በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤ከቃሉ አንዲቷም ፈፅሞ በማትታበል በአንድ አምላክ ስም
አምላክ ሁሉን ህዝብ ሲያይ በእኩል አይን ነው። ራሳችንን በወገንተኝነት፣ በጎጥ፣ በሀብት፣ በምን በምን ብንከፋፍል
እዚሁ ለኛው ይሆናል እንጂ፣ የእግዚአብሄርን አይን ልንጋርደው ወይም ተፅእኖ ልናሳድርበት ፈፅሞ አይቻለንም።
በሚመጣው ሁሉ በእግዚአብሄር ፍርድ የሚቀሰፈውም ሆነ የሚድነው እያንዳንዱ ግለሰብ የሚመዘነው ዘመን በማይለውጠው
በነበረው በሚኖረው አምላካዊ ሚዛኑ ነው እንጂ የኛ የቡድን ወይ የዘር መለያ ወይ ጎራ በሱ አይን ፊት እንደሌለ ነው የሚሆነው።
አንዴ በሱ ፊት ተመዝነን ከወደቅንና ለቅጣት ከተወሰነብን ምን አለም ቢሰለፍ፣ ምን ተአምር ቢሰራ የሚያድነን ከቶ ሊኖር
አይችልም፤ ደግሞ በዛው መጠን በሱ ፊት አንዴ ተመዝነን ከተመረጥን ምን እሳት ቢዘንብ፣ የእልቂት መአበል መሀል ብንገባ ከቶ
የሚነካን ሊኖር አይችልም።
ይህል ትልቁ ሀቅ በመሆኑ፣ በዚህ መሰረት ምን ስጋት ውስጥ፣ ምን ከበባ ውስጥ ብትገባ፣ ምን ጠላት ቢነሳብህ ቀድመህ
ዞረህ ልታየው የሚገባህ የቀረህን ጥይት ወይ የአባሪህን ዝግጅትና ትጥቅ፣ ወይ የምሽግህን ስፋት አይሁን። ይልቁንስ ከመደራጀቱና
መታጠቁ በፊት ቀድመህ ልታየው የሚገባህ ከጥንት ጀምሮ መከታ ሆኖ ያኖረህን፣ አንተነጥን የመሰረቱት አባቶጭን ያላሳፈራቸው
የሀያላን ጌታ አብሮህ መሆን አለመሆኑን ነው።
ለአባቶጭ እንዳደረገው ዛሬም የአምላክ ሰራዊት ከጎንህ እንዳይሰለፍ ምን ሊያርቀው እንደሚችል ቀድመህ ፈትሽ። ከአንተ
ጋር ምን አፀያፊ ነገር እንዳያሸሻቸው ዙሪያህን፣ ውስጥህን መርምር።
የምትኮራበት ነገር ሁሉ፣ የኢትዮጵያ የክብር ታሪክ ሁሉ መሰረትና ማዕከል፣ አላማም ጭምር አንድ እሱ እግዚአብሄር
ነበርና።
ለዘመናት ሊደፍሩህ ሳይቻላቸው ሲነኩህም ተዋርደው የወደቁት የውጭ ጠላቶች ዛሬ ይህን ታሪክህን እንዳትደግመውና
እንዳይዋሀድህ ፈርተው ከታሪክህ ይህንን መልክህን ቆርጠው አውጥተው አስረስተው፣ ትልቁን ትጥቕን አስፈትተው በባዶ እጅ ሙሉ
ትውልድ ሊማግዱ እየተሯራጡ ነው።
ግን ከኬንያው፣ ከአረቡ ወይ ከግብፅ ከጣልያን ወይ ከቱርክ ከደርቡሹ ጦረኛ ከቶ በምን ተለይቶ ነበር የሐበሻው
ኃያልነት፧ እውነት በቃ እንዲሁ ጀግንነትና ስልት፧ ለሱ ለሱማ እንደቻይናዎቹ የጥንት ወታደሮች በብዛትም ሆነ በልዩ ስልጠና፣
በማርሻል አርት፣ በዉሹ የተጠበበ… የተጠበበ ሰራዊት ከቶ ማን ነበረው፧ እሱስ ቢሆን በትንሿ ጃፓን የዘመናት አሰቃቂ ቅኝ ግዛት
ከመውደቅና ባርነት መች ታደጋቸው፧ አይደለም የኛን ከግብርና ተነስተው የሚዘምቱትን አባቶቻችን፧ ሳትዘነጋው ወይ ሳትተካው
አልቀረህም መሰል፧
ያንን ልዩነት ነው ሊያስረሱህ የሚተጉት። ብረትና ባሩድንማ ከግልብፅና ከቱርኮች አለፍ ካለም ከጣልያኖች በላይ አትርፎ
አብዝቶ የተሸከመው ከቶ ማን ነበረ፧
ታዲያ የቱ ነበረ ልዩነጥ፧ በአለም ካሉ ሀገራት ሁሉ ከሩሲያ በስተቀር በብቸኝነት ለማንም ወድቆ የማያውቅ ያደረገህ፧
ጌዴዎን ማሰሮና የቀንድ መለከት ብቻ ይዞ ወጥቶ አምላክ ሙሉ የምድያምን ሰራዊት ላይ ድልን አልሰጠውምን፧
እነሱ ባያስተምሩህ፣ ከታሪክ ትምህርጥ ቢቆረጥ በስራቸው ያከበርካቸው ምኒሊክ ሰይፍ ላይ በጉልህ የተቀረፀውን ፅሁፍ
ምነው ሄደህ ከቤተመዘክሩ አላየኸው፧ “የምኒሊክ ሀይሉ እግዚአብሄር ነው” የሚለውን፧
ወይ ታሪክ ራቁቱን ሲቀር፦ ግንድ መነሻውን አይተን እንዳታቆጠቁጥ ቅጠሉን ብቻ ሲተረት እንዲኖር ሲደረግ፦ ስንቱን
ታሪክ መሰረቱ ተረሳ፣ ተጠፋ፦
ሌላውስ፧ የቋራው ካሳ ብቻ ወይስ የማህበረስላሴ ገዳሙ ካሳ፧ አፄ ቴዎድሮስ የሚለውን ስም ከየት፣ በነማን ተምረው
ለምንስ መረጡት፧
ዳዊት ደጋሚውና ራሱን ከንጉስ ዳዊት ጋር የሚያስተያየውና በሱ መልክ ራሱን የሚያንፀው ቴዎድሮስ፧ ወይስ የሕዝቅኤልን
ትንቢት ሊፈፅም፣ ኢየሩሳሌምን ነፃ ሊያውጣ፣ ልጆቿን ሊሰበስብ የተነሳው፣ ሌላም በመልአኩ ቅዱስ ዑራኤል የተነገሩትን ሊፈፅም፣
