✍ አዲስ ምልከታ
በቀይ ባህር ዙርያ የሚደረገው ግጭት የ ሁለት ሃገራት ግጭት ብቻ ሳይሆን መካከለኛው ምስራቅ ሃገራትን ያካተተ ውስብስብ ግጭት ወደመሆን ተሸጋግሯል። በዚህም ትላልቅ አቅም ያላቸው የመካከለኛው ምስራቅ ሃገራት ጂኦፖእቲካዊ ተጽኖአቸውን ለማሳረፍ ሲሉ በአከባቢው ያሉ ሃገራትን መደገፍ ላይ ናቸው።
በዚህም መሰረት የተባበሩት አረብ እሚሬት በሱዳን የፈጥኖ ደራሽ ኃይልን እና የኢትዮጵያ መንግስትን፣ እንዲሁም ሶማሊላንድን የሚደግፍ ሆኖ ተገኝቷል። የኢትዮጵያ መንግስት ደግሞ አሰብን ተቆጣጥሮ ቀይ ባሕር ላይ የመስፈር ፍላጎቱን ካሳየ በኋላ ኤርትራም ሌሎች አጋር ሃገራት ፈልጋ ከነሱ ጋ ተሰልፋለች። በዚህም ከሱዳን መንግስት ጦር እና ከግብጽ እንዲሁም ከሶማልያ ጋር አንድነታቸውን አጠናክረዋል።
በዚህ መካከል ደግሞ ከሶማልያ መገንጠል የምትፈልገው ሶማሊላንድ በእስራኤል የሃገርነት እውቅና በማግኘቷ፣ ኢትዮጵያም ያንን ልትሰጣት በመስማማቷ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ተስማሚነቷን አሳይታለች። ይህ ደግሞ ሶማሊላንድን የተባበሩት አረብ ኢሚሬትም ጋር እንድትስማማ እና ከሳኡዲ አረቢያ ጋርም እንድትጣላ አድርጓታል።
አረብ ኢምሬት እና ሳኡዲ በየመንም የማይስማሙ እና የተለያዩ ታጣቂ ቡድኖችን የሚደግፉ ናቸው። ያም ግጭታቸው ወደ አፍሪካ ቀንድ ተሻግሮ፣ ሳኡዲ ከሶማሊላልንድ ጋ ያላትን ስምምነት ሁሉ አቋርጣ ሰራዊቷንም ከዛ እንድታነሳ ሲያደርጋት፣ አረብ ኢምሬት ደግሞ በዚያ ሰፍራ የጦር ሰፈርን ለመመስረት ተዘጋጅታለች። በዚያም ተጠቅማ በቀላሉ የጦር መሳርያዎችን በሶማሊላንድ በኩል አድርጋ፣ በኢትዮጵያ አሳልፋ፣ በሱዳን ላሉት ፈጥኖ ደራሽ ሰራዊቶችን ማሻገር ከጀመረች ሰነባብታለች። ከአረብ ኢምሬት ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ የጦር አውሮፕላኖች ቁጥርም እጅግ ጨምሯል። እስራኤልም ከሶማሊላንድ የተለያዩ ጥቅሞች ታገኛለች። እነዚህም፣ በኤደን ባሕረ ሰላጤ የጦር ካምፕ ገንብታ የየመን ሁቲዎችን ለመዋጋት ይጠቅማታል፣ እንዲሁም በጋዛ የሚገኙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያንን ወደዛ ለማስፈርም ስለምትፈልግ ያ ይረዳታል።
