"ኢትዮጵያውያን! አገራችሁን፤እግዚአብሔርን አምላካችሁን ሹ ፈልጉ! እኔን ብትሰሙኝ እናንተንም እግዚአብሔር ይሰማችኋል፡፡" ---አለቃ አያሌው ታምሩ



(ከሃያ ዓመታት በፊት በጦቢያ መጽሔት የታተመ)

በመግቢያ አንድ ታሪክ ልጥቀስ፡፡ መጽሐፈ መሳፍንት ም፡9 ቁጥር 17 እና 2ዐ፡፡ እንጨቶች መንግሥት ለመመሥረት ተሰበሰቡ፡፡ መንግሥታቸውንም የሚመራ ለመምረጥ አስበው ዘይትን ነይ በእኛ ላይ ንገሺ፡፡ አሏት፡፡ ዘይትም እግዚአብሔር የሰጠኝን ቅባቴን ትቼ በእናንተ ላይ አልነግሥም አለች፡፡ በለስም ተጠየቀች እግዚአብሔር የሰጠኝን ምጥቀቴን ትቼ በእናንተ ላይ አልነግሥም አለች፡፡ ወይንም ተጠይቃ እግዚአብሔር የሰጠኝን ጣዕሜን ትቼ በእናንተ ላይ አልነግሥም አለች፡፡ ሮማን ( ዶግ፣ቁጥቋጦ፣ጨባ) ተጠየቀች፡፡ እኔ በእናንተ አንድነግሥ የጠየቃችሁኝ ኑ ከጥላዬ እረፉ አለቻቸው፡፡ ኼደውም ከጥላዋ አረፉ፡፡ ከቁጥቋጦው ( ዶግ) እሳት ወጥቶ በላቸው፡፡
የዓረብና የምዕራባውያን ፖለቲካም ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን የሚሰጠው ጥቅም እንዲሁ ነው፡፡የዘመኑ ኢትዮጵያውያን ከምዕራባውያን ከሃይማኖታቸው እስከ በሕላቸው ወርሰዋል፡፡ ከዓረቦችም ከሃይማኖታቸው እስከ ትምባሆ አጫጫሳቸው ወርሰዋል፡፡ አገራቸውን፣ ርስታቸውን፣ ታሪካቸውን፣ ምጥቀታቸውንና ልዕልናቸውን ግን ነቅፈዋል፡፡ ይህም አልበቃቸውም፡፡ አሁንም ከእስቲ እንጨት ሥራ ተጠግተዋል፡፡ ይኸውም የዘመኑ ፖለቲካ ነው፡፡ እንግዲህ እኔ የምናገረው የለኝም፡፡ ከዚህ በፊት ¨ኢትዮጵያን እናድን ¨ በሚል ድምጽ ማሰማቴን አስታወሳለሁ፡፡
ስለ ኢትዮጵያ መጮኽ ከጀመርኩኝ 4ዐ ዘመን አልፏል፡፡ ግን ሰሚ አላገኘሁም፡፡
በቅዱስ መጽሐፍ ለሰዎች ብርቱ ብርቱ ምክር የሚሰጡ ቃላት አሉ፡፡ ነገር ግን ሰዎች የሚጠቅማቸውን ነገር የሚነግራቸው አይወዱም፡፡ ስለዚህ ከመምህራን ቃል የሚሰሙት፣ በመጽሐፍ የሚያነቡት የራሳቸው ጉዳይ እንደተዘጋ ወይም እንደታጠፈ መጽሐፍ ይሆንባቸውል፡፡ ትምህርት ለሌለው ሰው መጽሐፍ ሰጥቶ አንብብ ቢሉት ፊደል አልተማርኩምና ማንበብ አልችልም ይላል፡፡ ለተማረው ደግሞ መጽሐፉን አጥፈው ቢሰጡት ታጥፏልና ማንበብ አልችልም ይላል፡፡

