የጠቀስናቸው እስላማዊ ክታቦች የንጉሡን መስለም ይበልጥ ተአማኒ ለማድረግ ከመሐመድ ጋር ደብዳቤ ይለዋወጥ እንደነበር ዘግበዋል፡፡ ኢትዮጵያና ኢስላም የተባለው መጽሐፍ ስለ ሀበሻ ታሪክ የተፃፉ ያላቸውን የተለያዩ አረባዊ መጻሕፍት በመጥቀስ በመሐመድና በነጃሺ መካከል ስለተደረገው የደብዳቤ ልውውጥ ይዘት የሚከተለውን ብሏል።
“ነቢዩ በሂጅራ ስድስተኛው ዓመት ላይ ዐምር ኢብን ኡመያን ወደ ነጃሺ ደብዳቤ በማስያዝ ላኩት፡፡ ወደ ኢስላም ኦፊሴላዊ ጥሪ የማቅረብ ዓላማ ያለው ነበር፡፡ እንዲህ ይነበባል
‘በአላህ ስም እጅግ በጣም አዛኝ ሩኅሩኅ በሆነው ይድረስ ከሙሐመድ - የአላህ መልዕክተኛ - ወደ ነጃሺ አስሐማ የሐበሻ ንጉሥ ከዚህ በመቀጠል በቅድሚያ አላህን አመሰግናለሁ፡፡ አላህ ከእርሱ በቀር ሌላ አምላክ የሌለ (ጌታ) ነው፡፡ ንጉሥ ነው፡፡ ፍፁም ነው፡፡ ሰላምና የሚታመንበት አሸናፊ ነው፡፡ ዒሣ የማርያም ልጅ ራሷን በጠበቀችና ጻድቅ በሆነችው ድንግል ማርያም ላይ የተጣለ የአላህ መንፈስና ቃል መሆኑን እመሰክራለሁ፡፡ እርሷም ዒሣን አረገዘች - በአላህ መንፈስና እስትንፋስ፡፡ አላህ አደምን በእጁና በእስትንፋሱ እንደፈጠረው ሁሉ፡፡ እኔ ወደ አላህ እጠራሃለሁ፡፡ አንድ ነው፣ ሸሪክም የለውም፡፡ በእርሱ ትዕዛዝም ሥር እንድትውል አሳስብሃለው፡፡ እኔንም እንድትከተለኝ፣ እንድታምንብኝና ወደኔም የተወረደውን (ቁርአን) እንድታምንበት እጠይቅሃለሁ፡፡ ምክሬንም ለግሻለሁ፡፡ ተቀበሉኝ፡፡ ወደናንተም የአጎቴን ልጅ ጀዕፈርንና የተወሰኑ ሙስሊሞችን ልኬአለሁ፡፡... ሠላም ቀናውን ጎዳና በተከተሉ ላይ ይሁን’
በእርግጥ ነቢዩ ሙሐመድ ወደ ነጃሺ የላኩት ደብዳቤ ከተለያዩ ምንጮች አኳያ የተወሰነ የቅርጽ ልዩነት ቢስተዋልበትም ይዘቱ ተመሳሳይ ነው። ደብዳቤው ለነጃሺ በደረሰው ጊዜና በተነበበለት ወቅት በእጁ በመያዝ በጉጉት ተመለከተው፡፡ ከዙፋኑ ላይም በመተናነስ መንፈስ ወረደ፡፡ ከዚያም፡-
‘በአላህ ስም እምላለሁ ይህ መፃፍና ማንበብ የማይችለው ነቢይ ነው፣ የመጽሐፉ ባለቤቶች የሚጠባበቁትም እርሱኑ ነው፡፡ በኦሪት ሙሳ
አህያ ላይ ተቀምጦ ይመጣል ብሎ ያበሰረው ዒሣን እንደሆነ ሁሉ በወንጌል ዒሣ በግመል ላይ ተቀምጦ ይመጣል ያለው ደግሞ እርሱ (ሙሐመድ) ነው አለ፡፡
የነጃሺ መልስ
“በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡ ይድረስ ለሙሐመድ - የአላህ መልእክተኛ - ከነጃሺ አስሐማ
