ይድረስ ለእውነተኛ ኢትዮጵያውያን:- የኢትዮጵያ ትንሣኤ እስኪረጋገጥ ድረስ እንደ ቅዱስ ገብርኤል "ንቁም በበህላዌነ" ብላችሁ ጽኑ! አይቀርም!


በየመድረኩ የምናያቸው አንዳንድ የሁሉም የሃይማኖት አባቶች፣ እንዲሁም ሳያውቁ ያወቁ የሚመስላቸው ሁሉም የታሪክ ተመራማሪዎች፣ ጸሐፊዎች ምሁራን ነን የሚሉ የፖለቲካ አክቲቪስቶች የሚሰሩት ሥራ በእውነት ወዴት እየወሰደን ይሆን? ታሪክ ለምን ይጻፋል? ለማን ይጻፋል? እውነትስ የት አለች?  ኢትዮጵያዊነትንስ እስከምን ድረስ ነው የምትረዱት? ሃይማኖትን ከሃገር ሃገርን ከሃይማኖት የምታጣርሱትስ እስከመቼ ድረስ ነው?  በህዝብ ደም የምትነግዱት እስከየትኛው የሃብት ማማ ድረስ ነው? ለስልጣን ሴራ የምትቀምሩት እስከየትኛው የዙፋን መዘርጋት እርካታ ድረስ ነው?  ስለ ዘር የምታቀነቅኑት ከአዳምና ከሄዋን አልፎ የት እስኪደርስ ነው?  ስለቋንቋስ ከአሁን እስከ ባቢላናዊያን ዘመን የት እስኪያልፍ ነው የምትረዱት?  .......  ዓለምን፣ ሰውንና ፍጥረታትን በፈጠረ ፈጣሪ የምናምን እንዲሁም ለሀገርና ለወገን የምንጨነቅ ከሆነ ታሪክን ከምንጩ እና እውነትን ከመሠረቱ መረዳት ይገባናል። ነገር ግን ዛሬ የምናነበው ታሪክ፣ በየቦታው የምንሰማው ትርክት፣ ስለ ፈጣሪ፣ ስለ ሀገር አመጣጥ፣ ስለ ሕዝብ፣ ስለ ቋንቋና ስለ ማንነት የሚነገረው ሁሉ እውነትን ያራቀ ነው:: ለፖለቲካ ጥቅም፣ ለሥልጣንና ለግዛት ለክፍፍል የተገነባ ትርክት ሆኗል:: 

የታሪክ መዛባት ብዙ ጊዜ ከብዕር ይጀምራል፤ ነገር ግን መጨረሻው ከባድ የሰው ልጅ ዋጋ የሚያስከፍል ነው:: አንድ ትውልድ የተሳሳተ ትርክት ሲማር ጎረቤቱን እንደ ጠላት ሊያይ ይችላል፤ ሰውን በቋንቋው፣ በብሔሩ ወይም በሃይማኖቱና በማንነቱ ለመመደብ ይጀምራል። ይህም ክቡር የሆነውን የሰውን ልጅ የመከራ ቀንበሩን የሚያከብድና በሰቆቃ እንድንኖር የሚያደርገን ነው:: ኢትዮጵያውያን አሁን ያለንበት ሁኔታ እጅግ አስከፊ ደረጃ ላይ ነን:: አንድ አምባገነን መንግሥት ህዝብን በተገቢው መንገድ ማስተዳደር ካልቻለ ስልጣኑን ለማራዘም ሲል ህዝብን የማያስማማ እና አንድነትን የሚንድ የመከፋፈል መንገድ በሁሉም አቅጣጫ ይፈጥራል::  በዚህም ጊዜ የታሪክ ስርን በመነካካት ሀሳዊ ህሳቤን በማጉላት የህዝብን ስስ ብልቶችን በመንካት ሁሉም ለአንድነትና ለነጻነት እንዳይቆሙ ለማድረግ ይሰራል:: በዚህ ጊዜ አገዛዙ አንዱን አወድሶ አንዱን ይሰድባል ለአንዱ ጥቅም ለአንዱ ጉዳት ይጀምራል! ትርክት ፍሬውን ማፍራት የሚጀምረው ከዚህ ነው:: ብልጽግና እንደመጣ ኦሮማራ በሚል የትግራይ ህዝብ መገለል እንዲሰማው በእልህም ጦርነቱ እንዲቀጥል ተደረገ! ወዲያውኑ ደግሞ ሁላችሁም የምታስታውሱት አማራና ኦሮሞ እንዲጣሉ ደግሞ በአንድ ወገን መንጋ የሚል በሌላ ወገን ደግሞ የቀድሞ ስርዓት ናፋቂ የሚል ትርክት ተስፋፋ:: መንግሥትና ኢትዮጵያ ጠል ምሁራን ነን ባዮች ሀገራችንን ለማጥፋት ከበፊቱ በበለጠ መልኩ አመች ሁኔታ ተፈጠረላቸው:: በመሰረቱ ትርክት ጥቅምንና ሥልጣንን የሚፈልግ አካሄድ ነው። በህዝብ ደም የሚበለጽጉና ስልጣን ለመጨበጥ የሚፈልጉ ሰዎች መንገዳቸው እርሷ ናት:: ህዝብ ልብ ለልብ ከተገናኘ ካልተለያየማ የፖለቲካ ነጋዴዎች እንዴት ይሳካላቸዋል? 

