የኢትዮጵያ አስደናቂና የማይቀር ትንሣኤዋ



 በመጋቤ ሐዲስ ዶሮዳስ ታደሰ







ገነትን ከሚያጠጡ ወንዞች የግዮን ወንዝ የከበባት አስቀድማ በሕገ ልቡና በመልከ ጼዴቅ አባቷ በኩል ለልዑል እግዚአብሔር በስንዴና በወይን ቁርባንን ያቀረበች፤ በኋላም በእግዚአብሔር ጣት የተጻፉ 10 ቃላት ያሉባትን የኪዳን ምልክት ታቦተ ጽዮንን ከ3000 ዓመት በፊት የተቀበለች ታላቅ ሀገር ናት።

 ፈጣሪያችን ክርስቶስም በቤተልሔም ሲወለድ በሰብዐ ሰገል በኩል ስጦታን ለአምላኳ በማቅረብ እጆቿን ወደ ንጉሧ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘርግታ ያደረሰች ሀገር ኢትዮጵያ ናት፤ ሕይወቷ ኢየሱስ ክርስቶስም በስደቱ ጊዜ ዕንባቆም እንደጻፈው ከእናቱ ከእመቤታችን ጋር ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ዘላለማዊ ዐሥራት አድርጎ ሃገሪቱን ለእመቤታችን ሰጥቷልና ንግሥታችን የአምላክ እናት በርስት ሀገሯ በኢትዮጵያ ዘወትር ትከብራለች።
 የአትዮጵያ መምህር ማንም ሳይሆን መንፈስ ቅዱስ ነውና በ34 ዓመተ ምሕረት ኢትዮጵያዊው ጀንደረባን እንዲያስተምረው ፊልጶስን ፈጣሪያችን መንፈስ ቅዱስ አዞት ተጠምቆ ከዓለም አስቀድመን ከሥላሴ የምንወለድበት ረቂቅ ልደትን ጀንደረባችን ለኢትዮጵያውያን አምጥቶ ምድሪቱ በወንጌል አበራች።
 በተጨማሪም ምድሪቱ በወልደ እግዚአብሔር መስቀል ትጠበቅ ዘንድ በመድኃኔ ዓለም ፈቃድ ክቡር ደሙን ያፈሰሰበት የምስጢር መዝገብ በሆነችው በመስቀለኛዋ ተራራ በግሸን ደብረ ከርቤ እንዲቀመጥ ሆነ።
 ሊቁ አለቃ አያሌው ታምሩ ኢትዮጵያን ማንም ሊቀዳት የማይችል የክርስቶስ ሥረ ወጥ ቀሚሱ እንዳሏት እስከ ፍጻሜ ዘመን የምትኖር ዓለምን በቅድስናዊ ሕይወቷ የምትመራ የብርሃን ተስፋ ያላት ናትና ከከበባት ጨለማ ይልቅ እጅግ ደማቅ ብርሃኗ የሚታየን ነውና የኢትዮጵያ የማይቀር ትንሣኤዋ ተገልጾላቸው ከጻፉ አባቶችና ከመጻሕፍት ቃል ገልጾ ተርጉሞ የማስረዳት ጊዜው ሆኗል።
የኢትዮጵያን ትንሣኤ መንፈስ ቅዱስ ገልጾላቸው ቅዱሳን አበው ከጻፏቸው መጻሕፍት ውስጥ:-

ፍካሬ ኢየሱስ 

ራእዩ ለአቡነ ሲኖዳ 

ገድለ ፊቅጦር 
ራእየ ሳቤላ
መጽሐፈ ምስጢር
ትርጓሜ ወንጌል ይገኛሉ፨

 የኢትዮጵያ ክብር የሚገጥበት፣ ገናንነቷ የሚመለስበት፣ የተሻረው የቅብዐ መንግሥቷ የሚመለስበት፣ በቅብዐ መንግሥት የከበረ በሥላሴ ኃይል የበረታ ንጉሥ የሚመራበት፣ በዮጵ ወርቋ የምታጌጥበት፣ የእምነቷ ታላቅነት በዓለም አደባባይ የሚገለጥበት ጊዜ እንደሚመጣ አቡነ ሲኖዳ በራእዩ የጻፈውን ለአንባብያን ከግእዙ ተርጉሜ አቅርቤዋለሁ ሌሎቹነንም በተከታታይ እየተረጎምኩ አቀርብላችኋለሁ መልካም ንባብ፦
 አቡነ ሲኖዳ ባየውና በጻፈው ራእይ ላይ ስለዚኽ ነገር በስፋት እንዲኽ ይገልጠዋል፡- 
╬ “ወእምድኅረዝ በእሙንቱ መዋዕል ይትነሥኡ ክልኤቱ ነገሥት አሐዱ ንጉሠ ሮም ዘስሙ “እ” ወአሐዱ ንጉሠ ኢትዮጵያ ዘስሙ “ትዮዳ”... ” (ከዚኽ በኋላ በዚያ ዘመን ኹለት ነገሥታት ይነሣሉ፤ አንዱ ስሙ “እ” ተብሎ የሚጠራ የሮም ንጉሥ ነው፤ አንደኛውም “ትዮዳ” የሚባል የኢትዮጵያ ንጉሥ ነው።

