የፍልስጤምና የእየሩሳሌም ጦርነት፤ የ3ኛው ቤተመቅደስ መታነጽና ታቦተ ጽዮንን ፍለጋው በመጽሐፍ ቅዱስ፣ በቁርዓንና በታሪክ ንጻሬ!


✍ ሚካኤል ዘኢትዮጵ

በመካከለኛው ምሥራቅ በምትገኘው የእየሩሳሌም ከተማ ምክንያት ዘመናትን ያስቆጠረ ጦርነትና እልቂት አሁንም እንደቀጠለ ነው፡፡ የሀገር መሪዎች ማዶ ለማዶ ሆነው በፉከራና በማስፈራራት ከሚወራወሩት ቃላትና ከሚያምዘገዝጉት ሀገር አቁዋራጭ ሚሳይሎቻቸው አልፈው በጥይት ይጠዛጠዛሉ፣ በሳንጃ ይዘነጣጠላሉ፡፡ በክስተታዊነቱና በከባድነቱ እ.ኤ.አ. ከ1973 የዓረብ እስራኤል ጦርነት ጋር እየተነፃፀረ ያለው ቅዳሜ መስከረም 26 ቀን 2016 ዓ.ም. ሐማስ የከፈተው ድንገተኛ የሮኬት ጥቃት፣ በመካከለኛው ምሥራቅ አዲስ ዙር አደገኛ ጦርነት ቀስቅሷል፡፡ ይህ ጦርነት ደግሞ በዙሪያው ያሉ አገሮችን አልፎ በኢትዮጵያና በሌሎች አገሮች ላይ ተፅዕኖ እንዳያሳድር በመሠጋት ላይ ነው፡፡

እስከ ማክሰኞ መስከረም 29 ቀን 2016 ዓ.ም. ከቀትር በኋላ ድረስ አዲሱ ጦርነት ከእስራኤል ወገን ከ900 በላይ ሰዎች፣ እንዲሁም ከፍልስጤም ወገን ከ500 በላይ ሰዎችን ሰለባ ማድረጉ ታውቋል፡፡ ከእስራኤል ወገን 2,200 ሰዎች፣ እንዲሁም ከፍልስጤም 2,751 ሰዎች መቁሰላቸውም ተረጋግጧል፡፡ ግጭቱ ትኩስ ሆኖ እስከቀጠለ ድረስ ሰለባ የሚያደርጋቸው ሰዎች ቁጥርም በየሰዓቱ እየጨመረ እንደሚሄድ ነው የሚገመተው፡፡ ለዚህ ሁሉ ደም አፋሳሽ ጠብ ዋናው ምክንያት ደግሞ ይህች የኢየሩሳሌም ከተማ ለእኛ ትገባናለች፣ የእኛ ቅደስት ከተማ ናት በሚሉ የእምነት መሪዎች መኻከል የተነሣ ንትርክ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር በተለይ በብሉይ ኪዳን የሰለሞን ቤተመቅደስ የነበረው ቅዱስ ቦታ ለምን የጦርነት ማዕከል ሊሆን ቻለ? ይህ ቦታ ለአይሁዶች፣ ክርስቲያኖችና ሙስሊሞች ምን ዓይነት ቦታ ነው የሚለውን እናያለን። ለኛ ለኢትዮጵያዊያንስ ምናችን ነው የሚለውን እንዳስሳለን።

በብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ኢየሩሳሌም ከተጠቀሰችባቸው ስሞች መኻከል ሳሌም፣ ሞሪያ፣ እና ጽዮን የሚሉ ይገኙበታል፡፡ አይሁዶች የአብረሐም ዘር ያላቸው በመሆኑ በኢየሩሳሌም ከሚገኘው የሞሪያም ተራራ ጋር ከፍተኛ ትስስር አላቸው፡፡ ይህ ስፍራ በዘፍጥረት 14፣18 ላይ አብረሐም ከመልከ ጸዴቅ ጋር የተገናኘበት የንጉሥ ሸለቆ ተብሎ የተጠራው በሞሪያ (እየሩሳሌም) እንደሆነ ያምናሉ፡፡ በዘፍጥረት 22፣1-19 ደግሞ አብረሐም ይስሐቅን ለመሰዋት የወሰደበት ቦታ ስለሆነ ለአይሁዶች የተቀደሰ ስፍራቸው ነው፡፡ በሞሪያሜ ተራራ ላይ ያለው አብረሐም ልጁን ለመሰዋት ተዘጋጅቶበታል የሚባለው ዕለት ‹‹የመሰረት ድንጋይ›› (Even Shetiyah) ብለው የሚጠሩት ሲሆን የዓለም ሁሉ መንፈሳዊ ነገር የጀመረው እዚህ ስፍራ እንደሆነ በአጽኖት ይገልጻሉ፡፡ ይስሐቅ በዘፍጥረት 24፣63-67 ባለው ክፍል ርብቃን ከማግኘቱ ፊት የጸለየበት ስፍራና ያዕቆብ በዘፍጥረት 28፣ 10-22 ላይ የሰማይ መስኮቶች ተከፍተው መላእክት በመሰላላ ሲወጡና ሲወርዱ ሕልምን ያየበት ስፍራ ይህ የሞሪያም ምድር ወይም ቤቴል የተባለው ስፍራ እየሩሳሌም ውስጥ ያለ ቦታ ነው።

የእየሩሳሌም ምድርና የሞሪያም ተራራ ለአይሁድ ሕዝብ በሺህ ለሚቆጠሩ ዓመታት እንደ ብቸኛ የተቀደሰ ስፍራ አድርገው በመመልከት ቤተ መቅደሳቸውን ሠርተውበት ነበር፡፡ የአይሁድ ቤተ-መቅደስ ፈርሶ በምትኩ መስኪድ በተሠራበት በአሁን ዘመን እንኩዋን አይሁዶች በቀን ሦስት ጊዜ የሚጸልዩት ፊታቸውን ወደ ኢየሩሳሌም አድርገው ሲሆን፣ በኢየሩሳሌም ሆኖ የሚጸልይ ደግሞ ፊቱን ወደዚህ ቤተመቅደስ አዙሮ ይጸልያል፡፡ በአይሁዶች ጸሎት ውስጥ ‹‹ኢየሩሳሌም›› የሚለው ቃል በርካታ ጊዜ የተጠቀሰ ሲሆን አይሁዶች የፋሲካ በዓላቸውን ሲያጠናቅቁ የሚሰነባበቱት ‹‹በሚቀጥለው ዓመት በእየሩሳሌም እንገናኝ›› በሚል የመልካም ምኞት መግለጫ ነው ፡፡

እስራኤሎች ከግብጽ ባርነት ተላቀው ወደ ከነአን ከገቡ 400 ዓመታት በኋላም ቅዱስ ዳዊት ቤተመቅደስ ለማሠራት የሚያስፈልገውን ዕቃ ሁሉ አከማችቶ ልጁ ንጉሥ ሰለሞን የመጀመሪያውን ቤተመቅደስ በእየሩሳሌም አሠርቶበታል፡፡ ይህ ቤተመቅደስ 410 ዓመት አገልግሎት ከሰጠ በኋላ ባቢሎናዊያን ስላፈረሱት አብዛኛዎቹ አይሁዶች ከእየሩሳሌም ለቀው ወደ ባዕድ ሀገር እንዲሰደዱ ተደርገዋል፡፡ አይሁዶች በግዞት ምድር ለሃምሳ ዓመት ቆይተው ባቢሎኖች በፐርሽያ ሲሸነፉ አይሁዶች ደግሞ በዘሩባቤል አማካኝነት ወደ ሀገራቸው ተመልሰው ለሁተኛ ጊዜ በቀደመው ፍርስራሽ ላይ ሁለተኛውን ቤተመቅደስ ሠሩ (ነሕምያ 4-6)፡፡ ሁለተኛው ቤተመቅደስ ከክርስቶስ ልደት በኋላ በ70 ዓ.ም በሮማውያን ፈረሰ።

