✍ ሚካኤል ዘኢትዮጵ
እብዱ ጀሊል የተባለው የተረት ጸሐፊ እስልምና ከክርስትና በፊት እንደነበረ አድርጎ ያቀረበው ሙግት በሃይማኖታዊ ትርጓሜ እና በተጨባጭ የታሪክ እውነታ መካከል ያለውን ልዩነት ካለመረዳት የሚመነጭ አስቂኝ ጨዋታ ነው። ጸሐፊው "ኢስላም" የሚለውን ቃል "ለፈጣሪ መገዛት" በሚል ሰዋሰዋዊ ትርጉሙ ብቻ በመጠቀም፣ የታሪክን እውነት ለመቀየር ይሞክራል። ሆኖም ግን የታሪክ መዛግብት፣ የሃይማኖት መጻሕፍት እና የምድር ውስጥ ቁፋሮዎች (Archeology) ይህንን ተረት ፈጽሞ አይቀበሉትም።
1. የታሪክ እና የዘመን ስሌት እውነታ፡
ከታሪክ እና ከሳይንሳዊ መረጃዎች አንጻር ክርስትና ከእስልምና በ600 ዓመታት ቀድሞ የተመሠረተ ሃይማኖት ነው። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያስተማረው በመጀመሪያው ክፍለ ዘመን ሲሆን፣ ሙሐመድ እስልምናን ማስተማር የጀመረው ግን በ7ኛው ክፍለ ዘመን (በ610 ዓ.ም አካባቢ) ነው። ይህ ግልጽ የታሪክ ክፍተት እያለ "እስልምና ቀድሞ ነበረ" ማለት የታሪክን እውነታ መካድ ነው። ቁርአን በሱረቱ አል-ዒምራን (3:67) ላይ አብርሃም "ሙስሊም" እንደነበረ ቢናገርም፣ ተፍሲሮች (ለምሳሌ ተፍሲር ኢብኑ ከሲር) እንደሚገልጹት ይህ የሚያሳየው "የአንድ አምላክ አምላኪነትን" እንጂ ዛሬ የምናውቀውንና በሙሐመድ የመጣውን ሸሪዓ፣ ሕግጋት እና የሶላት ሥርዓት አይደለም።
2. በአርኪኦሎጂ ምስክርነት የእስልምና ሽታው አለመገኘት፡
አንድ ማኅበረሰብ ወይም ሃይማኖት በታሪክ ውስጥ "ነበረ" ለማለት ሊጨበጡ የሚችሉ አርኪኦሎጂያዊ ማስረጃዎች ያስፈልጋሉ። ለምሳሌ የጥንቷ ግብፅ ከክርስቶስ ልደት በፊት ምን ትመስል እንደነበረ በቅርጻቅርጽ እና በቁፋሮ ይታወቃል። እብዱ ጀሊል እንደሚለው እስልምና ከክርስትና በፊት የነበረ ከሆነ በሙሐመድ የትውልድ ስፍራዎች (መካና መዲና) ውስጥ የሚገኙት ጥንታውያን ፍርስራሾች ለምን "ሙስሊም" የሚባል ማኅበረሰብ አያሳዩም? በተቃራኒው በነዚህ ቦታዎች ደጋግመን ብንቆፍር የሚገኘው የዓረብ ጣኦታውያን፣ የአይሁድ እና የክርስቲያኖች አሻራ ብቻ ነው። ከ7ኛው ክፍለ ዘመን በፊት "ሙስሊም" የሚል መጠሪያ ያለው ማኅበረሰብ፣ መስጂድ ወይም እስላማዊ ጽሑፍ በምድሪቱ ላይ ጭራሽ ሽታውም የለም።
3. የሊቃውንት እና የጽሑፍ መረጃ እጥረት፡
