✍ መንግሥቱ ጎበዜ
ውድ ወንድሜ አሕመዲን ጀበል፤
በቅድሚያ የከበረ ሰላምታዬን አቀርብለዎታለሁ። ይህንን መልዕክት የምጽፍለዎት በቅንነት እና በኢትዮጵያዊ ጨዋነት በበጎ ይመለክቱት ዘንድ በማሳሰብ ጭምር ነው።
እስካሁን ባለው ጊዜ ውስጥ የጻፏቸውን መጻሕፍት፣ በማኅበራዊ ሚዲያ ያስተላልፏቸውን መልዕክቶች እና እንደ አንድ ሙስሊም አንቂ እንዲሁም የልዩ ልዩ እንቅስቃሴዎች አስተባባሪነተዎ የምታከናውኗቸውን ተግባራት ለመታዘብ ችያለሁ። ይህንን ደብዳቤ ለመጻፍ ያነሳሳኝ ዋና ምክንያትም፣ በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ የምታስተላልፏቸው መልእክቶች በተለያዩ እምነቶች ውስጥ ሆነው በአንዲት ሀገር ጥላ ስር ለዘመናት በፍቅርና በሰላም የኖሩ ኢትዮጵያውያንን የጋራ እሴቶች እየጎዱ መሆኑን በመረዳቴ ነው።
በእኔ ግንዛቤ፣ እስካሁን ያወጧቸው ጽሑፎች፣ የሰጧቸው ሥልጠናዎችና መግለጫዎች ከአንድነት ይልቅ ልዩነትን፣ ከአብሮነት ይልቅ መነጣጥልን፣ ከፍቅር ይልቅ ጥላቻን እና ከመገንባት ይልቅ ማፍረስ ላይ ትኩረት ያደረጉ ናቸው ብል የተሳሳትኩ አይመስለኝም። በጽሑፎቸዎ ውስጥ በብዛት የሚስተዋሉት በሐሰት ትርክት ላይ የተመሰረተ የታሪክ ሽሚያ፣ ሀገር ጠብቃ ያቆየችውን ነባር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንና መንግሥታዊ ታሪክን እንደ ጨቋኝ አድርጎ ማቅረብ፣ እንዲሁም ስለ አክራሪነት የሚሰነዘሩ ትችቶችን ለጠቅላላው ሙስሊም ማኅበረሰብ እንደተነገሩ አድርጎ የመተርጎም አዝማሚያዎች እጅግ አሳሳቢ ናቸው።
እንደ ታሪክ ተማሪነቴ፣ ከዚህ ቀደም በማኅበራዊ ሚዲያ ያሰራጨኋቸውን ታሪክ ነክ ጽሑፎቼን ሳይመለከቷቸው እንዳልቀሩ እረዳለሁ፤ በቅርብ ጊዜ ያወጧቸው ጽሑፎቸዎም ይህንኑ ፍንጭ ይሰጣሉ። ዋናው ቁምነገር ግን በእውነት ላይ የተመሠረተና ለሁሉም የሚበጅ አዎንታዊ ሐሳብ ላይ ብናተኩር ለትውልድም ሆነ ለሀገር የሚተርፍ ፋይዳ ይኖረዋል በሚል ዓላማ የቀረበ ነው።
በታሪክ መሠረት ወይም በተጨባጭ ማስረጃ ያልተደገፈውና 'ነጃሺ' በሚባል ንጉሥ ዙሪያ ለሚነሳው ሀሰተኛ ትርክት ከዚህ ቀደም ምላሽ የሰጠሁ ሲሆን፣ እውነቱን ለማወቅ ለሚፈልግ ሁሉ እርሱን ማንበብ ጠቃሚ እንደሚሆን አምናለሁ [የቆየ ሰነድ] ከዚህ ባለፈም፣ በሀገራችን ረጅም ታሪክ ውስጥ እርሰዎ ከሚያስተጋቡት በተቃራኒ፤ ማን ጎጂና ማን ተጎጂ፣ ማን ገዳይና ማን ሟች፣ ማን ጠፊና ማን አጥፊ እንደነበረ ሕሊናዎ ያውቀዋል ብዬ ባስብም በዚህም ጉዳይ ላይ በማኅበራዊ ሚዲያ በቅርብ ያጋራሁትን ዝርዝር የታሪክ ማስረጃ ታነቡት ዘንድ በድጋሜ እጋብዘዎታለሁ።
