የቅድስት ድንግል ማርያም፡ ወደአርያም ያደረገችው፡ የፍልሰቷ መታሰቢያ በዓል፡ በየዓመቱ የሚውለው፡ ጥር ፳፩ ቀን ነው። እርሱም፡ "አስተርእዮ ማርያም" በሚል ስያሜ ይጠራል። በዓሉ፡ እንዲህ ባለ ስያሜ ሊጠራ ያስፈለገበትን ምክንያት ለማብራራት፡ ይኸው ምክንያት፡ ታላላቅ የኾኑ አምላካውያት ምሥጢራት የተከሠቱበትን ኹኔታዎች ያካተተ በመኾኑ፡ ሰፊና ጥልቅ ቢኾንም፡ በጥቂቱ ሳንገልጸው አናልፍም።
ለመኾኑ፡ "አስተርእዮ" ምን ማለት ነው? መልእክቱስ፡ ምንድር ነው"
በመጀመሪያ ነገር፡ "አስተርአየ" የሚለው፡ የግእዙ ቃል፡ "አሳየ፤ ገለጠ፤ አበራ፤ ነገረ፤ አስተማረ፤ አሳወቀ፤ አስረዳ" ማለት ነው። "አስተርእዮ" የሚለውም ቃል፡ ከዚሁ የተገኘ ሲኾን፡ "የገለጠበት፥ የተገለጠበት፤ ያሳየበት፥ የታየበት፤" ማለት ነው። ምኑን የገለጠበትና ያሳየበት? ማንነቱን ነዋ! ምን ኾኖ፥ እንዴትስ ኾኖ የተገለጠበትና የታየበት? ይህ ኾኖ፥ እንዲህም ኾኖ የተገለጠውና የታየው፡ እርሱ፡ ማነው? "እውነትና መንፈስ የኾነው፡ እርሱ፡ የማይታየው፡ ፈጣሪና የአማልክት አምላክ እግዚአብሔር፡ በገሃድ ሊገለጥና በግዘፍ ሊታይ፡ ሰው ኾነ! በሰውነት ተገልጦ ታየ!" ለማለት፡ ይህ ኹሉ መለኮታዊ ትንግርት የተፈጸመበት ወራት፡ "አስተርእዮ" ተባለ።
ይህ አስተርእዮት፡ ማለትም፡ እግዚአብሔር፡ በሰውነት የመገለጡና የመታየቱ ምሥጢራዊ ትንግርት የተፈጸመበትን ኹኔታ፡ እስኪ፡ እንዲህ በሚል አጭር ቃል እናቅርበው! ቅድስት ድንግል ማርያም፡ በሰውነት አካሏና ባሕርይዋ፡ በተፈጠረችበት፡ በእግዚአብሔር መልኳ፥ በእርሱ በፈጣሪዋም፡ "ከእኛ፡ እንደአንዱ ኾነች!" በተባለችበት አምላካዊ ማንነቷ፡ ራሷን፡ ለዚያ ፍጹምነት አብቅታ ተገኘች። በዚህ ጊዜና ከዚህ የተነሣ፡ እግዚአብሔር ወልድ፦
በቅድሚያ፡ ለሌላ ለማንም ፍጡር ተገልጦና ታይቶ ሊታወቅ ባልቻለ የአስተርእዮቱ ምስጢር፡ ከፈጣሪ በኩል፡ ራሱ እግዚአብሔር፥ ቀጥሎ፡ ከቅዱሳን መላእክቱ ወገን፥ ቅዱስ ገብርኤል፥ በመጨረሻ፡ ከሰብኣውያን ፍጡሮቹም በኩል፡ ራሷ፡ ቅድስት ድንግል ማርያም፣ እኒህ ሦስቱ ብቻ ባወቁት ክሥተትና ርእዮት፡ የድኅነቱ ምሥራች በተነገረበት፡ በታኅሣሥ ፩ ቀን ፭ሺ፬፻፺፱ ዓመተ ኪዳን፡ እግዚአብሔር እም በተዋሓደቻት፡ በእርሷው፡ ቅድስት ድንግል ማርያም ማሕፀን፡ በትስብእትነት [በሰውነት] ተፀነሰ፤
