የአምኃ ኢየሱስ ገብረ-ዮሐንስ ለሰባተኛ ጊዜ ትምህርታዊ የሆነ የጽሑፍ መልእክት ነው።

ወደዋናው መልእክቴ ከመግባቴ በፊት ግን አጭር ማሳሰቢያ ተናግሬ ልለፍ። ይኸውም ድምፅህ ናፈቀን፣ ድምፅህን ባለመስማታችን ስለ ጤንነትህና ስለ ደህንነትህ እየተጠራጠርን ነው። እናም እባክህን መልእክትህን በድምፅህ ላክልን። በተጨማሪም ውጭ ሀገር የምንሠራ ሰዎች መልእክትህን ለማዳመጥ የምንችለውና የሚመቸን በድምፅ ሲሆን ነው። በጽሑፍ ሲሆን ከሥራ ጋር ለማንበብ ስለማይመቸን ነው። እንዲሁም ብዙ እናቶችም አባቶችም ጽሑፍ የማያነቡና መልእክትህን ግን ሥራየ ብለው መስማት የሚፈልጉና የሚጓጉ በየሀገሩ ስላሉ በድምፅ ቢሆን ደስ ይለናል እያላችሁ የምታደክሙኝ ብዙዎች ናችሁ። እኔ ግን ምክንያቴን ስንቴ ነው የነገርኳችሁ? እባካችሁን የተመለሰ ጥያቄ እየደጋገማችሁ አትጠይቁኝ። ስለ እናንተ ችግርና ፍላጎት እውነት ለመናገር ከሆነ ከእናንተ ይልቅ እኔ ሳላስብና ሳልጨነቅ የምቀር ይመስላችኋልን? በመንፈስ ብትመሩ ኖሮ ልቤንና አዕምሮየን ምንነቱን ከፍታችሁ ታዩት ነበር። ስለዚህ ማንበብ የሚመቻችሁ አንብቡ። የማይመቻችሁ ደግሞ አምኃ ኢየሱስ ምን አለ? እያላችሁ እየተጠያየቃችሁ እውነቱን በመነጋገር ለመስማትና ለማወቅ ሞክሩ። ሌላ የምላችሁ የለኝም። እናም አሁን አልተፈቀደልኝም። ሲፈቀድልኝ ነው በድምፅ የምለቅላችሁ ብየ ነገርኳችሁ እኮ። ለምን አይገባችሁም? የእናንተ ጥያቄ፣ ልመና፣ ተማጽኖ፣ አስተያየት፣ ሀሳብ ሁሉ ስለራሴ ምክንያት እኔ ከማውቀው ምስጢር ይበልጣልን? በሉ መልእክቴ ሁሉ ለበጎች መልካም ሣር ይሁንላችሁ። ለፍየሎች ደግሞ የሚሆነው ይሁንባችሁ። በተጨማሪም፦ ኢየሩሳሌም ግደይ (አስካለ ማርያም) የተባልሽው የትግሬ ተወላጅ እህቴ ሆይ፦ በተደጋጋሚ በውስጥ መስመሬ የጻፍሽልኝን ደብዳቤሽን በደንብ አይቸዋለሁ። የድምፅ መልእክትሽንም በደንብ አዳምጨዋለሁና አይዞሽ የእኔ እህት ተረጋጊ። ምንም አይነት ስህተትና ጥፋት የለብሽም። በፍጹም በፍጹም እመኝኝ። እንዲያውም ጥሩ ነው ያደረግሽ። ስለዚህ ኀዘን ይቅርና ሀሳብም አይግባሽ። እኔ የተናገርኩት አንቺ በነገርሽኝ መንገድ አይደለምና ምንም አይነት ሃሳብ እንዳይገባሽ በቃ። ለወደፊቱ ልጽፍልሽ እሞክር ይሆናል። በአካለ ሥጋም ለመገናኘት ያብቃን። ሆኖም ግን ቤተ-ሰቦቼን፣ ዘመዶቼን፣ ወገኖቼን፣ ነገዶቼን ትግሬዎችን እንዲህ መዓት የምታወርድባቸው ለምንድን ነው? ብትይና እንደ ጠፊዎቹ ወገኖችሽ መልእክትህማ ከነገዶቼ በምንም ሁኔታ አይበልጥብኝምና ጥንቅር ብሎ ይቅር አልሰማም፣ አላምንም፣አልቀበልም ብትይና ከአጥፊ ነገዶችሽ ጋር ብትጣበቂ ወዮልሽ። ከጥፋት ደምሽ ንጹህ ነኝ። ዝም ብለሽ የራስሽን ነፍስ ለማዳን በርቺ። የቅዱሳን አምላክ መድኃኒዓለም ከቅድስት እናቱ ጋር ከክፉ ነገር ሁሉ ይጠብቁሽ። ደህና ሁኝልኝ። በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ። ___በቁጥር አራት የጽሑፍ መልእክቴ አማካኝነት በውስጥ መስመሬ መልስ የሚያስፈልገው የተወሰኑ ትምህርታዊ ጥያቄዎች የጠየቁኝ ጤነኛ ክርስቲያን ቤተሰቦቼ የሆኑ ስላሉ ለነሱ ጥያቄዎች መልስ ሰጥቼ ስጨርስ የዘመድ-ኩን መልእክቴ ወደሆነው እለጥቃለሁና ሁሉም ትምህርት ስለሆነ ጤነኛ ክርስቲያኖች የሆናችሁ አንብቡት። በሽተኞች ክርስቲያን ተብየዎች ግን ተዉት ይቅርባችሁ አታንቡት። ያማችኋልና። የጥያቄው ትምህርት ግን ለሁላችሁም መሆኑን ልታዉቁት ግድ ነው። ስታነቡ ግን ደጋግሜ እንደነገርኳችሁ በዓይናችሁና በአፋችሁ መጋለብ ሳይሆን እባካችሁን እንደ ጎበዝ ጸሎተኛና ተማሪ በአዕምሮአችሁ እያሰባችሁና በልቦናችሁ እያገናዘባችሁ በማስተዋል በመንፈስ ነው ማንበብ። ከአፋቸዉ የድንቁርና ቃል የሚያወጡ አንባቢዎች እኮ የሚያነቡትንና ያነበቡትን የማያውቁ አዕምሮአቸዉና ልቦናቸዉ ምናምንቴ የሆነባቸዉ ምናምንቴ ናቸዉ። እነሱ ያላቸዉ ምናምንቴ የሆነ አፍ ብቻ ነው። አይደለም አዕምሮና ልቦና ጀሮና ዓይን እንኳ አላቸዉ ለማለት አልሞክርም። ጥያቄዎቹ የሚከተሉት ናቸዉ። ___አባታችን! በቁርባን የተጋባን ወጣቶችስ እንዴት እናድርግ? መቁረብ አንችልም ማለት ነው? መቸም ሰው ነንና በኃጢአት መውደቅ አይቀርምና ብላችሁ የጠየቃችሁኝ አላችሁ። ለጥያቄአችሁ መልሴ አጭር ነው። ከመልሴ በፊት ግን ራሳችሁን ደካማ አድርጋችሁና ደካማ መሆናችሁን አውቃችሁና አምናችሁ ራሳችሁን (መንፈሳችሁን) ከአጉል የመንፈስ ትዕቢት ዝቅ አድርጋችሁ መጠየቃችሁና መናገራችሁ በፈጣሪም በሊቃውንቱም ሁሉ የሚያስመሰግናችሁና የምታስደስቱ ናችሁና መድኃኒዓለም ይባርካችሁ ያክብራችሁ። ይህን ስላልኳችሁ ግን ገና ለገና ደካማ ነን እያላችሁ በቀላሉ የሥጋ ፈተና ለመውደቅና ለሰይጣን እጅ ለመስጠት መንገዳገድ የለባችሁም። ብትንገዳገዱ እንኳ ሳትወድቁ ተንገዳግዶ ቆሞ ለመቅረትና ለመበርታት መሞከርና መታገል ነው ያለባችሁና አይዟችሁ። ብትወድቁም እንኳ ፈጥናችሁ መነሳት ነው ያለባችሁ። መልስ፦ እናንተማ አንዴ ስትጋቡ በንስሐ ታስራችሁና በቁርባን ታማችሁ የተያዛችሁ ስለሆነ ወዴትም ወዴት አትሄዱም። ታስራችኋላ!! ታማችኋላ!! ስለዚህ መላ ውስጣዊና ውጫዊ አካላችሁን ከክፉ ነገር ሁሉ እየጠበቃችሁ በቁርባናችሁ ወደፊት መግፋት ነው ያለባችሁ። ቁርባኑ እኮ ወደ ክፉ የኃጢአት አውሬ እንዳትሄዱና እንዳትበሉ ተቆጣጣሪና ጠባቂ እረኛችሁ መሆኑን እወቁ። ሁሉም የሥጋ ነገር ፈተናው ከአቅም በላይ ሆኖባችሁና ድንገት ሳታስቡትም ሆነ ተስፋ ቆርጣችሁ በኃጢአት አውሬ ብትወድቁና ብትያዙ እንኳ ንስሐ አባት ስላላችሁ ከዛው ከሳቸው ጋር መነጋገርና መጨረስ ነውና አይዟችሁ ወንድሞቼና እህቶቼ ሁሉ። ብቻ ግን እናንተ ባላችሁ ሥጋዊይና ነፍሳዊ ብርታት እስከቻላችሁ ድረስ ከልባችሁ ያቅማችሁን ታገሉ። ከአቅማችሁ በላይ የሚሆነውን ራሱ መድኃኒዓለም ያውቀዋል ያስተካክለዋል። ብቻ ግን እናንተ በቀላሉ የሥጋ ፈተና ለመውደቅ አትርበትበቱ። በሚወድቅ ሰው ላይም እዘኑ እንጅ አትፍረዱ። ብዙ ማጽናኛ እነግራችሁ ነበር። ሆኖም ግን ትቀብጡና የባሰ ትዳፈራላችሁ። ስለዚህ ትቸዋለሁ። እግረ-መንገዴን ግን የምነግራችሁ፦ ንስሐ ማለት ምሳሌው እግርንና እጅን በእግር ብረትና በእጅ ካቴና ታስሮ በእስር ቤት እንደመቀመጥ ማለት ነው። ቁርባን ማለት ደግሞ ምሳሌው በሥጋ ደዌ ታሞ የአልጋ ቁራኛ የደዌ ዳኛ ሆኖ በቤቱና በአልጋው ላይ እንዲሁም በሐኪም ቤት መኖር እንደማለት ነው። የእነዚህ ሁለቱ ነገሮች ሲተነተኑ ምስጢራቸው ብዙ ነው። ምንኩስና ደግሞ ምሳሌው በእስር ላይ ሳለ ወደ ሕመም፣ በሕመም ላይ ሳለ ወደ ሞትና መቃብር መውረድና መኖር ማለት ነው። በተረፈ ግን ከላይ ስለ ቁርባኑ የጠየቃችሁኝ ሰዎች ጥያቄው ከዛው በንስሐ አባታችሁ የሚፈታ ነበር እንጅ ወደኔ የሚመጣ አልነበረም፣ ቀላል ነገር ነውና። እኔም መልስ የሰጠኋችሁ ደስ ይበላችሁ ብየ ነው እንጅ አልሰጣችሁም ነበር።