እሥራኤል ስለ አገራቸው ከነቢያት የሚነገራቸውን፤ በመጽሐፍ የተጻፈላቸውን ችላ ብለው በመመልከታቸው የእግዚአብሔር ቃል ¨እንደተዘጋ መጽሐፍ ሆነባቸው¨ ይላል፡፡ በሌላ በኩልም እግዚአብሔር ¨ የከለዳውያንን ቋንቋ እንደባልቀው¨ ማለቱንና የባቢሎን ግንብ ሠሪዎች በነገር አንጣጣም ብለው አገራቸውን ማነጽ ትተው ታላቅ አገር ሊገነቡ ያሰቡትን አሳብ አቋርጠው መበተናቸውንና ያቺ አገር ባቢሎን (ዝርውት) እንደተባለች፤ አንድ ቋንቋ ይናገር የነበረው ዓለምም በብዙ ቋንቋ እንደተለያየና ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ዝምድና ጠፍቶ፤ አንድነት ፈርሶ፤ ጥላቻና መለያየት ነግሦ እስከ አሁን መኖሩን እናያለን፡፡
ባለፉት 5ዐ ዓመታት ውስጥ በኢትዮጵያ ያለተማረው ጥቂት ነው፡፡ የሚሆነውን፣ የሚደረገውን አያውቅም ማለት ሞኝነት ነው፡፡ ነገር ግን የእግዚአብሔር ቁጣ ይመስለኛል፤ በአገሩ ጉዳይ ላይ የተማረውም ያልተማውም አንድ ሆኗል፡፡ ለሁሉም የአገራቸው ጉዳይ እንደታጠፈ መጽሐፍ ሆኖባቸዋል፡፡
በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያውያንን በመጉዳት ላይ የሚታየው የቋንቋ መለያየት ሳይሆን በአሳብ በንግግር አለመጣጣም ነው፡፡ በአገር ጉዳይ ላይ ቅን ፍላጐት ለማሳየት አለመሞከር ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን ሁሉ በአገራቸው ጉዳይ ላይ እየተነጋገሩ አይስማሙም፡፡ አይደማመጡም ለማለት ይቻላል፡፡
ብዙዎች ስለ አገራቸው ጉዳይ የሚነግራቸውን ጠልተዋል፡፡ ማየትም መስማትም አይፈልጉም ለማለት ይቻላል፡፡ የባቢሎን ግንብ እንዳይታነጽ ያደረገ አምላክ የዘመኑ ትውልድ የሚገነባውን ግንብም አልተቀበለውም፡፡
ከሁሉ አስቀድሞ ኢትዮጵያውያን የኢትዮጵያን ስም መስማት፤ የኢትዮጵያን ስም መጥራት፤ በእናትነቷ በታሪኳ መኩራራት ቅር ብሏቸዋል፡፡ አፍረውበታል፡፡ ከኢትዮጵያውን አባቶቻቸው ርስት ለመውረስ የመውደዳቸውን ያህል የአባቶቻቸው ሥም በእነሱ ላይ እንዲጠራ፤ የአባቶቻቸው ታሪክ በእነሱ ጸንቶ እንዲኖር አልፈለጉም፡፡
ሁሉም አዋቂ ነኝ በሚልበት፤ ከአገሩ አልፎ የሌላውን ታሪክ አጥንቻለሁ እመሠክራለሁ የሚል በበዛበት በአሁኑ ጊዜ፤ የአንድ አገር ሕዝብ ከዕውቀት ውጪ የሆነ ሥራ ሲሠራ ማየት እጅግ በጣም! እጅግ በጣም! እጅግ በጣም! አሳዛኝ ነው፡፡
ምነው እግዚአብሔር ቢፈቅድ ዓይኖቼ የሐምሌ የነሐሴ ደመና በሆኑልኝና ስለ ኢትዮጵያ መፍረስ የማፈሰው የዕንባ ዝናብ፣ የዕንባ ጐርፍ ባገኘሁ! ምክንያቱስ ብትሉኝ፤ የዳዊት ልጅ አቤሴሎም በአባቱ ዕቁባቶች ከተጫወተው ይበልጥ ኢትዮጵያውያን በእናታቸው ተጫውተዋል፡፡ አቤሴሎም በአባቱ ላይ ከፈጸመው በደል ይበልጥ ኢትዮጵያውያን በአባቶቻቸው ላይ በደል ፈጽመዋል፡፡ የአባቶቻቸውን ስም፣ ክብርና ታሪክ ረግጠዋል፡፡ የኔሮን ቄሣር እናት ልትገደል ቀርባ ሳለች በምን ሞት ልትሞት እንደምትፈልግ ተጠይቃ ነው የተገደለችው፡፡ ኢትዮጵያ ግን ጠላቶቿ ላደረጉባት ደባ ልጆቿ ተባባሪዎች ሆነው ሞትና መበጣጠስ ሲፈረድባት አልተጠየቀችም፡፡ በዚህ ምክንያት ነው የአንድ ክረምት ዝናብ ብቻ ሳይሆን የዘለዓለም ክረምት ዝናብ ያህል ዕንባ ያስፈልጋል የምለው፡፡
ስለዚህ ኢትዮጵያውያን ሁሉ አሁን ያልፈለጓትን ኢትዮጵያን ኋላ ሊያገኟት እንደማይችሉ ማወቅ አለባቸው፡፡ ይህ ራስን መጥላትንና አገርን መናቅ፤ የወላጆችን ታሪክ መጸየፍ፤ ባዕድን መውደድ፤ በባዕድ አገር ድለላ መደገፍ፤ በእነጨቶች መንግሥት እንደታየው የቁጥቋጦ እሳት ሳይሆን እንደማይቀር ጥርጥር የለውም፡፡
የእግዚአብሔር ያለህ! የሰው ያለህ! ያገር ያለህ! ኢትዮጵያውያን ሁሉ ለአገራችሁ አንድ ሆናችሁ ቁሙ!
ኢትዮጵያውያን! አገራችሁን፤እግዚአብሔርን አምላካችሁን ሹ ፈልጉ! 
እኔን ብትሰሙኝ እናንተንም እግዚአብሔር ይሰማችኋል፡፡
Share on Google Plus

ስለ የተለጠፈበት ቀን

    Blogger Comment
    Facebook Comment