✍ መንግሥቱ ጎበዜ
እንደ መግቢያ
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በቅዱስ ላሊበላ ላይ የሚሰነዘሩ ጥቃቶች ስልታዊ በሆነ መንገድ እየተጠናከሩ መጥተዋል። ከሦስት ወራት በፊት "በኢትዮጵያ የተገኘ መቃብር የክርስትናን ታሪክ ቀየረ" በሚል ርዕስ በሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) ተቀናብሮ በዩቲዩብ የተሰራጨው የሐሰት ቪዲዮ፣ የቅዱስ ላሊበላን ታሪካዊ ባለቤትነት ለመንጠቅና የኢትዮጵያን የሥልጣኔ አሻራ ለማጥፋት የታለመ ስውር ዘመቻ አካል ተደርጎ የሚወሰድ ነበር። ይህ ቪዲዮ ሳይንሳዊ ማስረጃ በሌለው መንገድ የላሊበላን ጥበብ ከባዕድ ኃይሎች ጋር ለማገናኘትና ቅዱስ ላሊበላን "እንግዳ" አድርጎ ለማቅረብ የሄደበት ርቀት፣ ስልታዊ የታሪክ ዝርፊያና የባሕል ወረራን ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ መሆኑን ከወራት በፊት አቅርቤ ነበር።
አሁን ደግሞ በሰሜን አሜሪካ ሰሜን ካሮሊና ግዛት በሚገኝ መካነ አራዊት ውስጥ በቅዱስ ላሊበላ አብያተክርስቲያናት አምሳያ የተገነባውን ሕንጻ ለአራዊት መጠለያነት /ለዝንጀሮዎች/ ማዋሉ፣ የአንድን ሕዝብ ቅዱስ ስፍራና የታሪክ ማማ ወደ "እንስሳት ቤት" ዝቅ የሚያደርግ፤ የቦታውን መንፈሳዊ ዕሴትና ግዙፍ ታሪካዊ ክብር የሚያቃልል ነው። በመሆኑም ኢትዮጵያውያን ይህንን ትክክለኛ ያልሆነ አካሄድ በመገንዘብና አግባብ አለመሆኑን ለሚመለከተው አካል በማቅረብ በተደራጀ መንገድ ድምፃቸውን ሊያሰሙ ይገባል የሚል እምነት አለኝ። በዚሁ አጋጣሚ ይህ ጉዳይ አሳስቧቸው ከሕዝብ ጆሮ እንዲደርስ ያደረጉትን “ምንግዜም ሚዲያን”፣ “ዓለም አቀፍ ለፍትሕ የኢትዮጵያ ጉዳይን” እና የድርጅቱን ሊቀመንበር ፕሮፌሰር አቻሜለህ ደበላን ለማመምስገን እወዳለሁ።
የቅዱስ ላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት ፋይዳ
የቅዱስ ላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት ተራ ሕንጻዎች ሳይሆኑ ደብረ ሮሃን "ምድራዊት ኢየሩሳሌም" ያሰኙና የአፍሪካውያን የጥበብ ልዕልና ማሳያዎች ናቸው። የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ከዓለት የተፈለፈሉ ግዑዝ ድንጋዮች ብቻ ሳይሆኑ፣ የአፍሪካውያን የጥልቅ እምነት እና የዓለም አቀፍ የክርስትና ታሪክ ጉልህ አሻራዎች ናቸው። ይህ ድንቅ ሥራ "ጥቁር ሕዝቦች ሥልጣኔ አልነበራቸውም" የሚለውን የተሳሳተ ትርክት በዐለት ላይ የታተመ ምላሽ የሰጠ ነው። አብያተ ክርስቲያናቱ ከላይ ወደ ታች ከአንድ ወጥ ድንጋይ ተፈልፍለው የተሠሩ መሆናቸው፣ በ12ኛው ክፍለ ዘመን የነበሩ ኢትዮጵያውያን የረቀቀ የጂኦሜትሪ፣ የሒሳብ እና የሥነ-ሕንጻ ዕውቀት ጣሪያ ላይ መድረሳቸውን ያረጋግጣል። በተጨማሪም እንዲህ ዓይነት ግዙፍና ረቂቅ ሥራዎችን ለማከናወን የተረጋጋ መንግሥትና ጠንካራ የኢኮኖሚ ሥርዓት መኖሩ የቅዱስ ላሊበላ ዘመነ መንግሥት የነበረውን ታላቅነት መገለጫ ነው።
