ፋ*ኖ ስራ ላይ ነው! ዝም ብላችሁ ስራችሁን ስሩ!


ቆሞስ አባ ጳውሊ | ከግንባር

ሰላም በመላው ዓለም የምትኖሩ የፋኖን የነፃነትና የህልውና ትግል የምትደግፉ እንዲሁም ለህዝባችሁ ስትሉ መስዋዕት የምትከፍሉ የፋኖ አባላት እንዲሁም ሁላችሁም ኢትዮጵያውያን በሙሉ ሰላምታዬ ይድረሳችሁ።  ዛሬ መሬት ላይ ስላለው እውነታና ሁላችሁም ኢትዮጵያውያን ቢመራችሁም ልትውጡት የሚገባቸውን ነገር ልነግራችሁ እፈልጋለሁ። 

ስለ ፋኖ ትግል ሳስብ ሁል ጊዜ በአእምሮ ላይ የሚመጣውን የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ በማስቀደም መልዕክቴን ለማስተላለፍ እሞክራለሁ። "የፈራ የደነገጠም ከገለዓድ ተራራ ተነሥቶ ይመለስ" ይህን ቃል የምናገኘው በመጽሐፈ መሳፍንት  7÷3  ላይ ሲሆን ጌዴዎን የተባለውም ይሩበኣል ከእርሱም ጋር የነበሩ ሕዝብ ሁሉ ማልደው ተነሡ፥ በሐሮድ ምንጭ አጠገብም ሰፈሩ፥ የምድያምም ሰፈር ከእነርሱ ወደ ሰሜን በኩል በሞሬ ኮረብታ አጠገብ በሸለቆው ውስጥ ነበረ።

እግዚአብሔርም ጌዴዎንን፦ ከአንተ ጋር ያለው ሕዝብ በዝቷል፥ ስለዚህ እስራኤል፦ እጄ አዳነኝ ብሎ እንዳይታበይብኝ እኔ ምድያምን በእጃቸው አሳልፌ አልሰጣቸውም። አሁንም እንግዲህ፦ የፈራ የደነገጠም ከገለዓድ ተራራ ተነሥቶ ይመለስ ብለህ በሕዝቡ ጆሮ አውጅ አለው። ከሕዝቡም ሀያ ሁለት ሺህ ተመለሱ፥ አሥርም ሺህ ቀሩ።

እግዚአብሔርም ጌዴዎንን፦ ሕዝቡ ገና ብዙ ነው፥ ወደ ውኃ አውርዳቸው፥ በዚያም እፈትናቸዋለሁ፥ እኔም፦ ይህ ከአንተ ጋር ይሂድ የምለው እርሱ ከአንተ ጋር ይሄዳል፥ እኔም፦ ይህ ከአንተ ጋር አይሂድ የምለው እርሱ አይሄድም አለው። ሕዝቡንም ወደ ውኃ አወረደ። እግዚአብሔርም ጌዴዎንን፦ ውሻ እንደሚጠጣ ውኃ በምላሱ የሚጠጣውን ሁሉ፥ እርሱን ለብቻው አድርገው፥ እንዲሁም ሊጠጣ በጉልበቱ የሚንበረከከውን ሁሉ ለብቻው አድርገው አለው። በእጃቸውም ውኃ ወደ አፋቸው አድርገው የጠጡት ቁጥር ሦስት መቶ ነበረ፥ የቀሩት ሕዝብ ግን ውኃ ሊጠጡ በጉልበታቸው ተንበረከኩ። እግዚአብሔርም ጌዴዎንን፦ በእጃቸው ውኃ በጠጡት በሦስት መቶ ሰዎች አድናችኋለሁ፥ ምድያማውያንንም በእጅህ አሳልፌ እሰጥሃለሁ፥ የቀሩት ሕዝብ ሁሉ ግን ወደ ስፍራቸው ይመለሱ አለው።

እግዚአብሔርም ብዛታቸውም እንደ አንበጣ የሆነ ምድያማውያንና አማሌቃውያን የምሥራቅም ሰዎችን  አሳልፎ ሰጣቸው ድል አደረጉ! ይህን ሙሉ ታሪኩን አንብቡት!

በዚህ ሶስተኛ ዓመቱን በያዘው የአማራ ህዝብ የኅልውና ትግልም እግዚአብሔር ስራውን እየሰራ እንደሆነ እንድትገነዘቡልኝ እወዳለሁ!   የፋኖ ትግል መለኮታዊ ጣልቃ ገብነት ያለው ስለሆነ ትግሉ እንደ ወርቅ ተፈትኖ እየጠራ ነው:: የሚመራውም በእርሱ ፈቃድ ነው! የፈሩ የደነገጡ እንደ ውሻ በምላሳቸውና ተንበርክከው የሚጠጡት (ትግሉን የሚጎትቱ ብዬ የሰየምኳቸው) እንዲሁም እኛ እኛ...ትግሉ ያለ እኛ...እያሉ በትዕቢት የሚመኩ ይውጡ ከገለዓድ ይመለሱ!  

