✍ ቲና በቀለ | ኢትዮጵያ አውታር
ከእለታት በአንዱ ቀዝቃዛ እለት ፀሐይ ከማደርያው ሳትወጣ ጨረቃና ከዋክብት ዝናብ ባዘለ በጥቁር ደመና ተሸፍነው በውርጭ የተመላ ካፊያ አግድም ይወርዳል። ከማደሪያየ ተነስቸ ጸሎተ ማርያምን አደረስኩ።
ለጉዞ የሚያገለግሉ እቃወቸን አሰናድቼ ለምግብነት የሚሆነኝን ቆሎ በፌሳታል ቋጥሬ መንገድ ለመጓዝ የሚያዳግት ደቅድቅ ዝናባማ ጨለማ መንገድ ተያያዝኩት።...
የገዳማት የአመት ክብረ በአልን ለማክብር ሳስብ ከእለቱ ቀን ቀደም ብዬ ገዳሙ ጋ የመገኘት እና የመሰንበት ልምዱ አለኝ።
በዚህ ልምዴ በርካታ ገዳማውያንን ወዳጆች አፍርቻለሁ አለም ስታዝለኝ የማርፍባቸው፣ መንፈሴ ሲታወክ የሚያድሱኝ፣ በአለም ፈተና ስወድቅ በሃጥያት ቀንበር ስያዝ በተስፋ ና በጸሎት የሚያበረቱኝ አባቶችን አግኝቸበታለሁ። የገዳማዊነት ሂወት፣ እራስን የመግዛት ጥበብ፣ አለምን ቀደመው የመረዳት ችሎታ፣ ትግስት፣ የሂወት ፍሬዋን ለመብላት የሚደረግን ጽናት፣ በገዳማውያኑ አኗኗር ዘየ ውስጥ አስተውያለሁ። ለዚህም ነው ከክብረ በአል እለቱ ቀደም ብየ የምገኝበት ምክኒያት።
ይህንንም ታሳቢ አድርጌ ረጅሙን መንገድ ሳይመሽ ለመቋጨት ነበር በዝናባማው ለሊት መንገዴን የጀመርኩ።
ከተወሰነ የመኪና ጉዞ ከሰአታት በኋላ ወደ ገዳሙ ለመሄድ በኮረብታማ ተራሮች በባርዛፍ በተጠቀጠቁ ደኖች ውስጥ ረዘም ያለ የእግር መንገድ መጓዝ ግድ ነበር። ይህ ጉዞ ደግሞ አብሮ የሚጓዝ መንገደኛ ከሌለ ለአደጋ ተገላጭ ያደርጋል። የተለያዪ አውሬ እንዲሁም ወንበዴ ሽፍቶች እንዳሉበት ስለሚወራ በዚህው አካባቢ መንገደኞች በአብሮነት የመጓዝ ልምድ አሏቸው።
ወደ ገዳሙ ለመጓዝ መንገደኞችን መጠበቅ ነበረብኝ እና ከአነስተኛ ከተማዋ ካለው ዳገት ወጥቸ ወደ ገዳሙ የሚወስደውን መንገድ ላይ ከሚገኝ ቋጥኝ ጥላ ስር ተጠልዬ አብሮ የሚጓዝ መንገደኛን ይመጣ ብዬ አይን አይን እመለከታለሁ...።
ለሰአታት ከዚሁ ቋጥኝ ስር ካለው ጥላ አቅጣጫ እየቀያየርኩ በመጠለል መንገደኛ መጠባበቅ ጀመርኩ..... የመጣ ግን አልነበረም። በጥቁር ፌስታል ከያዝኳት የሽንብራ ቆሎ ዘግኘ እየቆረጠምኩ ከኮረብታው ስር ያለችውን ቀጭን መንገድ ሰው አይበት ዘንድ እየተመኘሁ አሻግሬ እመለከት ጀመርኩ የመጣ አንድም ሰው ግን አልነበረም።
ወደረኛዋ ከደመናው ስር በስሱ የወጣችው ጸሃይ ወደ ማደሪያዋ እየገሰከሰች ጀንበሯን እያዘቀዘቀች ነው።