ከመንፈሳዊ ፋይዳቸው አንጻር ሲታዩ፣ እነዚህ አብያተ ክርስቲያናት ከሕንጻነታቸው ባለፈ "ሕያው ወንጌል" ተደርገው የሚወሰዱ መንፈሳዊ ትምህርት ቤቶች ናቸው። ቅዱስ ላሊበላ ከስምንት መቶ ዓመታት በላይ ያለማቋረጥ መንፈሳዊ አገልግሎት የሚፈጸምባት የተቀደሰች ስፍራ በመሆኗ፣ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የእምነት ጽናትና ጥንካሬ ምልክት ናት። በቅድመ ቅኝ ግዛት አፍሪካ፣ በአፍሪካ ምድር እንዲህ ያለ ቅዱስ ስፍራ መታነጹ አፍሪካውያን የራሳቸው የሆነ ጥልቅ መንፈሳዊ ማንነትና የዳበረ የሥልጣኔ ባለቤቶች እንደነበሩ የሚያሳይ የኩራትና የክብር ምልክት ነው።
ከዚህ ባሻገር፣ በ12ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ወደ ኢየሩሳሌም የሚደረገው ጉዞ በጦርነት ምክንያት ሲስተጓጎል፣ ንጉሥ ላሊበላ በኢትዮጵያ ምድር የኢየሩሳሌምን አምሳያ በመገንባት ለዓለም ክርስትና ያበረከተው አዲስ መንፈሳዊ መተንፈሻ ሕያው ምስክር ነው። ቅዱስ ላሊበላ የጥንቱን የክርስትና ሥርዓተ አምልኮ፣ ዜማና ሥነ-ጽሑፍ ሳይበረዝ ጠብቆ በማቆየት ለዓለም አብያተ ክርስቲያናት እንደ ሕያው የታሪክ መዝገብ ሆኖ ያገለግላል። የሰው ልጅ የፈጠራ ችሎታ የመጨረሻው ጥበብ ተብሎ በዩኔስኮ የተመዘገበ በመሆኑም የመላው የሰው ዘር የጋራ ሀብት ነው። በአጠቃላይ ቅዱስ ላሊበላ አፍሪካዊ ጥበብ ከሰማያዊ እምነት ጋር ተዋህዶ የተገኘበት ተአምር በመሆኑ ለኢትዮጵያውያን ብሎም ለአፍሪካውያን ከሀብት በላይ "ማንነታችን" ነው። በመሆኑም በአሜሪካ የሰሜን ካሮሊና ግዛት የመካነ ቅዱሳኑን አምሳያ ወደ መካነ አራዊትነት ቀይሮ ማስተዋወቅና የንግድ ሥራ ማድረግ፣ ከዚህ አኳያ ሲታይ ፈጽሞ ተገቢነት የሌለውና የሚያስተላልፈው መልዕክትም ጤናማ ያልሆነ ነው።
ቅዱስ ላሊበላ እና አሜሪካ ምንና ምን ናቸው?
የቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት የታነጹት በ12ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ሲሆን፣ ይህ ወቅት አሜሪካ እንደ ሀገር ከመመሥረቷ ከ550 ዓመታት በላይ፣ ክሪስቶፈር ኮሎምበስ የአሜሪካን አህጉር "አገኘሁ" ካለበት ዘመን ደግሞ ከ300 ዓመታት በላይ ይቀድማል።
ከዚህም በላይ፣ የታሪክ ምሁራን እንደሚስማሙበት አውሮፓውያን አዳዲስ ዓለማትን ለመፈለግ ባሕር አቋርጠው እንዲነሱ ካደረጓቸው ዋና ዋና ምክንያቶች አንዱ "የቄሱ ንጉሥ ዮሐንስን" (Prester John) ምሥጢራዊና ኃያል የክርስቲያን መንግሥት ፍለጋ ነበር። ይህ መንግሥት የሚገኘው በኢትዮጵያ እንደሆነ ይታመን ስለነበር፣ አውሮፓውያን ከዚህ ንጉሥ ጋር ለመገናኘት ባደረጉት ተከታታይ አሰሳ ነው በተዘዋዋሪ የአሜሪካን አህጉር ያገኟት። ስለሆነም የኢትዮጵያ ሥልጣኔና ዝና ለአሜሪካ "መገኘት" መንገዱን የጠረገ የታሪክ መነሻ ነው ማለት ይቻላል። ክህነትን ከቅድስና፣ ንግሥናን ከምሕንድስና አስተባብሮ ይዞ የነበረው ቅዱስ ላሊበላም በዚህ ዘመን የነበረና ለምዕራባውያን አሰሳና ጉዞ አንደኛው ምክንያትና ምልክት የነበረ ነው። ኢትዮጵያ እንዲህ ያለ ታሪካዊ ቀዳሚነትና ለአሜሪካ መገኘት እንኳ በተዘዋዋሪ ምክንያት የሆነ ሥልጣኔ ባለቤት ሆና ሳለ፣ ዛሬ ላይ በሰሜን አሜሪካ የቅዱስ ላሊበላን አምሳያ ለአራዊት መጠለያነት ዝቅ ማድረግ ሞራላዊም፣ ሕጋዊም፣ ፍትሐዊም ያልሆነ ክብረ ነክ ተግባር ነው።