ይሁንና አንዳንዶቹን የታሪክ እውነታዎች ዳግም ማስታወስ ተገቢ መስሎ ታይቶኛል፤ ስለሆነም ቀጥሎ ለቀረቡት ጥያቄዎች መልስ ይኖርዎት ይሆን ብዬ እሞግታለሁ። የእነዚህ ጥያቄዎች ዓላማ፣ እርሰዎ በተደጋጋሚ በማኅበራዊ ሚዲያ እያጋሩት ያለው 'የበዳይ-ተበዳይ' እና 'የጨቋኝ-ተጨቋኝ' ትርክት፣ በእውነታው ዓለም የተገላቢጦሽ መሆኑን አንባቢ እንዲረዳው ጭምር ነው።
ወደ ጥያቄዎቸ ስገባ፤ በጥንቱ ዘመን የቀይ ባሕር የንግድ መስመር ላይ አደጋ በመጣልና የኢኮኖሚ አቅሙን በማዳከም የአክሱም መንግሥት እንዲበታተን ምክንያት የሆነው ማን እንደሆነ አያውቁ ይሆን? በመካከለኛው ዘመን ደግሞ ሀገሪቱን በተለያዩ አቅጣጫዎች ወጥሮ ሰላም በመንሳት፣ የነበረው መንግሥት ቋሚ መቀመጫ እንዳይኖረውና ተረጋግቶ እንዳይኖር ያደረገው ማን ነበር? በቱርክና በደቡብ ዓረቢያ መንግሥታት ድጋፍ ለ15 ዓመታት ሙሉ ክርስቲያኑን ሲያርድ፣ መተኪያ የሌላቸውን የሀገርና የቤተክርስቲያን ቅርሶች ሲያወድም፣ እንዲሁም ምርኮኛ ኢትዮጵያዊ ክርስቲያኖችን እንደ ሸቀጥ ወደ ዓረብ ሀገራት ሲሸጥና ሲለውጥ የነበረው ማን እንደሆነ እናስታውስዎት ይሆን?
ከኢጣሊያ ኩባንያ ጋር በመመሳጠር የዓሰብን ወደብ አሳልፎ የሸጠው፣ በአፄ ዮሐንስ ዘመነ መንግሥት በተደጋጋሚ ጥቃት በመሰንዘር ሀገር ላይ ጉዳት ያደረሰው፣ አልፎ ተርፎም ፋሽስት ኢጣሊያ ሀገራችንን በወረረች ጊዜ ከወራሪው ጋር በመተባበር የሀገር ክህደት የፈጸመው ማን ነበር? የቅኝ ገዥዎችን አጀንዳ በመቀበልና በዓረብ ሀገራት በመታገዝ፣ በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመን ኤርትራ እንድትገነጠል ሲሠራ የነበረው ማን እንደሆነ ታሪክ አላነበቡ ይሆን?
በደርግ ዘመን የነበረውን የፖለቲካ ትርምስ እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም፣ የኢትዮጵያን ቤተክርስቲያን ለማዳከም 'ድንጋይ ሲያቀብል' የነበረው ማን እንደሆነ እንንገርዎት? በ1969 ዓ.ም የሶማሊያ ወረራ ወቅት፣ ሀገር በጠላት ስትወረር ከዚያድ ባሬ ጦር ጋር ወግኖ የገዛ ሀገሩን የወጋው ማን ነበር? ከዘመነ ኢሕአዴግ ጀምሮ 'በእኩልነትና በነፃነት' ስም በተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች—በተለይም በጂማ፣ በሐረር፣ በሶማሊያ፣ በባሌ፣ በአርሲ፣ በአጣየ፣ በከሚሴ እና በመሳሰሉት ቦታዎች ንጹሐን ኢትዮጵያውያን ሲገደሉ፣ ሲፈናቀሉና ሲሳደዱ ዋነኛ ተዋናዮች እነማን ነበሩ? በአሁኑ ወቅትስ ያለምንም ማቋረጥ በምድረ አርሲ በኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች ላይ 'የማጽዳት' ዘመቻ እያካሄደ ያለው ማን ነው?
