ሥውሩ መነኩሴ [ክፍል ፫] የመጨረሻው ክፍል

✍ ቲና በቀለ | ኢትዮጵያ አውታር 

....ስነ_ስእላቱ ስመለከት የቤተክርስቲያን ስእላት ሁሌም ከሚያስተላልፉት መልእከት ለየት ባለ የአሳሳል ስነ ዘዴ የተዋበ ነው።

ይምጡ እንጂ የሚል ድምጽ ከጎጆዋ ጣራ ስር ወጥቶ ከተመስጦዮ አባነነኝ። በገዳማት የሚኖሩ መነኮሳት ማንኛውንም አይነት ሰው አንቱ ብሎ የመጥራት ልምድ አላቸው።

#ያየሁትን እያብሰለሰልኩ ወደ ቤቷ አመራሁ.... ጋራውን ታካ በኖራ የተገነባችው ውብ ጎጆ ቤት ከውጭ በኩል ጓሮዋ በአትክልቶች የተሞላች ስትሆን ከውስጧ እንደገባሁ ለአይንም ለልብም የሚደንቅ ነገርን ተመለከትኩ።

#ወለሏ በቀይ አፈር ከተለቀለቀችው ጎጆ ይልቅ በኖራ አፈርና በተጠረቡ እንጨቶች ዙሪያውን ግድግዳው ጋ የተሰራችው የመጻህፍ መደርደሪያ ሙሉ መጻህፍ ሞልቶባት በተመለከትኩ ጊዜ የህዝብ ቤተመጻህፍት ውስጥ እንጂ ከአንድ የመነኩሴ ቤት የገባሁ አልመስል አለኝ።

በተለያዩ ቋንቋወች የተጻፉ በርካታ መጻህፍ በስርአት ተደራርበው ተቀምጠው ሳይ በመገረም መነኮሴውን ተመለከትኳቸው እሳቸው አንዳች ነገር እያዜሙ ለእኔ ምግብን ለማዘጋጀት ደፋ ቀና ይላሉ...!

ሰበዝና አክርማ በማዋህድ በወስፌ እየተነደለ በማሰናሰል በባህላዊ መንገድ የሚሰራ ቆለምሽሽ በሚባል መመገቢያ ላይ የገዳሙን ዳቤ በበርብሬ ለውሰው ከሱፍ የሚዘጋጂ ጭልቃን ከእንስራው አንቆርቁረው ይመገቡ ይመገቡ ብለው አቀረቡልኝ።

ከጀርባ የሆነ ነገር እንደ ተመለከትኩ ውስጥ ገብቸ ባየሁትም እንደተገረምኩ እና ሀሳብ ውስጥ እንደጣለኝ የገባቸው ይመስላሉ ካለሁበት ጭንቀት ለመገላገል በሚመስል ሁኔታ ስለተለያዩ ነገሮች እያነሱ ይጠይቁኝ ጀመር።

ወደ ገዳሙ ከመጣሁ ሶስት ድንቅ መነኮሳትን አገኘሁ አንደኛው ምንነታቸውን እንኳ ሳለውቃቸው የማይፈታ እንቆቅልሽ አሸክመው ተለዪኝ፤ #ሁለተኛው ምን እንዳሉኝ እንኳ ጭራሹን ሳልረዳቸው ሸኙኝ፤ #ሶስተኛው ደግሞ ቁምነገርን እንደ ቀልድ እያወሩ ከአምሮዬ በላይ በሆነ ልሳን ግራ በሚያጋባ የሂወት ፍልስፍና ይንጡኝ ጀመር።

በሶስቱም ቦታ ላይ የወይን ሃረግ ፍሬን በተለያየ አጋጣሚ እና ሁኔታ መመልከቴ ደግሞ ሌላ ጥርጣሬ ውስጥ ከቶኛል።

ወደ ምፈልገው ጥያቄ ለመውሰድ እያኮበኮብኩ ይህንን ያህል መጻህፍ የእርሶ ነው? አባ አልኳቸው የማያውቁት ይመስል ቀና ብለው እየተመለከቱት በፈገግታ አወን ያለኝ ትልቁ ውዱ ሃብቴ ይህ ነው ለበርካታ አመታት የሰበሰብኳቸው ልጆቸ ማለት ናቸው። 
መነኩሴው የተማሩ፣ ብዙ የተመራመሩ፣ አለም ላይ በነበራቸው ሂወት የስኬትን ቁንጮ የተቀዳጁ ሰው መሆናቸው ከሁኔታቸው ከንግግራቸው ከሁለንተናዊ ማንነታቸው መረዳት ይቻላል።

#በገዳሙ ውስጥ የተለያዩ የእጂ ስራ ውጤቶችን በመስራት፣ የጸሐይ ብርሃን መሰብሰቢያወችን በመገጣጠም፣ ለገዳሙ ዘመናዊ የእርሻ እና የመስኖ ግባእቶችን በማዘጋጀት፣ እንዲሁም የተለያዩ ምድር ውስጥ የሚገነቡ ሚስጥራዊ የዕቃ ማስቀመጫ የህንጻ ዲዛይኖችን ያለ ብረትና ሲሚኖት መገንባት፣ በቋሚነት በገዳሙ ውስጥ የሚሰሩት ስራ ነው።

