ሌላኛው ሐቅ መመርመሪያ የንጉሱና የስደተኞቹ ውይይት


የኢብን-ኢስሐቅ ሲራ ክርስቲያኑን ኢትዮጵያዊ ንጉሥ ሰልሟል በማለት የዘገበውን የሀሠት ዘገባ እውነት ለማስመሰል ተፈፅሟል ያላቸውን ብዙ ዝርዝር ነገሮች አጭቆ ይዟል፡፡ ነገር ግን ባስረዘመው ነገር ልክ ሀሠተኝነቱ ይገለጣል እንጂ የሚያተርፈው አንዳች ነገር የለም፡፡ ከእነዚህ ዝርዝር ጉዳዮች አንዱ ስደተኞቹ ሙስሊሞች ከክርስቲያኑ ንጉሥ ጋር ያደረጉት ቃለ ምልልስ ነው፡፡ ሙስሊም ጸሐፊያን ይህንንና ተያያዡን ታሪክ ከዋናው ሲራ በመቅዳት በበርካታ መጻሕፍት አሠራጭተውታል። በሀገራችንም ይህንን ርዕስ የሚመለከቱ መጻሕፍት አሉ፡፡ ከጥቂቶቹ  ላይ የታሪኩን ሂደት በመጥቀስ እንመልከት፡፡

የኢብንኢስሐቅና ሌሎች የእስልምና የታሪክ ድርሳናት እንደዘገቡት የሙሐመድ ተከታዮች በቅድሚያ በ615 ዓ.ም 11 ወንዶችና 4 ሴቶች በድምሩ 15 ስደተኞች ወደ አክሱም መጥተዋል፡፡ ሆኖም ከሁለት ወራት በኋላ የመካ ሙሽሪኮች እስልምናን ተቀበሉ የሚል የተሳሳተ ወሬ ደርሷቸው ወደ መካ ተመለሱ፡፡ በሥፍራው ሲደርሱ ግን የሰሙት ወሬ ሀሠት ሆኖ ስላገኙት በድጋሚ ለመሰደድ ተዳረጉ፡፡ ለሁለተኛ ጊዜ በ616 ዓ.ም አካባቢ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው የመጡት ስደተኞች በቁጥር በርከት ብለው ነበር፡፡ 83 ወንዶችና 18 ሴቶችን ያካተተው ቡድን አክሱም ደረሰ፡፡ ሆኖም የመካ ቁረይሾች ስደተኞቹን የሚመልሱ አብደላህ ቢን አቢ ረቢዐህ እና አምር ኢብኑል አስ የተሠኙ ሁለት መልዕክተኞች ላኩ፡፡ 

ልኡካኑ የመጡበትን ጉዳይ ለንጉሡ ካስረዱ በኋላ ንጉሡ ሁለቱንም ወገን ፊት ለፊት በማገናኘት ጉዳያቸውን አድምጧል፡፡ የቁረይሽ ተወካዮች በስደተኞቹ ላይ ከአባቶቻቸው አምልኮ አፈንግጠው መምጣታቸውንና ወደ ንጉሡ ሃይማኖትም ያልገቡ በመሆናቸው ወደ ሀገራቸው እንዲመልሷቸው እንዲፈቅዱላቸው ጠይቀዋል፡፡ ንጉሡ ግን ፍትሐዊ ዳኛ እንደሚያደርገው የተከሳሾቹን መልስ ሳይሰማ አንዳች ውሳኔ ላይ እንደማይደርስ ገልጦ ስደተኞቹ በቀረበባቸው ክስ ላይ ምላሽ እንዲሰጡ አድርጓል፡፡ የስደተኞቹ ተወካይና የመሐመድ አጎት ልጅ የነበረው ጃዕፈር ኢብኑ አቡ-ጧሊብ የሚከተለውን ምላሽ ሠጥቷል፦