ሆኖም ግን ፈጣሪ ይጠብቃችሁ፣ ያጽናችሁ። የረሳሁት ግን በተደጋጋሚ ነገርኳችሁ ግን አትሰሙም ለምን?? የእውነትም ይሁን የውሸት የጾታ መታወቂያ፣ መለያ፣ መጠሪያ፣ ገላጭ የሆነውን ስማችሁን ጻፉልኝ። ይህ ካልሆነ ደግሞ ክርስትና ስማችሁን ጻፉ ብየ ችግሬን ነገርኳችሁ። ግን ግን ምን አይነት ክርስቲያኖች እንደሆናችሁ ሊገባኝ አልቻለም። ከእንግዲህ ወዲያ ግን ይህንን ለማይፈጽም ለማንኛውም ጠያቂና ጥያቄው ምንም አይነት መልስ የማልሰጣችሁ መሆኔን በድንግል ማርያም ስም በመሐላ ዘጋሁ። _____ሌላው አሁንም መልስ የሚያስፈልገውና ለክርስቲያኑ ሁሉ ጥሩ ትምህርት የሚሆን የተጠየቅሁት ጥያቄ የወልደ ገብርኤል ነው። ጥያቄውም እንዲህ ይላል። ____<<........ስለ ደም ልገሳ እና ስለ ኩላሊት መቀያየር ምን ይላሉ? መልካም ፈቃድዎ ከሆነ በዚህ ዙሪያ ትምህርት ቢሰጡን ደስ ይለኛል....>> የሚል ነው። እውነታውን ትምህርትና እውቀት ለሚቀበለው ክርስቲያን ግሩም ጥያቄ ነው። መልስ፦ ውድ ወንድሜ ወልደ-ገብርኤል ሆይ! በቅድሚያ የጠየቅኸው ጥያቄ ራሱን የቻለ ሰፊና ጥልቅ የሆነ ሃይማኖታዊ ትምህርት ያለው መሆኑን አሳምሬና ጠንቅቄ የማውቅ መሆኔን ልነግርህ እወዳለሁ። በዚህ መሠረት የጠየቅኸው ጥያቄ ለክርስቲያኑ ሁሉ መልስ እንድሰጥበት የሚያስገድደኝ መሆኑን ባውቅም አሁን ግን ስለ ዘመኑ ሕዝበ-ክርስቲያን የተንኮል ክፋትና ኃጢአት ስል ሕዝበ-ክርስቲያኑን ወክየ መልስ ልሰጥህና ላስተምረው አልችልም (አልወድም፣ አልፈቅድም)። ምክንያቱም የዛሬው ክርስቲያን ነኝ ባይ ሁሉ ዓይኑ ባየው፣ ጀሮው በሰማው፣ አዕምሮው ባሰበው፣ ልቡ በፈቀደው በራሱ የስሜትና የፍላጎት መንፈስ ብቻ መሄድንና መኖርን ስለሚፈልግና በራሴ ጉዳይ ምን አገባህ? የሚልና በጽድቅ ቶሎ ከመሞት ይልቅ በኃጢአት ቆይቶ መሞትን የሚመርጥና የሚፈልግ ስለሆነ አሁን የምሰጥህ መልስ ሁሉንም ክርስቲያን ወክየ ሳይሆን አንተንና ራሴን ብቻ ወክየ፣ ሃይማኖቴንና ትምህርቴን ምክንያት አድርጌ አጭርና ጣፋጭ የሆነች መልስ ልስጥህ። እናም የመልእክቴ ምስጢሩ ላንተ ይገባሃል። ስለሌላው ግን ይግባው አይግባው አያገባኝም። ይኸውም፦ እኔ አምኃ ኢየሱስ በአርባ ቀኔ በቅዱስ ጥምቀት፣ በቅዱስ ቅብዐ-ሜሮን፣ በቅዱስ ሥጋ ወደሙ የተቀደሰውን፣ የተባረከውንና ከጌታየ ሥጋና ደም ጋር የተዋሃደውን ደሜንና ኩላሊቴን፥ ካንተ ጥያቄ ላይ እኔም ልጨምርበትና እንዲሁም ዓይኔን በተዋህዶ ሃይማኖቴ በጥምቀትና በቁርባን አንድነት ለሌለውና ለማይመስለኝ ለሱ መሆኑን እያወቅሁ ለመናፍቅና ለአሕዛብ አሳልፌ ልሰጥ አልችልም። ሃይማኖቴ አይፈቅድልኝምና። እኔም እንዲሁ በተዋህዶ ሃይማኖቴ በጥምቀትና በቁርባን ከማይመስለኝ አንድነት ከሌለው መናፍቅና አሕዛብ ደሙንም፣ ኩላሊቱንም፣ ዓይኑንም የሱ መሆኑን እያወቅሁ አልወስድም። ሞቴን እመርጣለሁ እንጅ። እኔም እንኳን ይኸን ከባዱን ነገር ኩላሊቴን፣ ደሜን፣ ዓይኔን ልሰጠውና ልፈጽም ይቅርና ከዚህ የቀለለውንም ነገር እንዳልፈጽም ሃይማኖቴ በብዙ መጽሐፍት ያዘኛል። ይኸ የእንጀራ፣ የልብስና የገንዘብ ምጽዋትና እርዳታ አይደለምና። ""ወደ እናንተ የሚመጣውን ይህንንም ትምህርት (የተዋህዶን) የማያመጣውን ወደ ቤታችሁ አታስገቡት። ሰላምም እንኳ አትበሉት። ሰላም የሚለው በክፉ ሥራው ይተባበረዋልና"" ፪ኛ የዮሐንስ መልእክት ፩፡ ፲__፲፩ ። ምስጢሩ፦ በተዋህዶ ትምህርትና ሃይማኖት የማይኖረውን ሰው (መናፍቁን አሕዛቡን......) በቅዱስ ሥጋውና በክቡር ደሙ የዋጀልኝን ኩላሊቴን፣ ዓይኔን፣ ደሜን ልሰጠው ይቅርና ወደ ቤታችሁ ቢመጣ በቤታችሁ አትቀበሉት። ማለትም፣ ቸር ዋልክ? ቸር አደርክ? ቸር ሰነበትክ? ቸር አለህ? እንኳን አትበሉት ብሎ ያዘኛል። ይህ ማለት ግን መሽቶበት ሊያድር ቢመጣና አስጠጉኝ ቢል፣ ራበኝ አብሉኝ ቢል፣ ጠማኝ አጠጡኝ ቢል፣ በረደኝ አልብሱኝ ቢል፣ ደከመኝ እርዱኝ አሳርፉኝ ቢል ወንበዴ ይግደለው፣ አውሬ ይብላው፣ ረሃብ፣ ጥማትና ብርድ ይጉዳው እንጅ ይህንን አትፈጽሙለት አባሩት ማለት አይደለም። ይህማ እንዳይሆን ምንም እንኳ ጥምቀትና ቁርባን ባይኖረውም በተፈጥሮ የፈጣሪ ገንዘብ የሆነ ሰው ነውና። ግን ግን ምግቡንና መጠጡን፣ ቦታውን፣ ምኝታውንና መብራቱን ለብቻው ለይታችሁ በመስጠት አስተናግዱት እንጅ የሱን የክህደት ኑፋቄ ትምህርት እንዳትሰሙና እንዳትማሩ። በዚህም ዙሪያ አታነጋግሩት፣ ምንም አታውሩት። እሱም ሊያነጋግራችሁና ሊያወራችሁ ቢሞክር ወግድ ዝም በል በሉት። (ዛሬ መናፍቃን እንደሚለፈልፉት ማለት ነው) እናም አስተናግዳችሁ ስታበቁ ወደመጣበት ስደዱት ማለት ነው። ይህ ካልሆነ ግን ክፉ (ኑፋቄ) ቃሉን እየሰማችሁ በክፉ እምነቱና ተግባሩ ትጠመዳላችሁ፣ ትወድቃላችሁ። ስለዚህ አታነጋግሩት ይሉናል ሐዋርያት። ይህን ስል ግን ጻድቅም ይሁን፣ ኃጢአተኛም ይሁን በተዋህዶ ሃይማኖቴ በአርባና በሰማንያ ቀን ጥምቀትና ቁርባን ለሚመስሉኝ ክርስቲያን ቤተሰቦቼ ለሆኑት ሁሉ ግን አካሌ የሆነውን ሁለመናየን ለአካላቸዉ መስጠት እችላለሁ። እኔም ከእነሱ ማንኛውንም አካላቸዉን ለአካሌ መቀበልና መውሰድ እችላለሁ። ከታችም ከዚህ አስለጥቄ በምርጥ ማስረጃ እነግርሃለሁ።