"አሰላሙ ዐለይኩም ወረህመቱላሂ ወበረካቱሁ ወደ ኢስላም ከመራኝ አላህ በቀር ሌላ ሊገዙት የሚገባ አምላክ እንደሌለ እመሰክራለሁ፡፡ከዚህ በመቀጠል የአላህ መልዕክተኛ ሆይ! ደብዳቤዎ ደርሶኛል፡፡ በሰማይና በምድር ጌታ እምላለሁ ስለ ዒሣ ቢን መርየም የጠቀሱልኝን በተመለከተ ራሱ ዒሣም ቢሆን እርስዎ ካሉት የጨመረው ነገር የለም። እና የሰማይና የምድር ጌታ የጠቀሱበትን ደብዳቤዎን ደርሶኛል፣ ኢየሱስ ከምትሉት አይበልጥም፡፡ ወደኛ የተላኩበትን ምክንያት አውቀናል፡፡ እርስዎም የአላህ መልዕክተኛ መሆንዎን እውነተኛና ሊተማመኑብዎት የሚገባዎ መሆንዎን ተገንዝበናል፡፡ ለዚህም ቃል ኪዳን ገብቻለሁ፡፡ ለአጎትዎ ልጅም ቃል ኪዳን (በይዓ) ፈፅሜለታለሁ። ለዓለማት ጌታ ለሆነው አላህም እጅ ሰጥቻለሁ፡፡ ወሰላሙ ዐለይከ ወረሕመቱላሂ ወበረካቱሁ” ¹
ፕሮፌሰር ስርግው ይህን ደብዳቤ በተመለከተ እንዲህ ብለዋል
“The authenticity of this letter is doubtful as there is not sufficient ground to believe that the Emperor of Ethiopia denied the christian faith and submitted himself to Islam.”
“የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ክርስቲያናዊ እምነትን ክደው ራሳቸውን ለእስልምና አስረክበዋል ብሎ ለማመን በቂ መሬት ስለሌለ የዚህ ደብዳቤ ትክክለኛነት አጠራጣሪ ነው” ²
ፕሮፌሰር ስርግው ኢትዮጵያዊው ክርስቲያናዊ ንጉሥ ሊሰልም የማይችልባቸውን ነጥቦች አስቀምጠዋል፡፡ ከዚያም በመነሳት በእስላማዊ ጸሐፍት የተከተበውና መሐመድና ንጉሡ የተለዋወጡት ደብዳቤ ነው የተባለውን ሊታመን እንደማይችል ጽፈዋል፡፡ ይህንን ነገር ከክርስትናው አስተምሕሮና መጻሕፍት አንጻር ስንመረምረው ደግሞ ይበልጥ ቀሎና ሃሳባዊ ወደ መሆን ወርዶ ነው የምናገኘው፡፡
ንጉሡ ከመሐመድ የተላከው ደብዳቤ ሲደርሰው አደረገ የተባለው እንቅስቃሴና የተናገራቸው ነገሮች ሊሆን የማይችሉ ከመሆናቸው የተነሳ አስቂኝ ወደመሆን ያዘነብላሉ፡፡ እስላማዊ ጸሐፍት በእስልምና ግንዛቤ ላይ ቆመው የክርስትና መጻሕፍትን የልባቸውን ምኞት ሊያናግሯቸው ሲዳዱ በግልፅ መመልከት ይቻላል፡፡ ንጉሡ የመልስ ደብዳቤውን ከመፃፉ በፊት
“በአላህ ስም እምላለሁ ይህ መፃፍና ማንበብ የማይችለው ነቢይ ነው፣ የመጽሐፉ ባለቤቶች የሚጠባበቁትም እርሱኑ ነው፡፡ በኦሪት ሙሳ
አህያ ላይ ተቀምጦ ይመጣል ብሎ ያበሰረው ዒሣን እንደሆነ ሁሉ በወንጌል ዒሣ በግመል ላይ ተቀምጦ ይመጣል ያለው ደግሞ እርሱ (ሙሐመድ) ነው”
ሲል መናገሩ ተዘግቧል፡፡ ለመሆኑ የመጽሐፉ ባለቤቶች የተባሉት አይሁዶችና ክርስቲያኖች ማንበብና መፃፍ የማይችል ነቢይ ይጠባበቁ እንደነበር በየትኛው መጽሐፋቸው ላይ ተጠቅሷል..? መቼም ክርስቲያናዊው ንጉሥ በክርስቲያኖች ቅዱሳት መጻሕፍት ያላገኘውንና መምሕራኑም ያላስተማሩትን እርሱ ሊያውቅ እንደዚያም ሊናገር አይችልም። በክርስቲያኖችም ሆነ በአይሁድ መጻሕፍት በትውፊታቸውም ቢሆን እንዲህ ያለው ነገር ፈፅም አይታወቅም፡፡ ይህ ነገር ያለው እዚያው ቁርአኑ ላይ ነው፡፡ እንዲህ ይነበባል