ብቻየን ለመጓዝ በተደጋጋሚ ተነስቼ ከዚህም በፊት በዚሁ መንገድ ላይ ብቻቸውን የሄዱ ሰወች ያጋጠሟቸውን ችግሮች ስለሰማሁ ተመልሽ እቀመጣለሁ።
ከአነስተኛ ከተማ ቀመስ ገጠር ርቄያለሁ እና በመሸም ጊዜ ወዘልውጥን ሰው የማትቀበል ስለሆነች መመለስን ፈራሁ። ወደ ገዳሙም ብቻየን ለመሄድ ልቤ ተሸበር። ከቋጥኙ ላይ ወጥቼ አይኖቼን በየአቅጣጫው እየወርወርኩ መጠለያ ቤተክርስትያን አገኝ ብዬ በአይኖቼ አስሳለሁ ነገር ግን ከተጠቀጠቀ ጫኳ ውስጥ መርፌ እንደ መፈለግ ሆነብኝ።
የፀሐይ ጉዞዋ ያለ ወትሮዋ የፈጠነም መሰለኝ ምናለ የኢያሱ ወልደነዌን ጸጋ ባደለኝ ወይ ደግሞ ከጠቢባኑ ጥብብን ብካፍል እንደገባኦን ምድር ፀሐይን ከማደሪያዋ አዘገያት ጨረቃን ከቤቷ አጸናት ነበር ብዬ ተመኘሁ።
ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ከተቀመጥኩበት ቋጥኝ ስር አሻግሬ ስመለከት ወደ እኔ እየመጣ ያለ ነገር ተመለከትኩ ሰው ይሁን እንስሳ መለየት የማልችልበት ሁኔታ ነበር።
እየቀረበ ሲመጣ ሰው እንደሆነ ተረዳሁ ምን አይነት ሰው ይሆን የሚለው ሌላ ጭንቀት ሆነኝ...።
እንደ #ዘኪወስ ያጠሩ የቆሸሸ ቡናማ አስኬማ(የምንኩስና ቆብ) አድርገው ግራጫ ቀሚስ፣ እንደ ነገሩ ትክሻቸው ጋ ያገለደሙት ቢጫ የመነኮሳት ፎጣ የለበሱ፣ ከጀረባቸው ጆንያን ያዘሉ፣ በቀኝ እጃቸው ከስሩ ጦር መሰል ከላይ መስቀል ያለው የብረት መቋሚያን የያዙ መነኩሴ ነበሩ።....
እፎይ አልኩ ክርስቶስ የላከልኝ መላክ እንጂ ሰው እስከማይመስሉኝ ድርስ ተደስትኩ። ለውሳኔወቸ ሁሉ አማካሪ ለችግሮቸ ሁሉ የጋራ ወሳኝ ሰው በማግኝቴ እጂጉን ተደስትኩ። ...
የያዝኩት የእጂ ስልክ ባትሪ ዘግቶ የስአቱን ሁኔታ ከጸሐይ ይልቅ የምገምትበት አጋጣሚ አላገኘሁም...።
ጸሐይዋ ቀና ብየ ስመለከት ለይቶላት ወደ ምዕራቡ ማደሪያዋ በር ተቃርባ የመግቢያ መስኮቶቿን ታንኳኳለች።
እንደ መላክ የወረዱልኝ መነኩሴ ሲጠጉኝ
እግዚአብሔር ለእኔ ሲል የላካቸው መላክ እንጂ ሰው አልመስል አሉኝ።
ካህን መነኩሴ መሆናቸውን በአንገታቸው ስር በወረደው በወፍራሙ በተገመደ ክር ያንጠለጠሉትን የብረት መስቀል አይቼ ከጉልበቴ በርከክ ብየ ቡራኬን ተቀበልኩ።