ስለዚህ ራሴንና አንተን ወክየ የመለስኩልህ መልስ እንኳን አንተ ሌላውም የገባው ይመስለኛል። ካላበደ በቀር። ከዚህ ውጭ ግን ሰይጣን መቼም ቢሆን ተንኮሉና ክፋቱ ብዙ ስለሆነ በፕሮቴስታንቶችና የነሱ ሰልፈኞች በሚመስሉት በወንጌል ደላላ ሰባኪ ተብየዎች መንፈስና አንደበት እያደረ እኔ ከተናገርኩት ጋር በትርጉም ምስጢር የማይገናኝ ቃል ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ እየጠቃቀሰ እንዳያስታችሁና እንዳያጠፋችሁ ተጠንቀቁ እላለሁ። ___ለምሳሌም፦ ""ስለ ወዳጆቹ ሕይወቱን አሳልፎ የሚሰጥ ሰው ያለ ከሆነ ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር የለም"" የዮሐ ወን ፲፭፥፲፫። ""እርሱ ራሱን ስለ እኛ አሳልፎ ሰጥቷልና፤ እኛም ስለ ባልንጀሮቻችን ራሳችንን አሳልፈን ልንሰጥ ይገባናል"" ፩ኛ ዮሐን መል ፫፥፲፮። ""እኔ ግን እጥፍ ድርብ አወጣለሁ፤ ስለ ሕይወታችሁም ሰውነቴን አሳልፌ እሰጣለሁ"" ፪ኛ ቆሮ ፲፪፥፲፭። ይላሉ ቅዱሳን ሐዋርያት። ስለዚህ ኩላሊትን፣ ደምንና ዓይንንማ ለሰው ቢያወጡና ቢሰጡ ምንድን ነው ድንቁ? ምንድን ነው ስህተቱ? ይህም የሐዋርያት ቃል የሚያዘን እኮ ይህንን እንድንፈጽም ነው እያሉ ያለ ምንም ትምህርታዊ መንገድ እንዳይወስዷችሁ ተጠንቀቁ። እንዲህ የምለው ወልደ-ገብርኤልንና ባልንጀሮቼን ነው እንጅ በጽድቄ ከምሞት ይልቅ በኃጢአቴ ብኖር ይሻለኛል ለሚሉት ምናምንቴ ክርስቲያኖች አይደለም። ስለዚህ እነዚህ ጥቅሶች የተነገሩትና በበለጠ የሚያስረዱት በተዋህዶ ሃይማኖት አንድ ለሆንነዉ ነው እንጅ ስለ መናፍቃንና ስለ አሕዛብ ብለን የአካል መስዋዕትነትን እንድንከፍል አይደለም። መናፍቃንና አሕዛብማ ምንጊዜም ቢሆን በተዋህዶ ሃይማኖታችን ምክንያት አጥፊዎቻችን ናቸዉ። ታዲያ ለአጥፊየ ነው እንዴ አካሌን አሳልፌ የምሰጠው? ከዚህ ላይ ደናቁርት ሁሉ ""ክርስቶስ ለአሕዛብና ለጠላቶቹ አይደል ራሱን አሳልፎ የሰጠ""? እንደምትሉኝ አውቃለሁ። ይህንን ለእኔ እናንተ አትነግሩኝም። እኔ እነግራችኋለሁ እንጅ። ይኸውም! አዎ ለሁሉም ሰጥቷል። የሰጠውም ያምኑበትና ይድኑበት ዘንድ ሲሆን ካላመኑበት፣ ካልተቀበሉትና ከካዱት ግን በሥጋም በነፍስ ለዘላለም ሊያጠፋቸው ነው እንጅ እንዲሁ ዝም ብሎ የሞተላቸው አይደለም። ስለዚህም ነው ሲኦልና ገሐነም የተከፈተውና የተዘጋጀው። ሌላው ነገር፦ የሰዎችን ሰይጣናዊይም ሆነ መንፈሳዊ ሐሳባቸዉን አስቀድሜ ስለማውቅ ""ምን አልባት እንደ አጋጣሚ ታምሜ ሆስፒታል ስሄድና ስመረመር ደምህ አልቋልና ደም ያስፈልግሃል ብባልና በተዋህዶ ሃይማኖት የሚመስለኝና ደም የሚሰጠኝ ክርስቲያን ሰው ቢጠፋና ከሆስፒታሉ በደም ባንክ የተቀመጠ፣ ሆኖም ግን የማን ይሁን የማን (በሃይማኖት የሚመስለኝና የማይመስለኝ) ሰው ደም ይሁን አይሁን ሳላውቅ በሕክምና ባለሙያ ትእዛዝ ተሰጥቼ ሳበቃ እንደ አጋጣሚ ሳላውቅ ከወሰድኩ በኋላ የወሰድኩት ደም ሆነ ዓይን በሃይማኖት የማይመስለኝ ሰው ሆኖ ቢገኝ ማድረግ የምችለው ነገር ምንድን ነው""? ካልከኝ፤ ሳታውቅ የሆነ ነገርማ አላወቅህም አላወቅህም ነው። እሱም ቢሆን መቼስ አውጥተህ አታፈሰውና አትጥለው ነገር ስለሆነ ከንስሐ አባትህ ጋር የምትጨርሱትን ነገር መጨረስ ብቻ ነው። ስልጣኑ በአጠገብህና በቅርብህ ያለው እረኛህ የሆነው የንስሐ አባትህ ብቻ ነው። ከዚህ ውጭ ሌላ ነገር ልነግርህ አልችልም። አለመታደል ሆኖብን እንጅ ቢያውቁትና ቢጠነቀቁማ ""ቄስ ብሂል አነ ውእቱ ክርስቶስ"" ትር፦ ""ቄስ ማለት እኔ ክርክቶስ ነኝ"" ብሎ መስክሮላቸው ነበር። እናማ በንስሐ አባት በኩል የማይፋቅ የኃጢአት አይነት የለምና አይዟችሁ ተረጋጉ አግድማችሁ አትጨናነቁ። ከዚህ በፊት ነግሬአችኋለሁና አሁንም ላስታውሳችሁ። አጉል አላስፈላጊ የሆነ ጭንቀት አዕምሮንና ልቦናን ሰውሮ ለማይመለስ የእብደት ሕመም ያጋልጣልና ተጠንቀቁ። ራሳችንን ከማንኛውም ሥጋዊ ሆነ ነፍሳዊ ጭንቀት ነጻ እናድርግና ከክፉ ሥራ እንሽሽ፣ መልካም ሥራ ብቻ እንሥራ። እውነትን ብቻ እንነጋገር። በል ደህና ሁንልኝ። በተረፈ ግን ሰሞኑን ፔጄን ከፍቸ ሳይ መልስ የሚያስፈልጋቸዉ የተጠየቅሁት ሌሎች ጠያቂዎችንና ጥያቄዎቻቸዉን አግኝቻለሁ። ሆኖም ግን መልእክቱ ስለሚበዛብኝና ለማንበብም እንዳይበዛባችሁ ብየ ለአሁኑ አስቀርቸዋለሁና ይቅርታ አድርጉልኝ። በሚለጥቀው መልእክቴ እጽፍላችኋለሁና በትዕግስት መጠበቅ ነው። ደግሞም ጥያቄአችሁ መልስ ለማግኘት የሚያስቸኩል አለመሆኑን ስለማውቅ ነው። እናንተየዋ! ገና በስደት ላይ ሆኜ ቢሮ ሳልይዝ የሚጎርፍልኝ ማንኛውም ጥያቄ፣ ልመና፣ ተማጽኖ፣ መልእክት ሁሉ ሳየው እንዲህ የበዛና የሚያሳዝን ሆኖ ሳየው ቢሮ ብይዝና ብገባማ የሰውን ሁሉ ችግር በአካል ስሰማውና ሳየው ከኀዘኔ ብዛት የተነሳ እንዲያው የማስተናግድ ሳይሆን ቢሮውንም፣ ሥራውንም፣ ሀገሩንም፣ ሰዉንም ሁሉ ትቸው ብር ብየ ባንዱ ዋሻ ወይም ገዳም የምቀመጥ ነው የሚመስለኝ። እናንተ ሕዝብን በእውነትና ያለምንም አድልዎና እንግልት ልታገለግሉ ከፈጣሪ ሆነ በሰው የተሾማችሁ የቤተ-መንግሥትና የቤተ-ክህነት ባለሥልጣናት ሁሉ በእውነት መንገድ ባለማገልገላችሁና ሕዝቡን ሁሉ በማስለቀሳችሁ ወዮላችሁ! ምኑ ይውጣችሁ ይሆን? አዘንኩላችሁ። እንዲያው ግን ወንበር ስትይዙ በአካላችሁ ዙሪያ አብሮአችሁ የሚቀመጠው ገንዘብን፣ ሥልጣንን፣ አምባ-ገነንነትን፣ ጭካኔን፣ ትዕቢትን፣ ተመጻዳቂነትን፣ራስ-ወዳድነትን፣ ዋልጌነትን.......የሚያሳያችሁና የሚያስፈጽማችሁ ጋኔል ነው? ወይስ የራሳችሁ የአዕምሮና የልቦና መንፈስ ነው? ወዮ ለእናንተ!!! በሉ ጤነኛ ክርስቲያን ወዳጆቼ ሁሉ ደህና ሁኑልኝ። የመጨረሻ መልእክት:- "ለዘመድ-ኩን በቀለ" በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ። የዛሬውን የዘመድ-ኩን ትምህርታዊ መልእክቴን ደግሞ እስቲ በቀላል የአማርኛ ኅብረ-ቃል በሆነው ሰምና ወርቅ ልጀምር። ቃሏንም አሁን በመግቢያየ ላይ ላስቀድማትና ኋላም በመዝጊያየ ላይ እደግማታለሁ። መተርጎም ለሚችል ምስጢሩ ልብ ይነካልና። ማር ቀምሸ አላውቅም እኔ ወገናችሁ፣ ባለ ቀፎ ሁሉ ልለምናችሁ፣ ኧረ ክርስቲያኖች ተማሩ እባካችሁ። በሉ በሦስት ትርጉም ነው የምትፈቱትና አስተዉሉ። ሁለት ልጨምራችሁ። ሁሉም በጣም ቀላል ናቸዉ። አስተምር ተብየ ሀገርን ስዞር፣ ብፈልግ ብፈልግ አጣሁ የሚማር። ስማኝ ልንገርህ አትስነፍ፣ ተው እየተማርክ እለፍ። ይድረስ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ወንድሜ ለሆንከው