ሮማዊያን እስራኤልን በቅኝ ግዛት ይዘው በሚያስተዳድሩበት ዘመን ነበር ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደው። ሄሮድስም በኢየሱስ ክርስቶስ መወለድ ይበሳጭ ነበርና የግድያ አዋጅ አወጀ። በርግጥ ኢየሱስ የሰው ልጆችን ኹሉ ከኃጢያት ሊያድን ነበርና ሰው የሆነው ሄሮድስ ኢየሱስን ለመግደል  ሥልጣን እንደሌለውና ነገር ግን በአባቱ ፈቃድና በራሱ ፈቃድ ሞቱ በኢየሩሳሌም እንደሚሆን ይናገራል:: ሆኖም ግን የጌታን ልብ የሰበረው በተንኮሉና በክፋቱ በነፍሰ ገዳይነቱ ቀበሮ የተባለው የሄሮድስ ጌታን ለመግደል መሞከሩ ሳይሆን የኢየሩሳሌም መሲሁንና አዳኟን አለመቀበልዋ ነበር:: ዶሮ ጫጩቶቹዋን ከጭልፊት እንደምትሰውር በክንፎችዋ ከብርድ ሰውራ ሙቀት እንደምትሰጥ ጌታም ኢየሩሳሌምን ከሚመጣባት ፍርድ ለመሰወር ምን ያህል እንደፈለገና ነገር ግን ኢየሩሳሌም የጌታን ፍቅር ለመቀበል እምቢተኛ እንደሆነች ይነግረናል:: ኢየሩሳሌም የአምላኩዋን ፍቅር እምቢ ብላ መግፋትዋ በስተኋላ በ70 ዓም ፍራሽ በፍራሽ እንድትሆን ልጆቹዋም በመላው ዓለም እንዲበተኑ አድርጎአል:: የጌታንም ልብ የሰበረው ይህ ሊመጣ ያለው የእግዚአብሔርን ፍርድ ለማየት አለመቻላቸው ነበር:: እስራኤልን ከሮም ቅኝ አገዛዝ ነጻ ለማውጣት ከ66-70 ዓ.ም ባደረጉት እንቅስቃሴ ጥጦስ የተባለው የሮም ንጉሠ ነገሥት ዘምቶ ኢየሩሳሌምን በ70 ዓ.ም ደመሰሳት፡፡ ትልቁን የአይሁድ ቤተመቅደስንም አቃጠለው፡፡ እስራኤላውያንም በመላው ዓለም ተበተኑ፡፡

ከፈረሰ በኋላም የቤተመቅደሱ ስፍራ ለ600 ዓመታት ምንም ሳይሠራበት ፍርስራሽ ሆኖ ቆይቶአል፡፡ ምንም እንኩዋን አይሁዶች በዓለም ዙሪያ ተበትነው ዐቅም ስላጡ የቤተመቅደሱ ስፍራ ለረጅም ዓመታት ባዶ ቢሆንም እስራኤሎች ስፍራው የተቀደሰ እንደሆነ ያምናሉ፡፡ እስከዛሬም ድረስ እምነታቸውን በማጽናት አይሁዶች የሚጠብቁት መሲሐቸው ሲመጣ ሦስተኛውና የመጨረሻው ቤተመቅደስ በዚሁ ስፍራ እንደሚሠራ በተስፋ ይጠብቃሉ፡፡ መሲሁን ቀድመው የገደሉትና 2000 ዓመታት ያለፉ ቢሆንም እነሱ ገና እንደሚወለድ በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ።

በዚህ የአይሁዶች ቤተመቅደስ ፍርስራሽ ላይ መስጊድ የገነቡት መቅደሱ ከፈረሰ ከ700 ዓመታት በኋላ ሙስሊሞች ናቸው። የእስልምናን እምነትን በ622 ዓ.ም የመሠረተው የሙስሊሞች ነቢይ መሐመድ በመካ የተወለደ ሲሆን፣ የትውልድ ስፍራው የሆነችው ቦታ ለእስላሞች የተቀደሰች ከተማ ሆናለች፡፡ ከመካ በተጨማሪም መዲና ሁለተኛዋ የተቀደሰች ስፍራቸው ናት፡፡ እስላሞች ከእየሩሳሌም ጋር ያላቸው ትስስር የጀመረው ከክርስቶስ ልደት ከ700 ዓመት በኋላ ነው፡፡ መሐመድ አንድም ጊዜ እየሩሳሌም ሔዶ የማያውቅ ሲሆን እየሩሳሌም የሚል ስም በቁርአን ውስጥ አንድም ቦታ አልተጠቀሰም፡፡ ምንም እንኩዋን መሐመድ እየሩሳሌምን ሳይረግጥ ቢሞትም የእስልምና እምነት ተከታዮች መሐመድ ‹‹የለሊት ጉዞ›› በሚሉት ተአምራዊ ሁኔታ እየሩሳሌምን እንደጎበኛት ይናገራሉ፡፡ መሐመድ ከሞተ በኋላ የእርሱ ተከታይ በሆነው በካሊፋ የሚመራ ጦር እየሩሳሌምን በ638 ዓ.ም በመያዝ ከመካና መዲና ቀጥላ ሦስተኛ የተቀደሰች ስፍራቸው አድርጓታል፡፡

