ዘርአዳዊት ዘ-ኢትዮጵያ
መንግስት አለ ይለኛል ገዳይ ሁላ
ፊት ለፊቱ እያየ እጅ እግሩ ተቆርጦ ወገኑ ሲቀላ!
በከንቱ የፈሰሰው የንጹሕ ኢትዮጵያውያንን ደም፣ ከደምቢዶሎ (ደም በ ዶሎ)ታግተው ለ ፪፻፲፩/211 ቀናት ያህል ለተሠወሩት እህቶቻችን ጉዳይ ዛሬውኑ መልስ የማንጠይቅ ከሆነ፤ ሰላም በውስጣችን ሊኖር አይችልም፤ ሰላም የሚባለው ነገርም በሃገራችን ሊኖር ፈጽሞ አይችልም። የምን ሰላም! እነዚህ ምስኪን የገበሬ ልጆች ምናልባት በስቃይ ላይ ምናልባት ተገድለው እያሉ እኔና እናንት ሆዳችንን እየሞላን “ሰላም፣ ሰላም!” እያልን በሰላም ልንኖር??? የት አባታችን! በሐሰት “ሰላም፣ ስላም፡ እንኳን በሰላም አደረሰን!” እያልን በግድየለሽነት መጓዙን የምንቀጥልበት ከሆነ የጠላታችን ዲያብሎስ እራት ከመሆን አንተርፋት! “ዲያብሎስ በእጁ ሲያስገባህ የሰላምን ትርጉም ያሳጣሃል” እንዲሉ ሐሰተኛ ሰላም በውሸት የሚገኝ ምናባዊ ሰላም ነው፡፡ ሰላም አለመኖሩ እየታወቀ “ሰላም አለ፣ ሰላም እንፈልጋለን” እየተባለ የሚነገርለት ነው፡፡ ሐሰተኛነት ባሪያ ያደረጋቸው ሰዎች ሰላም በሌለበት መካከል “ሰላምን አትፈልግሙን? ሰላም እኮ አለ” እያሉ ሕዝቡን ያታልላሉ፡፡ እንግዲህ ይህ እነርሱ አለ የሚሉት ሰላም የውሸት ነው፡፡ እነዚህ ሰዎችን ነቢዩ ኤርምያስ “ሰላም ሳይሆን ሰላም ሰላም ይላሉ” [ኤር ፮÷፲፬] በማለት ይገልጻቸዋል፡፡
ቁጥሩ ከ፲፪ቱ ነቢያት መካከል አንዱ የነበረው ይሁዳ “ሰላም ለአንተ ይሁን” ብሎ አምላክን ስሞ አሳልፎ ሲሰጥ በውስጡ ሰላም የለም ነበር፡፡ [ማቴ ፳፮÷፵፱]። ኢየሱስ ክርስቶስ ከተያዘ በኋላ በመጀመሪያ እንዳሰበው ሊሆንለት ባለመቻሉ በውስጡ ሳይኖር በአፉ ብቻ “ሰላም” ይል የነበረው የውሸት ሰላም አእምሮውን ነሣው፡፡ ንጹሕ ደም አሳልፎ በመስጠቱም መበደሉን ተረድቶ ገንዘቡን በቤተመቅደስ ጥሎ ታንቆ ሞተ፡፡ [ማቴ ፳፯÷፫፡፭]። ነገሮች ሁሉ ይሁዳ መጀመሪያ እንዳሰባቸው ሊሆኑለት አልቻሉምና የመጨረሻ ዕጣ ፈንታው የዘላለም ሞት ሆነበት፡፡
ኢትዮጵያ በውዳቂ ዘረኞች እጅ ወድቃ ስትሰቃይ ዝም ብለን ለማየት መምረጣችን አሳፋሪ አይደለምን?
Blogger Comment
Facebook Comment