‹‹የምኒልክ›› እየተባሉ የሚደቆሱ እሴቶች

 

ተጻፈ በእውነት ሚድያ

✍️ ምኒልክን በትውልዱ አእምሮ ውስጥ እንደ ጭራቅ የሳለው ፖለቲካ ሊያጠቃቸው የሚፈልጋቸውንም ተቋማት ‹‹የምኒልክ›› የሚል ቅጥያ ይሰጣቸዋል፤ ‹‹የምኒልክ ሃይማኖት›› እየተባለች የጠርዘኛ ፖለቲከኞቹና አክራሪ ሙስሊሞቹ ጥቃት የሚደርስባት ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን የዚህ ሤራ ዋነኛ ሰለባ ናት!

✍️ ‹‹የምኒልክ›› እየተባሉ የሚፈርሱ ተቋማት፣ የሚወገዙ ምልክቶችና የሚገደሉ እንስሳትም አሉ!

✍️ የወቅቱ ፖለቲካ ምኒልክን ከሌሎች ነገሥታት መርጦ ያወገዘበት የራሱ ምክንያት ቢኖረውም ጥፋት ቢኖር እንኳን በቅድመ አያት ወንጀል እንደ ማስተሰርያው ፍየል (Scapegoat) የልጅ ልጅ የሚወቀስበት አካሄድ ካልቆመ መችም ቢሆን ሰላምና መረጋጋት ሊረጋገጥ አይችልም!

‹‹እባብን ግደል፣ ከነበትሩ ገደል›› የሚባል ኢትዮጵያዊ ብሂል አለ፡- ጠላታችን ስለሆነው መርዘኛው እባብ ሲባል ለዘመናት ከአውሬ የተጠበቅንበትን፣ ጤዛ አርግፈንና እንቅፋት አስወግደን መንገዳችንን ያቀናንበትን፣ ሲደክመን የተሞረኮዝነውን፣ በአጠቃላይ ንብረታችንንና ደኅንነታችንን የጠበቅንበትን ያማረ በትራችንን ማስወገድ የግድ የሚባልበት አሳዛኝ ኩነት ነው፡፡ እንዲህ የምንወደውንና የሚጠቅመንን በትራችንን ያስጣለን ለእባቡ ያለን ገደብ የለሽ ጥላቻና ጽዩፍነት ነው፡፡ ገድለነው እንኳን ስለእርሱ የሚያስታውሰን ነገር አብሮን እንዲቆይ አንፈልግም፡፡

‹‹የዐጼ ምኒልክ›› የሚባሉ ነገሮች እጣ ፋንታም ከዚሁ ሁኔታ ጋር የሚመሳሰል እየሆነ ነው፡፡ ንጉሡ በትውልዱ አእምሮ ውስጥ ‹‹መርዘኛ እባብ›› ተደርገው ከመሳላቸው የተነሣ በእርሳቸው ስም የተሰየመ ማንኛውንም ነገር የማውድም፣ ከምድረ ገጽ የማጥፋት እንቅስቃሴ ይደረጋል፡፡ ቀድሞውንም ከንጉሡ ስም ጋር ምንም ንኪክ ያልነበራቸው ሆነው፣ ነገር ግን በተመሳሳይ ሤራ ጥቃት እንዲደርስባቸው የሚፈለጉ ካሉም አስቀድሞ ‹‹የምኒልክ›› የሚል ቅጥያ ስያሜ (Prefix) በመስጠት ላሰቡት ጥቃት ያመቻቹአቸዋል፤ ከዚያ ‹‹ከኑግ ጋር የተገኘህ ሰሊጥ አብረህ ተወቀጥ›› ለማለት፡፡ እስኪ ጥቂቶቹን ብቻ እንመልከት፡-

1.   ‹‹የምኒልክ ሃይማኖት››

ኦርቶዶክስን ‹‹የምኒልክ ሃይማኖት›› እያሉ መጥራት፣ ትውልዱ በዚሁ አግባብ አእምሮው ውስጥ እንዲስላት ማድረግ አስቀድሞ የተጠቀሰው ሤራ ዋነኛ አካል ነው፡፡ ያልነበራትን ስያሜ፣ እርሷም ራሷን የማትጠራበትን ቅጽል እየሰጡ ከ ‹‹እባቡ ንጉሥ›› ጋር ወደ ገደል ሊጥሏት ይቋምጣሉ፡፡

እንደ እውነቱ ከሆነ ይህንን ለማለት የተፈለገው ኢትዮጵያን ከመሩት ነገሥታት መካከል ለኦርቶዶክስ ስለሚቀርቡ ቢሆን ኖሮ ንግሥናን ከቅድስና አስተባብረው በመያዝ በሚታወቁት የዛጉዌ ካህናት ነገሥታት አማካይነት፡- የቅዱስ ላሊበላ ሃይማኖት፣ የቅዱስ ሐርቤ ሃይማኖት፣ የቅዱስ ይምርሃነ ክርስቶስ ሃይማኖት፣ የቅዱስ ነአኩቶ ለአብ ሃይማኖት እየተባለች ትሰየም ነበር እንጂ በምኒልክ አልነበረም፡፡ ክርስትናን ብሔራዊ ሃይማኖት አድርጎ በማወጅ ቢሆን ኖሮ ደግሞ ‹‹የአብርሃ ወአጽብሐ ሃይማኖት›› በተባለች ነበር፡፡

ከእርሳቸው ጋር የጊዜ ቅርበት ከነበራቸው ጋር ቢወዳደሩ እንኳን ወደ ሃይማኖት በማድላት ይታወቁ የነበሩት ዐጼ ዮሐንስ እንጂ ዐጼ ምኒልክ አልነበሩም፡፡ እንዲያውም ‹‹ሃይማኖት የግል ነው፣ አገር የጋራ ነው›› ያሉ የመጀመርያው መሪ በመሆናቸው ቤተ ክርስቲያን አስፈላጊውን ቅድመ ጥንቃቄ ሳታደርግ ብዙ ሚሲዮኖች አጋጣሚውን ተጠቅመው ወደ ኢትዮጵያ ገብተው የቅሰጣ ተግባራቸውን እንዲፈጽሙባት መሠረት ጥለዋል (ለምሳሌ፡- ዐጼ ዮሐንስ ከአገር አባርረውት የነበረው ‹‹አባ ማስያስ›› ተመልሶ የመጣው በርሳቸው ጊዜ ነበር)፡፡ በዚህ አግባብ ከሆነ ደግሞ ‹‹የዐጼ ዮሐንስ ሃይማኖት›› መባል ነበረባት ማለት ነው፡፡