ከዛ ውጭ ብዙ መጻህፍትን በመጻፍ ከአፋዊ የእውቀት ሽግግር ወደ መጻህፍዊ ሰንደው በማዘጋጀት ለተተኪው ትውልድ ለማቃበል ብራና ዳምጠው ቀለም በጥብጠው ብዕር ቀርጸው የብራና መጻህፍትን ያዘጋጃሉ ።

ከሂወታቸው አኗኗርን፣ ከኖራቸው ብርታትን፣ ከርዕዮተ አለማቸው የኑሮ ስነ ዘዴያቸውን፣ በአጠቃላይ የሂወትን ልምዳቸውን ያጫዉቱኝ ዘንድ ልቤ ፈልጓል ምን ብየ እንደምጀምር ግራ ቢገባኝም አባ ይህንን የምንኩስና ሂወት እንዴት እንደመረጡት ቢያጫዉቱኝ?

በመቀጠልም እኔ እንደተረዳሁት እርሶው በአለሙ የኖሩ፣ በእውቀትም የተራቀቁ፣ እንደሆኑ ነው ይህ ያሉበት ደግሞ ከዚያኛው እጂጉን የተለየ በእግዚአብሔር መመርጥ ነውና ከቁሳዊዋ አለም ይህኛውን ሂወት እነዴት መረጡ?

መልሱን ለመስማት ከመጓጓቴ የተነሳ ደረቴን ከ እግሮቸ ለጥፌ ጀሮየን እንደ ቆቅ አቁሜ አይን አይን እመለከት ጀመርኩ...

በእርግጥ አሉ ጠይሙ መነኩሴ በተንጀረገገ ጥቁር ጢማቸው ያሉ ነጫጭ ሽብቶች እየነካኩ። 

ሃብት፣ ንብርት፣ ገንዘብ፣ ሁሉም ቁሳዊ ናቸው ቁሳዊ ህላዊነት ደግሞ ከንቱ ነው። ማንኛውም ቁስ አካል የሚገለጸው ባሉት የአይነት መገለጫወች አይደለምን?!
ማለቴ የስሜት ህዋሳቶቻችን ተገዢ ከሆን ሁሌም ቢሆን የቁስ ባሪያወች ነን የቁስ ባርነት ደግሞ ዘላለማዊ ሞትን ታመጣለች።

እንግዲህ በአለሙና በገዳማዊያኑ ያለው ትልቁ ልዩነት ለቁሳዊነት ያለን አመለካከት ልዩነት የፈጠረው ነው።
ከቀለም፣ ሽታ፣ አይነት ፣መጠን፣ ቅርጽ ፣ውበት ፣ድምቀት፣ ምቾት፣ ለእነዚህ ያለን አመለካከት ነወ እንግዲህ የሰውን ሁለንተናዊ የሂወት ኡደቱን የሚወስኑት።

ቁሳዊነት ከመንፈሳዊ አለም ጋር የማይወዳደር የማይለካካ መሆኑን ለመረዳት አስተውሎት ያስፈልጋል፤ ለዚህም ነው ይህንን አለም የመርጥኩት... በእርግጥ ንግግራቸው ልቤን ቢማርከኝም የምፈልገውን ነገር እንዳልነገሩኝ ለእኔም ለእርሳቸውም ገብቿቸዋል...ንግግራቸው እጂግ ማራኪ እና ውብ እውቀትና ብልሃት የተሞላበት ስለሆን ቢዘገይም የችግሮቸን መፍትሄወች እሳቸው ጋ እንደማገኝ እርገጠኛ ሁኛለሁ።

ጀሮአቸውን እንደሰጡኝ ሲገባኝ ጥያቄን ቀጠልኩ.. በየ ባዕቱ ስዞር መነኮሳት ከጎጇቸው እንኳ ሳይወጡ በጽናት እና በጽሞና ያለ ማውራት በአርምሞ እንዴት መኖር ተቻላቸው? ለምንስ ስንፈልጋቸው አናገኛቸውም? ለጥያቄወቻችን መልሶችንስ ስለምን አርቀው ይቀብሩብናል? 

ለምን ጥበብን ለመግለጥ በሚስጥር የተሞላ መንገድን ይመርጣሉ? በእርግጥ ለመቀበል እኛ ስለማንችል ነው ወይስ እነሱ ንፉግ ሁነው?

የእኛ ትውልድ እርግማን ተሸካሚ ሁኖ ይሆን ከተካፈላችሁት ሚስጥርና ጥበብ ማታካፍሉን? ከተቀበላችሁት የማታቃብሉን ከተገለጠላችሁ ማትገልጡልን?! 