ለዘመድ-ኩን በቀለ። በቅድሚያ ከነ ባለቤትህና ከነ ልጆችህ እንዲሁም ከነ-ረዳትህ ፍቅርና ሰላም እንዲሆንላችሁ ክርስቲያናዊ ምኞቴ ነው። ወንድሜ ዘመድኩን ሆይ! ምንም እንኳ ለሰዎች ሐዋርያ ባልሆንም በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ ግን ሐዋርያ የሆንኩ ይመስለኛል። ሙሉ ለሙሉ ነኝ ለማለት ግን እውቀቱም፣ ብቃቱም የሌለኝ ደንቆሮና ዕውር ነኝና። በተጨማሪም በሰዎች ዘንድ ለሰዎች እውነተኛ ባልሆንም በእግዚአብሔር ለእግዚአብሔር ግን እውነተኛ ነኝና በደካማ ሥጋየ፣ በደንቆሮ አዕምሮየ፣ በዕውር ልቦናየ እንደ ቸርነቱና እንደ አቅሜ አመሰግነዋለሁ። ስለዚህ ወንድሜ ሆይ! እንደ ሐዋርያነቴና እንደ እውነተኛነቴ አሁን የምነግርህ ከእንግዲህ ወዲያ ስለ "ነጭ-ነጯን" ቃልህ ምንም ብትል ምን ለሦስተኛ ጊዜ "በላ ልበልሃ፣ እሰጥ-አገባ" የሆነ የማይሆን ሙግትና ክርክር አልጽፍልህም። ሁለተኛና የመጨረሻ የሆነውን ደብዳቤየን ይኸው ልኬልሃለሁ። ስለዚህ ከልብህና ከአዕምሮህ አውቀኸውና አምነህበት መቀበልና አለመቀበል፣ የፈቃደኛነትና የእምቢተኝነት መብቱ ያንተ ነው እንጅ የእኔ አይደለም። በተጨማሪም የፌስ-ቡክና የዩቲዩብ ኅብረተኛህ የሆነው ተከታይህም ሆነ አድማጭህ ሁሉ በእኔና ባንተ ውይይት ላይ ምንም አይነት የጣልቃ-ገብነት መብት የለውም። ምክንያቱም ቃሉን እነሱ አልሰጡህምና። ስለዚህ እኔ ንግግሬ ካንተ ጋር ነው እንጅ ከአድማጭህ፣ ከተመልካችህና ከተከታይህ ጋር አይደለም እልሃለሁ። ለአሁኑና እስከ መጨረሻው ባለው መልእክቴ ግን በድንቁርናየ ልንገርህና አድምጠኝ ብየህ ከሆነና በዕውርነቴ ልምራህ ተከተለኝ ብየህ ከሆነ ተሳስቻለሁና ለስህተቴ ከባድ ይቅርታ እጠይቃለሁ። በል እንግዲህ መልእክቴን ሁሉ በደንብ እየፈተፈትክ እየበላህ ጨርስ። ልተወውና ላስቀረው የማልችለው የሚገርም መልእክት። ለዘመድ-ኩን በቀለ። ""ተምዑ ወኢተአብሱ"" ትር፦ ተቆጡ፥ ነገር ግን አትበድሉ። ወንድሜ ዘመድኩን ሆይ፦ ባለፈው ስለጻፍኩልህ የእርምት ቃል ያደረከውን አጭር ንግግርና የሰጠኸውን አጭር መልስ ሥራየ ብየ ሁለቴም ሰምቸሃለሁ። እናም ወደሰጠኸው መልስ ከመግባቴ በፊት ከመልስህ በፊትም ሆነ በኋላ ካስተላለፍከው ንግግርህ ላይ ፭ ፍሬ ነገሮችን አግኝቸብሃለሁ። እኔና መሰሎቼ የፈጣሪ መልእክተኞች፣ የሐዋርያት ልጆች የሆንነው ሥራችንና እውቀታችን ማንኛውንም ነገር ሁሉ እንደ ደንቆሮዎቹ ዝም ብለን መስማትና አለማስተዋል ከዛም አፋችን እንዳመጣው መናገርና ፈጣሪንም ሰውንም ማስቀየምና ማሳዘን ሳይሆን ማዳመጥ፣ ማስተዋል፣ ማሰብ፣ ማገናዘብ፣ መጨረሻም መናገር ወይም ዝም ማለት ነው። በዚህ መሠረት ከንግግርህ ላይ ያገኘሁልህ ፭ ነገሮች የሚከተሉት ናቸውና አንባቢ ሁሉ እስቲ በደንብ አስተዉሉ። ፩ኛ አክብሮት፣ ፪ኛ ትህትና፣ ፫ኛ እውነት፣ ፬ኛ ፈቃደኛነት፣ ፭ኛ ፍጥነት ናቸዉ። እነዚህን በጣም ባጭሩ ልተርጉምልህ። _____አክብሮት፦ ምንም እንኳ እኔ ለራሴ ሰው ሳይሆን መድኃኒዓለም፣ እናቱ ድንግል ማርያምና ቅዱሳን በሚያዉቁት በተአምር የማልወደውና የማልፈቅደው መሆኑን የምንጊዜም የልብ አገልጋዮቼ ሁሉ የሚያዉቁት ቢሆንም አክብሮትን ሰጥተኸኛልና አመሰግንሃለሁ። ግን ግን ከልብህ ያድርግልህ። ደግሞም ለኔ እንዳደረከው ሁሉ ለሌሎችም ለማድረግ መሞከር አለብህ። ____ትህትና፦ ራስህን (መንፈስህን) ስለኔ ዝቅ አድርገህ በበታችነት መንፈስ ሆነህ መናገርህ ነው። እናም ከልብህ ይሁን፣ ግፋበት ያስፈጽምህ። _____እውነት፦ የሰየምከውን ቃል ከሊቃውንት እንዳልጠየቅህ፣ እንዳላማከርክና ያንተ የራስህ ፍልስፍና፣ ምሳሌና ትርጉም እንደሆነ ሳትዋሽ መናገርህ ነው። _____ፈቃደኛነት፦ የሰየምኩት፣ የመሰልኩትና የተረጎምኩት ቃል ስህተት ከሆነና ካላስፈለገ፣ ካልፈቀዱልኝ ከአባቶቼ ቃል አልወጣም አነሳውና የሚሉኝን አደርጋለሁ፣ እፈጽማለሁ፣ እንዲያውም ኤልያስም ተዘጋጅ (ለመቀየር) ማለትህ ነው። _____ፍጥነት፦ መልእክቴ ቅዳሜ ከሰአት በኋላ ደርሶህና አይተኸው በሰይጣናዊ የድንቁርና ትዕቢት ልትሞላና ጨርሰህ በማፈን ልታስቀረው ይቅርና ሳትውል ሳታድር ዕሁድ ማታ በፍጥነት መልስ መስጠትህ ነው። እንግዲህ ከሊቃውንት ጋር ስለኖርኩና እነሱንም ስላገለገልኩና የሚሉኝን ሁሉ ስለሰማሁ የታደልኩትን ታድያለሁና እኔም ላንተ ኢምንቷን ላድልህ ብየ ነው። እናም ስለመልስህ በጣም አመሰግናለሁ። ለወደፊቱ ግፋበት፣ በርታበት ነው የምልህ። በነገራችን ላይ ስለሰጠኸኝ መልስ የሰማህ እውነተኛው ክርስቲያን ሁሉ ስለ ቃልህ አመስግኖሃል። የዲያብሎስ አሻሮ የሆነውን የስም ክርስቲያን ማለቴ አይደለም። ሌላ ነገር ደግሞ በንግግርህ ላይ ጥፋትም ሆነ ልማት ይኑርም አይኑርም እግዚአብሔር ከፈቀደ ሌሎች አዋቂዎችና የሚቀርቡህ አባቶች ካሉ በውስጥ መስመርህ ለራስህ ብቻ እንዲጽፉልህ እኔ አሳስባቸዋለሁ። ከዚህ ላይ ግን አጥብቄ የማስጠነቅቅህ ነገር ይህን ስላልኩ ማንም ሰው አምኃ ኢየሱስ በነገረህ መሠረት ነው በውስጥ መስመርህ የጻፍንልህ። አባቶች ነን፣ ሊቃውንቶች ነን፣ እሱ ጻፉለት ብሎን ነው ቢሉህና አምነህ ተቀብለህ መልስ ብትሰጥ ከደምህ ንጹህ ነኝ። አስቀድመህ በሚዲያህ ባንተ ስም እንዲህ እንዲህ ተብያለሁ እውነት ካንተና ካንተ ሰዎች ነው ወይ? ብለህ በአደባባይ መጠየቅና መናገር አለብህ። በኔ ስም ብዙ ሰይጣናዊ ነገር የሚነግዱ መኖራቸውን አውቃለሁና። ____በል እንግዲህ ወደ ዋናው መልእክቴ እየወሰድኩህ ነውና በደንብ ተከተለኝ። መንገዴም አድካሚና ጉዳት፣ ተራራና ቁልቁለት፣ እንቅፋትና ሠርዶ የሌለበት ቀና ነውና አይዞህ። ____ነጭ ነጯን የሚለውን የመሰልክበትንና የተረጎምክበትን መልእክት ሰምቸሃለሁ። ምሳሌውና ትርጉሙ ጥሩ ነበር። ሆኖም ግን ለሱ አልሆነምና አይሆንም እንጅ። እናማ አሁንም ደግሜ እልሃለሁ! ምሳሌህና ትርጉምህ ለሌላ ትርጉም እንጅ ለእውነት በፍጹም አይሆንም። ምሳሌህ ""ምሳሌ ዘየሐጽጽ ወኢይመስል"" ነው የሆነብህ። ትር፦ ጉድለት ያለበትና የማይመስል የማይሆን ነው። ምክንያቱን አሁን ለመዘርዘር አልፈቅድም። ራሱን የቻለ ትምህርት ነውና ያለው። ስለዚህ አይሆንም አይሆንም ነው። አይ ዝርዝር መልስ ካልሰጠኸኝ አልቀይርም የምትለኝ ከሆነም መብትህ ነው። የሚያሳዝነኝ ግን አንተም ሆንክ አድማጭህና ተቀባይህ ሁሉ በተሳሳተ የቋንቋ አባባልና አተረጓጎም ስትወድቁ ነው። እናም ከኔ የተለየ እውነታ የምታገኝ ከሆነ ወደሌሎች ሃይማኖታዊ ሊቃውንቶች ሂድና ጠይቅ። ባይገርምህ ብታገኛቸዉና ብትጠይቃቸዉ ቃልህን ምንም ችግር የለበትም፣ ይሁን ጥሩ ነው ብለዉ በቁምህ ቀልደውብህ እንደሚመልሱህ መቶ በመቶ አምናለሁ። ስለ ሊቃውንት ጠባይ ምንነት ጠንቅቄ አውቃለሁና። የሚያናግሩትንና የሚነግሩትን ሰው ምንነት ያውቃሉና። አንድ ነገር ልንገርህማ፦ ያኔ ጎንደር ላይ ሳስተምር የካቶሊክ እምነት ያለው ሰው ያገባች ባለ ትዳር ሴት በሕዝብ ፊት በአደባባይ ስለሁኔታው ጠየቀችኝ። እኔም እውነታውን ትምህርት ወዲያውኑ ከዛው መለስኩላት። ሆኖም ግን መልሴ ሞት ሆኖባት አገኘችውና እሷን የሚያስደስት ሌላ መልስ ለማግኘት ብላ ""ይግባኝ"" ለማለት ወደ ሊቁ የጎንደር ጳጳስ ወደነበሩትና በወያኔ ዘመን ሰማዕት ወደሆኑት ወደ ብፁዕ አቡነ እንድርያስ ሄደችና ከኔ ጋር የሆነችውን ሁሉ በዝርዝር ነገረቻቸዉ። እሳቸውም ሰሟትና ስትጨርስ ምን እንዳሏት ታውቃለህ?? ""ታዲያ አምኃ ኢየሱስ ከነገረሽ ሌላ እኔ ምን ብየ እንድነግርሽ ነው ወደኔ የመጣሽ? ወይስ እኔን ሌላ ሃይማኖትና ሌላ ትምህርት አለው ወደርሱ ሂጅ ተብለሻል? ሲሏት መልሳ ታዲያ ምን ልሁን? ስትላቸው ባልሽን ወይም ሃይማኖትሽን መምረጥ ነዋ"" ብለዉ እየሳቁና እየተገረሙ በብዙኃኑ ሊቃውንት ፊት ቁርጧን ነግረዉ አሰናበቷት እልሃለሁ። ይህ ምስጢር ለሁላችሁም ትልቅ ትምህርት መሆኑን እወቁ። እናም ወንድሜ ሆይ! ስላንተ ምሳሌና ትርጉም ለመዘርዘር አሁን ጊዜ የለኝም። ይህንንም የጻፍኩልህ ሌሎቹ ሰዎች የቋንቋን የአባባል ስህተት እንዳይማሩ ብየ ነው እንጅ አልጽፍልህም ነበር። አንዴ አስረግጨ ተናግሬአለሁና። ያኔ ስናገር ደግሞ ለቃልህ የራስህ ምክንያት እንደሚኖርህ ለኔ የተሰወረና የማይታወቅ አልነበረም። ነገር ግን እንደማይሆን ስለማውቅ ነው ዘግቼ የነገርኩህ። ለማንኛውም ግን ስለ ለጠፍከው ቃልህ ከኔ በተጨማሪ አስደናቂውን መልስ ዛሬ ከታች ታገኘዋለህ። ተአምር ነው። እግዚአብሔር ከሰማነውና ከተቀበልነው ስህተታችንን በብዙ መንገድ ያስተምረናል፥ ያሳውቀናል። እናም አሁን የምመክርህ በሱ ቃልህ ብዙ ጊዜ ሳትርቅና አንተም ሆንክ አድማጮችህ መጥፎ ልምድ ሳይሆንባችሁ የምትለውን ምርጫ ልስጥህና፦ ወይ ""እውነት እውነቷን""፣ ወይም ""ሞትና ሕይወት""፣ (እውነትን ለሚናገራትና ለሚቀበላት የዘላለም ሕይወት ናትና። ለማይናገራትና ለማይቀበላት ደግሞ የዘላለም ሞት ናትና)። ወይም ""መራራ መራራዋን""፣ ወይም ""እውነት በጨለማ""፣ ወይም ""የምድር ውስጥ ማእድን"" ከእነዚህ መካከል አንዱን መርጠህ ብትሰይማት እንዴት ጥሩ ነበር። በዛውም ላይ ትርጉማቸዉ ሲተነተን ጣፋጭ የትምህርት እውቀት ነው ያላቸው። ሌላም ሌላም ከዚህ የበለጠ ካገኘህ የወደድከውንና የፈቀድከውን መሰየም ትችላለህ። ቀድመህ ግን መጠየቅና ማማከር አለብህ። ያሁኑን ስህተትህን እንዳትደግመው አደራህን። ___ወንድሜ ሆይ! ስለ ቋንቋ አበላሾች አንድ ተጨማሪ እውነታ ነገር ልንገርህ። የምናገረው ቃል ግን በሱ ስም ለሁላችሁም ትልቅ ትምህርትና እውቀት እንዲሆናችሁ ብየ መሆኑን እወቁልኝ። ____እናማ፦ ባሕር-ዳር ወህኒ-ቤት በእስር ላይ ሳለሁ ነው። በኢትዮጵያ ሬዲዮ ጣቢያ ብዙ አይነት ማስታወቂያወች ሲነገሩ በጀሮየ እሰማለሁ። ስሰማቸው ከነበረውና እጅግ በጣም ሳዝንበት የነበረው ማስታወቂያ ደግሞ ""ሕይወት ትረስት ኮንዶም ለመከላከል ብቃትና ለእርካታ"" የሚለው ነበር። በዚህን ጊዜ የሚገርማችሁ ነገር ሰዉ ሁሉ መስማቱን ብቻ እንጅ ውስጣዊ ትርጉሙ መጥፎ ይሁን ጥሩ ምን አይነት የሞት ቃል እንደሆነ አያስተውለውም ነበር። እኔ ግን እሰማና ብቻየን ሆኜ አይ ኢትዮጵያ! አይ ክርስቲያን! አይ ሰው! አይ ቋንቋ! እንዲህ ሆናችሁ ትቀሩ? እያልኩ እያዘንኩና እየቆዘምኩ እንዲያው ግን ""ተዉ፣ አስተካክሉ፣ ይህን ቃል አንሱ፣ ትውልዱን ሁሉ የማያውቀውንና የማያስበውን የባሰ እንዲያስበውና እንዲያውቀው እየገፋፋችሁትና እያበላሻችሁት ነው የሚል የቋንቋ ምሁርና የሃይማኖት ምሁር የሆነ አንድም ሰው ይጥፋ? እል ነበር። ወይንስ የፈለገው ቋንቋና ሰው ቢበላሽ ምን አገባኝ ነው? እል ነበር። እውነት ነው የምላችሁ ፈጣሪ ስለ ሰውም ድኅነት፣ ስለ ቋንቋውም ክብር ብሎ ሰማኝ መሰል ብዙ ጊዜ ሳይቆይ ያ ጸያፍ ቃል ተነሳና ተቀይሮ ስሰማው በጣም ገረመኝ። ያዘንኩበትና የቆዘምኩበት ቃል የቱ መሰላችሁ? ""ለእርካታ"" የሚለው ነበር። ኋላ ይህ ተነሳና ""ሕይወት ትረስት ኮንዶም ለመከላከል ብቃት"" የሚል ሆነ እላችኋለሁ። ምንም እንኳ ይህም ያልተነሳውና ያልቀረው ቃል አስፈላጊ ማስታወቂያ ባይሆንም ከዛኛው ቃል ይሻላል ማለቴ ነው እንጅ ላደለውማ ""የምን ኮንዶም ነው?"" ያለው እድል ተጠብቆ መኖር ወይንም አግብቶ መኖር ነው። ይህንን ስል ደግሞ እየፈረድኩባችሁ አይደለም። እንዲያው ብታስቡበትና ብትሞክሩት ማለቴ ነው እንጅ። ዋናው ነገር አያድርስ ነው። የሚገርማችሁ ነገር አስተዋዋቂው ያ ቃል ሳይነሳና ሲያስተዋውቅ ንግግሩን በጣም ያሟሙቀው ነበር። ኋላስ ያች ቃል ስትነሳና የቀረውን ሲናገር ባትሪው የሞተበት ቴፕና ሬዲዮ መስሎ አረፈው። እስቲ አሁን ደግሞ ይህንን ምክንያት አድርጌ አንድ ቀላል ሰምና ወርቅ ኅብረ-ቃል ልስጣችሁና ምስጢሩን አግኝታችሁ እዘኑ፣ ተክዙ። ዲያብሎስ ከምሽቱ ተጣልቶ ሲፋታ፣ ለሷ የደረሳት ቀሚስና ኩታ፣ ይህ ለሷ ቢደርሳት ምን ያሳዝንሃል? ብዙ ልብ-አልባ አለህ ላንተም ይደርስሃል። ""አስገራሚው መልእክት"" ___በል ወንድሜ ሆይ! አስገራሚ ወደሆነው ወዳንተ መልእክቴ ልምራህ። ይህ መልእክት ለምናምንቴ ቃዣታሞች ለሆኑት ክርስቲያን ተብየዎች ቅዠት ነው። ለባለ አዕምሮዎች ደግሞ እውነት ነው። ____በተለምዶ የዕለትና የቀን አቆጣጠር ሐሙስ ለዓርብ (ለስቅለት) ሃያ አንድ ለሃያ ሁለት፣ በተፈጥሮና በትክክለኛው የሕግ አቆጣጠር ግን በዕለተ ዓርብ በሃያ ሁለት ሌሊት ስምንት ሰአት ተኩል ላይ ከድካም እንቅልፌ ነቃሁና የምሠራውን ሥራየን ሠርቸ ስጨርስ ደከም-ከም አለኝና ተመልሸ ፲፩ ሰአት ተኩል ላይ ተኛሁ። ከዛም በሕልሜ ምን አየሁ መሰለህ? እኔ ወደ አንድ ሱቅ እቃ ለመግዛት እገባለሁ። ስገባና ስቆም ከዛ ሱቅ ውስጥ አንተ አለህ። አንተ የቆምከው እንደ ሻጮች በባንኮኒው ውስጥ ነው። እኔ ደግሞ የቆምኩት እንደ ገዥዎች (ሸማቾች) ከባንኮኒው ውጭ ነው። እንዲህ ሆነን እኔና አንተ ገና ፊት-ለፊት እንደተያየን እኔም ምን እንደምፈልግ ሳልነግርህ፣ አንተም ምን እንደምፈልግ ሳትጠይቀኝ ወዲያውኑ ያንተ የሥጋ ወላጅ አባትህ ይመጡና ከሱቅህ ገብተዉ ከእኔ በስተቀኝ ቆመዉ የቲማቲም ልጣጭ ይኸውልህ እንካ ያ የለጠፍከው ቃል ነው ብለዉ ወዳንተ ይጥሉልህና ወጥተዉ ይሄዳሉ። እኔም እቃ ካንተ እገዛዛና ከሱቁ ወጥቸ ስራመድ አባትህ ከውጭ ሜዳ ላይ ተቀምጠዉ ፊታቸውን ወደ ምሥራቅ አዙረዉ ፀሐይ ይሞቃሉ። የሚሞቁት ፀሐይ ደግሞ የምሽት መግቢያ (የከሰአት በኋላ) የሆነችውን ነው። እኔም ካንተ ጋር ከሱቁ የተገናኘነው በዛው በመሸው የፀሐይ ብርሃን ሰአት ላይ ነው። (ይኸ ሁሉ ነገር ይግባህ፣ ትልቅ ትርጉም አለው። ሊቃውንት ይተርጉሙልህ) እናም እኔ ከሱቅህ ወጥቸ ስራመድ አባትክን አየኋቸውና አባባ! እርስዎ የዘመድ ኩን አባት ነዎት እንዴ? ስላቸው በጥርሳቸዉ ብቻ በፈገግታ ሳቅ ሳ ቅ እያሉ አዎ ልጄ ይሉኛል። ከዛም እኔ መልሸ ለልጅዎ መልእክት ጽፌለታለሁ። አሁንም እንደገና ይኸው መልእክት ልልክለት ነው ስላቸው በፈገግታ ሳቅ ጥሩ ነው ይሉኝና ዝም ይላሉ። እኔም ወደቤቴ ሄጀ ስገባ ታናሽ እህቴን (የአጎቴን ልጅ) አገኛትና የገዛሁትን እቃ ከወለሉ ላይ ሳስቀምጠው እህቴ አንተ! ይኸ ሁሉ እቃ ምንድን ነው? ስትለኝ ገዝቸው ነው ስላት ለምንህ? ስትለኝ ለዘመድ-ኩን ልልክለት ነው ስላት በመገረም ኃዘንና በፈገግታ ሳቅ ሆና አይ አንተ! በቃ ለሁሉም ሰው እንዳሰብክና እንደላክ ልትኖር ነው? እያለችኝ ብንን አልኩ እልሃለሁ። እንግዲህ ከዚህ በላይ ምን አይነት ትምህርት እንደምትፈልግ አላውቅልህም። አንተም እንደ ደናቁርትና እንደ ሰይጣኒስቶች የወንጌል ደላላዎችና አለቅላቂ ተከታዮቻቸዉ ቃዣታም! ምን ይቃዣል? ደሞ በቅዠት ሕልም ልመን? ካላልከኝ በቀር። ለማንኛውም ከእኔ ከቃዣታሙ ሕልም ብዙ የእውነታ ትርጉም ታገኝበታለህና ሊቃውንት አባቶችን ጠይቅ። ይህንን ሁሉ ጉድ ያመጣችውና እኔንም አፍ ያስከፈተችኝ ያለቦታው ነጭ-ነጯን ያልካት ቃል ናትና በፍጥነት አስተካክል። በተለይ ደግሞ አባትህ በኔ ምስክርነትና ለኔ በማገዝ፣ አንተንም ለማስተካከል ብለው ከፊትህ ላይ የጣሉልህን የቲማቲም ልጣጭ በደንብ አስብ። እስቲ ልጠይቅህ? የቲማቲም ልጣጭ ወደ ቆሻሻ ይጣላል እንጅ ሌላ ምን ጥቅም አለው? ከዋናው ፍሬው ተልጦ የተወገደ ነውና። ሕልሙ በሙሉ ትርጉም ያለው ነውና አስተውለው። በተረፈ ደግሞ ኤልያስ የሚባለው ረዳትህ ቀድሞ የተቃወመህ ትርጉሙና ምስጢሩ ስህተት መሆኑን ገብቶትና አውቆት ከሆነ በጣም ጎበዝ ብለህ አመስግንልኝ። ሳያውቀውና ሳይገባው ከሆነም የተቃወመህ መንፈስ ቅዱስ አስቀድሞ አናግሮታልና አመስግንልኝ። ከዚህ ውጭ ጨው ለራስህ ስትል ጣፍጥ ካለበለዚያ........ነውና መልካሙን ነገር መርምር። ሌላው ተጨማሪ አጥብቄ የምነግርህ ነገር፦ ሀ፦ አድማጭ ተከታይህ የሆነው ሁሉ ነጭ ነጯን ስላለ እነሱን ለማስደሰት ብለህ የምትቀበላቸው ከሆነ የባሰ በጣም ትሳሳታለህ። እነሱ ምኑን አውቀዉት ነው? የክርስትና ስማቸዉን እንኳ ትርጉሙን የማይጠይቁና የማያዉቁ። ተናግረህ ተናግረህ ስታበቃ እስቲ ምን አልኩ? ብትላቸውና እስቲ ከተናገርኩት ውስጥ ንገሩኝ ብትላቸው ከሁለት ሰአት ንግግርህ ላይ የአሥር ሴኮንድ ቃል መናገር አይችሉም። ስለማውቅ ነው። የዘመኑ ክርስቲያን ሁሉ ማለት ይቻላል በማዳመጥ፣ በማሰብ፣ በማስተዋል፣ በማገናዘብ ሳይሆን በስሜት ብቻ የሚነዳ ነውና። አንተየዋ! ይህ ሕዝብ እኮ ራስ ደጀን ተራራን ከባዕዳ ፈረንጅ ዳሸን የሚል ትርጉም የለሽ ቃል ተቀብሎ ዳሸን ብሎ ለምዶ የቀረ ደንቆሮ ኢትዮጵያዊ ነው። ከፈለክ ደግሞ ያልኩህን ሁሉ ለአድማጭህ ሁሉ አንብብለትና ሰምቶ ወይ ይዳን፣ ወይ ይበድ። ማበድስ አብዷል። ካበደም ሠላሳ ዓመት እያለፈው ነው። ግን ተወው አታንብለት። ራሱ እያነበበ ይረዳ። በጥቅሉ እኔ ንግግሬ ካንተ ጋር ነው እንጅ ማንነቴን ከማያውቀኝ አድማጭህም ሆነ ተከታይህ ከሆነው ጋር አይደለምና አስተውል። ለ፦ ቃሉን እኔ ከሰጠሁህና ወይንም አንተ ሆንክ ሌሎች ሊቃውንት ከመረጡልህ ደግሞ ""ሐቅ ሐቋን"" የሚለውን ግን በምንም ተአምር እንዳትመርጠውና እንዳትለጥፈው አደራ። ምክንያቱም ሐቅ ራሷ ከእውነት የምትበልጥ የእውነት ወላጅ እናት ናት እንጅ እህት ወይም ጓደኛ፣ ወይም ባልንጀራ አይደለችምና አስተውል። ሐቅን ከእውነት በላይ ለመናገር ለሁላችንም የምትከብድ ናትና። ባጭሩ ልተርጉምልህ፦ እውነት ምንጊዜም ጨለማ ብትሆንም ጨለማነቷ ግን በሜዳ ላይ የሚሄዱባት ጨለማ ሆና ነገር ግን የሰማይ ቦቀታ ብርሃን ያለባትና የሚታይባት ጨለማ ስትሆን ሐቅ ግን በጥቅጥቅ ጫካ ላይ የሚሄዱባትና ምንም አይነት ቦቀታ የማይታይባት ድቅድቅ ጨለማ ናትና። በትርጓሜ ትምህርት ቤት ስንማር ሊቃውንት መምህራኖቻችን ኃጢአትን የሚመስሉልንና የሚተረጉሙልን በሜዳ ጨለማ ሳይሆን በገደልና በዛፍ ላይ ባለ ጨለማ ነው። ምስጢሩም ጨለማ ከጨለማነቱ በላይ የሚከብደውና ለማየት የሚያስቸግረው እንዲሁም የሚያስፈራው የገደል ጥላና የዛፍ (የጫካ) ጥላ ሲያርፍበት ነው። ይህንንም እኛ ምስክሮች ነን። ሁሌም በሌሊት ጨለማ ስለምንሄድ የጨለማውን አይነት ለይተን እናውቀዋለንና። እናም ከተግባር ኃጢአት ላይ የሃይማኖት ክህደት፣ ከሃይማኖት ክህደት ላይ የተግባር ኃጢአት ስንጨምርበት በሥጋም በነፍስም ፍዳው በጣም ከባድ ነው ማለት ነው። መቸ ይሆን በመድረክ የምንማማረው?? እናም ወንድሜ ሆይ! የሐቅ ትርጓሜ ምስጢሯ በጣም ረቂቅ ነውና አስተውል። በንግግር ላይ ሁላችንም ብንሆን ሐቅ ሐቋን እናውራ የምንባባለው እንዲያው በዘ-ልማድ ነው እንጅ ፈጽመን አንመጥናትም። እናም እንኳን ሐቅ እውነትም በጣም ከብዳናለች። ስለዚህ ሐቁ ቀርቶብን እውነቱን በተናገርነ። ኧረ እውነቱ ቀርቶብን ሐሰቱንም በልክ ባደረግነው። ከሐሰት አልፈን ተርፈን ፍጹም ቅጥፈት ነው