“አራሽ፣ ተኳሽ፣ ቀዳሽ”:- አደጋ ላይ የወደቀው አገራዊ የኅልውና ቀመር


✍ መንግሥቱ ጎበዜ 

“አራሽ፣ ተኳሽ፣ ቀዳሽ”:-ታሪካዊ አገር በቀል ዕሴት

በኢትዮጵያ የታሪክና የባህል አውድ ውስጥ "አራሽ፣ ተኳሽ፣ ቀዳሽ" የሚለው ብሂል የማኅበረሰቡን ህልውና የሚደግፉ ሦስት መሠረታዊ ምሶሶዎችን የሚገልጽ አገር በቀል ዕሴት ነው። ይህ ጽንሰ-ሐሳብ በዋናነት ሦስት የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ማለትም ገበሬውን፣ ወታደሩንና ካህኑን የሚወክል ቢሆንም፣ ባሕላዊ ትርጓሜው ግን ከዚያ የላቀ ጥልቅ ፍልስፍና አለው። በጥንታዊቷ ኢትዮጵያ ሥርዓት ውስጥ አንድ ሰው "ሙሉ ሰው" የሚባለው ወይም አንዲት ሀገር ጠንካራ ናት የምትባለው እነዚህ ሦስት አካላት ተግባራቸውን በቅንጅት ሲወጡ ብቻ ነው። አራሹ በሥራው ራሱንና ማኅበረሰቡን በመመገብ የኢኮኖሚ ዋስትና ሲሆን፣ ተኳሹ በጀግንነቱ የሀገርን ሉዓላዊነትና ድንበር ያስከብራል፣ ቀዳሹ ደግሞ በጸሎቱና በሥነ-ምግባር ትምህርቱ ሕዝቡ ከፈጣሪውና ከባሕላዊ ማንነቱ ጋር ተስማምቶ እንዲኖር ያደርጋል። እነዚህ ሦስቱ ተደጋጋፊ እንጂ ተነጣጣይ ባለመሆናቸው፣ አንዱ ከሌላው ቢጎድል የሀገር ህልውና አደጋ ላይ ይወድቃል።

ይህ የሦስትነት ቀመር አንድን ዜጋ በሥራው ጠንካራ፣ ለሀገሩ ቆራጥ፣ እንዲሁም ለሕሊናው የታመነ አድርጎ የመቅረጽ ጥበብ ነው። በአንድ ሰው ማንነት ውስጥ ሲተረጎምም የሥራን አስፈላጊነት፣ የሀገርን ሉዓላዊነት እና የመንፈሳዊነትን ሚዛን በአንድ ላይ አጣምሮ ይይዛል። በቀደመው ዘመን "አራሽ፣ ተኳሽ፣ ቀዳሽ" የሚሉት ባሕርያት በአንድ ሰው ውስጥ ተዋህደው የሚገኙ ዕሴቶች ተደርገውም ይወሰዱ ነበር። ለምሳሌ ታሪካዊ አርበኞቻችን በጦርነት ወቅት ተኳሽ፣ በሰላም ጊዜ አራሽ፣ በሃይማኖታዊ ሕይወታቸው ደግሞ ቀዳሽ በመሆን ሦስቱንም ሚናዎች በአንድነት ይወጡ ነበር። ይህም እጅ ለሥራ፣ ወኔ ለሀገር፣ ሕሊና ደግሞ ለጸሎትና ለሥነ-ምግባር መዋል እንዳለበት የሚያስተምር የላቀ የሕይወት መመሪያ ነው።

ከእነዚህ ዕሴቶች መካከል "አራሽ" ለሀገር የጀርባ አጥንትና የልማት መሠረት ሲሆን፣ ይህም በመጀመሪያው መጽሐፍ ዘፍጥረት ላይ እግዚአብሔር አዳምን በኤደን ገነት ውስጥ "ያበጃትና ይጠብቃት ዘንድ" ካስቀመጠበት መለኮታዊ ኃላፊነት ጋር ይያያዛል። "ተኳሽ" ደግሞ የሀገር አጥር በመሆን መስዋዕትነትንና ሰላምን ይወክላል፤ ኢትዮጵያም ነፃነቷን ጠብቃ የቆየችው በዚህ ሕዝባዊ ደጀንነት ነው። "ቀዳሽ" በተራው የማኅበረሰቡ ሕሊና ሆኖ ሰላምን፣ ጸሎትንና ሞራልን ጠብቆ ያቆያል። ባጠቃላይ ይህ አገር በቀል ዕሴት ሥራን ከጀግንነት፣ እውቀትን ከሃይማኖት ጋር በማጣመር የተገነባ የሰው ልጅ ሙሉዕነት መግለጫ ነው።

