ሐምሌ 22 1928ዓም 89ኛ ዓመት መታሰቢያ
ሰመአቱ አቡነ ጴጥሮስ
ሐምሌ 22 የሰማዕቱ አቡነ ጴጥሮስ መታሰቢያ
ሰማዕቱ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ጳጳስ ዘምስራቅ ኢትዮጵያ
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሃዱ አምላክ አሜን
ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ በ1875 ዓ.ም. በሰሜን ሸዋ አገረ ስብከት ሰላሌ አውራጃ ፍቼ ከተማ ተወለዱ። ወላጆቻቸው ዕድሜያቸው ገና በወግ ለትምህርት ሳይደርስ ወደ ደብረ ሊባኖስ ገዳም በመውሰድ ባሕታዊ ተድላ ለተባሉ መምህር አደራ ሰጧቸው። በዚያው ገዳም የንባብ ቤቱንና የዜማውን የትምህርት ደረጃዎች በሚያስገርም ሁኔታ በአጭር ጊዜ አቀላጥፈው በመጨረስ ገና በልጅነት የዕድሜ ደረጃቸው ሦስተኛውን የቅኔ ትምህርት ጀምረው በአጭር ጊዜ ሙሉ ቤት ተቀኙ። ይህንኑ የቅኔ ትምህርት ለማስፋፋት በምዕራብ ጎጃም አገረ ስብከት ወደ ሚገኘው የቅኔ ትምህርት ማዕከል ዋሸራ ተሻግረው ለመምህርነት የሚያበቃውን ትምህርት ፈጽመው አስመሰከሩ።
ከዚያም ከቅኔው ዐውድማ ጎጃም ወደ ዜማው አዝመራ ጎንደር ተሻገሩ። በዚያም እንደ ቅኔው ሁሉ እስከ ማስመስከር ባይደርሱም የዜማውን ትምህርት በአጥጋቢ ሁኔታ ቀጸሉ። ከጎንደርም በወቅቱ ወሎ ቦሩሜዳ ከተባለው ቦታ ላይ ወንበር ዘርግተው የመጻሕፍትን ምሥጢር በየዓይነቱ ሲመግቡ ወደ ነበሩት ስመ ጥሩው መምህር አካለወልድ ዘንድ በመሔድ ዋና ዋናዎቹን የመጻሕፍት ትርጓሜ ትምህርቶች ማለትም ብሉያትን፣ ሐዲሳትንና ሊቃውንትን በብቃት አካሔዱ።
ከዚህ በኋላ ልክ በ1900 ዓ.ም. እዚያው ወሎ አማራ ሳይንት በተባለው ቦታ ወደሚገኘው ምስካበ ቅዱሳን ገዳም በመሔድ ወንበር ዘረጉ። በዚያው ቦታ ለዘጠኝ ዓመታት ያህል ቅኔንና መጻሕፍትን አስተማሩ።
በዚህ ዓይነት በመማርና በማስተማር ራሳቸውን በእግዚአብሔር ቃል በሚገባ ከጐሰሙ በኋላ በ1909 ዓ.ም. ወደ ደብረሊባኖስ ገዳም በመሔድ ሥርዓተ ምንኩስናን ፈጸሙ። ብዙም ሳይቆዩ ማዕረገ ቅስናን ተቀብለው ከወንበሩ አገልግሎት ጋር የቤተመቅደሱን ተልእኮም ደርበው ያዙ።
በ1910 ዓ.ም. መምህር ኃይለ ማርያም ተብለው በወላይታ ሶዶ በሚገኘው ደብረ መንክራት ምሁር ኢየሱስ ገዳም ተሾሙ። በ1916 ዓ.ም. እንደገና በዝዋይ ደብረምሕረት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም በመምህርነት ተሾሙ። በ1919 ዓ.ም. ወደ አዲስ አበባ በመምጣት የመንበረ መንግሥት ቅዱስ ማርቆስ መምህርና በቤተ መንግሥት የግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ አበ ንስሐ ሆኑ።
