የኮሮናቫይረስ ተመራማሪው ዶ/ር ቢንግ ሊኡ ለምን ተገደሉ?


የ37 ዓመቱ ቻይናዊው የኮሮናቫይረስ ተመረማሪ ቢንግ ሊኡ ባሳለፍንው ሳምንት መጨረሻ በአሜሪካ ፒትስበርግ ሃውስ ሕይወታቸው አልፎ ተገኝተዋል።

ፖሊስ እንዳስታወቀው ግድያ እንደተፈፀመባቸውና ገዳያቸው ራሳቸውን ሳያጠፋ እንዳልቀረ አስታውቋል። ይሁን እንጅ እስካሁን የሞታቸውን ምክንያት የሚያስረዳ ሌላ ተጨባጭ መረጃ አልተገኘም።

ነገር ግን ኮቪድ-19ን በተመለከተ የሚያደርጉት ምርመራ ውጤት ለማግኘት ጫፍ ላይ መድረሳቸውን የስራ ባልደረቦቻቸው ከተናገሩ በኋላ በቻይና የማህበራዊ ተጠቃሚዎች ዘንድ ውዝግብ ተነስቷል።

ዶ/ር ሊኡ ለምን ሞቱ?
እንደ ፖሊስ መረጃ ከሆነ ተመራማሪው በፒትስበርግ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ጭንቅላታቸው፣ አንገታቸው፣ ጉሮሯቸው ላይ በበርካታ ጥይቶች ተመትተው ነው ሞተው የተገኙት።

ገዳዩም የ46 ዓመቱ የሶፍት ዌር ኢንጅነር ሃኦ ጉ እንደሆኑም ተነግሯል። ባለስልጣናት እንዳስታወቁት ግለሰቡ ግድያውን ከፈፀሙ በኋላ ወደ መኪናቸው በመመለስ ራሳቸውን አጥፍተዋል።

ዶ/ር ሊኡ እና ጉ ከዚህ ቀደም ይተዋወቁ እንደነበር መርማሪዎች አስታውቀዋል።

ምርመራው ክስተቱ በሁለቱ ጓደኛሞች መካከል በተፈጠረ የቆየ አለመግባባት የተፈፀመ እንደሆነ አመልክቷል።
ይሁን እንጅ ግድያው ከዶ/ር ሊኡ የኮሮና ምርምር እንዲሁም አሁን ካለው የህብረተሰብ ጤና ቀውስ ጋር እንደሚገናኝ የሚያሳይ ምንም ማስረጃ የለም።

የተነሱ ውዝግቦች ምንድን ናቸው?

ከተማራማሪው ሞት ጋር ተያይዞ በርካታ መላ ምቶች እየተሰጡ ነው።

ምን አልባት ቫይረሱ ከአሜሪካ ላብራቶሪ የተነሳ ሊሆን ይችላል የሚለው አንዱ ነው።

የቻይና መንግስት ከዚህ ቀደም ለአገሪቷ መገናኛ ብዙሃን ቫይረሱ በአሜሪካ ላብራቶሪ የተፈጠረ ሲሆን ወደ ቻይና ውሃን እንዲገባ ተደርጓል ሲል አሜሪካ ላይ ጣታቸውን ቀስረው ነበር።

በሌላ በኩል የትራምፕ አስተዳዳርም ወረርሽኙን በተመለከተ ቻይናን እየወቀሰ ነው።

"ሁለተኛ እንዲህ ዓይነት ነገር ሊፈጠር አይገባም፤ ከምንጩ መድረቅ ነበረበት፤ ቻይና ላይ መቆም ነበረበት፤ ግን አልሆነም" ብለዋል- ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ።

ከተመራማሪው አሟሟት ጀርባ አንድ ሚስጢር እንዳለም የጠቆሙም በርካቶች ናቸው።

በተለያዩ ድረ ገፆች በርካታ አስተያየቶች እየተሰጡ ሲሆን ሊኡ ለዚህ የተዳረጉት ቻይናዊ በመሆናቸው ነው የሚሉ አስተያየቶች እየተንሸራሸሩ ይገኛሉ፤ ነገር ግን ግድያው ከዘራቸው ጋር የተገናኘ እንደሆነ የሚያሳይ ማስረጃ የለም።

በሌላ በኩል ለዚህ ድርጊት የቻይና መንግስት እጅ ሳይኖርበት አይቀርም እየተባለ ነው።

ዶ/ር ቢንግ ሊኡ በአሜሪካ ፔንሲልቫኒያ በፒትስበርግ ዩኒቨርሲቲ የህክምና ትምህርት ቤት ተመራማሪ ነበሩ።

የህክምና ትምህርት ቤቱ በድረ ገጹ ላይ ባስነበበው መግለጫ ዶ/ር ሊኡ በሲንጋፖር ዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን የተከታታሉ ሲሆን ለሳይንሱ ዘርፍ የተለየ አስተዋጽኦ ያደረጉ ጎበዝ ተመራማሪ ነበሩ ሲል ገልጿቸዋል፡፡

አክሎም ዶ/ር ሊኡ ከኮሮናቫይረስ ጀርባ ያለውን ዑደት ለመረዳት የሚያስችል ወሳኝ የሆነ የምርምር ውጤት ለማግኘት ጫፍ ላይ ደርሰው ነበር ብሏል፡፡

በመሆኑም ተመራማሪው የጀመሩትን ምርምር ለማጠናቀቅ ጥረት እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡
Share on Google Plus

ስለ የተለጠፈበት ቀን

    Blogger Comment
    Facebook Comment