ንጉሥ ቴዎድሮስ ማን ነው?



✍ቀሲስ መምህር ሄኖክ ወልደ-ማርያም

መነሻው ከየት ነው?

ከቴዎድሮስ ዘመን የሚደርሱት ደጉን ዘመን የሚያዩት ሦስቱ ናቸው እነሱ እነማን ናቸው?

ቴዎድሮስ ከመምጣቱ በፊት አሕዛብ ከጸለይን ለሦስት ወር ይገዙናል ካልጸለይን ለሦስት ዓመት ይገዙናል ይህ እንዴት ይሆናል?

በመከራው ዘመን የመከራው ትንቢት መፈጸምያ የመከራው ማብረጃ እነማን ናቸው?

ንጉሥ ቴዎድሮስ ከመምጣቱ በፊት አራቱ ታላላቅ መከራዎች ይመጣሉ እነሱ ምንድን ናቸው?
ይህ ሁሉ ትንቢት ይፈጸማል ወይስ ያልፋል?
ንጉሥ ቴዎድሮስ መቼ ነው የሚመጣው?
በኢትዮጲያ አይደለም ጠማማ ትውልድ ጠማማ እንጨት አይኖርም /ይህ ትንቢት የሚፈጸመው በዘመነ ቴዎድሮስ ነው/

ማሳሰቢያ ፦ ጽሑፉ ረጅም ቢሆንም የሀገራችን እና የቅድስት ቤተ ክርስትያናችን ብሎም የእኛም መጻኢ ዕድል ነውና ታግሳችሁ አንብቡት፡፡

ሼር በማድረግ ስለ መከራው፣ስለ ትንሣኤው እና ስለ ታላቁ ስለ ንጉሥ ቴዎድሮስ ለወዳጆን ያሳውቁ!
ተወዳጆች ሆይ ስለ ኢትዮጲያ ከጥንት ጀምሮ ከጅማሬዋ እስከ ፍጻሜዋ ትንቢት ተነግሯል፡፡ ከትንቢቶቹም የተፈጸሙና ያልተፈጸሙ ወደ ፊት የሚፈጸሙ አሉ፡፡ ግን አሁን ወደ ትንቢቱ ፍጻሜ እየደረስን ስለሆነ ሊመጣ ስላለው እና እየመጣ ስላለው የቤተ ክርስትያናችን መጻሕፍት እና አባቶች ምን ይላሉ የሚለውን እናያለን፡፡

አሁን ባለንበት ሁኔታ ሀገራችን ኢትዮጲያ መንታ መንገድ ላይ መሄድ አቅቷት ቆማለች፡፡ የሀገራችን የኢትዮጲያ የወደፊት መጻኢ እድልና ሕልውና የተንጠለጠለው በቅድስት ቤተ ክርስያናችን ላይ ነው፡፡ ስለዚህ ስለ ወደፊቱ የሀገራችን ሁናቴና ተስፋ ለማወቅ የግድ በቅድስት ቤተ ክርስትያናች ውስጥ ያሉትን መጻሕፍትን ማወቅ እና መመርመር ብሎም ማየት ያስፈልጋል፡፡
ወዳጆቼ እንደ ምታውቁት ‹‹ንጉሥ ቴዎድሮስ›› ስለሚባለው ደግ እና ጸሎተኛ ባሕታዊ የወደፊት በኢትዮጲያ ትንሳኤ ውስጥ የተቀባ እና የኢትዮጲያ ትንሳኤ መሪ እና አብሳሪ እንደሆነ ይታመናል፡፡ ግን በሚያሳዝን ሁኔታ ሾጥ የሚያደርጋቸው እንደ ማበድ ያሉ ሰዎች እየተነሱ ‹‹ቴዎድሮስ እኔ ነኝ›› እያሉ ሲወሸክቱ ሰምተናል አይተናል፡፡ እነዛ ሰዎች እንኳን ታላቁን ንጉሥ ቴዎድሮስን ቀርቶ እራሳቸውንም በአግባቡ መሆነ ያቃታቸው ሰዎች ናቸው፡፡
ንጉሥ ቴዎድሮስ ማንነው?