“ንጉሥ ሆይ! እኛ መሃይማን ሕዝቦች ነበርን፤ ጣኦታትን እናመልክ፣ በክት እንበላ፣ እናመነዝር፣ ዝምድና እንቆርጥና የጉርብትናን መብት እናጓድል ነበር፡፡ ከእኛ ኃያሉ ደካማውን ይበላል (ይበዘብዛል)፡፡ በዚህ ሁኔታ ላይ እያለን አላህ ከወገኖቻችን መካከል የምናውቀው መልእክተኛ ላከልን፡፡… ወደ አላህ ጠራን፣ እርሱን በብቸኝነት እንድናመልከው፣ አባቶቻችን ያመልኳቸው የነበሩ ከእንጨትና ከድንጋይ የተጠረቡ (ጣኦታት) አማልክትን እንድንተው፣ እውነት እንድንናገር፣ እምነትን እንድንወጣ፣ ዝምድናን እንድንቀጥል፣ ጥሩ ጎረቤቶች እንድንሆን፣ ከእርም ነገሮች እንድንታቀብና የሰዎችን ደም እንዳናፈስ አዘዘን፡፡ … ሙሐመድ አላህን በብቸኝነት እንድናመልከው፣ በርሱ ላይ ምንንም እንዳናጋራ አዘዘን፣ ሶላት እንድንሰግድ፣ ዘካ (ምፅዋት) እንድንሰጥና ጾም እንድንጾም አዘዘን… እኛም እውነት ብለን ተቀበልነው፡፡ በዚህም የተነሳ ወገኖቻችን ጠላት አድርገው ያዙን፡፡ መከራ ሲያበዙብንና ከእምነታችን ሊቀለብሱን ሲጫኑን ወደ እርስዎ ሀገር መጣን” አለ፡፡

ንጉሡም በጽሞና ካዳመጠ በኋላ ይህን ጥያቄ ጠየቀ፤ “ነቢያችሁ ይዞት ከመጣው መልዕክት ውስጥ የምታቀርብልን ይኖርሃል?” አለ፡፡ 

“አዎን ንጉሥ ሆይ!” አለ ጃዕፈር፡፡ 

"አንብብልኛ!" አለ ነጃሺ፡፡ 

ጃዕፈርም ከሱረቱል መርየም የመጀመሪያዎቹን አንቀፅ አነበበለት፡፡ ወላሂ ንጉሡ አለቀሰ፡፡ እንባው ጺሙን አራሰው፡፡ ቀሳውስቱም ተላቀሱ፡፡ እንባቸው መጻሕፍታቸውን አራሰው፡፡…” 

የመጀመሪያው ቀን ውይይት በዚህ ሲጠናቀቅ የቁረይሾቹ ተወካዮች ተልዕኮአቸው ባለመሳካቱ ተበሳጩ፡፡ ስለሆነም ንጉሡ ዘንድ ቀርበው ስደተኞቹ ኢየሱስን (ዒሣን) ባሪያ ነው እንደሚሉና ወደ ንጉሡ ዘንድ ሲገቡ እንኳ በማጎብደድ (በመስገድ) ሰላምታ ያላቀረቡ ትዕቢተኞች መሆናቸውን ገለፁ፡፡ ንጉሡም ስደተኞቹን ልኮ ካስጠራቸው በኋላ ስለዚሁ ጉዳይ ጠየቃቸው፡፡ ይህንንም አስመልክቶ እስላማዊ መጻሕፍት እንዲህ ይላሉ፦

“ከዚያም ወደ ንጉሡ ስንገባ ስለ ሰላምታው ሲጠይቀን ለነቢዩም ቢሆን እንደማንሰግድና ስግደት የሚገባው አንድ አላህ ብቻ ነው አልነው። ቀጥሎም ስለ ዒሳ (ኢየሱስ ክርስቶስ) ምን ትላላችሁ!? ብሎ ነጃሺ ጠየቀን፡፡ ጀዕፈር ኢብኑ አቡ ጣሊብ እንዲህ አለ፡- ‘ነቢያችን ያስተማረንን እንላለን፡፡ ዒሳ (ኢየሱስ) የአላህ ባሪያ፣ መልእክተኛና (እርሱ ከፈጠራቸው መንፈሶች መካከል አንዱ) መንፈሱ (ሩሁ) ነው። ወደ ድንግል መርየም የጣለው የይሁን ቃሉም ነው፡፡’ 

ንጉሥ ነጃሺ እጁን ወደ መሬት ሰደደና አንዲት ዘንግ አነሳ፡፡ ከዚያም ኢየሱስ ክርስቶስ (ዒሳ) አንተ ካልከው የዚህን ዘንግ ያህል እንኳን አያልፍም አለ፡፡ ይህን ሲናገር ቀሳውስቱ አጉረመረሙ፡፡ ነጃሺም እናንተ ብታጉረመርሙም እንኳ እውነታው ይሄ ነው አላቸው” ¹ 

