“ዝምታ ወርቅ አይደለም”
ምክንያተ ጽሑፍ
ለዚህ ጽሑፍ ምክንያት የሆነኝ የሁለት ሙስሊም ወገኖቸ ወቅታዊ የጽሑፍ ስራዎች ናቸው። አንደኛው በዐብዱልጀሊል "እስልምና በኢትዮጵያ ከቅድመ ክርስቶስ እስከ ዛሬ" በሚል ርዕስ ተጽፎ በያዝነው ወር መግቢያ ላይ በድምቀት የተመረቀው ግዙፍ መጽሐፍ ነው። ሌላኛው ደግሞ “የትርክት ጦርነት፦ የጽዮናዊነት ስልቶች በኢትዮጵያ አውድ” በሚል ርዕስ በአሕመዲን ጀበል ተጽፎ በማኅበራዊ ሚድያ የተለቀቀው ጽሑፍ ነው። እነዚህ ሙስሊም ወንድሞቻችን ከዚህ ቀደምም ከእውነት የራቀ፣ ታሪክን የገበረ፣ በማኅበረሰብ መካከለ መተማመን እንዲኖር የማያደርግ ወይም ክፋፋይ የሆኑ ጽሑፎቹን ማቅረባቸው ይታወሳል። ስለሆነም ዛሬ ደግሞ ያንኑ የልቦለድ ድርሰታቸውን አጠናክረው በመምጣታቸውና የእነርሱ ስራ ትልቅ ሀገራዊና ማሕበረሰባዊ ኪሳራ የሚያስከትል ስለሆነ መልስ መስጠቱ ተገቢ መስሎ ስለተሰማኝ እንድታነቡትና እንድታጋሩት ይኽንን ከትቢያለሁ። በዚህ ጉዳይ ሁለት ተከታታይ ጽሕፎችን የ“አል-ነጃሺ” የፈጠራ ትርክት እና “የሐሰት ተበዳይነት ትርክት እና የተገላቢጦሽ እውነታ” በሚል ለማቅረብ አስቢያለሁ። የመጀመሪያውን እነሆ!
እንደ መነሻ
በአሁኑ ዘመን ኢትዮጵያንና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን ከገጠሟቸው ታላላቅ ተግዳሮቶች መካከል በዘፈቀደ የሚባዙና እውነት የሌላቸው የሀሰት ትርክቶች ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛሉ። እነዚህ ትርክቶች የሀገሪቱን የዘመናት ታሪክ የሚያጠለሹና በሕዝቦች መካከል ጸንቶ የኖረውን አንድነት የሚሸረሽሩ ናቸው። በኢትዮጵያ የታሪክ ነክ ትርክቶች ውስጥ ታሪክን ለፖለቲካዊ እና ለማኅበራዊ አጀንዳዎች ማስፈጸሚያነት የመጠቀም አዝማሚያ ትልቅ ሀገራዊ ቀውስ እያስከተለ ይገኛል። ለዚህም አንዱ ጉልህ ምሳሌ በ7ኛው ክፍለ ዘመን በኢስላማዊ ትውፊት “አል-ነጃሺ” ተብሎ የሚጠራው የአክሱም ንጉሥ ወደ እስልምና የተቀየረ የመጀመሪያው ንጉሥ ተደርጎ የሚቀርብበት የፈጠራ ድርሰት ነው።
ብቸኛው እውነት
በዚህ ጉዳይ ያለው እውነቱ አንድና አንድ ብቻ ነው። ይኸውም እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ615 ዓ.