ክርስቶስ ባለ መድኃኒት ሆኖ በኃጢአት ለታመሙ ደቂቀ አዳም ሁሉ ሕይወትን ይሰጥ ዘንድ ወደዚህኛው ዓለም መጣ፡፡ በምድራዊ ሥርዓት እንደምናየው መድኃኒትና ባለ መድኃኒት እንደሚለያዩ አይደለም፡፡ ሁለቱንም እርሱ በመምጣቱ (ሰው በመሆኑ) ፈጸመ እንጂ፡፡ መድኃኒት አድርጎ ሥጋውን ደሙን የሰጠ እርሱ ነው፡፡ በካህናት አድሮ ሰው በንስሐ ሲመለስ መድኃኒት ወደሆነው ወደ ራሱ የሚመራ እርሱ ነው፡፡
ክርስቶስ መድኃኒት መሆኑ በሕማሙ እና በሞቱ ነው፡፡ በእመቤታችን ማኅፀን የተጀመረው የእርሱ መድኃኒትነት እና ፍቅሩ ፍፃሜውን ያገኘው በሕማሙ እና በሞቱ ነው፡፡ መሐሪ ንጉሥ እርሱ መሆኑን ይገልጥ ዘንድ በፈቃዱ ወደ ኢየሩሳሌም መጣ፡፡ ጌታ ወደ ኢየሩሳሌም ከመግባቱ አስቀድሞ ከኢየሩሳሌም ፲፮ ያህል ምዕራፍ በምትርቀው በቤተፋጌ ከደቀመዛሙርቱ ጋር ነበር፡፡
ከደቀ መዛሙርቱም ሁለቱን (ማለትም ጴጥሮስን እና ዮሐንስን) በፊታችሁ ወዳለችው መንደር ሂዱ ወዲያውም ወደ እርሷ ገብታችሁ ከሰው ማንም ገና ያልተቀመጠበትን ውርንጫ ታስሮ ታገኛላችሁ ፈትታችሁ አምጡልኝ፡፡ (ማር ፲፩፡፪) በማለት አዘዛቸው፡፡ ዳግመኛም ሰው ወዳልገባባት የተዘጋች የምሥራቅ ደጅ ወደ ምትባል ወደ ድንግል መጥቶ ዘጠኝ ወር ማኅፀኗን ከተማ አድርጎ እንደኖረ፤ ማኅየዊት ከምትሆን ሕማሙ በኋላም ሰው ባልተቀበረበት መቃብር እንደተቀበረ፤ አሁንም ጌታ ወደ ኢየሩሳሌም ለመግባት ማንም ሰው ያልተቀመጠባቸውን በሌላ መንደር የሚገኙ አህያንና ውርንጫን እንዲያመጡ ደቀመዛሙርቱን አዘዘ፡፡
የፍጥረት ሁሉ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በልደቱ እስትንፋሷን የገበረችለትን አህያ አሁን ደግሞ በፈቃዱ ስለ ሰው ሁሉ ሊሞት ሲል ንጉሥነቱን ሊያስመሰክርባት ወደደ፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እስከ ኢየሩሳሌም ድረስ ካለው ፲፮ ምዕራፍ አሥራ አራቱን በአህያ ላይ ሳይቀመጥ በእግሩ ሄደ፡፡ ከዚያም ሁለቱን ምዕራፍ በአህያ ላይ በመቀመጥ ከተጓዘ በኋላ የኢየሩሳሌምን መቅደስ ሦስት ጊዜ በውርጫዋ ላይ በመሆን ዞረ፡፡ በዚህም ለሰው ሁሉ ያለው ቸርነቱ፣ ሕግ የተሰጣቸው አይሁድ እና ሕግ ያልተሰጣቸው አሕዛብ ላይ እኩል ቀንበርን መጫን እንዳይገባ አጠየቀ፡፡
