እትዮጵያዊቷ፡ ንግሥት ማክዳ እና እስራኤላዊው፡ ንጉሥ ሰሎሞን

ከአዳምና ከሔዋን የፍጥረት ልደት ጊዜ አንሥቶ፡ በሰዎች ኪዳነ ልቦና ላይ የተመሠረተውን፡ እውነተኛውንና ትክክለኛውን አምልኮተ-እግዚአብሔር፡ በቅዱሱ ኪዳን ጠብቀውና ሕይወት አድርገው፡ በዚያን ዘመኑ መላ የምድሪቱ ዓለም ላይ፡ ይኖሩ የነበሩት፡ በእትዮጵያ ስሜ፡ የተጠሩት እትዮጵያውያንና እትዮጵያውያት ልጆቼ ብቻ ናቸው። እነርሱም፡ በኹለቱ ምድሮቻቸው ተዘልለው ይኖራሉ። ከኹለቱ ምድሮቻቸው አንዲቱ፡ አዳምና ሔዋን የተፈጠሩባት፥ የኖኅ መርከብም፡ በጥፋት ውኃ ተንሳፍፋ፡ ምድሪቱን እስከለቀቀችባት ሰዓት ድረስ፡ ከነትውልዶቻቸው የቆዩባት፡ ዐፅመርስታቸውና ማዕከላቸው የኾነችው፡ ዋናዋ አገራቸው፡ የዛሬይዪቱ እትዮጵያ ስትኾን፥ ሌላዪቱ አገራቸው ደግሞ፡ ኖኅና ልጆቹ፡ ከጥፋት ውኃ ከዳኑባት መርከባቸው ወጥተው የሠፈሩባትና የኖኅ የልጅ ልጅ የኾነው "መልከ-ጼዴቅ" የተባለው ታማኙ አጼያችን፡ እትዮጲስ፡ የቈረቈራትና ብሔረ-ሙላዳቸው የኾነችው፡ የዛሬዪቱ እየሩሳሌም ናት።

የእትዮጵያ ልጆቼ፡ እንዲህ እየኖሩ ባሉበት፡ በዚያን፡ በማክዳና በሰሎሞን ጊዜ፡ በመላው ዓለም የሚርመሰመሰው፡ ሌላው ሰብኣዊው ፍጡር ኹሉ፡ በጣዖት አምልኮ የተዋጠ ነበር። በእየሩሳሌም የሚኖሩት፡ የእስራኤል ልጆችም እንኳ፡ ለእትዮጵያዊነት በበቃው አገልጋያችን በሙሴ መሪነት፡ ቀደም ብለው፡ ከግብፅ የፈርዖን ባርነት፡ ነጻ ወጥተውና ባሕረ-ነጋሢን ተሻግረው፡ በሲና በረሀ ሣሉ፡ ከእትዮጵያ ልጆቼ፡ በትምህርት የተቀበሉትን፡ የእኛን፡ የእትዮጵያ፡ የእግዚአብሔርን ሥርዓተ-መንግሥት፡ በነቢያችን በሳሙኤል የሥልጣን ጊዜ፡ ባደረሱት ፀረእግዚአብሔር ዓመፃቸው ምክንያት፡ ያ፡ መለኮታዊው የአስተዳደር ሥርዓታችን ጸጋ፡ ከእነርሱ ስለተገፈፈ፡ ከሳዖል እስከሰሎሞን በደረሰው የሰዎች አገዛዝ ቀንበር ሥር ወድቀው የነበሩበት ዘመን ነበር። (፩ሳሙ. ፰፥ ፬-፳፪።)

በዚህ ጊዜ ነበር፦
፩. እትዮጵያዊቷ ልጃችን፡ ንግሥት ማክዳ፡ የባለቃል ኪዳን ታማኝ አገልጋያችን፡ የእስራኤላዊው ዳዊትና የእትዮጵያዊቷ የቤትሳባ ልጅ፡ ንጉሥ ሰሎሞን፡ በአባቱ ዙፋን ተቀምጦ፡ አባቱ፡ ለእኛ ሊሠራ ቃል የገባውን፡ "ቤተ-መቅደስ እያሳነፀ ነው!" የሚል ዜናን የሰማችው!