ተወዳጆች ሆይ ስለ ታላቁ የወደፊት የሀገራችን ንጉሥ ‹ቴዎድሮስ› ማንነት በትንቢት የምናገኘው በፍካሬ ኢየሱስ፣በድርሳነ ቅዱስ ዑራኤል፣በገድለ ፊቅጦር ላይ ነው፡፡ በጀምስ ብሩስ ተሰርቆ በብሪትሽ ሙዝየው ውስጥ የሚገኘው ታላቁ የትንቢት መጽሐፍ የሆነው በፍካሬ ኢየሱስ ላይ ንጉስ ቴዎድሮስን ‹ቴ› በማለት የስሙን የመጀመርያ ፊደል በመጥቀስ ስለ ቴዎድሮስ ይናገራል፡፡ ይህ ብቻ አይደለም ቴዎድሮስ የእግዚአብሔርን ጸጋ እና ኃይልን ተላብሶ ከመምጣቱ በፊት ስለሚፈጠሩት አስቸጋሪ ክስተቶች እና ምጦች ይተነብያል፡፡ ይህ ታላቅ ንጉሥ ቴዎድሮስ ንግሥናው ከሀገራችን ከኢትዮጲያ ትንሣኤ ጋር የተያያዘ ነው፡፡
አባቶቻችንን የዚህን ንጉሥ መምጣትና የሀገራችንን የማይቀረውን የወደፊት ትንሣኤ ቅዱስ የሆነው የእግዚአብሔር መንፈስ በገለጠላቸው መጠን ለኛ ከትበውልናል፡፡ ለምሳሌ ስለ ኢትዮጲያ ትንሣኤ ብቻ በፍካሬ ኢየሱስ፣በድርሳነ ዑራኤል፣በገድለ ፊቅጦር፣በገድለ አቡነ ሲኖዳ፣በራዕየ ሳቤላ፣አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ በጻፉት በመጽሐፈ ምስጢር እና በትርጓሜ ወንጌል ላይ ይገኛል፡፡ ይህ ሁሉ የወደፊት የኢትዮጲያ የማይቀረው ትንሣኤ ከቴዎድሮስ ጋር የተያያዘ ነው፡፡

በድርሳነ ቅዱስ ዑራኤል ላይ ስለ ቴዎድሮስ ከመላኩ ከቅዱስ ዑራኤል አፍ የሰማው ዲያቆኑ ባሮክ ነው፡፡ ይህ ባሮክ የተባለ የተባረከ ዲያቆን በኢየሩሳሌም የጌታን መቃብር በመጠበቅ የሚኖር ነበር፡፡ ባሮክ እንደ ነብዩ ኤርሚያስ ደቀ መዝሙር እንደ አቤሜሌክ የኢየሩሳሌምን ጥፋት አታሳየኝ እያለ የሚጸልይ ደግ ሰው ነበር፡፡ እግዚአብሔርም የባሮክን ጸሎት ሰምቶ የኢየሩሳሌምን ጥፋት እንዳያይ ለሰባ ዓመት እንቅልፍ ጣለበት፡፡ በዚህም ባሮክ ሥጋው ሳይፈርስ ሳይበሰብስ በእግዚአብሔር መለኮታዊ ጥበብ ለሰባ ዘመን ተኝቶ ኖረ፡፡

ባሮክ ከእግዚአብሔር የተሰጠው ሰባ የእንቅልፍ ዘመን ካለፈ በኃላ በጎልጎታ ባለች በጌታችን ስም በተሠራች ቤተ ክርስትያን ገብቶ እህል ሳይቀምስ ውኃ ሳይጠጣ ለአርባ መዓልት እና ሌሊት ሱባኤ ገባ፡፡ ወዳጆቼ ከዚህ በኃላ ነው የቴዎድሮስ ነገር እና ምስጢር የሚጀምረው፡፡ ነገረ ቴዎድሮስ በትንግርት ሳይሆን በሱባኤ በሆነ ጸሎት የመጣ መሆኑን ልብ በሉ፡፡
ባሮክ ሰባ ዘመን ተኝቶ የመከራውን ዘመን ስላሳለፈ ነው እግዚአብሔር ከኢየሩሳሌም እስከ ሀገራችን ኢትዮጲያ ያለው የወደፊት የመከራ እና የትንሣኤ ዘመን ትንቢት የነገረው፡፡ ቅዱስ ዑራኤል ለባሮክ ስለ ወደፊቱ ሲነግረው ግድ ይፈጸም ስለነበር ‹‹የምነግርህን ልብ አድርገህ ስማ›› እያለው የሚነሱትን ነገሥታት የስማቸውን የመጀመርያ ፊደል ለምልክት እየነገረው ዘርዝሮ ገልጾለታል፡፡

ቅዱስ ዑራኤል ለዲያቆን ባሮክ ‹‹በመጨረሻውም የአረማውያን ዘመን በመሆኑ ፍቅር በየጊዜው እየጎደለ ይመጣል፡፡ በዚያን ዘመን ስለ እግዚአብሔር ብሎ ሃይማኖትን ማጠንከርና ደጋግ ሰዎች መውደድ እውነትና መልካም ሥራ መሥራት ፈጽሞ የለም፡፡ ከመነኮሳት ማህበር ሆነ ከካህናት ወገን ሁሉ ወንዶችም ሴቶችም በመልካም ሥራ አይሄዱም፡፡ ጻድቃን ይመስላሉ በውስጣቸው ግን ተንኮለኞችና ሐሰተኞች ሴሰኞች ናቸው››/ይህ ትንቢት በዘመናችን መፈጸሙን ልብ ይሏል?/ በማለት የጊዜውን ሁኔታ ካስረዳው በኃላ ስለ መጪው ንጉሥ ቴዎድሮስ ‹‹አመድ ከዘነመ ከአራት ዓመት በኃላ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሰማዕት የሆነ በፊቅጦር በገድሉ መጽሐፍ እንደተነገረው የስሙ ምልክት ‹ቴ› ተብሎ የተመለከተው ይነግሳል ብሎ አስረድቶታል፡፡ ግን በዘመኑ የግብጻውያን ጳጳሳት እና የኢትዮጲያውያን ጳጳሳት በአባ ሲኖዳ ገዳም ስለ ሃይማኖት ታላቅ ጉባኤ ያደርጋል፡፡ ይህም የሚሆነው በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ምስጢረ ሥጋዌ ላይ ነው፡፡ በጉባኤውም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አካላዊ ቃል ከሥጋ ጋር አንድ ባሕርይ መሆኑን በማስረዳት ይፈጽማሉ፡፡ ቅዱስ ዑራኤልም በዚህ አላበቃም ስለ ደጉ ዘመን በኢትዮጲያ ውስጥ እና በዓለም ላይ ሁሉ ሰላም ደስታ ጥጋብና ፍጹም ተድላ እንደሚሆን ነግሮታል፡፡