የሚወራልን ነገር በእውነተ አለ? ወይም በዘመናት የተሸበበ ዘመን ያስረጀው የአፈ ታሪክ ባለቤቶች ነን?!

ጠቢባን አባቶቻችን ፀሐይን ያቆሙ፣ መላከ ሞትን ያወገዙ፣ በደመና የተጓዙ፣ ሰማያትን የመረመሩ፣ ምድርነንም ያጠኑ፣ በእወቀት የነጠቁ፣ መዳሃኒትን አዋቂወች፣ እጂግ የተራቀቁ፣ ከአንድ አለት ላሊበላን የገነቡ፣ በንፋስ አውታር አክሱምን ያቆሙ፣ ፍልሱፎች፣ ስልጡኖች፣ ከስልጣኔ የተቋደሱ፣ ከአለም የቀደሙ ሃያላን ነበሩ ትሉናላችሁ... ከእውቀታቸው እንድንካፈል ከጥበባቸው እንደንቋደስ በፈለግን ጊዜ ጥበቡን አርቃችሁ ትቀብሩብናላችሁ...ሁሉንም በጽሞና ታልፉታላችሁ...ዝምተው ምንድን ነው

#የአባቶቻችን ልጆች እንድንሆን ትፈልጋላችሁ መንገዱን ደግሞ ትሰውሩብናላችሁ፤ የጥበብ ጫፏን ትነግሩን እና መዳረሻዋን ግን ትሸሽጉናላችሁ? ስንርቃችሁ ጎተት ስንጠጋችሁ ገፋ ታደርጉናላችሁ፤ የአንድን እውነት መዳረሻ የሌሎች አልቆ መሳፍርት ጥያቆወች መጀመሪያ ይሆንብናል፤ እና እኛ ወይስ እናንተ ነን የታሪክ ተጠያቂወች? የእኛ አለመቀበል ወይንስ የእናንተ አለመስጠት ነው ክፍተቱ?!... 

#ለበርካታ ጊዜያት የሚሰማኝን ነገር ስሜታዊነት በተቀላቀለበት አነጋገር ነበር የተናገርኳቸው...። እጂግ በተረጋጋ ሁኔታ አድምጠው ከናፍሮቻቸውን በፈገግታ አጂበው ከፈቱና ''አብዝተው ዝም የሚሉት ድንገት ስንናገር የማሰብ ችሎታችን ይቀንሳል ብለው ይሆናላ '' አሉና ፈገግ አሉ...

በአቅማችሁና በምኞቶቻችሁ መካከል ያለው ክፍተት አላስተዋላችሁም፤ ምኞቶቻችሁ ሁሉ ከአቅሞቻችሁ የገዘፉ ናቸው፤ በምኞት ብቻ የሚገኝ በፍላጎት ብቻ የሚመጣ እውቀትና ጥበብን ከወዴት ነው የምትፈልጉት?

በአቅማችሁ እና በምኞቶቻችሁ መካከል ያለውን ክፍተት ሁለት ነገር የሞላዋል አነሱም እውቀትና እምነት ናቸው።
እውቀትና እምነት ወደ ምኞቶቻችሁን ሲገፏችሁ ያኔ ከእኛ እንደ አንዱ ትሆናላችሁ፤ ከእውቀታችን እውቀትን፣ ከጥበባችንም ጥበብን፣ ትከፈሉ ዘንድ ፈቃዳችን ይሆናል።

ለዚህ ብቁ ላልሆነ ምኞት ብቻ ለናጠው፣ ሰሜት ብቻ ለገፋው ትውልድ፣ ስለምን እኛነታችንን እንግለጥ?
#በልቦናው ለማያዳምጥ በሆዱ ለሚሰማ ስለምን ብልን ሚስጥራችንን እንግለጥ?

ምዕመኑ መስማትና ከሚፈልጋቸው ነገሮች ውጭ ብትነግረው አይሰማም፤ ማየት የሚችለው፣ ብርሃን የሚያሳየውን ብቻ ከሆነ፤ የሚሰማውም፣ ድምጽ የሚያሰማውን ብቻ ከሆነ፤ በእውነት ይህ ህዝብ ያያል ወይስ ይሰማልን?!

#ጽሞናችንን የሚያደምጥ ነግግራችንን ይሰማል፤ በዝምታችን ውስጥ ብዙ ሚስጥራትን እንናገራለን፣ በከናፍሮቻችን እስክንገልጥላችሁ የምትጠብቁ ከሆን የልቦናችን ሚስጥር ፈጽሞ ልታውቁት አትችሉም።

#በልባችን ያሉትን ሚስጥራት ለማየት የሚችሉት በልቦናቸው ሚስጥሮችን የያዙ ብቻ ነው። አለም ላይ እንዳሉ የአለሙ ጠቢባን የኪሶቻችንን እየሰጠን የልባችሁን አንወስድባችሁም። ይሉቁንስ ለመሸከም ብቁ በሆናችሁበት ጊዜ ያለስስት የልባችንን እንሰጣችሁ አለን እንጂ።

