ስለ ትምህርት ስርአት [ክፍል 1]

 እለ አጽበሐ | አዲስ ምልከታ

በመጀመርያ ስለትምህርት ስናነሳ ምን ልናነሳ እንችላለን? ትምህርት በመላው ዓለም ታሪክ የነበረ ነው። የሰለጠኑ ማህበረሰቦች በሙሉ የራሳቸው የትምህርት ስረአት ነበራቸው። ነገር ግን ብዙሃኑ ህዝብ መሰረታዊ መነሻ የሆነውን ትምህርት ብቻ ይይዛል፣ ከዚያ ወደ ህይወቱ ይቀጥላል። ጥቂት ሰዎች ግን ገፍተውበት ለረጅም ጊዜ በጥልቀት ይማራሉ። ከዚያም ምሁራን፣ በመንግስት ወይም በእምነት አከባቢዎች የሚያገለግሉ፣ አልያም በቤተመጻህፍት የሚያገለግሉ ይሆናሉ። ለምሳሌ ከክርስቶስ ልደት በፊት በግብጽ እስክንድርያ ታላቅ ላይብረሪ ነበር። በአረቡ አለምም የባግዳድ ካሊፌት ዘመን ላይ ጥናትና ምርምር ተስፋፍቶ የነበረ በመሆኑ ብዙ ሊቃውንት በአረብኛ መመራመርም ሆነ የግሪኮቹ ፈላስፎች የጻፏቸውን በመተርጎም ስራ በሰፊው ይሳተፉ ነበር። በዚህም በባግዳድ ትልቅ ቤተመጻህፍት የነበር ሲሆን በዚያም እነዚህ የተማሩ ምሁራንና ሊቃውንት በዉስጡ ይመላለሱ ነበር። የእስከንድርያውን ቤተመጻህፍት ሮማውያን ሲውሩት ተቃጠለ፣ የባግዳዱ ቤተመጻህፍት ደግሞ በምስራቅ በኩል የሞንጎል ሰራዊቶች በወረሯቸው ጊዜ ተቃጠለ ወይም ወደመ።

ከዚህም ውጪ ብዙ ምሳሌዎችን ማንሳት እንችላለን። በግሪክ ፕላቶ "አካደሚ" የሚባል ትምህርት ቤት የነበረው ሲሆን፣ የርሱ ደቀ መዝሙር የነበረው አሪስቶትልም ከፕላቶ ጋ የሃሳብ ልዩነት እያመጣ ሲመጣ ከርሱ ትለይቶ በመውጣት "ሊሲየም" የሚባል የራሱን ትምህርት ቤት ከፍቷል። ዛሬ ላይ የትምህርት ተቋማትን ስንገልጽ ብዙ ጊዜ "አካደሚ" የሚለውን ቃል እንጠቀማለን፣ ያ ከዚህ የመጣ ነው። እንዲሁም "ሊሲየም" የሚለውን ቃል ፈረንሳዮች ወስደው ይጠቀሙት ነበር። ከነሱም፣ ዘመናዊ ትምህርት ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ ያም ስያሜ አብሮ መጣ። የዚህን አሰያየም ለመረዳት የመጀመርያዎቹ የኢትዮጵያ ዘመናዊ ትምህርት ቤቶች የሆኑትን እንደነ ሊሴ ገብረማርያምን ሲያሜያቸውን ከዚህ እንደመጣ ማየት እንችላለን።

ሌላም ምሳሌ ብናይ ከሃይማኖት ጋር ተያይዞ የተለያየ የትምህርት ስረአቶች አሉ። ለምሳሌ በእስልምና የቁራን ትምህርት ለሁሉም ህጻናት የሚሰጥ ሲሆን የሚሰጥበት ቦታም "መድረሳ" በመባል ይታወቃል። መድረሳ ማለት በአረብኛ "ትምህርት ቤት" ማለት ነው። በዚህም አብዛኛው ሰው የሚያልፍበት ሲሆን ጥቂት ሰዎች ደግሞ ገፍተውበት ይሄዱና ለረጅም ዓመት ተምረውት የእምነቱ ሊቃውንት ይሆናሉ። እናም ሼክ፣ ኢማም ወዘተ የተባሉ ማዕረጎችን ይይዛሉ።

በኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነትም ስናይ "የቄስ ትምህርት ቤት" ወይም "አብነት ትህምርት" የምንለው በተመሳሳይ መልኩ የሚሄድ ሲሆን በመጀመርያ ፊደልን፣ ከዚያም ከመጽሀፍ ቀዱስ የዮሃንስ መልክትን እና መዝሙረ ዳዊትን ሁሉም ህጻናት ወንዶችም ሴቶችም ይማሩታል። ጥቂት ሰዎች ግን ገፍተውበት፣ በየቦታው እየዞሩ ለዓመታት ተምረው፣ ቅኔን፣ አቋቋምን፣ ዜማን፣ እንዲሁም የመጽሀፍ ቅዱስ አንድምታ እና ትርጓሜን፣ ወንጌል፣ ብሉይ፣ ሃዲስ እያሉ መርጠው ይማሩና፣ እንደተማሩት ልክ ዲያቆንም፣ ቄስም፣ ሊቅም፣ መጋቤ ብሉይ (የብሉይ መጻህፍትን የተማረ)፣ መጋቤ ሃዲስ (የሃዲስ መጻህፍትን የተማረ) እየተባሉ የተለያዩ ማዕረጎችን ይይዘሉ።

እነዚህ የትምህርት ስራቶች አብዛኛው ህዝብ መሰረታዊውን እውቀት ይዞ፣ ጠቂቶች ግን በደምብ እስከ ስር መሰረቱ ጠንቀቀው ያወቁ ሊቃውንት የሚሆኑባቸው ስርአቶች ናቸው። ዘመናዊው የትምህርት ስርአት ግን ከዚህ ፈጽሞ የተለየ ነው። ትልቅ ችግር ውስጥ እንዲገባም የሚያደርገው ይህ ነው። ይኸውም ሁሉም ህዝብ ረጅም ዓመታትን ወስዶ መማር አለበት የሚለው ቅድመ ግምት ነው። ይህም የብዙ ሰዎችን እድሜ በማይፈልጉትና በማያስፈልጋቸው ነገሮች ከማባከኑም በላይ የተማሩትን በትክክል የማያውቁና የማያስታውሱ ብዙ ባለቁንጽል እውቀት ሰዎችን መፍጠሩ ነው። ይህም ብቻ ሳይሆን ሆን ተብሎ እነዚህን ባለቁንጽል እውቀት ሰዎች የሚያመርት ፋብሪካ ይሆን ዘንድ ታስቦ የተሰራ መሆኑም ነው ይበልጥ እንዲከፋ የሚያደርገው። ዲግሪ፣ ማስተርስ፣ phd የያዙ አላዋቂዎችን በየዓመቱ ማምረቱ፣ እነዚህን ብዙሃን የተማሩ ያወቁ የሚጠይቁ፣ የነቁም ሰዎችን እንዲያፈራ ሳይሆን፣ የማይጠይቁ፣ የተሰጣቸውን ሁሉ የሚቀበሉ፣ ከመስመር የማይወጡ፣ ለስረአቱ ታዛዥ የሆኑ፣ ለትላልቅ ድርጅቶች ምርጥ አገልጋይ የሆኑ ዘመናዊ ባርያዎችን የሚያመርት ስርዓት መፍጠሩ ነው። ከፍተኛ የአእምሮ ብቃት ኖሮአቸው፣ ብዙ ትምህርት ተምረው ብዙ ታሪክ ብዙ ሳይንስ አንብበው፣ ብዙ ፍልስፍና ተፈላስፈውም ግን ተመልሰው ለስራቱ ታዛዥ፣ ምርጥ ሰራተኛ የሆኑ፣ የወር ደሞዝን ተጠባብቀው የሚኖሩ፣ እውቀታቸው ትምህርታቸው ከዚያ ተጠባባቂነት የማያድናቸው ሰዎችን የሚያመርት ስርዓት መሆኑ ነው። መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ ሆን ተብሎ፣ ታስቦበት፣ ተጠንቶ፣ በአሜሪካዎቹ የናጠጡ ቤተሰቦች በነ ሮኪፌለር እና በነ ካርኔጊ ቤተሰቦች ተጠንስሶ የተሰራ ስርዐት መሆኑ ነው። የዚህን መረጃና ማስረጃም እጅግ ብዙ ከመሆኑ የተነሳ በዚህ ጽሁፍ የማንጨርሰው በመሆኑ ጊዜ ወሰደን በረጅም ጊዜ ሂደት ውስጥ የምናየው ነገር ነው።
Share on Google Plus

ስለ የተለጠፈበት ቀን

    Blogger Comment
    Facebook Comment