አንድ የሃይማኖት ሥርዓት ካለ ያንን ሥርዓት የሚያስተምሩ ሊቃውንት እና የሚመሩባቸው መጻሕፍት መኖር ነበረባቸው። የጥንት ግብፃውያን በፒራሚዶቻቸው ላይ፣ አይሁዶች በብራናዎቻቸው ላይ፣ ክርስቲያኖችም በወንጌላትና በሊቃውንት ድርሳናት ታሪካቸውን አስፍረዋል። እብዱ ጀሊል በሚለው "ጥንታዊ እስልምና" ውስጥ ግን የነበሩ ሊቃውንትም ሆኑ በድንጋይ ላይ የተቀረጹ መረጃዎች አይገኙም። ይህም የሚያሳየው ጸሐፊው የታሪክን ሳይንሳዊነት ወደ ጎን በመተው ለማያነበውና መን*ጋው ማኅበረሰብ በጭፍን ተረት ላይ የተመሠረተ ድርሰት ማቅረቡን ነው።
4. የታሪክ ስርቆት እና ማጭበርበር፡
እብዱ ጀሊል ሊጠቀምበት የሚሞክረው ብልሃት የቀደሙትን ነቢያት (እንደ አብርሃም፣ ሙሴ እና ዳዊት) ታሪክ በመስረቅ "ሙስሊም ነበሩ" ብሎ ማቅረብ ነው። ሆኖም እነዚህ ነቢያት የኖሩበት ባሕል፣ የቋንቋ ዘይቤ እና የሕግ መዋቅር ከዓረብ እስልምና ጋር ፈጽሞ የማይገናኝ መሆኑን አርኪኦሎጂ ያረጋግጣል። በመካ የነበረው የ360 ጣዖታት አምልኮ እንጂ "እስልምና" እንዳልነበረ ቁርዓኑ ራሱ የሚመሰክረው ሀቅ ነው።
እብዱ ጀሊል "ቀዳሚዎቹ ነቢያት ሙስሊም ነበሩ" ሲል፣ እነዚህ ነቢያት የሚናገሩት ቋንቋም ሆነ የሚከተሉት ባሕል ከዐረብ እስልምና ጋር ያለውን ሰፊ ልዩነት ሆን ብሎ ይዘነጋል።
አብርሃም የኖረው በለሙ አካባቢ (Mesopotamia) ሲሆን ይናገር የነበረውም የጥንት አረማይክ ወይም አካድያን ዝርያ ያላቸውን ቋንቋዎች ነው። ሙሴ እና ዳዊት ዕብራውያን ናቸው። ቋንቋቸውም ሆነ የጽሑፍ ስልታቸው ከዓረብኛ ቋንቋ ስርጭት በመቶዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት የነበረ ነው።
ሙሴ የተቀበለው ኦሪት (Torah) የራሱ የሆኑ 613 ሕግጋት (Mitzvot) አሉት። እነዚህ ሕግጋት ከእስልምናው "ሸሪዓ" ጋር በይዘትም ሆነ በአፈጻጸም ይለያያሉ። አርኪኦሎጂያዊ የብራና ግኝቶች (እንደ ሙት ባሕር ጥቅልሎች - Dead Sea Scrolls) የሚያረጋግጡት የእነዚህ ነቢያት እምነት አይሁድ (Judaism) መሆኑን እንጂ እስልምና የሚል ስያሜ ወይም የዓረብ ባሕል እንደሌለው ነው።
በመካና በመዲና አካባቢ እንዲሁም በመላው የዓረብ ምድር የተገኙ የድንጋይ ላይ ጽሑፎች (Inscriptions) የእብዱ ጀሊልን ሙግት ውድቅ ያደርጉታል። በሳፋይቲክ (Safaitic) እና በታሙዲክ (Thamudic) ጽሑፎች ላይ የሚገኙት ምልጃዎች "አላት" (Al-Lat)፣ "ዑዛ" (Al-Uzza) እና "መናት" (Manat) ለተባሉ የአረብ ጣዖታት የቀረቡ ናቸው። ከ7ኛው ክፍለ ዘመን በፊት "ሙስሊም" የሚል መጠሪያ ወይም "ሙሐመድ ረሱሉላህ" የሚል ዐረፍተ ነገር በአንድም ድንጋይ ላይ ተቀርጾ አልተገኘም።
