ኢትዮጵያ ትንሳኤ አላት?


ጥያቄ:- ኢትዮጵያ ትንሳኤ አላት?

መልስ:- አበው ገዳማውያን እንደነገሩን፥ ድርሳናቱ እና ገድላቱ እንደገለጹት፥  አወ አላት!
አብዝሀኛው ክርስትያንም የ ሀገራችን ትንሳኤዋ እንደደረሰ ያምናል፥ እኛም እናምናለን።

ጥያቄ: 2016 የኢትዮጵያ ትንሳኤ ይገለጣል?

መልስ: ሁሉም ህዝበ ክርስትያን ንስሀ ቢገባ ወደ እግዚአብሔርም ብንመለስ፡ በገድለ አቡነ ሙሴ መጽሀፍ ላይ እንደተገለጸ፡ የሀገራችን ትንሳኤ ቶሎ ይገለጻል። ንስሀ ካልገባን ግን ምድራችን እንደምትጠፋ መጽሀፉ ላይ ተጽፏል።

ጥያቄ:- ንጉስ ቴዎድሮስ የት ነው ያሉት? ምን አይነት ሰው ናቸው?

መልስ:- ንጉስ ቴዎድሮስ የት እንዳሉ፡ ምን እንደሚሰሩ ከበቁ ሰወች በቀር የሚያውቅ እንደሌለ በ ገድለ አቡነ ሙሴ፣ በ ራዕየ ሳቤላ እና ሌሎች መጻህፍት ላይ ተጽፏል።
 
ስለዚህ ንጉስ ቴወድሮስ የት እንዳሉ ከበቁ ሰወች በቀር ማንም አያውቅም። የብቃት ደረጃ ማለት፡ ከንጽህና ህይወት ቀጥሉ ያለ የ መንፈሳዊ እድገት ደረጃ ነው። ነገር ግን የብቃት ደረጃ ላይ ሳይደርስ፡ እኔ አውቃቸዋለሁ፣ ጓደኞች ነን፤ ተገለጹልኝ የሚል ሰው ብትሰሙ እሱ ሀሰተኛ ነው። ራዕዩም ከ ሰይጣን እንጅ ከሰው አይደለም። ነገር ግን ያ ሰው የብቃት ደረጃ መድረሱን እና አለመድረሱን በንግግሩ፣ በስራው እና በድርጊቱ እንዲሁም ትክክለኛ መልስ የሚያሰጥ ሱባኤ በመያዝ እናውቃለን።

ስለ ንጉስ ቴወድሮስ ቅድስት ሳቤላ በመጽሀፏ: ረዝም፣ መልከ መልካም፣ እና በደረቱ ላይ የመስቀል ምልክት ያለው (በደረቱ የሚያሳልምበት መስቀል ያንጠለጠለ ወይንም ያነገተ) ካህን እንደሆነ ትገልጻለች። ካህናቶች ደግሞ ደግሞ ከ ሌዋውያን ወገን ይቆጠራሉ። ንጉሱም የዘር ሀረጉ ከነገደ ሌዊ እንደሆነ ግልጽ ነው። ይህ ሰው ቅን፣ የዋህ እና ጻድቅ ሰው ሲሆን አካሄዱም እንደ እግዚአብሔር ፍቃድ እንጅ እንደ ሰው አይደለም። በሁለት ቃል አይናገርም፥ ሽንገላም የለበትም።
ከየት እንደሚነሳ፣ እንዴት እንደሚነሳ እና መቸ እንደሚነሳ ከበቁ አባቶች በቀር የሚያውቅ የለም።

ጥያቄ:- ወደ ኢትዮጵያ ትንሳኤ እንዴት መሻገር ይቻላል?

