የካቶሊክ ልብሰ ተክህኖ ቤተክርስቲያናችንን እየወረራት ነው‼️





✍ ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው

ቅድስት ቤተክርስቲያናችን ስንዱ እመቤት ናት ሲባል እንዲሁ ዝምብሎ አይደለም። ከሕንፃ ቤተክርስቲያን እስከ ልብሰ ተክህኖ ባሉ ንዋዬ ቅድሳትና አገልግሎቶች ድረስ ሁሉ ለምታደርገው ለእያንዳንዷ ነገር ምክንያት፣ ምሥጢርና ምሳሌ እንዲኖረው ተደርጎ ሁሉም ነገር ጥንቅቅ ተደርጎ የተሠራ ሥርዓት፣ ቀኖናና ዶግማ ያላት ስለሆነችና ዝም ተብሎ በነሲብ ወይም በደስ አለኝና መሰለኝ የሚደረግ ምንም ነገር ስለሌላት እንጅ‼️ 
ግን ምን ዋጋ አለው በመንፈስ ቅዱስ በተቀኙ ቅዱሳን አባቶቻችን በስንት ድካም እንዲህ ጥንቅቅ ተደርጋ የተሰናዳችው ቅድስት ቤተክርስቲያናችን በዓመፃ ልጆች እጅ በመውደቋ ጥንቅቅ ተደርጎ የተሠራው ሥርዓት እየፈራረሰ ይገኛል። እየፈራረሰ ካለው ሥርዓቷ ውስጥ አንዱ የልብሰ ተክህኖ ሥርዓቷ ነው‼