ከዐውድ ውጭ የሆነ ተግባር
ይህንን ድርጊት የፈጸሙት አካላት ድርጊታቸውን እንደ "ጥበብ" ወይም "ማራኪ እይታ" ቆጥረውት ሊሆን ይችላል። የቅዱስ ላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት ከዓለት የተፈለፈሉ በመሆናቸው፣ እንደ "ተፈጥሯዊ ዋሻ" በመቁጠር ለእንስሳት መኖሪያነት "ቆንጆ ንድፍ" ይሆናል የሚል የተሳሳተ የተፈጥሮአዊ ገጽታ (Naturalistic Aesthetics) እይታ ኖሯቸው ይሆናል። በተጨማሪም በሰሜን አሜሪካ ያሉ ተቋማት ጎብኚዎችን ለመሳብ ሲሉ፣ ከምዕራቡ ዓለም ወጣ ያሉና "ልዩ" (Exotic) የሆኑ ምስሎችን በመፈለግ፣ የቅዱስ ላሊበላን ልዩ ዲዛይን ለንግድ ስሌትና ለ"ጥንታዊነት" ስሜት መፍጠሪያነት ተጠቅመውት ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ ይህ ድርጊት በዋናነት "ዐውድን ከመሳት" (Lack of Context) እና ከባሕል ግንዛቤ ማነስ (Lack of Cultural Sensitivity) የሚመነጭ በመሆኑ ዝም ሊባል የማይገባው ነው።
አንድምታውና ተጽዕኖው
ይህ ታላቅ የታሪክ ፋይዳ ያለው ቅዱስ ስፍራ ለአራዊት መኖሪያነት መታሰቡ በርካታ አሉታዊ አንድምታዎች አሉት። ሚሊዮኖች ምዕመናን "ዳግማዊት ኢየሩሳሌም" ብለው የሚያምኑባትን የቅዱስ ላሊበላን አምሳያ አራዊት እንዲኖሩባት ማድረግ የቦታውን ቅድስና የሚጋፋና ለኢትዮጵያ ታሪክና ጥበብ ያለውን ዝቅተኛ አመለካከት የሚያሳይ ነው። የቅዱስ ላሊበላን ታላቅ የሕንጻ ጥበብ ከአራዊት ጋር ቀላቅሎ ማቅረብ ምዕራባውያን አፍሪካን ሲያስቡ ሁልጊዜ ከዱር አራዊትና ከጫካ ጋር የማገናኘት (Stereotyping) ዝንባሌያቸው መገለጫ ነው። ይህም ተመልካቹ ስለ ኢትዮጵያ ሥልጣኔ ከማሰብ ይልቅ ስለ ዱር እንስሳት ብቻ እንዲያስብ የሚያደርግ የታሪክ ማሳነስ ነው።
ቅዱስ ላሊበላ የሰው ልጅ ከፍተኛ የምሕንድስና ደረጃ ላይ መድረሱን የሚያሳይ ምስክር ሆኖ ሳለ፣ ከአራዊት ጋር ማገናኘት ሥልጣኔውን ከሰው ልጅ የላቀ ጥበብ ይልቅ ወደ "ተፈጥሯዊ ወይም ኋላቀር" እይታ ዝቅ ያደርገዋል። ይህም ቤተክርስቲያኑን እንደ ተራ "ዋሻ" ወይም "የድንጋይ ቤት" የማየት ዝንባሌ እንዲፈጠር ያደርጋል። በተጨማሪም ስለ ኢትዮጵያና ስለ ላሊበላ የማያውቁ ሰዎች ይህንን ስፍራ ሲጎበኙ፣ ላሊበላን እንደ ታሪካዊ መንፈሳዊ ቦታ ሳይሆን እንደ "ጥንታዊ የእንስሳት መጠለያ" አድርገው እንዲያስቡ የሚያደርግ የተሳሳተ ግንዛቤ (Misrepresentation) ይፈጥራል። በተጨማሪም የሌላን ማኅበረሰብ ቅዱስ ምልክት ወስዶ ለራስ የመዝናኛ ዓላማ ማዋል በባሕሎች መካከል ያለውን መከባበር የሚሸረሽር ድርጊት ነው።
ከዚህ በተጨማሪ ጉዳዩን ከየዕውቀት ባለቤትነት መብት (Intellectual Patent Right) አንጻር በጥልቀት ሊመለከቱት የሚገባ ነው። የቅዱስ ላሊበላ ልዩ የሥነ-ሕንጻ ጥበብ ወይም ረቂቅ የምሕንድስና ዕውቀት የአንድ ማኅበረሰብ የፈጠራ ውጤትና የታሪክ ባለቤትነት መገለጫ በመሆኑ፣ ያለ ባለቤቱ ፈቃድ ለንግድና ለመዝናኛ ዓላማ ማዋል በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚተገበሩ የባሕልና የዕውቀት ንብረት ጥበቃ ሕጎችን የሚጥስ ተግባር ነው።