መልስ:- ወደ ኢትዮጵያ ትንሳኤ ማን እንደሚሻገር የሚያውቀው እግዚአብሔር ብቻ ነው። በዚህ ምድር ላይ ሲኖሩ በቅንነት፣ በየዋህነት፣ በፍቅር እና በትህትና የሚኖሩ ሰወች  ቢሆሩ የኢትዮጵያን ትንሳኤ ያያሉ፥ ቢሞቱም ገነት መንግስተ ሰማያትን ይወርሳሉ። ስለዚህ እለት እለት መንፈሳዊ ድክመታችንን እያሰብን በጾም፣ በጸሎት፣ በሥግደት እና መንፈሳዊ ምግባራትን እያደረግን እግዚአብሔርን ይህን ክፉ ዘመን እንዲያሻግረን መማጸን እንጅ መጽሀፍ እንደሚል ስለ ስጋ ማሰብ ሞት መሆኑን ተረድተን ስለ ነፍሳችን አብዝተን ማሰብ ይኖርብናል እንጅ የጽድቅ ህይወት ሳይኖረን ስለ ትንሳኤ ብናስብ ከንቱ ምኞት ነው የሚሆነው።

ጥያቄ:- ቤተ ክርስትያን ውስጥ ሁሉም ካህናት ውግዛን ናቸው ማለት ነው? ስለ ቅዱስ ስጋ ወደሙስ ምን ትላላችሁ?

መልስ:- አይደሉም። እንደ ዘመኑ አነጋገር ደብተራወች፣ ቅባት፣ ጸጋ፣ አምልኮተ ባዕድ ያለባቸው፣ መናፍቅ እና ለፖለቲካው ወግነው መክሊታቸውን የቀበሩት በ ስራቸው ውጉዛን ሲሆኑ፡ ሌሎች ቅን የዋህ እና ትሁታን የሆኑ፣ ራሳቸውን አስጨንቀው ስለ ምዕመኑ የሚኖሩ አንዳንዶቹም የንጽህና እና የብቃት ደረጃ ላይ ያሉ አባቶች በቤተ ክርስትያን ውስጥ አሉ። ቅዱስ ስጋ ወደሙ ቤተ ክርስትያን ሙሉ ለሙሉ እስክትዘጋ፣ ንጹህ ካህናት፣ ምእመናን እንዲሁም ህጻናት እስካሉ ድረስ ይኖራል፥ ይቀጥላል።

ጥያቄ:- ንስሀ የት እና እንዴት እንግባ? ወጥ የሆነ መልስ ካላችሁ?

መልስ:- ስለ ንሥሀ ብዙ ትምህርቶች ተሰጥተዋል፡ ነገር ግን ባጭሩ እውነተኛ ንስሀ በሀሳብ፣ በንግግር እና በድርጊት የሰራናቸውን ሀጥያቶች በመዘርዘር በመጀመርያ መጸጸት እና ማልቀስ ይገባል። ከዚያም እነዚህን ሀጥያቶች ለ እውነተኛ ንጹህ ካህናቶች በመናገር ሀጥያትን  መናዘዝ እና የተሰጠንን ቀኖና መጨረስ ያስፈልጋል። ከዚያም ድጋሜ በተመሳሳይ ወይንም በሌላ ሀጥያት እንዳንወድቅ በጾም፣ በጸሎት እና በስግደት እየበረታን የስሜት ህዋሳቶቻችንን ሁሉ መጠበቅ ይኖርብናል። በተለይ ቅዱስ ሥጋ ወደሙ የምንቀበል ከሆነ አብዝተን በመስገድ እና በመጸለይ እንዲሁም የረሳናቸው መንፈሳዊ ምግባራት ካሉ በመፈጸም  ልባችንን አብዝተን መጠበቅ ይኖርብናል።

ጥያቄ:- ከቤተ ክርስትያን አገልግሎት ራስን መለየት እና በቤተ ክርስትያን ውስጥ እያገለገሉ መኖር እንዲሁም ውግዘት ስለሚባለው ነገር ትክክለኛው መንገድ ምንድነው?