“ለእነዚያ ያንን እነሱ ዘንድ በተውራትና በኢንጂል ተጽፎ የሚያገኙትን የማይጽፍና የማያነብ ነቢይ የኾነውን መልክተኛ የሚከተሉ ለኾኑት (በእርግጥ እጽፍለታለሁ)” (አል-አዕራፍ፡7÷157)
ይህን ቁርአናዊ አንቀጽ አንብቦ ጥቅሱ ወይም ሃሳቡ በተውራት (ኦሪት) እና በኢንጅል (ወንጌል) ይገኝ እንደሆነ የሚፈልግ ሰው ቢኖር ትርፉ ድካም ብቻ ነው የሚሆነው፤ ምክንያቱም ፈፅሞ ሊገኝ አይችልምና። ያልተፃፈ ነገር ቀድሞውኑ እንዴት ሊገኝ ይችላል..? ይህንን ቁርአናዊ ሃሳብ በመያዝ ከሊቅ እስከ ደቂቅ፣ ከምሑር እስከ ባላገር፣ ከጎምቱ እስከ ከንቱ ያሉ ሙስሊሞች ማንበብና መፃፍ የማይችለው መሐመድ “በተውራትና በኢንጅል ተጽፏል” ይላሉ። እስካሁን ግን ይህንን ወሬ ኦሪትና ወንጌልን በመረጃነት በመጥቀስ ያመለከተ አንድም እስላማዊ ሊቅ የለም፡፡ እስላማዊ ታሪክ ጸሐፊዎቹ ኢትዮጵያዊው ንጉሥ ላይ የራሳቸውን ምኞትና ግንዛቤ በማሳረፍ እንዲህ እንደተናገረ አድርገው ፃፉት እንጂ እርሱ ፈፅሞ እንዲህ ሊል አይችልም፡፡
ተከታዩም ነገር ቢሆን “ጥቂት ቆሎ ይዞ ወደ አሻሮ” እንደሚባለው ዓይነት ነው፡፡
“በኦሪት ሙሳ አህያ ላይ ተቀምጦ ይመጣል ብሎ ያበሰረው ዒሣን እንደሆነ ሁሉ በወንጌል ዒሣ በግመል ላይ ተቀምጦ ይመጣል ያለው ደግሞ እርሱ (ሙሐመድ) ነው”
ከእዚህ አንቀጽ ውስጥ ትንሽ እውነት የሚመስለው ኢሣ (ኢየሱስ) በአህያ ላይ ተቀምጦ ይመጣል የተባለው ነው፡፡ እርሱም ቢሆን በኦሪት መጻሕፍት ውስጥ የተፃፈ አይደለም፤ ተናጋሪውም ነቢዩ ሙሴ አይደለም፡፡ ይህ ቃል የሚገኘው በነቢዩ ዘካርያስ ትንቢት ውስጥ ነው
“አንቺ የጽዮን ልጅ ሆይ፥ እጅግ ደስ ይበልሽ፤ አንቺ የኢየሩሳሌም ልጅ ሆይ፥ እልል በዪ፤ እነሆ፥ ንጉሥሽ ጻድቅና አዳኝ ነው፤ ትሑትም ሆኖ በአህያም፥ በአህያይቱ ግልገል በውርጫይቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል” (ትንቢተ ዘካርያስ 9÷9)
የትንቢት ቃሉ ኢየሱስ ክርስቶስ በአህያዪቱና በውርንጫይቱ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም በገባ ጊዜ መፈፀሙን የወንጌል መጻሕፍት በተደጋጋሚ ተናግረዋል (ማቴ.21÷4-5, ዮሐ.12÷14-15)፡፡ ይህንን እውነታ እስላማዊ ታሪክ ጸሐፊዎች አጣመውና አዘባርቀው ትንቢቱን ተናጋሪው ሙሴ፣ የተነገረበትም መጽሐፍ ኦሪት እንደሆነ አድርገው ከመግለፃቸውም በላይ ሐበሻው ንጉሥ እንደተናገረው ለማስመሰል ጥረዋል፡፡ ጥረታቸውን ያልተሳካ የሚያደርገው ግን እስላማዊውን ምኞት ክርስቲያናዊ ግንዛቤ አድርገው ማቅረባቸው ነው፡፡
