“ጅራፍ ራሱ ገርፎ ራሱ ይጮኸል”የውሀብያ እስላም ‘ተበዳይነት’ ትርክት እና ታሪካዊ እውነታው


✍ መንግሥቱ ጎበዜ

ምክንያተ ጽሑፍ

ታሪካዊ እውነታው በተገላቢጦሽ ቢሆንም የአክራሪው ውሀብያ "ተበዳይነት ትርክት" በኢትዮጵያ ለዘመናት የቆየውን አብሮ የመኖር እሴትና የሀገረ መንግሥት ሂደት የሚፈታተን አሳሳቢ ጉዳይ ሆኗል። ይህ ትርክት "በታሪክ ተጨቁነናል፣ የእምነት ነፃነት አጥተናል" የሚሉ መሠረተ ቢስ ክሶችን ለፖለቲካዊና ለርዕዮተ ዓለም ማስፋፊያነት በመጠቀም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናትና በምእመናን ላይ ለሚፈጸሙ ዘግናኝ ጥቃቶች እንደ ምክንያትና እንደ ሽፋን እየቀረበ ይገኛል። ስለሆነም የዚህ ጽሑፍ ዋና ዓላማ የውሀብያ አስተምህሮ የሚያስተጋባው "የተበዳይነት ትርክት" ከታሪክ እውነት የራቀ መሆኑን በግልጽ ማሳየት ነው። ጽሑፉ እስልምና በኢትዮጵያ ታሪክ ከጥንት እስከ ዛሬ የነበረውን ጉዞና ከቤተክርስቲያን ጋር የነበረውን ግንኙነት አጠቃላይ ሥዕል በማሳየት አንባቢዎች እውነታውን በራሳቸው መንገድ እንዲገነዘቡ ታስቦ የቀረበና በዋና ዋና ነጥቦች ላይ ብቻ ትኩረት ያደረገ ነው። ታሪኩ ዐባይን በጭልፋ እንዲሉ ለቅምሻ ያህልና ማሳያ ይሆን ዘንድ ብቻ ተቆንጥሮ የቀረበ መሆኑን ማስገንዘብ እወዳለሁ። 

የሐሰተኛ ተበዳይነት ትርክት አደጋዎች

በውሀብያ የሚቀነቀነው የሐሰተኛ ተበዳይነት ትርክት በሀገር ብሔራዊ ደኅንነትና በቤተክርስቲያን ህልውና ላይ የተደቀነ ከፍተኛ አደጋ ነው። ቤተክርስቲያኒቱን እንደ "ታሪካዊ ጨቋኝ" አድርጎ የመሳል ስልታዊ አካሄድ በእሷ ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች በጽንፈኛ ኃይሎች ዘንድ እንደ "ፍትሐዊ እርምጃ" እንዲቆጠሩ በማድረግ ጥቃትን ሕጋዊ የማስመሰል አደጋ እየፈጠረ ነው።  በተጨማሪም "ተበድለናል" የሚለው ሰበብ የቤተክርስቲያኒቱን ጥንታዊ ርስትና ቅርሶች ለመንጠቅ እንዲሁም በምእመናን ላይ ዜግነታዊ መገለልና የመብት ጥሰት ለማድረስ እንደ ስልታዊ መሣሪያ በማገልገል ላይ ይገኛል። ይህ ትርክት ለሺህ ዓመታት አብሮ የኖረውን ሕዝብ በ"በዳይና ተበዳይ" ጎራ በመከፋፈል ማኅበራዊ ትስስሩን ለማላላትም ምክንያት ሆኗል። እንዲህ ያለው የውስጥ መከፋፈል ደግሞ የኢትዮጵያን መዳከም ለሚፈልጉ የውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት ምቹ በር ይከፍታል። በተለይም የውሀብያ አስተምህሮ ለሀገራዊ እሴቶች የሚሰጠው ቦታ ዝቅተኛ መሆን፣ ዜጎች ከሀገራቸው ይልቅ ለድንበር ተሻጋሪ ርዕዮተ-ዓለማዊ ትስስር ታማኝ እንዲሆኑ በማድረግ ብሔራዊ አንድነትን ይሸረሽራል። ይህም ወጣቶችን በተሳሳተ መንገድ በመግራት ለአመጽ፣ ለጽንፈኝነትና ለደኅንነት ስጋት እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል።
 