ሦስቱ ምሰሶዎች በዘመናዊ እይታ

በዘመናዊው ዓለም "አራሽነት" ከባሕላዊው የእርሻ ሥራ በዘለለ የሥራ ክብርንና ራስን የመቻል ጥበብን ያመለክታል። አንድ ዜጋ የሚሰማራበት የሥራ መስክ ምንም ይሁን ምን (በቢሮ፣ በንግድና በመሳሰሉት) በትጋት ውጤታማ መሆኑ የአራሽነት መገለጫ ነው። "አራሽ" ዜጋ ከጥገኝነት ወጥቶ ለራሱና ለቤተሰቡ የሚተርፍ በመሆኑ፣ ለሀገሩ የኢኮኖሚ ዋስትና እንጂ ሸክም አይሆንም። በመሆኑም ዘመናዊ አራሽነት ማለት በማንኛውም የሙያ ዘርፍ ምርታማ በመሆን ለሀገር ዕድገት መሠረት መሆን ማለት ነው።

በተመሳሳይ መልኩ፣ የ"ተኳሽነት" ትርጉም በዘመናዊው ዕሳቤ መሣሪያ ከመያዝም ተሻጋሪ ነው። ይልቁንም በማንኛውም አጋጣሚ የሀገርን ክብር፣ ደኅንነትና ጥቅም በዕውቀትና በሐሳብ መጠበቅን ይመለከታል። በሐሰተኛ ወሬዎችና በጥላቻ ንግግሮች ማኅበረሰቡ እንዳይፈርስ መታገል፣ ለእውነትና ለፍትሕ መቆም፣ እንዲሁም የዜግነት ግዴታን በኃላፊነት መወጣት የዘመናዊ “ተኳሽነት” ተግባራት ናቸው። ይህም የሀገርን ዳር ድንበር ብቻ ሳይሆን ባህልን፣ ቅርሷንና ጥቅሟን ከሚጋፉ የሐሰት ምሽጎች ሁሉ በንቃት የመከላከል ጥበብ ነው።

"ቀዳሽነት" ደግሞ ከመንፈሳዊ አገልግሎት ባሻገር ለፈጣሪና ለሕሊና የታመነ ሕይወት የመምራት መርህ ነው። ይህም በቅንነት መኖርን፣ ለሌሎች መልካም ማሰብን እና ከክፋትና ከተንኮል መራቅን ይጨምራል። በተለይም ከሙስናና ከብልሹ አሠራር በመራቅ ማኅበረሰቡን በሰላምና በሞራል የሚያንጽ ሥራ መሥራት የቀዳሽነት ዋነኛው መገለጫ ነው። 

ባጠቃላይ አራሽነት በሥራ ራስን መቻልን፣ ተኳሽነት ለእውነትና ለሀገር መቆርቆርን፣ ቀዳሽነት ደግሞ በሥነ-ምግባር የታነጸ ሕይወትን በመወከል የአሁኑን ትውልድ ለታላቅነት የሚያበቁ የሕይወት መመሪያዎች ናቸው።

“አራሽ”፣ “ተኳሽ”ና “ቀዳሽ” በትናንትና በዛሬ መካከል

በጥንቱ ሥርዓት "አራሽ" የሀገር የጽናት መገለጫና ለም መሬቱን በላቡ አልምቶ ሀገር በምግብ ራሷን እንድትችል የሚያደርግ የህልውና መሠረት ነበር። ዛሬ ግን አራሹ የሰላም እጦትና የጦርነት ቀጥተኛ ሰለባ ሆኗል። በብዙ የሀገሪቱ ክፍሎች አርሶ አደሩ ከመሬቱ ተፈናቅሎ፣ በሰላም አርሶ የመሰብሰብ ዕድሉ እየጠበበ መጥቷል። በዚህም ምክንያት ምርታማነት በረሃብ ስጋትና በዋጋ ግሽበት ተተክቷል፤ ሀገርን ይመግብ የነበረው አራሽም በግጭት ሳቢያ የእርዳታ እጅ ጠባቂ ወደ መሆን ደረጃ ወርዷል።

