‹‹ሰማእቱ ቅዱስ ፊቅጦር ስለ ኢትዮጵያ ያየው ራእይ››‼️


ሰማዕቱ ቅዱስ ፊቅጦር አንድ የሚነገር ትልቅ ታሪክ አለው፡፡ እርሱም በሰማዕትነት ካረፈ ከብዙ ዘመን በኋላ በራእይ ተገልጦ በ8ኛው ሺህ ዘመን በሀገራችን በኢትዮጵያና በግብፅ እንዲሁም በቁስጥንጥንያና በሮም ወደፊት የሚሆነውን ነገር ሁሉ በግልጽ የተናገረ መሆኑ ነው፡፡

‹‹ስለ ሃይማኖት ቅዱስ ፊቅጦር ያየው ራእይ›› የሚል መጠሪያ ያለው ይህ ራእይ በሀገራችን ጎጃም ደብረ ጽሞና ገዳም ውስጥ ይገኛል፡፡ ይህንን በተመለከተ ቅዱስ ፊቅጦር የተናገረውንና ቅዱስ ገድሉ ላይ የተጻፈውን ቀጥሎ እንመለከተዋለን፡-

‹‹…በእስላሞችም ጊዜ በግብፅ ሀገር ሁሉ የክርስቶስ ሕግ አይቋረጥም፡፡ የጾም፣ የጸሎትና የቍርባን እምነት ይኖራል፡፡ ከእስላሞች ጋር እየኖሩ የሃይማኖት ጽናት ትበዛለች፤ በማርቆስ መንበርም የሊቀ ጳጳሳት መሾምም አይቋረጥም፤ በሊቀ ጳጳሳት እጅ በየደረጃው የጳጳሳት፣ የኤጲስ ቆጶሳት፣ የቀሳውስትና የዲያቆናት ሹመትም አይቋረጥም፡፡ የእስላሞችም መንግሥት ጥቂት ዘመናት ናቸው፡፡ ከጥቂት ዘመናት በኋላ እግዚአብሔር በኢትዮጵያ ሀገር ክርስቶስን የሚወድ ቅዱስ ሰው ያነግሣል፡፡

ዐረማውያንም በእርሱ እጅ ይደመሰሳሉ፡፡ ከዚህ በኋላ ወደ ግብፅ ሀገር ሄዶ እስላሞችንና መንግሥታቸውን ሁሉ ያጠፋል፡፡ እግዚአብሔር በቍስጥንጥንያ እርሱን የሚወድ ስሙ ትውልደ አንበሳ የተባለ ሰው ያነግሳል፡፡ ከኢትዮጵያ ንጉሥ ጋር ይገናኝ ዘንድ ይመጣል፡፡ በግብፅ መሀል ቦታ ላይ ይገናኛሉ፡፡ 

ከእርሱ ጋርም የእስክንድሪያ ሊቀ ጳጳሳትና የቍስጥንጥንያ ሊቀ ጳጳሳት ይገናኛሉ፡፡ የኢትዮጵያ ንጉሥ ሠራዊቱን በደቡብ በኩል ትቶ የቍስጥንጥንያም ንጉሥ ሠራዊቱን በሰሜን በኩል ትቶ ሁለቱ ነገሥታትና ሁለቱ ሊቃነ ጳጳሳት ተገናኝተው እርስ በእርሳቸው ሰላምታ ይሰጣጣሉ፤ ሊቃነ ጳጳሳቶቹ በመንበራቸው ላይ ተቀምጠው ነገሥታቱን ‹በየመንበራችሁ ላይ ተቀመጡ› ይሏቸዋል፡፡ የቍስጥንጥንያ ሊቀ ጳጳሳት ‹የእኛ ሃይማኖት ትበልጣለች› ይላል፡፡ የእስክንድሪያውም ሊቀ ጳጳሳት ‹እግዚአብሔር የሰጠኝን ቃል እኔ እነግራችኋለሁ› ይላል፡፡ ሁለቱ ነገሥታትም ‹አባታችን በል ንገረን› ይሉታል፡፡ 