፪. በተለይም፡ አምልኮ-ጣዖት ፈጽሞ አጥለቅልቆ በሰፈነበት፡ በዚያን ዘመኑ ዓለም፡ ይህ፡ "ለእኛ፡ ለእግዚአብሔር ቤተ-መቅደስ የሚሠራ አንድ ንጉሥ ተነሥቷል!" የሚለው ዜና፡ ከዚችው ልጃችን፡ ከንግሥት ማክዳ ጆሮ ሲደርስ፡ ቀደም ብሎ፡ በእኛ መንፈስ ቅዱስ የተቃኘውና የተነሣሣው ልቦናዋ፡ በመለኮታዊው የፍቅርና የቅንዓት እሳት የተኰሰተረው።  ተኰስትሮም፡ "ይህ ዜና፡ በእርግጥ እውነት መኾኑን፡ በዓይኖቿ አስተማምና በማየት ለማጽደቅ፥ እስራኤላዊዉን ንጉሥ ሰሎሞንንም፡ በተለይ፡ ስለሃይማኖቱ አማናዊነትና ስለአምልኮቱ ትክክለኛነት በማረጋገጥ፡ በራሷ በኩል፡ በእንቆቅልሽ ትፈትነው ዘንድ፥ በእኛም በኩል ደግሞ፡ ያዘጋጀንላትን አምላካዊ ተልእኮ ፈጽማ ትመለስ ዘንድ፡ ለተቀደሰው ዕፁብ ድንቅ ጉዞዋ አነሣሥተን ያስጀመርናት።

ይህንም፡ ቅዱሳት መጻሕፍታችሁ ፡ "ወንግሥተ ሳባ፡ ሰምዓት ስሞ፡ ለሰሎሞን፤ ወስሞ፡ ለእግዚአብሔር። መጽአት፡ ትፍትኖ፡ ምስለ ጥበባ። ወቦአት ኢየሩሳሌም፡ በኃይል ክቡድ ፈድፋደ፤ ወአግማል ይፀውሩ አፈዋተ፥ ወወርቀ ብዙኀ ፈድፋደ፥ ወዕንቈ ክቡረ።
"የሳባም ንግሥት፡ የሰሎሞንን ስም፡ በዝና ሰማች፤ የእግዚአብሔርም ስም፡ ከእርሱ ስም ጋር ሲጠራ ሰማች። በጥበቧ ትፈትነው ዘንድ መጣች። በግመሎችም ላይ፡ ሽቱና እጅግ ብዙ ወርቅ፥ የከበረም ዕንቍ አስጭና፡ ከታላቅ ጓዝና ከሚያስፈራ ሠራዊት ጋር ወደኢየሩሳሌም ገባች።" በማለት፡ የጉዞዋን ዓላማ ገልጠውታል። ከዚህ በቀር፡ በእርሷ በኩል፡ ስለሃይማኖቱና ስለአምልኮቱ አጣርታ ለማወቅ ስትል፡ በጥበቧ እየፈተነችው፡ ላቀረበችለት ጥያቄ፡ ከእርሱ፡ ተገቢውን ምላሽ ማግኘቷን፡ ጨምረው ጽፈዋል። በዚህ ረገድ፡ በዓይኖቿ ባየችውና በጆሮዎቿ በሰማችው ኹሉ፡ የእርሷ አምላክ የኾነው እግዚአብሔር፡ የእርሱም አምላክ ኾኖ በማግኘቷ፡ እጅግ ተደስታ፡ በማመስገን፡ ያሳየችውን ስሜት፡ ሰሎሞን፡ "ወርእየት ንግሥተ-ሳባ፡ ...ወመሥዋዕቶኒ ዘይሠውእ ለቤተ-እግዚአብሔር፤ ወተደመት።
"የሳባ ንግሥት፡ ...ሰሎሞን፡ በእግዚአብሔር ቤተ-መቅደስ የሚያሳርገውን መሥዋዕት አየች፤ በአንክሮም ተደነቀች።" በሚል ቃል፡ እኒሁ ቅዱሳት መጻሕፍታችሁ አመልክተውታል። (፩ነገ. ፲፥ ፩-፲፫።)