ለስለስ ባለ የደካማ ሰው ድምጽ ሰላምታ ሰጠውኝ በዚህ ስአት ብቻየን ለምን ከዚህ እንደተገኘሁ ጠየቁኝ። ወደ ገዳሙ ለመሄድ ፈልጌ መንገደኛ ስጠብቅ እንደመሸብኝ አስረዳዋቸው።
''በል እኔም ወደዚያው ነኝ ተከተለኝ ብለው ፈጠን ፈጠን አሉ ''...እንዴ አባቴ መሽቷል መንገዱ ኮ ከ ሶስት ስአታት በላይ የእግር መንገድ ነው ስለዚህ በአቅራቢያ መጠጊያ እንፈልግ አልኳቸው ''አይ አይ መነኩሴ ከባዕቱ( ከመኖሪያ ) ወጥቶ አያድርም በል አቋራጨ መንገድ ስላለ በዚያ እንሄዳለን ባይሆን ለ አውሬና ሽፍቶች ጸሎተ ማርያምን እየደገምን እንጓዛለን ''... በማለት መንገዳቸውን ቀጠሉ...እጂግ በሚገርም እምንነት በሙሉ ልቡና መንዱን ሲጀምሩ ወደራሴ እንዳይ የ ማንነቴን ዝቅታ የእምነቴን ወሃልክ እንድመለከት አደረጉኝ እንዲህ ያለ ባለጽኑ እምነት ክርስትያን ባለበት እኔም ክርስትያን ተብሎ የመጠራት የሞራል ልዕልና ከእኔ እራቀ።
ቢሆንም አማራጭ ስለሌለኝ ከአማኝ በጎደለ እምነት በፍራቻ በርኖስ ተሸብቤ ከኋላቸው መንገድ ጀመርኩ.... አባ ገብረ ሂወት እንደሚባሉ ተዋውቀን የእኔንም ስም ነግርያቸው ከያዝኳት ጥቁር ፌስታል ቆሎን ዘግነን እያወጋን ባለ ግርማውን ጫካ ደርት ደረቱን እየገመስን እንገሰግሳለን።
ስለ እርሳቸው ልጂነት የወጣትነት ሂወት ኑሮ የገዳማዊ ሂወትን እንዴት እንደመሰረቱ ሁሉ ከላይ ከላይ በጥያቄ ይዣቸዋለሁ......
በደጋው አካባቢ በ1940ወቹ መጀመርያ እንደተወለዱ እና በልጂነታቸው አባታቸው እንደሞተ በእረኝነት ኑሮ የልጂነት ሂወታቸውን እንዳሳለፉ በእረኝነትም ላይ የእግዚአብሄር ጥሪን ሰምተው ወደ ገዳም ሊሄዱ ሲያስቡ እያለ ቤተሰብ ሊድሯቸው ሲሉ በለሊት ሸሽተው እንደሄዱ ለረጂም አመታት በተለያዩ ቦታወች እንደተዘዋወሩ እና ይህንን የምንኩስና ሂወትም ከፈጸሙ ከ አርባ አመታት በላይ እንደሆናቸው ደስ በሚል አረጋዊ ድምጽ በሹክሹክታ እየተረኩልኝ መንገዳችንን ቀጠልን...።
ከብዙ_ድካም በኋላ ጋራ ሸንተረሩ ዱርና ባህሩን የአራዊቱን ጩሆት አሳልፈን በድንገዝጋዛ ምሽት ግርማው በሚያስፈራ ጨለማ ውስጥ አልፈን ከሩቅ የሚታይ ቦቀታ ብልጭ ድርግም የሚል የኩራዝ ጭላንጭል ሲታየኝ ሌላ አለም የገባሁ የተስፋዋን የከንአንን ምድር አሻግሬ ያየሁ ያክል ደስታ እና ሲቃ ተሰማኝ።......
''ደርሰናል ደርሰናል አሉ በዝግታ....በል ዛሬ ወደ እንግዳው ቤት ለመሄድ ስአት ስለመሸ ከእኔ ዘንዳ ታርፋለህ''....