140,000 ካሬ (አንድ መቶ ዐርባ ሺህ ካሬ ሜትር) ስፋት እንዳለው የሚነገርለት ይህ አወዛጋቢ ቦታ በእስላሞች ይዞታ ሥር ያለ ሲሆን በስተቀኝ በደቡብ በኩል “ኤል አቅሳ” (El Aqsa Mosque) የሚባለው መስጊድ፣ እንዲሁም በጥንቱ የሰሎሞን ቤተ መቅደስ መሠረት ላይ እንደታነጸ የሚነገርለት “የዑመር ከሊፋ መስጊድ” ወይም የድንጋይ ጉልላት (Dom of the Rock) በላዩ ላይ ታንጸው ከኢየሩሳሌም በአንጻር ባለው በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ቆሞ የድሮዋን ኢየሩሳሌም ለሚቃኝ ሁሉ ከሁሉም ነገር ጎልተው ይታያሉ።

ይህንን እምነታቸውን የሚገልጽ አሁን ያለውን ‹‹አል-አቅሳ›› የተባለውን መስኪድ እና የከሊፋ ዑመር መስጊድ የሠሩት መሐመድ ወደ ሰማይ በመላኩ በጅብሪል ታጅቦ ያረገበት ስፍራ እንደሆነ በማመልከት ነው። ከ638 እስከ 1917 ባሉት ረጅም ዓመታት አይሁዶች በምድር ሁሉ ስለተሰደዱ እየሩሳሌም እንደ ሦሪያ፣ ግብጽ፣ ቱርክ በመሳሰሉ የእስልምና እምነት ተከታዮች ቁጥጥር ስር ነበረች፡፡ ነገር ግን አንዳቸውም የእስልምና ተከታይ መንግሥታት እየሩሳሌምን ዋና ከተማቸው አላደረጓትም ነበር፡፡ ላለፉት 3000 ዓመታት ከአይሁዶች ቀጥሎ እየሩሳሌምን ለጥቂት ጊዜ ዋና ከተማቸው ያደረጓት ከ1099 እስከ 1187 ዓ.ም የላቲን መንግሥት ተቀናቃኝ ሽምቅ ተዋጊዎች ብቻ ናቸው፡፡

እ.ኤ.አ. 1947 የመካከለኛው ምሥራቅ ይገባኛል ጭቅጭቅን ለመዳኘት የዓለም አገሮች ድምፅ እንዲሰጡበት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ውሳኔ ቁጥር 181 ወይም ‹‹ፓርትሽን ፕላን›› የተባለውን የውሳኔ ሐሳብ ለጠቅላላ ጉባዔ አቀረበ፡፡ ይህ የውሳኔ ሐሳብ በ33 በአገሮች ድጋፍ፣ በ13 አገሮች ተቃውሞና በአሥር አገሮች ድምፀ ተዓቅቦ መፅደቁ ይነገራል፡፡ ይህ የውሳኔ ሐሳብ እስራኤል የተባለች አገር በመካከለኛው ምሥራቅ እንድትወለድ መሠረት መጣሉ ይነገራል፡፡ በጊዜው ኢትዮጵያ ድምፀ ተዓቅቦ ካደረጉ ጥቂት አገሮች አንዷ ነበረች፡፡ ቻይናና ሶቭየት ኅብረትን ጨምሮ ከእነ አሜሪካ ጎን ሆነው በመካከለኛው ምሥራቅ የሁለት አገሮች መመሥረት ዕቅድን ድጋፍ ሲሰጡ፣ ኢትዮጵያ ግን ድምፀ ተዓቅቦ በማድረግ ነበር ሚዛናዊ አቋም ለመያዝ ጥረት ያደገችው ተብሎ በታሪክ ይወሳል፡፡