ጥበብ ሻማ ስር እንደተወሸቀች ክር ማለት ነች፤ ፈጽማ መገለጥም ሆነ ፈጽማ መሰወርን አትፈቅድም፤ ፈጽማ ከተሰወረች ለኩሶ የሚያበራትን ታጣለች፤ ፈጽማም ከተገለጠችም ሳትበራ ትጠፋለች። ለዚህም ነው ጥበብ ጅማሬዋ እንጂ ፍጻሜዋ አትገለጽም የሚባለው። ስለዚህ እውነትን ለማግኘት አንዳችን እንድንናገር ሌላችን እንድንረዳው ሲሆን ብቻ ነው። ታድያ ጥበብ ተገለጠች የሚባለው የተነገረው በሰሚው ልቦና ቦታ አግኝቶ ቃሉ ህያው ሲሆን ነው።

አዎ እውነት ነው! እውነትና ጥበብን ምንገልጠው ለራሳችን ብቻ ነው፤ ያልመረመርናቸው በርካታ ድንቅ እውነቶች ስላሉ፣ ፈልገን ባገኘናቸው ጊዜ የምንናገረው ለራሳችን ብቻ ነው።

ግን ሁሌም በዝምታችን ውስጥ ጮክ ብለን ስንናገር በልባቸው የሚያዳምጡ ሰወች ያዳምጡናል። ታድያ ወዳጄ የእኛ አለመናገር ሳይሆን የሰወች የልቡና ጆሮ አለመከፈት ነው፤ ታድያ ለዚህ ተጠያቂው ማን ነው?!

#ለመነኮሳት ጽሞናቸው ልብሳቸው ነው ፤ሰው እኮ የሚያወራው ከውስጡ ከራሱ ከህሊናው ጋር መስማማት ሳይችል ሲቀር ሰላምን ሲያጣ ነው።

መነኮሳያቱ ደግሞ በልቦናቸው ጋ ካለው እግዜሩ ጋር ስለሚያወሩ በከናፍሮቻቸው የሚገለጥ ቃላት የላቸውም።  ጽሞናቸው ለአይኖቻቸው ብርሃን ለልቦናቸው ደስታን ያጎናጽፏቸዋል።

በርካታ መነኮሳት በውስጣቸው እውቀትን በልቦናቸው ጥበብን ቢይዙም በአደባባይ የማይገልጡት በኣፋ የማይናገሩት ምክኒያት የጥበብን ክብሯን ላለማሳጣት ነው''።....አሉና ከተቀመጡበት አርጩሜ አንገታቸውን ወደ ምድር ቀርቅረው ዝም አሉ....!

እኔም ከአንደበታቸው የሚወጣው ቃላት የልቦነዬን ፍላጻ እየመታ ለጠየኩት ተጠያቂነት ምክኒያቱ ራሴው እንደሆንኩ ተረዳሁ....

አባ አልኮቸው ከአቀረቀሩበት ቀና እያሉ አቤት አሉኝ... ከትላንት ማታ ጀምሮ ያልጠበኩት ነገር ተከስቶ ነበር..
ዛሬ ማለዳ ያገኘኋቸው መነኩሴ ባልገባኝ ነገር ሌላ ጊዜ ከተመለሰሰክ ''ዛቲ ይእቲ መካንየ '' ይች ነች ቦታየ ብለው ወደ አቀጠቀጠች የወይን ተክል ጠቆሙኝ። 

በመገርም ስሜት ይመለከቱኛል ያልኳቸው መነኩሴ ነገሩ አዲስ ስላልሆነባቸው አንገታቸውን ነቅንቀው ዝም አሉኝ። እጂግ አስጨንቆነኛል አባ ገ/ሂወት የሚባሉ አጠር ያሉ መነኩሴ ያውቃሉ? 

ማን አልከኝ አሉ በመገረም ስሜት እኔም ቀጠልኩና አባ ገ/ሂወት... አጠር ያሉ ሙሉ ነጭ ጢም ከአስኬማቸው የተረፉ ጸጉራቸው ሉጫ የሆነ ... መጡ እንዴ? አሉ ማለቴ አሉ መነኩሴው የት አገኘሀቸው? ማለት እንዴት አሉና ለተወሰነ ጊዜ ዝምታ ነገሰ...ምነው ምነው ያውቋቸዋል አልኩ ነገሩን ለመስማት ካለኝ ጉጉት የተነሳ።