''ከጫካው ስር ቤተክርስቲያኑ አለ ክብ ሰርቶ አምሮ እና አብቦ የሚታየው ዛፍ ከልሎታል አሉ''።
ቤተክርስቲያኑ አለበት ወዳሉኝ አቅጣጫ ተሳልሜ እሳቸው ከፊት እኔ ከኋላ ወደ ባእታቸው ተጓዝን።
#የመነኮሳቱ_ባዕት ጣሪያው ከሳርን ከአገዳ የተሰራ ቋሚው ደግሞ ከባህር ዛፍ እንጨት የሚዘጋጂ የጎጆ ቤት ነው። ጭል ያሉ የመነኮሳት ጎጆወችን እያለፍን ቁልቁል እንወርዳለን። ራቅ ራቅ ብሎ ከሚታዩት የኩራዝ መብራቶች እና ከወዲያ ማዶ ነፋስ ይዞት ከሚመጣ የእንጉርጉሮ መሰል ዜማ ውጭ ጭር ያለ ባለ እርጥበት ያዘለ ሞገድኛ ነፋስ ያየለበት ስፋራ ነበር።
#ከዋርካው_ስር በዘፈቀደ የተቀለሱ አምስት ባዕቶች አንዱ የአባ ገ/ሂወት ነበርና ወደ ባእታቸው ገባን ከ መቅረዙ ላይ ያለውን ኩራዝ በማንሳት ላንባ ጨምረው ለኩሰው መልሰው አስቀመጡት። ያለ ወጋግራ የቆመች ጎጇቸው በቀይ አፈር የተለቀለቀች በግራና በቀኝ በከል መደብ የተሰራባት በርካታ መጻህፍትና ከቅል የተሰራ ገንበራ(መጠጫ) እና በአክርማና ሰብዝ የተሰፋ የምግብ መመገቢያ የያዘች አነስተኛ ቤት ነበረች።
የበግ ለምድ ከመደቡ ላይ ዘርግተው እንደቀመጥ ጋበዙኝና በገንበራዎ ውሃ አዘግጂተው እኒያ አረጋዊ እግሬን ሊያጥቡ ተጎነበሱ። የገዳሙ ስርአት ቢሆን እንኳ ይህንን ፈጽሜ እሽ እንደማልላቸው በግድ አሳምኘ የገዳሙ ምግብ መኮሬታ በበርበሬ እንድባላ ሰጠው ወደ ጸሎታቸው ተመለሱ።
#ከተዘጋጀልኝ ምኝታ በሳሩ በኩል የሚንጠባጠበው ዝናብ ከለበሱኩት የብርድ ልብስ ውስጥ ሰርጎ በመግባት አባነነኝ። ድቅድቅ ጨለማ ገርበብ ብሎ ከተከፈተው የጎጆዋ በር ጀርባ ሲታየኝ...። በሩን ሳይዘጉ ረስተውታል በማለት በለሁሳስ አባ አባ ብየ ብጣራ ምላሽ ግን የለም...ኩራዙን ለኩሰው ያስቀመጡትን ክብሪት በደበሳ አስሸ ኩራዙን ሳበራ አባ ከመኝታቸው የሉም....
ከሌሊቱ ግርማ ይልቅ እንደ ሙዜር የሚያፏጨው ነፋስና ምድርን የሚያናውጣት ነጎድጓድ በደሳሳዋ ጣሪያ የሚፈሰው ዝናብ በጎጆዋ ሽንቅር በኩል የሚያልፈው የመብርቅ ብልጭታ እለተ ምጻት የቀረበ እስኪ መስል ድርስ መድረሻ አሳጣኝ።
ከተኛሁበት ራስጌ በኩል በለሰለሰ አራት መአዘን ወፍራም ብራና የተቀመጠች የወይን ፍሬ ተመለከትኩ ከመተኛቴ በፊት ቢሆን አስተውል ነበር ግን ከአባ ገ/ሂወት ለሆነ ጉዳይ በአጋጣሚ ያስቀመጣት መሰለችኝ።
ዶፍ ዝናብ የሚወርድባት፤ ወዥንብር የሚያወዛውዛት ጎጆ እንደ ቅቤ አንጋች ወደ ግራና ቀኝ ይንጧታል።
ከአንደበቴ የማትጠፋው ከብዙ መከራ የታደገችኝን ጸሎተ ማርያምን እንየጸለይኩ የአባ ገ/ሂወትን መምጣት እጠባበቃለሁ።