ይበልጥ አጋላጭ የሚሆነው ደግሞ “በወንጌል ዒሣ በግመል ላይ ተቀምጦ ይመጣል ያለው ደግሞ እርሱ (ሙሐመድ) ነው” የሚለው ቃል ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ የትንቢት ቃል የትኛው ወንጌል ላይ ነው የተፃፈው ግን..? የትኛውም ወንጌል ላይ የለም፡፡ በእርግጥም እንዲህ ያሉ “እዚህኛውና እዚያኛው መጽሐፍ ላይ ተፅፏል” የሚሉ ነገሮች በወቅቱ ለሚገኙና ላልተማሩ፣ መጻሕፍትንም መርምረው የማይጠይቁ አረባውያን ምስኪኖችን ለማሳመን የተነገረ እንደሆነ መገመት ይቻላል፡፡
በክርስትናው ዓለም ጨርሶ የማይታወቅን ዕውቀት ክርስቲያኑ ንጉሥ ሊያውቅ አይችልም፡፡ በግሉ እስልምናን ቢቀበል እንኳ ያልሆነ፣ የማይታወቅና ፈፅሞ ከእውነት የራቀን ነገር በመጽሐፉ ሰዎች ላይ የሚደፈድፍበት ምክንያት የለም፡፡ እንዲህ ያለው ልማድ እጅግ የተዘወተረው በሙስሊሞቹና በመጻሕፍቶቻቸው በመሆኑ ንጉሡ ያልተናገረውን ነገር እስላማዊ ታሪክ ጸሐፊዎች ጽፈውታል ማለቱ ነው ወደ እውነታው የሚቀርበው፡፡
የንጉሡ የመልስ ደብዳቤ ይዘትም እስካሁን ከጠቀስነው የተለየ ነገር አናገኝበትም፡፡ እንዲያውም በጥልቀት ለመረመረው በንጉሡ ስም የተፃፈ ለመሆኑ ፍንጮች ያገኝበታል። ለምሳሌ የመሐመድ ደብዳቤ በተባለው ላይ ስለ ዒሣ የጠቀሰውን ነገር ለማረጋገጥ ንጉሡ
“በሰማይና በምድር ጌታ እምላለሁ ስለ ዒሣ ቢን መርየም የጠቀሱልኝን በተመለከተ ራሱ ዒሣም ቢሆን እርስዎ ካሉት የጨመረው ነገር የለም... ኢየሱስ ከምትሉት አይበልጥም”
የሚል ግብረ መልስ መስጠቱ ተከትቧል።
ይህንን ምላሽ የሰጠው መሐመድ በደብዳቤው ኢሣን (ኢየሱስን) አስመልክቶ “እርሷም ዒሣን አረገዘች - በአላህ መንፈስና እስትንፋስ። አላህ አደምን በእጁና በእስትንፋሱ እንደፈጠረው ሁሉ” ሲል ፃፈ ለተባለው ኃይለ ቃል ነው፡፡ ንጉሡ ይህን ዓይነት ቃል የተናገረው በደብዳቤው ብቻ አይደለም፡፡ ገና በመጀመሪያ ስደተኞቹ ሙስሊሞች በፊቱ ቀርበው ስለ እምነታቸው ሲያስረዱ ተመሳሳዩን ምላሽ ነው ሰጠ የተባለው፡፡
ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ፣ የሰማይና የምድር ጌታና ሁሉን የፈጠረ ፈጣሪ እንደሆነ በጥብቅ በሚታመንበትና በሚሰበክበት የክርስትና ሃይማኖት ውስጥ የኖረ ሰው ያውም ንጉሥን ያህል ስብዕና በአንዲት ንግግር ብቻ ተስቦ ክርስቶስ ባሪያና ልክ እንደ አዳም የተፈጠረ ፍጡር ነው ብሎ በዙሪያው ላሉት ካሕናትና ሊቃውንት ነገራቸው ማለት ጨርሶ ሊታመን የማይችል ነገር ነው፡፡
ይህን ነገር ንጉሡ እንደተናገረ አድርገው የፃፉት የእስልምና ታሪክ ጸሐፊዎች ናቸው የሚለው የተሻለ ተቀባይነት አለው፡፡ ገና በመጀመሪያው ቀን፣ በመጀመሪያ ንግግር፣ መሠረታዊ የሃይማኖት ትምህርት በመረጃና በአመክንዮ ባልተፈተሸበት፣ መሐመድ ስለተባለው ሰው ማንነት ባልተብራራበት ሁኔታ ንጉሡ የኖረበትን እምነት ትቶ ክርስቶስን በመካድ እንደተናገረ የፃፉ ወገኖች “የንጉሡ ደብዳቤ” ባሉት ላይ ተመሳሳዩን ነገር አይፅፉም ማለት የዋሕነት ብቻ ነው የሚሆነው፡፡