አልፎም ስንትና ስንት እስከዛሬ በትክክል እንኳን ተረድቶ የሚያውቃቸው የሌሉ ረቂቅ ህልሞችን ይዞ የተነሳው ቴዎድሮስ ወይስ
እንዲሁ ሽፍታው ቴዎድሮስ፧ ከማህበረስላሴ መነኮሳት ጋር የነበረው ቃልኪዳንስ፧ አፅማቸውስ ካረፈበት ስለምን ወዴጽ ተቀበረ፧
በአድዋስ ዘመቻ ከምኒሊክ ሰራዊት ፊት ቀድሞ የሚመራው ምን ነበረ፧ ለምን የጊዮርጊስ ታቦት ተመረጠ፧ የጦር ጀግኖች
የክብር ሽልማቶች፣ ይሰራዊቱ አርማ ስለምን ነበረ በቅዱስ ጊዮርጊስ ምስል የሚቀረፀው፧
ቢያንስ በጣም ታወቁ ከተባሉት ታሪኮች እንኳን እነኚህ ሁሉ ስለምን ተነጠሉ፧
ሁሌም ከነበረን ሀያል ታሪክ ጀርባ ዋናው ታላቁና ቀዳሚው ትጥቅ እግዚአብሄር ነበረ። ያ ብቻ ነበረ የሐበሻው ልዩነት።
ልብነድንግል ቁጥር ስፍር የሌለው ሰራዊት ይዞ ስለምን ክፉኛ ወደቀ፧ ልጁስ ገላውዲዎስ በተቃራኒው የጠላቱን ሩብ ያህል ይዞ
እንዴት ታላቅ ድልን አገኘ፧
ሌላው ቢቀር ሁልጊዜ የማትለይህ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ቀለም ስለምን ይሆን ስሟ ሰንደቅ አላማ የተባለው፧
ሰንደቅ አላማ፧ ምን ትርጉም አለው፧ የንጉስ ስም እንደነበረ ማን አስተምሮህ ይሆን፧ በሳባውያን ፅሁፎች እንደተፃፈው
የአለምን ክፍል እስከ አንድ ሶስተኛ ያክል ያስገበረው ንጉሰነገስት ሰንደቅ አላማ ስሙን ዘወትር ሳያውቁት ከመጥራት ያለፈ ማን
በሙሉ ታሪኩ ያስታውሰው ይሆን፧ ከኛ ጠፍተው በውጭ ሀገራት እንኳን የተገኙት የእግዚአብሄርን ስም ሳይጠቅስ የማይሆንለት
የተፃፃፋቸው የጥንት ደብዳቤዎቹስ ለዛሬ ኢትዮጵያውያን ይደርሱ ዘንድ ማን ተርጉሟቸው ይሆን፧
አንተስ ዛሬ በችግር ውስጥ ባለህበት ጊዜ ምን ያህል ትልቁን ትጥቕን አምላክህን ይዘኸዋል፧
ንብ አበባ ባለበት እንዲሰፍር፣ በየትኛውም ጊዜ እግዚአብሄር በመሀል የሚገኘው ፍቅርና እምነት ባለበት ነው። በመሀልህ
የሚገኝ ወንድምህን አንዱን ከሌላው ለይተህ ያየህ፣ ምን ቢወድቅ ቢነሳ በማይቀይረው መስፈርት ከፍቅርህና ማህበርህ በለየኸው
ጊዜ፣ ያኔ በፈቃድህ አምላክህን እንዳይቀርብህ እንደገፋኸው፣ ሀቁን፣ እውነቱን እወቀው።
የሁሉ ነገር ከልካይ ዘረኝነት ባለቀ ጊዜ ወደ አማራው ሊገባ እየታገለ ይገኛል።
ከዘረኛ በላይ ክፉና እጅግ ወንድሙን የሚጠላ የዲያቢሎስ ፈረስ የለም። ዘረኛ በነገሰበት በትኝውም የሀገራችንም ሆነ
የአለም ስፍራ ፍቅር ሰላም ተዋህዶ እምነት ምልክታቸውም አይኖሩም። ይህ የሚታየው ሀቅ ነው።
ከየትኛውም ዘር ብትሆን፣ ምንም ምክንያትም ብትሰጠው ይህንን የተላበስከው ዕለት የደነበረ ፈረስ ላይ የታሰረን ገመድ
በአንገጥ ፈቅደህ እንዳስገባኸው እወቀው። የእግዚአብሄርም ቁጣ ዘራቸውን ሳይጠይቅ ዘረኞችን ሁሉ ይመታል።
አምላክ ሁሉ ነገር ያለው ሆኖ ሳለ ከኛ የሚጠብቃትን አንዲቷን ነገር ፍቅርን የሚሰብር፣ አምላክን (እስከዛሬ መከታ
ሆኖ ያኖረህን ትጥቅ) የሚያርቅ ፀያፍ ነገር በመሀልህ ሊያስተጋባ ዳር ዳር እያለ ነውና ፈጥነህ ይህንን ሰደድ እሳት ደርሰህበት
ግታው። ለምታገኘው ወንድምህም ሁሉ አሳውቀው።
የክርስቶስ ሌላው መጠሪያው የሆነውን ወንድማዊ ፍቅርን ከመሀልህ አስወጥተህና ከፍለህ እግዚአብሄርን የሚያፀይፍ ነገር
ካንተጋር ኖሮ ፈፅሞ አብሮህ ሊገኝ አይችልምና ከእይታህና ከጠበቅከው ፍፁም ውጪና በላይ በሆነው ፅኑ መቅሰፍት አወዳደቕ የከፋ
ይሆናል። ቀድሞም አሁን ያለንበት ሁኔታ የኛ ጉዳይ ሳይሆን ቀድሞ የተነገረ የሚጠበቅ፣ ውጤትና ደረጃውም ከኛ ያለፈ ነውና፣
ለምናደርጋቸው ነገሮች ሁሉ አምላክን አስቀድመን ከዛ የኛን ድርሻ መታገል ይኖርብናል።
ዘር ለቅሞ ከራስ መሀል ለይቶ በመደራጀት ስም ወደጥፋት መስመር ቀድሞም ጠንካራ የነበረውን ህዝብ እየወሰዱት ነውና
ፈጥነህ ቀድመህ ልትመልሳቸው ይገባሀል። መደራጀቱስ ምን ጥፋት ሆነ፧ ግን ከመሀልህ አንድ የዋህ የእግዚአብሄር ሰው ተነስቶ
ወዳንተ ቢመጣ የሚያገለው አደረጃጀት ከሆነ ፍፁም አምላክህን ካንተ የሚያርቅና እጣህ በሰይፍ ብቻ እንዲሆን የሚያደርግህ ነው።