የ"ተኳሽነት" ትርጉምም በተመሳሳይ መልኩ አቅጣጫውን ስቷል። በቀደመው ዘመን ተኳሽ ማለት ለሀገር ዳር ድንበር የሚቆም፣ ግፍን የሚከላከልና ሉዓላዊነትን የሚያስከብር ጀግና ነበር። ዛሬ ግን ጥይቱ የውጭ ወራሪን ከመመከት ይልቅ በወንድማማቾች መካከል ወደሚደረግ የእርስ በርስ እልቂት ዙሯል። ተኳሽነት ለሕግና ለፍትሕ ከመቆም ይልቅ፣ በብሔርና በቡድን ተከፋፍሎ ንጹሐንን የሚያጠቃበት የ"ጠመንጃ አገዛዝ" መሣሪያ ሆኗል። የሰላማዊ ዜጎች ደም በገዛ ወገኖቻቸው ጥይት የሚፈስበት ደረጃ ላይ መድረሱ የዚህን ታላቅ እሴት መርከስ በግልጽ ያሳያል።

የማኅበረሰቡ የሕሊና መሪ የነበረው "ቀዳሽ" ዛሬ በዝምታና በፖለቲካ ተጽዕኖ ውስጥ ወድቋል። ድሮ ቀዳሽ ማለት ግፈኛን የሚገሥጽና ለእውነት የሚቆም የሞራል ልዕልና ነበረው፤ ዛሬ ግን የሃይማኖት ተቋማት በብሔር ፖለቲካ ተከፋፍለው የሰላም አስከባሪነት ሚናቸውን አዳክመዋል። ቀዳሹ ግፍን በድፍረት ከመገሠጽ ይልቅ "ዲፕሎማሲን" በመምረጡ፣ ሕዝቡ በመከራው ጊዜ የሚጠለልበት መንፈሳዊ ጥላ አጥቷል። በቀደመው ጊዜ ተኳሹ የሕሊና ዳኛ የሆነውን ቀዳሽ ይፈራና ይሰማ ነበር፤ ዛሬ ግን ቀዳሹ ስለፈራ ወይም ስለተገዛ የታጠቀው ኃይል የፈለገውን የሚያደርግበት ክፍተት ተፈጥሯል።

ባጠቃላይ "አራሽ፣ ተኳሽ፣ ቀዳሽ" የሚለው የኢትዮጵያዊነት ሦስትዮሽ ቀመር ዛሬ በፅኑ ሕሙማን ክፍል (ICU) ውስጥ ይገኛል። አራሹ ተርቧል፣ ተኳሹ ወንድሙን እየገደለ ነው፣ ቀዳሹ ደግሞ መንፈሳዊ ኃላፊነቱን ዘንግቷል። አምራቹ የኢትዮጵያ ሕዝብ (አራሹ) በተኳሹ ጥይትና በቀዳሹ ዝምታ መካከል ተፈርክሷል። አብዛኛው የቤተክርስቲያን አባቶች መንፈሳዊ በትራቸውን ጥለው የፖለቲካ ጋሻጃግሬ መሆናቸው የሀገሪቱን ማኅበራዊና ሞራላዊ መሠረት አናግቶታል።