የግብፅ ቤተ ክርስቲያን ከአንድ ሺ ስድስት መቶ ዓመታት በኋላ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በዕውቀት መንፈሳዊ ከእርሷ ተወልደው በእቅፏ ውስጥ ባደጉ ኢትዮጵያውያን ጳጳሳት እንድትመራ ፈቃዷን ስትገልጽ ከተመረጡት አባቶች አንዱ በመሆን ግንቦት 18 ቀን 1921 ዓ.ም. በእስክንድርያው መንበረ ማርቆስ ቤተ ክርስቲያን ማዕረገ ጵጵስናን ተቀበሉ። ከዓመት በኋላም “አቡነ ጴጥሮስ ጳጳስ ዘምሥራቅ ኢትዮጵያ ተላዌ አሠሩ ለአቡነ ኢየሱስ ሞዓ” ተብለው በያኔው መንዝና ወሎ አገረ ስብከት ተሾሙ።
በ1928 ዓ/ም ፋሺስት ኢጣሊያ የዓድዋ ሽንፈቱን ለመበቀል ዳግም በቁጭት መጣ፡፡ ከአራቱም ማዕዘናት የባሩድ ጭስ ምድረ ኢትዮጵያን አፈናት፡፡ ሥልጡን፣ሰብአውያን ነን ያሉ ነጮች በምስኪኑ የአገሬ ሰው ላይ መርዛማ ጋዝ ለማዝነብ የጦር ጀቶቻቸውን በገዛ ሰማያችን ላይ ማክነፍ ተያያዙት፡፡
ያማጧቸውንም መርዛማ ገዳይ ኬሚካሎች ቂም ባመረቀዙበትና ዘመናዊ ትጥቅ ባልታጠቁ ኢትዮጵያውያን እና ኢትዮጵያውያን አርበኞች ላይ ዘረገፉት፡፡ ብዙዎች በየጦር አውድማው ወድቀው ቀሩ፣ጠላት ድል ነሣቸው፣የአንዲት አገር ፍቅር ያስቆጫቸው ጀግኖች ደማቸው ሕያው ታሪክን እየጻፈ ወደ ሞት ነጎዱ፣የነጻነት ጎሕ የቀደደው የዓድዋው የጦር ውሎ ዳግም በሽንፈት ደበዘዘ ብዙዎችም ተስፋ ቆረጡ፡፡ ይህን ጊዜ አገር በባዕድ እንዳትገዛ፣ሃይማኖት በከሃድያን እንዳይጣስ ጀግናው አባት በቁጡ መንፈስ ተነሡ፡፡ እኚህ ሰው ደግሞ ጀግናው፣ቆራጡ፣ስመ ገናናው አቡነ ጴጥሮስ ነበሩ፡፡
አቡነ ጴጥሮስ በዘመኑ በንጉሡ፣በመኳንንቱ እና በሕዝበ ኢትዮጵያ ዘንድ የነበራቸው ከበሬታ በፋሽስት አበጋዞች ዘንድ ታላቅ ፍርሃትን አጭሮ ነበር፡፡ ለዚህ ነው ፋሽስት ለጉልበቱ ማሳያና ለጭካኔው ጣሪያ መድረስ እንደማሳያ አድርጎ እርሳቸውን ለመግደል የወሰነው፡፡ አቡነ ጴጥሮስን መግደል አርበኞች ዘንድ በነበረው የተጋጋለ ስሜት ላይ ውሃ እንደመከልበስ አድርጎ ያሰበው ሥልጡን ነኝ ባዩ ፋሽስት ጳጳሱን ከመግደል በቀር ደግሞ ማሰብ ተስኖት አቡኑን ማደን ተያያዘው፡፡
ፋሺስት ኢጣሊያ አቡነ ጴጥሮስን በመደለል ሃሳባቸውን እንዲቀይሩ እና ለጣሊያን መንግሥት እንዲገዙ ያላደረገው ጥረት አልነበረም፡፡ እርሳቸው ግን ‹‹ሰማያዊ ንጉሤ ኢየሱስ ክርስቶስ ምድራዊ ንጉሤ ደግሞ ኃይለ ሥላሴ ናቸው ከዛ ውጭ ለማንም አልገዛም!›› አሉ፡፡ ግራዚያኒም ይህን ጽኑ እምነታቸውን በምንም እንደማይቀይሩ ስለተረዳ እንዲገደሉ ወሰነ፡፡ ለዚህ ውሳኔ ያበቃው ደግሞ አቡነ ጴጥሮስ በሕዝብ ዘንድ ከነበራቸውን ተሰሚነት አንጻር ቢገደሉ ሕዝቡ ተስፋ ቆርጦ የተፋፋመውን ጦርነት የሚገታ ስለመሰለው ሲሆን በተጓዳኝ የጎመዠላት ኢትዮጵያ ከእጁ እንዳትወጣ ስለ ሳሳ ነው፡፡