መቼስ የትኛውም ህብረተሰብ እንዲህ ነህ ብለው ለይተው ቦድነው ሲያጠቁት ማንም ቢሆን እራሱን ለመከላከል መሰባሰቡ
የማይቀር ነው። ጠላት ከፊት ቢገፋህ ወደኋላ ስትሸሽ የምትወድቅበትንም ጭምር አስቦ ነውና በታቀደልህ መንገድ ገብተህ ትልቁን
ትጥቕን እንደፈለገው አትፍታለት። ሀይልና መከታ ሆኖ ያኖረህ ዛሬም ለምንም ብሎ ጥሎ የማይጥልህ አምላክህን አታርቅለት። ይህም
ስለሚታወቅ አውቀህ ትድንበት ዘንድ ነውና ቅዱሳን አባቶጭ ነብያት ዛሬ ባይደርሱልህ እንኳን ልጃቸው ዛሬ አንብበህ እንድትድንበት
ስለዚህ ቀን ፅፈው ያኖሩልህ።
ቆይ ግን ለመሆኑ፣ ማንነት ማለት ራሱ ምን ማለት ነው፧ እንዲሁ እንደፈለጉ በየጊዜው የሚቀያየር ነገር ነውንዴ፧
ትላንት የሆንከው ዛሬም የሆነው ነገም የምትሆነው ፅኑ ነገር ነውንጂ፧ ካልሆነማ እንዴት ማንነት ይሆናል፧
የአማራ ክልል ህዝብ ከኢትዮጵያዊነት ከፍያለም ከኢትዮጵያዊነት ዝቅም ያለ ማንነት አልነበረውም፣ የለውም። ታዲያ
እንዲህ ነህ ተብሎ ተለይቶ ሲጠቃ፣ አሁንም ለታቀደ ጥፋት ኢላማ ተደርጎ ሲነሱበት ተባብሮ መቆሙ ግድ ቢሆንበትም፣ እንደሚታየው
ወደባሰ ፍፁም ውድቀት ዝቅ በሚያደርግ፣ ከመጀመርያውም የሁሉ መንስኤ የሆኑት በክህደት ፀንተው አጋንንት በህቡእ አንድነት
ሚመራቸው የውጪ ጠላቶች እቅድ ሙሉ በሙሉ በሚፈፅምላቸው፣ እግዚአብሄርንም አፀይፎ በሚያርቀው መልኩ ፈፅሞ መሆን የለበትም።
ከመጀመሪያውኑ የዚህ ሁሉ መነሻና የጠላቶች መዳረሻ ግባቸው አምላክን አክባሪነት የሆነውንና በአምላክም የተወደደውን
ባለቃልኪዳኑን ኢትዮጵያዊነት ማጥፋት ነበርና።
ከሁሉ በፊት፣ እንቁ ኢትዮጵያዊና የእግዚአብሄር ህዝብ የነበረው የትግራይ ምድር ህዝብ በኢትዮጵያዊነቱና በእምነቱ
ምክንያት ቅድሚያ ኢላማ ተደርጎ እግዚአብሄርን በጠላ ርዕዮት እንዲመረዝ ተደርጎ፣ ድንገት የተነሳ ዘረኝነትና ጥቅመኝነት ያወረው
ቡድን በዛ መልካም ህዝብ ላይ ነግሶና ሰልጥኖበት ህዝቡ የኔ ብሎ እንዲያየውም በተለያዩ ስነልቦናዊና የጥቅም ውስብስብ መንገዶች
ስራ እየተሰራበት ሙሉ ህዝብ ለመለወጥ ባቀደ መንገድ አዲስ ትውልድ ያውም ኢትዮጵያዊነት ምኑም የማይመስለው፣ ለእግዚአብሄር
ያለው እይታና ቅርበት፣ ከምእራባውያን ቸልተኛ ህዝቦች ያልተለየ የሆነ፣ ኢትዮጵያን እንደውም ከማንም በላይ የሱም አባቶች
ጠብቀው ባቆዩት የአምላክ ቃልኪዳኗ፣ ታሪካዊና መንፈሳዊ ማንነቷ ሳይሆን የሚያውቃት እንዲሁ ማንም ተነስቶ ገነጣጥሎ ሊያፈርሳት
የሚቻለውና የራሱ አባቶች ሳይቀር ያቆዩት መንፈሳዊ መሰረት የሌላት አድርጎ የሚያስብ ትውልድ እንዲፈጠር ጫና እየተደረገ ኖሯል።
ከሰሜን ከኤርትራ ጀምሮ በጊዜ ወደታች እየወረደ ኢትዮጵያዊነትን እያጠበ መምጣትን አቅዶ የሚሰራው ክፉ ጠላት ዛሬ
አንተ ላይ ቢደርስ በተመሳሳይ አንተም ያንኑ ደግመህ ስታሳካለት ማየትን ያህል የሚያም ነገር የለም።
ከጥንትም ሰንሰለቱ ሆኖ ያያያዘን እግዚአብሄርን ሁሉም ቢረሳው እንዲህ መለያየት ሰፈነ እንጂ፣ በስነልቦናና እምነት፣
በድህነት ፍቅር ፍፁም አንድ የሆነህን ህዝብ ጋር ማን ይለይህ ነበር፧ ፈጣሪህን ልትይዘው ይገባሀል፦ አንድ የሚያደርግ የፍቅር
ሰንሰለት እሱ ነውና።
በምንም መልኩ ልትበገር የማትችለውን ኢትዮጵያን ሊንድ ይቻለው ዘንድ ከትግራይ ምድር ኢትዮጵያውያን ጋር ያላችሁን
የጋራ ማንነታችሁን ሊያጠፋ ጠላት አቅዶ እንዳደረገው፣ በወንድምህ ላይ ዘምቶ ካንተ ቢለየው፣ ልታዝንለት፣ ወንድምህ ፈልጎ
ያመጣው ሳይሆን ያንተውም መልክ በሆነው በኢትዮጵያዊነቱና እምነቱ ምክንያት ለጥፋት ነውና በእንባ ልትፀልይለት እንጂ፣
ልትፈርድበት ፈፅሞ አይገባህም፦
ሀገሩን ከ ፰፫ ወዲህ በግፍ የገዛው ባንተ ስም ካንተ ወገን ተነስቶ ቢሆን ኖሮ ተመሳሳይ ተግባርና ሁኔታ ባንተ ይሆን
እንደነበረ እውነት ሀቅ ነውና በነሱ የሆነ የወገንተኝነት ፈተና ባንተም ፀንቶ በተመሳሳይ መልኩ ይታገልህ፣ ይፈትንህ እንደነበረ
ፍፁም ሀቅ ነውና ስለውሸት ፈፅመህ እንዳትመፃደቅ። ዛሬ በትግራይ መሬት እንደሚሰበከው በከፊልም በአዲሱ ትውልድ እንደሰፈነው
