ወደ ርስታችን ያልተመለስንበት ኢዮቤልዩ


“አምሳኛውንም ዓመት ትቀድሳላችሁ ፥ በምድሪቱም ለሚኖሩባት ሁሉ ነጻነትን ታውጃላችሁ ፤ እርሱ ለእናንተ ኢዮቤልዩ ነው፤ ሰው ሁሉ ወደ ርስቱና ወደ ወገኑ ይመለስ ።” (ዘሌ. 25፡10)

ዛሬ መስከረም 2 ፣ 2017 ዓ.ም. ነው ። እንደ ሶቭየት ሕብረት እና እንደ ቻይና በኮሚዩኒዝም ጸንተን ቀጥለን ቢሆን ኖሮ ምናልባትም በዚህ ቀን የሚደረገው በዓል በታሪካችን ታይቶና ተሰምቶ የማይታወቅ በሆነ ነበር ። እንደ አንዳንድ “የድሮው ሥርዓት ናፋቂዎች” ቢሆን ደግሞ – ማቅ ለብሰን እና አመድ ነስንሰን የምናለቅስበት – መጽናናትንም የማንወድበት ቀን በሆነ ነበር ። ግን ቀድሜ እንደምገምተው ከሆነ – አሁን አሁን ስለ ብዙ ነገሮች እንደምናደርገው ሁሉ – ምንም ሳይመስለን እና ምንም የተለየ ነገር ሳይፈጠር ያልፋል ። የተወሰኑ የሬዲዮ እና የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች ይኖራሉ ፤ አንዳንድ ዩቲዩበሮች ይንጫጫሉ – ቲክቶከሮች ስለ ጉዳዩ ምንነት የሚያውቁ አይመስለኝም ። ምናልባት ጥቂት ጽሑፎች ይጻፋሉ ፤ ይህን ጽሑፍ ጨምሮ ። ሌላ ብዙ ነገር አይሆንም ።

መስከረም ሁለትን በዋናነት ከንጉሡ ከሥልጣን መውረድ ጋር የሚያያይዙ ትረካዎችን እንሰማለን ብዬ እጠብቃለሁ ። ደርጉ እንዴት ይህን እርምጃ ለመውሰድ እንደ ደፈረ ፥ ጓድ ደበላ ዲንሳ እንዴት ለንጉሡ የደርጉን ውሳኔ እንዳነበበላቸው እና እሳቸው እንዴት ያለ መልስ እንደሰጡ ፥ ራስ እምሩ ለንጉሡ ስለሰጧቸው ምክር ፥ ከዚያ በኋላ እንዴት ቮልስ ዋገን ውስጥ እንዳስገቧቸው ፥ ሰዎች እንዴት ሌባ እያሉ እንደጮሁባቸው . . . ወዘተርፈ ። ነገር ግን ጉዳይ ልናደርጋቸው ይገባሉ ብዬ የማስባቸው ነገሮች ጉዳያችን ይሆናሉ ብዬ አላስብም ። ያን የታሪክ ምዕራፍ ከትናንት አምጥቶ የዛሬ ኑሮአችን አካል የሚያደርግ ወይም የዛሬ ኑሮአችን አካል እንደሆነ የሚያስረዳን አቅርቦት ይኖራል ብዬ አላስብም ። እንዲህ ማለቴ ደስ ላያሰኝ ፤ ጨለምተኛ ሊያሰኘኝም ይችላል – ነገር ግን አይፈረድብኝ – ተስፋ የሚሰጠኝ ብዙ ነገር አላየሁም እስካሁን ።

ባለፉት ስድስት ወራት በተለያዩ መድረኮች የየካቲቱን “ዐብዮት” 50ኛ ዓመት አስመልክቶ አንዳንድ ውይይቶች ሲቀርቡ ተመልክተናል ።  ዳግመኛም ባለፉት 40 ያህል ዓመታት – ስለዚያ ሒደት እና ስለተከተሉት ሁነቶች የሚገባውንም ያህል ባይሆን የተጻፉ መጻሕፍት እና የተደረጉ ጥናቶች ፣ ውይይቶች እና መጠይቆችም ነበሩ ። ነገር ግን እነዚህን ሁሉ ባየሁበት መጠን ከላይ እንዳልሁት በመሠረታዊነት መነሣት የነበረባቸውን ጉዳዮች በሚገባ አንሥተው ጉዳይ አድርገዋቸዋል ብዬ አላስብም ። አሁንም ቢሆን የደፈረሰው አልጠራም ። ሐሳቦቻችንም ሆኑ ሩጫዎቻችን ቦታ ቦታ አልያዙም – መደምደሚያም ባይሆን መሰብሰቢያ ምዕራፍ አላገኙም ።

ይህን ስል ከዚያ ሁነት እና ሒደት በኋላ ሁላችንም ወደ አንድ ዓይነት ሐሳብ እና ድምዳሜ መድረስ ነበረብን ፤ በተመሳሳይ መንገድ ለመሔድም ስምምነት ሊኖረን ይገባ ነበር ለማለት አይደለም ። ቢሆን ደስ ባለኝ ነበር ፤ አይሆንም እንጂ ። ነገር ግን ይህ እንኳን ቢቀር ፥ ሁለትም ፣ ሦስትም ፣ አራትም ጎራዎች ይኑሩ ፤ ግን የተብራራ እና የተገለጠ የሐሳብ መሠረት ላይ የቆሙ እና ከየቆሙበት ሥፍራ ታሪካዊውን እውነታ አጥንተው ፣ ተርከው እና ተንትነው ስለነገሩ ግልጥ ያለ አቋም የያዙ ቡድኖች ቢኖሩ ምንኛ የታደልን በሆን ነበር ። የኛ ሁኔታ ግን ከከባድ ስካር በኋላ ጠዋት ነቅቶም ስካሩ ያልለቀቀው ሰው ዓይነት ነው ። ምን እንደተፈጠረም ጥርት ብሎ አይታወሰንም – አሁን ያለንበትንም ሁኔታ በቅጡ አልተረዳንም ። ከስካሩ ጠብ ያተረፍነው ቁስልም አልታከመም ።

