✍ ቆሞስ አባ ጳውሊ | ከግንባር
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በረጅም ታሪኳ ውስጥ በርካታ ውጫዊና ውስጣዊ ፈተናዎችን፣ የወረራና የደስታ አብሮነት ጊዜያትን አልፋ እዚህ የደረሰች ታላቅና ጥንታዊት ቤተ ክርስቲያን ናት። ሆኖም ግን ይህች ብቸኛ እውነተኛ መንገድ የሆነች ሃይማኖት በአሁኑ ወቅት እያጋጠማት ያለው እጅግ አደገኛና ውስብስብ ፈተና ምእመናኗና አገልጋዮቿ ከቀኖናና ዶግማ እንዲሁም ከወንጌል አስተምህሮና ከክርስቲያናዊ አንድነታቸው ይልቅ ብሔራቸውን፣ ቋንቋቸውንና አካባቢያዊ ማንነታቸውን በማስቀደማቸው ምክንያት የመጣው ውስጣዊ መከፋፈል ነው። ይህ በብሔርተኝነትና በፖለቲካ አስተሳሰብ የተመረዘ መከፋፈል ምእመናን በመንፈሳዊ ፍቅርና በክርስቶስ አካልነት እንዳይያያዙ በማድረግ እርስ በእርስ እንዲጠራጠሩና ጠንካራ የክርስቲያን ሕብረት እንዳይኖራቸው አድርጓቸዋል። በአሁኑ የኢትዮጵያ ነባራዊ የፖለቲካ ሁኔታ ብሔርን ማዕከል ያደረገው አስተሳሰብ ማኅበራዊውን፣ ኢኮኖሚያዊውንና ሃይማኖታዊውን መስተጋብር በጥብቅ በመቆጣጠሩ የቤተ ክርስቲያን አጥፊዎች ይህንን ደካማ ጎን እንደ መልካም አጋጣሚና ትልቅ ተገን አድርገው ተጠቅመውበታል። ጠላቶችና ኢ-አማንያን ቤተ ክርስቲያንን በአንድ የተወሰነ ብሔር በተለይም "የአማራ ሃይማኖት" ወይም "የአማራ ተቋም" አድርገው በመሳል የሌሎች ብሔረሰቦች ተወላጆች (ለምሳሌ የኦሮሞ፣ የትግራይና ጉራጌ ደቡብ ወዘተርፈ የሌሎችም ብሔር ብሔረሰቦች ተወላጆች) ዘንድ ጥላቻ፣ ባዕድነትና የባለቤትነት ስሜት ማጣት እንዲሰማቸው በስልት እያደረጉ ይገኛሉ። በዚህ የጠላቶቻችን ከፋፈለህ ግዛው ስልት ምክንያት ቤተ ክርስቲያን ከመንግሥት አካላትም ሆነ ከተለያዩ አጥፊዎች ጥቃት፣ መከራና ውድመት ሲደርስባት በአንድነትና በጽናት ቆሞ የመመከትና የመከላከል መንፈሳዊ አቅም አጥታለች::
እጅግ አሳዛኙና አስደንጋጩ ነገር ደግሞ በብሔር ጥላቻ የተወጠሩና መንፈሳዊ አስተዋይነታቸውን ያጡ በርካታ ወገኖች ቤተ ክርስቲያን ስትጠቃ፣ ታሪካዊ ሕንፃዎቿና ገዳሞቿ ሲቃጠሉ፣ ካህናት፣ መነኮሳትና ምእመናን ሲገደሉና ሲፈናቀሉ ጉዳቱ የቤተ ክርስቲያን ሳይሆን የዚያ የተጠላው (የጠሉት ብሄር) እንደሆነ አድርገው ስለሚያስቡ በደስታና በቸልተኝነት መመልከታቸው ነው። የብሔር ማንነት መንፈሳዊውን ዓይናቸውን ስላወረወረው የክርስቶስ ደም የተከፈለባትን ቤተ ክርስቲያን መጎዳት ጠላቶች እንደ አቅጣጫ ማስቀየሪያ የፖለቲካ ድል አድርገው ይቆጥሩታል። አጥፊዎች ይህን የሕዝቡን የብሔር ክፍፍልና የመንፈሳዊ ንቃት ማነስ ተገን በማድረግ ቤተ ክርስቲያኗን በስልታዊ መንገድ የማዳከም፣ ታሪካዊና መንፈሳዊ ሀብቷን የማውደም፣ እንዲሁም ሀገራዊና