የ “ቀዳሹ” ተግዳሮትና የቤተክርስቲያን ፈተና

የኢትዮጵያ ወቅታዊ ቀውስ ዋነኛ ምንጭ የመሪነት እንጂ የተከታይ ችግር አለመሆኑን መረዳት ለዘላቂ መፍትሔ መነሻ ነው። አብዛኛው ሕዝቡ ወይም "አራሹ" ዛሬም ለቤተክርስቲያኑ ታማኝ ቢሆንም፣ እውነትን በድፍረት የሚመሰክርና ትክክለኛውን አቅጣጫ የሚያሳይ "ቀዳሽ" (መሪ) በማጣቱ ለከፍተኛ ግራ መጋባት ተዳርጓል። ቤተክርስቲያን ዛሬ ያለችበትን "የእቶን እሳት" የፈጠሩት መሠረታዊ ምክንያቶች በርካታ ሲሆኑ፣ ዋነኛው ለዘመናት የቆየው የቤተ-መንግሥትና የቤተ-ክህነት ያልተመጣጠነ ቁርኝት ነው። ይህ ተቋማዊ ጥገኝነት አባቶች ገዥዎችን በድፍረት እንዳይገሥጹ እንቅፋት ከመሆኑም በላይ፣ በዓለማዊ ሹመትና በቤተ-መንግሥት ግብዣ መታለል የአባቶችን አንደበት በማሰር መንፈሳዊ ግዴታቸውን እንደ "ፖለቲካዊ ተቃውሞ" እንዲቆጥሩት አድርጓቸዋል።

ሌላው ትልቁና አደገኛው የወቅቱ ፈተና የብሔር ማንነትና የጎሳ ፖለቲካ መቅደሱን መውረሩ ነው። አባቶች ከወንጌላዊው ተልእኳቸው ይልቅ ለብሔራቸው ተወላጅነት ቅድሚያ መስጠታቸው የሀገሪቱን ቁስል በጎሳ መነጽር ብቻ እንዲመለከቱ አድርጓቸዋል። ይህም አንዲት ቤተክርስቲያን የጋራ የሰላም ድምፅ እንዳታወጣ አግዷታል። ከዚህ ጎን ለጎን የእምነት መላላትና የቁሳቁስ ምቾት መስፋፋት ሌላው ተግዳሮት ነው። እንደ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ያሉ የቀደሙት አባቶች ለሰማያዊ ሕይወት ሲሉ ለሞትና ለእስራት ራሳቸውን አሳልፈው ይሰጡ ነበር፤ የዛሬዎቹ ግን በምድራዊ ምቾትና በቁሳዊ ሀብት በመጠመዳቸው ያንን ኑሮ ሊያናጋ የሚችል የድፍረት ቃል መናገር ከብዷቸዋል። ይህም "መስቀሉን መሸከም" በ"ጥቅም መታለል" እንዲተካ አድርጓል።

በመጨረሻም የማኅበራዊ ሚዲያና የምዕመናን ያልተገራ ተጽዕኖ በቤተክርስቲያን አባቶች ላይ የፈጠረው ስጋት ቀላል አይደለም። ዛሬ አባቶች የሚፈሩት የመንግሥትን ጫና ብቻ ሳይሆን በማኅበራዊ ሚዲያ የተደራጀውንና ስም አጥፊውን "መንጋ" ጭምር ሆኗል። በቀላል ቁጥር የማይገመት ምዕመን አባቶች እውነትን እንዲናገሩ ከመጠየቅ ይልቅ የራሱን ብሔር ፖለቲካ እንዲደግፉለት ይፈልጋል። ይህ "የዲጂታል ስቅላት" ፍርሃት አንዳንድ የቤተክርስቲያን አባቶችን "ከመናገር ዝምታ ይሻላል" ብለው እንዲሸሹና ከመሪነት ሚናቸው እንዲቦዝኑ ሳያደርጋቸው አልቀረም። እነዚህ ተደራራቢ ተግዳሮቶች ቀዳሹን ለፈተና በመዳረጋቸው፣ በቤተክርስቲያንና በሀገር ህልውና ላይ ከፍተኛ አደጋ ፈጥሯል።

