የቃል ቀጣፊዎች

✍ ዘርአዳዊት ዘ-ኢትዮጵያ 

አባቶቻችን 300ው ሊቃውንት በኒቂያ ጉባኤ ያስቀመጡልን "የሃይማኖት መሠረት" ጸሎት መጀመሪያው እንዲህ ይላል፦

"ሁሉን በያዘ ሁሉን በፈጠረ አንድ አምላክ በሚሆን በእግዚአብሔር አብ እናምናለን"
"ሁሉን በያዘ" የሚለው ክፍል አሁን ባሉ የጸሎት መጻሐፍት ላይ የለም ተቆርጦ ወጥቷል። መጻሕፍቶቻችን ብዙ ነገራቸው ተሰርዞ ተደልዞ ነው ያለው። በዚህም ምክንያት ትክክለኛውን ቃል ለመረዳት ከባድ ሆኖ ይገኛል።

በቤተክርስቲያን ላይ ካሉ ከባድ ፈተናዎች አንዱ ይህ ነው። መጻሕፍቱን መሰረዝ መደለዝ ቃላትን መለወጥ። ሰዎች ለቃሉ የተሳሳተ አረዳድ እንዲኖራቸው ማድረግ አልያም አንዳንድ እውነቶችን እንዲደበቁ ማድረግ ነው። ይህ ደግሞ ከውስጥም ባሉ በራሳችን ሰዎች ጭምር የሚካሄድ ሆኖ እናየዋለን።

ሌሎች ደግሞ ክፉዎች መጻሕፍትን አውጥተው ለፈረንጅ ይሸጣሉ። ምዕመናን ቢያነቡት ብዙ ነገርን የሚማሩባቸው መጻሕፍት ተሽጠው ከሀገር ወተው ጠፍተዋል። ባሉት መጻሕፍትም በትክክል የሚያስተምር የለም። 

በዚህም ምክንያት ምዕመኑ ዕውቀት የሌለው ሆኗል። ከውጪም ለሚመጣበት ፈተና መልስ የሌለው ያልተዘጋጀ ሆኗል።

ሌሎች ሰዎች "እናንተ ክርስቶስን" አታውቁትም ሲሉን እንኳ ይህ ስህተት እንደሆነ ማስረዳት አልቻልንም። ከስማችን ጀምሮ ተዋሕዶ የሚለው የክርስቶስን ሰው መሆን የሚገልጽ መሆኑን... ቤተክርስቲያን ማለት የክርስቶስ ስጋው እንደሆነ... የግቢው አጥር እንኳ የሱ የቀሚሱ ዘርፍ ተደርጎ እንደሚቆጠር... ስለ ክርስቶስ ፍቅሩን ለኛ የከፈለውን ዋጋ ህማሙን ጭምር የሚገልጹ ታላላቅ አባቶች እንዳሉን የሚያስተምር ባለመኖሩ ነው እየጠፋን ያለነው። በቅርቡ ነው ጥቂቶች እንኳ አንዳንድ ነገሮች እያነሱ ማስተማር የጀመሩት። 

ከሚያስተምረው ደግሞ የራሱን ጥቅምና ክብር ብቻ የሚጠብቀው ይበዛል። ምዕመኑን የመጠበቅ ሃላፊነት ያልተወጣው ይበዛል።

በሰንበት ትምህርት ቤቶች ስለ አስራ አራቱ ቅዳሴ ወይም ስለ ሃይማኖተ አበው፣ ወይም ስለ ቤተክርስቲያን ታሪክ ስለ ሰማዕታት ታሪክ ከመማር ይልቅ ድራማ መስራትን ይመርጣሉ። 

ወጣቶች ከዓለም ፈተና ከፍትወት ከዝሙት በሙዚቃ ዓለም ከመስመጥ እንዴት እንደሚጠበቁ ከመማር ይልቅ ድራማ እና ትርዒት ስለ መስራት ይማራሉ። ብዙዎቹም በዓለም ተወስደው በገንዘብ ፍቅር ተይዘው የሚጠፉ፣ በዝሙት የሚወሰዱ ከመሆን የሚጠብቃቸው የለም። 

ዘመኑ ካመጣቸው ፈተናዎች፣ አጉል እንዘመንና ቤተክርስቲያንም እናዘምናት ከሚለው አስተሳሰብ፣ እምነትን ጥሎ እንደፈለጉ የመኖርን ባህሪ፣ ፈጣሪን የመካድ አስተሳሰብን ወዘተ ለመከላከልና ትውልዱን አስተምሮ ለመመለስ የሚንቀሳቀስ አባት አይታይም። መንጋው በብዙ ተኩላዎች ሲወሰድ እረኞቹ ዝም ብለው ብቻ ማየት ሆነ ስራቸው።
Share on Google Plus

ስለ የተለጠፈበት ቀን

    Blogger Comment
    Facebook Comment