ይህ ከላይ የተጠቀሰው ምልልስ በሁለቱ የቁሬይሻውያን መልዕክተኞችና በስደተኞቹ የሙሐመድ ተከታዮች መካከል በንጉሡ ፊት የተካሔደ ክርክር እንደሆነ አድርገው ታሪክ ጸሐፊዎቹ ዘግበዋል፡፡ ሆኖም በክርክሩ ውስጥ የሚታዩት አንኳር ሐሳቦች ታሪኩ ሆን ተብሎ በኋለኛው ዘመን የተፈጠረ ተረት ተረት መሆኑን በግልፅ ያሳያሉ። ይህም ክርስቲያኑ ንጉሥ ፈፅሞ ያለመስለሙን ፍንትው አድርጎ የሚያመለክት ነው፡፡ በክርክሩ የተጠቀሱትን ዋና ዋና መግለጫዎች እንዴት ሐሰት እንደሆኑ በቅደም ተከተል እንመልከት፡፡ 

፩. ስለ በክት መብላት የተናገረው

በንጉሡ ፊት ሙስሊሞቹን ወክሎ የተናገረው ጃዕፈር ከሠጠው መልስ መካከል “ነቢዩ” መሐመድ አስተምሮናል ብሎ ከገለፀው ውስጥ የሚከተለው አንቀጽ ይገኝበታል

“…እኛ መሃይማን ሕዝቦች ነበርን፤ ጣኦታትን እናመልክ፣ በክት እንበላ፣ እናመነዝር፣ ዝምድና እንቆርጥና የጉርብትናን መብት እናጓድል ነበር፡፡ …ከእርም ነገሮች እንድንታቀብና የሰዎችን ደም እንዳናፈስ አዘዘን፡፡ …”

ጃዕፈርና መላው ስደተኞች ወደ ኢትዮጵያ የገቡበት ጊዜ ላይ ቆመን ይህንን አባባል በቁርአን መነጽር ስንመዝነው ጃዕፈር ይህንን ሊናገር ፈፅሞ አይችልም፡፡ ምክንያቱም ይህ ዕውቀት ሊኖረው ስለማይችል፡፡ ስደተኞቹ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው በንጉሡ ፊት ከቁረይሽ ተወካዮች ጋር የተከራከሩትና የተጠቀሰውን ገለፃ ያደረጉት ከ615 - 616 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ ነው፡፡ ቁርአን ውስጥ በክት መብላትን ከሚከለክሉት አንቀጾች መካከል ቀዳሚው በ 55ኛ ደረጃ የወረደው ሱረቱል አል-አንአም ሲሆን ይህ ሱራ የወረደው በመሐመድ የመካ የመጨረሻ ቆይታ እንደሆነ ምሑራን ይገልፃሉ፡፡ ይህም ከ 620 - 622 ዓ.ም ማለት ነው፡፡²

ግብፃዊው የአዝሃር ዩኒቨርስቲ ምሩቅና ዳኛ Muhammad Habib Shakir (1866-1939) የተባሉ ሰው የጻፉት “Chronological Koran” የተሠኘ መጽሐፍ ገጽ 3 ላይ ይህ ሱረቱል አል-አንዓም የተሠኘ ሱራ በመካከለኛው የመካ ነቢያዊ ዘመን ማለትም ከ618 - 620 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ እንደወረደ ፅፈዋል፡፡ በቁርአን ሱራዎች የአወራረድ ቅደም ተከተል መሠረት ሌሎቹ በክት መብላትን የሚከለክሉት አንቀጾች የሚገኙት በ70ኛ ደረጃ በወረደው ሱረቱል አን-ነህል፣ በ87ኛ ደረጃ በወረደው ሱረቱል አል-በቀራና በ114ኛ ደረጃ በወረደው ሱረቱል አል-ማኢዳ ውስጥ ነው፡፡ 