የ“ቀዳሹ” እና የ“አራሹ” ጥምረት እንደ መፍትሔ

ኢትዮጵያን አሁን ካለችበት መከራ ለማውጣት "አራሽ፣ ተኳሽ፣ ቀዳሽ" የሚለው ጥንታዊ እሴት በአዲስ መንፈስ ሊታደስ ይገባዋል። የሀገራችን ትንሣኤ የሚጀምረው ከመቅደስ ነው የሚል እምነት አለኝ።  የቀዳሹ (የመሪው) እና የምዕመኑ (የተከታዩ) ሚና በአንድነት መተሳሰር ይኖርበታል። አባቶች ዝምታቸውን ሰብረው እንደ ነቢዩ ናታንና እንደ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ለሰው ፊት ሳይራሩ እውነትን ሊመሰክሩ ይገባል። ቃላቸው ሰላምን የሚዘራ "አራሽ"፣ ጥላቻን የሚመታ "ተኳሽ" እንዲሆን፣ ሁኔታውን መረዳት ያለባቸው ከመንግሥት መግለጫ ሳይሆን ከምዕመኑ እንባ ተነስተው መሆን አለበት። ጦርነቱ በየትኛውም ወገን ይካሄድ፣ የቤተክርስቲያን አባቶች የሚፈሰው ደም የእግዚአብሔር አምሳያ የሆነው የሰው ልጅ ደም መሆኑን ተገንዝበው "ደም ማፍሰስ ይብቃ!" የሚል የእውነት ሰይፍ መምዘዝ ይኖርባቸዋል።

ኢትዮጵያ ዛሬም እንደ ጥንቱ "አራሽ፣ ተኳሽና ቀዳሽ" መሪዎችንና ዜጋዎችን ትፈልጋለች። አባቶች በመቅደስ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በአደባባይም የእውነት መብራት ሊሆኑ ይገባል። አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ችግር የፖለቲካ ብቻ ሳይሆን "የክፋት መንፈስ" ወይንም ከስጋዊ ጦርነት ባሻገር "መንፈሳዊ ውጊያ" የሰለጠነበት ወቅት መሆኑን  በቅጡመረዳት ያስፈልጋል።  ጥላቻ፣ በቀል እና የሰውን ህይወት ማቃለል ከመንፈሳዊ ድቀት የሚመጡ አደገኛ በሽታዎች ናቸው። ካህናት ይህንን ሁኔታ "ንስሐ የሚያስፈልገው ብሔራዊ ቀውስ" አድርገው በመረዳት ችግሩ መንፈሳዊ መፍትሔ ስለሚያስፈልገው ለዚያው ተግባር መትጋት ይጠበቅባቸዋል።

በሌላ በኩል፣ ምዕመናን በብሔር መከፋፈሉን አቁመው "እውነትን ለሚናገሩ አባቶቻችን ጋሻ እንሆናለን" የሚል ጽኑ ቃል ኪዳን መግባት አለባቸው። አንድ አባት ስለ እውነት በመቆሙ ምክንያት እስራት ወይም እንግልት ቢደርስበት፣ ምዕመኑ በሙሉ በአንድነት ቆሞ የሞራል፣ የሕግና የዲፕሎማሲ ድጋፍ ሊያደርግላቸው ይገባል። አንዳንድ ለእውነት የሚቆሙ አባቶች ከጀርባቸው የሚጸልይ ብቻ ሳይሆን የሚከላከልላቸው ሕዝብ እንዳለ ሲረዱ፣ የ"ተኳሽነት" ወይም የድፍረት መንፈሳቸው ሊታደስ ይችላል። ምዕመኑ የብሔር መነጽሩን አውልቆ አባቶችን በመንፈሳዊነታቸው ብቻ መቀበል ሲችል፣ መንግሥት ቤተክርስቲያንን በጎሳ ከፍሎ ለማዳከም የሚያደርገው ጥረትም ሊያከትም ይችላል።

መንግሥታዊ ተጽዕኖን መቋቋም የሚቻለው ካህኑ የሕዝቡ "ድምፅ" ሲሆን፣ ሕዝቡ ደግሞ የካህኑ "ጡንቻ" መሆን ሲችሉ ብቻ ነው። ምዕመናንና ካህናት "ከብሔራችን በፊት ቤተክርስቲያናችን" በሚል መርህ የአንድነት ግንባር መፍጠር አለባቸው። ይህም ቤተክርስቲያን ከፖለቲካ ተጽዕኖ ነፃ እንድትሆንና በሊቃውንትና በምሁራን የሚመራ፣ የሕዝቡን ስቃይ ለዓለም የሚያሳውቅ ጠንካራ የሚዲያ መዋቅር በመፍጠር ትግሉን ዓለማቀፋዊ ገጽታ እንዲኖረው ማድረግ ይቻላል። እንዲህ ዓይነት ተቋማዊ ጥንካሬ ሲኖር፣ ገዥዎች በሚፈጽሙት ግፍ በዓለም ፊት ተጠያቂ እንደሚሆኑ ተረድተው የአባቶችን ድምፅ ለማዳመጥ ይገደዱ ይሆናል።