በተቃራኒው ግን በናግራን (ደቡብ ሳዑዲ) እና በሰሜን ዓረቢያ አካባቢ የሚገኙ አርኪኦሎጂያዊ ግኝቶች የመስቀል ቅርጾችን እና በግዕዝ፣ በሶርያክ (Syriac) እና በጥንት አረማይክ የተጻፉ የክርስትና መዝገቦችን ያሳያሉ። ይህም ከእስልምና በፊት ክርስትና በአካባቢው በስፋት እንደነበረ ህያው ምስክር ነው።
ሌላው እብዱ ጀሊልን የማያራምደው ጉዳይ የዓረቡ ዓለም አል-ጃሂሊያ (የድንቁርና ዘመን) ምስክርነት ነው። ቁርዓኑ ራሱ ከሙሐመድ መምጣት በፊት የነበረውን ዘመን ጃሂሊያ (ድንቁርና) ይለዋል። ይህ ስያሜ በራሱ በምድሪቱ ላይ የእስልምና ትምህርት እንዳልነበረ ለመግለጽ የተነገረ ነው።
በቁርዓን (ሱረቱ አል-በቀራህ 2:135) ላይ አይሁዶችና ክርስቲያኖች "የእኛን እምነት ተከተሉ" ብለው ሲከራከሩ ይታያል። ይህ የሚያሳየው እነዚያ እምነቶች በታሪክ መድረክ ላይ ቀድመው የነበሩ፣ መጻሕፍትና ሊቃውንት የነበሯቸው መሆኑን ነው።
እብዱ ጀሊል እንደሚለው እስልምና ከቀደመ፣ የጃሂሊያ (የጣዖት አምልኮ) ዘመን ለምን አስፈለገ? በካዕባ ውስጥ የነበሩት 360 ጣዖታት ከየት መጡ? ቀዳሚዎቹ ሙስሊሞች ከነበሩ እነዚህን ጣዖታት ለምን አልተከላከሉም? ለሚሉት ጥያቄዎች የታሪክ ምላሽ "ሙስሊም የሚባል ማኅበረሰብ በወቅቱ አልነበረም" የሚል ብቻ ነው።
እብዱ ጀሊል የሚያደርገው ተግባር ታዲያ በታሪክ ጥናት Anachronism (ዘመንን ማዛባት) ይባላል። ይህም ማለት ዛሬ ያለን ነገር ወይም ስም በታሪክ ውስጥ ባልነበረበት ዘመን እንደነበረ አድርጎ ማቅረብ ነው። ለምሳሌ፦ "ዐፄ ቴዎድሮስ በሞባይል ስልክ ደወሉ" እንደማለት ነው። አብርሃም በኖረበት ዘመን "እስልምና" የሚል ተቋማዊ ስም፣ መስጂድ፣ "አላህ አክበር" የሚል አዛን ወይም ረመዳን የሚባል ጾም አልነበረም። እነዚህ ሁሉ በ7ኛው ክፍለ ዘመን በሙሐመድ አማካኝነት የተደነገጉ የዓረብ እስልምና መገለጫዎች ናቸው።
በአጠቃላይ የእብዱ ጀሊል ጽሑፍ ምንም ዓይነት የታሪክ፣ የሎጂክ ወይም የአርኪኦሎጂ ድጋፍ የሌለው የፈጠራ ተረት ነው። ታሪክ የሚሠራው በመረጃና በተጨባጭ ማስረጃ እንጂ ቃላትን በማጣመም በሚፈጠር የዕ*ብደት ምኞት አይደለም።
Blogger Comment
Facebook Comment