ብዙ ጊዜ መነኮሳት ቀን ሲሰሩ ውለው ሰፋ ያለ ጸሎት የሚያደርሱት ለሊት ነው ይህ በተደጋጋሚ ስለገጠመኝ አውቀዋለሁ ስለዚህ ባዕታቸውን ስለያዝኩባቸው ቤተክርስትያን ለጸሎት ሂወደው እንደሆን ጠረጠርኩ በዚህ ዶፍ ዝናብ እንዴት ሁኖ የሚለው ሌላ ሃሳብ ሆነኝ...።
የነፋሱ አነፋፈስ ከሚያሰማው ድምጽ አንጻር የነፋሳቱ መነሻ መስኮት እንብርት ላይ ያለሁ እስኪመስለኝ ድረስ አጠራጠረኝ ስለ ገዳሙ ለማወቅ ያለኝን ጉጉት ይበልጥ ጨምሮልኛል።
#በጎጆዋ ጭንቁር በኩል የሚነፍሰው ነፋስ በደሳሳዋ ጎጆ እያፈተለከ የለኮስኳትን ኩራዝ በተደጋጋሚ ያጠፋዋል። በዛ ላይ ኩራዟ ላንብ አንሷት እርግብ እርግብ ትላለች።
ወደዚህ ገዳም የሄድኩበት ምክኒያት ከሚከበረውን አመታዊ ክብር ባዕል ባሻገር የማስስውና የምፈልገውን እውነትና እውቀትን ከቦታው ካሉ መነኮሳት ለመካፈል ነው።
ቢሆንም እንዳሰብኩት ሳይሆን በሚያስፈራው ለሊት የመነኩሴው ድንገት መሰወር አይሎ የመጣሁበትን ከማሳካት ይልቅ ነግቶ ማየትን ተመኘሁ።
የእኒያ መነኩሴ በድንገት መሰወር ብዙ ሃሳብና ጭንቀት ውስጥ ጣለኝ ስሰማው ያደኩት ሰው መሰል የጂንና የቆሌ ታርኮች እውን የሆኑም መሰለኝ።
በሂወቴ ካሳለፍኳቸው ፈታኝ ለሊቶች ይህ የማይረሳ ዋናው የሂወት ገጠመኘ ነው።
ሰማዩ ወጋገን እየለበሰ ዝናቡም ቀለል ያለ ካፊያ እየሆነ ከ ዚያ ሁሉ ጭንቀት ምድሪቱ ተገላግላ የፀሐይዋን መውጣት ትጠብቃለች።
የጨለማው በርኖስ ተገፎ በደመና የተሸፍነ የብርሃን ወጋገን ቦታውን ሲይዝ እፎይ አልኩ።
አሁንም መነኩሴው አባ ገ/ሂወት አልተመለሱም....
በማለዳ ተነስቸ ምድሩ በሳር በተሞላው ጤዛማ ሜዳ አልፌ ወደ ቤተክርስትያኑ ውስጥ አቀናሁ ይህንን ብርሃን ያሳየኝ ጌታየን አመስግኘ የመነኩሴው ድንገት መጥፋት አሳስቦኝ ስለ ሁኔታው ላጠያይቅ በአቅራቢያ ወዳሉ ባዕቶች አቀናሁ አካባቢው ጸጥ ረጭ እንዳለ ነው። ድምጼን ጎላ አድርጌ ሰላምታ ሰጠሁ ከጎጆዋ ውስጥ ይመስገን ፈጣሪ የሚል መልስ አገኘሁ።
#ቢጫ የመነኩሴ ፎጣ ደርበው የለበሱ ጎልማሳ መነኩሴ አስኪማቸውን እያስተካከሉ ከጎጆ ባእታቸው በቅ አሉ። እንደምን አሉ አንድ ነገር ጨንቆኝ ላወያይወት ነው የመጣሁ.. ከሩቅ ሃገር ነው የመጣሁት ብየ አንገቴን ስሰብር ምነው ምነው ምን ገጠምወት አሉኝ።
አባ ገ/ሂወት የሚባሉ መነኩሴ ያውቃሉ? እርሳቸው ለማስታወስ እየሞከሩ አባ ገ/ሂወት አባ ገ/ሂወት አይ አይ እንዲህ የሚባል መነኩሴ እዚህ አላውቅም በእጃቸው የመጋቢውን ቤት እያመለከቱ ግን በይበልጥ ከ መጋቢው ዘንዳ ሂዱና እሳቸው መነኮሳቱን በደንብ ያውቋቸዋል ይጠይቁ አሉኝ።
