✍ አሰፋ አበበ
1. መግቢያ
ፖለቲካና ሐይማኖት አፈጣጠራቸውም፥ ዓላማቸውም፥ አሠራራቸውም ወይም አፈጻጸማቸውም የተለያየ ነው:: ሆኖም አንዱ በአንዱ ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል:: ለምሳሌ በአንዳንድ አገሮች የፖለቲካው ወይም የመንግስት አሰራር ከሐይማኖታዊ አስተምሮት ጋር ተጣጥሞ እንዲካሄድ ይደረጋል:: ለምሳሌ ሳዑዲ አረቢያንና ኢራንን እንድሁም ሌሎች የሙስሊም አገሮችን መመልከት ይቻላል:: ሐይማኖተኛው የሻሪያ ሕግ ተፈጻሚ እንዲሆን የመንግስት መዋቅርን መጠቀም ይፈልጋል:: ፖለቲከኛው ደግሞ በሐይማኖት ተቋማት አሰራር ላይ ተጽዕኖ በማሳረፍና የሐይማኖት አባቶችን ድጋፍ በማግኘት ሕጉ፥ ደንቡና መመሪያው ተፈጻሚ እንዲሆለት ይፈልጋል:: እነዝህ ፍላጎቶች ፖለቲካውንና ሐይማኖቱን ቢያቀራርቡም አንድ ሊያደርጉ ግን አይችሉም:: ምክንያቱም ፖለቲካ የተፈጠረው ለምድራዊ (ከሞት በፊት) ላለው ሕይወት ሲሆን ሐይማኖት ደግሞ የተፈጠረው በዋነኛነት ለሰማያዊ (ከሞት ብኋላ ላለው) ሕይወት ነው:: በአሰራራቸውም ፖለቲካ እንደሁኔታው መተጣጠፍን (flexibility) የሚፈልግ ሲሆን ሐይማኖት ግን ቀኖናው(dogma) እንዲጠበቅ ይፈልጋል :: በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 11 መሠረት መንግሥት (ፖለቲካ) እና ሐይማኖት የተለያዩ ናቸው:: አንዱ በአንዱ ጣልቃ እንዳይገባም ተካልክሏል::
ፖለቲካና ሐይማኖትን የሚያመሳስላቸው ደግሞ የፖለቲካ ደጋፊው በሚደግፈው መሪው: የሐይማኖት ተከታዩ ደግሞ በሚያመልከው አምላኩ ላይ የሚጥለው እምነት ነው:: ለምሳሌ እ.አ.አ. በኣፕሪል 2018 ዶ/ር አቢይ አህመድ ወደ ሥልጣን ሲመጡ አገሩንና ሕዝቡን ወደ ተሻለ ደረጃ ይወስዳሉ በማለት የተለያዩ ቡድኖች የጣሉባቸው እምነትና ተስፋ ከፍተኛ ነበር:: ከመጽሐፍ ቅዱሱ ሙሴ ጋርም ያመሳሰሉአቸው ነበሩ::
በሐይማኖታዊው መንገድ ደግሞ የታመነው አምላክ ወደ ገነት እንደሚያስገባ የሚታመንና ተስፋ የሚደረግ ሲሆን የእምነት ውጤት ግን እንደፖለቲካው ቶሎ ላይታይ ይችላል:: ስለሆነም አብዘኞቻችን እስከ ዕለተ ሞታችን ድረስ በእምነታችንና ተስፋችን ጸንተን እንቆያለን:: የፖለቲካ እምነታችንን ውጤት ግን ቶሎ በአመትና ሁለት ዓመት እናያለን:: በመሆኑም ያመነው ሳይሆን ሲቀር፥ ተስፋ ያደረግነው ሳይፈጸም ሲቀር ከደጋፊነት ወደ ተቃዋሚነት ልንቀየር እንችላለን:: በመሆኑም በፖለቲካ ከደጋፊነት ወደ ተቃዋሚነት ወይም ከተቃዋሚነት ወደ ደጋፊነት መቀየር እንደ አሳፋሪ ድርጊት መታየት የለበትም:: ለምንወስደው የፖለቲካ አቋም መሰረት መሆን የሚገባው ያለው ተጨባጭ ሁኔታ: በሕይወት እያለን ማየት የምንፈልገው ውጤት እንጂ ይሉኝታ ወይም የማይጨበጥ ተስፋ መሆን የለበትም::
2. የፖለቲከኞች እንደ ሁኔታው መተጣጠፍ (Flexibility) የተለመደ ነው::
አቋምን ማስተካከል ወይም መለወጥ ወይም መተጣጠፍ በፖለቲካው የተለመደና አንዳንዴም እንደ የጥሩ መሪነት ችሎታ እንጂ እንደ ደካማነት ወይም አቋም የሌሽነት አይታይም:: አካሄዳቸውን ከሁኔታዎች ጋር እያስማሙ የሚሄዱና ዕቅዳቸውን ከሚፈጠሩ አዳዲስ ክስተቶች ጋር እያጣጣሙ የሚሄዱ መሪዎች በብዛት ስኬታማ መሪዎች ናቸው ይባላል:: የአዋቂዎችን ምክር ሰምቶ ወይም ያለውን ሁኔታ ገምግሞ በቀደመው አካሄድና ባሕሪ ልፈታ ያልተቻለውን ችግር በአዲስ አካሄድና ባሕሪ ለመፍታት