"ባለፉት ሁለት ዓመታት 20 አብያተ ክርስትያናት ሙሉ በሙሉ ወድመዋል" ማህበረ ቅዱሳን

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ

Image copyrightSERGEI FADEICHEV
አጭር የምስል መግለጫየኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን በሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ስር የሚገኘው ማህበረ ቅዱሳን ዋና ፀሀፊ የሆኑት አቶ ውብሸት ኦቶሮ ባለፉት ሁለት ዓመታት ብቻ በተለያየ ስፍራዎች በእምነታቸው የተነሳ ብቻ ጥቃት የደረሰባቸውን መልሶ ለማቋቋም ከ600 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚያስፈልገው ለቢቢሲ ገለፁ።
በማህበረ ቅዱሳን ጉዳት በደረሰባቸውና መንቀሳቀስ በቻለባቸው አካባቢዎች የደረሰው ጥቃት ምንድን ነው? ምእመናን ምን ዓይነት ጉዳት ደረሰባቸው ? ምን ቢሰራ እነዚህን ሰዎች ማቋቋም ይቻላል የሚለው መጠናቱን ተናግረዋል ዋና ፀሃፊው።
ማህበሩ መንቀሳቀስና ማጥናት በቻለባቸው ስፍራዎች ካገኘው መረጃ በመነሳት ይፋ እንዳደረገው የተለያየ ጉዳት ያስተናገዱ ሰዎችን ለማቋቋም የገቢ ማሰባሰቢያ ለማድረግ ከጴጥሮሳውያን የቤተክርስትያን መብትና ክብር አስጠባቂ ህብረት፣ እንዲሁም ከዳንዲ አቦቲ ማህበር ጋር በጋራ በመሆን ማህበረ ቅዱሳን በጃንሜዳ የገቢ ማሰባሰቢያውን እንደሚያደርግ ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜዎች የተደረጉ የለውጥ ሂደቶች ቤተክርስቲያኒቷ እና በአማኞቿ ላይ የተለያየ ጥቃት ደርሷል ያሉት ዋና ጸኃፊው ለዚህም ምክንያቱ በተለያዩ ጊዜያት የሚነገሩ የሀሰት ትርክቶች ናቸው ሲሉ ይናገራሉ።
ባለፉት ሁለት ዓመታት ብቻ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የተቃጠሉና ሙሉ በሙሉ የወደሙ ከ20 በላይ ፣ ከአስር የማያንሱ ደግሞ የተለያየ መጠን ጉዳት የደረሰባቸው አብያተክርስቲያኖች መኖራቸውን ዋና ጸኃፊው ጨምረው ገልፀዋል።
ከአብያተ ቤተክርስትያናቱ በተጨማሪ ምዕመናኑ ላይ የተለያየ ጉዳት መድረሱን የገለፁት የማህበረ ቅዱሳን ዋና ጸኃፊ፣ ከሞቱት ባሻገር ቤት ንብረታቸው ሙሉ በሙሉ የወደመባቸው፣ አካል ጉዳት የደረሰባቸው፣ ወደተለያየ አካባቢ የተፈናቀሉ ምዕመናን መኖራቸውን ይናገራሉ።
የወደሙባቸው አገልግሎት መስጫ ተቋማትና ቤታቸው የሚሰራላቸው 417 ሰዎች፣ ሌሎች በተለያየ መንገድ ድጋፍ የሚደረግላቸው ደግሞ 1ሺህ 700 ሰዎች መሆናቸውን አቶ ውብሸት ተናግረዋል።
አቶ ውብሸት አክለውም ንብረቶቹን ብቻ መልሶ ለመተካት 400 ሚሊዮን ብር እንደሚፈጅ መገመቱን ገልፀው፤ 200ሚሊዮኑ ለሕክማናና ለስነልቦና ድጋፍ እንደሚውል ተናግረዋል።
ጉዳት የደረሰባቸው አብያተ ክርስትያናት በምዕመናኑ ድጋፍ እየታነፁ መሆኑን የጠቀሱት ዋና ጸኃፊው፣ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ግን አስታዋሽ አጥተው መቸገራቸውን ጠቅሰዋል።
እስካሁን የተጎዱ ሰዎችን መልሶ ለመማቋቋም የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም የፊታችን መጋቢት 27 ቀን በአዲስ አበባ ጃንሜዳ ፕሮግራም ማዘጋጀቱንም አቶ ውብሸት ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በዚህ ፕሮግራም ላይ በትንሹ 30 ሺህ የእምነቱ ተከታዮች እንደሚገኙ የሚጠበቅ ሲሆን፣ ከአገር ውጪ የሚኖሩ በዕለቱ በማህበሩ ድረገፅ በቀጥታ በመግባት ድጋፍ ማድረግ እንደሚችሉ ተናግረዋል።
ማህበረ ቅዱሳን ይህንን ሥራ እንዲሰራ ከጠቅላይ ቤተክህነት በተጻፈ ደብዳቤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርን ጠይቆ ፈቃድ ማግኘቱን ጨምረው ገልፀዋል።
አቶ ውብሸት በተለያዩ ጊዜያት በተለያዩ የሀይማኖት ተቋማት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን እንደሚያወግዙ በመጥቀስ በቤተክርስቲያኒቷ ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች ግን ተገቢውን ትኩረት አላገኙም ሲሉ ይወቅሳሉ።
ተመሳሳይ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃግብር በተለያዩ የኢትዮጵያ ከተሞች ለማካሄድ ዕቅድ እንዳለ አቶ ውብሸት ጨምረው ገልፀዋል።
Share on Google Plus

ስለ የተለጠፈበት ቀን

    Blogger Comment
    Facebook Comment