ም የሙሐመድ ተከታዮች በትውልድ ሀገራቸው መካና በወገኖቻቸው በቁሬሽ ጎሳዎች እንግልትና ስደት ሲደርስባቸው፣ 70 አካባቢ የሚደርሱ ሰዎች ወደ ኢትዮጵያ ተሰደው መምጣታቸው ነው። በወቅቱ የነበሩት የኢትዮጵያ ንጉሥ (አርማህ)፣ እነዚህን ስደተኞች በታላቅ ሰብአዊነትና ርኅራኄ ተቀብለው በሀገራቸው ያለባቸው ችግር እስኪያልፍ ድረስ በእንግድነት እንዲቀመጡ መፍቀዳቸው የታሪክ እውነት ነው። ንጉሡ ለስደተኞቹ የሰጡት ጥበቃና ያሳዩት ፍትሐዊ አቀባበል በታሪክ የማይዘነጋ ከመሆኑም በላይ ኢትዮጵያ የስደተኞችን መብት በማክበር ረገድ የሺህ ዓመታት ጥንታዊ ታሪክ ያላት ሀገር መሆኗን የሚያመለክት ኩራት ነው። ከዚህ ታሪካዊ እውነት ውጭ ንጉሡን ወደ እስልምና የመለወጥም ሆነ ሌላ መልክ የመስጠት ትርክት በሙሉ መሠረተ ቢስና ለተለያዩ ፍላጎቶች ተብሎ የተቀነባበረ የፈጠራ ወሬ ነው።
የስህተት መጀመሪያው
ስህተቱ የሚጀምረው ከስሙ ነው። በትረካው ውስጥ የሚጠቀሰው የዚያ ዘመን የኢትዮጵያ ንጉሥ ትክክለኛ ስሙ ንጉሥ አርማሕ ሲሆን፣ “ነጃሺ” የሚለው ቃል የግል ስም ሳይሆን “ንጉሥ” ከሚለው የግዕዝ ቃል የተወሰደና ከአረብኛ አጠራር ጋር የተስማማ የሥልጣን ማዕረግ ነው። በመሆኑም “ነጃሺ” የሚለውን የማዕረግ ስም እንደ ግል መጠሪያ አድርጎ መውሰድ መሠረታዊ የታሪክ ስህተት ነው።
የአርኪኦሎጅና የታሪክ ማስረጃዎች
ንጉሥ አርማሕ ወደ እስልምና መለወጡን የሚያሳይ አንዳችም ተዓማኒ የታሪክ ሰነድ ወይም የአርኪኦሎጂ ማስረጃ የለም። ይልቁንም እስካሁን ያሉ መረጃዎች ንጉሡ በዘመነ መንግሥቱ ሁሉ የጸና ክርስቲያን እንደነበረ ያረጋግጣሉ። ከዚህ ውስጥ በንጉሥ አርማሕ የቀብር ቦታ ላይ በአርኪኦሎጅ ቁፈራ የተገኙት ሳንቲሞች ቀዳሚውን ቦታ ይይዛሉ።
• በንጉሥ አርማሕ ስም የታተሙት የነሐስና የብር ሳንቲሞች በሁለቱም ገጻቸው ላይ ግልጽ የሆነ የመስቀል ምልክት ይዘዋል። በአንደኛው ገጽ ላይ ንጉሡ በዙፋኑ ላይ ተቀምጦ ሲታይ፣ በሌላኛው ገጽ ላይ ደግሞ በትልቅነቱ ጎልቶ የሚታይ መስቀል ተቀርጾበታል። ይህ የሚያሳየው ንጉሡ ክርስትናን እንደ ግል እምነት ብቻ ሳይሆን እንደ መንግሥታዊ አርማ ይዞት እስከ መጨረሻው መዝለቁን ነው። ንጉሡ ወደ እስልምና ተቀይሮ ቢሆን ኖሮ፣ እነዚህን መሰል ሃይማኖታዊ ምልክቶች ከሳንቲሞቹ ላይ በማንሳት አዲስ አርማ ይጠቀም ነበር።
• በሳንቲሞቹ ላይ በግዕዝ ቋንቋ “ንጉሥ አርማሕ” የሚል ስሙ በግልጽ ተጽፏል። ይህም በኢስላማዊ ትውፊት “አል-ነጃሺ” ተብሎ የሚጠራው አካል ማንነቱ አርማሕ መሆኑን በአማናዊ የታሪክ ሰነድ ያረጋግጣል። በወቅቱ የነበሩት የሳንቲም ጽሑፎችና መልእክቶች ለሕዝቡ የሚተላለፉ የመንግሥት አዋጆች እንደመሆናቸው፣ ንጉሡ ክርስቲያናዊነቱን በይፋ ሲያውጅ እንደነበረ ያሳያሉ።
• በአርማሕ ሳንቲሞች ላይ የሚታየው የንጉሡ ምስል በቤተክርስቲያን ውስጥ ያለውን ሥርዓተ ንግሥ የሚያሳዩ ምልክቶች (ለምሳሌ ዘንግና ዘውድ) ይዟል።
