ሙሴ የሥነ ፍጥረትን ታሪክ በተናገረበት በመጀመሪያው መጽሐፍ ኢትዮጵያ በዐባይ ወንዝ የተከበበች አገር መሆኑዋን ተናግሯል። “የሁለተኛው ወንዝ ስም ግዮን ነው፤ እርሱም ኢትዮጵያን ምድር ይከበዋል” የሚል ማስረጃ ተጽፎ እናገኛለን፡፡ ዘፍ 2÷13
እስራኤልን ከግብፅ ነጻ ያወጣው ታላቁ ነቢይ ሙሴ የዮተር ኢትዮጵያዊ ልጅን ያገባ መሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል። ዘኁ. 12÷1
መጽሐፍ ቅዱስ የኢትዮጵያን ሕዝብና ምድር ሁልጊዜ ከግብፅ ጋር በማያያዝ ይናገራል፡፡ ኢሳ. 20÷3-6፣ ሕዝ. 20÷4-51፣ ዳን. 11÷43፤ ናሆ. 3÷9
በጂኦግራፊ አቀማመጥም ኢትዮጵያ ከግብፅ ደቡብ የምትገኝ አገር መሆኑዋ በቅዱስ መጽሐፍ ተነግሯል ሕዝ. 29፣10፣ ዮዲ .1÷10
ሱዳንንና ግብፅን ሲያጠጡ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ወንዞች ዐባይና ተከዜ በመጽሐፍ ቅዱስ የታወቁ ታላላቅ ታሪካዊ ወንዞች ናቸው ኢሳ. 18÷1
ኢትዮጵያ በማዕድን የከበረች አገር እንደመሆንዋ አልማዟና ወርቋም በዓለም ተደናቂ ነበር፡፡ኢዮ. 28÷19
ሕዝቧም በንግድ ሥራ በዓለም የታወቁ ነበር። በንግዳቸውም በልጽገውና ተደስተው ይኖሩ ነበር። ኢሳ. 43÷3
የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደ ድንክ አጭር፣ እንደ አዛሔል ረዥም ሳይሆኑ ልከኛና መጠነኛ ናቸው። ኤር. 13÷23
የኢትዮጵያ ግዛትም እጅግ በጣም ሰፊ እንደ ነበር ቅዱስ መጽሐፍ ይመሰክራል። በዜና መዋዕል ካልዕ እንደተገለጸው ኢትዮጵያውያን በጦር ስልትና በጀግንነት ከጥንት ጅምሮ የታወቁ ናቸው ዜራህ (ዝሪ) በሚባለው ንጉሣቸው እየተመሩ ዘምተው ምድረ ይሁዳን ያዙ 2ኛ ዜና መዋ. 14÷9-15፣ 16÷8
ኢትዮጵያውያንን ያለ ፈቃደ እግዚአብሔር በኀይላቸው ተመክተው በሚሠሩት ሥራ ነቢያት ይገሥፁአቸው ነበር። ሶፎ. 2÷12
በእግዚአበሔርና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን የማያቋርጥ ፍቅርና ግንኙነት ሲገልጡ ደግሞ “ኢትዮጵያ እጆቹዋን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች” እያሉ በግልፅ ተናግረዋል። መዝ. 68÷31
ከዚህ ሌላ እንደ ባጅ ያሉ ታዋቂ ታሪክ ጸሐፊዎች ኢትዮጵያ ያለ ሃይማኖት የኖረችበት የታሪክ ዘመን እንደሌለ ጽፈዋል። ይህም ያገር ውስጥ ታሪክ ጸሐፊዎች ከሚሰጡት የምስክርነት ቃል ተጨማሪ ነው።
ኢትዮጵያ ከክርስትና በፊት ስለነበራት ሃይማኖት ስንናገር የአቅኒዎቹዋን የሕይወት ታሪክ በመመርመር ነው። ኢትዮጵያን ያቀኑ ሰዎች የመምለኬ እግዚአብሔር የኖኅ የልጅ ልጆች የአያታቸውን አምላክ አንድ እግዚአብሔርን ያመልኩ ነበር።
በተጨማሪም በሐዲስ ኪዳን ክርስትናን በ34 ዓ.ም እንደተቀበለች እነዚሁ ብሔራውያን ሊቃውንት፦ ኢትዮጵያውያን የቅዱስ ፊልጶስን ትምህርትና ስብከት ከጃንደረባው ሰምተው ክርስቶስን መቀበላቸውንና ማመናቸውን ሲገልጡ እንዲህ ብለዋል።
“…. መጥምቁና የወንጌል ሰባኪው ሐዋርያ ፊልጶስ ሆይ! ኢትዮጵያውያን ትምህርትህን ከብልሁ ጃንደረባ ሰምተው ለድንግል ማርያም ልጅ ይሰግዳሉ…..”
ወይም መባቸውን ይዘው ለተወለደው ሕፃን ሊሰግዱለት ቤተልሔም ከተገኙ ሰብአ ሰገል አንዱ ኢትዮጵያዊ ከባዜን ንጉሥ የተላከ መሆኑ ግልጽ ነው።
ይህ አገላለጥ ጃንደረባው በመንፈስ ቅዱስ ከተላከለት አስተማሪው ከቅዱስ ፊልጶስ የተማረውን ትምህርት ለኢትዮጵያውያን በማስተማሩ ዳዊት በመዝሙሩ 72÷9 “በፊቱም ኢትዮጵያውያን ይሰግዳሉ” ሲል የተናገረው ትንቢት እንደተፈጸመ ያሳያል።
Blogger Comment
Facebook Comment