ተወዳጆች ሆይ የጥቅምት ድርሳነ ዑራኤል ላይ ስላለው የኢትዮጲያ መጻኢ መከራ እና ትንሳኤ በአጭሩ በዚህ መልኩ ካየን ዘንዳ ወደ ገድለ ቅዱስ ፊቅጦር ደግሞ ጉራ እንበል፡፡ ቅዱስ ፊቅጦር የአንጾኪያው መስፍን ርህራሄ የሌለው የህርማኖስ ልጅ ነው፡፡ እናቱም ማርታ ትባላለች፡፡ ቅዱስ ፊቅጦር ገና በሕፃንነቱ የእግዚአብሔር መልአክ ከሰማይ የወርቅ ልብስ አውርዶለት የለበሰ ወጣት ሰማዕት ነው፡፡ ቅዱስ ፊቅጦር እጅግ ብዙ መከራና ስቃይ ተቀብሎ በጣኦት አምላኪው በአርያኖስ እጅ ሚያዝያ 27 ቀን ሰማዕት የሆነ ነው፡፡

ቅዱስ ፊቅጦር ሰማዕትነት ተቀብሎ ካረፈ በኃላ የከበረውን ሥጋውን እናቱ ማርታ ሃይማኖቱ በጸና እና ቤተ ጣኦትን አጥፍቶ አብያተ ክርስትያንን ባነጸው፣አምልኮተ ጣኦትን አጥፍቶ አምልኮተ እግዚአብሔርን ባስፋፋው ደጉ ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ በነገሠበት ዘመን በልጇ ስም በወርቅና በብር አስጊጣ በእስክንድርያ ቤተ ክርስትያን አሳነጸች፡፡ ከዚህ በኃላ ማርታ ሌሊት ተኝታ ሳለች ሰማዕቱ ቅዱስ ፊቅጦር በራዕይ ተገልጾላት በግብጽ ላይ አሕዛብ እንደሚነግሱባት እና እሷ በወርቅ እና በብር አስጊጣ ያሠራችው ቤተ ክርስትያን ለወርቁና ለብሩ ብለው አሕዛብ እንደሚፈርሱት ነገራት፡፡ ማርታም በግብጽ ሀገር አሕዛብ እንደሚነግሡ ከልጅዋ ከቅዱስ ፊቅጦር በሰማች ጊዜ እጅጉን አዝና ‹‹እንደዚህ ከሆነማ ቤተ ክርስትያን በመሥራት ለምን እደክማለሁ›› አለች የዚህን ጊዜ ነው ቅዱስ ፊቅጦር እግዚአብሔር የገለጸለትን ስለ ኢትዮጲያዊው ደግ ንጉሥ ቴዎድሮስ ቅድስናውን ገልጾ ስሙን ሸፈን አድርጎ የነገራት፡፡