በሌላ በኩል ደግሞ በኤርትራው የአሰብ ክልል/ግዛት የሚገኙት አፋሮች የኤርትራ መንግስት ሰብአዊ መብት ጥሰቶችን አድርሶብናል፣ ከሱ ተለይተን መውጣት አለብን በሚል ወደ ኢትዮጵያ ቀርበዋል። እንዲሁም ከየመን ካላቸው ቅርበት የተነሳ የየመን ሁቲ አማጺዎችም ወደዚያ መጥተው አንዳንድ ቡድኖችን እያስታጠቁ እንዳሉ እና እነሱንም እያጠቁ እንዳሉ አቤቱታ አቅርበዋል። ይህንንም አንስተው እስራኤልን እርዳታ ጠይቀዋል። እስራኤልም ሁቲዎችን ለማጥፋት ካላት ፍላጎት አንጻር እነርሱን ልትረዳ ትችላለች፣ ከዚህም በተጨማሪ ኢትዮጵያ ኤርትራን ወግታ ቦታውን እንድትይዝ ልትረዳም ትችላለች፣ ያ ከሆነ በኋላ በሁቲዎች ቅርብ ርቀት ላይ የጦር ካምፕ ለመመስረት ስለሚረዳት።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ደግሞ ኢትዮጵያም ያሏት ውስጣዊ መከፋፈሎች ሌላ ራስ ምታት ናቸው። በሃገሪቱ ያሉት ታጣቂ ኃይሎች የተለያየ የፖለቲካ አሰላለፍ ሊኖራቸውም ይችላል። በአንድ በኩል የህወሓት ቡድን ከኤርትራ ጋር ሲሰለፍ፣ የአፋር ኃይሎች ደግሞ ከመንግስት ጋር ተሰልፈዋል። የፋኖ ኃይል ደግሞ ከኤርትራ ጎን የቆመ እና መንግስትንም አክርሮ ለመቃወም የወሰነ ይመስላል። በሌላ በኩል ደግሞ የሶማሊ ክልል ሃይል ከሶማልያ የሚመጣውን ወረራ ለመከላከል እየተዘጋጀ ይመስላል። አንዳንድ በሶማልያ ያሉ ሰዎች፣ የሶማልያ መንግስት በኢትዮጵያ ይህን ያህል ከተከዳ፣ እንግዲያውስ ከአልሸባብ ጋር ተሰልፎ ኢትዮጵያን መውጋት አለበት የሚሉ ተከስተዋል። ይህም እውነት የሆነ ቀን ኢትዮጵያ ትልቅ ችግር ሊያጋጥማት ይችላል።
አንድ ብዙ ሰው ያላወቀው እና ተሰውሮ የነበር በቅርቡ የወጣ መረጀ እንደሚያሳየው ደግሞ የተወሰነ የአልሸባባ ኃይል ወደ ኢትዮጵያ ገብቶ እንደነበር፣ የመከላከያ ኃይልም ሊመልሰው እንዳልቻለ እና ዘልቆ ገብቶም የባሌ ተራሮች አከባቢ እንደተቀመጠ፣ በዚያም ሃይሎችን እያሰለጠነም እንደሚገኝ ይነገራል።
እነዚህ እና ሌሎችም ያልተገለጹ ብዙ ችግሮች የአፍሪካ ቀንድን እና ቀይ ባሕርን ቀጠና በሚቀጥሉት ወራት እጅግ ጥልቅ እና ውስብስብ ጦርነት እና ቀውስ ውስጥ ሊከቱት በመንገድ ላይ ናቸው።
ይህም ቀውስ በቀጠናው ያሉ ህዝቦች ላይ ከፍተኛ የሆነ የረሃብ፣ ሞት እና ስደት የሚያስከትል እንደሆነ በተለያዩ ጊዜ ነጮች ጥናት ሰርተው ተንብየዋል። በመካከለኛው ምስራቅ በነበሩ አስከፊ ጦርነቶች እንደ ሶርያ ካሉት ሃገራት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ህዝቦች ወድ እውሮፓ እንደተሰደዱት ሁሉ፣ አሁንም አፍሪካ ቀንድ ያሉ ህዝቦችም ያ እጣ ሊደርስባቸው ያለ ይመስላል።
Blogger Comment
Facebook Comment