ይህን የውሳኔ ሐሳብ ተከትሎ እስራኤል የዛሬ 75 ዓመታት እ.ኤ.አ. 1948 ተመሠረተች፡፡ ወዲያው ግን የዓረብ አገሮች ተባብረው ጦርነት ከፈቱባት፡፡ ጦርነቱ ከሁለቱም ወገን 15 ሺሕ ሰዎች ተገደሉ፡፡ ከ750 ሺሕ በላይ ፍልስጤማዊያንን አፈናቀለ፡፡ ከዚህ በላይ ደግሞ ጦርነቱ አካባቢውን እስራኤል፣ ዌስት ባንክና ጋዛ በማለት ለሦስት ቦታ እንደከፋፈለው ይነገራል፡፡ ዛሬ ድረስ የቀጠለውና በየጊዜው የሚያገረሸው የእስራኤልና የፍልስጤም ግጭት በዚህ መንገድ ነው እያደገ የመጣው፡፡

ጋብ ብሎ የማያውቀው የመካከለኛው ምሥራቅ ውጥረት በየጊዜው ወደ ግጭት ባደገ ቁጥር ደግሞ፣ ዓለም አቀፋዊ ቀውስ ይዞ መምጣቱ የተለመደ ይመስላል፡፡ እ.ኤ.አ. የ1956 የስዊዝ ቦይ ቀውስ የዚህ ውጤት ነው፡፡ በ1967 የስድስቱ ቀናት ጦርነት፣ እንዲሁም በ1973 የዮም ኪፖር ወይም የኦክቶበር ጦርነት ወቅት ዓለም ተያያዥ ቀውሶችን አስተናግዳለች፡፡

እስራኤል እንደገና እንደ ሉዓላዊ ሀገር በ1948 ዓ.ም ስትመሠረት በ1967 በተደረገው “የስድስቱ ቀን ጦርነት” አይሁዶች ከ1300 ዓመት በላይ በእስልምና እምነት ተከታዩች ተይዞ የነበረውን የእምነታቸው መሠረት የሆነውን አሮጌ ከተማ (Old City) በመባል የሚታወቀውን የቤተመቅደሱን አካባቢ በቁጥጥር ስር አደረጉ፡፡ አይሁዶች አካባቢውን ከተቆጣጠሩ በኋላ እስላሞችን ከማስወጣትና መስኪዳቸውን ከማጥፋት ይልቅ የ‹‹ዲፋክቶ›› ስምምነት ተፈራርመው ሰላማዊ ግንኙነት ጀመሩ፡፡ ስለዚህ ምንም እንኳን አይሁዶች ሉዓላዊ ሀገር በመሆን እስራኤልንና አካባቢውን ቢቆጣጠሩም ይህንን የእምነት እምብርት የሆነውንና አሁን መስኪድ ያለበትን ስፍራ የሚቆጣጠሩት እስላሞች ናቸው፡፡

በርግጥ የሙስሊሞች ነቢይ መሐመድ በቁርዓንና ሐዲሳቱ አይሁዶችን እንደሚጠላና እነሱን ማጥፋትም የመጨረሻ ግቡ እንደሆነ ይናገራል። መሐመድ ሙስሊሞች ክርስቲያኖችንና አይሁዶችን ማዋረድ እንደሚገባቸው አስተምሯቸዋል፡፡ በመንገድ ላይ እንኳ ሲመጡባቸው ሰላም እንዳይሏቸውና እንዲገፈትሯቸው ነግሯቸዋል፡- “ነቢዩ እንዲህ ብለዋል ‹አይሁዶችን ወይንም ክርስቲያኖችን ሰላም አትበሉ፡፡ በመንገድ ላይ ቢመጡባችሁ ወደ ጠባቡ የመንገድ ጠርዝ ግፏቸው፡፡›” (Sahih Muslim, 2167; Sahih Ai-Bukhari Book 25, Number 5389)። እንዲሁም በቁርዓን ውስጥ የእርግማንን ቃላት በክርስቲያኖችና በአይሁዶች ላይ ሲናገር እንመለከታለን፡- “አይሁድ ዑዘይር የአላህ ልጅ ነው አለች፡፡ ክርስቲያኖችም አልመሲሕ የአላህ ልጅ ነው አሉ፡፡ ይህ በአፎቻቸው (የሚናገሩት) ቃላቸው ነው፡፡ የእነዚያን ከነሱ በፊት የካዱትን ሰዎች ቃል ያመሳስላሉ፡፡ አላህ ያጥፋቸው፡፡ (ከእውነት) እንዴት ይመለሳሉ!” (ሱራ 9፡30)። መሐመድ በሞቱ አልጋ ላይ ተኝቶ እያጣጣረ ሳለ የመጨረሻው ንግግሩ አይሁዶችንና ክርስቲያኖችን መርገም እንደነበር እስላማዊ ትውፊቶች ይናገራሉ። ከዚህም በተጨማሪ ሙስሊሞች አይሁድና ክርስቲያኖች የሚያደርጉትን ነገር በተቃራኒው ማድረግ ግዴታቸው ነው፡፡ ሐዲሱ እንደሚናገረው መሐመድና ተከታዮቻቸው በወቅቱ ፀጉራቸውን እንኳን ቀለም ይቀቡ የነበረው አይሁድና ክርስቲያኖች ፀጉራቸውን ቀለም ስለማይቀቡ ከእነርሱ በተቃራኒ ለመቆም ሲሉ ነው፡፡ “The Prophet said, ‘Jews and Christians do not dye their hair so you should do the opposite of what they do.’” Sahih Bukhari 7:72:786.።