አረባዊ የጸረ ኢትዮጵያ አመለካከት ትውፊታዊ መነሻዎች

ኢትዮጵያ በሙስሊም አረቦች ዘንድ እንደ ‘ጸረ-እስልምና’ ኃይል እንድትታይ የሚያደርጉ ሁለት መሠረታዊ እስላማዊ ትውፊቶች አሏቸው። የመጀመሪያው፣ ሙሐመድ በተወለደበት (በ570 ዓ.ም) ‘የዝሆን ዓመት’ ተብሎ በሚታወቀው በዚያው ዓመት አብርሃ የተባለው ኢትዮጵያዊ ካዕባን ለማፍረስ በዝሆኖች የታጀበ ጦር ወደ መካ መርቷል የሚል ነው። ሁለተኛው ደግሞ፣ ኡሁድ ተብሎ በሚታወቀው ጦርነት ወቅት (በ632 ዓ.ም) ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች በነቢዩና በተከታዮቻቸው ላይ ጥቃት በመሰንዘር ለሙሐመድ መቁሰል ምክንያት ሆነዋል የሚለው ትረካ ነው። በእነዚህ ክስተቶች ሳቢያ፣ ኢትዮጵያውያን በካዕባና በነቢዩ ላይ ጥቃት እንደሰነዘሩ ተደርገው ስለሚቆጠሩ አገሪቱ ‘መጥፋት ወይም መስለም’ አለባት የሚል ጽንፈኛ አመለካከት እንዲሰርጽ መነሻ ሆኗል ይባላል። እነዚህ ጉዳዮች በጥንታውያን ሙስሊሞች ዘንድ ለኢትዮጵያ አሉታዊ አመለካከት እንዲፈጠርና እንደ ስጋት እንዲመለከቷት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጋቸው ይነገራል። 

የጳጳሳት ሹመትና የግብፅ እስላማዊ መሪዎች ተፅዕኖ

ኢትዮጵያ ጳጳሳትን ከግብፅ እስክንድርያ መንበር ለማግኘት የነበራት ጥገኝነት ለዘመናት ለከባድ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጫና ዳርጓታል። የግብፅ ሙስሊም ሡልጣኖች የጳጳሳትን ሹመት እንደ ስልታዊ መሣሪያ በመጠቀም ከኢትዮጵያ ነገሥታት ከፍተኛ ገጸ-በረከት ያስገብሩ ነበር። ይህም መንፈሳዊውን ጥሪ ወደ ንግድ ልውውጥ ከመቀየሩ ባለፈ፣ የካይሮ ቤተ-መንግሥት በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ እንዲገባ በር ከፍቷል። ለዚህም እንደ ማሳያ በ11ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ ላይ አብዱም የተባለ ግብፃዊ ሙስሊም "ጳጳስ ቄርሎስ ነኝ" የሚል የሐሰት ደብዳቤ ይዞ በመምጣት ቤተክርስቲያኒቱን ለማታለልና የእስልምናን ጥቅም ለማስፋፋት ጥሯል። በተመሳሳይ ሁኔታ፣ በግብፅ ሱልጣን ተጽዕኖ ተሹመው የተላኩት አባ ሳዊሮስ የተባሉት ጳጳስ በኢትዮጵያ ቆይታቸው ሰባት መስጊዶች እንዲገነቡ በማመቻቸት ለሙስሊሙ ማኅበረሰብ ግልጽ ድጋፍ ሲያደርጉ ነበር። ይህ የውጭ ተፅዕኖ እስከ 19ኛው ክፍለ ዘመን ድረስ የቀጠለ ሲሆን፣ በ1868 ዓ.ም የግብፁን ወረራ ተከትሎ ዐፄ ዮሐንስ 4ኛ አቡነ አትናቴዎስ የተባሉትን ጳጳስ ከወራሪው የግብጽ ኃይል ጋር በማበር ጠርጥረዋቸው ከመንግሥት ጉዳዮች እንዲገለሉ አድርገዋቸዋል።