ወዳጆቼ ቅዱስ ዑራኤል ለዲያቆኑ ለባሮክ እግዚአብሔር የገለጠለትን ሲነግረው የቅዱስ ፊቅጦር ገድል ላይ ያለውንም ትንቢት አጣምሮ ነው የነገረው፡፡ ይህም የሆነው ባሮክ ከመላኩ ከቅዱስ ዑራኤል አንደበት የሰማውን በገድለ ቅዱስ ፊቅጦር እንዲያመሳክረው ነው፡፡ ለዚህም ነው መልአኩ ‹‹የኢየሱስ ክርስቶስ ሰማዕት የሆነ በፊቅጦር በገድሉ መጽሐፍ እንደተነገረው የስሙ ምልክት ‹ቴ› ተብሎ የተመለከተው ይነግሳል›› ያለው፡፡ እዚህ ላይ ቅዱስ ዑራኤል የደጉን ንጉሥ ስም ‹ቴ› ብሎ ተናግሯል፡፡ ገድለ ፊቅጦር ግን ‹‹በኢትዮጲያ ሀገር ክርስቶስን የሚወድ ቅዱስ ሰው ይነግሣል›› አለ፡፡ ቅዱስ ዑራኤል የንጉሡ የቴዎድሮስን የስሙን የመጀመርያ ፊደል ጠቆም አድርጎ ሲናገር ቅዱስ ፊቅጦር ደግሞ የንጉሥን ቅድስና ገልጾ ‹‹ቅዱስ ሰው›› አለው፡፡
ይህንንም ቅዱስ ፊቅጦር ‹‹አሕዛብ መንግሥት ጥቂት ዘመናት ናቸው፡፡/ይህቺ ጥቂት ዘመናት ትያዝልኝ ልብ ትባልልኝ/ ከጥቂት ዘመናት በኃላ እግዚአብሔር በኢትዮጲያ ሀገር ክርስቶስን የሚወድ ቅዱስ ሰው ያነግሳል፡፡ አረማውያንም በእርሱ እጅ ይደመሰሳሉ፡፡ ከዚህ በኃላ ወደ ግብጽ ሄዶ አሕዛቦችንና መንግሥታቸውን ሁሉ ያጠፋል›› ይላል፡፡ ከዚህ ሁለት ነገር መረዳት እንችላለን፡፡ አንደኛው ‹‹የአሕዛብ ጥቂት ዘመን›› የተባለው ነው፡፡ ይህም አሁን ያሉት እነ እከሌ የማንላቸው ግን በሂደት ላይ ያሉት የአሕዛብን መንግስት በሀገራችን ላይ ለመመስረት መንገድ ላይ ናቸው፡፡ አንዱ ትንቢት ይህ ነው፡፡ ሁለተኛው ንጉሥ ቴዎድሮስ ትንቢት ከኢትዮጲያ እስከ ግብጽ ነው፡፡ እኛንም ግብጾችንም ከአሕዛብ ቀንበር በእግዚአብሔር ኃይል ነጻ ያወጣናል፡፡

ወዳጆቼ በደጉ ንጉሥ ዘመን የቁስጥንጥንያው ጳጳስና የእስክንድርያው ጳጳስ የእኔ ሃይማኖት ይበልጣል ብለው በአባ ሲኖዳ ቤተ ክርስትያን ገብተው ሁለቱም በአንድ ታቦታ ላይ ቀድሰው መንፈስ ቅዱስ በነጭ ርግብ አምሳል በገሃድ ወርዶ የእስክንድርያው ጳጳስ በሰዋው ቅዱስ ቁርባን ላይ መውረዱንና በዚህም የሮሙ ጳጳስ ሊዎንን ረግሞት የኑፋቄ እንክርዳድ የተዘራበትንና የበቀለበትን መጽሐፎቻቸውን ጥለው የእኛንና የእስክንድርያን ሃይማኖት ስለመምሰላቸው በሰፊው በገድለ ፊቅጦር፣በአቡነ ሲኖዳ ገድል ላይ ስለተጻፈ እሱን አንብቡት፡፡

መነሻው ከየት ነው?

ተወዳጆች ሆይ ከላይ እንዳየነው የጥንቱ ፍካሬ ኢየሱስ ስለ መጪው ንጉሥ ቴዎድሮስ አመጣጥ እና ቤተሰብ ይናገራል፡፡ ይህንን ለጊዘው እንለፈውና አሁን ባለበት ሁኔታ ንጉሥ ቴዎድሮስ መነሻው በቅርባችን ባለው ኤረር በዓታ እንደሆነ አባቶቻችን ይናገራሉ፡፡ የሚመጣውም አዛውንት ሆኖ ነው፡፡ ሥጋው በጾም በጸሎት በገድል የደከመ መንፈሱ ግን በእግዚአብሔር ጸጋ የበረታ ሆኖ ነው፡፡ የሚመራን በእግዚአብሔር ቅዱስ መንፈስ እና ጸጋ ነው፡፡ የሚገዛንም በእግዚአብሔር ሰማያዊ ሕግ ነው፡፡ ኢትዮጲያንም ለአርባ ዓመታት ይመራታል፡፡ ጊዜው ደርሶ፣የደፈረው ጠርቶ እስኪመጣ በዚሁ በኤረር በዓታ በጾም፣በጸሎት ተወስኖ እንዳለ ነው አባቶቻችን የሚያስረዱን፡፡
ከቴዎድሮስ ዘመን የሚደርሱት ደጉን ዘመን የሚያዩት ሦስቱ ናቸው እነሱ እነማን ናቸው?