እንግዲህ ከሁሉ የሚቀድመው ሱራ የወረደው ከ618 ዓ.ም በኋላና ከዚያም ተሻግሮ ከሆነ በዚያን ወቅት ጀዕፈርና ከእርሱ ጋር የነበሩ ሙስሊሞች የት ነው የነበሩት..? ኢትዮጵያ ውስጥ እንጂ መካ አልነበሩም። እነርሱ ኢትዮጵያ ሲገቡና ቁሬይሻውያኑ ንጉሡ ፊት ሲያቀርቧቸው አንቀጾቹ ለሙሐመድ ለመውረድ ሁለት ዓመታትና ከዚያ በላይ ይቀራቸው ነበር፡፡ ታዲያ ጃዕፈር ባልነበረበት፣ ደግሞ ገና ከሁለት ዓመት በኋላ ሊወርድ ያለውን ጉዳይ ከመሐመድ እንደተማረ አድርጎ እንዴት ሊናገር ይችላል..? ፈፅሞ ሊናገር አይችልም፡፡ 

ይህ ሊሆን የሚችለው ታሪክ ጸሐፊዎቹ ፈፅሞ ያልሆነን ነገር እንደሆነ አድርገው በማዋቀር ንጉሡን ለማስለም ሲሉ በኋለኛ ዘመን ፈጥረው የጨመሩት የሐሠት ትርክት በመሆኑ ነው፡፡ ይህ መሠረታዊ ነገር ነው፡፡ ክርስቲያናዊው ንጉሥ ሰልሟል የሚለውን የሙስሊም ጸሐፊዎችን ወሬም ድቡሽት ላይ እንደታነፀ ቤት ያፈራርሰዋል፡፡

፪. ስለ ሶላት፣ ዘካና ፆም የሰጠው ገለፃ

ጃዕፈር በንጉሡ ፊት አቅርቦታል ከተባለው ንግግር ውስጥ የሚከተለውም ይገኝበታል “ሙሐመድ አላህን በብቸኝነት እንድናመልከው፣ በርሱ ላይ ምንንም እንዳናጋራ አዘዘን፣ ሶላት እንድንሰግድ፣ ዘካ (ምፅዋት) እንድንሰጥና ጾም እንድንጾም አዘዘን…”

ሐሳውያኑ የታሪክ ጸሐፍት ከልባቸው ወልደው የጻፉት ሌላው ታሪክ ይሄኛው ነው፡፡ በመሠረቱ ሶላትን፣ ዘካንና ጾምን የሚያዙ አንቀጾች የወረዱት መዲና ውስጥ እንጂ መካ ላይ አልነበረም፡፡ በመዲና የወረዱ የሚባሉ የቁርአን አንቀጾች በሙሉ ከ622 ዓ.ም. በኋላ የተገለጡ መሆናቸው ሲታወቅ በ615/16 ዓ.ም. ጃዕፈር ከየት አምጥቶ ይህንን ሊል ይችላል? ታሪኩ ቅጥፈት ያለበት መሆኑን የተረዳው ኡስታዝ አሕመዲን ጀበል “የኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ከ615 - 1700 
የጭቆናና የትግል ታሪክ” በተሰኘው መጽሐፉ ገጽ 39-40 ላይ በግርጌ ማስታወሻው እንዲህ የሚል ማስተባበያ ጽፎ እንመለከታለን፡-

“ኢብኑል ሐጀር፣ በፈትሁል ባሪ ጥራዝ 4፣ ገጽ 486 ላይ እንዳብራሩት ጃዕፈር ‘በሶላት፣ በዘካትና ጾም ያዘናል’ ያለው የኢስላም መሠረት የሆኑትን ሶላት (ስግደት)፣ ዘካ (ሰደቃ) እና ጾምን ሳይሆን እነኝህ ግዳጅ ሳይሆኑ በፈቃደኝነት ይደረጉ የነበሩትን ተግባራት ለመግለጽ ነው። እርሱ ይህንን በተናገረበት ሰዓት በበጎ ፈቃድ የሚፈጸሙ የአምልኮ ተግባራት ሱናን ነበሩ እንጂ ገና ግዳጅ አልተደረጉም ነበር …” 