ከኢትዮጵያ አልፎ ከሀገር ውጭስ በኢትዮጵያውያን ላይ የመከራ ዶፍ እያዘነበ ያለው ማነው? ሴት እህቶቻችን በስደት ዘግናኝ መከራና ስቃይ የሚደርስባቸው የት እንደሆነ አያውቁ ይሆን? በተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች ወገኖቻችንን ለመፍጀት ጥቅም ላይ የሚውሉ ድሮኖችና መሰል ፀረ-ሰው መሣሪያዎችስ የሚመጡት ከየትኛው ሀገር እንደሆነ ማስታወሱ ተገቢ ይሆን?
ውድ ወንድሜ ሆይ፤ በሚዲያና በአደባባይ መርሐግብሮች ላይ በእርሰዎ እና በመሰሎቸዎ የሚተላለፉ ጥንቃቄ የጎደላቸው መልዕክቶች ሰላምን የሚያውኩ በመሆናቸው በቀላሉ የሚታለፉ አይደሉም። ለምሳሌ በቅርቡ 'ነጃሺ ለሀገር' በሚል በተከናወነው መርሐግብር ወቅት፣ መስቀል አደባባይን 'አብዮት አደባባይ' ወይም 'ኢድ አደባባይ' ብላችሁ ለመጥራት የሄዳችሁበት ርቀት የሚገርምና እጅግ የሚያሳዝን ነበር። ኢትዮጵያን የዓረብ ሊግ አባል ለማድረግ ያላችሁ ህልምና የምታደርጉት ድካምም ከብዙዎች የተሰወረ አይደለም።
በአንድ ወቅት በትልቅ የሀገር ሚዲያ ቀርበው፣ ለሁለት ሺህ ዓመታት የዘለቀውንና የኢትዮጵያ ልዩ ገጽታ የሆነውን የዘመን አቆጣጠር 'የክርስትና መሠረት ስላለው መቀየር አለበት' ብለው መሟገተዎ የአደባባይ ምስጢር ነው። በተጨማሪም በቤተልሔም ታፈሰ ሚዲያ ላይ ቀርበው፣ በጥንቱና በመካከለኛው ዘመን ኢትዮጵያ የሚባል ሀገር እንዳልነበረ በድፍረት የተናገሩት ንግግር እጅግ አሳፋሪ ነበር። 'ክርስትና ወይስ እስልምና ወደ ኢትዮጵያ ቀድሞ የገባው?' ለሚለው ጥያቄ የሰጡት ምላሽም በተመሳሳይ እጅግ አስገራሚ ነው። ከአክሱም ውጭ ባለው የኢትዮጵያ ክፍል እስልምና ቀድሞ እንደገባ አድርገው ሲናገሩ ትንሽ እንኳ ሀፍረት አይታይበዎትም ነበር /ከታች የተያያዘውን link ይመልከቱ/።
ለነገሩ ቅጥ ያጣ ድፍረታችሁንና በውሸት ምን ያኽል ርቀት አንደምትጓዙ ባለፈው ወር "እስልምና በኢትዮጵያ ከቅድመ ክርስቶስ እሰከ ዛሬ" በሚል በወሀብያ ባልንጀራዎ አብዱል ጀሊል ዐሊ ካሳ የተጻፈውን ግዙፍ የተረት "መጽሐፍ" በትልቅ አዳራሽ ተሰብስባችሁ ስታስመርቁ ተገንዝበናል። ለውሸትም እኮ ልክና መጠን አለው፤ ይኽን ዓይነቱን ግዙፍ ውሸት ሌላውም ዓለም ይታዘበናል ማለት እኮ ይገባ ነበር። እናንተ ምን ታደርጉ "ውሸት ሲደጋገም እውነት ይሆናል" የሚለውን ብሂል እንደ ስልት ተጠቅማችሁ በነጃሺው ልብ ወለድ ድርሰት ያሳካችሁትን በሌላውም ለመድገም አስባችሁ ይሆናል።