ስለ ቴዎድሮስ የተጻፉት መጻሕፍትና አባቶቻችን እንደሚሉት ከደጉ ዘመን ከንጉሥ ቴዎድሮስ የሚደርሱት ሦስት ናቸው፡፡ አንደኛው በዓለም ሆነው ቢያንስ በቀን አንዴና ሁለቴ ስመ እግዚአብሔርን የሚጠሩና የሚጸልዩ ናቸው፡፡ እነዚህም በንስሐ ተወስነው የበረቱትም በቅዱስ ቁርባን ታትመው ከሆነ ከደጉ ዘመን ይደርሳሉ ደጉንም ንጉሥ ያያሉ፡፡ ሁለተኛው በደዌ፣በአጋንንት እና በተለያየ ነገር ተይዘው ዘመናቸውን በመከራ በገዳማት በአድራት የሚገፉ ናቸው፡፡ ሦስተኛ እውነተኛ የእግዚአብሔር ፍቅር አገብሯቸው ቃለ እግዚአብሔርን ለመማር የሚንከራተቱ ተማሪዎች ናቸው ይላሉ፡፡

ቴዎድሮስ ከመምጣቱ በፊት አሕዛብ ከጸለይን ለሦስት ወር ይገዙናል ካልጸለይን ለሦስት ዓመት ይገዙናል ይህ እንዴት ይሆናል?

ተወዳጆች ሆይ ከላይ እንዳየነው በገድለ ቅዱስ ፊቅጦር ላይ ‹‹የአሕዛብ ጥቂት ዘመን›› ያለው ነው፡፡ ይህም የሚሆነው አሁን ባለው የፖለቲካ ምህዳር እንደ ግብጽ የሃይማኖት ፓርቲን በማቋቋም ስም ነው አሕዛብ ወደ መንበሩ የሚመጡት፡፡ የፖለቲካ ፓርቲን በሃይማኖት ከባ በመሸፈን በመምጣት ወንበሩ ላይ በመውጣት ሊገዙን ብሎም ሊያስጨንቁን ይችላሉ፡፡ እንዲሁም አሕዛብ ሰው ወደ መሪነቱ በመምጣት በመሪነት ስምና ሽፋን የአሕዛብን ሃይማኖት በማስፋፋት ይገዙናል፡፡ ግን ይህ ከበረታን በጸሎት የሚያልፍ ነው፡፡ በርትተን ካልጸለይን ግን የትንቢቱ ሰለባ በመሆን ወደ እግዚአብሔር አልጮህ ብለን ወደ አሕዛብ እንጮኻለን፡፡

አገዛዛቸውም እንደ ሴት ልጅ ምጥ ነው፡፡ የሴት ልጅ ምጥ እሷም ባልዋም ቤተሰቦችዋም ከአሁን አሁን ወለደች ወይስ ሞተች ብለው እንደሚጨነቁ ሁሉ እነሱ ወደ መንበሩ ከመጡ የሃይማኖት እና የአምልኮት ነጻነት በማጣት ከዛሬ ነገ ፈጁን ገደሉን በማለት በስጋት ስለምንኖር ነው ጭንቀታችን መከራችን በሴት ልጅ ምጥ የተመሰለው፡፡ ትንቢቱም ‹‹የኢትዮጲያ ሕዝብ ከጸለየ የመከራውን ዘመን ሦስት ወር አደርግለታለሁ ካልጸለየ ግን ሦስት ዓመት ይሆናል›› የሚል ነው፡፡ ስለዚህ ትንቢት ስለ ተነገረለት የአሕዛብ መንግስት እና አገዛዝ እድሜውን ማሳጠርም ማስረዘምም ብሎም ማሳለፍ የምንችለው እኛው ነን፡፡

በመከራው ዘመን የመከራው ትንቢት መፈጸምያ የመከራው ማብረጃ እነማን ናቸው?

ወዳጆቼ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ እንደሚነግረን በሁለቱ የመከራ ዘመናት የመከራው እሳት ያቃጠላቸው መከራው ይመጣል እየተባለ እየተነገራቸው ጆሮ ዳባ ልበስ ብለው በኃጢአት በመርከስ የኖሩት ናቸው፡፡ ለዚህም እንደ ምሳሌ ብናይ በኖኀ ዘመን ለንስሐ የተሰጣቸውን አድሜ እና እድል ሳይጠቀሙት የቀሩት ከወጣት እስከ አዛውንት ያሉት በሙሉ በጥፋታቸው የጥፋት ውኃ አንፍሮ ገሏቸዋል፡፡ እነሱ በንስሐ ወደ እግዚአብሔር አልመለስም በማለታቸው የእነሱ ዕዳ ለሕፃናትም ተርፎ እነሱም አልቀዋል፡፡ እንዲሁም በሎጥ ዘመንም ዘማውያን ግብረ ሰዶማውያን በእሳት ተቃጥለው አልቀዋል፡፡ ይህ የሚያሳየን ኃጢአት ሠርቶ ኃጢአቱን ትቶ በንስሐ ሳይዘጋጅ የሚኖር የመከራው ማብረጃ እና የትንቢቱ ሰለባ ይሆናል፡፡