ሱና ማለት የመሐመድን ንግግሮችና ተግባራት በፈቃደኝነት መተግበር ማለት ነው፡፡ መሐመድ እነዚህ ተግባራትን እንዲፈፅም ወይም ለተከታዮቹ እንዲያስተምር ትዕዛዝ ካልደረሰው ከየት አግኝቷቸው ሊፈፅማቸው ቻለ..? እነዚህን የአምልኮ ተግባራት ቅድመ እስልምና ቁረይሾች ለረዥም ዘመን ይፈፅሟቸው እንደነበር ይታወቃል፡፡³ በዚያው አካባቢ ተንሠራፍተው ከኖሩ ጣኦት አምላኪ ማሕበረሰቦች ውስጥም ሳቢያኖችና መጁሶች በማለት ⁴ ቁርአን የሚጠራቸው 
ወገኖችም ይኸው ልማድ ነበራቸው፡፡ ⁵

እነዚህን ተግባራት መሐመድ ከጣኦታውያኑ ሙሉ በሙሉ በመቅዳት በተግባር ይፈፅማቸው ለተከታዮቹም ያስተምራቸው እንደነበር ነው ከላይ ያለው ማስተባበያ መጽሐፍ የሚነግረን፡፡ በእርግጥ ይህ ከሆነ የመሐመድ ሱና የጣኦት አምላኪዎች ልማድን ያስቀጠለ እንደሆነ ነው የምንገነዘበው፡፡ እነዚህ የእስልምና ማዕዘናት ተብለው የሚታወቁ የአምልኮ መግለጫዎች 
የጣኦታውያን ውርሶች ከሆኑ እስልምና መለኮታዊ ሃይማኖት ነው ማለት እንዴት ይቻላል..?

ይህን የጃዕፈር ገለፃ ከበርካታ ዘመናት በኋላ የመሐመድን ታሪክ የፃፉ ሰዎች የጨመሩት ለመሆኑ “ነቢያችን አዘዘን” የሚለው ንግግር ያስረዳል፡፡ ጃዕፈር “ሶላት እንድንሰግድ፣ ዘካ (ምፅዋት) እንድንሰጥና ጾም እንድንጾም አዘዘን” አለ እንጂ እርሱ ሲያደርግ ያየነውን እንፈፅም ነበር አላለም፡፡ የተጠቀሱት ትዕዛዛት ደግሞ በመዲና የወረዱ አናቅጽ በመሆናቸው ገና መሐመድ በመካ ሳለ ወደ አቢሲኒያ የተሰደዱ ሰዎች ይህን ቃል ሊናገሩትም ሆነ ሊያውቁት አይችሉም፡፡ ያልተፈፀመን ነገር እንደ እውነተኛ ታሪክ ደጉሰው ያቀረቡ ወገኖች ሀሰተኝነቱ ሲገለጥ እርሱኑ በሌላ ውሸት ለመሸፈን የሚያደርጉት ጥረት ሌላ ጣጣ እንደጋረጠባቸው ይታያል፡፡ ውሸትን በውሸት ለማዳን መሞከር ትርፉ ይኸው ነው፡፡ ያም ሆኖ ይህ የነገሩ ያለመግጠም ክርስቲያኑ ንጉሥ ሰልሟል የሚለውን ተረት ያጋለጠ ሆኗል፡፡ 

፫. ስለ ዒሣ (ኢየሱስ ክርስቶስ) አለ የተባለው

ሌላው አጋላጩና አስገራሚው የጃዕፈር ንግግር ደግሞ ስለ ዒሣ (ኢየሱስ ክርስቶስ) አለ የተባለው ነው፡፡ እንዲህ ይላል፦

“ከዚያም ወደ ንጉሡ ስንገባ ስለዒሳ (ኢየሱስ ክርስቶስ) ምን ትላላችሁ!? ብሎ ጠየቀን ንጉሥ ነጃሺ፡፡ ጀዕፈር ኢብኑ አቡ ጣሊብ እንዲህ አለ፡- ‘ነቢያችን ያስተማረንን እንላለን፡፡ ዒሳ (ኢየሱስ) የአላህ ባሪያ፣ መልዕክተኛና (እርሱ ከፈጠራቸው መንፈሶች መካከል አንዱ) መንፈሱ (ሩሁ) ነው፡፡ ወደ ድንግል መርየም የጣለው የሁን ቃሉም ነው፡፡’ ንጉሥ ነጃሺ እጁን ወደ መሬት ሰደደና አንዲት ዘንግ አነሳ። ከዚያም ኢየሱስ ክርስቶስ (ዒሳ) አንተ ካልከው የዚህን ዘንግ ያህል እንኳን አያልፍም አለ”