እስልምናና ካህናት ነገሥታቱ

በ12ኛው ክፍለ ዘመን የነበሩት የኢትዮጵያ ካህናት ነገሥታት፣ ለሌላ እምነት ተከታዮች በተለይም ለሙስሊሞች በነበራቸው ርኅራኄና ሰብአዊ አመለካከት በአረብ የታሪክ ድርሳናት ሳይቀር ይወደሳሉ። እነዚህ ምንጮች ነገሥታቱ በግዛታቸው የሚኖሩ የሌላ እምነት ተከታዮችን በነፃነት እንዲኖሩ እንጂ እምነታቸውን እንዲቀይሩ እንደማያስገድዱ በአድናቆት መዝግበዋል። ይህ ጥበብ የተሞላበት አመራር ይበልጥ ጎልቶ የታየው በመስቀል ጦርነት ወቅት ኢትዮጵያ በያዘችው ሚዛናዊና ገለልተኛ አቋም ነበር። ነገሥታቱ የጦርነቱ ተሳታፊ እንዲሆኑ ቢጋበዙም በራሳቸው የውስጥ ጉዳይ አተኩረው ገለልተኛ መሆን መርጠዋል። ታዋቂው የእስልምና መሪ ሱልጣን ሳላህ አድ-ዲን በ1187 ዓ.ም. ኢየሩሳሌምን በተቆጣጠረ ጊዜ፣ የኢትዮጵያ ንጉሥ በወሰደው ሰላማዊ መንገድ እጅግ በመደሰቱ ለቅዱስ ላሊበላ በቅድስት ሀገር ውስጥ በርካታ ወሳኝ ቦታዎችን በስጦታ አበርክቷል። በዚህም ምክንያት በኢየሩሳሌም ይኖሩ የነበሩ ኢትዮጵያውያን ልዩ ክብርና ድጋፍ እንዲያገኙ ተደርጓል። ይህም የኢትዮጵያ መሪዎች ለሰላምና ለእኩልነት የነበራቸውን የጸና አቋም በዓለም አቀፍ ደረጃ ያስመሰከረ ታሪካዊ ክስተት ነው።

የአሕመድ ግራኝ ጦርነትና ጥፋት

በ16ኛው ክፍለ ዘመን ለዐሥራ አምስት ዓመታት የዘለቀው የአሕመድ ግራኝ ጦርነት፣ በኢትዮጵያ ክርስትናና ብሔራዊ ህልውና ላይ የማይፋቅ ጥልቅ የታሪክ ቁስል ጥሎ አልፏል። ይህ መጠነ-ሰፊ ወረራ ለከፍተኛ የሰው ሕይወት መጥፋት፣ ለሕዝብ መፈናቀልና ለዘመናት የተከማቹ በዋጋ የማይገመቱ ቅርሶች መውደም ዋነኛ መንስኤ ሆኗል።  የጦርነቱን ታሪክ በዝርዝር የያዘው "ፉቱህ አል-ሐበሻ" የተባለው የታሪክ መዝገብ እንደሚያረጋግጠው፤ ወታደራዊ ዘመቻው በዋናነት የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያንን፣ ንብረቶቿንና በደጋማው ክፍል የሚኖሩ ክርስቲያን ማኅበረሰቦችን ኢላማ ያደረገ ነበር።  በዚህ ጦርነት ምክንያት በሀገርና በቤተክርስቲያን ላይ እጅግ ከባድ ሰብአዊ፣ መንፈሳዊና ኢኮኖሚያዊ ውድመት ደርሷል። በርካታ ክርስቲያኖች በባርነት ወደ አረብ አገራት የተላኩ ሲሆን፣ ከሞት የተረፉትም በጦርነቱ ግፊት እምነታቸውን እንዲቀይሩ ተደርገዋል። ታላላቅ ገዳማትና አድባራት ለዝርፊያና ለቃጠሎ በመዳረጋቸው፣ ለዘመናት ተጠብቀው የቆዩ ጥንታዊ የብራና መጻሕፍትና ቅዱሳን ንዋያተ ቅድሳት ወድመዋል። ከቁሳዊ ጥፋቱ ባለፈ ካህናትና መነኮሳት የጅምላ ጭፍጨፋ ሰለባ ሆነዋል፤ እንዲሁም የበርካታ ታሪካዊ የክርስትና ቦታዎች ስም ተቀይሮ የቀድሞ ማንነታቸውና ታሪካዊ አሻራቸው እንዲጠፋ ተደርጓል። 