 ከሊቃ ጳጳሶቻቸው፤ ከሰራዊቶቻቸው፤ ከሕዝብ ኹሉ ጋርም በኢየሩሳሌም ይሰበሰባሉ፤ ሃይማኖትን እያቀኑ በዚያ ለሰባት ወር ይቀመጣሉ፤ ያን ጊዜ በየቋንቋው የእኛ ሃይማኖት ይሻላል እያሉ ክርክር ሙግት ይኾናል፤ ከዚኽ በኋላ የእስክንድርያው ሊቀ ጳጳሳት ተነሥቶ በጉባኤው ኹሉ ፊት “እግዚአብሔር በጥንተ ተፈጥሮ የፈጠራችኊ ተቀዳሚ ተከታይ የሌለው ብቸኛ ልጁን በማመን የጠራችኊ ወገኖች ስሙኝ፤ በዛሬው ዕለት ግሩምና ቅዱስ ራእይን ተመለከትኊ።
 ነገር ግን ያየኹትን ራእይ አልናገርም፤ የሚያምነኝ የለምና፤ ነገር ግን ወደ ጎልጎታ ሰዎችን ላኩ፤ ከጌታችን መቃብር መሬትን (ዐፈርን) አምጡ፤ በቤተ ክርስቲያን ውስጥም እነሰንሳለኊ፤ የእኛ የሚኾን ቅዳሴን በአንድ ወገን እንቀድስ፤ የሮሜ ሊቀ ጳጳሳት በሌላኛው ወገን ቅዳሴን ያድርግ፤ ሰዎች ኹሉ እየተመለከቱት ከእኛ በአንዱ ላይ ከሰማይ ተአምር የኾነ ከኾነ ከዚኽ በኋላ በዚያ ሃይማኖት በአንድ ላይ እንተባበር፤ ሕዝቡም ኹሉ በዚያ ሃይማኖት አንድ እንኾናለን ይበሉ” ይላል።
ኹሉም ሕዝብ የዚኽን ፍጻሜ የሚያይ ንዑድ ክቡር ነውና በአንድ ቃል ተስማምተናል ይላሉ፤ አይሁድም ኢአማንያን አረማውያንም ከእሊኽ በአንዱ መሠዊያ ላይ ተአምር ከሰማይ ሲወርድ ካየን ዛሬውን ክርስቲያን እንኾናለን ይላሉ፤ ከዚኽ በኋላ ለሦስት ጊዜያት ኪርኤኤሌይሶን እያሉ ቅዳሴን ያደርጋሉ ከዚኽ በኋላ መንፈስ ቅዱስ ፊቱ የሰው መልክ በኾነ በነጭ ርግብ አምሳል ይወርዳል።
 አንገቱ እንደ ንስር ረዥም ነው፤ የዠርባው ጠጒር መልኩ እንደ ኢያሰጲድና ሰርዴዎን ዕንቊ ነው፤ ክንፎቹም የሰባት ዓመት ልክ እንደ ኾነ ቀስተ ደመና ብልጭታን ያንጸባርቃል፤ እግሮቹም እንደ ሊባኖስ ብርት ነው፤ ራሱና ዐይኖቹ እንደ ፀሓይ የሚያንጸባርቁ ናቸው፤ ኾዱ በሰንፔር ዕንቊ እንዳጌጠ እንደ በረዶ ነጭ የኾነ እንደ ዝኆን ጥርስ ነው (መሓ ፭፥፲፬)።
 ከአፉም ዐሥራ ኹለት ጫፎች ያሉት የእሳን ልሳን ይወጣል፤ በራሱም ላይ የብርሃን ማኅተም የቆመ ነው፤ በብርሃን ማኅተም ውስጥ በግልጥ በሰባት ዐይኖችና አቅርንት ባለው ነጭ በግ በሰው አንደበት እየተናገረ በግልጥ ይታያል፤ “የያዕቆባውያን አምላካቸው የናዝሬቱ ኢየሱስ እኔ ነኝ” ይላል።
 ይኽነንም ብሎ የእስክንድርያው ሊቀ ጳጳሳት በሠዋው መሥዋዕተ ወንጌል ላይ ይቀመጣል፤ ሰው ኹሉ እያየው በክንፉ ዓለምን እየጋረደ ወደ ሰማያት ውስጥ ያርጋል፤ ከዚኽ በኋላ የኢትዮጵያ ንጉሥ ከሰራዊቱ ጋር በእልልታ ቃል ከሰራዊቱ ጋር ይመለሳል፤ የኢትዮጵያውን ንጉሥ ሃይማኖት እግዚአብሔር ወድዶለት አይቷልና፤ ሮማውያንና መለካውያን የስሕተት መጻሕፍቶቻቸውን አቃጥለው ወደ ባሕር ውስጥ ይወረውራሉ፤ ሮማውያን፣ ኢጥሙቃን፣ አይሁድ በመላ በአንድነት በሥላሴ ስም ይጠመቃሉ።