ይህኛውም የጃዕፈር ምላሽ ፈፅሞ ከእርሱ አንደበት በዚያን ወቅት ሊወጣ አይችልም። ምክንያቱም “ዒሳ (ኢየሱስ) የአላህ ባሪያ፣ መልዕክተኛና (እርሱ ከፈጠራቸው መንፈሶች መካከል አንዱ) መንፈሱ (ሩሁ) ነው፡፡ ወደ ድንግል መርየም የጣለው የሁን ቃሉም ነው” 
የሚለው ዕውቀት በዚያን ጊዜ ሊኖረው አይችልምና፡፡ ይህ አንቀጽ በቁርአን ውስጥ በአንድ ሥፍራ ብቻ የሚገኝ ሲሆን ቦታውም ሱረቱል አል-ኒሳዕ፡4÷171 ላይ ነው፡፡ ይህ አንቀጽ ያለበት የሴቶች ምዕራፍ የተሠኘው ሱራ ደግሞ በሱራዎች የአወራረድ ቅደም ተከተል በ92ኛ ደረጃ በመዲና የወረደ ነው፡፡ ጊዜውም በ4ኛውና በ5ኛው ዓመተ ሂጅራ መካከል እንደሆነ እስላማዊ ምንጮች ይገልፃሉ፡፡ ⁶

ይህ ማለት በ626 እና በ627 ዓ.ም መካከል ማለት ነው፡፡ ጃዕፈርና ቡድኑ ከንጉሡ ጋር 
የተነጋገሩት ደግሞ ከ615 - 616 ዓ.ም እንደሆነ ተደጋግሞ ተጠቅሷል። ያን ጊዜ ስለ ዒሣ የተባለው አንቀጽ ለመሐመድ ሊወርድለት ገና ድፍን 10 ዓመት ይቀረዋል፡፡ ታዲያ በምን ተአምር ጃዕፈር ይሄን ሊል ይችላል..? ነገሩ ግልፅ ነው፡፡ ጃዕፈር ፈፅሞ ይህን አንቀጽ ሊናገር አይችልም። ስለ ዒሣ እንዲህ ያለ ዕውቀትም አልነበረውም፡፡ ታሪክ ጸሐፊዎቹ ፈጥረውና አቀናብረው የፃፉትና ጃዕፈር ስብዕና ላይ ያሳረፉት የሐሠት ወሬ ነው፡፡

እንዲህ ያለው ዘዴና ያልተባለን ነገር በጥንት ሰዎች ስብዕና ላይ በማሳረፍ እንደዚህና እንደዚያ ብለዋል ብሎ የኋሊት መተረክ በቁርአንና በእስላማዊ ትርክቶች የተለመደ ነው፡፡ ታሪክ ጸሐፊዎቹ ይህንኑ ሥልት የተከተሉ ይመስላል፡፡ ንጉሡ ይህን ቃል ሲሰማ “ንጉሥ ነጃሺ እጁን ወደ መሬት ሰደደና አንዲት ዘንግ አነሳ። ከዚያም "ኢየሱስ ክርስቶስ (ዒሣ) አንተ ካልከው የዚህን ዘንግ ያህል እንኳን አያልፍም አለ” የተባለውም ፍፁም ውሸት ነው፡፡ መነሻ ቃሉ ሐሠት ከሆነ ውጤቱና ተከታዩ ነገር ሁሉ ሐሠት መሆኑ ይታወቃል። መቼም በዚህ ሁሉ የሐሠት ትርክት የተሞላ ታሪክ አጠቃላይ ግቡ ክርስቲያኑን ንጉሥ እንደሰለመ ማስመሰል ቢሆንም በእንዲህ ያለ ምርመራ ሀሠተኝነቱ ተጋልጦ እርቃኑን ይቀራል፡፡

፬. መልክአ-ምድራዊ አገላለጥ 

ተጨማሪው አጋላጭ ነገር በታሪክ ጸሐፊዎቹ ስለ መልክአ-ምድር የተፃፈው ነገር ነው፡፡ እንዲህ ይላል፦

“ሐበሾች ተነሱበት፤ ለነጃሺም አንተ ሃይማኖታችንን ትተሀል አሉት፤ አመፁበትም፡፡ እርሱም ወደ ጀዕፈር ጀልባን በማዘጋጀት ላከበት እንዲህም አለው፡- እርሷ ላይ ውጡ እና ዝግጁ ሁኑ፤ ከተሸነፍኩ የፈለጋችሁበት ቦታ እስክትደርሱ ሂዱ፤ ካሸነፍኩ ደግሞ እዚሁ ተረጋግታችሁ ቆዩ...” ⁷

