በእኛ ዘመን የኢትዮጵያ ሰማይ ስር እየተከሰተ ያለው እውነታ፣ ከታሪካዊ ክብራችንና ከጥንታዊ ጥበባችን እየራቅን መሄዳችንን ብቻ ሳይሆን፣ ወደማያልቅ የመንፈስ ድቀት ውስጥ እየሰመጥን መሆናችንን በግልጽ ያሳያል። ሕዝባችን ዛሬ የቆመበት መሠረት መናዱን፣ ከብርሃን ወደ ድቅድቅ ጨለማ፣ ከሕይወት ወደ ሞት፣ እና ከሕብረት ወደ ጠባብ ግለሰባዊነት የሚደረግ የስልጣኔ መቃብር ጉዞ ላይ መሆናችንን ልብ ማለት ይገባል።
በቁስ አካል እየበለፀግን ስንሄድ፣ በመንፈስ ግን እየሞትን ነው። መንፈሳችን የቁሳቁስና የካፒታል እሳቤ ስግብግብነት ውስጥ ሰምጦ፣ ጥልቅ የሞራል ውድቀት ውስጥ ገብቷል። በዚህ አሳዛኝ እውነታ ውስጥ ሆኖ የሀገራችንን የወደፊት እጣ ፈንታ ለመለወጥ የሚደረጉ ጥረቶች ሲታዩ፣ አዳዲስ ሐሳቦች መፍለቃቸው አይቀሬ ነው።
ከእነዚህም መካከል በጠቅላይ ሚኒስትሩ የረቀቀውና በሰፊው የሚነገረው የ«መደመር» ፍልስፍና ከፍተኛ ትኩረትን ይስባል። መደመር ሲባል፣ በሳይንሳዊው የSynergy መርህ ላይ ተመስርቶ፣ ሁለት ወይም ከዚያ በላይ የሆኑ አካላት ለየብቻቸው ከሚያመጡት ድምር ውጤት ይልቅ ተነጋግረው አንድ ሲሆኑ የሚፈጥሩት ኃይል እጅግ የላቀና አሻጋሪ እንደሚሆን ማሳየት ነው።
ይህ እሳቤ የታሪክ መገፋፋቶችን፣ የዘመናት ቁስሎችንና አለመግባባቶችን በይቅርታ ለማስታረቅ፣ ልዩነቶችን እንደ ማህበራዊ ጌጥ ወስዶ ሕብረ-ብሄራዊነትን ለሳይንስ፣ ለቴክኖሎጂ እና ለኢኮኖሚያዊ ግንባታ ማዋልን ዓላማ ያደርጋል። በንድፈ-ሐሳብ ሲመዘን፣ ይህ ሐሳብ ሀገሪቱን ከደም ምህዳር አውጥቶ ወደ ሰላም እና ልማት ማማ ለማድረስ የሚያስችል ግሩም መሣሪያ ነው።
ነገር ግን፣ አንድ ወሳኝና መሠረታዊ እውነት ሊሰምርበት ይገባል፡- በመደመር ፍልስፍና ላይ ልትሰራ የታሰበችው ኢትዮጵያ ያለ ንቃተ ሕሊና፣ ያለ መንፈሳዊ እና ሞራላዊ ልዕልና ፈጽሞ ልትሳካና ልትቆም አይቻላትም። ንቃተ-ሕሊናው ባልዳበረ፣ በመንፈሳዊ ብርሃን ባልታነፀ፣ እና በሞራላዊ ልዕልና ላይ ባልቆመ ማህበረሰብ ውስጥ መደመር ሲሞከር፣ ሂደቱ የዕድገት መንገድ ሳይሆን የጥፋትና የሞት አውራ መንገድ ይሆናል።
ሐሳቡ በወረቀት ላይ ውብና ማራኪ ቢሆንም፣ የሚተገበረው ሕዝብ አእምሮ በጠባብነት፣ በስግብግብነት እና በጨለማ የተሞላ ከሆነ፣ መደመር መርዘኛ ንጥረ ነገሮችን ደምሮ ይበልጥ ገዳይ መርዝ እንደማዘጋጀት ይቆጠራል። ውስጣችን ያልሴላ ዕይታና የሞራል ልዕልና ከሌለ፣ የምንፈጥረው ማንኛውም አንድነት ወይም መደመር መልካም እውነታዎችን ወደ መጥፎ ገሃነም የመለወጥ አቅም አለው።
የሞራልና የመንፈስ ልዕልና ሲጠፋ፣ በህብረተሰቡ ውስጥ የነበሩ እሴቶች ሁሉ ይረክሳሉ። ዛሬ ሴቶች ሴትነታቸውና ማህበራዊ ክብራቸው ለገንዘብ ረክሷል፣ ተዋርዷል፤ ወንዶችም ወንድነታቸው ከፍትህና ከከለላ ወጥቶ ዓለምን በደም የሚያራጭ የኃይል ማሳያ ሆኗል። ሰው በአካል አለ፣ ነገር ግን እውነተኛው የሰው ልጅ ሞቷል፤ እውነተኛው ሕብረትም ተሰባብሯል።
ስልጣኔ የሚሞተው ሰው ሲሞት እና ግለሰባዊነት ሲገለጥ ነው። ዛሬ የምንከተለውና የምንመኘው የምዕራባዊው ስልጣኔ (Western Civilization) መንገድ፣ ከጊዜ በኋላ በውስጡ የያዘውን የግለሰባዊነት እና የካፒታል ማርከት መርዝ አፍልቆ ራሱን እየበላ የሚወድቅ ስልጣኔ ነው። በታሪክ ውስጥ የነበሩት ታላላቅ ስልጣኔዎች ሁሉ የወደቁት በዚሁ የሞራል ድቀትና በቁስ አምልኮ ምክንያት ነው።
ዲሞክራሲ ከዓለም ላይ እየጠፋ መምጣቱ፣ ሀያላን ሀገሮች ሳይቀሩ ወደ አምባገነናዊና የግራ ዘመም ፖለቲካ ማዘንበላቸው፣ የዚህ የንቃተ-ሕሊና ውድቀት ሕያው ማሳያ ነው።
ሞታችንን የሚደመድምልን ሐሳዌ መሲህም በዚህ የተበላሸ የሞራል ምህዳር ውስጥ ተቃርቧል። ስለዚህ፣ በኢትዮጵያ ምድር መደመርን እውን ማድረግ ከፈለግን፣ ከግንባታዎችና ከቁሳዊ ዕድገት አስቀድሞ የሰውን ልጅ ንቃተ-ሕሊና መገንባት አለብን። መንፈሳዊና ሞራላዊ ልዕልናን መሰረት ያላደረገ መደመር፣ የጥፋታችን አክሊል ሊሆን ይችላልና፣ ራሳችንን ከመሠረቱ በመመርመር ንቃተ-ሕሊናችንን ከፍ ማድረግ የግድ ይላል።
Blogger Comment
Facebook Comment