 ዐዋጅ ነጋሪም አስቀድሞ ሐዋርያት በዓለም ዳርቾች ኹሉ አስተማሩ፤ ዛሬ ግን እንዳያችኹትና ቃሉን እንደሰማችኹት ርሱ ራሱ ሐዋርያ ኾነ፤ ኺዱ አይሁድ ለአይሁድ፤ ኢጥሙቃን ለኢጥሙቃን፤ አረሚ ለአረሚ በዓለሙ ኹሉ ቃሉን አስተምሩ፤ ማመንን እንቢኝ ያለ ሰይፍ ትከለክለዋለች ይላል፤ ለአረማዊቷ ሀገር ወዮላት፤ ጥቋቊር ከኾኑ ከኢትዮጵያዊው ንጉሥ ሰራዊቱ ብዛትና ከብዙዎች ታላላቆች (አረጋውያን) የተነሣ ለማፍረስ አንድ አንድ ደንጊያ እንኳን አትደርሳቸውም።
 የምስርን ንጉሥ ሽሮ በርሱ ምትክ ሌላ ይሾማል፤ ከግብጽ ግብርን ይቀበል ዘንድ ግዮንን ይመልሳታል፤ የሮም ንጉሥም ኢየሩሳሌምን ይገዛታል፤ የኢትዮጵያዊው ንጉሥ ምልክቱ ይኽ ነው፤ መልከ መልካም፤ ረዥም፤ በጡቶቹ መኻከል መኻከል የመስቀል ምልክት አለው።
 ከዚያም ወደ ሀገራቸው ይመለሳሉ፤ የኢትዮጵያዊው ንጉሥ ወደ ኢትዮጵያ ሀገር ሲመለስ የምስር ንጉሥ ሚስትን ይማርካታል፤ ከዚኽ በኋላ ለአርባ ዓመት አጋንንት ይታሰራሉ፤ በዓለም ኹሉ ጸጥታ፣ ደስታና ሰላም ይኾናል፤ ከሰላም ብዛት የተነሣ ያለ ደመና ዝናም ሰባት ቀን ይዘንባል፤ ሰውም ኹሉ እግዚአብሔር ለሚያወርሳት ገነት ይኾናል፤ እኛንም ከእነሱ ጋር አንድ ያድርገን፤ አሜን።
 በዚያ ዘመን የሚሞት ያለ ጭንቅ ይሸጋገራል፤ ሞት የሚያመጣ ጠብ ኹሉ ተሽሯልና፤ ከጾምና ከጸሎት ውጪ ጠብ የለም፤ ተድላ ደስታ እንጂ ኀጢአት የለም፤ ከዚኽ በኋላ ሰባት ነገሥታት ተነሥተው ይነግሣሉ፤ ስማቸውም የአንደኛው “አ”፤ የኹለተኛው “ሮ”፤ የሦስተኛው “ወ”፤ የአራተኛው “ፊ”፤ የዐምስተኛው “ማ”፤ የስድስተኛው “ዮ” ሲኾን፤ ሰባተኛው ሐሳዌ መሲሕ ነው፤ ከዚያ የእግዚአብሔር ቃል እንደ ነጣቂ መብረቅ ይመጣል፤ በሰው ኹሉ ላይ ፍርዱን ያቆማል፤ ከርሱም እጅ የሚያመልጥ የለም፤ ከዚያም ወደ ዘላለማዊ ርስቱ ይገባል፤ ይኽ ዓለም ያልፋል፤ በቃልም ኾነ በኅሊና ይኽነን ዓለም ማንም ማን የሚያስበው የለም) (ራእየ ሲኖዳ ምዕ ፯)
ይቀጥላል

 በመጋቤ ሐዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ ከግእዝ ወደ ዐማርኛ ተተረጎመ (ጥቅምት 17/2012 ዓ.ም)
Share on Google Plus

ስለ የተለጠፈበት ቀን

    Blogger Comment
    Facebook Comment