በታሪክ ውስጥ “ከፋፍለህ ግዛ” የሚለው ስልት የታወቀ ነው። ይህ አካሄድ  ለህዝብ ሰላም፣ ፍቅርና ጥቅም የማያስገኝ በጦርነት በመታመስ እንድንኖር የሚያደርግ ሴራ ነው:: ሰዎች እንደ ሰውና እንደ ዜጋ ሳይሆን በቋንቋ፣ በብሔር ወይም በሃይማኖት ብቻ እንዲተያዩ ሲደረግ ተጠቃሚው ሕዝብ ሳይሆን ሥልጣንና ጥቅም የሚፈልጉ ኃይሎች ናቸው።  ኢትዮጵያ ላይ ይህ እየተደረገ ያለው ሴራ ከበርካታ ጊዜ ጀምሮ እስከ ዛሬ በዓለም የሚካሄዱ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የኃይል ፉክክሮች፣ እንዲሁም ስለ “አዲስ የዓለም ሥርዓት”  ጋር ለማስኬድ የታለሙ እንደሆኑ ማወቅ ይገባናል::  የዚህ ዓላማው ደግሞ አንድነት ቢመስልም ህዝብን ሊወጣው የማይችለው መከራ ውስጥ በመክተት ከእግዚአብሔር ህግ ውጭ እንዲጓዝና  እንዲጠፋ ለማድረግ ነው:: ግን ስልት እየቀያየረ ብዙ መልክ ይይዛል:: ኢትዮጵያ ትልቋ ኢላማ ለምን እንደሆነች ብትነገሩ ተረት ተረት ስለሚመስላችሁ ዝም ብሎ ማለፍ ይሻላል:: 

ማንኛውም ሐሳብ ሰውን ከሰው፣ ወገንን ከወገን እየለየ ከሆነ ጥያቄ ማንሳት የግድ ነው። እውነተኛ ፖለቲካ ሕዝብን ያገለግላል፤ የጥቅም ፖለቲካ ግን ሕዝብን ይከፋፍላል። እውነተኛ ታሪክ ሕዝብን ያቀራርባል፤ የተዛባ ትርክት ግን ለትውልድ የማይጠፋ ቁስል ይተዋል። በእውነት ምሁር ማለት ማነው? የታሪክ ጸሐፊ ማለት ማነው? የተጻፈውን ሁሉ ሳይመረምር መቀበል እውቀት አይደለም። የጻፈ ሁሉ ምሁር አይሆንም፤ ያነበበ ሁሉም የተማረ አይሆንም፤ የተናገረ ሁሉ አንደበቱ የቀና አይደለም!  ታሪክን ማዛባት፣ ሃይማኖትንና ሰዎችን ለፖለቲካ ጥቅም መጠቀም ሕዝብን በጥላቻ መከፋፈል በህሊና ፊት የሚያስጠይቅ ነገር ነው።እውነተኛ ምሁር የሕዝብን ቁስል የሚፈውስ ነው፤ እውነተኛ ጸሐፊ ሰዎችን የሚያቀራርብ ነው። እውነተኛ የሃይማኖት አባትም ለእውነት የሚኖር ነው!  ስለዚህ ዛሬ መጠየቅ ያለብን ሰዎችን ብቻ ሳይሆን ሐሳቦችንም ነው። የምናነበውን ሁሉ በእውነት፣ በማስረጃና በህሊና እንመዝን። ዛሬ የምናየው ግጭት፣ መከፋፈል፣ መተማመን መጥፋት፣ ስደትና ህመም ከየት መጣ? ለዚህ ጥያቄ ሁላችንም መልስ መፈለግ አለብን። መልሱም አንድ ሆነን ለጋራ የሚበጀንን ስርዓት መስራት ብቻና ብቻ ነው! ፖለቲከኞችን እንርሳቸው! ህዝብ ሆይ እንንቃ ኢትዮጵያውያን ጠፍተናል!   ታሪክን በሚገባ እንወቅ እውነትን ከምንጩ እንፈልግ:: ህሊናችንን ከጥላቻና ከሐሰት ትርክት እናጽዳ።
ሀገርን በፍቅር፣ በእውነትና በፍትሕ እንታደግ።