ንጉሡ በደብዳቤው ስለ መሐመድ ሰጠ የተባለው ምስክርነትም ቢሆን አንድ ከእስልምና ግንዛቤ ውጭ ሌላ ነገር የማያውቅና በዚያው አስተሳሰብ ብቻ የተጠመደ ሰው ሊፅፈው የሚችለው ነው፡፡ ክርስቲያን የነበረ ሰው ስለ መሐመድ “ወደ እኛ የተላኩበትን ምክንያት አውቀናል፡፡ እርስዎም የአላህ መልዕክተኛ መሆንዎን እውነተኛና ሊተማመኑብዎት የሚገባዎ መሆንዎን ተገንዝበናል” ብሎ ለመፃፍ ይቸገራል፡፡
መሐመድ የፈጣሪ መልዕክተኛ መሆኑን መስክሮ ንጉሡ የፃፈው የመጽሐፉ ሰዎች የሚጠባበቁት የማይፅፍና የማያነብ ነቢይ እንደሚመጣ ከኦሪትና ከወንጌል አግኝቶ ነው እንዳይባል ይህ አስተሳሰብ መሠረተ ቢስና ፈፅሞ በተጠቀሱት መጻሕፍት ውስጥ እንደማይገኝ አይተናል። እንግዲህ መሠረቱ ሀሠት ከሆነ ቋሚውና ግድግዳው ድቡሽት ላይ የተመሠረተ ፈጠራ መሆኑ አይቀርም፡፡ ስለዚህም ይህኛውም ገለፃ የጸሐፍቱ እንጂ የንጉሡ ሊሆን አይችልም፡፡
“ሊተማመንብዎት የሚገባዎ” የሚለውም ዋስትናና መተማመንን በክርስትና ግንዛቤ ተረድቶ የኖረ ሰው ሊናገረው የሚችለው አይደለም። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ፈፅሞ ሊተማመኑበት የሚገባው ኢየሱስ ክርስቶስ የሠጠው ዋስትና ነው፡፡ የዘላለም ሕይወትን አስመልክቶ
“እውነት እውነት እላችኋለሁ በእኔ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው” ሲል አስረግጦ ተናግሯል (ዮሐ.6÷47)፡፡ በእርሱ ያመነ ሰውም ከሞት የተሻገረ ተሥፋ እንዳለው ሲገልጥ
“ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል” ብሏል (ዮሐ.11÷25)፡፡ በእርሱ ጥላ ሥር ለተሰበሰቡት የሚሰጣቸውን የጥበቃ ዋስትና ሲገልጥም “እኔም የዘላለም ሕይወትን እሰጣቸዋለሁ፥ ለዘላለምም አይጠፉም፥ ከእጄም ማንም አይነጥቃቸውም” ሲል በተጨማሪም “ወደ እኔም የሚመጣውን ከቶ ወደ ውጭ አላወጣውም” ብሏል (ዮሐ.10÷28፣ ዮሐ.6÷37)፡፡ ለደካሞችም የሰጠውን ዋስትና ሲገልጥ “እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፥ ወደ እኔ ኑ፥ እኔም አሳርፋችኋለሁ” ብሏል (ማቴ.11÷28)።
እነዚህ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መረጃዎች የክርስትና እምነት ራስና መሪ የሆነው ክርስቶስ ለአማኞቹ የሠጠውን ግልፅና የጠበቀ ዋስትና ያመለክታሉ፡፡ ንጉሥን የሚያህል ስብዕናና በታላላቅ የሃይማኖቱ ሊቃውንት የሚከበብ ሰው እነዚህ ተደጋጋሚ ኃይለ ቃሎች ይጠፉታል ብሎ ማሰብ መቼም የዋህነት ነው፡፡ ታዲያ በዚህ ሁሉ የዋስትናና የመተማመኛ አጥር ውስጥ ያለን ክርስቲያን መሐመድን በምን መስፈርት “ሊተማመኑብህ የሚገባ” ይለዋል..?