ከዚያ ተያይዞ፡ የአስተርእዮቱን አድማስ በበለጠ በማስፋት፡ በፈጣሪ በኩል፡ ራሳቸው ቅድስት ሥላሴና በመንበረ ጸባዖቱ ዙርያ ያሉትን፥ በሱራፌልና በኪሩቤልም የታቀፉትን አርባዕቱ እንስሳን፥ ከቅዱሳን አንጋደ መላእክትም፡ ከነመንጎቻቸው፡ በሜዳ ሠፍረው በነበሩ እረኞች ዘንድ የታዩት፡ የሰማይ መላእክት፣ የምድር ሠራዊት ከኾኑት፡ ከሰው ወገኖች ደግሞ፡ ቅዱስ ዮሴፍና ቅድስት ሰሎሜ፥ እንዲሁም፡ ሕፃኑን ኢየሱስን ያሟሟቁት እንስሳት፥ እረኞቹም፡ ከነመንጎቻቸው፥ ከዚያም፡ እነሰብአ ሰገል ብቻ ባወቁት፡ የምሕረቱ ዓመት በባተበት፡ በመስከረም ፩ ቀን፡ በሰውነት ተወለደ፤
እንዲህ፡ በፍጹም ሰውነት፡ እስካኹን፡ ለጥቂቶችና ለብዙዎች ብቻ የተገለጠውና የታየው እግዚአብሔር፡ አኹን ደግሞ፡ ይኸው፡ እውነተኛ ማንነቱና ምንነቱ፡ ለፍጥረተ ዓለሙ በሙሉ፥ ለኹሉም፡ በይፋ ይታወቅ ዘንድ፡ በጥር ፩ ቀን፥ ፴ ዓመተ ምሕረት፡
ሰማዩ ተከፍቶና አባቱ እግዚአብሔር አብ፡ "ዝንቱ ውእቱ ወልድየ፡ ዘአፈቅር፡ ዘቦቱ ሠመርኩ! ቀድሞ፡ በመጀመሪያ፡ በመለኮትነት፥ ኋላም፡ በመጨረሻ፡ በሰውነት፡ ከእግዝእተብሔር እም ቅድስት ድንግል ማርያም የወለድሁት፡ የምወድደው፥ በእርሱም ደስ የምሰኝበት ልጄ፡ ይህ ነው!" ብሎ ቃሉን በማሰማት፣
ቅድስት እናቱ እግዝእተብሔር እም፡ ቅድስት ድንግል ማርያምም፡ በወንዙ አጠገብ ቆማ፡ የራሷንና የእርሱን ማንነት፡ በእናትነቷ በማረጋገጥ፣
እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስም፡ "ወናሁ ተርኅወ ሎቱ ሰማይ፤ ወርእየ መንፈሰ እግዚአብሔር፡ እንዘ ይወርድ፡ በአምሳለ ርግብ፤ ወነበረ ላዕሌሁ። እነሆ! ሰማይ ተከፈተለት፤ የእግዚአብሔርም መንፈስ፡ በርግብ አምሳል፡ ሲወርድ፥ በእርሱም ላይ ሲያርፍበት አየ።" እንደተባለለት፡ ከሰማይ ወጥቶ በሚበርር ርግብ ተመስሎ፡ ወርዶ፡ በላዩ ላይ በማረፍ፡
ራሱ አጥማቂው ዮሓንስም፡ "ወበውእቱ፡ ያጠምቀክሙ፡ በመንፈስ ቅዱስ፥ ወበእሳት!" ማለትም፡ "በመንፈስ ቅዱስ፥ በእሳትም የሚያጠምቃችሁ፡ እርሱ ነው!!" ብሎ ለደቀ መዛሙርቱ በማመልከት፡ ኹሉም፡ ስለማንነቱ መስክረውለት፥ በመጥምቁ ዮሓንስ እጅ፡ በዮርዳኖስ ወንዝ ተጠመቀ። (ማቴ. ፫፥ ፲፩-፲፯።)
በዚህ መልክና ይዘት፡ በታኅሣሥ ፩ ቀን በኾነው ፅንሰቱ የተጀመረውና በመስከረም ፩ ቀን በኾነው ልደቱ የቀጠለው፥ ሲካኼድ ቆይቶም፡ በጥር ፩ ቀን በኾነው ጥምቀቱ ያበቃው፡ እግዚአብሔር፡ በሰውነት በመገለጥና በመታየት የፈጸመው የቸርነት ሥራው፡ እየታሰበ የሚከበርበት፡ በተለይ፡ ከጥር ፩ እስከ "በዓለ ኢትዮጵያ" (የቀድሞው ጾመ ኢትዮጵያ = ጾመ ነነዌ) መግቢያ ድረስ ያለው ወራት፡ "አስተርእዮ" ተባለ።
Blogger Comment
Facebook Comment