ወደድንም ጠላንም ማወቅ ያለብን አይቀርም ኢትዮጵያ ጠላቶቿ እያዩ ትነሳለች! የህዝብን መከራ ያከበዱ የፖለቲካ ቁማርተኞች ሁሉ ታሪክ ይሆናሉ!  ትንሳኤያችንን ለማፍጠን የህዝብ ንቃተ ኅሊና ያስፈልጋልና ንቁ  አታንቀላፉ!  አንድ ነገር ማሳሰብ የምፈልገው እኔ ብሄርተኛ አይደለሁም! የቆምኩት ለእውነትና ለፍትህ ነው:: እግዚአብሔር የበጎች እረኛ ስላደረገኝ በጎቼን ከነጣቂ ተኩላ ለመጠበቅ ነው ጫካ የገባሁት:: ምንም ብትሉ ለእውነትና እግዚአብሔርን በመታዘዝ ስለወጣሁ ምንም አይመስለኝም! ለይሉኝታ ሰውን ሳይሆን እግዚአብሔር ብቻ እንስማ!  እግዚአብሔር የቀባችሁ የበጎች እረኞች ሆይ ውጡ የመከራው ቀንበር የከበደውን ህዝብ አድኑ! እኛ በቻልንና እግዚአብሔር በረዳን መጠን ህዝብን ለማዳን ከመሰል አባቶቼ ጋር ከወጣን ቆይተናል:: ሰው የተባለ ሁሉ ዘር የምትሉት ምድራዊ እንዲሁም ሃይማኖት አይገድበንም! ሰው ለተባለ ሁሉ ነጻነት መቆም ግድ ይለናል::  የሰው ልጅ በምድር ሰላም ካገኘ ፈጣሪውን ለማወቅ መንፈሳዊ አገልግሎት ለማግኘት እድል ይኖረዋል:: ወንጌልም የሚስፋፋው ያኔ ነው:: አንዳንድ አስመ*ሳይ የነጠላ ክርስቲያኖች ሐዋርያት ወንጌልን በመከራ ነው ያሰራጩት ብሎ ስንፍናውን በስህተት ለመሸፈን ይሞክራል! በሐዋርያት ዘመን እንደ ነበሩ አባት እናቶቻችን አይነት ትዕግስትና ቀና ልቦና ካለህ በል በጽድቅ ጎዳና ተመላለሳ!  ኢትዮጵያ እንዴት ተጠብቃ ማንስ ጠብቋት እንደኖረች በውል ስለማታውቁ አንፈርድባችሁም!  ለማንኛውም ሰው የተባልክ በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠርክ ክቡር ፍጥረት ሆይ አስተውል!  ያለንበትን ዘመን እንመርምረው!  እያንቀላፋን ለስጋችንም ለነፍሳችንም አልሆንም! ንቁ ንቁ ንቁ....!   ንቁ ስላችሁ ምን ለማለት እንደፈለጉ  የምትረዱት ይመስለኛል! 

ቆሞስ አባ ጳውሊ ከግንባር
Share on Google Plus

ስለ የተለጠፈበት ቀን

    Blogger Comment
    Facebook Comment