የትኛው የልብሰ ተክህኖ ሥርዓታችን ነው የተሻረው? ያላቹህ እንደሆነ በልብሰ ተክህኖ ሥርዓታችን መሠረት ካህናት ለቅዳሴ፣ ለኪዳንና ለመሳሰሉት አገልግሎቶች ሲሰማሩ ዲያቆን የሚለብሰው ልብሰ ተክህኖ ቀሚስ ከላንቃ ነው። ቄሱ ደግሞ ካባ ከላንቃ ወይም ካባላንቃ ነው። ቀሚስ አይለብስም። መነኩሴ የሆነ እንደሆነ ደግሞ ካባ ከላንቃውን በቀሚስ ላይ ያደርጋል። ቀሚስ የጃንደረባነት ወይም የድንግልናና የምንኩስና ምልክት ስለሆነ ነው ቄስ ቀሚስ ሊለብስ የማይችለው። ስለሆነም ቄስ ኩታውን ወይም ጋቢውን አደግድጎ ይለብስና በላዩ ላይ ካባ ከላንቃውን ለብሶ ነው የሚቀድሰው ሌሎች አገልግሎቶችንም የሚያገለግለው። ዲያቆንም ቀሚስ ከላንቃ የሚለብሰው የዛሬን አያድርገውና ሥርዓቱ እንዲህ ከመበለሻሸቱ በፊት ዲያቆን በዲቁናው እስካለ ጊዜ ድረስ ድንግል ስለሆነ ነው የዲያቆን ልብሰ ተክህኖ ቀሚስ ከላንቃ እንዲሆን የተደረገው። ዲያቆን ካገባ በኋላ በዲቁና ገብቶ መቀደስ አይችልም። ምክንያቱም ድንግልናውን አጥቷልና ቀሚስ መልበስ ስለማይችል። በዚህም ምክንያት ካገባ በኋላ ቀስሶ በቄስነት ካልሆነ በስተቀር በዲቁና መቀደስ አይችልም ነበር። ዛሬ ግን እንደምታዩት ዲያቆናት አግብተውም በዲቁና ገብተው እንዲቀድሱ እየተደረገ ያለበት ዘመን ላይ ነው ያለነው። ኧረ ጭራሽ እንዲያውም ያፈረሱ ዲያቆናት ጭምር ክህነታቸውን ማፍረሳቸው ወይም መጣላቸው እየታወቀ ገብተው እንዲቀድሱ እየተደረገ ያለበት ዘመን ላይ ነው ያለነው። ያፈረሱ ዲያቆናት ብቻ ሳይሆኑ ያፈረሱ ቀሳውስትና ያፈረሱ መነኮሳትም ናቸው ገብተው እንዲቀድሱ እየተደረገ ያለው። አየ ወገኖቸ ይሄ ሁሉ መቅሰፍት ታዲያ በምን ምክንያት የመጣ መሰላቹህ??? በቀደመው ጊዜ አርበኞቹ "ረድኤተ እግዚአብሔር ይከተለኝ፣ ኃይለ እግዚአብሔር ይደርብኝ!" ለሚል ተማጽኖ ዘመቻ ሲኖርባቸው ከየደብራቸው ይሄንን የዲያቆን ልብሰ ተክህኖ ወስደው በመልበስ የመዝመት ልማድ ነበር‼️ 
አሁን የልብሰ ተክህኖ መበረዝ የተከሰተው ወይም የራሳችንን ጥለው የካቶሊክ ልብሰ ተክህኖን እንዲለብሱ እየተደረገ ያለው ቄስና መነኩሴ በሚለብሱት ልብሰ ተክህኖ ነው። የበፊቱ ካባላንቃ ቀርቶ ካባ በሚመስለውና እስከ መሬት ድረስ በሚጎተተው የካቶሊክ ልብሰ ተክህኖ ተተክቶ አገልግሎት እንዲከወን እየተደረገ ነው ያለው። ላንቃ ስላቹህ እሳት ትዝ እንደሚላቹህ አልጠራጠርም። የእሳት ላንቃ ሲባል ትሰማላቹህና። አባቶቻችን የእሳት ላንቃን ምሳሌ በልብሰ ተክህኗችን ላይ እንዲቀመጥ ያደረጉበት ምክንያት መንፈስቅዱስ በእሳት ይመሰላልና የካህናቱ አገልግሎት በመንፈስ ቅዱስ ምሪትና ቅኝት እንደሚፈጸም ስለምናምን ነው ይሄንን ለማመልከት አባቶቻችን በልብሰተክህኗችን ላይ የእሳት ላንቃ ምሳሌ እንዲቀመጥ ያደረጉት የነበረው። በልብሰ ተክህኖው ላይ የሚደረገው የላንቃዎቹ ቁጥር አምስት ሲሆኑ አምስቱን አዕማደ ምሥጢራትን የሚወክሉ ናቸው‼
ካባላንቃ የምላቹህ ልብሰ ተክህኖ በቁጥ አንድ ፎቶ ላይ ቅዱስ ፓትርያርኩ ማለትም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ እና የውሸቱ ወይም ከቀኖና ውጭ የተሾሙት የወያኔው ሹመኛ አቦይ ማትያስ ለብሰውት የምታዩት እንዲሁም በቁጥር ሁለትም ላይ ካህናት ለብሰውት የምታዩት ልብሰ ተክህኗችን ነው ካባላንቃ የሚባለውና ትክክለኛው ልብሰ ተክህኗችን። 

በቁጥር 3፣ 4፣ 5፣ 6 እና 7 ፎቶዎች ላይ ለብሰውት የምትመለከቱት ግን የካቶሊኮቹ ልብሰ ተክህኖ ነው። እንደምትመለከቱት በካቶሊኮቹ ልብሰ ተክህኖ ላይ ላንቃ የለበትም።