“የክርስቲያን ደሴት” እና ታሪካዊ መነሻው

ኢትዮጵያ ራሷን "በሙስሊም ባሕር መካከል ያለች የክርስቲያን ደሴት" አድርጋ የመግለጿ ትርክት ለዘመናት የቆዩ ውጫዊና ውስጣዊ ግፊቶች ውጤት ነው። ከ7ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ እስልምና በዙሪያዋ ባሉ አካባቢዎች በፍጥነት መስፋፋቱ፣ ኢትዮጵያን ከቀሪው የክርስቲያን ዓለም ነጥሎ በሙስሊም መንግሥታት እንድትከበብ አደረጋት። ይህ መገለልና በተለያዩ ዘመናት የተሰነዘሩት ጥቃቶች በተለይም በ16ኛው ክፍለ ዘመን የነበረው የአሕመድ ግራኝ ጦርነት በሕዝቡና በመሪዎች ዘንድ የማይፋቅ "ታሪካዊ ቁስል" እና ስልታዊ የመከበብ ስሜት (Siege Mentality) እንዲፈጠር አድርገዋል። በዚህ የተነሳ የመካከለኛው ዘመን የኢትዮጵያ ነገሥታት ለአውሮፓውያን ደብዳቤ ሲጽፉ "እኛ በሙስሊሞች የተከበብን ክርስቲያኖች ነን" የሚለውን ሐሳብ ይጠቀሙ ነበር።  አፄ ቴዎድሮስ የቱርክን ኃይሎች ጥቃት ለመመከትና የሀገርን ሉዓላዊነት ለማስከበር የነበራቸው ጽኑ አቋም ከዚሁ የታሪክ አሻራ የመነጨ ነው። ነገሥታቱ የጎረቤት ሙስሊም አገራት በሃይማኖት ሽፋን የኢትዮጵያን ብሔራዊ ደኅንነት ይፈታተናሉ የሚል የጸና እምነት ነበራቸው። በአንጻሩ፣ ይህ "የክርስቲያን ደሴት" ትርክት በጽንፈኛ የውሀብያ መሪዎች ዘንድ የተዛባ ትርጉም ይሰጠዋል። ሙስሊሙ ማኅበረሰብ በሀገሩ እንደ ባዕድ ተቆጥሯል የሚል ቅሬታ በመቀስቀስ፣ "እኛና እነሱ" የሚል የከፋፋይነትና የቂም ስሜት እንዲነግሥ ጥረት ያደርጋሉ። ይህም የታሪኩን ትክክለኛ መነሻ በማጣመም ለጽንፈኝነት ምቹ መደላድል እየፈጠረ ይገኛል።

የቦሩ ሜዳ ጉባኤ እና ዐፄ ዮሐንስ 4ኛ

 ዐፄ ዮሐንስ 4ኛ የሃይማኖት አንድነትን ለሀገር ፖለቲካዊ መረጋጋትና ለብሔራዊ ደኅንነት እንደ መሠረታዊ ምሶሶ ይመለከቱት ነበር። በተለይም በወቅቱ ከግብፅና ከማህዲስት ሱዳን ይሰነዘር የነበረውን የውጭ ወረራ ለመመከት፣ የውስጥ አንድነትን ማጠናከር ወሳኝ እንደሆነ አምነዋል። የቦሩ ሜዳ ጉባኤም በዚህ መንፈስ የተቃኘ ነው። በዚህም ምክንያት ሙስሊም የነበሩ የየአካባቢው መኳንንትን ወደ ክርስትና ለመለወጥ ከፍተኛ ጥረት ተደረገ። የእነሱ አርአያነት ብዙኃኑ ሕዝብ ፈለጋቸውን እንዲከተል ያደርጋል ብለው ያምኑ ነበር። በዚህም መሠረት የውሎዎቹ ታዋቂ መስፍኖች መሐመድ አሊ እና አባ ዋጠው ተጠምቀው የክርስትና ስማቸው ሚካኤል እና ኃይለማርያም ተባለ። ታዋቂው የሃይማኖት ሊቅ አካለወልድ አስተማሪ ሆነው ተመደቡላቸው። አንዳንዶች ከሚገምቱት በተለየ፣ የቦሩ ሜዳ ጉባኤ የተካሄደው በዲፕሎማሲያዊ መንገድ፣ በጥንቃቄና በሥርዓት እንጂ በኃይል ወይም በማስገደድ አልነበረም። ለምሳሌ ዐፄ ዮሐንስ ቀደም ሲል መሐመድ አሊ ለነበሩት ለራስ ሚካኤል የክርስትና አባት ሲሆኑ፣ ንጉሥ ምኒልክ ደግሞ ቀደም ሲል አባ ዋተው ለነበሩት ለደጃዝማች ኃይለማርያም የክርስትና አባት ሆኑ። ይህ የታቀደ ስትራቴጂ ሙስሊም ተከታዮቻቸው ክርስትናን እንዲቀበሉ የሚያበረታታና አዲስ የተጠመቁትን መሳፍንት እንደ አርአያ የሚያቀርብ ነበር። በመሆኑም የቦሩ ሜዳን ጉባኤ ተከትሎ በርካታ ሙስሊሞች ክርስትናን የተቀበሉት ተገደው ሳይሆን በፈቃደኝነት መሆኑን እንገነዘባለን።