ምንም እንኳን ስለ ጉዳዩ የተጠናቀቀ ዕውቀት ባይኖረኝ እና አቅሜ ውሱን እንደሆነ ብረዳም ይህን ጽሑፍ ለመጻፍ ራሴን ያስጨነቅሁት እና እናንተንም የምዘበዝባችሁ ስለ ነገሩ መነሣት የሚገባቸው መሠረታዊ ነጥቦች እንዳሉ ስላሰብሁ ነው ። እነዚህ ነጥቦች ምንም እንኳን በበለጠ ሥልጣን ፣ ስለት እና ርቃቄ ቢነሡ የተሻለ የነበረ ቢሆንም ጨርሶ ሊያነሧቸው የማይቻሉ ውስብስብ ግን አይደሉም ። እርግጥ ነው – ስንከተላቸው ፣ ወይም እነሱን ያካተተ ተዋሥኦ ለማድረግ ስንሞክር ነገሩ መወሳሰቡ አይቀርም ፤ ለመጠቆም ያህል ግን በኔ አቅም የማይሞከር አይደለም ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ ።

ወደ ዝርዝሩ ከመግባቴ በፊት ግን የጽሑፉን ገዢ መንፈስ ጠቅለል አድርጌ ለመግለጽ እሞክራለሁ ። እንደምመለከተው ከሆነ ፥ ተዋሥኦዎቻችን – ተዋሥኦ ሊባሉ ከቻሉ – ከመሠረታዊ ጥያቄዎች ተፋትተዋል ። ብዙ ጊዜ ዐቢይ ጉዳያችን “ወቅታዊው” እና “ተግባራዊው” ነገር ነው ። መሠረታዊ እና ሐሳባዊ የሆኑትን ረቂቅ ጥያቄዎች ጉዳይ ማድረግን ከሥራ ፈትነት ቆጥረነዋል ። የሚነሡ ሐሳቦቻችን አላማ እና መመዘኛ – መሠረታዊ አመክንዮአቸው እና ውሳጣዊ ስምምነታቸው ሳይሆን “አዋጭነታቸው” ነው ። ማለትም ተቀባይነት ቢያገኙ እና ቢተገበሩ ያስገኙልናል ብለን የምናስበው ነገር ነው ። ሁልጊዜም ቢሆን ታዲያ የጠበቅነውን አላገኘንም ፤ እንክርዳድ ዘርቶ ስንዴ የሚያጭድ ማነው ? ፍላጎቶቻችንን ፥ ከየት እና እንዴት እንደመጡ ሳያሳስበን ፥ ፈላጭ ቆራጭ አድርገን ሾመናቸዋል ። እምነት ብለን የማንጠራቸው ብዙ እምነቶች አሉን ። በእኛ ቤት እነዚህ ነገሮች ማስረጃ እና ማረጋገጫ የማያሻቸው እውነቶች ናቸው ። በውስጣችን እጅግ ከመዝለቃቸው እና ከደማችን ጋር ከመዋሃዳቸው የተነሣ – ሃይማኖት ብለን ለያዝነው ነገር እንኳን ብዙ ማረጋገጫ እና ማስተማመኛ ስንሻ – እነዚህን ስውራን እምነቶቻችንን በተመለከተ ግን ጥያቄ የሚያነሣባቸው ሰው ቢገኝ እንኳን ጤንነቱን ከመጠራጠር በቀር የመከራከር እና የማስረዳቱ አስፈላጊነት ፈጽሞ አይታየንም ። ይህ ጽሑፍ ሲያልቅ – ምናልባት ጤንነቴን ትጠራጠሩ ይሆናል ፤ ነገር ግን . . . ምናልባት እኔም ጤንነቴን እጠራጠረው ይሆናል ።

፠፠፠

ራሴን ለማጥፋት ብወስን እና ይህን ለማድረግ የተሻለው መንገድ ከከፍታ ላይ ራሴን መወርወር ነው ብዬ ባምን ፥ ነገር ግን ለመወርወር የሚሻለው 10ኛው ፎቅ ወይስ 11ኛው ፎቅ የሚለው ጥያቄ ነፍሴን ቢያስጨንቃት ፥ ስለዚህም ጉዳይ ወዳጆቼን ሰብስቤ ባማክራቸው – እነሱም ለሁለት ተከፍለው ግማሾቹ ‘10ኛው ፎቅ ነው ትክክለኛ ምርጫ’ ፥ የቀሩት ደግሞ ‘የለም 11ኛው ፎቅ መሆን አለበት’ እያሉ ፥ እኔን ከመምከር አልፈው ፥ ስሜታቸው ገንፍሎ እርስ በእርስ ሲጨቃጨቁ እና ለጸብእ ሲጋበዙ ብትደርሱ ፥ ነገሩን ስትረዱ ምን ይሰማችኋል ? “ዐብዮቱ” ላይ እያደረግን ስላለው ተዋሥኦ እንዲያ ነው የሚሰማኝ ።

“የዐብዮቱን” ሒደት የሚተርኩትም ሆኑ የሚተነትኑት ፥ እንዲሁም ተከትለውት በመጡት ሁነቶች ላይ ያሳረፈውን ተጽዕኖ የሚያብራሩ መጻሕፍት እና ውይይቶች ውስጥ አንድ ዓይነት ስምምነት ይታያል ። ምንም እንኳን ለሚያነሧቸው ጥያቄዎች የሚሠጧቸው መልሶች እና የሚያቀርቧቸው ትንተናዎች ልዩ ልዩ እና አንዳንዴም ፍጹም የሚቃረኑ ቢሆኑም – መልስ በሚሹላቸው ጥያቄዎች ዙሪያ ግን ሥሙር ሆነው ይታያሉ ። ሁል ጊዜም ጉዳይ የሚያደርጉት  “በዐብዮቱ” ዘመን በዐብዮተኞቹ የተነሡትን ጥያቄዎች ፣ በተለይ ደግሞ በመካከላቸው ልዩነት የፈጠሩትን ጉዳዮች ነው ።