በተለይ ወጣቱ ከቤቱ እንደ ወጣ መቅረቱ አይቀርም ይላሉ፡፡ እራሳቸውን በንስሐ ያላዘጋጁ፣ከእግዚአብሔር ጋር በጸሎት ያልተወዳጁ የመከራው ማዕበል ያሰጥማቸዋል፡፡ በዝሙት የሚደሰቱ በአጠቃላይ በኃጢአት ፈጣሪን የሚያሳዝኑ የሚነደው እሳት ይበላቸዋል ከደጉ ዘመንም ሳይደርሱ ሞት ይቀድማቸዋል፡፡ ወዳጆቼ ጊዜው ደርሶ ሞት ቀድሞን በሥጋ ከደጉ ዘመን ሳንደረስ፣በነፍስ የእግዚአብሔር ዘላለማዊ መንግስት ሳንወርስ እንዳንቀር ንስሐ እንግባ ወደ ፈጣሪም እንመለስ፡፡

ንጉሥ ቴዎድሮስ ከመምጣቱ በፊት አራቱ ታላላቅ መከራዎች ይመጣሉ እነሱ ምንድን ናቸው?
ቴዎድሮስ ከመምጣቱ በፊት ሊመጣ ያለው ግድ የሆነው መከራ አሉ፡፡ እነሱም ሞት፣ረሃብ፣በሽታ፣ጦርነት ናቸው፡፡

ሞት ፦ ሞት የተባለው በተለይ የወጣቶች ሞት ይበዛል፡፡ ደማቸውም በከንቱ ይፈሳል፡፡ ከሞት እና በግፍ ከሚፈው የወጣቶች ደም የተነሳ አስከሬን እስኪረገጥ ደም እንቦጭ እስኪል ነው፡፡ ንስሐ ያልገቡት በጸሎት ወደ ፈጣሪ ያልተመለሱት ለሞት ሲሳይ ይሆናሉ፡፡ ቀባሪው ግራ ይጋባል ማንን ቀብሬ ማንን ልተው ይላል፡፡ አንዱ የአንዱን ለቅሶ አይደርስም የሚያላቅሰውም አያገኝም፡፡ ለቀስተኛውም ለቅሶ ማዳረስ ያቅተዋል፡፡

ረሃብ ፦ በድርሳነ ዑራኤል ላይ ‹‹አመድ ከሰማይ ይዘንባል›› የተባለው ከሰማይ የተዘዘ ክፉ ረሃብ እና መከራ ናቸው፡፡ ረሃቡ በሀገራችን ታሪክ ታይቶ እና ተሰምቶ የማይታወቅ ነው፡፡ እስራኤላውያን በረሃም ዘመናቸው የአህያ ጭንቅላት ገዝተው በልው ነበር፡፡ እግዚአብሔር ሲቆጣ የናቅኸውን በጭራሽ ያላሰብከውናን ልታስበው የማትችለውን ለረሃብህ ሊያደርግብህ ይችላል፡፡ እኛም እስራኤል ዘነፍስ ነንና ካልጸለይን እየነሱን የጥንት ጽዋ መጠጣታችን አይቀርም፡፡

አንዳንድ ሞኞች ረሃቡ ክፉ ነውና የማይነቅዝ እህል ገዝታችሁ አስቀምጡ ለረሃቡ ዘመን ይሆናችኃል እየተባሉ እህል እየገዙ የሚያስቀምጡ አሉ፡፡ ምን አለ እህል ከሚገዙ ልብ ቢገዙ፡፡ ወዳጄ አንተ ገንዘብ ስላለህ በገንዘብህ የማይነቅዝ እህል ገዝተህ ጎተራህን ትሞላ ይሆናል፡፡ ግን ምንም የሌለው ድኃ የረሃቡ ዘመን አንተን ነው የሚበላህ፡፡ የማይነቅዝ እህል ገዝተው ግን በኃጢአት የነቀዙ ያን የመከራ ዘመን አያልፉትም። ደግሞስ እንደ ሽኮኮ ቤትህን ዘግተህ እየበላህ የረሃቡን ዘመን የምታልፍ ይመስልሃል? በፍጹም፡፡ የረሃቡ ዘመን የሚያልፈው የማይነቅዝ እህል በማስቀመጥ ሳይሆን ተባብሮ በመጸለይ ነው፡፡

ደግሞም አትርሳ ጌታ አምላከ ነደያን ነው የተባለው፡፡ የነደያን አምላክ ድሆችን አይተውም፡፡ እህል ብታከማችም ያከማቸኸውን የሚያስበላህ ዘመን ይመስልሃል? ያለ ጸሎት ያከማቸኸው እህል የድሆች ቀለብ ሊሆን ይችላል፡፡ በር ዘግተን የምንበላበት የረሃብ ዘመን ከሆነማ ቤትህ የድሆች የጨረባ ተስካር ይሆናል፡፡ በዛን ዘመን የሚያስበላን ሲኖር ነው እየበላን ዘመኑን የምንገፋው የምናልፈው፡፡ በቤታችሁ እህል ከምታከማቹ የጽድቅ ሥራ አከማቹ እሱ ነው በክፉ ዘመን ማለፊያ ቀለብ የሚሆናችሁ፡፡ በኃጢአት ስንጨማለቅ ከርመን እህል አከማችተን የመከራውን ዘመን ልናልፍ? አሄሄ ….