ልጅ ኢያሱና እስልምና

በኢትዮጵያ የሥልጣን መንበር ላይ ለሦስት ዓመታት (1913-1916) የቆዩት ልጅ ኢያሱ፣ ወደ እስልምና ያጋደለና አወዛጋቢ የሆነ የሃይማኖት ፖሊሲ ይከተሉ ነበር። የዘር ግንዳቸውን ወደ ነቢዩ መሐመድ በመመዘዝ ራሳቸውን ከእስልምናው ዓለም ጋር ለማስተሳሰር መሞከራቸውና የቤተ-መንግሥቱን ወግ በመጣስ ከሙስሊም ብሔረሰቦች በርካታ ሚስቶችን ማግባታቸው በወቅቱ እንደ ትልቅ የማንነት ለውጥ ተወሰደ። በተጨማሪም እንደ ድሬዳዋና ጂጂጋ ባሉ ከተሞች መስጊዶችን በማስገንባት ለእምነቱ ያላቸውን አጋርነት በተግባር አሳይተዋል። በውጭ ግንኙነት ረገድም በብሪቲሽ ሶማሊላንድ ከነበረው ዓመፀኛ መሪ "ማድ ሙላህ" ጋር መቀራረባቸው፣ በወቅቱ የጎረቤት ሀገራት ቅኝ ገዥዎች የነበሩት እንግሊዝና ፈረንሳይን ከኢትዮጵያ ጋር አቃረነ። በተለይም "ከአላህ በቀር ሌላ አምላክ የለም" የሚል መፈክር ያለበትን የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ለቱርክ ቆንስላ መስጠታቸው፣ አገሪቱ ከእስልምናው ዓለም ጋር መወገናዋን እንደሚያሳይ ምልክት ተደርጎ ተቆጠረ። ይህ ድርጊታቸው ከሥልጣን ለመውረዳቸው እንደ ዋነኛ ምክንያት ተደርጎ ይወሰዳል።

ፋሽሽት ኢጣልያንና እስልምና

የፋሺስት ጣሊያን ወረራ በኢትዮጵያ ሙስሊም ማኅበረሰብ ላይ ያሳደረው ተፅዕኖ እጅግ ውስብስብና ዘርፈ-ብዙ ነው። ወራሪው ኃይል በክርስቲያኑና በሙስሊሙ ማኅበረሰብ መካከል የታሪክ ቅሬታዎችን በመፍጠር ለፖለቲካዊ መጠቀሚያነት እንዲውሉ "ከፋፍለህ ግዛ" የተሰኘውን ስልቱን በስፋት ተግባራዊ አድርጓል። ፋሺስት ጣሊያን ኢትዮጵያን በወረራ በያዘበት ወቅት፣ ሙስሊሙ ማኅበረሰብ "ተበድሎ እንደቆየ" በመቀስቀስ ከጎኑ እንዲሰለፍና በክርስቲያኑ ወገኑ ላይ በአሉታዊ መልኩ እንዲነሳሳ አድርጓል። ፋሺስቶች ራሳቸውን የ"እስልምና ጠባቂ" አድርገው በመሳል፣ የሙስሊሙን ድጋፍ ለማግኘትና የክርስቲያኑን መንግሥት ተጽዕኖ ለመቀነስ የተለያዩ ስልቶችን ተጠቅመዋል። ለዚህም ማሳያ እንዲሆን ከሃምሳ በላይ አዳዲስ መስጊዶችን የገነቡ ሲሆን፣ ነባሮቹንም እንዲታደሱ አድርገዋል። በተጨማሪም የእስልምና ትምህርት በአረብኛ ቋንቋ እንዲሰጥ በማበረታታት ማኅበረሰቡ ከሰፊው የእስልምና ዓለም ጋር እንዲገናኝ መንገዶችን አመቻችተዋል፤ የመካ የሐጅ ጉዞንም በገንዘብና በሎጂስቲክስ በመደገፍ ከፍተኛ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ጥረዋል።