ለምሳሌ ያህል እስከ ዛሬ ስለዚህ የታሪክ ክፍል ከሚነሡ ዐበይት ጥያቄዎች መካከል ጥቂቶቹን ላንሣ ። ተማሪዎቹ “የብሔር ጥያቄን” ማንሣታቸው ትክክል አልነበረም ወይ ? “የብሔርን ጥያቄ” ለመፍታት “ሕብረ ብሔራዊ” የነበሩት ድርጅቶች አካሔድ ወይስ “የብሔረሰብ ትግል” ያካሔዱት ድርጅቶች መስመር ነበር ትክክል ? የመሬት ዐዋጁ “የመሬት ጥያቄን” ፈትቷል ወይስ አልፈታም ? “ዐብዮቱ” ከፈነዳ እና ደርግ የበላይነቱን ይዞ የመሬቱን አዋጅ ካወጀ በኋላ የመኢሶን “የሒሳዊ ድጋፍ” መስመር ወይስ የኢሕአፓ “ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥት አሁን” መስመር ነበር ትክክል ? በቀይ እና በነጭ ሽብሮች ለተፈጠረው እልቂት ተጠያቂው ማነው ? “ዐብዮቱ” ግቡን መትቷል ወይስ ሐዲዱን ስቷል ?

በዐብዮተኞቹ ዘንድ እነዚህ ጥያቄዎች የተነሡት እና በመካከላቸውም እነዚህ የልዩነት ነጥቦች የተፈጠሩት – በተማሪዎቹ መካከል መሠረታዊ ስምምነት ስለነበረ ነው ። ለመለያየትም ስምምነት ያስፈልጋልና ። እንደሚታወቀው የተማሪው ንቅናቄ በጠቅላላው ማርክሳዊ-ሌኒናዊ ነበረ ። የማርክስን መነሻዎች እና ትንተናዎች የተቀበለ እና ያስቀመጣቸውን ግቦችም ሁሉ ማሳካትን ሕልም ያደረገ እንቅስቃሴ ነበር ። ከላይ የተነሡት ጥያቄዎች ሁሉ በማርክስ መነሻዎች እና ትንተናዎች ማዕቀፍ ውስጥ የተነሡ ነበሩ ። ስለዚህ በወቅቱ እነሱ እነዚህን ጥያቄዎች ጉዳይ ማድረጋቸው ሊገርመን አይችልም ።

እነዚህን ጥያቄዎች “ከዐብዮቱ” በኋላ በድጋሚ አንሥተን ጉዳይ ማድረጋችን እና በአንዱ ወይም በሌላው ወገን ሆነን አጥብቀን መከራከራችን ግን አስደናቂ ነው – ማናችንም ማርክሳውያን እና ሌኒናውያን አይደለንምና ። ባለፉት 30 ዓመታት “ዐብዮቱን” ወደኋላ በመቃኘት በሚደረጉት ሕዝባዊም ይሁኑ “ምሁራዊ” ተዋሥኦዎች ውስጥ ወይም በወቅታዊ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ በሚደረገው ሲታፌም ቢሆን ማርክሳዊ የሆነ ወጥ አቋም ያላቸው ሰዎች እና ቡድኖች አላውቅም ። በወቅቱ የነበሩት ዋና የፖለቲካ ቡድኖች ወይም ቅሪቶቻቸው (ኢሕአፓ ፣ መኢሶን ፣ ሕወሓት ፣ ኦነግ ወዘተርፈ) ማርክሳዊነታቸውን ትተዋል ። “በመርሕ ደረጃ” ቢያንስ የሊበራል ባለ ብዙ ፓርቲ ዲሞክራሲ አቀንቃኝ ናቸው ። ማርክሳዊ ሆነው የደርግን ዘመን እንኳን የዘለቁ ድርጅቶች አይገኙም – ኢሠፓን ራሱን ጨምሮ ።

በወቅቱ የዐብዮታዊ እንቅስቃሴው መሪዎች ወይም ተሳታፊ የነበሩ እና በኋላ እንቅስቃሴያቸውን እና ድርጅቶቻቸውን ወክለው ታሪኩን የመዘገቡልን ሰዎች በተማሪነት ዘመናቸው እንዴት ማርክሳውያን ሊሆኑ እንደበቁ ሲያብራሩ በዋናነት በዘመኑ ማርክሳዊነት “ፋሽን ስለነበረ” በዚያ መንገድ ሔድን ይላሉ እንጂ ማርክሳዊነት ያኔም አሁንም ትክክል ነው ብለው አፋቸውን ሞልተው አይናገሩም ። ምሳሌዎች[1] መጥቀስ እችላለሁ – በያይነቱ ። ከመኢሶን ሰዎች እንጀምር ።

“ሌላው ነገር ደግሞ የኛ ትውልድ በዚያ ዘመን ኢትዮጵያ ውስጥ ይፈጸም የነበረውን ግፍና ዓለም ላይ ኃያላን መንግሥታት ያደርሱት የነበረውን ጭቆና ለመቃወም እስከተነሣ ድረስ ፣ ይህን ርዕዮተ ዓለም ላለመከተል ምርጫ አልነበረውም ። ዛሬ የደርግ “ሶሺያሊዝም” አስመርሯቸው ጭምር ዘውድ አምላኪ የሆኑ ‘ኃይሌ ማረኝ’ ባዮች በዝተዋል ። እኛ ግን የፖለቲካ ዓይናችን ሲከፈት ‘ከምናውቀው ሰይጣን የማናውቀውን መልአክ’ ላለመናፈቅ ቀጥተኛ ምክንያት አልነበረንም ።”[2]