መንፈሳዊ ሚናዋን ሙሉ በሙሉ የማጥፋት ዘመቻቸውን አፋጥነውታል። ይህ አካሄድ ቤተ ክርስቲያኗን አጠቃላይም የመላው ምእመናንን መንፈሳዊ ሕይወትና የነገ ዕድል ፈንታ በእጅጉ የሚጎዳ ነው። ክርስቲያኖች በቋንቋና በብሔር ተከፋፍለው እርስ በእርስ ሲጠቃቀሱና የቤተ ክርስቲያንን መጎዳት በዝምታ ሲመለከቱ ጥቃቱ ተራዝሞ በየደጃፋቸው ከመድረስ አይመልስም። አጥፊዎች ለጊዜው አንዱን ብሔር ጠላት አድርገው በመሳል ሌላውን ቢደልሉም የመጨረሻ ግባቸው ግን የክርስቶስን ስም ከምድር ማጥፋትና የቤተ ክርስቲያንን ህልውና ማክሰም ነው። ይህን ደግሞ በመላው ዓለም እየሰሩበት ሲሆን የእኛ ድክመት ውጤታማ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል:: ስለዚህ ይህንን ድብቅ አጀንዳ ተረድቶ በወቅቱ አለመነሳት መከራው በየተራው ሁሉንም እንዲያገኘው መንገድ መክፈት ነው።
ይህንን ዘመናዊና አደገኛ ፈተና ለማሸነፍ ሁላችንም የክርስትናን መሠረታዊ አስተምህሮ ማስታወስ፣ ከጥላቻ አስተሳሰብ መንጻትና ወደ ቀደመው መንፈሳዊ ማንነታችን በአስቸኳይ መመለስ አለብን። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ "በክርስቶስ ኢየሱስ ያለው ሁሉ አንድ ነው እንጂ አይሁዳዊ ወይም የግሪክ ሰው የለም" (ገላትያ ፫:፳፰) እንዳለው በክርስቶስ ደም የተገዛን ምእመናን ሁላችንም የአንዲት ቤተ ክርስቲያን አካላት ነን። በሰማይ ብሄራችን አያጸድቀንም! ክርስቲያን ቢሄር የለውም:: እኛ ሰማያዊያን ነንና ይህን ለክርስትና ሃይማኖት ጸር የሆነን ክፍፍል ማስወገድ አለብን:: ምድራዊ ብሔራችን፣ ቋንቋችንና ባህላችን ጊዜያዊና ምድራዊ ሲሆኑ ቤተ ክርስቲያን ግን የዘላለም ቤታችንና የሰማያዊቷ ኢየሩሳሌም ጥላ ናት። ስለዚህ ማንኛውንም የፖለቲካና የብሔር ልዩነት ወደ ጎን ትተን ስለ ቤተ ክርስቲያን ህልውናና አንድነት ስንል በአንድ ልብና በአንድ መንፈስ መቆም ይኖርብናል። ቤተ ክርስቲያን የአንድ ብሔር ብቻ ሳትሆን የሁሉንም ብሔር፣ ቋንቋና ነገድ ልጆች እኩል የምታቅፍ የክርስቶስ አካል መሆኗን በተግባር ማሳየት ያስፈልጋል። አገልጋዮችና ምእመናን በየአካባቢያቸው በሚነገሩ ቋንቋዎች ሁሉ ወንጌልን በማስፋፋት፣ ሥርዓተ አምልኮን በየቋንቋው በማቅረብና የአካባቢውን ማኅበረሰብ በማቀፍ ቤተ ክርስቲያን የሁሉም አባትና እናት መሆኗን በጥበብ፣ በትምህርትና በጥሩ አርአያነት ማረጋገጥ አለባቸው። በሕዝቡ ዘንድ የገባውን የብሔር ጥላቻና መጠላላት መፈወስ የሚቻለው በመንፈሳዊ ትምህርትና በፍቅር ብቻ ነው። የሌላው ወንድም ሕመም የእኔ ሕመም ነው የሚለውን የሐዋርያት ዘመን ሕብረትና የመተሳሰብ መንፈስ በጥልቅ ማደስ ያስፈልጋል። ቤተ ክርስቲያን በየትኛውም የአገሪቱ ክፍልና በማንኛውም ማኅበረሰብ ዘንድ ስትጠቃ ጥቃቱ በሙሉ አካሏና በራሳችን ላይ እንደደረሰ ተረድቶ በአንድ ድምፅ ማወገዝ፣ መጠበቅና አብሮ መቆም የሁሉም ክርስቲያን ሃይማኖታዊና መንፈሳዊ ግዴታ ነው።