እስልምናና የነጻ አውጭ ትግሎች

በዘመናዊቷ ኢትዮጵያ የታዩ የመገንጠል እንቅስቃሴዎችና የትጥቅ ትግሎች ከእስላማዊ ኃይሎች ድጋፍ ጋር ጥብቅ ቁርኝት ነበራቸው። በ1950ዎቹ የሶማሊያ ነፃ መውጣትና የ"ታላቋ ሶማሊያ" ራዕይ መፈጠር፣ በደቡባዊ ኢትዮጵያ ለተነሱት የባሌና የኦጋዴን የትጥቅ ትግሎች ዋነኛ መንስኤ ሆኗል። በተመሳሳይ፣ የኢትዮ-ኤርትራ ፌዴሬሽን መፍረስን ተከትሎ በቆላማ አካባቢ የሚኖሩ ሙስሊሞች የመጀመሪያውን የተቀናጀ የነፃነት ትግል መስርተዋል። በወቅቱ የነበረው የግብፁ መሪ ጋማል አብደል ናስር ርዕዮተ-ዓለምም፣ የኢትዮጵያ ሙስሊሞችን የሰፊው እስላማዊ ማንነት አካል አድርጎ በማንቀሳቀስ ለኤርትራና ለኦጋዴን ጦርነቶች መባባስ እንደ አንቀሳቃሽ ኃይል አገልግሏል። በዚህ ሂደት ውስጥ በካይሮ የሚገኘው የአል-አዝሃር ዩኒቨርሲቲ ምሩቃንና የዐረብ አገራት ያደርጉት የነበረው ዲፕሎማሲያዊና ወታደራዊ ድጋፍ ከፍተኛ ነበር።

እስልምና በንጉሡና በደርግ ጊዜ

አፄ ኃይለ ሥላሴ የሸሪዓ ፍርድ ቤቶችን በሕግ እውቅና ሰጥቶ ማቋቋምን የመሰሉ አስተዳደራዊ ለውጦችን ተግባራዊ አድርገው ነበር። ይሁንና በሃይማኖቶች መካከል የነበረው ግንኙነት በይፋ የተቀየረው በደርግ ዘመን ነው። በሚያዝያ ወር 1966 ዓ.ም. በአዲስ አበባ የእስልምና እምነት ተከታዮች ታላቅ ሰላማዊ ሰልፍ ማድረጋቸውን ተከትሎ፣ ደርግ ይህንን አጋጣሚ "የሃይማኖቶች እኩልነት" በሚል ሽፋን የቤተክርስቲያኗን ተፅዕኖ ለማዳከም ተጠቀመበት። በ1968 ዓ.ም. የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት እንዲመሠረትና የእስልምና በዓላት በይፋ እውቅና እንዲያገኙ መደረጉ፣ ሙስሊሙ ማኅበረሰብ ከመንግሥት ጋር እንዲሰለፍ ምክንያት ሆኖ ነበር። በአንጻሩ ደርግ ፖትርያሪኳን ገድሎ፤ ንብረቷንና መሬቷን በአዋጅ ቀምቶ፤ አሉታዊ የሆነ የርዕዮተ ዓለም ዘመቻ ከፍቶባት ቤተክርስቲያኗን በከፍተኛ ሁኔታ እንድትዳከም አድርጓል።

እስልምና በዘመነ ኢሕአዴግ

ኢሕአዴግ የሙስሊሙን ማኅበረሰብ መብቶች ለማስከበር የተለያዩ ስልታዊ እርምጃዎችን ወስዷል። ከእነዚህም መካከል የመንግሥት ሠራተኞች ለጁምዓ ጸሎት የሥራ እረፍት እንዲያገኙ መደረጉ፣ የመጅሊስ ሕጋዊ እውቅና ማግኘትና የሸሪዓ ፍርድ ቤቶች በመንግሥት በጀት እንዲደገፉ መወሰኑ ተጠቃሽ ናቸው። በተጨማሪም ለአል-ነጃሺ መስጊድ ታሪካዊ እውቅና በመስጠት በዩኔስኮ የዓለም ቅርስነት እንዲመዘገብ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች ተካሂደዋል። ይሁንና ይህ ዘመን በሀገር ውስጥና በዓለም አቀፍ ክስተቶች ሳቢያ በርካታ ፈተናዎች የታዩበት ነበር። በ1987 ዓ.ም. በፕሬዝዳንት ሆስኒ ሙባረክ ላይ የተፈጸመው የግድያ ሙከራና ከ9/11 በኋላ የተጀመረው የጸረ-ሽብር ዘመቻ በመንግሥትና በጽንፈኛ ኃይሎች መካከል ያለውን ግንኙነት አሻክሮታል። በተለይም በ1999 ዓ.ም. በጂማ ዞን በክርስቲያኖች ላይ የተፈጸመው ጥቃት፣ በሊቢያ በ'አይኤስ' አማካኝነት የተፈጸመው አሰቃቂ ግድያና የአል-ሸባብ ፀረ-ኢትዮጵያ ቅስቀሳዎች ለሰላሙ መደፍረስ ምክንያት ሆነዋል። በተጨማሪም በአንዳንድ አካባቢዎች የቤተክርስቲያን ይዞታዎችን በመጋፋት ሆን ተብሎ የሚደረጉ የመስጊድ ማስፋፋት ጥረቶች፣ የቆየውን አብሮ የመኖር እሴት የሚፈታተኑ ሆነው አልፈዋል። በሌላ በኩል  መንግሥት ሲኖዶሱን ለሁለት በመክፈልና በአስተዳደሯ ውሰጥ ጣልቃ በመግባት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን በከፍተኛ ሁኔታ አዳክሟታል።