በዚያን ዘመን የነበረው የኢትዮጵያ ንጉሥ መቀመጫ አክሱም ነበረ። የሚጠራውም የአክሱም ንጉሥ በመባል ነው፡፡ ይህንንም ራሳቸው ሙስሊም ጸሐፊዎች የሚጠቀሙበት ቃል ነው፡፡ ንጉሡ አለ የተባለው ይህ ንግግር ግን “ነጃሺ” የአክሱም ንጉሥ እንዳልሆነ በግልጽ ያሳያል። ምክንያቱም አክሱም ላይ ምንም ዓይነት ከቀይ ባሕር ጋር የሚገናኝ የወንዝ ዘር የለምና፡፡ አክሱምና ጀልባ ፈጽሞ አይተዋወቁም፡፡ ቅርቡ የቀይ ባሕር ጠረፍ እንኳ ከአክሱም ከ150 ኪ.ሜ በላይ ርቀት አለው። ጀልባ አንሳፋፊ ወንዝ በሌለበትና የመጓጓዣ መሣሪያዎች ኋላቀር በሆኑበት በዚያ ዘመን ንጉሡ ይህንን የመሰለ መልዕክት ሊያስተላልፍ አይችልም፡፡

በእርግጥ ብሏል የሚባል ከሆነ ታሪኩ ከአክሱም ወደ ምጽዋ ይሸጋገራል ማለት ነው፡፡ እናም ነጃሺ የአክሱም ንጉሥ ሳይሆን በቀይ ባሕር ዳርቻ የሚገኝ አንድ ነዋሪ ሰው ወይም የአካባቢው የንጉሥ እንደራሴ ነበር ማለት ነው፡፡ ይህን የሚያረጋግጥልን ምጽዋ ውስጥ የሚገኘው የነጃሺ መስጊድ ነው፡፡ እውነት ለመናገር አረቦች “ነጃሺ” እያሉ የሚጠሩት ቃል የማዕረግ ሥያሜን የሚያመለክት ትርጓሜውም “አስገባሪ” ማለት ነው፡፡ ተክለ ጻድቅ መኩሪያ ስለዚህ ጉዳይ በመጽሐፋቸው እንዲህ ይላሉ 

“... ከኢትዮጵያ ግብር እያስወጣ ለእነዚያ የሚልከው ነጋሲ ወይም ነገሥት ትርጓሜው በሳባውያን ቋንቋ ‘አስገባሪ ወይም አስገባሪዎች’ እንደሚባል ይገልፃሉ፡፡ አስገባሪ ማለትም ግብር አስወጭ ከማለት ልዩነት የለውም” ⁸

ይህም የሚያመለክተው ቃሉ በአክሱም ንጉሥ ሥር ባሉ ግዛቶች ላሉ አስገባሪዎች የሚሰጥ የማዕረግ ሥያሜ መሆኑን ነው፡፡ ይህ ሥያሜ በተለይ በባሕር ጠረፍ አካባቢ ላለ ግዛት ባለ ሥልጣን የሚሠጥ መጠሪያ ነበር፡፡ የምፅዋ ገዢ “ባሕረ ነጋሽ” ተብሎ የሚታወቅበት ሰፊ ልማድ አለ፡፡ በአረብኛ ለንጉሥ የሚሰጥ ስያሜ “አሚር” ወይም “ኸሊፋ” ነው፡፡ “ነጃሺ” የሚለው ቃል እዚያው አክሱም አካባቢ ጥቅም ላይ የሚውል ከሆነ ትርጓሜውንም ከዚያው ነበር ማግኘት የሚገባቸው። አረብ ጸሐፊዎች ግን ነጋሽ የሚለውን ቃል ንጉሥ ከሚለው ቃል ጋር በማቀራረብ የኢትየጵያ ነገሥታት የሚጠሩበት መጠሪያ እንደሆነ አድርገው ለማቅረብ ሞከሩ፡፡ ይህ ግን ፈፅሞ ስሕተት ነው፡፡ 

