ከበረሃው ገነት ከታላቁ ማኅበረ ሥላሴ ገዳም ለሕዝበ ክርስቲያኑ ሁሉ የተላከ አስቸኳይ መልእክት!


ከላይ እጅግ ከፍተኛ የፀሐይ ሙቀት ከታች የመሬቱና የድንጋዩም ግለት እንደ ነደድ ዕሳት በሚያቃጥልበት፣ የአካባቢው ሞቃታማ አየር (ወበቅ) እንደ እንፋሎት በሚጋረፍበት፣ የጠጣነው በላብ እየወጣ በየደቂቃው ውሃ ጥሙ በሚያንገበግብበት፣ እጅግ በጣም መርዘኛ የሆኑ ተናዳፊ እባቦችና ጊንጡ እንደ አሸን በሞላበት፣ ጥጋጥጉን ሁሉ ሰውና እንስሳትን የሚውጥ ዘንዶ በተሰገሰገበት፣ አስፈሪ የዱር አራዊት ለደቂቃ እንኳን ከማይጠፉበት በዚያ ሃሩር በረሃ በሚገኘው አስደናቂ ገዳማችን ውስጥ በዓታቸውን ሰርተው ዘወትር በጸምና በጸሎት ጽሙዳን ሆነው ግርማ ሌሊቱን ጸብዓ አጋንንቱን ታግሰው ለዓለማዊያን የተፈሩ አራዊትን ሁሉ አገርመው ከመኮሬታው መቁነናቸው ለቁመተ ሥጋ ያክል ብቻ እየቀመሱ በተጋድሎ ጸንተው የሚኖሩ ከሕይወታቸው ጸዓዳነት የተነሳ ምድራዊ መላእክት ከተሰኙት የበረሃው ከዋክብት ክቡራን ግኁሣን አበው የተላከ ነውና ችላ እንዳትሉት ወገኖቼ!!!
የታላቁ የማኅበረ ሥላሴ ገዳም የጾም አዋጅ መልእክት በዓለም ላይ ለሚገኘው ለመላው ሕዝበ ክርስቲያን ይደርስ ዘንድ "share" አድርጉት!
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በዕብ 13፡7 ላይ "የእግዚአብሔርን ቃል የተናገሩአችሁን ዋኖቻችሁን አስቡ፥ የኑሮአቸውንም ፍሬ እየተመለከታችሁ በእምነታቸው ምሰሉአቸው።" ብሎ እንዳስተማረን የክቡራን አባቶቻችንን የከበረ መልእክት ተቀብለን ተግባራዊ በማድረግ መንፈሳዊ ሕይወታችንን አስተካክለን ለንሥሓ እንድንበቃ የቅዱሳን አባቶቻችን አምላክ ሁላችንንም ይርዳን!
የማኅበረ ሥላሴ አንድነት ገዳም ሙሉ መልእክት እንዲህ ይላል፦ 
✞ ✞ ✞ ✞ ✞ ✞ ✞ ✞ ✞ ✞ ✞ ✞ ✞ ✞ ✞ ✞ ✞ ✞ ✞ ✞ ✞ ✞ ✞ ✞ ✞

"በስመአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ፩ዱአምላክ አሜን
በክርስቶስ ክርስቲያን ለተሰኛችሁና በደሙ የዋጃችሁ በኢትዮጵያ የምትገኙ ሕዝበ ክርስቲያን በሙሉ በቤታችሁም ያላችሁ በህመም ምክንያት በሆስፒታል ያላችሁ በማረሚያ ቤት ያላችሁ በጦር ሜዳም ያለችሁ እንዲሁም በተለያየ ስፍራ የምትገኙ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም የከበረ ሰላምታችንን በያላችሁበት ይድረሳችሁ፡፡
እኛ ማኅበረ ስላሴ እንድነት ገዳም የምንገኝ ማኅበረ መነኩሳት በሀገራችን ሰላም መታጣት ምክንያት ከሀዘናችን ጋር አምላክ አበው ክብር ምስጋና ይግባዉ ደኅና ነን፡፡
እግዚአብሔር ገና ሃያ ሁለቱን ስነ-ፍጥረት ፈጥሮ ሳያበቃ ሳጥናኤል በዓለተ ረቡዕ በሶስተኛዉ ሰማይ በጌታ ላይ በማመጽ በጀመረዉ ጸብ ምክንያት ከመላዕክቱ ጋር ተዋግቶ ተሸንፎ ወደ ምድር ተጥሎ እነሆ ያለ እረፍት ለሰባ ሺ አምስት መቶ አመታት በመላዉ ዓለም ደም ሲያፈስ ቆይቷል፡፡ ዛሬም እንደቀጠለ ነዉ፡፡ ጌታ የተሰጠዉ የቀጠሮ ቀን እስኪፈጸም ድረስ ታግሶታል፡፡
አሁን ግን ከወትሮዉ ለየት ያለዉ ነገር የእግዚአብሔር ቤተ - መቅደስ በሆነችዉና የቅዱሳን የአስራት ሀገር በተሰኘችው በኢትዮጵያ ሀገራችን የሳጥናኤል ጭፍሮች ክተት ሰራዊት ምታ ነጋሪት ብለዉ ዘምተዉ በታሪክም ያልሰማነዉ በዘመናችንማ አይተን የማናቀዉ የአርስ በአርስ እልቂት እንኳን ከክርስቲያን ከሰብአዊ ፍጡር የማይጠበቅ ድርጊት ተፈጽሟል እየተፈጸመም ነዉ፡፡
ሰይጣን ብቻዉን ምንም ማድረግ አይችልም፡፡ ከሰዉ ጋር ሆኖ በሰዉ ልብ አድሮ ግን ምንም የሚቀረዉ የሀጢያት ሥራ የለም፡፡ በዮሐንስ ወንጌል ምዕ ፲፭፡፲፭ ላይ ብትወዱኝስ ትዕዛዜን ጠብቁ ያለዉ የጌታ ቃል ተጥሷል፡፡
ቀድሞ አንድ ሰዉ ለሥራም ሆነ ለንግድ ወይም ለተለያየ 
ጉዳይ ወደ ማያዉቀዉ ወደ ሚያዉቀዉም በኢትዮጵያ ክፍላተ ሀገር ወይም ክልል ሲዘዋወር ለሀገሩ እንግዳ ለሰዉ ባዳ ነኝ ብሎ አይጨነቅም፡፡ የእግዚአብሔር እንግዳ ተብሎ ከመሸበት ገብቶ እግሩን ታጥቦ ቤት ያፈራውን በልቶ ጠጥቶ ከመልካም ምንጣፍ ተኝቶ አድሮ ሲነጋ ተነስቶ መርቆ ቀሪዉን ምንገድ ይጓዛል፡፡