ዛሬ ኢትዮጵያ የምትፈልገው የቢሮክራሲ ጳጳሳትን ሳይሆን፣ እንደ ዮሐንስ መጥምቁ በበረሃ የሚጮህ ድምፅ የሚሆኑና ለምቾታቸው ሳይሆን ለበጎቻቸው የሚሳሱ እረኞችን ነው። አባቶች ድፍረትን፣ ምዕመናን ደግሞ አንድነትን ሲይዙ ቤተክርስቲያን ከገባችበት "የእቶን እሳት" እንደ ወርቅ ነጥራ ትወጣለች።

የማጠቃለያ አስተያየት

ባጠቃላይ፣ የኢትዮጵያ ትንሣኤና ዘላቂ ህልውና የሚመሠረተው በሥራ በሚተጋ አራሽ፣ ለእውነትና ለሀገር በሚቆም ተኳሽ እንዲሁም የሀገር ሕሊና በሆነው ቀዳሽ መካከል በሚኖር ፅኑና የማይበጠስ ቅንጅት ላይ ነው። እነዚህ ሦስት ምሰሶዎች ተነጣጥለው የማይቆሙ፣ አንዱ ለሌላው ህልውና ዋስትና የሚሰጥባቸው የሀገር ማገርና የማዕዘን ድንጋዮች ናቸው። ዛሬ ሀገራችን የገጠማት ፈተና ከፖለቲካዊ ቀውስ ባሻገር፣ እነዚህ ሦስት የኅልውና መሠረቶች አቅጣጫቸውን እንዲስቱና መለኮታዊ እንዲሁም አገራዊ ተልዕኳቸውን እንዲዘነጉ ካደረጋቸው የሞራል ድቀትና የመንፈስ ዝለት ጭምር የሚመነጭ ነው።

አራሹ የልፋቱን ፍሬ ማግኘት ተስኖት ተርቦና ከመሬቱ ተፈናቅሎ፣ ተኳሹ ሰይፉን በወንድሙ ላይ መዞ የገዛ ወገኑን እያደነ፣ ቀዳሹም በዝምታ ተሸብቦና በሥጋዊ ፍርሃት ተውጦ የሞራል መሪነቱን በዘነጋበት በዚህ አስቸጋሪ ወቅት፣ ብቸኛው የመውጫ መንገድ ወደ ቀደመውና ወደ ታደሰው አገራዊ እሴታችን መመለስ ብቻ ነው። ይህ መመለስ ደግሞ በባዶ ቃላትና በምኞት ብቻ የሚመጣ ሳይሆን፤ አራሹ የሥራ ክብርንና የሰላም ዋስትናን የሚያገኝበት፣ ተኳሹ የሕዝብ ደጀንነቱን በተግባር የሚያረጋግጥበት፣ ቀዳሹም እንደ ብርሃን በማኅበረሰቡ መካከል ሆኖ ያለ አንዳች ፍርሃት እውነትን የሚመሰክርበት ተግባራዊ ጉዞ ሲጀመር ነው።

ለዚህ ታሪካዊ ሽግግር እውን መሆን የካህናትና የምዕመናን ጥምረት ማጠናከር ወሳኙን ሚና ይጫወታል። አባቶች (ቀዳሾች) ድፍረት የሚያገኙት ምዕመኑ እንደ ጋሻ ከጀርባቸው ሲቆም ሲሆን፣ ሕዝቡም (አራሹ) ተስፋ የሚሰንቀው አባቶች ከብሔርና ከፖለቲካ ወገንተኝነት ወጥተው የሁሉ አባት መሆናቸውን ሲያረጋግጡ ነው። “ድር ቢያብር አንበሳ ያስር” እንደሚባለው ሁሉ፣ ይህ የአባቶችና የልጆች ጥምረት ወቅታዊውን የቤተክርስቲያንና የሀገር ችግር ለመፍታት ጊዜ ሊሰጠው የማይገባ ወሳኝ ተግባር ነው።
Share on Google Plus

ስለ የተለጠፈበት ቀን

    Blogger Comment
    Facebook Comment