ተግዳሮቱን ወደ መልካም አጋጣሚ መለወጥ
በሰሜን ካሮሊና የእንስሳት ማቆያ ውስጥ የተፈጠረው የታሪክ መዛባት የማስተካከል ትግል፣ እግረ መንገዱን የኢትዮጵያን እውነተኛ የሥልጣኔ ታሪክ ለዓለም ለማስተዋወቅ ትልቅ በር የሚከፍት "መልካም አጋጣሚ" ሊሆን ይችላል። ሙዚየሙ ይህንን ሕንጻ የገነባው ካለማወቅ ከሆነ፣ ኢትዮጵያውያን ቀርበው ሕንጻው ከአራዊት መጠለያነት ወጥቶ ወደ "የኢትዮጵያ ባሕልና ታሪክ ማሳያ ማዕከል" እንዲቀየር በማሳመን አደጋውን ወደ ድል መለወጥ ይቻል ይሆናል። ይህም በሰሜን ካሮሊና የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና የኮሚኒቲ አባላት በጋራ በመሆን፣ ለሙዚየሙ አስተዳደርና ለግዛቱ የባሕል መመሪያ ክፍል "ሕንጻው የሚወክለው የአንድን ትልቅ ሕዝብ እምነትና ታሪክ ነው" የሚል ይፋዊ የቅሬታ ደብዳቤና ፊርማ በማቅረብ ስልታዊ ጫና መፍጠርን ይጠይቃል።
ይህንን አሉታዊ ሂደት ወደ አዎንታዊ ውጤት ለመቀየር ዓለም አቀፍ የሚዲያ ዘመቻ መጀመር ወሳኝ ነው። የጉዳዩን አነጋጋሪነት በመጠቀም እንደ CNN እና BBC ያሉ ታላላቅ ተቋማት ትኩረት እንዲሰጡት በማድረግ፣ ላሊበላ አሜሪካ ከመገኘቷ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዓመታት ቀድሞ የታነጸና ለዓለም መንፈሳዊነትና ምሕንድስና ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረከተ ጥንታዊ ሥልጣኔ መሆኑን ማስገንዘብ ይቻላል። እንዲህ ዓይነቱ ንቅናቄ "ጥቁር ሕዝቦች ታሪክና ሥልጣኔ የላቸውም" የሚለውን የተሳሳተ ትርክት የሚሰብር መድረክ ይፈጥራል። በተጨማሪም በዲጂታል ዲፕሎማሲ ታግዞ ሰዎች ስለ ሰሜን ካሮሊናው ሕንጻ ኢንተርኔት ላይ ሲፈልጉ እውነተኛውን የቅዱስ ላሊበላ ምስል፣ ምሕንድስና እና መለኮታዊ ጥበብ እንዲያገኙ በማድረግ የሐሰት ትረካዎችን ማክሸፍ ይቻላል።
ሌላው ትልቅ ዕድል ይህንን አጋጣሚ ለቱሪዝም ማስተዋወቂያነት መጠቀም ነው። "በሰሜን ካሮሊና አምሳያውን ካያችሁ፣ እውነተኛውን ተአምር ለማየት ወደ ኢትዮጵያ ኑ" የሚል ጥሪ ማስተላለፍ የዓለም አቀፍ ተመራማሪዎችንና የሃይማኖት ተጓዦችን ቀልብ ለመሳብ ይረዳል። ይህም ለቅዱስ ላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት ነፃ የገበያ ማስታወቂያ (Free Publicity) በመሆን የጎብኝዎችን ፍሰት ሊጨምር ይችላል።
ባጠቃላይ፣ ይህ ዘመቻ በሚገባ ከተመራ የኢትዮጵያን የሥልጣኔ ልዕልና ለዓለም ዳርቻ ለማድረስ ታላቅ ዕድል ነው። ዛሬ በጋራ የምንሰጠው ምላሽ በሀገር ውስጥና በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያንን በአንድ ዓላማ የሚያስተሳስር ከመሆኑም በላይ፣ ለቀጣይ ትውልድ ታሪክን የማስተላለፍ ኃላፊነትን ያጠናክራል። ይህ አጋጣሚ የቅዱስ ላሊበላን የሥልጣኔ ማኅተም ይበልጥ ደምቆ እንዲበራ ለማድረግ የምንጠቀምበት ወሳኝ የታሪክ ምዕራፍም ማደርግ እንችላለን።
ከማን ምን ይጠበቃል?
