አቡነ ይምዓታ ገረኣልታ


ሰማይን እንደ ምሰሶ ደግፈው የያዙ ከሚመስሉት ረጃጅም ተራሮች መካከል በአንዱ የሚገኝና በ፮ኛው መቶ ክ/ዘ ከመካከለኛው ምሥራቅ በስደት ምክንያት ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ወንጌልን ያስተምሩ ከነበሩት ዘጠኙ መነኮሳት መካከል አንዱ በሆኑት በአቡነ ይምዓት ስም የተሰየመ ውቅር አለት ቤተ ክርስቲያን ነው፡፡

ቤተክርስያኑ ከባህር ወለል በላይ በ፪፼፪፻ ሜትር ከፍታ ላይ ይገኛል፡፡ ከዚህ ከፍታ ላይ ለመድረስ ከፊት ለፊቱ የተጋረጠውን የዓለት ተራራ መውጣት ግድ ነው፡፡ ጉዞውን እጅግ አስቸጋሪ የሚያደርገው ወደ ቤተክርስቲያኑ መውጣት የሚቻለው ለእጅና ለእግር መቆንጠጫ እንዲያገለግሉ ተደርገው የተጠረቡትን ጉድጓዶች ያለምንም አጋዥ ቁስ በመጠቀም ብቻ መሆኑ ነው፡፡ ከ፪፻፵ - ፫፻ ሜትር ርዝመት ያለውን ገደል ቁልቁል ሲመለከቱትና ወደ ተራራው ከወጡ በኃላ ከ፷ሴ.ሜ በማይበልጥ ስፋት የተጠረበ፣ በጣም በሚያስፈራ ገደል የተከበበና ኃይለኛ የአየር ግፊት ያለው አንድ ጠባብ መንገድን ሲያልፉ እጅግ አስደንጋጭና አስፈሪ ስሜት ውስጥ ይገባሉ፡፡ ቤተክርስቲያኑ አራት ራሳቸውን ችለው የቆሙ አምዶች አሉት፡፡ ጠቅላላ ስፋቱም ፮ ሜትር በ፱ ሜትር ከወለሉ ወደ ጣሪያው ያለው ከፍታ ደግሞ ፫ ሜትር ነው፡፡

የጥንት አባቶቻችን አሻራና የእግዚአብሔርን ድንቅ ጥበብ እያየን በአድናቆት እጅን በአፋ ላይ እንድንጭን ከሚያስገድዱን የዚህ ቤተክርስቲያን እውነቶች ፡- አጠገቡ ካልደረሱ በአይን ማየት የማይቻል በር መኖሩና ድንቅ የሆነው የህንፃው ጥበብ ብቻ ሳይሆን በአሁኑ ዘመን መነፅር ሲታዩ ጥንታዊ ናቸው ብሎ ለማለት እንኳ የሚከብዱ ግን ደግሞ በ፲፫ኛው ክፍለ ዘመን በቡርሾቻቸው ያቀለሟቸው ደማቅ ሥዕሎች በግድግዳዎቹ ላይ ማየታችን ነው፡፡

በተጨማሪም ከዓለት የተፈለፈለ የበርካታ ሰዎች አፅም የተቀበረበት የመቃብር ስፍራም በዚህ ቦታ ይገኛል፡፡ በአሁኑም ሰዓትም በአካባቢው የሚኖሩ ሰዎች ከ፪፻ ኪሎ ሜትሮች በላይ አቋርጠው በመምጣት በተራራው ላይ እንደ ዝንጀሮ ተንጠላጥለው በቅዱሱ አባት በአቡነ ይምዓታ ስም ወደ ተሰየመው ሥፍራ አስከሬን ይዘው መጥተው ይቀብራሉ፡፡ ቤተክርስቲያኑ ከተራራ ጉያ በመሸጎጡና እጅግ አስቸጋሪ የቦታ አቀማመጥ በመኖሩ ምክንያት በዮዲት ጉዲትና በግራኝ አህመድ ምንም ጉዳት አልደረሰበትም፡፡

ይህንን ሰማይጠቀስ አለት በጥበባቸው የቃኙት የእነኛ ድንቅ አባቶች የልጅ ልጆች የሆንነው እኛስ ለዚች አገር፣ ህዝብና እምነት ድርሻችን ምንድን ነው ???!


Share on Google Plus

ስለ የተለጠፈበት ቀን

    Blogger Comment
    Facebook Comment