የምንናገረው። ኧረ ተዉኝ!!! ሐ፦ እንግዲህ በአዕምሮህና በልቦናህ መልእክቴን ተቀብለህ ከፈጸምከው መልካም፣ ሸጋ፣ ደግ፣ እሰየው፣ ወሸኔ ትባላለህ። ይህንንም የምታደርገው ለኔ ብለህ ሳይሆን ለቋንቋው ትርጉምና ጤናማነት፣ እንዲሁም ለራስህ እውቀት ብለህ ነው። ካልፈጸምከው ግን መልእክትህን ሁሉ በአዋቂወች ዘንድ ገደል እንዳስገባሃው፣ እያስገባሃውም እንደሆነ፣ እንደምታስገባውም አስረግጨ ነገርኩህ። ወንድሜ ሆይ፦ ሊቃውንት አባቶች ምን ይላሉ መሰለህ? ""የሚጠቅማችሁ እስከሆነ ድረስ እንኳን ይኸን ቀላሉን ነገር ይቅርና ከባዱንም ነገር ቢሆን እንኳ ፈጽሙት ብንላችሁ ባደረጋችሁት ነበር"" ይላሉ። አዎ! እውነት ነው። ምን እያልኩህ እንደሆነ ገባህ? የሰውንና የሕዝቡን ነገር እኔ አሁን ለመናገር እተወዋለሁ። ምክንያቱም እኔ አምኃ ኢየሱስ ሰውና ሕዝብ የምለው እውነቱን ልንገራችሁና ከጠረጋ በኋላ ተርፎ የሚቀረውን ነው እንጅ አሁን ያለውን አይደለም። ይህንም ያልኩበት ምክንያት እውነተኞች ንጉሥ ወነገሥታትና ጳጳስ ወጳጳሳት ስለሚመጡ ያኔ በመልካም ትምህርትና በመልካም አስተዳደር ልክ ስለሚያስገቡት ነው እንጅ ያኔም ቢሆን ምናምንቴ የሆነ ሰው ጨርሶ ይጠፋል አይኖርም ማለት አይደለም። ተርፈዉ ለትልቅ ሥጋዊ ቅጣትና ለንስሐ፥ እንዲሁም ለሁለት ዓለም ቅጣት የሚጠበቁ አንዳንድ ሰዎች አሉ። ስለሆነም አሁን ከጠረጋ በፊት ያለው ሰውና ሕዝብ ንጹሕ ሣር መሰል ዋጅማ ነው እንጅ ጤናማ ሣር ነው አልለውም። ይህ ዋጅማ የሚባለውን አንተ ገጠር ስላልተወለድክና እረኝነትን ስለማታውቅ ላታውቀው ትችላለህ። እናም ከብቶች ዋጅማው ጤናማ ሣር ስለሚመስላቸውና በዛውም ላይ ክፋቱ ደግሞ ከጤናማው ሣር በላይ ስለሚጥማቸዉ በደንብ ይበሉታል። ሆኖም ግን ከጣምናው ጋር መርዛም ስለሆነ ቶሎ ብለዉ ማክሸፊያውን መድኃኒት ካላጠጧቸው ሆዳቸውን ነፍቶ በሰአታት ውስጥ ወይም ውሎ አድሮ ይገላቸዋል እልሃለሁ። እናም ይህ አሁን ከጠረጋ በፊት ያለው ሰውና ሕዝብ በአምኃ ኢየሱስ እይታ፣ እውቀትና እምነት ላይ-ላዩ ጤናማ ሰው የመሰለ ነገር ግን ውስጡ መርዛም የሆነ ገዳይ ዋጅማ ነው። የምልህ ግን ይገባሃል? አድማጭህና የፌስ-ቡክ ሆነ የዩቲዩብ ተከታይህ የሆነው ሁሉ ያለምንም ትምህርቱና እውቀቱ አሁን በለመደው ነጭ-ነጯን ይሁን ስላለህ አንተ ልትቀበለውና በአጉል ነገር ልታስደስተው ተገቢ አይደለም ብየ አሁንም በድጋሚ ነው የነገርኩህ። ካለበለዚያ ግን አንተም ሆንክ አድማጭህና የድህረ-ገጽ ኅብረትህ ሁሉ የያዛችሁት ጤናማ ቃል ሳይሆን ጤናማ መሰል ገዳይ የሆነ ብላሽ የዋጅማ ቃል ነው እልሃለሁ። መምህርህ ሐዋርያው ጳውሎስ ምን ነበር ያለው? ""ንባብ ይቀትል ወትርጓሜሰ የሐዩ"" ትር፦ ንባብ (ጥሬ ቃል፣ ነጠላ ቃል) ይገላል። ትርጉም ግን ያድናል ማለት ሲሆን ነጭ ነጯን ያልካትና አሁን አሁን አንተም ሆንክ አድማጮችህ እንደልምድ እየተናገራችኋት ያለችው ቃል እውነት እልሃለሁ በቋንቋና በትርጉም አዋቂወች ዘንድ ፕሮግራምህን በንባብም ሆነ በትርጉም ገሎብሃል፥ እየገደለብህም ነው፣ ገናም ጨርሶ ይገድልብሃል እልሃለሁ በድጋሚ።ልክ አንተ ከንጹህ ነጭ ላይ ጠብታ ጥቁር ቢያርፍበት ያን ሙሉ ነጭ ያበላሸዋል ብለህ እንደመሰልከውና እንደተረጎምከው ነው የሆነብህ። ከገባህ ወላጅ አባትህ በሕይወተ ሥጋ ይኑሩ አይኑሩ እኔ እንደማላውቅና እንዲሁም በአካል እንደማላውቃቸው ታውቃለህ። ሆኖም ግን እኔ ሳላስበውና ሳላውቀው እሳቸው በመንፈስ መጥተው የነጭ-ነጯን ምሳሌህና ትርጉምህ የቲማቲም ልጣጭ ነው ብለው ነግረውህና ከፊትህ ጥለውልህ ምንም ሳያናግሩህ ወጥተው ሄዱ እኮ። ሌላ ምን ልበልህ? ወንድሜ ሆይ፦ አባትህ ነብዩ ዳዊትስ ምን ነበር ያለው? በመልእክቴ ርእስ ላይ ያስቀደምኩትን መሪ ቃል አሁን አመጣሁልህ። ""ተምዑ ወኢተአብሱ"" ትር፦ ተቆጡ ነገር ግን አትበድሉ አለ። ምስጢሩ፦ ሕጻናት ሆኑ ማንኛውም ሰው የተማሩትንና ያወቁትን መልካም ትምህርት እንዳይተዉ፣ እንዳይረሱ፣ እንዳይክዱ። ያልተማሩትንና ያላወቁትን ትምህርት ደግሞ እንዲማሩና እንዲያውቁ ምከሯቸዉ፣ በተገቢው መልክ ተቆጧቸዉ። ነገር ግን ያልተማሩትንና ያላወቁትን መልካም ትምህርት ሲማሩ፣ የተማሩትንና ያወቁትን መልካም ትምህርት ደግሞ ሳይተዉ፣ ሳይረሱ፣ ሳይክዱ ዝም ብላችሁ ከመሬት እየተነሳችሁ ያለ አንዳች ምክንያትና ያለ አግባብ አትቆጧቸዉ፥ አታሳዝኗቸዉ፣ አታስቀይሟቸዉ። ይህ አይነት ቁጣ ለእናንተ ለመምህራንም ቁጣ ብቻ ሳይሆን የበደል ኃጢአት ስለሚሆንባችሁ ያለ አግባብ አትበድሏቸዉ ተጠንቀቁ ማለት ነው። ስለዚህ ወንድሜ ሆይ፦ እኔ ስለ ቃላትህ ስያሜ፣ ምሳሌና ትርጉም ስህተት መሆኑንና ማስተካከል ያለብህን በወንድምነት ነገርኩህ፣ መከርኩህ፣ ተቆጣሁህ እንጅ እኔንም አንተንም የሚጎዳ ሌላ የኃጢአት ትምህርትና ደብዳቤ እንዳልጻፍኩልህ ሊቃውንት አባቶቻችንና ቅዱሳን ሐዋርያት ምስክሮቼ ናቸዉ እልሃለሁ። እስቲ ከአሁን በፊት ከማንኛውም ስህተትህ ተው ተመለስ ብሎ በማንኛውም መንገድ የነገረህ ካለ በል ንገረኝ?? እንደማይኖርማ በደንብ አውቃለሁ። እርግጥ ነው አንተ እኔን እንደ አዳመጥከኝ፣ እንደ አመንከኝ፣ እንደ ተቀበልከኝ በንግግርህ ሰምቸሃለሁ። ስለዚህም ነው ከንግግርህ መካከል ከሊቃውንቱ በቀር ማንም የማያስተውለውን ፭ ነገሮችን አውጥቼ የነገርኩህ። በዚህ መሠረት አንተም በማንኛውም ነገር የበታቾችህ የሆኑትን ሁሉ በአዕምሮ እሳቤና በልቦና ግንዛቤ ጤነኞች የሆኑትን ምከራቸዉ፣ ተቆጣቸዉ። ከዚህ ውጭ የማይሰሙህ ከሆነ ግን ልክ እንደ ጋኔል ክብሪት (ዳንኤል ክብረት) ወትሮም ቢሆን ፍቅራችሁ የሐሰትና አግድሞ ነበርና እንደሱ ደህና ሰንብቱ በቃችሁኝ በላቸዉ። በል እንግዲህ ወንድሜ ሆይ፦ መቼም አንዴ ስህተት አይቸብህ ካየሁብህ ስህተት ለመመለስ ስል በፍቅርና በእውነት ትምህርት ጀምሬሃለሁና ያየሁብህንና በቀደም አብሬ ያልነገርኩህንና በይዋል ይደር የተውኳትን ሁለተኛዋን ስህተትህን ደግሞ አሁን ልንገርህና አብረህ እንድታስተካክል እየመከርኩህ ያንተን መልእክቴን እቋጫለሁ። አይዞህ ደሞ ምን ሊለኝ ነው? እንዳትልና በሐሳብ እንዳትሰቀቅ። መልእክቴ ሁሉ ጤናማና ሰላም ነው። እንዲያውም ይኸ ሰውየ ዓይኑና ጭንቅላቱ ምንድን ነው? ብለህ ሳትስቅ የምትቀር አይመስለኝም። ባለፈው ያልነገርኩህና አሁን ግን ልነግርህ የምገደደው፦ ""ከዘመዴ"" ያልከውን የቁልምጫ ስያሜህን አንሳውና በትክክለኛው ስምህ ""ከዘመድ-ኩን"" ጋር ብለህ ሰይመው። የቁልምጫ ስም በማንኛውም የመደበኛ ጽሑፍ ላይ፣ በመደበኛ መድረክ ንግግር ላይ፣ በመደበኛ የቃል መልእክት ላይ አይጻፍም፣ አይጠራም፣ አይነገርም፣ ክልክል ነው። በጣምም ነውር ነው። ወይስ አንተም ከዓብይ አመድ ተማርከው?? እሱ ኢሳይያስ አፈ-ወርቅን በመድረክ ላይ፣ በሕዝብ ፊት፣ በመደበኛ ንግግር ላይ ""ኢሱ ኢሱ"" ማለቱ ማፍቀሩና ማቆላመጡ መስሎታል። አለማወቅና አጉል አውቃለሁ ብሎ መዳፈር ከስንት አይነት ስህተት ይጥላል መሰለህ። ስለዚህ የቁልምጫውን አጠራር ከመደበኛ የጽሑፍ ቃልህና የንግግር መልእክትህ ውጭ ተጠቀምበት ይጠቀሙበት። ስለዚህም ነገር ብዙ ሐተታ ቢኖረውም አሁን ግን አልጽፍልህም። እንዲያው ባጭሩ ልጠይቅህና አንድ ወንጀል ሠርተህ ብትሰወርና ድንገት ብትታይና ከዛም የፍርድ ቤት መያዣ ዘመዴ በሚል የተጻፈ ወረቀት ይዞ ፖሊስ ቢመጣና ቢሰጥህ መልስህ ምንድን ነው የሚሆነው? ኧረ እኔ ዘመዴ አይደለሁም ተሳስታችኋል እንደምትል እሙን ነው። ሰማህ? ገባህ? ፓስፖርትህስ ዘመዴ ነው የሚለው? በመደበኛ ሥራህ ሁሉ የስም መዝገብህ ዘመዴ ነው የሚለው? የልጆችህ መታወቂያ እከሌ ዘመዴ፣ እከሊት ዘመዴ ነው የሚለው? ተው እንጅ የአባትህንና የእናትህን ምስጢራዊ ታላቅ ስም በማይሆን ቦታ ላይ በቁልምጫ አጠራር አታበላሸው። እኔ ስጽፍልህ እነ ጋኔል ክብሪት ሆኑ የወንጌል ደላላዎች ሁሉ በድለላ የቁልምጫ ስም ዘመዴ እያሉ ሲጽፉልህ እንደነበረና አንተም ራስህ ዳኒ ዳኒ ስትለው እንደነበር ሁሉ እኔም ዘመዴ፣ ዘመድ ዓለም፣ ዘመድየ እያልኩ መለቅለቅ አቅቶኝ ነው?? አላቃተኝም። ነገር ግን እኔ የአፍና የቃል ደላላ አይደለሁም። ደግሞም ስምን ያለቦታው በመጠቀም ሕግን አላበላሽም። የቁልምጫ ስምህ በሰዎችና በልጆችህም ጭምር እንደ ቀልድ ይለመድና መደበኛ ስምህ ተረስቶና ጠፍቶ ይቀራል። ይህ ደግሞ እናት አባትን ፈጽሞ መርሳት ነው። ይህ ሲሆን ደግሞ በጣም ያሳዝናል። ትልቅ ስህተትና ነውርም ነው። ምንም እንኳ ኃጢአትነት ባይኖረውና ባይሆንም። የጎንደር ሰው እኔን ማን እያለ እንደሚጠራኝ ታውቃለህ?? አምኃየ፣ አምኃ፣ አባ ሆዴ፣ አምኃ ሆዴ፣ ሆድየ፣ አባ አምኃ.......እያለ ነው እንጅ ሙሉ ስሜን አይጠሩትም። ይህ የሚሆነው ግን ከመደበኛ የመድረክ ንግግርና አጠራር ውጭ መሆኑን አትርሳ። ይህን ስልህ ግን ከዛው ጎንደር ያሉት ሰይጣናዊያን ጠላቶቼ ደግሞ በስውርና በሩቁ ሆነው ያ ሰይጣን ያውና፣ ያ ሰይጣን መጣ መጣ ነው የሚሉ እልሃለሁ። ሰይጣን የሚለኝ ሁሉ ስለማስጨንቀው ነው። በል አስተውል። ____ለመሆኑ ግን ዘመዴ የሚለው በቁልምጫ አጠራር የቃል (የድለላ) መሆኑን ታውቃለህን? ____ዘመድ-ኩን የሚለው ግን የትእዛዝና የተግባር ስም መሆኑንስ ታውቃለህን? ____ዘመድ-ኩን የሚለው ሙሉ ቃል (ስምህ) ትልቅ ምስጢር ያለው የግእዝ ቃል መሆኑንስ ታውቃለህን? ለዚህም፦ <<.....እንተ ኀደረት ዲበ ዘመድነ.....>> ይላል። ትር፦ በባሕርያችን ጸንቶ የነበረ ማለት ነው። <<< ኮነ መድኃኒተ ዘመድነ >>> ይላል። ትር፦ የባሕርያችን ድኅነት ሁኑዋልና ማለት ነው። ይኸውም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ሲጠቅስ ነው። <<< አንቲ በአማን ምክሐ ዘመድነ >>> ትር፦ በእውነቱ የባሕርያችን መመኪያ ነሽ ማለት ነው። ይኸውም እመቤታችን መድኃኒታችን የሆነችውን ቅድስት ድንግል ማርያምን ሲጠቅስ ነው። ስምህን ግን ያወጡልህ የሃይማኖት ሊቃውንት ናቸው? ወይስ ወላጅ አባትህ የተማሩ ናቸው? ነበሩ? እንግዲህ በቁልምጫ ስም ያለ ቦታው ለጥፈህ ያበላሸኸው ይህንን ታላቅ ስም ነው። ኧረ እባክህን ስማኝና አስተካክል። በል እንግዲህ ሙሉ መልእክቴን አንተ ሰምተህና ተቀብለህ ከፈጸምከው ትጠቀምበታለህ። ካልሆነም ደግሞ አዕምሮና ልቦና ያለው ሌላው ሰው ይጠቀምበታል። ሁሉም ሰው ካልተጠቀማችሁበት ደግሞ የዘራሁት እውቀት ወደኔ ተመልሶ ከኔው ጋር ይኖራል ማለት ነው። ____ስላንተ ያለኝን መልእክት ስቋጭ፦ የበጌምድር ክ.ሀገር የዛራውን ቅዱስ ሚካኤል በተስኪያን ታላቁን የቅኔ መምህር ቅዱስ አባታችን የሆኑትን የመሪ-ጌታ ጥበቡን ዜና እረፍት ካንተ ስሰማ ክው ነው ያልኩ። በጣም ደነገጥኩ፣ በጣምም አዘንኩ። ቤተሰብ እንዳይነግረኝ ደግሞ ሩቅ ነኝና። በስልክም አልገናኝምና። ቢያገኙኝም እንኳ በስንቱ ሐዘን ይጎዳ ስለሚሉ አይነግሩኝም። ይገርማችኋል ከባሕር-ዳር ወህኒ ቤት ከእስር እንደተፈታሁ የልደት ዕለት ቅዱስ ላል-ይበላ ለመሳለም ሄጀ ሳለሁ የደብሩ ዋና አስተዳዳሪውና ሊቃውንቱ ካህናቱ ሁሉ ወደዉና ፈቅደዉ በግድ ለስብከት ጋብዘዉኝ ሁለት ቀን ሳስተምር መሪ-ጌታ ጥበቡ ከበጌምድር ሆነው ወዲያው ሲሰሙ ወደ ጎንደር ቤተሰቦቼ መልእክት ልከው ""እባካችሁ እባካችሁ በእግር ብረት አስራችሁ ወደኔ አምጡልኝ። እድሜውን በመከራ ይጨርሰው ወይ?"" ነበር ያሉት። ይህን ያሉበትም ምክንያት ለኔ በጣም በማዘን ነበር። ምናምንቴዎች የቤተ-ክህነት ከሃዲዎች ደግሞ ከምናምንቴዎቹ የቤተ-መንግሥት ሰዎች ጋር አንድ ሆነዉ እስከዛሬ ድረስ በተለያየ መንገድ ሊገሉኝ ያሳድዱኛል። እናማ ሰዎች እየሄዱ፣ ምናምንቴዎች እየቀሩ ሀገርና ሃይማኖት፣ ታሪክና ማንነት ፈርሰዉ ቀሩ። በዚህም ጉዳይ ኀዘኔና ጭንቀቴ በጣም የበረታ ሆነብኝና ከስደት ላይ የተለያየ ሥጋዊ ሕመም ተጨምሮብኝ እያሰቃየኝ እገኛለሁ። የኢትዮጵያና የሰንደቅ-ዓላማዋ አምላክ እስኪፈርድልኝ ድረስ። ደግሞም ይፈርድልኛል። በዓይኔም አየዋለሁ። ማር ቀምሸ አላውቅም እኔ ወገናችሁ ባለ ቀፎ ሁሉ ልለምናችሁ ኧረ ክርስቲያኖች ተማሩ እባካችሁ። አስተምር ተብየ ሀገርን ስዞር ብፈልግ ብፈልግ አጣሁ የሚማር። ኧረ ተው ስማኝ አትስነፍ ተው እየተማርክ እለፍ። ""ተፈጸመ ኩሉ""!!! ተጻፈ፦ ከአምኃ ኢየሱስ ገብረ-ዮሐንስ ሚያዚያ ፳፯ ፪ሺ ፲፫ ዓ ም ከስደት ምድር።
Share on Google Plus

ስለ የተለጠፈበት ቀን

    Blogger Comment
    Facebook Comment