ወንድምዓለም ተጨባጭ ማስረጃ በማቅረብ እንጂ በጉልበትና በፈጠራ ድርሰት የታሪክ ባለቤት መሆን አይቻልም። እርሰዎና መሰሎቸዎ በምታሰራጩት ኃላፊነት በጎደለው የሐሰት ትርክት የኢትዮጵያን የታሪክ እውነታ መቀየር ፈጽሞ የማይቻል መሆኑን ልታውቁት ይገባል።
ይፋ የሆኑትና በተለያዩ ጊዜያት የሰጧቸው ሥልጠናዎችም ቢሆኑ አብሮነትን የሚሸረሽሩና የሚያሳቅቁ ናቸው። ከዚህም ባለፈ ውስጥ ለውስጥ እንደምታራምዱት በሚነገረው 'ጸረ-ሴማዊ' እንቅስቃሴ ምክንያት፣ ብዙዎች መርጠው ባልተገኙበት የብሔር ታርጋ ለእልቂትና ለስደት መዳረጋቸውን የሚያጡት አይመስለኝም። በቅርቡ የእምነት መሪያችሁ በኢራን ኤምባሲ ተገኝተው ልቅሶ መድረሳቸውም የሚያስተላልፈው መልዕክት ለሁላችንም ግልጽ ነው።
ስለሆነም ወንድሜ ሆይ፤ ከጥላቻና ከመለያየት ማንም አትራፊ የለምና፣ ሁላችንም ያለንን አቅም ለትውልድ ግንባታና ለሀገር ልማት በሚጠቅም መንገድ ብናውለው መልካም ነው። ይህ መልእክቴ እርሰዎንና በአመለካከተዎ ዙሪያ ያሉትን ጥቂት ግለሰቦች እንጂ፣ በጎውንና ሰላማዊውን፤ ከወሀብያ ውጭ ያለውን ብዙኀኑን የኢትዮጵያ ሙስሊም ማኅበረሰብ ፈጽሞ የማይመለከት መሆኑን ልገልጽለዎት እወዳለሁ።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ለሙስሊም ወገኖቻቸው ምን ያህል አክብሮትና ፍቅር እንዳላቸው በቅርብ ያለፉትን የቀዳማዊ ሙፍቲ ሐጅ ዑመር እድሪስ የሽኝት መርሐግብር ማስታወስ በቂ ነው። በዚህ ወቅት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርካችን ጨምሮ እጅግ ብዙ ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች እንባ በማፍሰስ ጭምር የሐዘን ተካፋይ የነበሩ መሆናቸው በአደባባይ የታየ ነው። መዳበር ያለበትና ለሀገራችን የሚበጀው እንደዚህ ዐይነት ልባዊ ኩነቶችን ማበረታት ነው።
በመጨረሻም፤ ታሪክ የጋራ መስተዋታችን ነው፤ በዚህ መስተዋት ውስጥ ራሳችንን በምናይበት ጊዜ፣ ለቀጣዩ ትውልድ የምናስተላልፈው ቅርስ የጥላቻና የልዩነት ግድግዳ ሳይሆን፣ የመከባበርና የሰላም ድልድይ ሊሆን ይገባል። በጎም ይሁን መጥፎ ያሳለፍነው ታሪካችን በሙሉ የጋራችን ነው። እኔ ይህን ደብዳቤ የጻፍኩለዎ በልዩነት ውስጥ ሆነን እንኳ፣ በጋራ የምንኖርባት ሀገር ሰላም ይበልጥ እንዲጠበቅና እውነታዎች ላይ ተመርኩዘን ለጋራ መግባባት ሁላችንም የበኩላችንን አስተዋጽኦ እንድናበረክት ወንድማዊ መልዕክቴን ለማድረስ ነው። በቀናነትና በኢትዮጵያዊ ወንድማማችነት መንፈስ፣ እነዚህን ነጥቦች በአንክሮ እንድታጤኗቸው እጋብዘዎታለሁ።
ከሰላምታ ጋር!
አክባሪ ወንድመዎ
Blogger Comment
Facebook Comment