ይህንን የስህተት አውድ ለማስተካከል ከቅዱስ ሲኖዶስ ጀምሮ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ሊወስዳቸው የሚገቡ ወሳኝ እርምጃዎች አሉ። ቅዱስ ሲኖዶስ የላሊበላን ቅድስና የሚያስረዳና ድርጊቱን የሚያወግዝ ዓለም አቀፍ መግለጫ ለዩኔስኮ -(UNESCO) እና ለዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ማድረስ ቢችል መልካም ነው። በአሜሪካ የሚኖሩ የቤተክርስቲያን አባቶችና ምዕመናን ደግሞ ለሰሜን ካሮሊና ግዛት አስተዳደርና ለእንስሳት ማቆያው የቅሬታ ደብዳቤ በማስገባት፣ ሕንጻው ወደ "የኢትዮጵያ ባህልና ታሪክ ማዕከልነት" እንዲቀየር ወይም ከአራዊት መኖሪያነት እንዲወጣ ዲፕሎማሲያዊና ሕጋዊ ጫና መፍጠር ይኖርባቸዋል። የቅርሱ ቀጥተኛ ባለቤት የሆነው የቅዱስ ላሊበላ ገዳምም እውነተኛውን የታሪክ መረጃና ምስክርነት በተለያዩ ቋንቋዎች ለዓለም ማኅበረሰብ በማሰራጨት ስሁት ትርክቶችንና ተገቢ ያልሆኑ እይታዎችን ማፍረስ ይጠበቅበታል።
ከእነዚህ ተቋማዊ ሥራዎች ጎን ለጎን፣ የተቀናጀ የዲጂታል ዲፕሎማሲ ዘመቻ ማካሄድ ይጠበቅብናል። የታሪክ ምሁራን፣ የሃይማኖት አባቶችና ወጣቶች ማኅበራዊ ሚዲያን በመጠቀም ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጉዳዩን እንዲያውቀውና ድርጊቱ ትክክል እንዳልሆነ እንዲረዳ ማድረግ ተገቢ ነው። በዋሽንግተን ዲሲ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲም በባሕል ዲፕሎማሲ በኩል ጥያቄ እንዲያቀርብ ግፊት ማድረግና የሕግ ባለሙያዎችን በማማከር፣ የሃይማኖት ምልክቶችን ያለአግባብ መጠቀምን በሚከለክሉ ሕጎች ዙሪያ መሥራት አስፈላጊ ይሆናል። የኢትዮጵያ የቅርስ ባለሥልጣንም ለUNESCO እና ICOMOS ለመሳሰሉ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጉዳዩን አቅርቦ የመፍትሔው አካል መሆን ቢችልና ኃላፊነቱን ቢወጣ ይመከራል።
ማጠቃልያ
"ዝምታ ለበግም አልበጃት፤ ዘጠኝ ነፍስ ሆና አንድ ነብር ፈጃት" እንዲሉ፣ ዛሬ በቸልታና በዝምታ የምናልፈው የታሪክ መዛባት ነገ ለማይቀለበስ ማንነታዊ ጥፋት በር መክፈቱ አይቀሬ ነው። በሰሜን ካሮሊና የቅዱስ ላሊበላን አብያተ ክርስቲያናት አምሳያ ለአራዊት መጠለያነት ዝቅ ማድረግ ዛሬ በዝምታ ከታለፈ፣ ነገ ሌሎች ተቋማት በታሪካዊ ቅርሶቻችን ላይ የከፋ የድፍረት እርምጃ ከመውሰድ አይመለሱም። ዝምታ የሐሰት ትርክትን እንደ እውነት የሚያጸድቅና የታሪክ ወረራን የሚያበረታታ በመሆኑ፣ እንዲህ ዓይነቱን ስሁት አካሄድ በተደራጀና በተባበረ የሁለንተናዊ ትግል መንፈስ መመከት የትውልድ ግዴታ ነው።
Blogger Comment
Facebook Comment