• የቀብር ሥፍራ፦ በታሪክና በትውፊት ንጉሥ አርማሕ የተቀበረው በአክሱም መሆኑ ይታወቃል። ይህ ሥፍራ ደግሞ ጥንታዊ ክርስቲያናዊ መካነ-መቃብር ነው። ንጉሡ እስልምናን ተቀብሎ ቢሆን ኖሮ፣ እንደ አንድ ሙስሊም መሪ በኢስላማዊ የቀብር ሥርዓት ሊቀበር ይገባ ነበር፤ ነገር ግን በአክሱም ያሉ የነገሥታት መቃብሮች ሁሉ ክርስቲያናዊ ይዘት ያላቸው ናቸው።
• የነጃሽ መስጊድ ታሪክ፦ በአሁኑ ወቅት በትግሬ ክልል የሚገኘው የነጃሺ መስጊድ በስደት የመጡት የመሐመድ ተከታዮች ስደተኞች ያረፉበትና የሰፈሩበት ቦታ እንጂ ንጉሥ አርማሕ መስጊድ የሠራበት ወይም የሰገደበት ቦታ ለመሆኑ ምንም ዓይነት ጥንታዊ የጽሑፍ ማስረጃ የለም።
ከአመክንዮ (logic) አንጻር ትርክቱ ሲመዘን
• በ7ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ ኢትዮጵያ ጽኑና ተቋማዊ መዋቅር ያላት የክርስትና መንግሥት ነበረች። ክርስትናን የመንግሥት ሃይማኖት አድርጋ የተቀበለችው ቢያንስ በ4ኛው ክፍለ ዘመን በንጉሥ ኢዛና ዘመን መሆኑ ይታወቃል። ስደተኞቹ በመጡበት ወቅት ክርስትና በኢትዮጵያ ማኅበረሰብ ውስጥ ከሦስት መቶ ዓመታት በላይ ሥር ሰዶ፣ በባህልና በፖለቲካዊ ሕይወቱ ውስጥ የማይነቀል መሠረት ጥሎ ነበር። በመሆኑም ጥቂት አዲስ መጠጊያ ፍለጋ የመጡ ስደተኞች፣ በጠንካራ ክርስቲያናዊ ማኅበረሰብ ላይ የሚገዛንና የቤተክርስቲያን ጠባቂ የሆነን ንጉሥ አሳምነው እምነቱን አስለውጠውታል የሚለው አመለካከት ከታሪካዊ አመክንዮ ውጪ የሆነ የማይመስል ነገር ነው። የአብዱልጀሊልን “የቅድመ ክርስቶስ እስልምናን” ተረት ተረት እንተወውና ያኔ እስልምና የሚባል ነገር በወጉ የተቋቋመ ሃይማኖት አልንበረም። እንዲያውም አንዳንድ የታሪክ ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት፣ ወደ ኢትዮጵያ ከሸሹት ሙስሊም ስደተኞች መካከል በሀገሪቱ ባዩት ጥልቅ ክርስቲያናዊ ሥርዓትና ባህል ተፅዕኖ በመመሰጥ እስልምናን ትተው ወደ ክርስትና መለወጣቸውን ነው።
• የኢትዮጵያ ንጉሥ እስልምናን ተቀብሎ ቢሆን ኖሮ፣ ይህ ክስተት ከብዙ መቶ ዓመታት በኋላ በአካባቢው ለተከናወኑት ኢስላማዊ እንቅስቃሴዎችና ወረራዎች ትልቅ የታሪክ መሠረትና ቀደምት ምሳሌ በሆነ ነበር። በተለይም በ16ኛው ክፍለ ዘመን በክርስቲያን ኢትዮጵያ ላይ መጠነ-ሰፊ ጦርነት የከፈተው አሕመድ ግራኝ (ኢማም አሕመድ ኢብኑ ኢብራሂም)፣ ይህን ታሪክ ለጦርነቱ ሞራላዊና ሕጋዊነት ማግኛ ዋነኛ መሣሪያ አድርጎ ሊጠቀምበት ይችል ነበር። ይሁን እንጂ በአሕመድ ግራኝ ዜና መዋዕልም ሆነ በወቅቱ በነበሩ የታሪክ ሰነዶች ውስጥ ንጉሥ አርማህን እንደ ቀዳሚ ሙስሊም መሪ በመጥቀስ የቀረበ የይገባኛል ጥያቄ አይታይም። ይህ ታሪካዊ ዝምታ የሚያረጋግጠው፣ የንጉሡ ወደ እስልምና መለወጥ ትረካ በኋለኛው ዘመን ለሃይማኖታዊ ፕሮፓጋንዳ ተብሎ የተፈጠረ እንጂ በወቅቱ የነበረ እውነተኛ የታሪክ ክስተት አለመሆኑን ነው።