‹‹ሃይማኖቱ ወደ ኦሮሞ ሕዝብ የደረሰው በዐጼ ምኒልክ ዘመን ስለሆነ›› ብሎ የሚያስብም ይኖር ይሆናል፡፡ ይህ የኦሮሞን ታሪክ ራሱ ጠንቅቆ አለማወቅ ካልሆነ በቀር ከዐጼ ምኒልክ የ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ደቡባዊ ማካለል በርካታ ዓመታት በፊት የኦሮሞ ሕዝብ በማዕከላዊና ሰሜናዊ የሀገሪቱ አከባቢዎች እንደነበሩ፣ ለኦርቶዶክስ ሃይማኖትም ባዕዳን እንዳልነበሩ ሀገራዊ የታሪክ ድርሳናት፣ ዜና መዋዕላቱ፣ ገድላቱ ሁሉ ይመሰክራሉ፡፡ ለምሳሌ፡- የ13ኛውን መ/ክ/ዘመን ኩነት የሚያትተው ገድለ ተክለ ሃይማኖት ኦሮሞዎችን ይጠቅሳቸዋል፡፡ ሌላው ቢቀር በዐጼ ልብነ ድንግል ዘመነ መንግሥት (1508 - 1532) ንጉሡ ከግራኝ ጋር ይዋጋ በነበረበት ወቅት ወታደሮቹ ሁሉ ፈርተው ሲፈረጥጡ ዐጼው ‹‹ሌላው ቢፈራ ቱሉ እንዴት ፈራ?›› ብሎ ማድነቁ ተጽፏል፤ ይህ ደግሞ የቱሉን ልዩ ጀግንነት ከመመስከርም አልፎ በዚያን ወቅት ኦሮሞ የሆኑ ወታደሮች (እነ ቱሉ) ቀድሞውን በሰሜንና ማዕከላዊው የኢትዮጵያ ክፍል (ሃይማኖትም ጭምር እየተጋሩ) እንደቆዩ ያሳየናል (ተክለ ፃድቅ መኩሪያ፤ የኢትዮጵያ ታሪክ፤ ከዐጼ ልብነ ድንግል እስከ ዐጼ ቴዎድሮስ፤ 1961፡94)፡፡ ይህ ብቻም ሣይሆን ቅድመ ዐጼ ምኒልክ በኦሮሞዎች ምድር ላይ የተተከሉ ጥንታውያን አብያተ ክርስቲያናትና ገዳማት እንዲሁም በሕዝቡ ሲፈጸሙ የነበሩ የአምልኮ ሥነ ሥርዓቶች በርካቶች ለመሆናቸው ከበቂ በላይ ምስክርነቶች አሉ (ወደፊት በቦታው ሰፋ አድርገን የምንዘረዝራቸው ቢሆንም ቢያንስ ቅድመ ልደተ ክርስቶስ 800 ዓመታት ጀምሮ መሥዋዕተ ኦሪት ሲሠዋባት የነበረችው ብርብር ማርያም ገዳም፤ በ4ኛው መ/ክ/ዘመን ውስጥ እንደተመሠረቱ የሚታመኑቱ እነ የረር በዓታ ለማርያም ገዳም እና የመናገሻ አምባ ማርያም/ የጋራው መድኃኔዓለም አንድነት ገዳም፤ የ12ኛው መ/ክ/ዘመን አከባቢው ዝቋላ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ፣ የ13ኛው መ/ክ/ዘመን የአዳዲዋ ማርያም እና የአሰቦት ደብረ ወገግ ቅድስት ሥላሴ ወአቡነ ሳሙኤል ገዳም፤ የ15ኛው መ/ክ/ዘመን ወንጪ ቅዱስ ቂርቆስ ገዳም፣ መጥቀስ ይቻላል)፡፡ እናም ኦርቶዶክስን ‹‹የምኒልክ ሃይማኖት›› ለማለት የሚፈልጉት ‹‹ዐጼ ምኒልክ ኦርቶዶክስን ወደ ኦሮምያ ስላመጡ›› በሚል ድምዳሜ ከሆነ ከዚህ በላይ ተረትም፣ ድንቁርናም ሊኖር እንደማይቻል መታወቅ አለበት፡፡

ዐጼ ምኒልክ ኦርቶዶክስን ‹‹ስለጠቀሟት ነው›› ብሎ የሚያስብም ካለ ተሳስቷል፤ ምንም አልጠቀሟትም ባይባልም ሁሉም ነገሥታት ሲጠቅሟት እግረ መንገዳቸውንም ሲጠቀሙባት እንደነበር መረሳት ግን የለባትም፡፡ ነገሥታቱ ወደ ሥልጣን ለመምጣት እርስ በርሳቸው ያደርጓቸው በነበሩ ሽኩቻዎችና ግጭቶች ሁሉ ተጠቂዋ እርሷ ነበረች፡፡ ይልቁንም ኦርቶዶክስ ሃይማኖት ብቻ ሳትሆን ሀገር የመምራትም ኃላፊነት ጭምር ስለነበራት ለሀገር የመጣው መከራ ሁሉ ግንባር ቀደም ገፈት ቀማሽ ነበረች፡፡ የዐጼ ምኒልክን ዘመን ብቻ እንኳን ብንጠቅስ፡- በዓድዋ ጦርነት ምክንያት ከ2,000 በላይ አብያተ ክርስቲያናትና ገዳማት ከነመነኮሳቱና ባህታውያኑ ወድመዋል፤ እንስሳትም ሳይቀሩ በአውሮፕላን በተረጨ መርዝ አልቀዋል፡፡ በሁለተኛው የጣሊያን ወረራ ወቅትም ሀገርን ወክላ መስዋዕትነት የከፈለች፣ ሁለቱ ብርቅዬ ሊቃነ ጳጳሳቷ (አቡነ ጴጥሮስና አቡነ ሚካኤል) በፋሺሽቱ የተረሸኑባት ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ በዚህ ታሪኳም ‹‹የኢትዮጵያ ሃይማኖት›› እንጂ ‹‹የምኒልክ›› መባል አልነበረባትም!