በዚህ አንጻር ደግሞ፡ የልጃችን፡ የንግሥት ማክዳ፡ የሕይወቷ መመሪያ በኾነው፡ በቅዱሱ ኪዳን እትዮጵያዊነት ሃይማኖትና ምግባር፡ በዚህ፡ በኢየሩሳሌም ጉዞዋ የተከሠተውንና የተንፀባረቀውን፡ የእኛን የእግዚአብሔርን እውነት፥ ከዚህ የተነሣም፡ በእትዮጵያዊት እናቱ፡ በቤትሳባ በኩል፡ ወንድሟ ለኾነው፡ ለእስራኤላዊው ንጉሥ ሰሎሞን፡ ይህችው ንግሥት ማክዳ፡ በእትዮጵያዊትነት እኅትነቷ፡ያበረከተችውን ምዕዳኗን [ምክሯንና ተግሣፅዋን] በማስተዋል ተመልከቱት!

አዎን! ይህችው እትዮጵያዊት ንግሥት ማክዳ፡ የሰሎሞን ሰብኣዊና እስራኤላዊ፥ ሥጋዊና ምድራዊ፥ ዓለማዊና ጣዖታዊ ጥበብ፡ ከእርሷ እግዚአብሔራዊና እትዮጵያዊ፥ መንፈሳዊና ሰማያዊ፥ ሃይማኖታዊና አምልኮታዊ ጥበብ ጋር፡ የቱን ያህል ይመሳሰል፥ ወይም፡ ይቀራረብ እንደኾነ፡ በዚሁ ጥበቧ ትፈትነው ዘንድ፡ወደኢየሩሳሌም መጥታ፡ ከእርሱ፡ ከሰሎሞን በሚበልጠው በእየሱስ መሲሕ ጥበብነት፡ እግዚአብሔራዊዉን ዕውቀትና እትዮጵያዊውን ትምህርት፡ ለሰሎሞን በማበርከት፡ ይህንኑ የተልእኮ ግዳጇን፡ በብቅዓት አከናውና፡ ወደአገሯ በድል ፍሬያማነት መመለሷን፡ ከዚህ ቀደም ብዬ ገልጬላችኋለሁ።

እንግዴህ፡ በእውነተኛ ማንነቷና ምንነቷ፡ በእኛ በእግዚአብሔር ዘንድ፥ በእውነተኞቹ ፍጡሮቻችንም ዘንድ፡ እንዲህ፡ በግልጽና በእውን ታውቃ፡ በሕያውነት የኖረችው፥ ዛሬ ያለችውና ወደፊትም የምትኖረው ልጃችን ንግሥት ማክዳ፡ ጥንት፡ ከአዳምና ከሔዋን፥ ቀጥሎ፡ በኖኅና በሓይከል፥ ተያይዞም፡ "መልከ-ጼዴቅ" በተባለው፡ በእትዮጲስና "ሳሌም" በተባለችው፡ በእንተላ፥ ከዚያም፡ በአብርሃምና በሣራ፥ በኬጡራም፥ ተከታትሎም፡ በሙሴና በሲጳራ፥ በመጨረሻ፡ በዳዊትና በቤትሳባ በኩል፡ ቀደም ብሎ፡ ለአራት ሽህ አምስት መቶ ዓመታት ያህል፡ ያለማቋረጥ ተራዝሞ፡ ከእኛ ጋር፡ በቅዱሱ ኪዳን በመዋዋል፡ እኒህን የመሰሉ፡ የእኛ "የእግዚአብሔር ልጆች!"፥ ይልቁንም፡ ከሌሎቹ፥ ከእስራኤልም ልጆች ለይተን ለመጥራት ስንል፡ የእኔ፡ "የእትዮጵያ ልጆች!" ያልናቸው ሰብኣውያን ፍጡሮቻችን፡ በኪዳነ ልቦና ተቀብለው፡ ከትውልድ ወደትውልድ፡ ሲወርድ ሲዋረድ፡ ባልተቋረጠ ህልውናቸው፡ በእኛ፡ በእግዚአብሔር እውነትና መንፈስ፡ ሲያካኼዱት የኖሩት፥ ፍጹም የኾነው አምልኮተ-እግዚአብሔራቸው ያስገኛት ናት።