እስልምና በዘመነ ብልጽግና

በዘመነ ብልጽግና በአክራሪ ሙስሊሞችና ብሔርተኞች በተለይ በኦሮሚያ፣ በሶማሌ፣ በሲዳማ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎችና በሥልጤ ዞን ውስጥ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንና በምእመናን ላይ የሚፈጸሙ መጠነ-ሰፊ ጥቃቶችና ስደቶች ተጠናክረው ቀጥለዋል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ በ2014 ዓ.ም. በመስቀል አደባባይ የተካሄደውን "ታላቁ የጎዳና ላይ ኢፍጣር" መነሻ በማድረግ፣ አክራሪ ኃይሎች ቦታውን "ዒድ አደባባይ" በሚል በመጥራት የፈጠሩት ትንኮሳ በሃይማኖቶች መካከል ያለውን ግንኙነት ይበልጥ ለማሻከር የታለመ ነበር። በውጭ ግንኙነት ረገድም፣ በሳውዲ ዓረቢያ በኢትዮጵያውያን ሴት ሠራተኞች ላይ የሚፈጸመው አስከፊ የሰብአዊ መብት ረገጣ ተባብሶ ቀጥሏል። በተጨማሪም ኢትዮጵያን የአረብ ሊግ አባል ለማድረግ የሚካሄደው ፖለቲካዊ ቅስቀሳ አወዛጋቢ ሆኖ የቆየ ሲሆን፣ ለዚህም እንደ አምባሳደር ዲና ሙፍቲና ኡስታዝ ካሚል ሸምሱ ያሉ ግለሰቦች የሚያቀርቡት ሙግት እንደ ማሳያ ይጠቀሳል። በሌላ በኩል እንደ ቱርክ፣ ኢራንና የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ያሉ ሙስሊም አገራት እንደ ድሮን ያሉ ዘመናዊ ወታደራዊ ቁሳቁሶችን ለኢትዮጵያ መንግሥት በማቅረብ፣ በሀገር ውስጥ ጦርነት ወገኖችን ለመጨፍጨፍ መዋላቸው በዘመኑ ከታዩት ዋና ዋናና አሉታዊ ክስተቶች መካከል ይጠቀሳሉ።