በኢትዮጵያ ታሪክም ሆነ የነገሥታት ስም አጠራር ውስጥ “ነጃሺ ወይም ነጋሲ” ተብሎ የሚታወቅ የማዕረግም ሆነ የተፀውዖ ስም የለም፡፡ ሙስሊም አረብ ጸሐፊዎች እየደጋገሙ “ነጃሺ” እያሉ የሚጠሩት ግለሰብ ከላይ በተጠቀሰው በርካታ ምክንያት የአክሱም ንጉሥ ሳይሆን በምፅዋ አካባቢ የሚገኝ የአንድ አውራጃ አስተዳዳሪ ሊሆን እንደሚችል ጠቅሰናል፡፡ ይህንን ነገር ጽንፈኝነት የሚታይባቸው አንዳንድ ሙስሊም ጸሐፊዎች ሳይቀሩ አምነው የፃፉት ሐቅ ነው፡፡ 

በካይሮው ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር አብዱል ሐሊም መሐመድ ረጀብ ተፅፎ በ "The institute Africa Research studies, Cairo University" ታትሞ የተሠራጨው

"Al-Alaqat Al-Siyasiyya bayna muslim Al-Zaila wa nussara al-Habasha fi al usur al wusta."

“በዘይላ ሙስሊምና በክርስቲያን አቢሲኒያ መካከል በመካከለኛው ዘመን የነበረው ፖለቲካዊ ግንኙነት”

የተሠኘ የጥናት ጽሑፍ  “ነጃሺ ወደ እስልምና መለወጡ እርግጥ ቢሆንም በሥልጣኑ ግን ንጉሥ ሳይሆን የአንድ አካባቢ ገዥ (ባሕረ ነጋሽ) ነው፡፡ እስልምናን ከተቀበለ በኋላ ከፍርሃት የተነሳ ‘የእስልምና ጠላቶች የሆኑት ሕዝብ ማለትም ክርስቲያኖቹ እምነቱን እንዳይገልጥ አድርገውታል" ይላል። ⁹ እንግዲህ ወደ እውነታ ሊቀርብ የሚችለው ይህ አገላለጥ ሆኖ ሳለ እንደዚህ ያለው ውዥንብር የተፈጠረው የአካባቢውን መልክአ ምድር የማያውቁ የእስልምና ታሪክ ጸሐፊዎች የማይገናኝ ነገር በማገናኘት ልብ ወለድ ታሪክ በመፃፋቸው ነው፡፡ 

ማጣቀሻዎች 

¹ ነጃሽና የሀበሻ ምድር በእስልምና መነጽር፣ ገጽ 60-63፤ 
ኢትዮጵያ እና ኢስላም፣ ገጽ 15 -17

²https://en.m.wikipedia.org/wiki/Al-An’am

³ አብዱልሃቅ ጀሚል 2011 ዓ.ም. "ኢስላም መለኮታዊ ሃይማኖት ነውን?" ገጽ፡189-199

⁴ ሱረቱል አል-በቀራ፡2÷62, ሱረቱል አል-ማዒዳህ፡5÷69, ሱረቱል አል-ሐጅ፡22÷17

⁵ አብዱልሃቅ ጀሚል 2011 ዓ.ም. "ኢስላም መለኮታዊ ሃይማኖት ነውን?" ገጽ፡189-199

⁶http://www.englishtafsir.com/quran/4/index.html#sdfootnote214sym

http://www.quran-wiki.com/surah-overview.php?sura=4#4409

⁷ ነጃሺ እና የሀበሻ ምድር በእስልምና መነጽር ገጽ 66

⁸ ተክለ ጻድቅ መኩሪያ 1951ዓ.ም. የኢትዮጵያ ታሪክ፣ ኑብያ አክሱም ዛጉዌ ገጽ፡337

⁹ Abd al Halim Muhammad Rajab [1985] pp. 31-38 as quoted ኤፍሬም እሸቴ - አክራሪ እስልምና በኢትዮጵያ ገጽ፡31-32

(የሳንኮፋ ሰንኮፍ እና ሌሎች ከገጽ 107-116)
Share on Google Plus

ስለ የተለጠፈበት ቀን

    Blogger Comment
    Facebook Comment