‹የአባ ሲኖዳ ወደምትሆን ወደዚህች ታላቅ ቤተክርስቲያን ገብተን በአንዲት ታቦት ላይ እኔ እቀድሳለሁ፣ ይህ ባልደረባዬ ሊቀ ጳጳሳት በአንዲቷ ታቦት ላይ ይቀድስ፤ ሁሉም ሕዝብ ሠራዊቶቻችሁም መጥተው ይመልከቱ› ይላል፡፡ ‹መንፈስ ቅዱስ እያያችሁት ከሁለታችን በአንዱ ቁርባን ላይ ከወረደ በዚያ ሃይማኖት ሁላችን እንሂድ፣ ሃይማኖቷም ትታወቃለች ቀንታለችና› ይላቸዋል፡፡ 

ሁለቱ ነገሥታት ‹እሺ በዚህ ቃል ተስማምተናል፣ የእግዚአብሔር ምክር ናትና› ይሉታል፡፡ ያን ጊዜ ሁለቱ ነገሥታትና ሊቃነ ጳጳሳት ሠራዊቶቻቸውም ሁሉ ካህናቶቻቸውም፣ ሕዝቡም ወደዚህች ታላቅ ቤተ ክርስቲያን ይገባሉ፡፡ ሁለቱ ሊቃነ ጳጳሳትም በሁለቱ ታቦታት ላይ ይቀድሳሉ፡፡ በዚያ ያሉ ሁሉ እያዩ መንፈስ ቅዱስ በነጭ ርግብ አምሳል ከብርሃን ጋር የእስክንድሪያው ሊቀ ጳጳሳት በቀደሰው ቍርባን ላይ ይወርዳል፡፡ ያን ጊዜ የኢትዮጵያ ንጉሥ ይደሰታል፣ የእርሱም ሊቀ ጳጳሳት ነውና፡፡ በእግዚአብሔር ፊትም የእርሱ የሃይማኖት ሕግ የተወደደ ይሆናል፡፡

የሮም ንጉሥ ግን ከሕዝቦቹ ጋራ ያዝናል፡፡ መጻሕፍቶቻቸውን ሁሉ ሰብስበው ወደ ባሕር ይወረውሯቸዋል፡፡ ሃይማኖታቸውንም ስለአጠፋና መናፍቃን ስላደረጋቸው የቀድሞውን ሊቀ ጳጳሳቸውን ሊዎንን ይረግሙታል፡፡ ሁሉም ወደ አንዲት የእስክንድሪያ ሊቀ ጳጳሳትና የኢትዮጵያ ንጉሥ ሃይማኖት ይመለሳሉ፡፡ 

ሮምም፣ ግብፅም፣ ኢትዮጵያም ሁሉም የተስማሙ ይሆናሉ፤ በመካከላቸውም ጽኑ ፍቅር ይሆናል፡፡ ሁሉም ሃሌ ሉያ እያሉ እግዚአብሔርን ፈጽመው ያመሰግኑታል፡፡ የኢትዮጵያ ንጉሥና የሮም ንጉሥ እርስ በእርሳቸው እጅ መንሻንና ሰላምታን ተሰጣጥተው ወደየሀገራቸው ይመለሳሉ፡፡ ቅዱስ ፊቅጦርም ለእናቱ የሚነግራትን ይህንን ሁሉ ትንቢት ከጨረሰ በኋላ ‹እናቴ ማርታ ሆይ ሰላም ላንቺ ይሁን› ብሎ ከእርሷ ተሰወረ፡፡››

የሰማዕት የቅዱስ ፊቅጦር ረድኤት በረከቱ ይደርብን በጸሎቱ ይማረን!
Share on Google Plus

ስለ የተለጠፈበት ቀን

    Blogger Comment
    Facebook Comment