መልስ:- ውግዘት የቤተ ክርስትያን ሥርዓት፣ ዶግማ እና ቀኖና ሲሻር ቅዱሳ አባቶች ተሰባስበው የሚወገዘው ሰው ከክፉ ስራው ይመልስ ዘንድ እንዲሁም ምዕመኑን በኑፋቄው እንዳይበክል የሚደረግ የመለየት ሥርዓት ነው።

የቅዱስ ጴጥሮስ እና የቅዱስ ጳውሎስ ስልጣን ያላቸው ካህናት አባቶች (እውነተኞቹ ካህናት) በሰማይም ሆነ በምድር የማሰርም ሆነ የመፍታት ስልጣን አላቸው። ለምሳሌ በቤተ ክርስትያናችን ውስጥ ተደብቀው ንጹህ ካህን መስለው የሚኖሩ ቅባት እና ጸጋ (ካቶሊክ) ፣ መናፍቅ (ምዕመኑን ለ መናፍቃን አሳልፈው የሚሰጡ)፣ በክፉ መናፍስት አምልኮት የተጠመዱ፣ እንደ ዘመኑ አነጋገር ድብትርና ሙያ ላይ ያሉ፣ እነዚህ እና ሌሎች ብኩርናቸውን ረስተው የፖለቲካ ስራ ላይ የገቡ ሁሉ እውነተኞቹ አባቶች ባያወግዟቸው እንኳን ውግዛን ናቸው። ከነዚህ ሰወች ጋር ፈጽሞ ህብረት ሊኖረን አይገባም።
 
ነገር ግን አሁን ባለው ሁኔታ በ ነዚህ ክፉ አገልጋዮች በግድ ተገፍተው ወጥተው ራሳቸውን ለይተው በጾም፣ በጸሎት፣ በስግደት እያተጉ ራሳቸውን ከሀጥያት ስራ ለይተው የሚኖሩ አባቶች እና ምዕመናንም ሊኖሩ ይችላሉ። ነገር ግን እነዚህ አባቶች እና ምዕመናን በአንደበታቸው፣ በሀሳባቸው እና በድርጊት ሀጥያት እንዳይሰሩ እየተጠነቀቁ ይኖራሉ እንጅ፣ ስድብ፣ ጥላቻ፣ ክፋት፣ ምቀኝነት፣የሰውን ሀጥያት መግለጥ እና ማዋረድ እንዲሁም አድመኝነት አይሰለጥንባቸውም። እንዲያውም በቤተ ክርስትያን እና በምዕመኑ ስለሚደርሰው ነገር እያዘኑ እና እየጸለዩላቸው ይኖራሉ። ነገር ግን አንደበታቸውን ሳይገቱ፡ በሀጥያት ውስጥ ተዘፍቀው ከቤተ ክርስትያን ስለራቁ ብቻ ይበልጥ የሰይጣን እና የዓጋንንት መጫወቻ ከመሆን ውጭ ምንም የጽድቅ ህይወት ሊኖራቸው አይችልም። እንደውም ቢቻል ምዕመኑ እንዳይበተን ከ እውነተኞቹ አባቶች ጎን በመቆም ለ ቅድስት ቤተክርስትያን እስከ ሞት ድረስ ልንቆምላት ይገባናል። እንግዲህ ከቅዱሳን አባቶቻችን እና ከሰማዕታት ህይወት የምንማረው ይህንን ነው።

ጥያቄ:- በቤተ ክርስትያን ውስጥ ከቤተ ክርስትያን ውጭም ብዙ ተዓምራት እና ምልክቶች እንዲሁም ብዙ ምስክርነቶች ይሰጣሉ። ዘመኑን የዋጀው እና ትክክለኛው መንገድ የቱ ነው?

መልስ:- አሁን ዘመኑ የመጨረሻው ዘመን ነው። ሰይጣንም ከእስራቱ ለጥቂት ጊዜ የሚፈታበት ጊዜ ስለሆነ ተዓምራት እና ምስክርነቶችን ተከትሎ መንጎድ ተገቢ አይደለም። እያንዳንዷ የምናደርጋት ነገር ነፍሳችንን አስይዘን እንደሆነ ለ አፍታም መዘንጋት የለብንም። ስለዚህ ከ ቅድስት ቤተ ክርስትያን ሳንርቅ እንደ ምዕመኑ እንደ ምዕመን፥ ካህናቱም እና እንደ ጸጋቸው መጠን ክፉውን እየተውን እና እየተቃወምን መልካሙ እየያዝን በመንፈሳዊ ህይወታችን እለት እለት ለማደግ እየጣርን መኖር ይኖርብናል።


Share on Google Plus

ስለ የተለጠፈበት ቀን

    Blogger Comment
    Facebook Comment