የተረሳችው ገነት



✍ ታርቆ ክንዴ

ብዙ ያላት፣ ቅዱሳን አበው በቅድስና የኖሩባት፣ የሚኖሩባት፣ የሁሉም እምነት ተከታዮች ያለ ማቋረጥ ለአምላክ ምስጋና የሚያቀርቡባት፣ ነብሳቸውን አጥግበው፣ ሥጋቸውን አስርበው፣ አንደበታቸውን ከክፉ ንግግር ቆጥበው፣ ወገባቸውን በገመድ አስረው፣ ጤዛ እየላሱ፣ ድንጋይ እየተንተራሱ፣ ድምጸ አራዊትን እየታጋሱ፣ ለምድር ሰላምና ፍቅርን የሚለምኑባት ከአምላክ በረከት የሚቀበሉባት ቅዱሳን የበዙባት ምድር ናት ኢትዮጽያ፡፡ 

ነብዩ እውነትና ፍትሕ ያለባት፣ ፍትሕ አዋቂ ንጉሥ የነገሠባት ያሏት፣ ከሀገርም አስበልጠው የመረጧት፣ አትንኳት ሲሉ ትዕዛዝ ያስቀመጡባት፣ ከልባቸው የወደዷት፣ ከልባቸውም የመረቋት፣ ሁሉም በሰላም እንደሚኖርባት ያዩዋት ድንቅ ሀገር ናት ኢትዮጵያ፡፡ 

በሐይቅ ውስጥ ገዳማት የተገደሙባት፣ ከአለት ላይ ቤተ መቅደስ የታነጸባት፣ በዋሻ ውስጥ አድባራት ያሉባት፣ ሐይማኖታዊ አሻራዎች የሚንጸባረቁባቸው መስጊዶች ያሉባት፣ በምድሯ የተዋቡ አብያተ መንግሥታት የታነጹባት፣  በቤተ መንግሥቷ ለዘመናት የጸና  ዙፋን የኖረባት፣ በዙፋኑ ላይ ኃያላንና ቅዱሳን ነገሥታት የነገሡባት፣  አምላክን እየፈሩ፣ ሕግጋትን እያከበሩ የኖሩባት፣ ጠላት የማይገረስሳቸው የጦር መሪዎች የኖሩባት፣ አራሽና ተኳሾች የሚወለዱባት ምድር፡፡ 

ድንቅ ባሕሎችና የረቀቁ እሴቶች ከእነ መልካቸውና ከእነ ማዕረጋቸው ለዘመናት የጸኑባት፣ ጠላቶች አፍረው የሚመለሱባት፣ ድል በስሟና በግብሯ የተቸራት፣ ከድል አድራጊነት ውጭ ሌላ ግብር የማይስማማት፣ ነጻነቷን ለመውሰድ የመጡ ኹሉ እጅ የነሱላት፣ ነጻነትን የተጠማ ሁሉ የነጻነት እናት የሚላት፣ በባርነት ጨለማ የኖረ ሁሉ  የነጻነት ብርሃን እያለ የሚጠራት  ሀገር ኢትዮጵያ፡፡  

ታይተው የማይጠገቡ ኮረብታዎች፣ ልብን የሚሰርቁ ተራራዎች፣ ከምድር የእሳት እንፋሎት የሚያወጡ ሞቃታማ ሥፍራዎች፣ ሀሴትን የሚሰጡ ሜዳዎች ሁሉም ያሉባት ሀገር ናት ኢትዮጵያ፡፡

“ወንዝም ገነትን ያጠጣ ዘንድ ከዔደን ይወጣ ነበር፡፡ ከዚያም ለአራት ክፍል ይከፈል ነበር፡፡ የአንደኛው ወንዝ ስም ፊሶን (ኤፌሶን)፣ እርሱም ወርቅ የሚገኝበትን የኤውላጥ ምድርን ይከብባል፡፡ የዚያም ምድር ወርቅ ጥሩ ነው፡፡ ከዚያም ሉልና የከበረ ድንጋይ ይገኛል፡፡ የሁለተኛውም ወንዝ ስም ግዮን ነው፡፡ እርሱም የኢትዮጵያን ምድር ሁሉ ይከብባል፡፡ የሦስተኛውም ወንዝ ስም ጤግሮስ ነው፡፡ እርሱም በአሦር ምሥራቅ የሚሄድ ነው፡፡ አራተኛውም ወንዝ ኤፍራጥስ ነው፡፡ እግዚአብሔር አምላክም ሰውን ወስዶ ያበጃትም ይጠብቃትም ዘንድ በዔድን ገነት አኖረው”  እንዳለ መጽሐፍ  ገነትን የሚያጠጣ  አፍላግ ከዔደን የወጣባት፣ ምድሯንም የሚከብባት፣ የተመረጠች፣ የተከበረችና የረቀቀች መሆኗን የሚመሰክርላት ምስጢራዊት ሀገር ነች ኢትዮጵያ፡፡ 

ኢትዮጵያ ታይተው የማያልቁ፣ ተነግረው የማይዘለቁ ውብ ስጦታዎችን በእቅፏ ይዛለች ፤ በአጸድዋም  ሰብስባለች፡፡ በውስጧ ያሏትን ሀብቶቿን፣ አምላክ የቸራትን ውበቷን፣ ልጆቿ የገነቡትን ታሪኳን፣ ባሕሏንና ወጓን እያሳየች፣ ታሪኳን ሁሉ ለዓለም እየነገረች መኖር የምትችል ስንዱ እመቤት  ናት፡፡ ዳሩ የተሰጣትን አልተጠቀመችበትም፣ ያልታየውን አላሳየችውም፣ ኅብስቱን ለዓለም አልሰጠችውም፡፡ 