“(የመኢሶን መስራች አባላት ፣ ምንም እንኳን ለማርክሲዝም ሌኒኒዝም ወጣንያን የነበሩ ቢሆንም) ነገር ግን ሁሉም ደግሞ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ዐበይት ጠላቶች ፊውዳሊዝም እና ኢምፔሪያሊዝም መሆናቸውን የተረዱ ፣ ጭቆናና ብዝበዛ ከኢትዮጵያ እንዲጠፋ ፤ ዲሞክራሲ ፣ ፍትሕ እና እኩልነት እንዲነግሡ ፤ የብሔሮች ጭቆና እንዲወገድ ፤ አገራቸው እንድትበለፅግ ፤ ክብርና ኩራትን እንድትጎናጸፍ ፤ ለዚህም ሕዝባዊ ዲሞክራቲክ መንግሥት መቋቋም እንዳለበት የሚያምኑና እስከ መጨረሻውም ድረስ ለመታገል ቆርጠው የተነሡ ነበሩ ። ከዚህም አንጻር ከላይ እንዳወሳነው ፣ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ፣ በ1950ዎቹ ዓመታት ውስጥ በዓለም አቀፍ ደረጃ ይካሔዱ በነበሩት የሦስተኛው ዓለም ሕዝቦች የነፃነትና የፀረ ኢምፔሪያሊስት ትግሎች ገናናነት ጭምር የተቀሰቀሱ ነበሩ ።”[3]

የኢሕአፓ አባል የነበሩት እና በኋላ ግን በታሪክ ምሁርነታቸው “ወገንተኛ ያልሆነ” የተማሪውን እንቅስቃሴ ታሪክ ጽፈው ያበረከቱልን ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴም እንዲሁ ማርክሳዊነት የኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ብቻ ገንዘብ እንዳልነበረ ያትታሉ ።

“(Professor Mesay Kebede) seems to believe that radicalism or infatuation with Marxism-Leninism was a unique malady of Ethiopian students. But, (as will be demonstrated later), both had universal resonance, particularly in the 1960s. The negation of tradition and the dream, as it turned out to be, of constructing a new world untainted by the ills and imperfections of the past were not a monopoly of the Ethiopian youth.”[4]

ከኢሕአፓ መሪዎች አንዱ የነበሩት አቶ ክፍሉ ታደሰም ይህን አባባል ያጸናሉ ። (በእርግጥ በመጻፍስ እሱ ነበር የሚቀድመው ።)

“የዚህ ትውልድ ግንባር ቀደም አባላት ፣ በቅን ፍላጎት ተነሥተው ነበር አካባቢያቸውን ለመለወጥ የመጀመሪያ ተቃውሟቸውን የተነፈሱት ። የከበባቸው ኦሪታዊ የአሠራር ሁኔታም ፣ እያዘገመ ሔዶ ይለወጣል የሚል ተስፋም ነበራቸው ። በፖለቲካው አደባባይ ላይ ወጣ ወጣ ማለት የጀመሩት ይህን ቅን ጥረታቸውን የሚያይና የሚያበረታታ በማጣታቸው ነበር ። አማራጮችን ፍለጋ ድንበር ተሻግረው በመሔድ ፣ እነርሱም ሆኑ መንግሥት በቅድሚያ ባላሰቡትና ባልወጠኑት አዲስ መላ ላይ የሙጥኝ አሉ ። በርግጥም ዛሬ ታሪክ እንደሚመሰክረው ፣ እነዚህ ምሁራን የኋላ ኋላ የኅብረተሰቡ ነገረ ፈጅና የለውጥ ቆስቋሾች ሆነዋል ።

“ከ1950ዎቹ መጨረሻ እስከ 1960ዎቹ መጀመሪያ ድረስ የነበረው ወቅት በአፍሪካ የፀረ ቅኝ አገዛዝ ትግል ያየለበት ፣ በላቲን አሜሪካና በሩቅ ምሥራቅ አገሮች የሶሻል ዐብዮቶችና እንዲሁም በአሜሪካ የሲቪል መብቶች እንቅስቃሴዎች የነበሩበት ዘመን ነበር ። በተጨማሪ ፣ ወቅቱ የሶቭየት ኅብረትና ቻይና እንደ ዐበይት ዓለም አቀፋዊ ሶሻል ኃይሎች መጥቀው የወጡበትና የታወቁበትም ዘመን ነበር ። ስለሆነም ፣ ጤና ላጣች ሀገሩ መፍትሔ ፍለጋ ፣ ኢትዮጵያዊው ሥር-ነቀል ለውጥ አቀንቃኝ ትውልድ የገሰገሰው ወደ እነዚህ ሀገሮች ሆነ ።”[5]

ምናልባት አንዳንድ ግለሰቦች ሲቀሩ – “የዚያ ትውልድ” አባላት ማርክሳዊነትን “ፋሽንነቱ ሲያልፍ” ትተውታል ። አሁን ኢምፔሪያሊዝም ስለ ጋረጠው ስጋት እና ስለ ቢሮክራሲው ሤራ እያሰቡ እንቅልፍ አያጡም ። ወይም የቡርዧውን መደብ አጥፍቶ ሠራተኛውን የምርት ባለቤት ስለማድረግ አያልሙም ። አንዳንዶች የትግሉን ዓለም አቀፋዊነት ክደው ኢትዮጵያውያን ከሌሎች ሕዝቦች የተለዩ ስለመሆናቸው ይናገራሉ ። በጭቁን ሕዝቦች መካከል ከትብብር ይልቅ ፉክክር እና እኔ እበልጥ ባይነትን የሚያሰፍን ብሔርተኝነትን ያራምዳሉ ። ሌሎች ሃይማኖት ሁሉ አላቸው ።