አይ አይ አሉና የሚያውቁት ነገር እንዳለ ከሁኔታቸው ብረዳም ሊገልጡልኝ ፈቃዳቸው አለመሆኑን ተረዳሁ።

#የወይን_ፍሬ ሃረግ ትርጉሙ ምን ይሆን አልኳቸው እኒህ መነኩሴ እውነትን ለመገለጽ ቢከብዳቸውም ከተቀመጡበት በዝግታ ተነስተው ወደ ተደረደሩት መጻህፍት አመሩ ረጂም ዘመናት ያስቆጠር የብራና መጻህፍ አውጥተው እያራገፉ ገልጠው ለጥያቄዬ ድንገት መልሱን ካገኘህ ብለው ሰጡኝ፣ ይህንን የጥንት ብራት ገልጨ በጽሞና ሳነብ ከተወሰነ ገጾች በኋላ በተለያየ ቀለማት የተሳሉ የተለያዪ እጽዋቶች ስምና ጥቅሞቻቸው እንዲሁም ውክልናቸው በስርአት ተቀምጠው ተመለከትኩ።

ከተዘረዘሩት እጽዋቶች አንዱ የሆነውን የወይን ዛፍ ከድርብርብ ፍሬወቻቸው ጋር ተመለከትኩ፤ ውክልናውን ስመለከት፤ የዘር ልምላሜ፣ መለወጥ፣ አንድነት፤ የሚሉ ትርጉሞችን ተመለከትኩ። ግራ እንደተጋባሁ ቀና ብየ ተመለከትኳቸው የራሴን አንድምታ ሳስቀምጥ... በእነዚህ ቃላት መሪ ቃልነት የተመሰረተ አንድ ስውር ማህበር ይኖርን የሚል ጥያቄ አቀረብኩላቸሰው....አንገታቸውን በመሰበቅ እንጃ አይነት ንግግር ተናገሩኝ።

ይቅርታ አሁን ትንሽ ስራ ስላለብኝ ልሄድ ነው ማደርያ ካላገኘህ ከዚህው ታድራለህ ሰላም ዋል....አሉና ከጎጆዋ በር ላይ ቁመው ዞር አሉ... በሂወትህ የሚያጋጥሙህን ሚስጥሮች በሙሉ ስትፈታቸው ፍችው ዞሮ ዞሮ የሂወት ሌላው ሚስጥር በመሆኑ ሞትን ያስናፍቃል እና ተጠንቀቅ! አሉኝ...

እየሆነ ያለው ነገር ግራ ገባኝ ይህ ነገር አጋጣሚ አይደለም። መጨረሻውን ካላወኩ በዘመኔ ሁሉ ያቅበዘብዘኛል።

የእግዚአብሔር ፈቃድ ይሁን አይሁን በሙከራየ ይረጋገጥ ብዬ አሰብኩ፤ የመንኩሴው ንግግር ጠንከር ያለ ነው በእርግጥ በዚህ ጉዳይ ላይ እንድገባበት ባይፈልጉ ኑሮ ለምንስ ከተደረደሩት መጻህፍት አውጥተው ስለወይኑ ሃረግ ፍሬ ትርጓሜ እንድረዳ ፈለጉ?!

ስለምንስ በፍለጋዬ ወቅት በምፈታው ሚስጥር የሌላ ሚስሮች በርን እነደሚከፍት እና ተስፋ እንዳልቆርጥ አስተነቀቁኝ?።

ይህ ነገር አጋጣሚ አይደለም በዘፈቀደ የተገጣጠሙ ነገሮች ሊሆኑ አይችሉም።

እሽ ይሁን በተጨነኩበት ሰወ አጥቸ በባዘንኩበት ስአት የአባ ገ/ሂወት መምጣት፤ ባልተለመደ አደገኛ በሆነ መንገድ ረጅሙን ጉዞ በአጭር ማጠናቀቅ፤ ለበርካታ አመታት ያልተከፈተ የተዘጋ ነው ከተባለው ጎጆ ቤት ውስጥ መገኘቴ፤ የአባ ገ/ሂወት በለሊት ድንገት መሰወር፤ የወይን ፍሬ ከትራሴ ላይ ማግኘቴ ፤የአረጋዊዉ መነኩሴ ''ዛዕቲ ይዕቲ መካንየ '' የወይን አትክልት እየጠቆሙ ያች ናት ቦታየ ያሉት፤ ከጋራው ስር የተመለከትኩት የሸራ ላይ ስእል የተሰናሰለ ወይና ሀረግና እና ፈሬው....ይህ ሁሉ እንዴት ተራ ግጥጥሞሽ ነው ልበል? ከዚህ ቦታ በዘፈቀደ የሚሆነ አንዳችም ነገር የለም ነበር መነኩሴው ያሉኝ። 

ስለዚህ መዳረሻውን ባላወኩት መንገድ መቋጫው ባልተገለጠልኝ ውስብስብ ጉዞ የተዳፈነ ሚስጥር ዙርያየን እንደከበበኝ ይሰማኛል።

የሂወት ዘመን አላማየ ከእወቀት መካፍል፣ ከጥበብ መቅመስ ነውና፤ የምፈልገው ነገር እኔንም ይፈልገኝ ይሆናል በሚል አቋም የነገሮችን መቋጫ ለማግኘት ከቀደመው መበርታት እንዳለብኝ ተሰማኝ።

''በሂወትህ የሚያጋጥሙህ ሚስጥሮችን በሙሉ ስትፈታቸው ፍችው ዞሮ ዞሮ የሌላኛው የሂወት ሚስጥር ሲሆንብህ ተጠንንቅ ሞትህን እንዳትናፍቅ''።

ይህ ቃል ምን ማለት ነው? ሚስጥሮች እንድትፈታ አግዝሃለሁ፣ የተፈታ የመሰለህ ነገር ግን ሌላ ውስብስብ ነገር ያመጣብሃል ለማለት ይሆን?