ወደ ኢየሩሳሌምም ሲሄድ ብዙ ሰዎች ልብሳቸውን በመንገድ ላይ አነጠፉ፣ ሌሎችም ከዛፍ ቅጠሎችን እየቆረጡ ያነጥፉ ነበር፡፡ (ማር. ፲፩፡፰)፡፡ ከዚያም ሰዎች ሆሣዕና በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው (ማር. ፲፩፡፱) በማለት አመሰገኑ፡፡ ይህም ዛሬ ለቤተ ክርስቲያን እኛ ክርስቲያኖች ቡሩክ ስሙ ለእግዚብሔር ወቡሩክ ዘይመጽእ በስመ እግዚአብሔር፤ የእግዚአብሔር ስሙ ምስጉን ነው፡፡ እግዚአብሔር ነኝ ብሎ በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ እርሱ ክርስቶስም ምስጉን ነው በማለት የአብ እና የወልድን መስተካከልን ገልጸን ጌታን እናመሰግናለን፡፡ ጌታን የሚከተሉት ሰዎች ሆሣዕና በአርያም እያሉ ይጮኹ ነበር (ማር.11፲፩፡፲) ይኸውም በልዕልና፣ በሰማይ ያለ መድኃኒት፣ ከሰማይ የመጣ መድኃኒት ማለት ነው፡፡
የእግዚአብሔር ፍቅር እና መሓሪ መሆን በክርስቶስ ሕማም እና ሞት ከመቼውም ጊዜ በላይ ተገልጧል፡፡ ክርስቶስ የተቀበለው ሕማም እና ሞት የእርሱን አምላክነት እና ንጉሥነት አልሸሸገውም፡፡ እንደውም ዙፋኑን መስቀል በማድረግ ንጉሥነቱን በመድኃኒትነቱ ገልጿል እንጂ፡፡ በነቢይ እግዚአብሔርሰ ንጉሥ ውእቱ እምቅድመ ዓለም ወገብረ መድኃኒተ በማዕከለ ምድር፣ እግዚአብሔር ከዓለም አስቀድሞ ንጉሥ ነው፤ በምድር መካከልም መድኃኒትን አደረገ መዝ. ፸፫፤፲፪ ተብሎ የተነገረው እግዚአሔብር ድኅነትን በፈጸመበት ማዕከለ ምድር ሲሰቀል በመድኀኒትነቱ ንጉሥነቱን መግለጡን ያመለክታል፡፡ ዳግመኛም አንሰ ተሰየምኩ ንጉሠ በላዕሌሆሙ በጽዮን በደብረ መቅደሱ፤ እኔ ንጉሥ ሆኜ ተሸምኩ በተቀደሰው ተራራ ላይ (መዝ.፪፡፮) ተብሎ የተነገረው ኦርቶዶክሳውያን አበው እነርሱ (አይሁድ) ሰቅለነው ገድለነው ኋላ ፈርሶ በስብሶ ይቀራል ይሉኛል እንጂ እኔ ደብረ መቅደስ በምትባል በመስቀል ላይ ነግሻለሁ በማለት ይተረጉሙታል፡፡
ጌታ ንግሥናው ክብሩ የተገለጠበት ሆነ እንጂ መታመሙ እና መሞቱ ውርደት ክብሩንም የሚሸሽግ አይደለም፡፡ ሊቁ ዮሐንስ አፈወርቅ ይትባረክ እግዚአብሔር ዘሰመየ ሕማማት ወልዱ ክብረ ወስብሐት፣ የልጁን ሕማማት ክብርና ምስጋና አድርጎ የሰየመ እግዚአብሔር ይመስገን አለ፡፡ እኛን ያከበረበት በመሆኑ ሕማሙ ክብር እንደተባለ እናስተውል፡፡ በመስቀል ላይ ሆኖም በቀኝ የተሠቀለው ወንበዴ አቤቱ በመንግሥትህ በመጣህ ጊዜ አስበኝ (ሉቃ ፳፬ )በማለት ንጉሥነቱ መስክሮለታል፡፡ ለዚህ ነው ጌታ ወደ ኢየሩሳሌም በምስጋና መግባቱ መድኃኒትነቱን እና ንጉሥነቱን ያሳያል ያልነው፡፡ ዳግመኛም ሁሉን የያዘ ጌታ በአህያ ላይ መቀመጡ ትህትናው ያስረዳል፡፡ ሊቁ ቅዱስ ያሬድ ዘይነብር ዲበ ኪሩቤል ዲባ ዕዋለ አድግ ነበረ፡፡ በማለት ሰማያዊ ልዑል አምላክ ትሑት ሆኖ እንደተገለጠ ተናገረ፡፡
