የእኩልነት ዓለም ብለው የሚገልጿት የአውራምባውያኑ አምባ - "ዳግማዊት ዩቶጵያ"

የዘመኑ የሴቶች እኩልነት እንቅስቃሴ አራማጆች (feminist) የጾታ እኩልነት ባልተገባና ተፈጥራዊው ስርዓተ ጾታ በሚቃረን መልኩ ሲንቀሳቀሱ ይታያሉ። ከ አውራምባ ማህበረሰብ ብዙ ትምህርት በመውሰድ አካሄዳቸው እንዲያስተካክሉ ኢትዮጵያ አውታር መልዕክትዋ ታስተላልፋለች።

ብርቱካን ክብረትና ጥሩሰው ባንቴ ተወልደው ያደጉት አውራምባ ማህበረሰብ ውስጥ ነው። ሁለቱ ሴቶች አስጎብኚዎች ናቸው።

ማህበረሰቡ በዙምራ ኑሩ በ1964 ዓ. ም ከተመሰረተ ጀምሮ ያለፉበትን ሂደት ለጎብኚዎች ይተርካሉ። አውራምባን ሲገልጹ የእኩልነት፣ የመከባበር፣ የመደማመጥና የመቻቻል አካባቢ ብለው ነው።

ብርቱካንና ጥሩሰው ማስጎብኘት "በማህበረሰቡ የተሰጠን የሥራ ሀላፊነት ነው" ይላሉ። እያንዳንዱ የአካባቢው ነዋሪ ውጤታማ ይሆናል በተባለበት የሥራ ዘርፍ ይሰማራል።
አንድ የአውራምባ ነዋሪ ጠዋት ከተነሳች ወይም ከተነሳ በኋላ ቤት ውስጥ ያለውን ሥራ አብሯት ከሚኖረው ወይም ከምትኖረው ሰው ጋር በጋራ ይወጣሉ። አስከትለውም ወደየተመደቡበት መደበኛ ሥራ ያቀናሉ።
ብርቱካንና ጥሩሰውን ስናገኛቸው "የተመደበልን ሥራ ማስጎብኘት ይሁን እንጂ ሌላ ማከናወን የምንችለውን ሥራ ከመሥራትም ወደኋላ አንልም" ብለውናል።

የጾታ እኩልነት ከሥራ ክፍፍል በዘለለ

የአውራምባ ስም እየገነነ ከመጣባቸው ምክንያቶች አንዱ በማህበረሰቡ ውስጥ ለአንድ ወገን የተለየ ሥራ አለመኖሩ ነው። 'የሴቶች ሥራ' እንዲሁም 'የወንዶች ሥራ' የሚለውን የተዛባ ክፍፍል አንቀበልም ይላሉ።

ብርቱካን እንደምትለው በሴቶችና ወንዶች መካከል ጾታን መሰረት ያደረገ የሥራ ክፍፍል አለመኖሩ አንድ የማህበረሰቡ መገለጫ ነው። በአንድ ቤት ውስጥ ወንድም ሆነ ሴት ልጅ እኩል የትምህርት እድል እንዲያገኙም ይደረጋል።

"በማህበረሰባችን የጾታ እኩልነት አለ ስንል መገለጫው የሥራ ክፍፍል ጾታን መሰረት አለማድረጉ ብቻ አይደለም። እኩል ሀሳብን መግለጽና ውሳኔ መስጠት ሌሎቹ መገለጫዎች ናቸው።"

ብርቱካን ጠዋት እንጀራ ስትጋግር ባለቤቷ ወጥ መሥራቱ ብቻ የጾታ እኩልነትን እንደማያረጋግጥ ታምናለች። ሀሳቧን በነጻነት መግለጽ መቻሏ፣ በጋራ ህይወታቸው ላይ የሚያስተላልፏቸው ውሳኔዎች ላይ በህብረት መድረሳቸውን በዋናነት ትጠቅሳለች።
"የሀሳብ ልውውጥ ሲኖር አንድ የተሻለ ሀሳብ ይወለዳል ብለን እናምናለን።"