በእርግጥ አልኩኝ ለራሴ ከተቀመጥኩበት ከኖራ አፈር ከተሰራች መደብ እየተደላደልኩ።

በእርግጥ በትንሿ እድሜየ የተገነዘብኩት አንድ እውነት አለ። በአይነ ስጋ ከተገለጠችው አለም ከሚታየውና ከሚሰማው ውጭ በስጋ ብቃት የማትመዘን ና የማትገለጥ ሌላ ሌሎች የሚኖሩባት አለም አለች።
የምንም ነገር መጨረሻ ወይም መደምደሚያ ራሱ ምንም ነው። የማይቋጭ ጉዞ፣ መጨረሻ የለሌው ፍለጋ፣ ከተጀመረበት ፈቅ ሳይሉ ከተነሱበት መገኘት የሂወት አካል ናቸው።

በእርግጥ ፍለጋ ለሰዋዊ ስሜት አዲስ የሚመስል የነበር ግን ያልተገለጠን ግኝት ታስገኛለች፣ የተሰወረ ሲገለጥ ያለተገለጡ እልፎችን አዝሎ ይመጣል። በግትልትሏ አለም ምንም አዲስ የሚባል ነገር የለም፤ ድሮም የነበረ በጊዜ ውስጥ እስረኛ የሆነ ራሱ ጊዜ የሚፈታው እንጂ፣ ካለመኖር ወደመኖር የሚመጣ አንዳችም ጥበብ ሆነ እውነት የለም።

በአንድ ዘመን የተገለጠው በሌላኛው ጊዜ ስወር ይሆናል በዘመን ውስጥ መታሰር ሆነ መፈታት አለ። ከጊዜ መቅደምመ ሆነ መዘግየትም ዋጋ ያስከፍላል በጊዜ ከመዘግየት ይልቅ ግን ከጊዜ መቅደም ይሻላል። ለዛ ነው የዛሬቱ ኢትዮጵያ ከጊዜ መዘግየቷ ይህንን ሁሉ ዋጋ ሚያስከፍላት።

እኒህ መነኩሴ የተናገሩት ነገር ጥልቅ መልዕክት ያለው የሂወት ዘመን ስንቄ ሊሆን ይቻላል። #መነኩሴው ልክ ናቸው ሁሉም በተወሳሰበ ሚስጥር የተገነባ እንጂ በዘፈቀደ የተመሰረተ አይደለም። ፍጻሜ የሚመስሉን ነገሮች እልፍ መንታ መንገዶችን ይወልዳሉ። ቢሆንም ግን እውነትና እውቀትን ታላቋን ጥበብ መፈለጌ የሂወት ዘመን ስንቄ ነው።

ከኖራ መደብ ላይ እንደተቀመጥኩ ጎጆዋን በአይኖቼ አስሳለሁ ወደ ተደረደሩት መጻህፍት ተጠግቼ በትኩረት ስመለከት፤ ስለ መጻህፍት የሚገልጽ የገጽ ሽፋን ባለመኖራቸው የውስጡን ቀለም አይተው አንበበው ካአልተረዱ ምንነቱን ለማወቅ ይዘቱን ለመረዳት አዳጋች ነው።

#የተወሰኑትን እያነሳሁ እመለከት ጀመር ከዚህ በፊት የማላውቃቸው ያልተለመዱ መጻህፍት ናቸው። ስለ ስነ-ፍጥረታት፣ ፕላኔቶች፣ ስለ እጽዋቶች፣ እሳት ስለ ሚተፉ ድንቅ ፍጥረታት፣ ብረትን ስለሚያቀልጡ ማዕድናት፣ ስለ ዘረ-መል፣ መርበበተ-ሰሎሞን(ዲያቢሎስን በመረብ የመያዝ ጥበብ)፣ ስለ አለማት ክፍል፣ ስለ ዘመናት አቆጣጠር፣ ስለ ከዋክብቶች.. የተለያዩ ይዘት ያላቸው መጻህፍትን በግርምት ተመለከትኩ። እንዴት ከአንድ ግለሰብ ቤት እኒህን የመሳሰሉ ድንቅ መጻህፍት ሊገኘ እንደቻሉ ግራ ገባኝ። 

#በድንቅ_መገረም ውስጥ ሁኞ የእነሱ እና የእኛ አለመገናኘት የፈጠረው ትልቅ የታሪክ ክፍተት መኖሩን ተረዳሁ ይህ ክፍተት ደግሞ እንደ አገር የዉድቀታችን ምክኒያት ሁኗል።