ከዚህ አንጻር ሙስሊሞች አይሁዶችንና ክርስቲያኖችን ከምድረገጽ ለማጥፋት እንደሚጥሩ ሁሉም ሊያውቀው ይገባል። እስራኤል ለብዙ ዓመታት ከካርታ ላይ ተሠርዛ ብትቆይም አሁን ራሷን የቻለች ሀገር ናትና ታሪካዊና የእምነት ቦታዋ የሆነውን የሰለሞን ቤተመቅደስን ይገባኛል ብትል አይፈረድባትም።

ነገር ግን ለእኛ ክርስቲያኖች ቦታው ለየትኛውም አካል ቢሆን አይጠቅመንም። ይልቁንም ይህ ግጭት የሚነግረን ሌላ ምልክት አለ። እስራኤላዊያን መሲሐቸው የሚወለድበትን መቅደስ በማዘጋጀት ላይ ናቸው። ያ ቦታ ደግሞ ይህ ለጦርነት የሚዳርጋቸው ቦታ እንደሆነ ያምናሉ። በዚህ ቦታ ላይም ሦስተኛውን ቤተመቅደስ ለመገንባት ያስባሉ።

በአይሁድ ዘንድ የሦስተኛው ቤተ መቅደስ መታነጽ ሃይማኖታዊ ጉዳይ ስለሆነ ጥያቄ ውስጥ የሚገባ አይደለም። አይቀሬ ነው። የሦስተኛው ቤተ መቅደስ መታነጽ ከዛሬ 2500 ዓመት በፊት ከአይሁድ ሕዝብ የተቋረጠው የመለኮት መገለጥ ዳግም የሚመለስበት ነው ተብሎ ይታመናል።

የእስራኤል የቀደመ ክብርና ሞገስ የሚመለሰው በመሲሑ ዘመን ሦስተኛው ቤተ መቅደስ በታነጸ ጊዜ መሆኑንና በዚህ ጊዜ ጉባኤያቸው ጸሎታቸው መስዋዕታቸው ሁሉ ቅድመ እግዚአብሔር የሚደርስበት መለኮታዊው ኃይል በመካከላቸው የሚገኝበት እንደሆነ ያምናሉ።

ለሦስተኛው ቤተ መቅደስ መሠራት ጥርጊያ መንገድን ለማዘጋጀት በማሰብ “Shechinah Third Temple, Inc” የተባለ በትርፍ ላይ ያልተመሠረተ ድርጅት ለዓለም ሁሉ ለማስገንዘብ ተልዕኮን አንግቦ እንደተነሣ በመግለጽ ለዚህ በጎ ዓላማ መሳካት ፍላጉት ያላቸው ሁሉ እጃቸውን በመዘርጋት የገንዘብ ድጋፍ እንዲያደርጉለት በኢንተርኔት ባሰራጨው ጽሑፍ ገልጾአል።