እናም ‹‹የምኒልክ ሃይማኖት›› ለማለት የተፈለገው በአማራው ገዢ መደብነት ከተፈረጀውና እንደ ጭራቅ ከተሳለው ምኒልክ ጋር አብራ እንድትከስም፣ በአንጻሩ ደግሞ ሃይማኖት የለሽ ኮሚኒስታዊ ትውልድ እንዲያብብ ነበር፡፡ የዚህ ጽርፈታዊ አገላለጽ ፈጣሪ ሕወሓት ፖለቲካም ‹‹ጸረ ጽዮናዊ›› እንደነበር፣ ዋና መርኁም ‹‹ሃይማኖት የትውልድ አደንዛዥ ዕጽ፣ የገዢዎችም ማስገበርያ መሣርያ ነው›› የሚለው ሌኒናዊ አስተሳሰብ ነበር (የሺሐሳብ አበራ፤ ሰርሳሪ ተረከዞች፤ 2012፡ 58)፡፡ ወርኃ የካቲት 1968 ዓ.ም ተቀርጾ፣ በእጅ ጽሑፍ ቅጅ የሚገኘው የድርጅቱ ፖለቲካዊ መግለጫ (ማኒፌስቶ) ገጽ 38 ላይም ትብብሩ ከጸረ-ጽዮናውያን ጋር መሆኑ በግልጽ ተቀምጧል፡፡ የድርጅቱ ቀደምት አመራር ዶ/ር በርኄ ወ/አረጋይ የዓይን ምስክርነትና ጥናታዊ ጽሑፍም ይኸንኑ ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ነው፡፡ መሪዎቹም በሚዲያ ላይ ጭምር፡- ‹‹ኦርቶዶክስን አከርካሪዋን ሰብረናል›› ብለው እስከመናገር ተዳፍረዋል፡፡ በመሠረቱ ግን ሕዝባዊ መሠረት አለኝ ብሎ የሚያስብ ፓርቲ ከ90 በመቶ በላይ ኦርቶዶክሳዊ የሆነን የትግራይ ሕዝብ እወክላለሁ እያለ ‹‹ጸረ-ኦርቶዶክስ›› ሆኖ፣ በአክሱም ጽዮን ምድርም ‹‹ጸረ-ጽዮናዊ›› ሆኖ ለመምራት ማሰቡ እንቆቅልሽ ነው! 

2.   ‹‹የምኒልክ›› የሚባሉ ተቋማትና ምልክቶች

አብዛኞቹ ጠርዘኛ የኦሮሞ ፖለቲከኞች ከዐጼ ምኒልክ በፊት ያሉትን ነገሥታት ‹‹የኢትዮጵያ መሪዎች›› አይሏቸውም፤ ሌሎች የሀገሪቱን ክፍሎች ወደ አንድነት ጠቅልለው ሳያጠናቅቁ በማለፋቸው ምክንያት ‹‹የአቢሲኒያ ነገሥታት›› ይሏቸዋል (የሰሜኑ ክፍል ብቻ ገዢዎች እንደማለት)፡፡ በዚህ አስተሳሰባቸው ብንስማማ እንኳን ዐጼ ምኒልክ የዛሬዪቱ ኢትዮጵያ ፈጣሪና የመጀመርያ ንጉሥ በመሆናቸው ብቻ ልዩ ክብር ሊሰጣቸው በተገባ ነበር፡፡ የዓለምን ታሪክ እንደ ተሞክሮ ስንመለከት የዛሬዋ ሰሜን አሜሪካ በጀኔራል George Washington በተመራ የአመጽ እንቅስቃሴ ለመጀመርያ ግዜ ከአውሮፓውያን ቅኝ ግዛት በመላቀቅ ራሷን የቻለች ነጻ ሀገር ለመሆን ስትበቃ አሜሪካውያኑ የጀግናውን (የመጀመርያው ፕሬዝዳንትም ነው) ውለታ አልረሱትም ነበር፤ ዛሬ የሀገሪቱ ርእሰ ከተማ የሆነችውን ‹‹ዋሽንግተን›› ብለው በስሙ ጠሩ እንጂ፡፡ ዛሬ በኢትዮጵያ ግን ‹‹ምኒልክ›› የሚባል ከተማ የለንም፤ አደባባይ፣ ሆስፖታል፣ ትምህርት ቤትና መሰል ተቋማት እንኳን በስሙ በመሰየማቸው ምክንያት ዓይናቸው ደም ለብሶ በቁጭት የሚኖሩ ዜጎች ሞልተውናል፡፡