በመሠረቱ የፋኖ ትግል ሲጀመር የመነሻ ዓላማና የመድረሻ ራዕይ ባላቸው ሰዎች ነው የተጀመረው። ምናልባት ይህን ሁሉ ሰው ላይረዳው ይችልና የፋኖ ትግልም ቅጽበታዊ ለድንገት በስሜት የተጀመረ የሚመስላቸው ሳይኖሩ አይቀሩም። የፋኖ ትግል በአንድ ወይም በሁለት ሰዎች የተጀመረ አይደለም። በመጀመሪያ ደረጃ የእግዚአብሔር ህዝብን ከመከራ የመታደግ አላማ ያለበት ሲሆን በመቀጠልም ደግሞ አማራ እንደ ህዝብ መከራው ጸንቶበት ሆ ብሎ በአንድነት የተነሳበት የነፃነት  ትግል ነው። አንድ ሰው አኩርፎ ሲወጣ የሚቀንስ ወይንም ደግሞ ፈተና ውስጥ የሚወድቅ ትግል አልተጀመረም። የፋኖ የነፃነት ትግል ከተጀመረ ጀምሮ እየወጡ ያሉት የትግሉን አላማ በውል ያልተረዱ ናቸው። እነዚህ አይነት ታጋዮች በብዛት በትግል ሜዳ ላይ የማይገኙ ሲሆን ራሳቸውን በማህበራዊ ሚዲያ በትግሉ ውስጥ እንደዋና ተዋናይ በመምሰል የሚቀርቡ ናቸው። እነዚህ አይነት ሰዎች ቢወጡ ትግሉን የሚጠቅሙ እንጂ የሚጎዱ አይደሉም። እስካሁን ካስተዋልኩት መካከል በብዛት ራሳቸውን በሚዲያ  ያገነኑ አንዳንድ ስለ ትግሉ ዓላማ በውል ያልተረዱ እውነተኛ ፋኖ ያልሆኑ አካላት ያልተገባ ነገር በሚዲያ በማሰራጨት  አንዳንድ ጊዜም በፋኖ መካከል ያለመግባባት ችግር እንዳለ በማስመሰል የሚያቀርቡ ራሳቸውን ቁልፍ ሰው አድርገው የሚያስቡ ናቸው። ትግል ፈታኝ ስለሆነ መሰልቸት የለብንም!  ትግል ከስሙ እንደምንረዳው ብዙ ተግዳሮት ቢኖረውም ለዓላማችን መጽናት ግድ ይለናል::  በፋኖ ውስጥ ሆነው ፋኖ ፋኖ የሚጫዎቱ አስመሳዮች ከመጀመርያውም የመንግስት የሴራ ስራ አስፈጻሚዎች እንጅ የፋኖ ታጋይ አልነበሩም ማለት ነው::  እነዚህ ለትግሉ አያስፈልጉም። በመውጣታቸው እናተርፋለን እንጂ አናጎድልም። ይሂዱ መንግስትም የተለመደ ድራማውን ይሥራባቸው። እውነተኛዎቹ የህዝብ ልጆች ስራ ላይ ናቸው! 

ፋኖ አያሸንፍም ብላችሁ የምታስቡ አይደለም ይቅርና በትንሹ የምትጠራጠሩ እንኳን ልታፍሩ ይገባችኋል፤ ምክንያቱም እናሸንፋለንና! የማናሸንፈውን ትግል አልጀመርንም።  ብዙ ጊዜ ከማስተውለውና ከሚያስቁኝ ነገሮች መካከል አንዱ መንግስት አንድ የፋኖ አባላት እጅ ሲሰጥ እምቢልታ እያስነፋ ነጋሪት እየጎሰመ በሚዲያ የሚያራግበው ነገር ነው። በአይነ ስ*ው*ር ቤት አንድ ዓይና ብርቅ ነው የሚለው አባባል ምንኛ ትክክል ነው!  ከዚህ መረዳት የምንችለው መንግስት እንደተሸነፈ ነው። በየዕለቱ ወደ ፋኖ የሚጎርፈው መከላከያ ሰራዊት ስፍር ቁጥር የለውም ሆኖም ግን ፋኖ አሸናፊና የሞራል ልዕልና ያለው የአባቶቹ ልጅ ስለሆነ ምንም አይመስለውም። 

በስተመጨረሻም ልነግራችሁ የምፈልገው ነገር እንኳንስ ይህን ያክል መላውን ሰፊውን የአማራ ክልል ተቆጣጥሮ ያለ በቁጥርም ከመከላከያ ሰራዊት የሚልቅ ኃይል እያለ ይቅርና በትንሽ ሰዎችም እናሸንፋለን። እውነትና ፍትህ አሸናፊ ናቸውና። ሁላችሁም መንግስት ያሸንፋል ብላችሁ የምታስቡ ሁሉ ተስፋ ቁረጡ። 

የእግዚአብሔር ዓላማ አይሠረዝም! እግዚአብሔር ለሰው ልጅ ያዘጋጀውን ቁጣ እንደ ስራችን እንደ ምላሻችን ወደ ምህረት እንዲሁም ምህረትን ወደ ቁጣ ልናስቀይር እንችላለን! የእግዚአብሔር ዓላማ ግን ይፈጸማል! ምን ለማለት እንዳሰብኩኝ ይገባችኋል ብዬ እገምታለሁ! ድሉ አይቀርም ለማለት ነው! 

ከአገዛዙ ጎን የቆማችሁ የህዝብን መከራና ስቃይ የምታራዝሙ ሁሉ አብራችሁ ዋጋ ትከፍላላችሁ። ሁልጊዜ እንደምናገረው አሁንም እንድትመለሱና ከህዝብ ጋር እንድትቆሙ ላሳስብ እወዳለሁ። ይህን ካላደረጋችሁ ነገ የተወለዳችሁበትን ቀን ትረግማላችሁ። ሰማይ ዝቅ ምድር ከፍ ብትል ድሉ አይቀርም!  ትግላችንን እንጠብቅ በአቋማችን እንጽና! 


Share on Google Plus

ስለ የተለጠፈበት ቀን

    Blogger Comment
    Facebook Comment