የቤተ ክርስቲያን አበው ጳጳሳት፣ ካህናትና አገልጋዮች ከፖለቲካዊና ከብሔርተኝነት አስተሳሰቦች ሙሉ በሙሉ ነፃ በመሆን የመንፈሳዊ አባትነታቸውን ድርሻ መወጣት አለባቸው። አሁን በዋናነት ቤተክርስቲያንን እየፈተናት ያለው አገዛዙ የቤተክርስቲያንን አባቶች ለጥፋት እየተጠቀመባቸው በመሆኑ ነው:: አገዛዙ ክርስቲያኑ እንዲበታተን ስለሚፈልግ ዘረኛ አባቶችን ወደፊት በማስቀደም እቅዱ እንዲሳካለት እያደረገ ነው:: አባቶች ሆይ ምእመናንን በክርስቶስ ፍቅር ማስተሳሰር እንጂ በብሔርና በቋንቋ ከፍሎ ማየት የክርስቶስን መንጋ ለተኩላ አሳልፎ መስጠት ነው። አገልጋዮች የወንጌልን እውነት ብቻ በመስበክ የሕዝቡን ልብ ወደ እግዚአብሔር የመመለስ ታላቅ ኃላፊነት አለባቸው። ምእመናን በየአካባቢያቸውና በዓለም ዐቀፍ ደረጃ በብሔር ሳይሆን በሃይማኖታቸውና በክርስቲያናዊ ማንነታቸው ተደራጅተው ቤተ ክርስቲያናቸውን የሚያገለግሉበት፣ ሕግን መሠረት አድርገው መብታቸውን የሚያስከብሩበትና አብረው የሚቆሙበትን ጠንካራ መዋቅር መገንባት አለባቸው። ከእነዚህ መንፈሳዊና ማኅበራዊ መፍትሔዎች ጎን ለጎን ሌላው እጅግ አስፈላጊና ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው መፍትሔ የክርስቲያኑን የኢኮኖሚ አንድነትና ትስስር ማጠንከር ነው። ክርስቲያኑ በድህነት እየሟቀቀ እንደ ኤሳው ብኩርናውን (ሃይማኖቱን) በጥቅም እየለወጠ ነው:: ዘፍ. ፳፭፥፳፱-፴፬ አብዛኛዎቹ ክርስቲያኖች ከመንግሥት ጋር ሆነው እያጠፏት ያሉት በጊዜያዊ ጥቅምም በመታለል እንደሆነ አንዘንጋ!
በአሁኑ ወቅት በአብዛኛው የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ የሚታየው ትልቅ ክፍተት ጠንካራ የኢኮኖሚ ትስስር አለመኖሩ ነው። ብዙ ጊዜ ምእመናን በንግድና በማኅበራዊ እንቅስቃሴዎቻቸው ወቅት ከሌሎች ኢ-አማንያን ጋር የመገበያየት፣ የመግዛትና የመሸጥ ልማድ ያላቸው ቢሆንም ከራሳቸው ወንድሞችና እህቶች ከሆኑ ክርስቲያኖች ጋር ግን በንግድ የመደጋገፍ፣ እርስ በእርስ የመጠቃቀምና የመረዳዳት ፍላጎት ሲያንሳቸው ይታያል። ይህ አመለካከት ደግሞ ክርስቲያኑ በኢኮኖሚ አቅሙ ዝቅተኛ እንዲሆን፣ የንግድ ትስስሩ እንዲላላና እውነተኛ እህት-ወንድማዊ ትስስር ውስጥ እንዳይገባ አድርጎታል።