ፋሺስት ኢጣሊያ በኢትዮጵያ ላይ የግፍ ጦርነትን ባነሣ ጊዜ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ከጦር ስፍራ ለመለየት ስላልሆነላቸው፣ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን ተከትለው ወደ ሰሜን ጦር ግንባር ዘምተዋል፡፡ ፋሺስቱ በማይጨው የመርዝ ጦርነት ከማድረጉ የተነሣ፣ የኢትዮጵያ ሠራዊት ሲበታተንም ከንጉሠ ነገሥቱ ጋር የተመለሱት አቡነ ጴጥሮስ ወደ ደብረ ሊባኖስ ሄደው ለአገርና ለነፃነት መሞት ቅዱስ ተግባር መሆኑን ለሥላሴ አርበኞች በመስበክም ይታወቃሉ፡፡
አርበኞች አዲስ አበባን በሁለት አቅጣጫዎች ከሰሜናዊ ምዕራብ እና በደቡባዊ ምሥራቅ አቅጣጫ ለመቆጣጠር ውጊያ በከፈቱበት ጊዜ የተማረኩት አቡነ ጴጥሮስ፣ ለፋሺሽትእንዲገዙ የኢጣሊያ መንግሥት ገዢነትንም አምነው አሜን ብለው እንዲቀበሉ ግፊት ቢያደርጉባቸውም፤ እምቢኝ ለሀገሬና ለሃይማኖቴ ብለው ለሰማዕትነት ያበቃቸውን የሞት ጽዋ ተቀብለዋል፡፡
ቅዱስ ጳውሎስ ደቀ መዝሙሩ የሆነው ጢሞቴዎስን የተሰጠውን አደራ በመጠበቅ ሓላፊነቱንና ግዴታውን መወጣት እንደሚገባው ሲገልጽ «እቀብ ማህጸንተከ፤አደራህን ጠብቅ» በማለት ነው፡፡ 1ኛጢሞ.6 .2፡፡ ጢሞቴዎስ በመምህሩ የተጣለበትን አደራ ለመወጣት የዚህ ዓለም ፈቃድ ሳያሸንፈው ተወጥቷል፡፡ የዓላውያን ነገሥታት ማዋከብ፣ ድብደባ አደራውን እንዳይወጣ አላደረገውም፡፡ የአቡነ ጴጥሮስ የሰማዕትነትም ጉዞ መነሻውም መድረሻውም የእነዚህ አባቶች አርአያ ፍኖት ነው፡፡
ለሀገራቸውና ለወገናቸው እስከ መጨረሻዋ ሰዓት ድረስ እውነቱን ከሐሰት በመለየት ለሕዝባቸው የሰጡት ምስክርነት የተጣለባቸውን አደራ ከመወጣት ነው፡፡ አለቃ ተጠምቀ የተባሉ ቅድስናን ከሊቅነት ጋራ አስተባብረው የያዙ የቅኔ መምህራቸው አንድቀን ብፁዕነታቸውን ጠርተው የሚከተለውን የአደራ ቃል ያስተላልፋሉ፡፡
«ኀይለማርያም አንተ ወደፊት ጳጳስ ትሆናለህ፤ በወቅቱም አረመኔ በዚህች ሀገር ይሠለጥናል፡፡ ታዲያ ያኔ አንተ ለነፍስህ ሳትሳቀቅ በሰማዕትነት እለፍ፤ ሰማዕትነት ክፍልህ ነው፡፡ አደራ፡፡»
ሐዋርያው ቅዱስ ጢሞቴዎስ የመምህሩን የአደራ ቃል በመያዝ እስከ መጨረሻው እንደጸናው ብፁዕነታቸውም የመምህራቸውን የአደራ ቃል በሰማዕትነት አትመው ጠበቁ፡፡ አንዲትም ቀንና ሰዓት ከሞት ሳይሸሹ እና ሳይደበቁ ለአገራቸው ፣ለቤተ ክርስቲያናቸው እና ለሕዝባቸው ሲሉ ሞትን ተጋፈጡ፡፡ የሰማዕትነትን ጽዋ ተጎነጩ፡፡ የዚህ ምንጩ አደራ ነው፡፡ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ቤተክርስቲያን በአደራ የሰጠቻቸውን ሓላፊነት ለመወጣት ሕዝበ ክርስቲያኑን በጸሎታቸው እየደገፉ፣ በትምህርታቸው እያበረቱ አስተዳድረዋል፡፡
ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ሕዝብ ቀስቅሰዋል፤ራስዎም አምጸዋል፣ ሌሎችንም እንዲያምጹ አድርገዋል በሚል የወንጀል ክስ ፍርድ ቤት ቀረቡ፡፡ ችሎቱ ተሰይሞ ሲቀርቡ ዳኛው«ካህናቱም ሆኑ የቤተክህነት ባለሥልጣናት ጳጳሱ አቡነ ቄርሎስም የጣሊያንን መንግሥት ገዥነት አምነው አሜን ብለው ሲቀበሉ እርስዎ ለምን ዐመፁ) ለምን ብቻዎን አፈንጋጭ ሆኑ)» ሲል ጠየቃቸው፡፡
ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ በቆራጥነት «አቡነ ቄርሎስ ግብጻዊ ናቸው፤ ስለ ኢትዮጵያና ስለ ኢትዮጵያውያን የሚገዳቸው ነገር የለም፡፡ እኔ ግን ኢትዮጵየዊ ነኝ፡፡ ሓላፊነትም ያለብኝ የቤተክርስቲያን አባት ነኝ፡፡ ስለዚህ ስለሀገሬና ስለ ቤተ ክርስቲያኔ እቆረቆራለሁ፡፡ እኔን ለመግደል እንደወሰናችሁ አውቃለሁ፡፡ስለዚህ በእኔ ላይ የፈለጋችሁትን አድርጉ፡፡ግን ተከታዮቼን አትንኩ» በማለት ሕያው በሆነ ቃላቸው መለሱ፡፡
ኢጣልያዊው ጋዜጠኛ ቺሮ ፓጃሊ «እኒህ ጳጳስ ሐቀኛ ነበሩ። ነገር ግን ለኢጣልያ ለጋስዮን ታዝዞ የመጣው አስተርጓሚ ዳኞች የሚሉትን ብቻ ከማስተርጐም በቀር ጳጳሱ የሚናገሩትን ሐቀኛ ንግግር አላስተረጐመም። እኔ እንኳን የሰማሁት በአዲስ አበባ ለሠላሳ ዓመት የኖረው የእቴጌ ሆቴል ኃላፊ የነበረው የግሪክ ዜጋ ማንድራኮስ አጠገቤ ተቀምጦ ስለነበር የተናገሩትን ሁሉ ስለገለጠልኝ ነው። እኔ እንደ ሰማሁት ፍርዱን ለመስማት በብዛት የተሰበሰቡት ጣልያኖችና ታዝዞ የወጣው የአዲስ አበባ ሕዝብ ሐቀኛ የሆነውን ንግግራቸውን ቢሰሙ ኖሮ ልባቸው ይነካ ነበር» ይላል።
ሆኖም አስተርጓሚው በጳጳሱ ላይ ተጽዕኖ ስላሳደረባቸው እውነተኛ ንግግራቸው ሳይገለጥ እንደ ቀረ ይጽፋል። ቀጥሎም ብፁዕነታቸው በፍርድ ችሎት ላይ እንዳሉ ሕዝቡ ሁሉ ስለእርሳቸው እያዘነ ሳለ መስቀላቸውን አውጥተው እየጸለዩ ሕዝቡን ባረኩ። ወዲያው የሞታቸው ሰዓት መድረሱን ዐውቀው ሰዓታቸውን ከኪሳቸው አውጥተው ተመለከቱ። በዚህ ጊዜ ሁሉ ምንም ፍርሃት አይታይባቸውም ነበር። የሞታቸውን ፍርድ ያነብ የነበረው ኢጣልያዊ ዳኛ ግን ይንቀጠቀጥ ነበር። ታላቅ ፍርሃትም በፊቱ ይታይ ነበር።
«ይሙት በቃ» የተፈረደባቸው ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ በችሎት ፊት ለብዙ ሰዓታት ቆመው ስለዋሉና ደክሟቸው ስለነበር ለመቀመጥ ፈልገው ዳኛውን በትሕትናና በፈገግታ ጠየቁት። እንዲቀመጡም ፈቀደላቸው። በመጨረሻም የሞታቸው ፍርድ ከተነበበ በኋላ የፈረዱባቸውን ዳኞች ጸልየው በመስቀላቸው ባረኳቸው። ብፁዕነታቸው እስከመቃብር አፋፍ ድረስ የፍርሃትና የድንጋጤ ምልክት ያይደለ ከልብ የሆነ ፍጹም የክብር ትሕትና ይታይባቸው ነበር።