ኔ ይልቅ እኛ

እያንዳንዱ የማህበረሰቡ አባል ከግል ጥቅሙ በዘለለ ለማህበረሰቡ በአጠቃላይ እንደሚያስብ ጥሩሰው ትናገራለች።

"እኔን አይመለከተኝም የሚባል ነገር የለም፤ ሁሉም ይሠራል። አንድ ሰው የሚያገኘውን እውቀት 'የኔ ብቻ' አይልም፤ ለሁሉም ያካፍላል።"

በማህበረሰቡ ደንብ መሰረት 18 ዓመት የሆነው ሰው ሥራ ይይዛል። በሽመና፣ በቤት ውስጥ መገልገያ ቁሳቁሶች ሥራ. . . እና በሌሎችም ዘርፎች እንደየሰዉ ችሎታ ሀላፊነት ይሰጣል።

በማህበረሰቡ ውስጥ በተለያየ የሙያ ዘርፍ የሚሰማሩ ሰዎች አንዳቸው እንደ አዛዥ ሌላቸው እንደ ታዛዥ እንደማይተያዩ ብርቱካን ትናገራለች።
"ለምሳሌ አመራር ላይ የሚቀመጠው ሰው ሥልጣን አለኝ ብሎ ወደ ታች ያለውን ሕዝብ አይጫንም። ሰው ስልጣን ላይ ሲቀመጥ የሕዝቡ ተሸካሚ ነው ተብሎ ይታሰባል።"

ቀና አመለካከት

ገበያ መኮንን ከማህበረሰቡ አባላት አንዷ ናት። አውራምባ ሰላም እንደሰፈነበት ትናገራለች።

አንድ ሰው ሌላ ሰውን ካስቀየመ ይቅርታ እንዲጠይቅ፣ ግጭት እንዳይፈጠር ከተፈጠረም በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ይጥራሉ።

"መጥፎ አነጋገር ከመጥፎ ሀሳብ ቀጥሎ የሚመጣ ነው" የምትለው ገበያ፤ በግለሰቦች መካከል መቃቃር ቢፈጠር ነገሩን የሚያረግብ ቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ መኖሩን ታስረዳለች።

"ውሸትን፣ ነገረኛነትን አንፈልግም። በእኔ ላይ እንዲደረግ የማልፈልገውን በሌላው ላይ አላደርገም። በምድር ላይ ትልቁ ሀብት ሰው ነው። ሁለተኛው ሀብት ገንዘብ ነው። ሁለተኛው ሀብት ትልቁን ሀብት መደገፍ አለበት።"

ስለ አውራምባ ምን ይባላል?

ያነጋገርናቸው የማህበረሰቡ አባላት የአኗኗር ዘዬያቸውን ከዙምራና ዙምራ ካስተማሯቸው ቤተሶቦቻቸው እንደወረሱ ይናገራሉ።

ሀሳቡ ከተጠነሰሰበት ጊዜ ጀምሮ አኗኗራቸው ብዙም ያልተዋጠላቸው ሰዎች ትችት መሰንዘራቸው አልቀረም። በአንዳንዶች ዘንድ ደግሞ አድናቆት አትርፎላቸዋል።

ብርቱካን፣ ጥሩሰውና ገበያ መደበኛ ትምህርት ቤት ገብተው እውቀት አልቀሰሙም። ሆኖም ልጆቻቸው ተግተው እንዲማሩ ግፊት ያደርጋሉ። ልጆቻቸው የማህበረሰቡን አኗኗር አጉልተው እንደሚያሳዩም ያምናሉ።