ጌታ ከመድኃኒትነቱ የተነሣ ድንቅ የሆኑ እና ተአምራትን ለሰዎች አሳየ (ገለጠ)፡፡ እም ሆሳዕናሁ አርአያ ተአምረ ወመንክረ (ቅዳ. ጎርጎ.ዘኑሲስ) እንዲል፡፡ ይኸውም በአህያ ተጭኖ ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ አእምሮ ጠባይዕ ያልቀናላቸው ሕፃናት ዕውቀት ተገልጾላቸው ሆሳዕና በአርያም እያሉ ጌታ በማመስገናቸው ነው፡፡ ዳግመኛም በከሃሊነቱ መናገር ለማይችሉ ዕውቀት ለሌላቸው ድንጋዮች ዕውቀት ተሰጥቷቸው መናገር ችለው ጌታን አመስግነዋል፡፡ እርሱ የባሕርይ አምላክ መሆኑ በሰውነቱም ቀድሞ በበደል ምክንያት ለሰው ከመገዛት ውጪ የሆኑ ፍጥረታት ዳግመኛ በሥጋዌ ለሰው እንደተገዙ ከዚህ ሁሉ ማስተዋል ይገባል፡፡
ጌታ ከመድኃኒትነቱ የተነሣ ልጅነት እና ተአምራት ማድረግን ገለጸ፡፡ እም ሆሳዕናሁ አርአያ ጸጋ ወኅይለ እንዲል (ቅዳሴ ጎርጎ. ዘኑሲስ)፡፡ የእርሱ ማዳን ከሰው ተወስዶበት የነበረ የጸጋ ልጅነት እንዲመለስለት አድርጋ በልጅነት ላይ ገቢረ ተአምራት (ተአምራትን ማድረግ) ገልጿል፡፡ ይኸውም እርሱ በረድኤት አድሮባቸው ድንቅ ተአምራትን ለሚያደርጉ ቅዱሳን መሠረት ነው፡፡ በተጨማሪም ልጅነትን ካገኙ በኋላ በበደል ሲገኙ ለንስሓ የሚሆን እንባን ሠጠ፡፡ እምሆሳዕናሁ ወሀበ ፈልፈለ አንብዕ ለኅጥአን እንዲል (ቅዳሴ ጎርጎ. ዘኑሲስ) ይኸውም የበደሉትን ያከብራቸው ዘንድ፣ ኀጥአንን ከኃጢአታቸው ያነጻቸው ዘንድ እንዲሁም የሳቱትን በንስሐ ይመልሳቸው ዘንድ ነው፡፡
ዳግመኛም ጌታ መድኀኒት ከመሆኑ የተነሣ ለዕውራን ዳግመኛ ብርሃንን ሰጠ፡፡ ይኸውም ለጊዜው በተፈጥሮ ዐይን ተሰጥቷቸው የታወሩትን ፈውሶ በሥጋ ብርሃን መስጠቱ ሲሆን፤ ፍጻሜው ግን በነፍስ ዕውቀትን ከማጣት የተነሣ ዕውራን የነበሩትን ትምህርትን; ዕውቀትን ገለጸላቸው፡፡ ይኸውም የእርሱ ገንዘቡ ስለሚሆን አንድነት ሦስትነት፣ አምላክነቱን መድኃኒት መሆኑን ገለጠላቸው ማለት ነው፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
Blogger Comment
Facebook Comment