#አለም ተመራምሮ ያልደረሰባቸው እንቆቅልሾችን የሚፈቱ መጻህፍት እንደ ዘበት በየ ጎጆው ቤት ተወሽቀው ተረካቢ ጠፍቶ ሚገልጣቸው አጠው የሸረሪት ድር እያደራባቸው ያረጃሉ።

ስለ መጻህፍቱ እያሰብኩ ከመደርደሪያው ስር ያየሁት ነገር ትኩረቴን ሳበኝ እና ከተቀመጥኩበት በዝግታ ተነሳሁ።

አራት ማዕዘን ቅርጽ ያለው ነገር ትኩረት እንዳይስብ ተደርጎ በአረጀ ጥቁር ፍጦ ተጠቅልሎ ተቀምጧል። ምን ሊሆን እንደሚችል መገመት አልተቻለኝም የሰውን ዕቃ ያለፈቃድ መንካትም አላስፈላጊ ነው። 

#ሐምራዊ_ቀለም የለበሰችው ፀሐይ ሮዝ ቀለም ካለው የኮክ ዛፍ ስታርፍ አካባቢውን ሙሉ በሙሉ የተለየ ገጽታ አልብሳዋለች።

በበርካታ የዛፍ እና የእጽዋት እንክብካቤ የማትታማው ቅድስት ቤተክርስትያን በዚሁ ገዳም ውስጥም በርካታ ዛፎች ይገኛሉ።

በተለይ እስከ ስምንት ሜትር የሚረዝመው የኮክ ዛፍ በሰፊና በተበታተኑ ሮዝ ቅጠሎቹ ለገዳሙ ሞገስን አልብሰውታል።

#ፀሐይዋ ወደ ማደሪያዋ እየገባች ትገኛለች ቅዝቃዜን ያዘለ ነፍስ ከ ሚፈሰው ወንዝ ከበስተ-ደቡብ በኩል የሚመጣው እርጥበቱን እያራገፈ በየ ዛፎች ይወሸቃል የቅጠሎችንም ሰላም ያውካል ለእኔ ግን ፍጹም ሰላምን ለግሶኛል።

ከጎጆዋ መግቢያ በር በስተቀኝ ለመቀመጫ የምታገለግል የባህር ድንጋይ ላይ ተቀምጨ ቀዝቃዛውን ነፋስ እምጋለሁ። ቢጫ ፎጣ የለበሰ በገዳሙ ስርአት የአሞክሮ ቆብ የለበሰ ለመመንኮስ የፈተና ጊዜ የተሰጠው ልጂ እግር አባ አባ እያለ እየተጣራ ወደ እኔ ተጠጋ እንደምን ዋሉ አለኝ ለየት ባለ የአነጋገር ዘዬ ይመስገን ፈጣሪ አልኩ።

'' አባ ወየት ሂዲው ነው የሉም ወይ''?
የት እንደሄዱ አላውቅም ቅድም ነው የወጡት። 
''ከደጀ ሰላሙ መቁነን ሳይወስዱ ሲቀሩ እኮ ምን ገጠማቸው ብጌ ነው መቁነናቸውን ይዠላቸው ወዲህ የመጣሁ '' መቁንን ማለት ለገዳማውያኑ የተመጠነ ምግብ ከደጀ ሰላሙ የሚሰጡት ዳቤ ነው።
''አንቱ አለኝ ለመነኩሴው የመጣላቸውን ምግብ እንዳስቀምጥ እያቀበለኝ።

''እንግዳ ነወት መሰል እኔም መቸ እንግዳ ያለ መስሎኝ ይበሉ ለእርስውም ይዠ መጣሁ ''

በጥቅጥቁ ዛፍ እየተሽሎከሎከ ወደ መመገቢያ ቤቱ ነጎዶ...።

ምን አይነት ራስን የመግዛት ችሎታ ቢኖር ነው ይህን የመሰለ ለጋ ልጂ ለመመንኮስ የአሞክሮ ቆብና መቁጠርያ ተሸክሞ በጉብዝናው ወራት እግዚአብሄርን ያስቀደመ።

#የዛሬው_ዕለት እንደ ትላንቱ ዝናባማ አይደለም በስሱ በደመና የተጀቦነችው ጨረቃ ብርሃኗን አልነፈገችንም። ከተወሰን ደቂቃ በኋላ መነኩሴው ከእጃቸው አቧራ እያራገፉ አንቱ እንዳይሉኝ ስለነገረኳቸው ወፈር ባለ ልሳን ''እንደምን አመሸህ እንዴው ስራ እኮ በዝቶብኝ እንግዳዬን በሚገባ ባለማስተናገዴ ይቅርታ ይደረግልኝ'' አሉ በፈገግታ በታጀበ አነጋገር።

ምንም ችግር የለውም ያው አንዳንድ ነገሮችን ሳነብ ስመለከት ዋልኩ መነኩሴው ቀጠሉና ድንቅ ድንቅ ጥሩ ስራ ይዝህ ወልሃሏ... የእጃቸውን አቧራ ሳያራግፉ ወደ ጎጆቸው ገቡና የሆነ ነገር ላይ አተኮሩ...