ያም ሆኖ ግን ስለ “ዐብዮቱ” ዘመን ሲጽፉና ሲናገሩ ፥ በዚያ ዘመን በማርክሳዊነት ማዕቀፍ ሲነሡ የነበሩ ጥያቄዎችን ደግመው እያነሡ በእነሱ ላይ መከራከርን ፣ በዘመኑ የተደረጉ ውሳኔዎችን መከላከልን ፣ ሌሎች ውሳኔዎችን ማውገዝን ዐቢይ ጉዳያቸው ያደርጉታል ። ምንም እንኳን አሁን ማርክሳዊነት ትክክለኛው መንገድ ነው ብለው ባያስቡም (ቢያስቡ አሁንም ማርክሳውያን ይሆኑ ነበርና) ነገር ግን ማርክሳውያን በነበሩበት ዘመን ስትራቴጂያዊ እና ታክቲካዊ ውሳኔዎቻቸውን በትክክል አድርገው ቢሆን ኖሮ ፥ አንዱ ወይም ሌላው ሁነት በተለየ መንገድ ሔዶ ቢሆን ኖሮ በእጅጉ የተለየ ውጤት ላይ ይደርሱ የነበረ እና ሀገሪቱም አሁን ከሔደችበት በጣም በተሻለ መንገድ ተጉዛ ፥ የተሻለ ሁኔታ ላይ ትገኝ የነበረ አድርገው የሚያስቡ ይመስላሉ ። ትልሞቻቸው እና እቅዶቻቸው አለመሳካታቸው ፣ ውጥናቸው ከግብ አለመድረሱ ያንገበግባቸዋል ። ለምሳሌ ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ መኢሶን እና ኢሕአፓ የትኞቹ ቦታዎች ላይ ዋናዎቹን ስሕተቶች እንደፈጸሙ ሲያስረዱ እንዲህ ይላሉ።

“Had (the divisions that resulted in antagonism between the student-body abroad before the revolution) been confined to the student and leftist movement outside the country, they might have remained the senseless bickering of exiles, with little impact on the domestic scene. Unfortunately for the Left and for the country at large, they were transposed onto the home territory after 1975, impacting negatively on the revolutionary struggle, resulting in the death of thousands of young Ethiopians, and culminating in the mutual destruction of both parties and the ascendancy of the ethno-nationalist opposition. Both parties had their share of responsibility for that fateful outcome. Ma’ison’s strategy of allying with the Derg was probably the greatest strategic mistake it has made in its history. It certainly proved costly both to itself and the revolution. The strategy might well have arisen from both the uncompromising opposition of the EPRP and Ma’ison’s own relative organizational weakness, more particularly its failure to penetrate the youth and working class to the same degree as EPRP. But the belief that it could temporarily ally with the Darg to strengthen itself and then shunt it aside to emerge as the dominant force dominant force proved singularly naïve…

“As for EPRP, while its opposition to the Darg was justified, the strindency with which it pursued it and the intransigence it showed towards the pro-Darg leftist parties could be said to have contributed to the final grim outcome…. This policy (of urban insurrection and assassination) eventually proved counter productive, however. On the one hand, it drove the Darg to an even greater repression, including the launch of the notorious Red Terror, leading to the eventual decimation of all leftist forces. Secondly, divergence within the EPRP leadership over the strategy of urban guerilla warfare led to a split within the organization. This also accelerated the collapse of EPRP’s urban struggle as some members of the faction (dubbed anja) sought refuge with the Darg and exposed the structure of the organization, leading to the massive arrest, torture and liquidation of EPRP members.”[6]

አቶ አንዳርጋቸው አሰግድም መጽሐፋቸውን ሲያጠቃልሉ በመኢሶን የተፈጸሙት ዐቢይ ስሕተቶች ምን ነበሩ ብለው ይጠይቁና እንደሚከተለው ይመልሳሉ ።

“በመኢሶን ላይ መሰንዘር ያለበት የመጀመሪያው ሂሳዊ ጥያቄ (የሂሳዊ ድጋፍ) መስመሩን የሚመለከት አይደለም ። ይልቁኑ መኢሶን ለሂሳዊ ድጋፍ መስመሩ የቱን ያህል ታማኝ ሆኗል ? ብሔራዊ ዲሞክራቲክ አብዮት በሚል ላስተጋባው ፕሮግራም ምን ያህል ታማኝ ሆኖ ሠርቷል ? የሚሉት ናቸው . . .

“መኢሶን እነዚህን ሁለት መሠረታዊ ጉዳዮች ሙሉ በሙሉ ተርጉሟል ለማለትም አይቻልም ። ‘ሂስንና ድጋፍን እንደሁኔታው ማፈራረቅ’ የሚለው መመሪያ በተለይ ከጥር/የካቲት 1969 እስከ ነሐሴ 1969 በነበረው የፍጥጫ ዘመን ወቅት በእጅጉ ሰልሎ ነበር ። መኢሶን በዚህ ወቅት በአንዳንድ መሠረታዊ ጥያቄዎች ላይ . . . ነፃና ግልጽ አቋም ከመግለጽና ከማስተጋባት ታቅቦ ተገኝቷል ። ይህ አንደኛው ስሕተቱ ነው ።

“ሁለተኛ ፣ የድርጅቱን የኅቡእ እና የትጥቅ ትግል በውል የማደራጀቱ ጉዳይ በተግባር ሳይተረጎም ቀርቷል ። ይህም ዙሮ ዙሮ መኢሶንን ራሱን ለመከላከል የተሳንው ድርጅት አደረገው ። እንዲያም ሲል በቀላሉ የተመታ ድርጅት አደረገው ። እንዲያም ሲል በቀላሉ የተመታ ድርጅት ሆነ ። በእኔ እምነት ትልቁ የመኢሶን ስሕተት ይህ የኋለኛው ነው ።

“ነገር ግን መኢሶን በብሔራዊ ዲሞክራቲክ አብዮት ፕሮግራም አንፃርም አንዳንድ መሠረታዊ ስሕተቶችን ፈጽሟል ። በዚህም ረገድ – ወሳኝ የሆነ ባይባልም ቅሉ – ለአብዮቱ መቀልበስ አስተዋጽኦ አድርጓል ።”[7]