የታሪክ ተመራመሪው ፕሮፌሰር አደም ካሚል ኢትዮጵያ ረጅም ዘመን ታሪክ ያላት ሀገር ናት፡፡ ረጅም ዘመኗ ምናባዊ ሳይሆን በጥናት የተረጋገጠ ነው ይላሉ፡፡ ኢትዮጵያ አሁን ካላችበት በብዙ የሰፋችና ታላቅ ሀገር መሆኗን ታሪክ ይዘክራል፡፡ ታላላቅ ሥርወ መንግሥታት፣ አያሌ የስልጣኔ ዘመናት፣ እጅግ ታላቅና የተከበረ  የመንግሥት ሥርዓት  የነበራት ሀገር ናት፡፡ ኢትዮጵያ በዓለም ታላላቅ ታሪኮች ላይ አሻራዎቿን ያስቀመጠች፣ ለየትኛውም ቀኝ ገዢ ያልተበገረች ሀገርም  ናት ይላሉ የታሪክ ተመራማሪው፡፡ 

አፍሪካውያን እናታችን እያሉ የሚጠሯት የነጻነት እናት ናት ኢትዮጵያ፡፡  ኢትዮጵያ ነብዩ መሐመድ( ሰ.ዐ.ወ) የእውነት ምድር ያሏት ሀገር ናትም ይሏታል ፕሮፌሰር አደም፡፡ በሙስሊሙ ዓለምም ኾነ በሌሎችም ዘንድ ትልቅ ክብር ያላት ሀገር መሆኗን ነው የነገሩኝ፡፡በየሄዱበት ሀገር ኹሉ "እናንተኮ የእኛ አባቶች፣ የእኛ መሪዎች ናችሁ"የሚሉ ምስክርነቶች እንደሚበዙ ገልጸውልኛል።  አፍሪካውያን ነጻነታቸውን ባገኙ ጊዜ ምልክት ይሆናቸውን ዘንድ ሰንደቅ ዓላማ ሲመርጡ ቀለሙን ከነጻነት እናታቸው ወስደዋልም ነው የሚሉት፡፡ 

ኢትዮጵያዊ ትውልድ የኢትዮጵያን የውጭ ፖሊሲ እና ታሪኳን የሚያከብር፣ የሚያስከብር፣ በቅጡ የሚያውቅና የሚያሳውቅ መሆን አለበት፤  ኢትዮጵያ የተሰጣትን ውበት ብቻ አሳይታ ሃብታም መሆን ትችላለች፣ ነገር ግን ውበቷን አሳይተን መጠቀም አልቻልንም ነው ያሉት፡፡  

ኢትዮጵያ በቱሪዝም ሃብቷ ብቻ በሙቀት፣ በውኃ ማጣት እና በልዩ ልዩ የተፈጥሮ ችግሮች የሚሰቃየውን የመካከለኛውን ምሥራቅ ዓለም መያዝና፣ በዓመት ሚሊዮን እንግዶችን ተቀብላ ሚሊዮን ዶላሮችንም መሰብሰብ ትችላለች ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያ ሁሉም አይነት የአየር ጠባይ ያላት ምቹ ሀገር ናት፣ ኢትዮጵያ  አያሌ ሃይማኖታዊና ታሪካዊ ቅርሶች፣ ታሪካዊ ሥፍራዎች እና ተፈጥሮ ያሳመራቸው የቱሪዝም መደረሻዎች እንደሏትም የታሪክ ተመራመሪው አንስተዋል፡፡  ያላትን ሁሉ ታሳይ ዘንድም ሰላም እንደሚያስፈልጋት አመላክተዋል፡፡ 

ኢትዮጵያን ማወቅ ባለመቻላችን ብዙ ነገር አጥተናል የሚሉት የታሪክ ተመራማሪው ብዙዎች የተረሳችው ገነት ብለው ይጽፉባታል ይላሉ ፕሮፈሰር አደም፡፡  በገነት ሁሉም አለ፣ ዋናው በገነት ያለውን አጠቃቀሙ ላይ ነው፣ ኢትዮጵያ የተረሳች ገነት ናት፣ ሁሉም እያላት ምንም እንደሌላት ችግር ያሰራት፣ ሰላም ሲገባት ሰላም የራቃት፣ አንድነትና ፍቅር ሊኖራት ሲገባ እርሱ የተናጋባት፣ እንደ ገነት ሁሉ ጸጥታ፣ እርጋታ ሲገባት ሁከት የበዛባት ሀገር ሆናለች ነው ያሉት፡፡ 

ልጆቿም እንደ ጀነት ሰላም፣ ደስታ፣ ጸጥታ፣ ምስጋና፣ ፍቅርና ተድላ ይኖርባት ዘንድ ሥሩላት፡፡ ሰላምን ስጧት፣ ፍቅርን አትንፈጓት፣ በሚመጥናት ሥፍራም አኑሯት፡፡  እርሷ ብዙዎች ሊያዩዋት የሚጓጉላት፣ ስለ እርሷ መልካም ነገርን ይሰሙ ዘንድ ጆሯቸውን የሚያዘነብሉላት፣ በአሻገር ሆነው የሚናፍቋት እና የሚሳሱላት ሀገር ናት ነው ያሉት፡፡ 




Share on Google Plus

ስለ የተለጠፈበት ቀን

    Blogger Comment
    Facebook Comment