ዛሬ ግን ያ ቀረና የእግዚአብሔር እንግዳ እራቱ ጥይትና ገጀራ መጠጡ ደም ሆኗል፡፡ በማቴዎስ ወንጌል ምዕ ፳፭፥፵፪ ላይ የተጠቀሰዉ እንግዳ ሆኜ ብመጣ አልተቀበላችሁኝም ብራብ አላበላችሁኝም የሚለዉ የጌታ ቃል ትዉልዱን እየተዋቀሰዉ ነዉ፡፡
በእርግጥም በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነዉ ብሎ ዮሐንስ ወንጌላዊ እንደተናገረዉ እንግዶች የሰላም ተጓዦች መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡ነገር ግን የሰላም ሰዎችም አብረዉ ተጨፍልቀዉ የጥፋት ሰለባ ሆነዋል፡፡ ሁሉን ቻይ የሆነ እግዚአብሔር አሁንም ታግሶናል፡፡እኛ አሁን ከሞት የተረፍነዉ ከጥላ ያረፍነዉ በጽድቃችን አይደለም በቸርነቱ ለንስሐ ጊዜ ተሰጥቶን ነዉ እንጅ፡፡
ነቢያት ስለ ጥፋት ሲተነብዩ በሰዉ ልጅ ሐጥያት ከእግዚአብሔር የሚታዘዘዉን መቅሰፍት ማስገንዘባቸዉን እንጅ ጥፋት ዝም ብሎ ደርሶ የሚታዘዝ አይደለም፡፡ አሁን በኃጢያታችን ምክንያት እየተጎነጨነዉ ያለዉ መከራ ከዚህ በፊት ብዙ የተነገረ ቢሆንም በትንቢተ ዮናስ ታሪካቸዉ እንደተጠቀሰዉ እንደ ሰብዓዊ ነነዌ ወደ እግዚአብሔር በጾም በጸሎት ሆኖ በመለመን በማልቀስ መከራዉን ማስቀረት እንዲቻል ቅዱሳን በመጽሐፍት አስተምረዉናል፡፡ በኖህ ዘመን ምድር በዉሃ ሙላት የጠፋችዉ በኃጢያት ምክንያት ነዉ፡፡ በሎጥ ዘመን በሰዶም ሀገር የተቃጠለችዉና ከምድረ ገጽ የጠፋችዉ በኃጢያት ምክንያት ነዉ፡፡ ዛሬስ እየተሰራ ያለዉ ኃጢያት በዚያ ዘመን ከነበረዉ ያንሳልን ? ያን ጊዜስ በንስሀ ላልተመለሱ ሰዎች ፈርዶ ያጠፋቸዉ አምላክ ዛሬስ ፈርዶ ማጥፋቱ ይሳነዋል ወይ ? አይሳነዉም እንዲያዉም እንደ ዘመናችን ኃጢያት ብዛትና ክብደት ላልፈረደብን እግዚብሔር እያመሰገንን ይህን መልዕክት በያላችሁበት ሲነበብላችሁ ከሰማችሁት በኋላ ወደ ልባችሁ ተመለሱ ከእንግዲህ ወዲህ በዘር ፣ በጎሳ ፣ በቋንቋ ፣ በሀገር ፣ በብሔር መለያየት ይብቃ ፣ መገዳደል ይብቃ ፣ መዘራረፍ ይብቃ ፣መሰደድም ይብቃ አጠቃላይ የጥፋት ዘመቻ ይብቃ፡፡ ወደ ቀድሞ ኢትዮጵያዊ አንድነታቸን እንመለስ በኅብረት ተቻችለን እንኑር፡፡
የኃጢያታችንን ካባ አዉልቀን በነብስም በሥጋም የሚያድነንን የንስሐ ካባ እንልበስ በዮሐንስ ወንጌል ምዕ ፲፭፥፲፪ ላይ እኔ እንደወደድኳችሁ እርስ በእርሳችሁ ተዋደዱ ብሎ ጌታችን ባዘዘብ መሰረት ጥላቻን አስወግደን የዘር ፣የጎሳ፣ የቋንቋ ፣ የክልል ልዩነት ሳይኖረን እርረ በእርሳችን እንዋደድ፡፡ በዮሐንስ ወንጌል ምዕ ፲፬፥፳፯ ሰላሜን እሰጣችኋለሁ ያለዉ ጌታ ቃሉ አይለወጥም እና ይህ ከሆነ ብቻ እዉነተኛዉን ሰላም ማግኘት ይቻላል፡፡
የተከበራችሁ ሕዝበ ክርስቲያን ሆይ ነብዩ ኢሳያስ በትንቢቱ ምዕ ፩፥፲፱ ላይ ‹‹ እሺ ብትሉና ብትሰሙኝ የምድርን በረከት ትበላላችሁ እምቢ ብትሉና ባትሰሙኝ ግን ሰይፍ ትበላችኃለች የእግዚአብሔር አፍ ይህንን ተናግሯልና›› የሚለዉን የትንቢት ቃል ዛሬም በእኛ ኢትዮጵዊያን ላይ እንዳይደርስብን ለእግዚአብሔር ቃል እንታዘዝ እና ክፋትን ሁሉ ትተን ንስሀ ገብተን የምድርና በረከት እንብላ፡፡ አለበዚያ ግን ምሕረት በእጁ የሆነ አምላክ መዓተም በእጁ ነዉና ምርጫዉ ግን የእናንተ ነዉ፡፡ በሀገራችን ሰላም ይሰፍን ዘንድ ማንኛዉም ክርስቲያን የተጣላ ታርቆ ፣ የበደለ ክሶ ፣ ይቅር ተባብሎ ፤ ከጥቅምት ፳፬ እስከ ጥቅምት ፴ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም ድረስ ልጅ አዋቂ ሳይለይ እስከ ዘጠኝ ሰዓት እየጾማችሁ በሀዘን በለቅሶ ምህላ በመያዝ ከእግዚአብሔር ምህረትና ይቅርታ በጋራ እንድንለምን እኛ የማኅበረ ሥላሴ አንድነት ገዳም ማኅበረ መነኮሳት ሁሉን በፈጠሩ በቅድስት ሥላሴ ስም አምላክን በወለደች በእናታችን በቅድስት ድንግል ማርያም ስም በታላቅ አክብሮት መልዕክታችንን ለመላዉ ሕዝበ ክርስቲያን አስተላልፈናል፡፡
እግዚአብሔር አምላክ ለሀገራችን ሰላም ይስጥልኝ
የሞቱትን ሁሉ ነብስ ይማርልን
የጠፋዉን የተቃጠለዉን የወደመዉን ንብረት ሆሉ ይተካላችሁ
አሜን ይሁን ይደረግልን

መምህር አባ ወልደ ሰንበት ነጋሽ
የማኅበረ ሥላሴ አንድነት ገዳም አበመኔት"

(የገዳሙ ማኅተምና ፊርማ አለው፦ ከፎቶው ላይ ይመለከቷል)






Share on Google Plus

ስለ የተለጠፈበት ቀን

    Blogger Comment
    Facebook Comment