✍ ይታገሡ በቀለ | ኢትዮጵያ አውታር | ሰላቢ እጆች
የኢትዮጵያ የችግር ምንጭ ነው ፌደራሊዝም
በዓለም ላይ ከ190 በላይ አገሮች ሲኖሩ 30 አካባቢ የሚሆኑት ብቻ ናቸው የተለያየ አይነት የፌደራል ሥርዓት የሚጠቀሙት። የፌደራል ሥርዓት ያስፈለገበት ዐብይ ጉዳይ የዲሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋትና ዜጎች እንደ ፈለጋቸው ነጻነታቸውን እንዲጠቀሙና የኢኮኖሚ እድገትን ለማምጣት ነው። ለዚህም ጥሩ ምሳሌ የምትሆነን የፌደራሊዝም መሥራችና አበልጻጊ የሆነችው አሜሪካ ነች።
የኢትዮጵያ ፌደራሊዝም በቀጥታ ኢትዮጵያን ሊበቀል የተናደደ ታሪካዊ ጠላት ያዋቀረው ይመስላል። ኢትዮጵያ የወደ ፊቱን ትውልድ የሚመለከት የተማረ ሰውና መካሪ ሽማግሌ የሌላት ይመስል እንዴት በዓለም ላይ ታይቶ የማይታወቅ የሚበታትን ፌደራሊዝም ሊመሰርቱ ቻሉ?
ቢያንስ ታሪክ መመርመርና ያለውን የሚታይ እውነት ማየት ቢሳናቸው እንዴት የደቡብ አፍሪካንና የናይጀሪያን የፌደራሊዝም መመዘኛ አይተው ቢያንስ እሩቡን ማካተት እንዃን ተሳናቸው? አስገራሚ ነው።
ለምሳሌ ያህል የደቡብ አፍሪካውያን ፌደራሊዝማቸውን ካዋቀሩበት ዋና ዋና መስፈርቶች መካከል :-
የአገልግሎት አሰጣጥ አመችነት
የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ አመችነትና እድገት
ለሃገሪቱ ትላልቅ ተቋማት ያለው ቅርበት ( ማለት ለወለጋ ከአዲስአበባ ይልቅ ጎጃም ቅርብ ሲሆን ለምንጃር ከባሕርዳር ይልቅ አዲስአበባ ይቀርባል)
የህዝብ አሰፋፈርና የወደፊት እንቅስቃሴን በመተንበይ
ታሪካዊ ድንበርተኝነት (የኛ የጥንቱን በማፍረስ ይታወቃል)
የሕዝብ ምቾትና እንደአስፈላጊነቱ ባሕልንና ቋንቋን ሲጠቀም....
የናይጀሪያው ፌደራሊዝም ደግሞ በዋናነት የመልከአምድር አቀማመጥን፣ የሕዝብ ቁጥርን፣ የመሬት ሁኔታ፣ የነዋሪዎች የጥንትና የአሁን አሰፋፈር፣ የዘር ምስስሎሽና ባሕልንና እና ሌሎችን እንደ መስፈርት ተጠቅመው የፌደራል ሥርዓት መስርተዋል።
ልብ_በሉ እነዚህ ሁለት አፍሪካዊ አገሮች በቅኝ ገዥዎች ሲሰቃዩና በተለያዬ መንገድ በቅኝ ገዥዎች አማካኝነት የተከፋፈለ ሕዝብን ወደ አንድ ለማምጣት ሲጥሩ በአንጻሩ እኛ በቅኝ ያልተገዛነው በጋራ አባቶቻችን ደምና አጥንት አንድ የሆነችውን አገር የሚያፈርስ
ፌደራሊዝም ሰሩ።
የኢትዮጵያ ፌደራሊዝም በዋናነት ቋንቋ ላይ ብቻ ያተኮረና የመጀመሪያና የመጨረሻ መመዘኛው ቋንቋ የሆነ ብሔራዊ ስሜቶችን በመናድ ላይ የተጠመደ በዓለም ላይ የሌለ ፌደራሊዝም ነው።
የኢትዮጵያ ፌደራሊዝም
ከዲሞክራሲ ይልቅ ጭቆናን፣ ከሰላም ይልቅ ጦርነትን፣ ከነጻነት ይልቅ ሰቀቀንን፣ ከእድገት ይልቅ ድህነትን፣ ከአንድነት ይልቅ ልዩነትን፣ ከመዋድድ ይልቅ መቃቃርን በወረቀት ብቻ ሳይሆን በገቢር የፈጸመና እየፈጸመ ያለ አሳዛኝ ሥርዓት ነው።
እንዴት አንድ የመንግስት ሥርዓት በራሱ ዜጎች ላይ የልዩነት ሰነድ ያዘጋጃል? ሲሆን ገና ወደ ፊት ለሚፈጠሩ ልዩነቶች መፍትሄ እያበጀ መሄድ ሲገባው እንዴት በዓለም ላይ የሌለና የሚያዋርድ የቋንቋ ጎጠኝነት ይፈጥራል? ይኸ መረገም ነው
በዚሁ የሚቀጥል ከሆነ የዳሞትና የኢናርያ ሕዝቦች ፓርቲም መመስረቱ አይቀርም። ብዙ እና ብዙ ሊታዩ የሚገባቸው ጉዳዮች እየተድበሰበሱ በመሄድ ችግር እየፈጠሩ ስለሆነ ቋንቋ መናገር የዘር ማንነትን ይወስናል እየተባለ የሚለፈፈው የአላዋቂዎች ጩኸት በጊዜ ምሱን አግኝቶ ለሁላችንም የምትሆን አገር መገንባት ይሻለናል።
Blogger Comment
Facebook Comment