የአገራቸው በጠላት መወረር፣ የሕዝባቸው መገደልና መታሰር፣ የቤተ ክርስቲያናቸው መደፈር እስከ ሞት ያደረሳቸው እኒህ እውነተኛ ጳጳስ ለመገደል ሲወሰዱ ጥይት አልፎ ሌላ ሰው እንዳይጐዳ ግንብ ይፈለግ ጀመር። ሩቅ ባለመሔድ ከመካነ ፍትሑ 10 ሜትር ርቆ ግንብ ያለው መግደያ ቦታ ተገኘና ወደዚያ ተወሰዱ። ከገዳዮቹም አንዱ «ፊትዎን ለመሸፈን ይፈልጋሉን?» ሲል ጠየቃቸው። «ይህ የአንተ ሥራ ነው» ሲሉ ብፁዕነታቸው መለሱ። ከመግደያውም ቦታ እንደ ደረሱ ወንበር ቀረበላቸውና ፊታቸውን ወደ ግንቡ ጀርባቸውን ወደ ሕዝቡ አድርገው እንዲቀመጡ ሆኑ።
ከዚያ በኋላ ስምንት ወታደሮች በስተጀርባቸው ሃያ እርምጃ ርቀው ተንበርክከው በተንጠቀቅ ቆሙ። ወዲያው አዛዡ «ተኩስ» በማለት ትእዛዝ ሲሰጥ ስምንቱም ተኩሰው መቷቸው። ግን በስምንት ጥይት ሳይሞቱ ቀሩ።
መሞታቸውንና አለመሞታቸውን ለማረጋገጥ ዶክተር ተጠራ። ዶክተሩም እንዳልሞቱ አረጋገጠ። ከዚያም ሌላ ወታደር በሦስት የሽጉጥ ጥይት ራስ ቅላቸውን መትቶ ገደላቸው። ብፁእ አቡነ ጴጥሮስ ሰማዕተ ጽድቅ በሆነ ደማቸው አተሙ፡፡ አኩሪ በሆነ አባታዊ ሓላፊነታቸው ለአገር፣ ለቤተክርስቲያን፣ለወገን ሁሉ አለኝታነታቸው አረጋግጠው ሐምሌ 22 ቀን 1928 ዓ.ም. በሰማዕትነት አለፉ፡፡
የብፁዕነታቸው አስከሬን ማንም እንዳይወስደው በአስቸኳይ ከአዲስ አበባ ውጭ ማንም በማያውቀው ቦታ በምሥጢር እንዲቀበር ተደረገ። በዚያች ሌሊት በአዲስ አበባ ውስጥ በየቤቱ ልቅሶና ዋይታ ሆነ»።
ይህም ጠላት የሰጠው ምስክርነት በካቶሊካዊው ፓፓ ቡራኬ አገራችንን የወረረውን የፋሺስት ኢጣልያን ጦር አረመኔነትና በአንጻሩ የታየውን የኢትዮጵያን ሕዝብ ጀግንነት ሲያረጋግጥ ይኖራል።
በተጨማሪም ደራሲና ጋዜጠኛ ጳውሎስ ኞኞ «አቡነ ጴጥሮስ እንዴት ሞቱ?» ሲል ሙሴ ፓይላክን ጠይቋቸው እርሳቸውም የሚከተለውን ተናግረዋል።
«አቡነ ጴጥሮስ የተገደሉ ዕለት እዚያው ነበርኩ። መጀመሪያ በእጃቸው ይዘውት የነበረውን መጽሐፍ ቅዱሳቸውን ተሳለሙት። ቀጥለውም የያዙትን መስቀል አማትበው ሕዝቡን ባረኩ። የኪሳቸውንም ሰዓት አውጥተው ካዩ በኋላ መልሰው ከኪሳቸው ከተቱት። ወዲያው ወታደሮች በእሩምታ ተኩሰው ገደሏቸው። ይህ እንደ ሆነ አስገዳዩ ኮሎኔል ተመልካቹን ሕዝብ አጨብጭቡ ብሎ አዘዘና ተጨበጨበ።