እነዚህን መጻሕፍት ፥ በተለይ ደግሞ እንዲህ ያሉትን ክፍሎቻቸውን ፥ ሳነብ የማስተናግደው ስሜት – አንዳንዴ በጣም የማሳከክ ስሜት እየተሰማኝ – ዙሪያ ገባውን በችኮላና በኃይል እያከክሁ ግን ትክክለኛውን ቦታ ማግኘት ስላልቻልሁ ፥ ማሳከኩ ምንም ጋብ ሳይልልኝ እየቀረ እንደምበሳጨበት ጊዜ ነው ። እነዚህም ጸሐፍት ያን ሁሉ ነገር ጽፈው – ግን ዋናውን ነጥብ እንደሳቱት አስባለሁ ።

አንድ ክርስቲያን ያልሆነ ሰው – አንድ ባሕርይ ወይስ ሁለት ባሕርይ የሚለው ክርክር ውስጥ ሊሳተፍ ይችላል ? በስሜት እና በክረት ሊያደርገው ቀርቶ ? የጸሐፊዎቻችን ትንተና እና ቁጭት ሁሉ እንዲህ ያለ ይመስለኛል ። ከላይ እኔ በቅድሚያ የዘረዘርኋቸውም ሆኑ ቀጥዬ ከጸሐፍቱ ያመጣኋቸው ጥያቄዎች እና ጉዳዮች ሁሉ በማርክሳዊነት መነሻዎች ላይ የተገነቡ ናቸው ። ስለሆነም – ጥያቄዎቹን ስናነሣ የማርክስን መነሻዎች ተቀብለን ነው ሊሆን የሚችለው – በግልጽ ባንለው ወይም ባናውቀው እንኳን ። ነገር ግን በጸሐፊዎቻችን ዘንድ ይህ እውነታ በጭራሽ ጉዳይ አልተደረገም ። ዕውቅና እንኳ አይሰጠውም ።

ይህ ችግር ደግሞ በጠቀስኋቸው ጸሐፊዎች ወይም በሌሎች የዐብዮታዊው እንቅስቃሴ ተሳታፊዎች የተወሰነ አይደለም ። “የዐብዮቱ” ተቃዋሚዎች እና አውጋዦችም ጭምር በተመሳሳይ ወጥመድ ተይዘው ይታያሉ ። “ከዐብዮቱ” ጋር በተያያዘ ከሚያከራክሩት ጉዳዮች ይልቅ አከራካሪ ያልሆኑት ጉዳዮች ይህን የተሻለ ያስረዳሉ ። ለምሳሌ ፥ የብሔር ጭቆና የነበረ መሆኑ ቢያከራክርም – የመደብ ጭቆና መኖሩ ግን ሲያከራክር አላይም ። የታወቀ እና የተረዳ መስሎ ይታያል ። የመሬት አዋጁ መሬትን ከመንግሥት ይልቅ የግል ይዞታ ማድረግ ነበረበት ተብሎ ቢተችም በአመዛኙ ዐቢይ ድል ተደርጎ ነው የሚቆጠረው ። ወይም የሃይማኖት እኩልነት መታወጁን እና መንግሥት እና ሃይማኖት የመለያየታቸውን መርሕ የሚቃወም ድምፅ ጎልቶ አይሰማኝም ። የሴቶች እኩልነት በዐብዮታውያኑ ዐቢይ ጉዳይ ሆኖ መነሣቱንም የሚኮንን ሰው አይገኝም – እንደማየው ከሆነ ። ነገር ግን እነዚህም ጉዳዮች ከላይ እንዳነሣናቸው አከራካሪ ጥያቄዎች ማርክሳዊ መነሻ ያላቸው እና በማርክሳዊነት የተቃኙ ናቸው ። ስለዚህ እነዚህ ጉዳዮች መነሻዎቻቸውን ሳይጠይቁ በመቀበላቸው  “ዐብዮቱን” የሚኮንኑ ሰዎች ሳይቀሩ በዐብዮታውያኑ ባሕር ውስጥ እየዋኙ ይገኛሉ ። ነገር ግን ጨርሶ ልብ የሚሉት አይመስሉም ።

ማርክሳዊነትን ትተነዋል እንላለን ፤ ግን ዛሬም በማርክሳውያን ቃላት ስለ ማርክሳዊ ሐሳቦች እንሟገታለን ፤ ለማርክሳውያን ችግሮችም ማርክሳውያን መፍትሔዎችን እናቀርባለን ። ተዋሥኦዎቻችን ከመቀንጨራቸው የተነሣ – እዚህ ውስጥ ምንም ቅራኔ አይታየንም ።

ይህ ተቃውሞዬ ተቃውሞ እንደሚገጥመው አውቃለሁ ። “ለብሔሮች ፣ ለጭሰኞች ፣ ለሴቶች ፣ ለወዛደሮች ፣ መብት እና ጥቅም ለመቆም ፥ የሃይማኖትን ነጻነት እና እኩልነት ለማቀንቀን ማርክሳዊ መሆን አያሻኝም ። ማርክሳዊ ባልሆንም የጥያቄዎቹን ፍትሐዊነት ስለምቀበል ከማርክሳውያን ጋር በእነዚህ ጉዳዮች እተባበራለሁ ፤ ቃልና ሐሳብ ፣ ዘይቤም እንዳሻኝ እዋሳለሁ ።” የሚሉኝ ይኖራሉ ። የተዋሥኦዎቻችን ችግር ልብም ያለው እዚህ ጋ ነው ።

ዐብዮታውያኑ በወጣትነት ዘመናቸው የማርክሳዊነትን መነሻዎች በማጥናት እና በማስጠናት ብዙ ጊዜ እና ጉልበት ያጠፉ እንደ መሆናቸው – “የዐብዮቱ ዘመን” ጥያቄዎች ከማርክሳዊነት መነሻዎች ጋር በጥብቅ የተሳሰሩ መሆናቸው እና መነሻዎቹን ሳይቀበሉ ወደ ግቦቹ መድረስ አለመቻሉ ግልጽ ሊሆንላቸው ይገባ ነበር ። ነገር ግን እነሱም ማርክሳዊነትን ትተው – ማርክሳዊ ግቦችን ግን ይዘው መቀጠል እንደሚችሉ ያስባሉ ።