የምኒልክ ጥላቻ በስሙ የተሰየሙ እነዚህን ተቋማትና ምልክቶችን የጎሪጥ እንዲታዩ እያደረገ፣ ብሎም እያስጠቃ ይገኛል፡፡ ፖለቲካዊ ሽኩቻዎችና ሕዝባዊ አለመረጋጋቶች በተፈጠሩ ቁጥር ‹‹የምኒልክ›› የሚል ቅጽል ያላቸው ተቋማት ትምህርት ቤት፣ ሆስፒታል፣ ወዘተ. የጥቃት ዒላማ መሆናቸው ያሳዝናል፡፡ በቅርቡ እንኳን ‹‹የዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል›› በልዩ ሁኔታ የጥቃት ሙከራ ተደርጎበት እንደነበር ተሰምቷል፡፡

በሀገራችን ውስጥ በቅርቡ የተከሰተው የአርቲስት ሐጫሉ ግድያ እንኳን ከምኒልክ ትርክት ጋር የተገናኘ መሆኑን ሁላችንም የታዘብነው ነው፡፡ በእርሱ ሞት ማግሥትም ‹‹የምኒልክ ሐውልት መፍረስ አለበት፤ የሐጫሉ አስከሬን በቦታው ማረፍና መታሰቢያ ሐውልትም ሊተከልበት ይገባል የሚሉ እንቅስቃሴዎች ተጀምረው ነበር፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ የምንታወቅባቸው፣ የጋራ ሊያደርጉን ይገባቸው የነበሩ ሀገራዊ ምልክቶች እንኳን ሳይቀሩ ‹‹የምኒልክ›› እየተባሉ መነቀፋቸው ሌላኛው አሳዛኝ ክስተት ነው፡፡ ለምሳሌ፡- የሀገሪቱ አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ሰንደቅ ዓላማ ‹‹የምኒልክ ባንዲራ›› ተብሎ በየቦታው ከመወገዙም ባሻገር ፖለቲካው እስከ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ቅጽር ግቢ ዘልቆ የገዛ ልጆቿ እንኳን በእጅጉ የተለያዩበት፣ ‹‹ባንዲራው ካልተነሳ ቤተ ክርስቲያን አንመጣም›› እስከማለት የተደረሰበት ነበር፡፡ 

ብሔራዊ ቤተ መንግሥታችንም ቢሆን የዘመኑ ብሔር-ተኮር ፖለቲካ ሤራ ዒላማ ከመሆን አልዳነም፡፡ የዶ/ር ዐቢይ መንግሥት በጠርዘኛ የዘውግ ፖለቲከኞች ከሚወቀስባቸው ነጥቦች መካከልም ‹‹የምኒልክ ቤተ መንግሥትን ማደሱ›› የሚለው ዋነኛው ነው፤ ቤተ መንግሥቱ ላይ የሚታዩት አንዳንድ ምኒልካዊ አሻራዎች ፈጽመው እንዲፋቁ በዘውገኞቹ ይፈለግ ነበርና፡፡