ከላይ እንደተገለጸው በይሁዲ እምነት ተከታዮች ዘንድ የሦስተኛው ቤተ መቅደስ መሠራት ጉዳይ ለድርድር የማይቀርብ ሃይማኖታዊ ግዴታ ነው። በአይሁድ ዘንድ ሦስተኛው ቤተ መቅደስ የቀደሙት ሁለቱ አብያተ መቅደሳት በታነጹበት ካልሆነ በሌላ በየትም ቦታ መታነጽ እንደሌለበት ይታመናል። እንደ እምነታቸው እንዳይሆን ደግሞ በታሪክ አጋጣሚ በቦታው ላይ እስላሞች ሁለት ታላላቅ መስጊዶችን ገንብተውበታል። ቦታውንም በይዞታነት ይዘውት ያሉት እስላሞች ናቸው። ይህ አጣብቂኝ ሁኔታ ነው የሦስተኛው ቤተ መቅደስ መታነጽ ጉዳይን የዓለም መነጋገሪያ ያደረገው።

አጥባቂ አይሁዶች በቦታው ላይ ያሉትን መስጊዶች በማፍረስና ሦስተኛው ቤተ መቅደስን በቦታው ቆሞ ለማየት ካላቸው ጉጉት የተነሣ በቦታው ላይ ተደጋጋሚ የጥፋት ሙከራ ለማድረግ አሲረው ሳይሳካላቸው በቁጥጥር ስር ውለዋል። በሌላ በኩል የሦስተኛው ቤተ መቅደስን መሠራት ጉዳይ ያዘገየው እስራኤል በግዛትነት በያዘችው በኢየሩሳሌም ባለው በሞሪያም ተራራ የተሠሩት የመስጊዶቹ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ከመነሻው የመጀመሪያውን ቤተ መቅደስ ንጉሥ ዳዊት ሊሠራ ሲያስብ የእግዚአብሔር የቃል ኪዳኑ ታቦት ከአንዱ ቤት ወደ ሌላው ቤት መንከራተትዋ አሳዝኖት ለቃል ኪዳንዋ ታቦት ማደሪያ (ማረፊያ)ይሆን ዘንድ በመሆኑ ቤተ መቅደስ ከመሥራት ለጊዜው ቸል እንዲሉ ያደረጋቸው የቃል ኪዳንዋ ታቦት ደብዛዋ መጥፋትና ያለችበትን ቦታ አለማወቅ ነው።

ለሦስተኛው ቤተ መቅደስ መታነጽ የታቦተ ጽዮን መገኘት ወሳኝ ጉዳይ ከሆነ የቤተ መቅደሱ ግንባታ በአወንታዊም ሆነ በአሉታዊ መንገድ የሚነካቸው ወገኖች ሁሉ የቃል ኪዳንዋ ታቦት ጉዳይ ትኩረታቸው እንደሚሆን ማንም ተራ ሰው የሚገምተው ነገር ነው። የቃል ኪዳኗ ታቦት ደግሞ በኢትዮጵያ እንደምትገኝ ይታመናል። አይሁዶች ከሕወሓታዊያን ጋር ሆነው ለመስረቅ እንደሞከሩም ይነገራል። ዳሩ አያገኟትም። ሊወስዷትም አይችሉም። አንደኛውና ኢትዮጵያን ለመበታተን የሚሠራበት ምሥጢራዊ ምክንያትም ይኸው ነው።

አሁን ግን ኢትዮጵያዊያን ሁላችሁም አንዱን ከመደገፍና ሌላውን ከመቃወም ልትወጡ ይገባል ባይ ነኝ። በ1948 ዓ/ም እስራኤል እንደገና ሀገር የመሆን ተግባር ላይ ንጉሡ ኃይለሥላሴ ሀገራቸውን ገለልተኛ አድርገው እንደቆሙ እኛም እንዲሁ ብንቆም ባይ ነኝ። ይህንን ሁሉ ችግርና ግጭት ስንመለከት በሰው አእምሮና በፖለቲካ አመራር የሚፈታ ችግር አይደለም፡፡ በተለይ በሴራ በተተበተበው በምዕራባዊያንና መካከለኛው ምሥራቅ ፖለቲካዊ አመራር! ዳሩ መዳረሻው የመጨረሻው ዘመን ፍጻሜ ምልክትና የኢትዮጵያ ትንሣኤ ምልክት ነው። ሲቋጭም የዓለም መጥፋትና ዳግም ምፅዓት አንዱ ምልክት ነው!

01/02/16 ዓ/ም
አዲስ አበባ፤ ኢትዮጵያ

Share on Google Plus

ስለ የተለጠፈበት ቀን

    Blogger Comment
    Facebook Comment