በሽታ ፦ በሽታ የተባለው ተላላፊና ወረርሽኝን ጨምሮ ነው፡፡ ረሃቡን ባስቀመጥነው እህል እናልፋለን ብለን በሥጋ ብንጠበብ ከገዳይ በሽታ እና ከወረርሽን ላናመልጥ እንችላለን፡፡ ለዚህም ነው ጊዜው የሚያልፈው እህል በማከማች ሳይሆን በጸሎት ነው የምለው፡፡ ወረርሽን ሰውን እንደ ቅጠል ያረግፋል ብዙዎችንም ይገድላል ግን በጸሎት ያልፋል፡፡ ካልጸለይን በረሃብ ብቻ ሳይሆን በበሽታም እንወረራለን፡፡

ጦርነት ፦ ጦርነት የተባለው ሁለት ነው፡፡ አንደኛው ከውጭ በሚመጣ በወራሬ ኃይል ሲሆን ሁለተኛው ከውስጥ ነው፡፡ ወራረው ሃይማኖችን ተገን አድርጎ የሚመጣ ነው፡፡ የውስጡ ሃይማኖትንና ብሔርን ተገን ያደረገ ነው፡፡ በዚህም ከፍተኛ የእርስ በእርስ ጦርነት ሊነሳና ብዙዎች ሊያልቁ እና ሊዋደቁ ይችላሉ፡፡ ይህም የሚያልፈው በጸሎት ነው፡፡ የሃይማኖቱንና የብሔሩን የጦርነት ዋዜማ በየቦታው እያየን ነውና መጸለዩ ስለሚያሳልፈው እንጸልይ፡፡

ይህ ሁሉ ትንቢት ይፈጸማል ወይስ ያልፋል?
ተወዳጆች ሆይ ትንቢት በባሕርይው ይፈጸማል ይልፋል፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተነገሩት ትንቢቶች የተፈጸሙ አሉ፡፡ ወደ ፊት የሚፈጸሙም አሉ፡፡ የሚያልፉም አሉ፡፡ ከላይ ያየናቸው ትንቢቶች ይፈጸማሉ ወይስ ያልፋሉ ለሚለው እድሉ ያለው በእኛ እጅ ነው፡፡ እኛ ከጸለይን ጌታችን የሚመጣውንና ሊመጣ ያለውን ትንቢት ያሳልፋል፡፡ ግን ይህ የሚሆነው በብርቱ ጸሎት እና ምህላ ነው፡፡ ለምሳሌ የነነዌን ትንቢት ብንመለከት ያቺ ከተማ ከነ ሕዝቦችዋ እንደ ትንቢትዋ ቢሆን አትተርፍም ነበር፡፡ ግን እግዚአብሔር የነነዌን ሕብዝ ጸሎት እና ብረቱ ጩኸት ሰምቶ ከተማዋም ሕዝቡም ከተነገረለት ትንቢት ተርፏል፡፡

እግዚአብሔር በዳዊት ላይ በተቆጣ ጊዜ መልአኩን ልኮ ኢየሩሳሌምን እንዲያጠፋት አዞ ነበር፡፡ ግን እግዚአብሔር የዳዊትን ጸሎት እና ጩኸት በማየት በመጸጸት ኢየሩሳሌምንና ሕዝቧን ሊያጠፋ የላከውን መልአክ መልሶ ‹‹በቃህ አሁን እጅህን መልስ›› አለው፡፡ /1ኛ ዜና 21÷15/ ዛሬም እንደ ዳዊት ወደ እግዚአብሔር በጸሎት ከጮኽን እግዚአብሔር ተጸጽቶ ‹በቃችሁ›› ይለናል፡፡ ስለዚህ ትንቢቱ እንዲፈጸም እና እንዲያልፍ የምናገደርገው እኛው ነን፡፡ እንዲሁም ንጉሥ ሕዝቅያስን እግዚአብሔር ‹‹ትሞታለህ እንጂ በሕይወት አትኖርምና ቤትህን አስተካክል›› ብሎ በነብዩ ኢሳያስ አንደበት ቢነግረውም የሕዝቅያስን ጸጸት ለቅሶ እና ጸሎት የተመለከተው እግዚአብሔር በሞት ከተቆረጠ ቀኑ ላይ አሥራ አምስት ዓመት ጨምሮለታል፡፡ /ት.ኢሳ 38÷1/
እኛም ከዚህ ሁሉ ሊመጣ ካለው ትንቢት ከጸለይህ እግዚአብሔር ሞታችንን ወደ ሕይወት ይቀይረዋል፣በሞት በተቆረጠው እድሜያችን ላይ ሌላ እድሜ ይሰጠናል፡፡ ለዚህም ነው ትንቢት በጸሎት ያልፋል ያልኳችሁ፡፡

ንጉሥ ቴዎድሮስ መቼ ነው የሚመጣው?

