“ዳግመኛው የአሕመድ ግራኝ ጥቃት በአትሮንሰ ማርያም”


መንግሥቱ ጎበዜ 

አትሮንሰ ማርያም የመካከለኛው ዘመን የኢትዮጵያ ታሪክ፣ ሥልጣኔና ባህል ፈርጥ ከመሆኗም በላይ፣ የእምነትና የመንግሥት አስተዳደር ማዕከል የነበረች ታላቅ ስፍራ ነች። ይህች ቤተክርስቲያን የተመሠረተችው በ15ኛው ክፍለ ዘመን በአፄ በእደ ማርያም (1468–1478) አማካኝነትI ነው። አባታቸው አፄ ዘርዓ ያዕቆብ "ደብረ ጰራቅሊጦስ" በሚል ስያሜ የጀመሩትን ግንባታ ልጃቸው አፄ በእደ ማርያም በማጠናቀቅ "አትሮንሰ ማርያም" ብለው ሰይመዋታል። ስፍራው የሰሎሞናዊው ሥርወ መንግሥት መሥራች አፄ ይኩኖ አምላክን ጨምሮ፣ የ18 ነገሥታትና ጳጳሳት አጽም ያረፈበት የክብር ማረፊያ ነው።

በቤተክርስቲያኗ ረጅም ታሪክ ውስጥ እጅግ አስከፊው ምዕራፍ በ16ኛው ክፍለ ዘመን በአህመድ ግራኝ ወረራ ወቅት የተፈጸመው ነው። በ1531 ዓ.ም የግራኝ ጦር የቤተክርስቲያኗን ውድ ቅርሶችና የነገሥታትን መቃብር ከዘረፈ በኋላ፣ ታሪካዊቷን ቤተክርስቲያንና ግምጃ ቤቷን ሙሉ በሙሉ አቃጥሏታል። ጥቃቱ ከመፈጸሙ አስቀድሞ ታቦቱ በምስጢር ተሰውሮ መትረፉ ባይዘነጋም፣ በቤተክርስቲያኗ ላይ የደረሰው ጉዳት የከፋ ነበር። ከግራኝ ወረራ በኋላ እንደገና ብታገግምም፣ በ1710 ዓ.ም በኦሮሞ ኃይሎች ዳግመኛ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባታል።

 ከ500 ዓመታት በኋላ "ታሪክ ራሱን ይደግማል" እንዲሉ፣ በአትሮንሰ ማርያም ላይ ዳግመኛ "ግራኛዊ" ጥቃት ተፈጽሟል። የካቲት 28 ቀን 2017 ዓ.ም የተፈጸመው ጥቃት፣ የቤተክርስቲያኗን አስተዳዳሪ ጨምሮ በርካታ ካህናትን፣ ዲያቆናትንና ምዕመናንን ለሞትና ለከፍተኛ ጉዳት ዳርጓል። ይህ አሰቃቂ መርዶ የተሰማው በአሩሲው የኦርቶዶክስ ምዕመናን እልቂት የሀዘን ድባብ ውስጥ ባለንበት ወቅት ነው። ይህ ሁኔታ ካልተገታና ስር ነቀል መፍትሄ ካልተገኘለት፣ መከራው ከ16ኛው ክፍለ ዘመን የ15 ዐመቱ የግራኝ አሕመድ ጥፋት በከፋ ሁኔታ እንደሚቀጥል የሚያሳይ ተደጋጋሚ የደወል ድምጽ ነው።

በአትሮንሰ ማርያም ላይ የተፈጸመው ጥቃት፣ በኢትዮጵያ ታሪክ፣ ሥልጣኔና መንፈሳዊ ቅርሶች ላይ እየተካሄደ ላለው ስልታዊ ጥቃት አንዱ ማሳያ ነው። እንደ አትሮንሰ ማርያም ያሉ ምትክ የማይገኙላቸው ታሪካዊ ስፍራዎች ላይ የሚፈጸመው ጥቃት፣ የኢትዮጵያን መንፈሳዊ ታሪክ ከሀገሪቱ የመደምሰስና ታሪክን በአዲስ መልክ የመቅረጽ አደገኛ አካሄድ ነው። በተለይም በአሩሲና በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች እየታየ ያለው ክርስቲያኖችን ከየአካባቢያቸው የማጽዳት ድርጊት፣ ይህንን ታሪካዊ አሻራ የማጥፋት ዘመቻ ወደ ገሃዱ ዓለም እልቂት የለወጠ መሆኑን በግልጽ እያየን ነው።

በሌላ በኩል፣ በአክራሪ የውሀቢያ አስተሳሰብ አራማጆች የሚቀነቀነው ታሪክን የመቀየር ዘመቻ፣ 'አል-ነጃሺ' የተሰኘውን የሐሰት ትርክት በማራገብ 'ኢትዮጵያ የእስላም ሀገር እንደሆነች' ለማሳየት በስፋትና በተደራጀ መልኩ እየተሠራ ነው። ይህ አካሄድ ከ 'ወሎ የእስልምና ማዕከል ነው' ከሚል አክራሪ ብሔርተኝነት ጋር ተዳምሮ፣ በክልሉ የሚገኙ ጥንታዊ ክርስቲያናዊ አሻራዎችን በማጥፋት የኢትዮጵያን ታሪክ በአዲስ መልክ ለመጻፍ የሚደረግ ስልታዊ ጥረት ነው።

በአትሮንሰ ማርያም ላይ የተፈጸመው ጥቃት፣ በአንድ ቤተክርስቲያን ላይ ብቻ የተሰነዘረ ሳይሆን፣ በጠቅላላ በኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያንና በኢትዮጵያዊነት ማንነት ላይ የተቃጣ የጥፋት መንገድ ነው። ታሪክን በሐሰተኛ ትርክት የመቀየር፣ ክርስቲያናዊ አሻራዎችን የማጥፋትና ቀጣዩን ትውልድ ከሥሩ የመንቀል ወይም ማንነት የማሳጣት አካሄድ በዚሁ ካልቆመ፣ እልቂቱ እጅግ አደገኛ ወደ ሆነ ምዕራፍ እየተሸጋገረ መሆኑን ለመረዳት አዳጋች አይደለም።

እስካሁን እንደታዘብነው፣ ከኦርቶዶክሳዊያን አንጻር 'መንግሥት ይጠብቀናል' የምንለው ተስፋ ከንቱ ሆኗል። ይልቁንም፣ መንግሥት ለጥቃቱ ሽፋን በመስጠት ወይም ዝምታን በመምረጥ በወንጀሉ ተባባሪ መሆኑን በግልጽ እያሳየን ነው። በአሩሲ፣ በአትሮንሰ ማርያምና በሌሎች አካባቢዎች እንደታየው፣ ኦርቶዶክሳዊ ክርስቲያኖች የሚያጠቃቸው እንጂ የሚከላከልላቸው መንግሥትም ሆነ የመንግሥት ተቋም የላቸውም። በመሆኑም፣ በገዛ ሀገራቸው እንደ አራዊት እየታደኑ ያሉ ኦርቶዶክሳውያን ራሳቸውን ማደራጀት፣ በየአካባቢያቸው መከላከል እና ህልውናቸውን ማስጠበቅ ብቸኛውና የመጨረሻው አማራጭ መሆን ከጀመረ ቆይቷል።
Share on Google Plus

ስለ የተለጠፈበት ቀን

    Blogger Comment
    Facebook Comment