"ባልተማረ አንደበታችን የምንናገረውን የተማሩ ልጆቻችን ያሳድጉታል ብለን እናምናለን" ትላለች ጥሩሰው።

ስለማህበረሰቡ ለማወቅ ወደ አካባቢው የሚያቀኑ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል። የመንግሥትና የግል ድርጅቶች እንዲሁም የዩኒቨርስቲ ተማሪዎችም አውራምባን ይጎበኛሉ።

ገበያ "ስለማህበረሰቡ መረዳት ፈልጎ ለጠየቀ መልስ እንሰጣለን ሠርተንም እናሳያለን" ትላለች።

"አውራምባ ለሁሉም ሰው ክፍት ነው"

ከማህበረሰቡ ውጪ ያሉ ግለሰቦች ወደ አካባቢው ሲሄዱ የማህበረሰቡን ህግና ደንብ ጠብቀው መኖር እስከቻሉ ድረስ ተቀባይነትን ያገኛሉ።

"ማህበረሰቡ ከሁሉም የሰው ልጆች ጋር ሰላምና ውህደት ፈጥሮ መኖር ይፈልጋል" ስትል ብርቱካን ታስረዳለች።

በአንጻሩ የማህበረሰቡ አባላት ከአካባቢያቸው ርቀው ሲሄዱ በመጠኑም ቢሆን እንደሚቸገሩ ይናገራሉ።

ክንድዬ ማስረሻ በአንድ ወቅት ከአውራምባ ወጥቶ ወደሌላ አካባቢ ሄዶ ነበር። ሆኖም ከማህበረሰቡ ተለይቶ መኖር ስላልቻለ እንደተመለሰ ይናገራል።

"በሄድኩበት አካባቢ ታምሜ ስለነበር ማረስ አልቻልኩም። አውራምባ ቢሆን ኖሮ ማንም ሰው የኔን መሬት አርሶ ያግዘኝ ነበር። እዛ ግን እንደዚህ አይደለም።"

የእድሜ ልዩነት የሌለበት ምክክር

ማህበረሰቡ እኩልነት የሰፈነበት፣ ሁሉም ሰው ሀላፊነቱን የሚወጣበት መሆኑን ከመናገር ባለፈ በተግባር እንደሚፈትሽ ይናገራሉ። ይህንን ለማረጋገጥም ሁሉም ቤተሰብ በየ15 ቀን ውይይት ያደረጋል።

የማህበረሰቡ መስራች ዙምራ ኑሩ እንደሚሉት ውይይቱ ትልቅ ትንሽ ሳይባል ሁሉም ነዋሪ የሚሳተፍበት ነው።

"ልጆች ከወላጆቻቸው ጋር ተወያይተው ችግር የመፍታትና አዲስ ሀሳብ የማፍለቅ መብት አላቸው" ይላሉ።

ዙምራ በአማራ ክልል የሚገኘ የአውራምባ ማህበረሰብ አኗኗር ምን መምሰል እንዳለበት መወጠን ከጀመሩ ዓመታት ተቆጥረዋል።

ስለእኩልነት ጥያቄ ማንሳት የጀመሩት በልጅነታቸው መሆኑን ይናገራሉ።

"ሰዎች የሚፈጠሩት እኩል ነው። ስለዚህ ምድር ላይ ሳሉም ጾታን መሰረት ያደረገ መድልዎ መኖር የለበትም" ይላሉ።

እሳቸው እንደሚሉት በማህበረሰቡ ውስጥ ሁሉም ሰው እድሜና ጾታ ሳይለይ መብትና ግዴታውን አውቆ እየተገበረ ይኖራል። ደንቦች መከበራቸውን ለማረጋገጥ ደግሞ ግልጽ ውይይት ይደረጋል። ያጠፋም ይታረማል።

ዙምራ ማህበረሰባቸውን ሲገልጹ "ፍትሀዊ ነው፤ ሰላማዊ ነው" ይላሉ።

Share on Google Plus

ስለ የተለጠፈበት ቀን

    Blogger Comment
    Facebook Comment