ሰመአቱ የኢትዮጵያ ንጉሥ ዓፄ ገላውዴዎስ‼️


"ዓፄ ገላውዴዎስ ጌታን ተከተለ
ፋሲካውን ሳይውል አርብ ተሰቀለ።"

መጋቢት 27 ቀን በኢትዮጵያ ምድር ታላቅ አባት በሰማእትነት አርፏል ይህም ዓፄ ገላውዴዎስ ነው፤ ይህ አባት ቤተክርስቲያን የቅድስና ማእረግ ሰጥታ ከምታዘክራቸው ነገስታት የመጨረሻው ንጉስ ነው። ከዚህ በኃላ በኢትዮጵያ ምድር የነገሱት ነገስታት ምን ደግ ስራ ቢሰሩ የቅድስና ማዕረገ አላገኙም። 

ዓፄ ገላውዴዎስ የዓፄ... ልብነ ድንግል ልጅ ናቸው፤ ግራኝ መሐመድ ኢትዮጵያን ሲወር ከአባታቸው ጋር ሸሽተው ወደ ደብረ ዳሞ ሄዱ በዚያም ለ 17 ዓመት ቆዩ አባታቸው ዓፄ ልብነ ድንግል ሲሞቱ ወራሽ ሆነው ነገሱ ጦራቸውን አደራጁ ከፖርጁጋሎች ጋር ሆነው ግራኝን ገጠሙት ለየካቲት ማርያም በ 1543 ዓም ወይናደጋ በተባለ ቦታ ላይ ድል አደረጉት ግራኝ ሞተ የቀሩት ሸሹ ይላል፡፡

 በጦርነቱ ማግስት ፖርቹጋሎች “አባትህ ቃል በገባልን መሰረት አገር ቆርሰህ ስጠን ሃይማኖታችሁንም ለውጣችሁ የካቶሊክን እምነት ተቀበሉ” አሏቸው፤ዓፄ ገላውዴዎስም ሲመልሱ “አገር ቆርሰን አንሰጥም ሃይማኖትም አንለውጥም፤ ለዋላችሁልን ውለታ ግን ወርቅ ብር እንሰጣቹሃለን አሏቸው” ዋ !!!  ብልህ መሪ ይሉሃል ይህ ነው፤
” ኢይኀድጋ እግዚብሔር ለብሔር ዘእንበለ አሐዱ ሄር” “ እግዚያብሔር አገርን ያለ አንድ ጠባቂ አይተዋትም ማለት ነው። በዓፄ ገላውዴዎስ መልስ የፖርቹጋሉ ጦር አዛዠ ቤርሙዳ ተቆጣ በስውርም ሊያስገድሏቸው አስቦ አልተሳካለትም። 

ከዚህ በኃላ ግራኝ ያጠፋውን አገር ማቅናት፤ የተጎዳ የተሰደደውን ህዝብ ማጽናናት ጀመሩ ከአቡነ ዮሳብ ጋር ሆነው ስርዓተ ቤተክርስቲያንን አጸኑ ብዙ አብያተክርስቲያናትን አነጹ። ከዚህ በኃላ እንዲህ ሆነ የሐረሩን ገዢ ኑር መሐመድን ጦሩን አደራጀቱ መጣ ዘመኑ 1552 ዓ.ም ወርሃ መጋቢት በሃያ ሰባተኛው ቀን ዕለቱ ደግሞ ዓርብ ነው ከሶስት ቀን በኃላ ፋሲካ ነው፤ በዙሪያቸው ያሉት መኳንንት መሳፍንቱ አማካሪዎቻቸው ፋሲካን አክብረን ጦርነቱን ብንጀምር ይሻላል አሏቸው፤ ዓፄ ገላውዲዎስ ሲመልሱ እንዲህ አሉ እኔስ ፋሲካን ከጌታዬ ጋር በሰማይ አከብራለሁ ጦርነቱ መጀመር አለበት አሉ ትንቢታዊ ንግግር ነበር፤ ጦርነቱ ተጀመረ ከፊት ሆነውም ሲዋጉ ሲያዋጉ ውለው ማምሻውን በጥይት ተመትተው ወደቁ አንገታቸውንም ቆርጠው ገደሏቸው። ታዲያ ህዝቡ እንዲህ ብሎ አለቀሰላቸው፦

ዓፄ ገላውዴዎስ ጌታን ተከተለ
ፋሲካውን ሳይውል አርብ ተሰቀለ።

የሰመአቱ አፄ ገላውዲዮስ በረከታቸው ይደርብን።

የመረጃ ምንጭ፥ ስንክሳር፤ የቤተክርስቲያን መረጃዎች።
Share on Google Plus

ስለ የተለጠፈበት ቀን

    Blogger Comment
    Facebook Comment