የማጠቃልያ አስተያየት

 ከላይ ከተዘረዘሩት የታሪክ ኩነቶች እንደምንረዳው በአክራሪው የውሀብያ እንቅስቃሴ አማካኝነት በኢትዮጵያ ለዘመናት የቆየውን አብሮ የመኖር እሴትና የሀገረ መንግሥት ግንባታ ሂደት የሚፈታተን አደገኛ የታሪክ ማዛባት ዘመቻ እየተካሄደ መሆኑን ነው። እነዚህ ኃይሎች "ተበድለናል" የሚል የሐሰት ትርክት በማንገብ ቤተክርስቲያኒቱን እንደ ታሪካዊ ጨቋኝ አድርገው ለመሳል ቢሞክሩም፣ ተጨባጩ የታሪክ እውነት ግን በተገላቢጦሽ ቤተክርስቲያን በተለያዩ አክራሪ ኃይሎች መጠነ-ሰፊ የሰው ሕይወትና የቅርስ ውድመት የደረሰባት መሆኑን ያሳያል። የታሪክ አውነታው የሚያሳዬን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የጥቃት ሰለባ እንጅ በየትኛውም ዘመን ቢሆን ሌሎችን በዳይ ሁና እንደማታውቅ ነው። ይህ "በዳይና ተበዳይ" የሚል ከፋፋይ ጎራ ለውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት ምቹ በር የሚከፍት ከመሆኑም በላይ፣ አክራሪዎች ይህንኑ የሐሰት ትርክት በቤተክርስቲያንና በምእመናን ላይ ለሚፈጸሙ ዘግናኝ ጥቃቶች እንደ "ፍትሐዊ እርምጃ" እና የጥቃት ሰበብ እየተጠቀሙበት ይገኛሉ። በመሆኑም፣ የታሪክ ማዛባትንና የሐሰት ትርክትን መመከት የሃይማኖት ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የሀገርን ህልውና የመታደግ ጉዳይ በመሆኑ፤ እያንዳንዱ ምእመንና የሀገር ወዳድ ዜጋ የታሪክ ባለአደራነቱን ተገንዝቦ ለሀገራዊ አንድነትና ለቤተክርስቲያን መከበር በንቃት ሊቆም ይገባል። ትውልዱ ከስሜታዊነት በራቀና በማስረጃ ላይ በተመሠረተ እውነት እንዲገነባ ማድረግ፣ የኢትዮጵያን የሺህ ዓመታት አብሮነት ከጽንፈኝነት አደጋ ለመጠበቅ ዋነኛው መንገድ ነው።

ማጣቀሻዎች (References)

Arabfaqīh, S. a.-D. A. ibn ʿA.-Q. (2003). Futuh al Habasha: The conquest of Abyssinia (P. L. Stenhouse, Trans.; R. Pankhurst, Annot.). Tsehai Publishers.
Abbink, J. (1998). An historical‐anthropological approach to Islam in Ethiopia: issues of identity and politics. Journal of African Cultural Studies, 11(2), 109-124. 

Ahmed, H. (2001). Islam in Ninteenth-Century Wallo, Ethiopia. Leiden: Brill.
Atiya A. S., ‘Abd al-Masih Y., Burmester, O.H.E., eds. (1948).  History of the Patriarchs of the Egyptian Church, known as the History of the Holy Church by Sawirus ibn al-Mukaffa, Bishop of al-Asmunin. Vol.II, Part III, Cairo: Publications de la société d’archéologie copte. 
Bekele, Y. (2022). Abbot ʿĔnbāqom and Islam: The Historical-Theological significance of Anqäs’ ä Amin’s contribution to Christian-Muslim engagement in sixteenth century Ethiopia (Doctoral dissertation, Stellenbosch: Stellenbosch University).

Demissie, T. E. (2020). Anti-orthodox Christian attitudes in Ethiopia: An assessment of historical and contemporary persecutions of Christians. International Journal of Orthodox Theology, 11(4), 9.

Ficquet, É. (2015). The Ethiopian Muslim: Historical controversies and ongoing process. In G. Prunier & É. Ficquet (Eds.), Understanding contemporary Ethiopia: Monarchy, revolution and the legacy of Meles Zenawi (pp. 93–122). Oxford University Press.

Gnamo, A. H. (2002). Islam, the Orthodox Church and Oromo nationalism (Ethiopia). Cahiers d’études africaines, 42(165), 99-120.

Haustein, J., Idris, A. K., & Malara, D. M. (2023). Religion in contemporary Ethiopia: History, politics, and inter-religious relations [Literature review]. Rift Valley Institute, Ethiopia Peace Research Facility.
Isaac, 2018. Erlich, H. (2013). Islam, Christianity, Judaism, and Ethiopia: The Messages of Religions. The Fifth Annual Levtzion Lecture, 1-28.

Liyew, D. M. (2024). The politics of secularism in Ethiopia: Repression and/or co-option towards EOTC. ESI Preprints (European Scientific Journal, ESJ), 27, Article 474.

Shenk, C. E. (1972). The development of the Ethiopian Orthodox Church and its relationship with the Ethiopian government from 1930 to 1970 (Doctoral dissertation). New York University.

Trimingham J. S. (1965). Islam in Ethiopia. Oxford: Oxford University Press. 
Østebø, T. (2023). Religious dynamics and conflicts in contemporary Ethiopia: Expansion, protection, and reclaiming space. African Studies Review, 66(3), 721-744.

Worku, Mengistu Gobezie (2025). The Church and the Crown in Ethiopia: A Historical Journey.
Share on Google Plus

ስለ የተለጠፈበት ቀን

    Blogger Comment
    Facebook Comment