ተወዳጆች ሆይ ብዙዎችን የሚያጓጓ ይሄ ጥያቄ ነው፡፡ አንዳንዶች የሚመጣበትን ዓመተ ምህረት ጠቅሰው እርግጠና ሆነው ይጽፋሉ ይናገራሉ፡፡ ግን የንጉሥ ቴዎድሮስን መምጣት የምናስተዝመው፣የምናዘገረው የምናቀርበውም እኛው ነን፡፡ ዓመተ ምህረቱ ይህ ነው ባይባልም ቅርብ መሆኑ ግን እርግጠኛ ነው፡፡ ምክንያቱም ከመምጣቱ በፊት የሚመጡት መከራዎች፣መሻገሪያ ድልድዮች እየታዩ ስለሆነ በተስፋ መጠበቁ ያዋጣል፡፡

እግዚአብሔር ሰውን እያማከረ አይሠራም የሚሠረውን ሥራ ለቅዱሳን ወዳጆቹ ይነግራል፣ የሚመጣውን ይገልጻል፡፡ አንዳንዶች ከእግዚአብሔር ጋር ሲመካከሩ የከረሙ ይመስል ዓመተ ምህረቱ ይህ ነው እያሉ እርግጠኛ ይሆናሉ፡፡ ግን ቴዎድሮስ ከመምጣቱ በፊት የሚመጡ ብዙ ነገሮች መኖራቸው እሙን ነው፡፡ ስለዚህ መምጫውን እግዚአብሔር ነው የሚያውቀው ከእኛ የሚጠበቀው ይህንን የመከራ ዘመን አሳልፈኸን ከደጉ ንጉሥ እና ከኢትዮጲያ የትንሣኤ ዘመን አድርሰኝ ማለት ነው፡፡ ግን ሩቅ እንዳልሆነ ቅርብ እንደሆነ እወቁ፡፡

በኢትዮጲያ አይደለም ጠማማ ትውልድ ጠማማ እንጨት አይኖርም/ይህ ትንቢት የሚፈጸመው በዘመነ ቴዎድሮስ ነው/

የትንሣኤው ዘመን በረከት እና ቡራኬ

ተወዳጆች ሆይ እድሜ ቢሰጠን ከደጉ ዘመን ከቴዎድሮ ቢያደርሰን ዘመኑ ‹‹አይደለም ጠማማ ትውልድ ጠማማ እንጨት አይኖርም›› የተባለለት ነው፡፡ ይህ የንጉሡን ደግነት የሚያሳይ ነው፡፡ ይህም የትንሣኤው የብሥራት ቃል ነው፡፡ በዘመኑ የእህል በረከት ይትረፈረፋል፣ በጥቂት እህል በረከት ሰው ሁሉ ይኖራል፡፡ የጤና በረከት አለው ታማሚ ይጠፋል፡፡ መተት ይሻራል ጠንቋን አስጠንቋይ ይበናል፡፡ መታች እና አስመታች አብረው ይጠፋሉ፡፡ የእድሜ በረከት አለው ሁሉም ዘለግ ያለ ዘመን ይኖራል፡፡ ከሀገራችን የወጡት ሁሉ ወደ ሀገራቸው ይመለሳሉ፡፡ ኢትዮጲያም ልዕለ ሀያል ሀገር ትሆናለች፡፡ የዓለም ዓይን ሁሉ ወደ እሷ ይሆናሉ፡፡ መሬትዋን ለመርገጥ የውጭ ሀገር ዜጎች ይጎርፋሉ፡፡ ፍቅር እንደ ሸማ ይነጠፋል፣ሰው ከሰው ጋር በአንድነት በመግባባት ይኖራል፡፡

ሃይማኖት ይስፋፋል፣እምነት በሰው ልብ ሰርጾ ይጠነክራል፡፡ ‹‹ኢትዮጲያ እጆችዋን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች›› የሚለው የዳዊት ትንቢት በግልጽ የሚፈጸመው ያኔ ነው፡፡ /መዝ 68÷31/ በዘመኑም ‹‹ፀሐይ›› የተባለው ጳጳስ ይነሳል፡፡ እሱም በጸሎቱ ኦርቶዶክስን ይመራል በቡራኬውም በረከትን ለሰዎች ይሰጣል፡፡ ንጉሡ እና ጳጳሱ ኢትዮጲያንና ኤርትራን አንድ ያደርጓቸዋል፡፡ በአንድነትም እንኖራለን፡፡ ጥላቻ ዘረኝነት ይጠፋል፡፡ ረሃብ፣በሽታ፣ጦርነት እስከ መኖሩም ይረሳል፡፡ ብቻ ከደጉ ዘመንና ንጉሥ የደረሰ ብዙ ያያል፡፡ ለዚህም ነው አባቶቻችን ስትጸልዩ ‹‹ከደጉ ዘመንና ከደጉ ንጉሥ አድርሰን በሉ›› የሚሉን፡፡ የአባቶቻችን አምላክ ከደጉ ዘመን ያድርሰን!

Share on Google Plus

ስለ የተለጠፈበት ቀን

    Blogger Comment
    Facebook Comment