“ሆኖም ግን ፣ መጽሐፉ የተሠዋ ትውልድ ፣ የተሸነፈ ድርጅት ፣ የተቀለበሰ ዐብዮት ታሪክ ቢሆንም ፣ አንባቢ እንደጉዞ ፍታት እንደማይወስደው ተስፋየ ነው ። የዚህን ትውልድ ቆንጆ ሕልም ይዞ ፣ ስሕተቶቹን ግን አስወግዶ ሶሺያሊዝሙ ቀርቶ ሕዝቧ በሰላም በልቶ የሚያድርባት ኢትዮጵያን ለመመሥረት እንደ ተደረገ የትግል ጥሪ እንጂ ።”[8]

“Whatever the failings of the global student movement, it would be difficult to dismiss all the issues they raised as youthful escapades hat can be explained away by psycho-historical analysis, and not all the problems raised at the time could be said to have gone away. Vietnam may be a matter of the past, but Iraq is still with us, living testimony to to the arrogance of power…. The student movement, the Ethiopian included, has to be viewed not as a philosophical issue but as a historical phenomenon…. (an exhaustive and objective historical) investigation has a better chance of appreciating the fundamental validity, for instance, of the two paramount issues raised by the Ethiopian student movement – the agrarian and the national question – while taking exeption to the solutions prescribed.”[9]

በእነዚህ አስተያየቶች ውስጥ ትልቅ የመሠረታዊ አመክንዮ ክፍተት እንመለከታለን ። ጸሐፊዎቻችን ሁል ጊዜም ቢሆን አመክንዮ እሙን ከሆኑ (ናቸው ተብለው ከሚታሰቡ) ቀዳማዊ መርሖች (first principles) መነሣቱ ግድ እንደሆነ ያልተረዱ ይመስላል ። በማርክሳዊ እሳቤም ሆነ በእስልምና ፣ በሊበራሊዝም ወይም በሌላ አመለካከት ፣ ፍልስፍና ፣ ርእዮት ፣ ሃይማኖት – በአንድ ወይም በሌላ ምክንያት – መለኮታዊ መገለጥ ወይም ራሱን በራሱ የሚያስረዳ እውነት (ስምዐ ርዕስ ሐቅ – slef evident truth) ናቸው ብለን በማመን ለአመክንዮዎቻችን መሠረት አድርገን የምንቀበላቸው መነሻዎች አሉ ። እነዚህ ነገሮች እንዲህ ስለተባሉ – ሙግት ሊደረግባቸው አይችልም ማለት አይደለም ። ከአንድ አስተሳሰብ ወይም ርእዮት ውጪ የሆነው ሰው እነዚህ መነሻዎች እርስ በራሳቸው ወይም ከእነሱ ከሚቀጥሉት የርእዮቱ ሐሳቦች እና መዳረሻዎች ጋር አለመግጠማቸውን በማሳየት ርእዮቱን እና መነሻዎቹን ጥያቄ ውስጥ ሊያስገባቸው ይችላል ። ነገር ግን በሁሉም አይነት አመለካከት እና ርእዮት ውስጥ መሠረት ሆነው የሚያገለግሉ – አመክንዮን ብቻ በመጠቀም ሊረጋገጡ የማይችሉ – አንዳች ‘leap of faith’ (የእምነት እመርታ (?)) የሚጠይቁ መነሻዎች መኖራቸው የግድ ነው ።

ከእነዚህ መነሻዎች በመነሣት ነው አንድን ነገር ጥሩ እና ተፈላጊ – ሌላውን የተጠላ እና መወገድ ያለበት ብለን የምንፈርጀው ። ጸሐፊዎቻችን ግን ፍትሕ ፣ ዲሞክራሲ ፣ እኩልነት ፣ ዕድገት እና የመሳሰሉት ቃላት በየትኛውም ርእዮት ቢሆን ተመሳሳይ ብያኔ ያላቸው እና መልካምነታቸው እና ተፈላጊነታቸው የማያጠያይቅ መልዕልተ ኵሉ እንደሆኑ የሚያስቡ ይመስላሉ ። ይህ መሠረታዊ ስሕተት ነው ። የእነዚህ ነገሮች ምንነት መብራራት የሚችለው መሠረታዊ መነሻዎችን መሠረት በማድረግ ነው ። ተፈላጊ ናቸውም ልንል የምንችለው የሚፈለጉት ነገሮች የትኛዎቹ እንደሆኑ በእነዚሁ መነሻዎች ላይ ተመሥርተን ከበየንን በኋላ ነው ። ይህን ችግር ሰርጌይ ቡልጋኮቭ “ሳይንሳዊነትን” እና ፖለቲካዊ ኢኮኖሚን ሲተቹ እንዲህ ያስተውሉታል ።

“What seems self evident in practice often poses the greatest problems for the philosophical mind. Such, for example, is the entire theory of knowledge that, essentially, investigates self evident forms of cognition and perceives in them the most difficult and complicated philosophical problems. The deceptive obviousness results in the common acceptance of such propositions as immutable and apoditic, so that to deny them seems absurd; or as is frequent in specialized sciences, they are taken as proven within the realm of that particular science, the outcome, in our time of scientific specialization is a peculiar but characteristic dogmatism of specialized sciences. We require the effort of philosophical analysis to free ourselves of this.”[10]