3.   ‹‹የምኒልክ ድኩላ››፡- የማስተሰርያው ፍየል

በታሪክ ውስጥ ተፈጽመዋል ስለሚባሉ ‹‹የግፍ ጭፍጨፋዎች›› ትክክለኛ ምንጭ ይኖራል፣ ነገሩም እውነታነት ይኖረዋል፣ የጥፋቶቹ ፈጻሚም ዐጼ ምኒልክ ናቸው ብለን ደግሞ እናስብ፡፡ እናስ? መሰል ጥፋትም ሆነ ልማት በብሔር ተደራጅቶ የሚፈጸም ሣይሆን በየትኛውም ሕዝብ ውስጥ ሊኖሩ በሚችሉ ሕገ ወጦችና ወንጀለኛ ግለሰቦች የሚከወን ድርጊት መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ሕገ ወጥነት ደግሞ ብሔርም፣ ሃይማኖትም የለውም! ተጠያቂነቱም በወቅቱ ጥፋቱን የፈጸሙት ግለሰቦች ላይ እንጂ ስለጉዳዩ አይቶም ሆኖ ሰምቶ የማያውቀውን ትውልድ በአያቶቹ ፋንታ ‹‹የጦስ ዶሮ›› እና ‹‹የመሥዋዕት በግ›› (Scapegoat) የማድረግ አካሄድ ፈጽሞ ትክክል አይሆንም! በአያትና ቅድመ አያት ወንጀሎች የልጅ ልጆች የሚወነጀሉበት፣ አላስፈላጊ ዋጋ የሚከፍሉበት አካሄድም እስከ መች እንደሚቀጥል ግራ ያጋባል፡፡

የቅድመ አያትን በደል በልጅ ልጅ የመበቀል አካሄዱ ከሰዎችም አልፎ ወደ እንስሳት እንኳን እየተዛመተ መሆኑ በሀገራችን ምድር እየተሰማ ነው፡፡ ለምሳሌ፡- በባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ውስጥ ‹‹የምኒልክ ድኩላ›› ተብሎ የሚጠራ እንስሳ እንዳለ ይነገራል፡፡ በቅርቡ ታዲያ ጸረ-ምኒልክ የሆኑ ጥቂት ወታደሮች ወደ ፓርኩ ቅጽር ጥሰው ገብተው እነዚህን እንስሳት እያደኑ በመግደል ላይ እንደነበሩ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ጭምር ሲራገብ ነበር፤ ስለ ሁኔታው ትክክለኛነት ግን ከሚመለከታቸው አካላት ለመስማት አልተቻለም፡፡

ጉዳዩ ምንም ይሁን ምን ክስተቱ (ቢያንስ መነጋገርያ ነጥቡ) አንድ የሚጠቁመን ነገር ግን አለ፡- እንስሳቱ ተለይተው እንዲገደሉ ምክንያት የሆነው ‹‹የምኒልክ›› የሚለው የስማቸው ቅጽል መሆኑ ነው፡፡ ወታደሮቹ በአእምሮአቸው ከተሳለው የጭራቅ ፖለቲካ የተነሣ በእንስሳው ውስጥ ምኒልክን ያገኙት ስለመሰላቸው ሊሆን ይችላል፡፡ እጅግ በጣም የሚያሳዝነውና ልንማርበት የሚገባው ሌላው ነጥብ ግን ድኩላው በዚህ ስም መጠራቱን፣ ለምን እንደተገደለም ጭምር የማያውቅ ምስኪን መሆኑን ነው፡፡ በእውነትም ድኩላው በርካታ የዋሐን ኢትዮጵያውያንን ይመስላል፡- ብዙዎች በማያውቁት የሐሰት ትርክት፣ አለመግባባቱ በምን ምክንያት እንደተቀሰቀሰ እንኳን በማያውቁት አመጽ ንጹህ ደማቸው ፈሷልና፡፡ የምኒልክ ድኩላም፣ በማያውቁት ጉዳይና ሌሎች በሰሩት በደል ተላልፈው ለሞት የተሰጡት (ደማቸው የፈሰሰው) ዜጎቻችን ሁሉ እንደ ‹‹የማስተሰርያው ፍየል›› (Scapegoat) ናቸውና ከማሳዘንም አልፈው አንጀት ይበላሉ!

Share on Google Plus

ስለ የተለጠፈበት ቀን

    Blogger Comment
    Facebook Comment