ጥያቄ ውስጥ የገባው “ሐበሾችን አትንኩ” የሚለው ትርክት
ኢትዮጵያን ከጂሃድ (ሃይማኖታዊ ጦርነት) ነፃ አድርጓታል የሚባለውንና ከሙሐመድ እንደተላከ የሚነገረውን "ሐበሻን አትንኩ" የሚለውን ትእዛዝ በአንዳንድ የታሪክ ምህራን ዘንድ እውነተኛነቱ ጥያቄ ውስጥ ገብቷል። እነዚህ ምሁራን እንደሚከራከሩት ኢትዮጵያ በወቅቱ ከነበረው የእስልምና መስፋፋት ጥቃት የዳነችው በመሐመድ ይፋዊ "ልዩ ፈቃድ" ሳይሆን መልክአ ምድራዊ አቀማመጧ ለወረራ እጅግ አስቸጋሪ በመሆኑና ከቢዛንታይንና ከፋርስ ግዛቶች ጋር ሲነጻጸር ያላት የኢኮኖሚ ጠቀሜታ በወቅቱ አነስተኛ ሁኖ በመታየቱ ነው። ከዚህ በተጨማሪ ኢትዮጵያ ከሙሐመድ "ከጂሃድ ነፃ የመሆን መልእክት" ተሰጥቷታል የሚለው መከራከሪያ ተጨባጭ የታሪክ መሠረት የሌለው በሀገሪቱ ላይ በተደጋጋሚ በእስላሞቹ የተደረገባት ጥቃት ነው። በታሪክ እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ እንደ ኦቶማን ቱርክ፣ ግብፅና የሱዳን ማህዲስቶች ባሉ ኃይሎች ለረጅም ዘመናት የእስላማዊ ጥቃቶች ሰለባ ሆና መቆየቷ የሚታወቅ ነው። በሀገር ውስጥም አውዳሚ የነበረው የግራኝ ጦርነት በቱርክና በአረቦች ሲደገፍ የቆየ ነው። ለኤርትራ መገንጠል ሲሰራ የነበረው በግብጽ ሲታገዝ የነበረው የጀብሐ ንቅናቄ፣ የሶማልያ ጦርነት፣ በዘመናችን በቱርክ፣ በተባበሩት አረብ ሚሬተስና በሌሎችም ሙስሊም ሀገሮች እገዛ በወገኖቻችን ላይ የሚዘንበው የድሮን ጥቃት ኢትዮጵያ በሙሐመድ ትዕዛዝ ከጂሐድ ነጻ ነች የሚለውን ትርክት ትክክል እንዳልሆነ ጥያቄ መፍጠሩ ተገቢ ነው። ከዚህ አንጻር ትርክቱ ለዲፕሎማሲያዊ ፍጆታ የተቀነባበረ ሊሆን እንደሚችል መገመቱ ሚዛን ይደፋል።
ትርክቱ የሚያመጣው ችግር
ይህ የ“አል-ነጃሺ” (ንጉሥ አርማሕ) ወደ እስልምና የመለወጥ የፈጠራ ትርክት በሀገርና በቤተክርስቲያን ላይ የሚያስከትለው ጉዳት ዘርፈ ብዙ ነው።
• ኢትዮጵያ በዓለም ካሉ ጥንታውያን ሀገራት መካከል ለየት ያለ ታሪካዊና መንፈሳዊ ማንነት ያላት ሀገር ናት። ይህን ታሪክ በፈጠራ ትርክት በመተካት “ኢትዮጵያ ከመጀመሪያውኑ በሙስሊም ንጉሥ የምትመራ ነበረች” ብሎ ማቅረብ፣ ሀገሪቱ ለሺህ ዓመታት ጠብቃ ያቆየችውን ነባር ክርስቲያናዊና ብሔራዊ ማንነት እንዲሸረሸር ያደርገዋል። ይህም ትውልዱ ስለ ሀገሩ እውነተኛ ታሪክ ግራ እንዲጋባና በማንነቱ ላይ ጥርጣሬ እንዲያድርበት ያደርጋል።