በተራነት እግዚአብሄርን መዘንጋት፣ በመሳሪያ ትጥቅና ወገንተኝነት ተማምኖ፣ በፉከራ፣ በመሳሪያ ታጋይነት ትርክት፣ ከንቱ ከሁሉ
የበላይነት ስብከት የትእቢት መንፈስ ተጠምቆ የእግዚአብሄርን ህልውና መዘንጋትን መሰረት ያደረገ የምእራባውያን የብልፅግና፣
ስልጣኔ መንገድ ምኞት ሰክሮ ስለእግዚአብሄር አንዳችም ሀሳብ ሳይኖረው በአባቶቹ በእምነት በክብር ተጠብቀው በኖሩ የእግዚአብሄር
ቃልኪዳኖች ምድር ከእግዚአብሄር ጋር እንደገነት እንደፅዮን መኖር ሳይሆን በግንጠላ ሲንጋፖርነትን የሚቃዥ ትውልድ እንዲፈጠር
ከባድ እንቅስቃሴ ይደረጋል። ነገር ግን እግዚአብሄር ዛሬም አለ፣ በአለም የሚሆነውም በኛ በብናኞች ባለቅፅበት እድሜ ፍጡራን
ሳይሆን በሱ ይፀናል።
በአሁን ጊዜ በመሀልህ የተነሳውን ከእግዚአብሄር የሚያርቅ ነገር ሁሉ ቀድመህ ተዋጋው። በመሀልህ የኔ ዘር ነው ልዩ፣
የኔ ዘር ነው ባለታሪክ፣ የኔ ዘር ነው ኢትዮጵያን ያቆየ የሚሉ ትእቢትና ማግለልን ቀላቅሎ የሚከፋፍል፣ እግዚአብሄርን አፀይፎ
ከመሀልህ የሚያርቅ ነገር ሁሉ አጥፋ። ይህ ሁሉ አነጋገር ባላዋቂው ትውልድ የመጣው ህዝቡ በእምነቱ ደክሞ እግዚአብሄርን ረስቶ
ሳለ ድንቅ ታሪኩን ቢመለከት፣ ዛሬ በረሳው እግዚአብሄር የተደረገው ተግባር ሁሉ ባለቤት ባዶ ሆኖ ቢታየው ለራሱ ወስዶ
የሚናገረው ነውና። ኢትዮጵያ ለሺ ዘመናት ስትጠበቅ በአክሱም ፅዮን፣ በደብረሊባኖስ፣ በምሁር ኢየሱስ፣ በላሊበላ… በአራቱም
ማእዘናት ባሉ ኢትዮጵያውያን ፀሎትና ምህላ፣ አምላክን በችግር ጊዜ ሁሉ ብትለምነው፣ በኑሯቸው በእምነት ቢገዙለት፣ በፍቅር ምስጋና
መኖርን ባህላቸው ቢያደርጉት፣ እሱም ልጅነታቸውን ቢቀበል ነውና ባላረፍንበት ዘመናችን ሁሉ ጠላት ቢነሳብን እግዚአብሄርን
ተማምነን ከእርሻላይ ተነስተን ጦርና ጋሻ ይዘን ብንወጣ፣ መድፍና ጥይት ይዞ፣ የተደራጀ ስልጡን ጦር ሁሉ ከእግራችን ጫማ በታች
የጣለልን፣ እንጂ በመላው አፍሪካ ግብፅን ጨምሮ ከቶ መች ሳይዋጋ ለቅኝ ግዛት፣ ለባርነት እንዲሁ ራሱን የሰጠ ነበር፧
ታዲያ ዛሬም በዘር ቡድን ለይተው ቢያጠቁህ እንዲህ ነህ ብለው ቢነሱብህ አይሆንም ብሎ መደራጀትና ለመከላከል በጋራ
መቆም አማራጭ የሌለው ትክክለኛ ቢሆንም፣ ስለምን አጥብበው የሰጡህን ትለብስላቸዋለህ፧ ቢሰጡህ ይበልጥ የሚያደክምህንና ያባቶጭን
ትጥቅ እግዚአብሄርን ይሚያስፈታህ ይሆን ዘንድ ነውና። ስለምን፨ስለማንስ ብለህ የማያሳፍርህ ብቸኛ መከታ አምላክህን አጋርነት
ትተህ እሱን ከመሀልህ የሚያርቅ ዘር ቡድን ላይ ራሽን ልትመድብ ትፈቅዳለህ፧ ቀድመህስ ስለማን ብለህ ነው አምላክህን የያዝከው፧
ዛሬስ የምትለቀው፧
አደረጃጀጥ ማንኛውም በመሀልህ የሚኖር አንድ የዋህ መልካም አሳቢ የእግዚአብሄር ሰው ሊቀላቀልህ ቢያስብ፣ በማይቀይረው
መስፈርት ዘር ቆጥረህ እንድታገለው የሚያደርግ ፈፅሞ አይሁን። እውነት ለምሳሌ ፃድቁ አቡነ አረጋዊ እንኳን መጥተው አብሬህ
ልሁን ቢሉህ አሻፈረኝ ብለህ ልታገላቸው ድረስ መርከስ ቀላል ሆነልህ፧፧ በዚህ መሰል አሰራር አምላክህን ልታፀይፈውና ልታርቀው
ግድ የሌለህ ነህን፧ እሱ ካንተጋር ይሁን አይሁን ግድ የሌለህ ኢአማኒ ሆነህ በስጋ በመርመስመስ ገባዥ የማያስፈልገው የአጋንንት
ማደሪያ እንደሆኑት ዘረኛ ታጣቂዎች ሆንክ፧ ይህንንስ እንዳታደርገው። ከምንም በላይ ለድል ቅድሚያ የሚሰጠው የእግዚአብሄር አብሮ
መኖር ነውና።
እንዲህ ነህ ተብለህ ለጥቃት ኢላማ የተደረግከው መደራጀት አለብኝ ካልክ፣ ቢጠብ ቢጠብ የአማራ ክልል ህዝብ አደረጃጀት
እንጂ የአማራ ዘር ብለህ አላስፈላጊ ክፉ መንገድ ውስጥ አትግባ። አብረውህ ያሉትን ማንኛቸውንም የማለይ፣ ክልል ሚጠብ ሚሰፋ
በመሆኑ ሌሎች በአንድነት ሀሳብ ያመኑ በግብለሰብም ሆነ በህብረት መጥተው የሚቀላቀሉህ፣ ሀይልም የሚሆኑልህ፣ እግዚአብሄር
ሊባርከው የማይጠየፈው የፍቅር አንድነትን ተላብሰህ ለማደግ ለመበርታት ቁም። እኛ ዘር ተማምነን ጎራ ይዘን ብንቆም፣ አምላክም
አንዱን ለይቶ የሚደግፍበት ምክንያትም አይኖረውም፣ ከሁላችን ርቆ በሰይፋችን ስንተራረድ እንከርማለን እንጂ። ከክልሉም ውጪ ያሉ