ጸሐፊዎቻችን ግን ወደ እንዲህ ዓይነቱ ጥልቅ ምርመራ መግባቱን አልወደዱም ። ፕሮፌሰር ባሕሩ እንዲያውም (ከላይ እንደተጠቀሰው) ‘ፍልስፍና ምን አገባው ?’ የሚል ዓይነት አስተያየት ነው ያላቸው ። ይህ አስተሳሰባቸው ሁለት ችግር ያለበት ነው ። አንደኛ በጉዳዩ ላይ ያለው ተዋሥኦ ከሁነቶቹ ወደ አለፈ ጥልቀት እንዳይደርስ በማገድ በፍሬቢስነቱ እንዲቀጥል የሚያደርግ ነው ። ሁለተኛ ደግሞ ታሪክ (ወይም እሳቸው ከጻፉት ታሪክ) ከጀርባው ምንም ዓይነት ፍልስፍና ወይም ርእዮት የሌለ “ገለልተኛ” ሜዳ ነው የሚል ስሑት መረዳትን የያዘ ነው ። ይህን ለማሳየት ወደ ታሪክ ፍልስፍና ወይም ወደ ነገረ ዕውቀት ባሕር መጥለቅ አያሻኝም ። የፕሮፌሰር ባሕሩ መጽሐፍ ራሱ ይመሰክርባቸዋል ። ከጻፉት ታሪክ ጀርባ የእሳቸውን እና የመሰሎቻቸውን የአስተሳሰብ መነሻዎች እና ማዕቀፎች ፣ ምኞቶቻቸውን እና የሞራል መርሖቻቸውን ብቻ ሳይሆን የግል ስሜቶቻቸውን ጭምር እናገኛለን ። መለስ ብሎ ከላይ የተጠቀሱትን ምንባቦች መቃኘት በቂ ነው ። ለምሳሌ ስለ ኢሕአፓ እና ስለ መኢሶን “ስሕተቶች” ሲናገሩ እና “ስለ ዐብዮቱ አለመሳካት” ሲጽፉ “የዐብዮትን” ፅንሰ ሐሳብ እየተቀበሉ እና “ዐብዮቱ” ካለመሳካቱ ይልቅ መሳካቱ የሚመረጥ እንደሆነ እየነገሩን አይደለም ? ከኢሕአፓ እና መኢሶን ይልቅ በየአካባቢው የተደራጁት “የብሔር ድርጅቶች” ድል በመጎናጸፋቸው ሲያዝኑ እያየን “ገለልተኛ” ታሪክ ጸሐፊ ብለን ብንጠራቸው ትክክል ይሆናል ? እነዚህ እና ሌሎችም ፍርዶቻቸው እና ምርጫዎቻቸው ከጀርባቸው ፍልስፍናዊ መነሻዎች አሏቸው ።  ወደፊትም እንዲሁ  ካፒታሊዝምን ሲተቹ እና ማርክሳዊነትን ከትችት ሲከላከሉ እናገኛቸዋለን ። እነዚህ ሁሉ የእሳቸው አቋሞች ናቸው ። ነገር ግን እነዚህን ሁሉ ሐሳቦቻቸውን “ገለልተኛ” (objective) እና የማይጠየቁ የታሪክ ሐቆች አድርገን እንድንቆጥራቸው ይፈልጋሉ ። የብዙ ጸሐፊዎችም ሐሳብ በእውነቱ ከዚህ ብዙ የተለየ አይደለም ። በዚህ ጽሑፍ መጠቆም እና መተቸት የምፈልገውም ይህን አካሔዳቸውን ነው ።

እዚህ ጋ ለነገራችንም ማዕከል ስለሆነ የማርክስን እና የኤንግልስን (ጓድ ኤንግልስን ችላ ብዬዋለሁ በእርግጥ እስካሁን) ፍልስፍናዊ መነሻዎች በማምጣት እና በጥቂቱ በማብራራት ፥ “በተግባራዊ” ጉዳዮች ላይ መፍትሔ ተደርገው የሚቀርቡት ሐሳቦች እንዴት ከእነዚህ መነሻዎች እንደሚፈልቁ እና በእነሱ እንደሚበየኑ ማሳየት እንዳለብኝ ይሰማኛል ። ነገር ግን ይህን ለቀጣዩ ክፍል እናቆየው ።

 

[1] እዚህ ጽሑፍ ላይ ስለ “ዐብዮቱ” ከቀረቡ ትረካዎች መካከል ሦስቱን (‘ያ ትውልድ’ ፣ ‘በአጭር የተቀጨው ረጅም ጉዞ’ እና ‘The Quest for Socialist Utopia’) መርጬ “ከዓብዮቱ” በኋላ “ዐብዮቱ” ላይ የሚደረገውን ተዋሥኦ እና በውስጡ ያሉትን ዐበይት ድምፆች እንዲወክሉልኝ አድርጌያለሁ ። ከጊዜ አንጻር ራሴን መገደብ ነበረብኝ እንጂ ሰፋ ባደርገው እወድ ነበር ። ለወካይነት አያንሱም ብዬ አምናለሁ ።

[2] አንዳርጋቸው አሰግድ (1992) ፣ በአጭር የተቀጨ ረጅም ጉዞ ። ሴንትራል ማተሚያ ቤት ፣ አዲስ አበባ ። መቅድም ፣ ገጽ 3

[3] ዝኒ ከማሁ ፣ ገጽ 15

[4] Bahru Zewde (2014), The Quest Socialist Utopia. Addis Ababa University Press, Addis Ababa. p. 8

[5] ክፍሉ ታደሰ (2013) ፣ ያ ትውልድ (ቅጽ 1) ። አምስተኛ እትም ። ገጽ 2

[6] Bahru (2014), p. 277-8

[7] አንዳርጋቸው (1992) ፣ ገጽ 431-2

[8] ዝኒ ከማሁ ፣ መቅድም ፣ ገጽ 5

[9] Bahru (2014), p. 9

[10] Bulgakov S. (2000), Philosophy of Economy: The World as Household. Translated and edited by Catherine Evtuhov, Yale University Press. p. 43


Share on Google Plus

ስለ የተለጠፈበት ቀን

    Blogger Comment
    Facebook Comment