መታጠፍ ጥንካሬ አንጂ ድክመት አይደለም:: “መካር የሌለው ንጉስ አለአንድ አመት አይነግስ” የሚለው የአማርኛ ብሂልም ይህንኑ ምክር ሰምቶ ተጨባጭ ሁኔታን አገናዝቦ አካሄድ የማስተካከልን አስፈላጊነት የሚገልጽ ነው:: የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ታምራት ላይኔ ሜይ 30, 2024 በኬኒያ ብሔራዊ የጸሎት ሥነ-ሥርዓት ላይ ተገኝተው “አሁን የኢትዮጵያ መሪ ቢሆን ኖሮ የሚሰራውን ሥራ ከድሮው በተለየ መንገድ እሰራ ነበር” ብለው የተናገሩት ንግግር እንደ ሁኔታው የአስተሳሰብና የአካሄድ ለውጥ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን የሚያሳይ ነው:: እውቁ ሳይንትስት አልበርት አነስታይን እንዳለው “ተመሳሳይ ድርጊትን ደጋግሞ በማድረግ የተለየ ውጤት መጠበቅ እብደት ነው”:: ስለዝህ ነገሮች እንደተፈለጉት አልሄድ ስሉ አስተሳሰብንም አካሄድንም ለውጦ መሞከሩ ተገቢ ይሆናል::
በኢትዮጵያ ፖለቲካ መተጣጠፍ የተለመደ ነው:: ደርግ ከሶሻሊዝም ወደ ቅይጥ ኢኮኖሚ ታጥፏል፥ ኢሐዴግም ከሶሻሊዝም ወደ ልማታዊ መንግሥት ከዝያም ወደ ካፒታሊዝም ታጥፏል:: መተጣጠፍ ባይኖር ኖሮ ፕሬዝዳንት መንግሥቱ ኃይለማሪያም አንድ ጥይትና አንድ ሰው አስኪቀር ወያኔንና ሻዕቢያን እዋጋለሁ ብሎ ስፎክር የነበረውን ትቶ መንግሥትና አገር ጥሎ ወደ ዝምባቢዌ አይፈረጥጥም ነበር፥ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ የኦሮሞ ቄሮን አመጽ በኃይል አቆማለሁ ብሎ መፎከሩን ትቶ በቃ ሥልጣን እለቅላችኋለሁ ብሎ ሥልጣን አይለቅም ነበር፥ ወያኔና ብልጽግና ፓርቲ ያን ሁሉ ፉከራ ትተው ፕሪቶሪያ ሄደው አይታረቁም፥ ናይሮቢ ሄደው አይተቃቀፉም፤ አዲስ አበባ ላይ አይሸላለሙም ነበር:: እስክንድር ነጋም የሰላማዊ ትግል አቋሙን ለውጦ መንግስትን በጠመንጃ ኃይል አስገድዶ ለመለወጥ ወደ ትጥቅ ትግል አይገባም ነበር::
አንዳንድ ሰዎች ‘ዶ/ር አቢይ ከዝህ ቀደም ወለጋ ከሄድኩ ይገሉኛል ብለው ነበር፤ ታዲያ በሚያዝያ ወር 2016 ለምን ወለጋ ሄዱ? ቀደም ሲል ሲያደርጉት የነበረውን የማስፈራሪያ ንግግርስ ቀይረው ለእርቅ የሚጋብዝና የለሰለሰ ንግግር ለምን አደረጉ’ ብለው ለመተቸት ይሞክራሉ::የአቢይ አህመድን ማዕከላዊ መልዕክት ለማግኘት ስዝት በቀጥታ በጎ ነገር ወይም የተለሳለሰ ነገር ስናገር ግን ግልብጦ በመስማት ተቀራኒውን ለማድረግ የተዘጋጀ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል ብለው ጥሪውን በአሉታዊ መልኩ ይመለከታሉ:: ይህም ካለመተማመን የመንጨ ነው:: እነዝህ ሰዎች የሁኔታዎች መለወጥና ጊዜ የውሳኔና የአካሄድ ለውጥን ሊያስከትል እንደሚችሉ ይረሳሉ:: ዶ/ሩ ነቀምቴ የሄዱት ቀደም ስል ልገለኝ ይችላል ብለው የጠረጠሩት ኃይል ልገላቸው እንደማይችል በማረጋገጣቸው ሊሆን ይችላል:: ይህም ወይ ያ ኃይል ተዳክሞ ስጋት በማይሆንበት ደረጃ ላይ ደርሷል ወይ ደግሞ የእርሳቸው ኃይል ተጠናክሮ ስጋቱ እንዳይኖር በሚያደርግበት ደረጃ ላይ ደርሷል ማለት ነው:: በመሆኑም ዶ/ር አቢይ አንደ ከአፋቸው ለወጣው ቃል ተገዥ ሁነው ይኑሩ የሚለው መከርራከሪያ ሊያስከድ አይችልም:: ግፋ ብል ከእርሳቸው የሚጠበቀው ቀደም ስል የያዙትን አቋም ወይም ቃል ለምን እንደለወጡ ማብራራት ይሆናል::
Blogger Comment
Facebook Comment