• ይህ ትርክት ኢትዮጵያን ከቀጣናዊው የእስልምና እና የአረብ ዓለም ፖለቲካ ጋር በግድ ለማስማማት እንደ ድልድይ ሆኖ ያገለግላል። ኢትዮጵያን “የእስልምና መሠረት ያላት ሀገር” አድርጎ በውሸት መሳል፣ የውጭ ኃይሎች በሀገሪቱ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ እንዲገቡና የሀገሪቱን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ወደ አረብ ዓለም አጀንዳዎች እንዲያዘነብል ግፊት ለማድረግ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል። ለምሳሌ ኢትዮጵያ በአረብ ሊግ (Arab League) ውስጥ አባል እንድትሆን የሚደረገው ግፊት አንዱ መከራከሪያ ይህ መሠረት የሌለው ትረካ ነው።
• ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖችና ሙስሊሞች ለዘመናት የኖሩበት መቻቻል የተገነባው በእውነተኛ ታሪክና በጋራ እሴቶች ላይ ነው። ሆኖም አንዱ ወገን ሌላውን ወገን “ታሪክህን ሰርቀህብኛል” ወይም “ታሪክህን ለውጠህብኛል” በሚል እንዲጠራጠር የሚያደርጉ ትርክቶች ሲስፋፉ፣ በሕዝቦች መካከል ያለው እምነትና ወንድማማችነት ይላላል።
• የነገሥታቱ ታሪክና ቅርሶች የቤተክርስቲያን ሀብቶች ብቻ ሳይሆኑ የሀገር ሀብቶች ናቸው። የንጉሥ አርማሕን ማንነት ወደ ሌላ እምነት በማዞር፣ ከእርሱ ጋር የተያያዙ ቅርሶችንና ታሪካዊ ሥፍራዎችን የሌላ እምነት ተቋማት ለማድረግ የሚደረገው ጥረት፣ ቤተክርስቲያን ለዘመናት ጠብቃ ያቆየቻቸውን ይዞታዎችና የባለቤትነት መብቷን እንድታጣ ያደርጋታል።
• ለፖለቲካዊ ትርፍ ሲባል ታሪክን መገበር ወይንም ታሪክን እንደ ሸቀጥ ለፖለቲካዊ ፍጆታ ማቅረብ ለሳይንሳዊ ምርምርና ለእውነት የሚሰጠውን ዋጋ ያሳንሳል።
ማጠቃልያ፦
ባጠቃላይ ሲታይ የነጃሺ (ንጉሥ አርማሕ) ወደ እስልምና መቀየር ታሪክ ከጊዜ በኋላ የተፈጠረና በማንኛውም የታሪክ ማስረጃ የማይደገፍ ትርክት ነው። ይህ ትረካ በቅርብ አሥርተ ዓመታት ውስጥ ዳግም ጎልቶ እንዲወጣ የተደረገው ኢትዮጵያን በታሪክ ሂደት ውስጥ “የእስልምና ሀገር” አድርጎ ለማሳየት ከሚደረጉ ስልታዊ ፖለቲካዊ ጥረቶች ጋር ስለሚጣጣም ነው። እንዲህ ያለው አካሄድ የኢትዮጵያን የተለየ ታሪካዊ፣ መንፈሳዊና ባህላዊ ማንነት ፍጹም የሚዘነጋ ሲሆን፣ ለሺህ ዓመታት ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ጋር በጥብቅ ተቆራኝቶ የጸናውን ክርስቲያናዊ መሠረት ሆን ብሎ የማኮሰስ አደገኛ አዝማሚያ ነው። ስለሆነም ኃላፊነት የሚሰማቸው ሁሉ እውነቱን ከሀሰት፣ ታሪኩን ከአፈ ታሪክ ለይቶ ለትውልዱ ማሻገርና ታሪክን ከፖለቲካዊና መሰል ፍጆታዎች የመታደግ ታሪካዊ ኃላፊነት ይኖርባቸዋል።
Blogger Comment
Facebook Comment