የኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር አምስት ስያሜዎች አሉት


✍ ይታገሡ በቀለ | ኢትዮጵያ አውታር | ሰላቢ እጆች

1. ኀሳበ ዘመን

ኀሳበ ዘመን ሲባል የዘመናትና የዓመታት፣ የወራትና የሳምንታት፣ የዕለታትና የሰዓታት የመሳሰለው የድቁቅና ደቃቅ ጊዜያት ሁሉ ይጠቃለሉበታል፡፡ አዎን እነዚህ ሁሉ በሐሳብ ተመርምረው፣ ተመዝነው፣ ተሰፍረው፣ ታውቀው፣ ተቈጥረው ሲያበቁ ምድብና ቀመር ተሰጥቶአቸው የሚገኙበትን ውሳኔና ድንጋጌ እያሰማ የሚጠራበት ትምህርታዊ ስያሜ ነው፡፡ ሃሳብንስ ቁጥር የሚል ምን ምስክር አለ ቢሉ “ኢትትሐሠብዎሙ ወርቆሙ ለእለ ይገብሩ እስመ በሐይማኖቶሙ ይገብሩ”

2. ባሕረ ሐሳብ

ይህ የዘመን አቈጣጠር ድንጋጌ (ባሕረ ሐሳብ) ተብሎ ይጠራል፡፡ ባሕረ ሐሳብ መባሉም በባሕር ምሳሌ ነው፡፡ “እስመ በመዳልው ደለወ ዓለመ ወበመስፈርት ሰፈራ ለባህር” እንዳለ እነሆም ባሕር ጥልቀትና ስፋት የሚታይበት ሲሆን እውስጡ ያሉትን ስፍር፣ ቁጥር የሌላቸውን የተለያዩ ነገሮች ዓይነትና ብዛት እያመላከተ የራሱ አቋም ይገልጻልና እንደዚሁ ታስቦ የተሰጠው ስያሜ ነው፡፡ መዝ.103/104/25፣27

3. አቡሻክር

የዘመን አቈጣጠር (አቡሻክር) እየተባለ የሚጠራበት ጊዜ አለ፡፡ ይኸውም የኀሳበ ዘመንን ትምህርት ካዘጋጁ ሊቃውንት አንዱ ዮሐንስ አቡሻክር ስለሆነ የእርሱ የሐሳብ አቈጣጠር መንገድ በኢትዮጵያውያን ሊቃውንት ዘንድ የተወደደ በመሆኑ የኀሳበ ዘመን ድንጋጌ በዚሁ ሊቅ ስም ስለሚጠራ ነው፡፡

4. የቁጥር ትምህርት

የዘመን አቈጣጠር ፈሊጥ (የቁጥር ትምህርት) ተብሎ ኢትዮጵያዊ በሆነ በከፍተኛ የትምህርት ሙያ ራሱን የቻለ ቀዋሚ መምመህር /ጉባኤ/ መደብ ተሰጥቶት ስለሚገኝ የቁጥር ትምህርትም ተብሎ ይጠራል፡፡

5. ዘመነ ዓለም

የዘመን አቈጣጠር (ዘመነ ዓለም) ተብሎ የሚጠራበት ጊዜም አለ፡፡ ይኸውም የሰው ልጅ ማለት ዓለመ አዳምን በሚመለከት ታሪክ የሚቀመረውን የዘመን አቈጣጠር ሲያይ የተሰጠው ስያሜ ነው ዕዝራ ሱቱኤል እዝ. ምዕ.18.10 – 13 በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ስለ ኀሳበ ዘመን ጠባይ ሲነገር ሦስት ሁኔታዎች ተቋጥረውበት እናገኛለን፡፡ እነዚህም፦

1 ኃላፊ ጊዜ (ትማልም)
2 የአሁን ጊዜ (ዮም)
3 ትንቢታዊ (መጻኢ) ጌሠም፡፡

እነሆም ኢትዮጵያዊ የዘመን አቈጣጠር እነዚህ ሦስት ጠባዮች የየጊዜያቱን ታሪክ ኅብረ መልኩን እያሳየ ሲያንጸባርቅ የሚኖር ልዩ ልዩ ቅርንጫፎች ያሉትና ሳይቈራረጥ እግቡ ድረስ የሚዘልቅ መሠረታዊና ታሪካዊ ሐረግ አለው፡፡ እርሱም በቅዱስ መጽሐፍ መሠረት አዳም ከተፈጠረ ጀምሮ እየቀጠለ የሚሄድ ዓመተ ዓለም ወይም የዓመተ ዓለም የዘመን አቈጣጠር ነው፡፡ በዚህ የዓመተ ዓለም የዘመን አቈጣጠር መሠረትነት ጥንታትና አቅማራት፣ አዕዋዳት እና ሠግር፣ አበቅቴና መጥቅዕ፣ የጨረቃ ልደትና ጠፍ፣ የምትሆንበት ሕፀፅ ተወሳክ ሌሎችም ብዙ ሁኔታዎች ሁሉ እንደ ቅርንጫፍ እንደ አጽቅ ውጤት እየሆኑ ይገኙበታል፡፡ ይህም ለእነዚህ ሁሉ የኀሳብ ዘርፎች መነሻና መደረሻ ነው፡፡

ተቃራኒ ሆኖ በመነጻጸር የሚወዳደረው የሌለው ብቻውን የሚጓዝ አንድ መስመር የያዘ አስደናቂ የዘመን አቈጣጠር ሲሆን ይበልጥ ደስ የሚያሰኝ ለአእምሮም ርካታ የሚሰጥ ቀዋሚ ታሪክ አለው፡፡ እርሱም የዘመን አሮጌ በሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመሥርቶ በመገኘቱ ነው፡፡ (ማቴ. 13.53) እንደሚታወቀው ሁሉ ይህን የዓመተ ዓለም የኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር በሁለት ከፍለን የተከፈለ ነው፡-

1፡ ከአዳም እስከ ልደተ ክርስቶስ የነበረውን ዓመተ ፍዳ ወይም ዓመተ ኩነኔ እና

2፡ ከክርስቶስ ልደት ወዲህ ያለውን ደግሞ ዓመተ ምሕረት እንለዋለን፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተጻፈውን የዘመን አቈጣጠር መሠረት በማድረግ አዳም ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ እስከ ክርስቶስ ልደት 5500 ዓመተ ዓለም ነበረ ብላ ታምናለች፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የባሕረ ሐሳብ አቈጣጠር ሐሳበ ሄኖክ ነው ይኸውም መጽሐፈ ሔኖክ ምዕራፍ 21፣ 22፣23 መመልከት ይቻላል፡፡ አንዳንዶችም ሐሳበ ኖኅ የሚሉም አሉ ይኸውም ማየ አይኀ ዘንቦ እስኪደርቅ የነበረው ጊዜ 150 ቀናት ስለነበረም 150ቀናት ሲቀመር በ30 ቀናት በመሆኑ ነው፡፡ በዚህም አለ በዚያ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ባሕረ ሐሳብ አዳም ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ ስለሚቈጠር ማዕከሉ መጽሐፍ ቅዱስ ነው፡፡

Share on Google Plus

ስለ የተለጠፈበት ቀን

    Blogger Comment
    Facebook Comment