ቅዱሳን ነገሥታት አብርሃ ወአጽብሓ
አባታቸው ታዜር እናታቸው ሶፍያ (አህየዋ) ይባላሉ፡፡ መንትዮች የሆኑት እነዚህ ቅዱሳን የተወለዱት ጌታችን በተወለደባት ዕለት በታኅሣሥ 29 ቀን 312 ዓ.ም ነው፡፡
አብርሃ ወአጽብሓ ከመንግሥት አስተዳደሩ ጋር ክርስትናንና ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን በመላ ኢትዮጵያ በማዳረስ እጅግ ከፍተኛ አስተዋፅዖ አድርገዋል፡፡ ካህናትንና ዲያቆናትን ይዘው በመላ ኢትዮጵያ ሐዋርያዊ ጉዞ በማድረግ ሕዝቡን ሁሉ እያስተማሩ፣ ሃይማኖትን እያጸኑ፣ ሥርዓተ ጥምቀትን እያስፋፉ ብዙ አብያተ ክርስቲያናትን አንጸዋል፡፡
ታላቁ አብርሃ በ364 ዓ.ም ጥቅምት 4 ቀን እሑድ ዕለት ዐረፉ፡፡ ከ13 ዓመት በኋላ ታናሹ አጽብሓ በ379 ዓ.ም ጥቅምት 4 ቀን ዐረፉ፡፡ ልደታቸውም ሆነ ሞታቸው አንድ ቀን ነው (የዕረፍታቸው ዓመቱ ይለያይ እንጂ) የተቀበሩበት ቦታም አንድ ነው፡፡ የንግሥና ስማቸው ኢዛናና ዛይዛና ይባላል፡፡
አቡነ በርተሎሜዎስ ዘደብረ ዘመዳ
ከአቡነ ተክለ ሃይማኖት ልጆች ውስጥ አንዱ ሲሆኑ ያመነኮሷቸውና የሾሟቸውም እርሳቸው ናቸው፡፡ የቆባ፣ የጠጠርና የኮረም ኤጲስ ቆጶስ ሆነው ተሹመው በብዙ ድካም አገልግለዋል፡፡ ጻድቁ ደብረ ሊባኖስን የሚያጥኑበት ተራቸው በወርሃ ጳጉሜ ነበር፡፡
ወሎ ራያ ውስጥ ያለችውን ጥንታዊቷንና ባለታሪኳን ደብረ ዘመዳን የመሠረቷት ይህ ታላቅ አባት ናቸው፡፡ ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ የሳላት የእመቤታችን ሥዕል ሁልጊዜ ሰዓታትና ማኅሌት በማይታጎልባት በዚህች ጥንታዊ ገዳም ውስጥ ትገኛለች፡፡
እጅግ በርካታ ቅርሶችም ይገኙባታል፡፡ በአካባቢዋም ዘብ ሆነው የሚጠብቋት በርካታ የዱር አራዊት ይገኛሉ፡፡ ጻድቁ በታላቅ መንፈሳዊ ተጋድሎ ኖረው በሰላም ዐርፈዋል፡፡
◦🍀◦🍀◦🍀◦
Blogger Comment
Facebook Comment