በትንሹ የታመነ በብዙ ይሾማል አሉኝ በቀልድ መሰል አነጋገር።  ምን ለማለት እንደፈለጉ ባይገባኛም የገባኝ ይመስል አንገቴን ልክ ንወት በሚል እንቅስቃሴ ገለጽኩላቸው።

ጸሎት ካደረጉ በኋላ የመጣልንን ዳቤ አቅረበው ተመገብን።

#መጻህፍቶች ላይ ስላየዋቸው ውስብስ የአሳሳል ስነ ዘዴወች ፤መልዕክትን በህቡዕ በመከተብ ሰወች በቀላሉ እንዳይረዷቸው በኮዲንግ የአጻጻፍ ስነ ዘዴወች የተጻፉ እኒህ ሁሉ መጻህፍት መች ነበር የተጻፉት የሚል ጥያቄ አቀርብኩላቸው።

መጻህፍቱን እየተመለከቱ በእርግጥ አብዛኛወቹ ከአያሌ ምዕተ ዓመታት በፊት ነበር የተጻፉት፤ የብዙሃኑ ጸሐፊ ማንነት በውል አይታወቅም፤ ንብረትነቱ የቤተክርስትያኗ ነው ብለው ስለሚያምኑ ስማቸውን አያሰፍሩትም።

ከጎጆዋ_በር ላይ ካሉት የባህር አለቶች ላይ ተቀምጠን ጋንብራ በሚባል የቅል ኩባያ ሞልተው ከሱፍ የተዘጋጀወን ጭልቃ አቀረቡልኝ። ከቅድሙ በተሻለ መልኩ የተጀቦነው ደመና ከ ጨረቃዋ ገለል ብሎላታል። አልፎ አልፎ ብልጭ ብልጭ የሚሉ ከዋክብቶች በሰማይ ላይ ይታያሉ።

ከወንዙ የሚነሳ ቀዝቃዛው ነፋስ በዛፎቹ እየሾለከ በረከቱን ያደርሰናል። እኔም ትኩርት እንደሰጡኝ ስረዳ ታድያ ለምን ይሆን እንዲህ የተወሳሰበ ነገሮችን የሚወዱት?! በሚስጥራዊ ኮድ የቆላለፉት ምክኒያት አልገባኝም? ዓመታትን የወሰዱ የጥንት ምርምሮች፣ ምትሃታዊ ተምሳሌቶቼ ፣እንግዳ ቃላትና የቤተሙከራ ግብአቶች ለምን አንብበን በቀላሉ እንድንረዳው እና ለሀገር ተገቢውን ጥቅም እንድናወለው አያደርጉትም ነበር?!

በተረጋጋ ሙህራዊ ሁነት ውስጥ በጽሞና ከሰሙኝ በኋላ ንግግራቸውን ቀጠሉ። 

ይህን የመረዳት ስልጣን የተሰጣቸው ሰወች ብቻ እንዲረዱት ነው የሚፈለገው።

ማንኛውም ሰው ወርቅን በፈለገበት ሰዓት ቆፍሮ እንደልቡ ቢያገኘው ወርቁ እሴትነቱን ያጣና ከአፈር ይረክሳል የወርቅ ተፈላጊነቱ እንደ ልብ አለመገኘቱ ነው።
''ጠቢብ ሰው ከሚነግርህ ይልቅ ያልነገረህን አድምጠው''፤ ጥበብ እንዲሁ ናት ክብሯን ለሚጠብቅ ብልህ ሰው ብቻ ነው ራሷን የምትገልጥ።

#ጥበባዊ ዕውቀትን በጊዜው ብልሆቹ ኢትዮጵያውያን በሚገባ ተጠቀሙበት፤ ሀገራቸውን በአለም የወረቅ መንበር ላይ ለዘመናት አስቀምጠዋት አልፈዋል፤ ሃያላን ጠቢባን ተከባሪወች አለም የሚርድላቸው ልዕለ ሃያል አገርን መስረተውበት እስከነ ክብራቸው አልፈዋል።
ያ ሃያልነት በአባቶችችን ድንቅ ጥበብ ይገለጥ ዘንድ አገራችን ሰወቿን ትፈልጋለች በተስፋም ትጠብቃቸዋለች። ያኔ ኢትዮጵያ ተነሳች ጥበብ ተገለጠች ይባላል...። Z

ያ የሚሆነው ግን በስጋ ነፍስና መንፈስ ትበብር ነው....''ልብ በል አሉ መነኩሴው ጠቢብ ሰው ከሚነግርህ ይልቅ ያልነገረህን አድምጠው '' ለሁለተኛ ጊዜ ይህንን ቃል ደገሙልኝ...!


Share on Google Plus

ስለ የተለጠፈበት ቀን

    Blogger Comment
    Facebook Comment