መሐመድ በራሱ አንደበት የተከታዮቹንም ሆነ የራሱን ፍፃሜ እንደማያውቅና ለማንም መተማመኛ መስጠት እንደማይችል በግልፅ ተናግሯል፡፡ «ከመልክተኞች ብጤ የሌለኝ አይደለሁም፡፡ በእኔም በእናንተም ምን እንደሚሠራም አላውቅም፡፡ ወደእኔ የሚወረደውን እንጅ ሌላን አልከተልም፡፡ እኔም ግልጽ አስፈራሪ እንጅ ሌላ አይደለሁም» በላቸው” (ሱረቱል አል-አሕቃፍ 46÷9)
በታማኝነት ደረጃው ቀዳሚውን ሥፍራ ይይዛል በሚባልለትና "ሳኂህ አል-ቡኻሪ" ተብሎ በሚታወቅ የሱኒ ሙስሊሞች ሀዲስ ላይ የሚከተለው ታሪክ ተዘግቧል
ኡስማን ቢን ማዙን የሚባል ሰሃባ ታሞ ይሞታል፡፡ ስታስታምመው የነበረች ኡም አል-አላ የምትባል ሴት አስከሬኑን እያየች “አቡ አስ-ሰዒብ ሆይ የአላህ እዝነት በአንተ ላይ ይሁን! አላህ እንዳከበረህ እመሰክራለሁ” ብላ ትናገራለች፡፡ በዚህ ጊዜ መሐመድ ሴትየዋን “አላህ እንዳከበረው እንዴት አወቅሽ?” ሲል ይጠይታል፡፡ እርሷም “አላውቅም፤ የአላህ መልእክተኛ ሆይ አባቴ እና እናቴ ለእርስዎ መስዋዕት ይሁኑ! ግን ለእርሱ (ለሟቹ) ካልሆነ አላህ ሌላ ማንን ሊያከብር ይችላል?” ስትል ትጠይቃለች፡፡ መሐመድም “እርሱን በተመለከተ - በአላህ እምላለሁ፣ ሞት ደርሶበታል፣ ለእርሱም መልካሙን እመኝለታለሁ። ሆኖም በአላህ እምላለሁ፣ እኔ የአላህ መልእክተኛ ብሆንም እንኳ አላህ በእኔ ላይ ምን እንደሚያደርግ አላውቅም” ሲል መለሰላት፡፡ ³
የመሐመድ ንግግር "እንኳን እርሱ ቀርቶ እኔ የአላህ መልዕክተኛው በራሴ ላይ ምን እንደሚደረግብኝ አላውቅም" የሚል ለዛ እንዳለው ግልፅ ነው፡፡ ለዛው ቢቀር እንኳ መሐመድ በቁርአንም ሆነ በሀዲስ ፍፃሜውን እንደማያውቅ መናገሩን ማስተባበል አይቻልም፡፡ ለራሱ የማያውቅ ደግሞ ለሌሎች ዋስትና መስጠት አይችልም፡፡ ተጨባጩ እውነት ይህ ቢሆንም ብዙ ሙስሊም ጸሐፊዎች ግን “ነቢያችን” ለሚሉት መሐመድ ከአቅሙና ከገዛ ንግግሩ ያለፈ በርካታ ችሎታዎች አሸክመውታል፡፡ በዚያው ስነ-ልቡና ውስጥ ያሉ የእስልምና ታሪክ ጸሐፊዎች ደግሞ አንድ ተጨማሪ እርምጃ በመራመድ የሚፈጥሯቸው ገጸ-ባሕርያት በመሐመድ እንደሚተማመኑ በማናገር መጻሕፍቶቻቸው ውስጥ ይዶሏቸዋል፡፡ ለዚህም ዋንኛው ማሳያ ኢትዮጵያዊው ክርስቲያናዊ ንጉሥ ነው፡፡
ማጣቀሻዎች
¹ ኢትዮጵያና ኢስላም ገጽ 29-32
² Sirgiw Hablesilassie; Ancient & Medieval Ethiopian History, p. 190
³ Sahih Al-Bukhari፡ Vol. 5, Book 58, No. 266
(የሳንኮፋ ሰንኮፍ እና ሌሎች ከገጽ 116-124)
Blogger Comment
Facebook Comment