሰቦችን አንድ የሚያደርግ የሃይማኖት ተቋማትን የማይነካ አዲስ ስርዓትን ለማምጣት ይህንን አምባገነን መንግስት ለ*ማ*ስ*ወ*ገ*ድ ማንኛውንም እንቅስቃሴ ማድረግ ይኖርብናል።
ይህ አምባገነን መንግስት ታሪክ ይሆናል ሀገራችን ትነሳለች ሃይማኖታችንም ለዘለዓለም ትቀጥላለች!
ድል ለኢትዮጲያ!
Blogger Comment
Facebook Comment