የአማራ ዘር ተብለው የሚገፉ ወገኖች፣ የአማራ ክልል ህዝብ ልጆች ናችሁ ተብለው ነውና፣ ለነሱም ብትቆም ይህ አደረጃጀት
ያስችልሀል። የዥንጉርጉር ልጆቹ አባት እግዚአብሄርንም ይዘህ ድልን ትለብሳለህ።
እንዲያ ካልሆነ ግን በራሽ እጅ እግዚአብሄርን ገፍተህ እንዳስወጣኸው እወቀው። ለነገሩ ክርስቶስ እራሱ በስጋ ተገልጦ
ከመሀላችሁ ልገኝ ቢል ምን ዘር ብለህ ልታስገባው ነው፧ ትመልሰዋለህንጂ። ይህ እውነተኛው የጉዞህ መልክ ነውና አይግረምህ።
ከተለያዩት የዘረኞች ጎራማ ያንተ ለምን ተለይቶ አብሮህ ይሆናል፧ ነው ወይስ በዚህ በታሪክህ ከባድ ጊዜ እሱን አትፈልገውም፧
ሌላኛው ሳይጠሩት የሚመጣው ጋባዥ የማይፈልገው ርኩስ መንፈስ ግን መገኘቱ አይቀርም። ምንጊዜም በመሀል ነግሶ ዘረኞችን አንድ
አይነት አድርጎ በሚዲያው እንደሚታየው እንደውም በብዛት የተማሩ ምሁር የሚባሉትን ሳይቀር አእምሮ አውርዶ የሚያስደነግጥ አፀያፊ
ንጝርና ተግባር ላይ ሲውላቸው ተመልክተሀል።
በዘረኝነት ግር ብለው በወጡ ሰወች መሀል ለሰው አእምሮ የሚከብድ አሰቃቂ ነገር ሁሉ የሚከሰተው ስለምን ይመስልሀል፧
እያንዳንዱን ሰው በተናጠል ብትጠይቀው ከቶ ሊያደርገው የማይችለውን የሚጠየፈውን ነገር በተሰበሰቡ ሰወች መሀል
ተደጋግሞ ሲደረግ ለምን ይመስልሀል፧ በየግል ያላቸው የተሻለ ሰብአዊ አእምሮ ጠፍቶ በጋራ አንድ የሚያደርጋቸው ሰው በቁሙ
የሚያስቃጥል፣ ዘቅዝቆ የሚያሰቅል፣ በስለት የሚቆራርጥ በስቃይ የሚደሰት አዲስ አእምሮ በአንድነት ይላበሳሉ እንጂ፤ በዛ የቡድን
መንፈስ ላይ መሪነቱን የሚቀዳጀው መሀል ለመግባት ግብዣ የማይፈልገው ክፉ መንፈስ፣ እያንዳንዱ ሰው አእምሮ ውስጥ እንደፈለገው
ተመሳሳይ ሀሳብ የማስቀመጥ፣ ትእዛዝ በመስጠት ማስተባበር የሚያስችለው መናፍስታዊ ተፈጥሮውን በመጠቀም አንድ የጋራ አእምሮ
አስይዞ በየግላቸው የሚጠየፉትን ቡሀላም የሚፀፀቱትን፣ እንደሌላ ሰው የሚኮንኑትን ተግባር እንዲሁም ሌላም ያለንጝር የተቀናጁ
ጥርጣሬዎች፣ ድንጋጤዎች፣ ፍርዶች፣ ያንድላይ ሀሰተኛ ፍረጃዎች በአንድነት ያለንጝር ተግባብተው አሰቃቂ ተግባሮችን በአንድ
አእምሮ ያሰራቸዋል። ሌላም ጊዜ በየትኛውም ቦታ ማንኛውም ሰው ክርስቶስ የሚቃወመውን ነገር ሲያደርግ፣ የፍቅር ፍፁም ተቃራኒ
የሆነውን ዘረኝነትን ሲሰብክ፣ ራሱን ጋብዞ የሚመጣ መንፈስ ምሁሩን አእምሮ አልባ እስኪመስል ድረስ ተቆጣጥሮ ክፉ ክፉ
ያናግረዋል፣ ያሰራዋል። የዚህ አይነት ክፉ ወንድምን ከሌላው መክፈልና ለይቶ ጥቅመኝነትን መስበክ ደግሞ አንዴ ባለቤቱ መንፈስ
ከገባበት ነገሩን አራማጁ ሰው እንዳቀደው አማራና ሌሎች፣ በሚለው ክፍፍል ፀንቶ የሚያበቃና በዛው የሚቀጥል ሳይሆን አንዴ
የክፍፍልና የወገንተኝነት መሪ መንፈስን ጋብዘው ካስገቡት ልክ ከላይ እንደመቱት መስታወት ከዋናው ስንጥቅ መስመር ተከትለው ሌላ
የበዙ ክፍልፍሎችን የሚፈጥር ሆኖ ስንጥቁ እስከጥጋጥጉ እንደሚዛመት፣ አማራ እና ኦሮሞ፣ ወይ አማራና ትግሬ የሚል ክፍልፍልን
አራግበው ከላይ ራሳቸውን የከፈሉበት መንፈስ ወርዶ የቅማንት፣ የአገው፣ የሸዋ ወዘተ እያለ እየቀጠለ መጨረሻ የሌለው ነቀርሳ
መንፈስ መሆኑ የሚወራ ሳይሆን በተግባር የሚታይም መገለጫው ነው። ቀድሞስ ቢሆን በዚህ መሀል የሚነግስ መንፈስ ከዛ ዘር ወይ
ከሌላው ዘር ምን የተለየ ጉዳይ አለውና፧ በቻለው መጠን የልዩነትና ባላንጣነትን፣ ወገን ለይቶ ጥቅመኝነትን መንፈስ አንግሶ
ፍቅርን እስከተቻለው መጨረሻዋ ቅንጣት መስበር ነውንጂ። በፍቅር የሚመሰለውን ክርስቶስ የወንጌል ህሉ ጭምቅ መልእክት በፅኑ
መዋጋት ነውንጂ።
ቅዱስ ጳውሎስ እንደተናገረው “ትንቢትም ቢኖረኝ ምሥጢርንም ሁሉና እውቀትን ሁሉ ባውቅ፥ ተራሮችንም እስካፈልስ ድረስ
እምነት ሁሉ ቢኖረኝ ፍቅር ግን ከሌለኝ ከንቱ ነኝ።”
ምን ባለመንፈሳዊ ፀጋ ባለቤት፣ ምን ባለቅዳሴ፣ ባለማህሌት ብንሆን፣ ያ ሁሉ በዜሮ ተባዝቶ እምነት ከሌላቸው
ሀጢያተኞች ጋር በአንድ ላይ እንድንቀሰፍ ያደርገናል።