ስለሆነም ይህንን የኢኮኖሚ ክፍተት ለመድፈንና ጠንካራ የኢኮኖሚ ጉልበት ለመገንባት ብሎም የንግድና የጥቅማ ጥቅም ነገሮችን ከክርስቲያናዊ አንድነት ጋር ማስተሳሰር ወሳኝ ነው። ምእመናን እርስ በእርስ የመጠቃቀም፣ የክርስቲያን ነጋዴዎችንና ባለሙያዎችን የመደገፍ፣ እንዲሁም በጋራ የንግድና የኢንቨስትመንት መድረኮች የመደራጀት ባህልን ማሳደግ አለባቸው። ክርስቲያኑ በኢኮኖሚ የተሳሰረና የካፒታል አቅም ያለው ሲሆን የቤተ ክርስቲያንን ዘመናዊና ታሪካዊ ቅርሶች ለመጠበቅ፣ ለጉዳት የተዳረጉ ምእመናንንና አገልጋዮችን ለመደገፍ፣ እንዲሁም ቤተ ክርስቲያን ጥቃትና ፈተና ሲደርስባት በገንዘብ፣ በሀብትና በቴክኖሎጂ አቅም መመከት የሚያስችል ትልቅ መከላከያ ይፈጥርለታል። በመሆኑም የኢኮኖሚ አንድነትና ትስስር የቤተ ክርስቲያናችንን ህልውና የማስጠበቂያና የማጠናከሪያ ዋና መሠረት ተደርጎ ሊወሰድ ይገባል። ይህንን ሁላችንም በመገንዘብ ለሃይማኖታችን ስንል ሁሉን መስዋዕት እየከፈልን የሚጠበቅብንን ሁሉ ማድረግ ይኖርብናል:: በአጠቃላይ የቤተ ክርስቲያን ጥፋትና መዳከም የሁላችንም ውድቀት ነው። ምድራዊ ማንነታችን፣ ፖለቲካችን፣ ሀብታችንና ብሔራችን የሚያልፉ ናቸው፤ ቤተ ክርስቲያን ግን ለዘላለም ትኖራለች። ስለዚህ አሁን ያለውን የከፋፈለንን የጥላቻና የብሔር ግንብ በአስቸኳይ አፍርሰን በክርስቶስ ፍቅርና በአንድነት ታስረን የሰማያዊቷን ቤታችንን የቤተ ክርስቲያንን ህልውና ከመቼውም ጊዜ በላይ በጋራ ልንጠብቃት፣ ልንከላከላትና ለተተኪው ትውልድ ልናስረክባት ይገባል። ቤተክርስቲያን ትልቅ ፈተና ላይ ስለሆነች መንቃት አለብን:: በዚህ እንዝላልነታችን ከቀጠልን እንደ መካከለኛውና ሩቅ ምስራቅ ሀገሮች ኢትዮጵያም የክርስቲያን ሀገር ነበረች እየተባለ ነገ በታሪክ ይሳለቁብናል:: እኛም ጠፍተን መጭው ትውልዳችንንም ለጨለማ አሳልፈን ሰጥተን እንዳናልፍ የምንነቃበት ጊዜው አሁን ነው:: ቤተክርስቲያንን እንጠብቅ፤ ቤተክርስቲያንን ለመታደግ ደግሞ ኢትዮጵያን ከህመሟ እንፈውሳት:: ኢትዮጵያና ቤተክርስቲያን የአንድ ሳንቲም ገጽታዎች ስለሆኑ ሁለቱም በእኛ ኅብረት ከውድቀታቸው መነሳት አለባቸው:: ቤተክርስቲያንን የሚጠሉ ሁሉ ኢትዮጵያንም ይጠላሉ ፤ ምክንያቱ ለሁላችሁም ግልጽ ስለሚመስለኝ ማብራራት አይጠበቅብኝም! ስለዚህ ኢትዮጵያን ከውድቀት የሚያነሳትም የክርስቲያኖች ኅብረት እንደሆነ ልብ በሉ! በአሁኑ ሰዓት በአምባገነኖች ምክንያት በመላው ዓለም ሠላም ሊሰፍን ያልቻለው እግዚአብሔርን ስላራቅነው ሃይማኖት ስለጠፋ ነው:: ሃይማኖታችንን ከጠበቅን ሰላም በእጃችን ነው! መዝ. ፻፳፯፥፩ “እግዚአብሔር ከተማውን ካልጠበቀ ጠባቂው በከንቱ ይተጋል።” ከዚህ ከዳዊት መዝሙር እንደምንረዳው ሀገር ሰላም የምትሆነው ትውልዱ ከእግዚአብሔር ጋር ሲኖር ብቻና ብቻ መሆኑን ነው!
ድል ለቤተክርስቲያን ድል ለኢትዮጲያ!
Blogger Comment
Facebook Comment