ከተጠቆምኩት ቤት ሄድኩ መጋቢውን ዘለግ ባለ ድምጽ ሰላምት ስስጣቸው መልስ የለም በጀርባ በኩል ስሄድ ከጎጆዋ ጀርባ ያሉ እጽዋቶችን ይኮተኩታሉ።
ሰላምታየን አቅርቤ አባ ገ/ሂወት የሚባሉ ሰውየ ጋ ትላንተ በምሽት ተጉዘን ከ ገዳሙ እንደደረስን በእጀ እየጠቆምኩ ከ ባዕታቸው እንዳሳረፉኝ መኮሬታ አቅረበውልኝ እራቴን እንደበላሁ እና እንደተኛሁ በለሊት ከእንቅልፌ ስነሳ መንኩሴውን እንዳጣዋቸው በመጥፍታቸውም እንደ ጠጨንኩ አስረዳሁ።
ልጀ አባ ገ/ሂወት የሚባል መነኩሴ እዚህ የለም ያ የጠቆምከኝ ቤት ሰው አይኖርበትም ከተዘጋ ረጂም ጊዜው ነው አዲስ መነኩሴ ሲመጣ ታይቶና ተመዝኖ ሊሰጠው የተዘጋ ቤት ነው ደግሞስ መኮሬታ ነው የተመገብከው አሉኝ? አው ከዳጉሳ የተዘጋጀ ምላስ ያዝ የሚያረግ አልኳቸው እንግዲያውስ የገዳሙ ምግብ ዳቤ እንጂ መኮሬታ አይደለም አካባቢው ደጋ ስለሆን በብዛት የገብስ ምርት እንጃ ዳጉሳ መሬታችን አያበቅልም አሉኝ።
ካለሁበት ደርቄ ፈዝዠ ስርበተበት ተመለከቱኝ ትላንትነት በቅጀቴ ውስጥ ያለፈ ህልም እንጂ ኑሬው ያለፈ አልመስል አለኝ።
ጤነኛ መሆኔ ተጠራጠርኩ ሰው መስሎ የተጫወተብኝ ባዕድ ፍጥረት የሆን ወይስ የአየር አጋንት እንደ ሰው የሚያወሩ የሚያናግሩ ሰውን የሚመስሉ ጂን እና ቆሌ ይሆን?!
መጋቢው መነኩሴ መጨነቄን ሲመለከቱ አረጋገተው አስቀመጡኝ። ጸሎት አድርገው ጸብል እንዲተምቁኝ ተማጸንኳቸው ለረጂም ስአት ድርሳናትን ደግመው ጸበሉን ጠመቁኝ። ቢያንስ መንፈሴን የሚያውክ ስሜት ስላልተሰማኝ ተረጋጋሁ።
ስለ ሁኔታው ጠየቋቸው ምን ሊሆን ይችላል አልኳቸው? .....
ግራ በመጋባት ስሜት አንድ አንድ መነኮሳት ከኢትዮጵያ ጫፍ ጫፍ ወደ የገዳማቱ የሚጓዙት በእግር ነው በዚህም አጋጣሚ ሲመሽ የተለያየ ቦታ ያድራሉ። እኒህ መነኩሴ ድንገት ከዚህ የነበሩ ግን አሁን ሌላ ገዳም ውስጥ የሚኖሩ ሲጓዙ መሽቶባቸው ወደዚህ ሲያመሩ አንተ ጋ ተገናኝታችሁ እዚህ አርፈው ሰው ሳይነሳ በለሊት ጉዞ ጀምረው ሊሆን ይችላል አሉኝ። ለምን በለሊት መሄድ አስፈለገ? ለምን አይሰናበቱኝም? በዝናብና ነጎድጓዱ እንዴት ሊሄዱ ቻሉ? ሌላው ደግሞ የወይን ፍሬው ነገርስ ከመሄዳቸው ጋር የሚገናኝ ነገር ይኖረው ወይስ አጋጣሚ የሆነ ነው? መጋቢው መልስ ይሰጠኝ ዘንድ አይን አይናቸውን አያለሁ።
መጋቢያው ቀጠሉ እዚህ ቦታ ላይ ለእንግዶች በርካታ እንቆቅልሽ የሆኑ ክስተቶች በየጊዜው ይከሰታሉ....
ቀጣዩን ያየሁትን የሚስደንቅ ነገር እነግራችኋለሁ!!!
Blogger Comment
Facebook Comment