ስለዚህ ምንም ቢጠብ ቢጠብ፣ ቢያንስ አብረውህ በክልሉ ያሉ ወንድሞጭን ለይቶ የማያገል አድርገው። ቦታ ሊሰጡ
የማይገባቸው ከንቱዎች በመልካም ሰብአዊ ፍቅር ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን መሀል አጥብበው ከፍለው “አማራ ክልል” የተባልክ መሆንህን
አትርሳ፦ የአማራ ክልል ኢትዮጵያዊ መሆንህን አትርሳ ፦ አማራክልል ተብለው የተከለሉ ኢትዮጵያውያን፦
የአማራ ክልል ኢትዮጵያዊ ፦፦
ነኝ ብለህ ልትናገረው የሚገባህ ያ ነው ያንተ መጠሪያ። ከዚያ አታጥብበው። ለልጁ “ተመልከት ያንተን ንብረት” ብሎ
የአክሱምን ሀውልት የሚጠቁም፣ “ተመልከት የርስጥን ጫፍ” ብሎ ከካርታ ላይ ኦጋዴንን የሚያሳይ፣ እሱራሱ እንዲህ ተብሎ ከአባቶቹ
የተረከበውን እንዳባቶቹ ታግሎ ጠብቆ ለልጁ ሙሉ መብትና ባለቤትነትን የሚሰጥ ነህ። ወደፊትም ኢትዮጵያን የሚያድነው ኢትዮጵያዊ
እንዳትሆን ከቶ ምን ያንስሀል፧
ጀግንነትና ሀይል አንሶህ ነውን የበታችነት የተጠናወታቸው፣ መቼም የማያሸንፉ፣ በተጎጅነት ትርክትና ሮሮ ሲያላዝኑ
ሀያል ጉልበታቸውና ጊዜያቸውን ሲጨርሱ እንደሚታዩት ዘረኞች፣ ከዘረኝነት የሚገኝ ሀይልን ለመላበስ የምትሯሯጠው፧ ነው ወይስ
እግዚአብሄር የለም ብለህ ክደሀል፧ ወይ በቃ ፈፅመህ ክደሀል፧ ታዲያ እሱን ይዘህ በፍፁም ስነልቦናዊ ሀይልና እምነት የዳዊትን
ሀይል መላበስን ትመርጣለህ እንጂ። ቀድሞስ ቢሆን መች ደካማ ሆነህ ነው የሰነፍ ዘረኝነት ሀይልን ልትይዝ ራሽን የምትከፋፍለው፧
በግፍ ጥቃት ለይተው ቢገፉህ፣ የሚገባህን ሊነጥቁህ ቢነሱ፣ በዚህ ክልል ላለን ኢትዮጵያውያን ይገባናል በል፣ አማራ
ብላችሁ ለይታችሁ የምታጠቋቸውን ለራሳችሁ በከለላችሁትም ያሉትን እኔዎች እከላከላለሁ በማለት ቁም እንጂ ይህን ሁን ብለው
የሰጡህን አጥብበህ ይዘህ ራሽን በክፉ መንገዳቸው አውለህ ውስጥህ ያሉትን ኢትዮጵያውያን እንደገና ዘር ብለህ ሳትከፋፍል
በፍቅርና ጠንካራ አንድነት እግዚአብሄርን ይዘህ ይህን አንድ የሚያደርግ በሌላም ክልሎች ያሉ መሰል አስተሳሰብ ካላቸው በዙሪያህ
ያሉ ኢትዮጵያውያን ጋር በአደረጃጀትም ሆነ በስፋት እያደግክ በዘረኛ ጠላቶጭ ላይ ባልፈለጉት መንገድ ክፉ መንፈሳቸውን የሚሰብር
አምላክህን ይዘህ ተነሳባቸው።
እምነታችን ደክሞ ከእግዚአብሄር ህግጋትና መመሪያ ብንርቅ እንኳን ከአደባባይ ታሪክ መማሩን ማን ጋረደን፧
አሁን በኢትዮጵያ ያለው መልክ አሜሪካ በክፍፍልና አደጋ ውስጥ ሆና የነበረበት ሚሊዮኖች የሞቱበት የእርስበርስ ጦርነት
ከነበረበት ወቅት ተማር። አንድነትን የሚያቀነቅኑት ቡድኖችና መገንጠልን የሚሰብኩት ዘረኞቹ ቡድኖች በተዋጉበት ወቅት እጅግ
ብዙዎች በዙሪያው የነበሩት ከያሉበት ወደ አንድነቶቹ ቡድኖች መቀላቀል ይችሉ ነበር። ከተገንጣዮቹም ወገን ብዙ መረጃዎችንና
ሀይሎችን በመያዝ በሂደት ወደአንድነት ሀይሎቹ መቀላቀላቸው ትልቅ አስተዋፅኦ ነበረው። የተገንጣዮቹ ጥቁር አፍሪካዊ ባሪያዎቻቸው
ሳይቀር በመኮብለል ወደዛኛው ሀይል ይቀላቀሉ ነበር። ይህንንም ያስቻለው አቃፊነታቸውና ይህንን ታላቅ ነገር ያስቻለ
አደረጃጀታቸው ነበር። በዚህም መሰረት በአብርሀም ሊንከን የሚመራው የአንድነት ሀይል ድል አድርጎ ያሁኗ ሀያሏ አሜሪካ
እንድትመሰረት መንገድ ከፍቷል።
ዛሬም አንተ ራሽን አቃፊ ሆነህ፣ በፍቅርና አንድነት ከሌሎች ጋር በመዋሀድ፣ ከዘረኞች ጎራም ጭምር ወደአንድነት
የሚመጡ የሚቀላቀሉበትን መንገድ በመያዝ ኢትዮጵያውያን በጋራ በፍቅር አምላካቸውን ይዘው ድል የሚያደርጉበትን መንገድ ልትከተል
ይገባሀል። ራስን በዘር ቆልፎ ለውድቀህ መሯሯን አስቀድመው የተዘጋጁለት የመረጡልህ መንገድ ነውና በሚሰፋና የሚያድግ እንቅስቃሴ
በርትተህ ተገኝባቸው። እግዚአብሄር የሚጠላውን ዘረኝነት፣ ጥቅመኝነትና መከፋፈልን በውስጥህም ሆነ በውጪ፣ ከየትኛውም ጎራ ይሁን
ፈፅመህ ተዋጋው።
ሀይል ለሚሆኑህ ለሌሎች መልካም ኢትዮጵያውያን ውሱንና ዝግ ሆነህ፣ ጠላት ያዝ ያለህን ይዘህ ሳይሆን ማደጊያ መስፊያ
የሆነውን ኢትዮጵያዊነት እንደፈለጉ የማይቀያየር እውነተኛው የማይቀየር ማንነጥን አፋፍመህ ይዘህ ራሽንም ላለመጣል ለጥቃት አማራ
