በዚያን ጊዜ አቡነ ጴጥሮስ የሞታቸው ሰዓት መድረሱን ዐውቀው ሰዓታቸውን ከኪሳቸው አውጥተው ተመለከቱ፡፡ በዚህን ጊዜ ምንም ፍርሃት አይታይባቸውም ነበር፡፡ የሞታቸውን ፍርድ ያነብ የነበረው ኢጣሊያዊው ዳኛ ግን ይንቀጠቀጥ ነበር፡፡ ታላቅ ፍርሃም በፊቱ ላይ ይታይ ነበር፡፡ የሞታቸው ፍርድ ከተነበበ በኋላ የፈረዱባቸውን ዳኞች ጸልየው በመስቀላቸው ባረኳቸው፡፡
የሀገራቸው በጠላት መወረር፣ የሕዝባቸው መገደልና መታሰር፣የቤተክርስቲያናቸው መደፈር እስከ ሞት ያደረሳቸው እኒያ እውነተኛ ጳጳስ እንዲገደሉ ሲወሰዱ ጥይት አልፎ ሌላ ሰው እንዳይመታ ግንብ ይፈለግ ጀመር፡፡ ሩቅ ባለመሄድ ከመካነ ፍትሑ ዐሥር ሜትር ርቆ ግንብ ያለው መግደያ ቦታ ተገኘና ወደዚያ ተወሰዱ፡፡ ከገዳዮቹም አንዱ ‹ፊትዎን ለመሸፈን ይፈልጋሉን?› ሲል ጠየቃቸው፡፡ ‹ይህ ያንተ ሥራ ነው› ሲሉ ብፁዕነታቸው መለሱ፡፡ ከመግደያውም ቦታ እንደደረሱ ወንበር ቀረበላቸውና ፊታቸውን ወደ ግንቡ ጀርባቸውን ወደ ሕዝቡ አድርገው እንዲቀመጡ ሆኑ፡፡ ከዚያም በኋላ ስምንት ወታደሮች በስተ ጀመርባቸው ሃያ እርምጃ ርቀው ተንበርክከው በተጠንቀቅ ቆሙ፣ ወዲያው አዛዡ ‹ተኩስ!› በማለት ትእዛዝ ሲሰጥ ስምንቱም ተኩሰው መቱዋቸው፡፡ ግን በስምንት ጥይት ሳይሞቱ ቀሩ፡፡ መሞታቸውንና አለመሞታቸውን ለማረጋገጥ ዶክተር ተጠራ፡፡ ዶክተሩም እንዳልሞቱ አረጋገጠ፡፡ ከዚያም በኋላ አንድ ወታደር በሦስት የሽጉጥ ጥይት ራስ ቅላቸውን መትቶ ገደላቸው፡፡ ብፁዕነታቸው የተገደሉበት ቦታ መሐል አዲስ አበባ ላይ ዛሬ መታሰቢያ ሐውልታቸው ቆሞ በሚገኝበት ቦታ ላይ ነው›› በማለት የጋዜጣ ወኪልና የምሥራቅ አፍሪካ ዜና መዋዕል አዘጋጅ የነበረው ጋዜጠኛው ፖጃሌ ስለ አቡነ ጴጥሮስ ሰማዕትነት ምስክርነቱን ሰጥቷል፡፡ በተጨማሪም ደራሲና ጋዜጠኛ ጳውሎስ ኞኞ ‹‹አቡነ ጴጥሮስእንዴት ሞቱ?›› ሲል በወቅቱ አባታችን ሰማዕትነትን ሲቀበሉ በቦታው ላይ በአካል በመገኘት ሁኔታውን ይከታተሉ የነበሩትንሙሴ ፓይላክን ጠይቋቸው እርሳቸውውም የሚከተለውንተናረዋል፡-
‹‹አቡነ ጴጥሮስ የተገደሉ ዕለት እዚያው ነበርኩ፡፡ መጀመሪያ በእጃቸው ይዘውት የነበረውን መጽሐፍ ቅዱሳቸውን ተሳለሙት፡፡ ቀጥለውም በያዙት መስቀል አማትበው ሕዝቡን ባረኩ፡፡ የኪሳቸውንም ሰዓት አውጥተው ካዩ በኋላ መልሰው ከኪሳቸው ከተቱት፡፡ ወዲያው ወታደሮቸ በሩምታ ተኩሰው ገደሏቸው፡፡ ይህ እንደሆነ አስገዳዩ ኮሎኔል ተመልካቹን ሕዝብ አጨብጭቡ ብሎ አዘዘና ተጨበጨበ፡፡ ማታ ከአስገዳዩ ኮሎኔል ጋር ተገናኝተን ስንጫወት ‹በዚህ ቄስ መገደልኮ ሕዝቡ ተደስቷል› አለኝ፡፡ ‹እንዴት?› ብለው ‹አላየህም ሲያጨበጭብ?› አለኝ፡፡
‹ባታውቀው ነው እንጂ የሕዝቡ ባሕል ሲናደድም ያጨበጭባል› አልኩት፡፡ ‹እንዴት?› ቢለኝ እጄን አጨብጭቤ አሳየሁት፡፡
‹ከዚህ በኋላ የሆነው ቢሆን እኔ ትልቅ ማስታወሻ አግኝቻለሁ› ብሎ አቡነ ጴጥሮስ ሲገደሉ ይዘውት የነበረውን መስቀልና መጽሐፍ ቅዱስ የኪስ ሰዓታቸውንም ጭምር አሳየኝ፡፡ መጽሐፍ ቅዱሱ መሐል ለመሐል በጥይት ተበስቷል፡፡ መስቀሉም ልክ በመሐሉ ላይ ጥይት በስቶት ወጥቷል፡፡ የኪስ ሰዓታቸውንም እንዳየሁት እንዲሁ ጥይት በስቶታል›› ብለው በወቅቱ የተመለከቱትን መስክረዋል፡፡ (ዝኒ ከማሁ) ብፁዕ አባታችን በአደባባይ በሕዝብ ፊት የሰማዕትነት ጽዋቸውን ሲቀበሉ ከሕዝቡ ጋር ሆና ትመለከት የነበረች አንዲት ከድጃ የምትባል እስላም ሴት ማንም ሰው ያላየውን ታላቅ ነገር እርሷ ተመልክታለች፤ ይኸውም አባታችን ሰማዕትነትን ሲቀበሉ የብርሃን አክሊል በራሳቸው ላይ ሲቀዳጁ ተመልክታ በዚያው እርሷም ‹‹የእኚህን አባት ሃይማኖት እከተላለሁ›› ብላ በመጠመቅ ክርስቲያን ሆናለች፡፡አኩሪ ገድል በመፈጸም የቤተ ክርስቲያንና የሀገራችን ታላቅ አለኝታ አባትና መሪ የሆኑት የዘመናችንን ታላቅ ሰማዕት አቡነ ጴጥሮስን ትውልዱ የግድ ሊያስባቸውና ሊዘክራቸው ይገባል። እንላለን የአባታችን በረከት በሀገራችን በኢትዮጵያ በመላው ህዝበ ክርሰረቲያን ላይ ፀንቶ ይኑር ለዘለአለሙ አሜን።
(ምንጭ፡- ዜና ጳጳሳት ኢትዮጵያውያን-ዲ/ን መርሻ አለኸኝ 1996 ዓ.ም፣ የዳጋ ቅዱስ እስጢፋኖስ አንድነት ገዳምያሳተመው ልዩ እትም መጽሔት፣ ስምዐ ጽድቅ 16ኛ ዓመትቁ.17 2001 ዓ.ም)
Blogger Comment
Facebook Comment