አንዳንዶቹ ካህናት ይሄንን የካቶሊኮቹን ልብሰ ተክህኖ ሲለብሱ እላዩ ላይ ሞጣሕት ያደርጉበታል። አንዳንዶቹ ደግሞ ሞጣሕቱን ከውስጥ ያደርጉትና ይሄንን የካቶሊኩን ልብሰ ተክህን ደግሞ በላይ ያደርጉታል። ይሄ የካቶሊኮቹ ልብሰ ተክህኖ እንደ የእኛው ካባላንቃ የእጅ ማውጫ ስለሌለው ለማእጠንትም ለምንም ፈጽሞ አይመችም። ካህናቱ "ማዕጠንት ልጠን፣ ቡራኬ ላድርግ!" ሲሉ ልብሱ በክንዳቸው እየተገፋ ወደኋላ ስለሚሸሸ ይወልቅባቸዋል። ይሄንን የካቶሊክ ልብሰ ተክህኖ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ቤተክርስቲያናችን ያስገቡት በካቶሊክነት የሚጠረጠሩት አባ ጳውሎስ ናቸው። ከዚያ በኋላ እሳቸውን ተከትለው ጳጳሳቱ ሁሉ ማድረግ ጀመሩ። በስደት ከነበረው ሕጋዊው ሲኖዶስ ያሉት ጳጳሳት ሳይቀሩ ይሄንን ካባ የሚመስለውን የካቶሊክ ልብሰ ተክህኖ መልበስ ቀጠሉ። ጳጳሳቱ ይሄንን ካባ የሚመስለውን የካቶሊክ ልብሰ ተክህኖ እንደ ካባ ዓይተውትና ከእኛው ካባ ጋር አጠጋግተው ዓይተውት ከሆነ እየለበሱት ያሉት ካባ የክብር ልብስ በመሆኑ ጳጳሳቱ በዐውደ ምሕረት ላይ፣ በጥምቀትና በመስቀል በዓላት ላይ ለብሰውት ቢታዩ ችግር ባልነበረው ነበር። ምክንያቱም ቁመቱ እረዘመ እንጅ ሥራው ካባ ነውና። እነሱ ግን እንደ ልብሰ ተክህኖ ቆጥረውት በቅዳሴና በሌሎች አገልግሎቶችም ላይ ነው እየለበሱት ያሉት። አሁን አሁን ደግሞ ከጳጳሳቱም አልፎ ወደ ሰሞነኛ ወይም ልዑክ ካህናቱም በመውረድ በውጭ ሀገራትና በአዲስ አበባ ባሉ አብያተክርስቲያናት ያሉ ካህናት እንደ ፋሽን አድርገው ይዘውት በምሥጢር የበለጸገውን የእኛን ካባላንቃ አውልቀው ጥለው ይሄንን ካባ የሚመስለውን የካቶሊኮችን ልብሰ ተክህኖ እየለበሱ ቅዳሴ ይቀድሳሉ ሌሎች አገልግሎቶችንም ያደርጋሉ። እነኝህን ካህናት ግን "በካባ ቀድሱ እስኪ?" ብትሏቸው "እንዴ እንዴት ተደርጎ? ካባ የክብር ልብስ እንጅ ልብሰ ተክህኖ ነው እንዴ?" እንደሚሏቹህ እርግጠኛ ነኝ።
ስለዚህ ይሄንን እንደ ፋሽን የያዙትን ካባ የሚመስለውንና ካቶሊኮቹ በቁጥር ሰባት ፎቶ ላይ አድርገውት የምትመለከቱትን የካቶሊኮችን ልብሰ ተክህኖ እንደ ልብሰ ተክህኖ ቆጥረውታል ማለት ነው‼

እናም እባካቹህ ተቆርቋሪ ካህናት እና ምእመናን ሆይ! ቅድስት ቤተክርስቲያናችን እንዲህ ዓይነት ጥፋትም እየተፈጸመባት ነውና ይሄ የካቶሊክ ልብሰ ተክህኖ ወደ ቀሪው የሀገራችን ክፍል ተዛምቶና ተለምዶ ከመቅረቱ በፊት ቅዱስ ቃሉ "አባቶችህ የሠሩትን የቀድሞውን የድንበር ምልክት አታፍልስ!" ምሳ. 22፤28 እንዲል ይሄ የጥፋት ሥራ እንዲቆምና ካህናቱ ወደራሳችን አባቶቻችን በመንፈስቅዱስ ተቀኝተው በምሥጢር፣ በምክንያት፣ በምሳሌ ወዳዘጋጁት የካባላንቃ ልብሰተክህኗችን እንዲመለሱ ታገሉ‼

Share on Google Plus

ስለ የተለጠፈበት ቀን

    Blogger Comment
    Facebook Comment