በሚል የተለዩትን ኢትዮጵያውያንም መጠበቅ ከአላማዎቹ ውስጥ አንዱ ዋና አላማው የሆነ አደረጃጀትን ይዘህ ለታላቅ ድል የሆነ
የጀግና ጋባዥ ትግል አድርገው። ክልሉ ውስጥ ያሉትን ሌሎች ወንድሞጭን ጭምር የሚያገል ዘር ቆጠራ ውስጥ ገብተህ አምላክህን
አታርቀው፦ ካሉት የዘር ጎራዎች መሀል የኔን ዘር መርጦ ይቀርባል ብለህ ክብሩን ዝቅ እንደማታደርገው ይታሰባል።
ዛሬ ያለን ትውልዶች መንገዳችን እግዚአብሄርን ያሳዘነ ነውና፣ የእግዚአብሄር ትንቢቶች እንደተናገሩት ከባድ ጊዜ
ከፊታችን ይጠብቀናል። አንተም ይየትኛውም ዘር ይሁን፣ ዘረኝነትን እንዲስፋፋ ፈቅደህ ለሚመጣው መቅሰፍት በግንባርህ ላይ የእርድ
ምልክት አታድርግ። ምን ጠላት ለይቶ ቢነሳብህ የአባቶጭን ትጥቅ ከፈታህ ብቻ ነውና የምትወድቀው እግዚአብሄር ከመሀልህ
እንዳይቆም ከሚያደርግ፣ ጠላትም ይህንን አውቆ ሊነዛብህ ከሚታገለው ዘረኝነት ራሽን ጠብቅ።
ዘረኝነት በትንሹ ተብሎ ሊወሰድ የማይችል ስካር፣ አንዴ መንከባለል ከጀመሩለት እዚህ ጋር አቆማለው የማይሉት ቁልቁለት
መሆኑን ማንም የማይክደው ተፈጥሮው ነውና ስለራሽ ስትል አትላበሰው፣ በሙሉ እንቅስቃሴህ ተጠንቅቀህ በሩቁ ያዘው።
አንተ አልክም፨አላልክም፨ተቃወምክም፨ደገፍክም ዘረኞች ሁሉ ይጠፋሉ። ጥንት በክፋት ተጠምደው የነበሩ የኔፍሊም ልጆች
የነቢዩን ማስጠንቀቂያና የንሰሀ ጥሪ ችላ ብለው በርኩሰታቸው ቢቀጥሉ “ቅዱስ ገብርኤል ሰይፉን ሰጣቸው” ተብሎ እንደተፃፈና
እርስበርስም በፍፁም ውድቀት እርስበርስ እንደተበላሉ ሁሉ፣ ጎራ ጎራ ይዘው በጥላቻም ሆነ በራስወዳድነት የተሰለፉ የዛሬ ዘረኞች
ከየትኛውም ዘር ይሁኑ እርስበርሳቸው እንዲሁ ፍፁም መተላለቅን ይቋደሳሉ፣ የእሳት ሰይፉን ይዘው መራራውን የመከራ ሞት ፀዋ
አንዱ ለሌላው ይጋታሉ።
በንግርትም ጭምር በሱ ዘመን እንኳን የሰው የእንጨት ጠማማ አይጠብቀውም እንደተባለው ክፉ ዘረኞችም ሆኑ የሀጢያት
ሰወች ከትንሳኤው በፊት በሚበላው እሳት ከስመው ይቀራሉ።
አይደለም ዘረኝነትን ጨምረህበት፣ እንዲሁ የምንኖረው የሀጢያት ኑሮ እንኳን ሩጫችን ከሚመጣው የእግዚአብሄር ቁጣ
ባላተረፈን ነበር።
ከሚመጣው ከተነገረው መከራ የሚተርፉት ጥቂቶች መሀል ሁን። ከመከራ በኋላ በሚሆነው ትንሳኤ የሚመጣውን ዘመን ዳዊት
በትንቢታዊ መዝሙሩ “ኢትዮጵያውያን ከፊቱ ይመራሉ” ከተባሉት ከመሆን ይልቅ ሌላ ዘረኛ ማንነትን መላበስን ከመረጥክ፣ ያንተው
ምርጫ ነው። በቃል ንግርት እንኳን “በሱ ዘመን እንኳን የሰው የእንጨት ጠማማ አይጠብቀውም” እንደተባለው ወንድሙን ለይቶ
የሚያርቅ ክፉ ዘረኝነትን ከሚሰብኩት፣ ከሚከራከሩለት ጋር ቀድመህ ከምድር ለመፀዳት፣ ለመጠረግ አትፋጠን።
ይልቅ ታሪክ እንደዘገበው፣ በዘመኑ በጎበኙን የውጪ ፀሀፊዎች ማስታወሻ እንደተዘገበው የኢትዮጵያውያን መለያ የሆነው፣
የጀግንነት፣ ከአህዛብ ሁሉ የበላይነትና የአምላክ ወዳጅነት ስነልቦናን ያላበሳቸው ምስጢር ሁሉም አዘውትረው የሚደግሙት
የተዋሀዳቸው መዝሙረ ዳዊት ነበር። አንዳንድ ኢትዮጵያን ጠል ፀሀፊያን እንኳን ያንጓጠጡን መስሏቸው “ከመዝሙረ ዳዊት ሌላ
መፅሀፍ የማያውቁ፣ በቃላቸውም ብዙዎቹ ሙሉውን የሚደግሙት” በማለት ዘግበው ነበረ የባህል ፍልስፍናና ኢትዮጵያዊ ስነልቦናችን
ምንጭ የሆነው መዝሙረዳዊት መሆኑን ዛሬ ላለነው ምስክር ይሆን ዘንድ የዘገቡልን። በአምላክ መታመን፣ በችግርና ማንኛውም
ፍልሚያም ቢሆን እግዚአብሄርን ሀይል ማድረግን የተማሩበት፣ የአፄ ቴዎድሮስ መሳሪያ፣ እንዲሁም የሀበሻ ጀግንነትና ማንነት ምንጭ
ይህ የተዋሀዳቸው መዝሙረዳዊት ነውና ዛሬም አንተም ይህንን መፅሀፍ አንሳው፦ እውነተኛ ሀይልህን ጀግንነትን ተላበስ።
እውነትም በመፅሀፍ ቅዱስ ማንም ባልተገለፀበት ቃል፣ ፈጣሪ ራሱ በቃሉ “ እንደ ልቤ የሆነ ሰው ፈቃዴንም ሁሉ
የሚያደርግ የእሴይን ልጅ ዳዊትን አገኘሁ ” ብሎ የመሰከረለት ቅዱስ ዳዊት ተከትሎ እንደ እግዚአብሄር ልብ ለመሆን የሚጥር