ማታ ከአስገዳዩ ኮሎኔል ጋር ተገናኝተን ስንጫወት «በዚህ ቄስ መገደል እኮ ሕዝቡ ተደስቷል» አለኝ። «እንዴት?» ብለው «አላየህም ሲያጨበጭብ?» አለኝ። እኔም «ባታውቀው ነው እንጂ የሕዝቡ ባሕል ሲናደድም ያጨበጭባል» አልኩት።«እንዴት?» ቢለኝ እጄን እያጨበጨብኩ አሳየሁት። እሱም አሳየኝ። «ከዚህ በኋላ የሆነው ቢሆን እኔ ትልቅ ማስታወሻ አግኝቻለሁ» ብሎ አቡነ ጴጥሮስ ሲገደሉ ይዘውት የነበረውን መስቀልና መጽሐፍ ቅዱስ፣ የኪስ ሰዓታቸውን ጭምር አሳየኝ። መጽሐፍ ቅዱሱ መሐል ለመሐል በጥይት ተሰንጥቋል። መስቀሉም ልክ በመሐከሉ ላይ ጥይት በስቶት ወጥቷል። የኪስ ሰዓታቸውንም እንዳየሁት እንደዚሁ ጥይት በስቶታል» ብለው ያዩትን መስክረዋል።»
/ትንሣኤ፣ ቁጥር 58፣ 1978 ዓ.ም./
እኚህ ጀግና አባትና ደገኛ ሰማዕት ፋሽስትን ድል የነሡባቸው መንገዶች 2 ነበሩ፡-
1ኛው) ከሰማዕትነት በፊት በነበራቸው ቆይታ አርበኞችን በየጦር አውድማው በማበርታት እና አገራዊ ወኔ በመስጠት የተወጡት ግዴታ ሲሆን
2ኛው) ደግሞ ስለ አገር ነጻነትና ስለ ሃይማኖታቸው ሲሉ እራሳቸውን ለፋሺስት መትረየስ አሳልፈው መስጠታቸው ነው፡፡ ሆኖም ከሰማዕትነት በፊት ከነበራቸው ተጋድሎ ይልቅ በሰማዕትነት የተወጡት ተጋድሎ ኢትዮጵያን ከግራ ወደ ቀኝ፣ከጨለማ ወደ ብርሃን መርቷታል፡፡
ምክንያቱ ደግሞ በኢትዮጵያውያን አርበኞች ዘንድ ትልቁን ቁጣ የቀሰቀሰውና ለተጋጋለ ጦርነት ያነሣሣው ፋሺስት ኢጣሊያ በአቡነ ጴጥሮስ ላይ የወሰደው ዘግናኝ ግድያ በመሆኑ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ጠላት በአምስት አመት ግዞት ብቻ ኢትዮጵያችንን ለቆ እንዲወጣና ነጻነቷ ዳግም እንዲጠበቅ ትልቁን ድርሻ የተወጡት ጀግናው አቡነ ጴጥሮስ ናቸው፡፡
በሞት አፋፍ ላይ ሆነው የተናገሩትም ሕያው ቃል ኋላ ለተገኘው ነጻነት ጎሕ የሚቀድ ትንቢታዊ ንግግር ነበር ይህም፡- ‹‹ወርውሬ የሃይማኖቴን ጠላት ባልገድልም ሞቼ ፈጣሪዬ በደሜ ይበቀልልኝ!›› የሚለው ኃይለ ቃል ነው፡፡
ይህ ንግግራቸው ከርሳቸው ሞት በኋላ አርበኞች በቁጭት እንደሚነሡና ፋሽስትን ድል እንደሚነሡ የሚያሳይ ሲሆን እራሳቸውን ለሞት የሞሸሩ ዘመን የማይሽራቸው ታላቅ ሰማዕት ናቸው፡፡
የብፁዕነታቸው አኩሪ ታሪክ ትውልድ ሲያዘክርላቸው እንዲኖር መታሰቢያ ይሆናቸው ዘንድ ሐምሌ 16 ቀን 1938 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ እምብርት ሐውልት ቆሞላቸዋል። የተጋዳዩና ሰማዕቱ አባታችን በረከት ይደርብን። አሜን።
ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች!
ወስብሀት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር!
አሜን!
የመረጃ ምንጭ፦ ሐመር መጽሔት፣ ዲያቆን መርሻ አለኸኝ /ዜና ጳጳሳት ኢትዮጵያውያን/፣ ቢኒ ዘልደታ
Blogger Comment
Facebook Comment