አዎን! እርሷ፡ በልጄ በወዳጄ በእየሱስ መሲሕ ቃል፡ ሰሎሞንና በዘመኑ የነበረው ትውልድ፡ የሚገኙበትን ኹኔታ ሰምታ፡ በእትዮጵያነቷ፡ የእግዚአብሔርን መንግሥት መሲሓዊ ዕውቀትና ጥበብ፥ መልእክትና ምሥራቹን፡ ለሰሎሞንና በዘመኑ ለነበረው፡ ለዚያ ትውልድ ልትገልጥና ልታስተምር፥ ልታደርስና ልትሰብክ፡ ወደኢየሩሳሌም ተጉዛ፡ ተልእኮዋን፡ በመልካም ፍሬያማነት ፈጽማ፡ ወደአገርዋ ወደእትዮጵያ የተመለሰች ናት።

የእርሷ ነገር፡ በዚህ ብቻ የተወሰነም አይደለም፤ በመሲሕነቱና በጥበቡ፡ ከሰሎሞንና ከጥበቡ የሚበልጠው እርሱ ልጄ ወዳጄ እየሱስ፡ በሕያዋንና በሙታን ላይ፡ የመጨረሻውን ብያኔ ሊሰጥ፡ በሚመጣበት ጊዜ፡ እትዮጵያዊት ልጃችንን፡ ንግሥት ማክዳን ተቀብሎ ያስተናገደውን፡ የሰሎሞንንና በዘመኑ የነበረውን ትውልድ ፈለግ ባለመከተል፡ የልጄን የወዳጄን ትምህርቱንና ጥበቡን ብቻ ሳይኾን፡ ራሱንም እንኳ፡ በእግዚአብሔር ልጅነቱ ለመቀበል፡ "እንቢ!" ብሎ፡ በመስቀል ሥቃይ፡ እስከመግደል የደረሰውን፡ ያን የኋለኛውን የእርሱን ዘመን፡ ክፉና ከሃዲ፥ ዓመፀኛና አመንዛሪ ትውልድ፡ በእርሱው ፊት፡ በዚያው፡ የሃይማኖትና የምግባር ጥበቧ የምትፋረደው፡ ይህችው፡ እትዮጵያዊቷ ንግሥት ማክዳ መኾኗን እንደተናገረላት፡ መላው ዓለም በተቀበላቸው የሃይማኖት መጻሕፍቶቹ ውስጥ ተመዝግቦ ስለሚነበብ፡ በኹላችሁ ዘንድ ይታወቃል።

"የሳባ ንግሥት" በመባል የምትታወቀው፡ ይህችው ንግሥት ልጃችን ማክዳ፡ "እትዮጵያ" ለኾንሁት፡ ለእኔ፡ ለድንግል ማርያም፡ ሰብኣዊት ጥላና ቀዳሚት አርአያ፥ አብነትና ምዝላቴ ናት። ይህን እውነታ የማያውቅ፡ ሰብኣዊ ፍጡራችን ካለ፡ እንግዲህ ወዲህ ይወቅ!
Share on Google Plus

ስለ የተለጠፈበት ቀን

    Blogger Comment
    Facebook Comment