ህዝብን መሆንን ያክል ክብር በምድርም በሰማይም ከቶ እንዴት መታደል ነው ፦፦
ቅዱስ ዳዊት ጠላት፣ ሰልፍ በበዛበት ጊዜ፣ ሀብት ሆኖ ድልን ያለበሰውን አምላኩን የተማፀነባቸው መዝሙሮች፣
በእግዚአብሄር መተማመንን፣ እሱን ሀይል ማድረግን የሚያላብሰውን ይህን መፅሀፍ በዚህ ጊዜ አንተም ያዘው።
አንዷ ፯ መስመር የምታሞላ ናትና በዕለት ፭ ምዕራፍን ብቻ ከልቦናህ ሆነህ ብታነብ ለዚህ ዘመን ስልቹ ሰው እጅግ
ቀላል፣ ግን ፍፁም ሀያል ተግባር ነውና ከአባቶጭ ስነልቦና፣ ከእውነተኛ ኢትዮጵያዊነት፣ ከሀበሻ ተአምራዊ ጀግንነት እንደቀድሞህ
ተዋሀድበት ፦
ሁሉ ህይወጥ የአምላክ ፈቃድ እንዲነግስበት ፍቀድ፣ አምላክህን ልጅ ሁነው፣ አባጥ ነውና እመነው፣ የአምላክን ፈቃድ
መኖርን ራሽን አለማምደው።
መኪና ስትሳፈር እንኳን “በሰላም አስገባኝ” አትበለው፣ ይልቅ እስቲ ደፍረህ አምነኸው “ፈፅሞ ያንተው ፈቃድህ
ይሁንልኝ” በል፣ ፈቃዱን ማስቀደምን፣ መቀበልን ተለማመድ ፦ ፦ ፦ “ፈፅሞ ፈቃድህ ይሁንልኝ፣ ግን ከተቻለ የይቅርታና ቸርነጥ
እንዲሆን እለምንሀለሁ” ብለህ አምነኸው ራሽን ስጠው፣ ፈቅዱ ሞጥም ከሆነ በደስታ ለመቀበል እስካልቻልክ እውነተኛ እምነት
የለህምና ራሽን በዛ መንገድ አንፀው፣ ይህንን ሳትረሳ በመኪናም ሆነ በስጋጥ ጊዜ አትዘንጋው፣ ራሽን ወደአምላክህ አለማምደው።
አባት ሆኖ ሳለ ደካማ ልጁ አምኖት ከእግሩ ስር ሲሸጎጥ ልቡ ችሎ የሚጎዳ፣ ችሎም ዝም የሚል አባት የለምና፣ እሱስ እንደሆነ
ከኛ ልጅነትን እንጂ ጎሎበት ለሱ ልንሰጠው የምንችል እሱም የሚፈልገው አንዳችም የሌለው ደግ አባት ልጁ ሁንለት እንጂ ሁሉን
እንዳይሰጥህ ቀድሞስ ምን አጋጅ ምክንያት አለውና፧
የብዙ ገንዘብ እጣ ሊወጣልህ ቢል፣ “እባክህን አምላኬ ያንተ ፈቃድ ብቻ ይሁንልኝ፣ ለኔ ፈቃድህ እሱ ከሆነ ባዶ እጄን
እንድትመልሰኝ፣ አንዳችም እንዳላገኝ አብዝቼ እለምንሀለሁ፣ አገኝ ዘንድ ፈቃድህ የሆነውን ግን ስጠኝ” ብለህ ፈጣሪህን ማመኑን
የህይወጥ መርህ አድርገው።
በህይወጥም፣ በድልህም፣ ዳዊትን መስለህ ኑር።
የሀገራችን መፃኢ ሁኔታና ውጊያው ባይንህ ያየኸው፣ ነው ብለህ የምታስበው፣ የተዘጋጀህለትና የጠበቅከውን መልክ የያዘ፣
በዛም የተወሰነ ሳይሆን፣ ይልቅስ የራሽ አባቶች ጭምር ከጥንት በትንቢት አውቀውት፣ ሲጠብቁት የኖሩት ውጊያውም የምድራውያን
ጎሳዎች ተራ ግጭት ሳይሆን የእግዚአብሄር የቁጣ አይኖች ወደሀገራችን የሚመለከቱበት፣ ከህሊናህ በላይ የፀና፣ የእግዚአብሄር
ፍርድ የሚገለጥበት በመሆነውና በምድር ፉክክራችን ታውረን ልክ ከታላቅ ጎርፍ መንገድ ስር ቆመው ትኩረታቸው እርስ በርስ ላይ
አድርገው ጨርቅ የሚጓተቱ ሁለት ሰወች አይነት ሁኔታን አትላበስ። የነሱ መሸናነፍ ምን ሊሆናቸው፧ ትልቁ አስፈሪ ጎርፍ በነሱ
ላይ እንደሆነ ልብ ይገዙ ዘንድ ማን በነገራቸው። የሚመጣው ክስተት አንተ ባሰብከው ውሱንነት የሚታይ ሳይሆን የእግዚአብሄር
ክንድ ወይ ባንተላይ ወይ ካንተጋር ከሁለት አንዱን ይዞ በፅኑ የሚቀስፍበት፣ ከባድ ጊዜ መሆኑን ልብ በል። ከእስራኤላውያን
መሀል ጎሳ ለይተው ሰልፍ በወጡ ጊዜ ለእግዚአብሄር በአንድነት መገዛት ይሻለናል ብለው፣ አምላካቸውን ይዘው የወጡትን በሀይላቸው
የተማመኑት በድንገት አዘናግተው ጦር አዙረው ከበባ ውስጥ በከተቷቸው ጊዜ፣ ይሁዳውያ በእግዚአብሄር ታምነው ያባቶቻቸውን አምላክ
ከሁሉ ትጥቃቸው አምነው አስቀድመው ይዘው በመውጣታቸው ከበባውን ሰብሮ በአንዲት ሰአት ግማሽ ግማሽ ሚሊዮኖችን እንደመታ
አስታውስ። በማይቀረው ምታደርገው ምድራዊ ዝግጅጥም ሁሉ የዳዊት አምላክ ሀይል ይሆንሀል። የመጣውን የዘረኝነትና ዘር ቆጠራ
መርዝ ራሽን ከወጋኸው ግን፣ አምላክን አታስፈልገኝም በራሴው እሞክረዋለሁ ካልክ ምርጫው ያንተ ነው። የሀጢያተኞችና ዘረኞች፣
ባጠቃላይ የጠማሞች መደምሰሻ ጥፋታቸውና ሞት እንደሆነ በፊታችን ገፁን አበርትቶ ፀንቶ ቆሟልና በግንባርህ ላይ የትኛውን ምልክት
አድርገህ እንደምትጠብቀው ምርጫው ያንተ ይሆናል።
Blogger Comment
Facebook Comment